እንዴት እንጹም?
ክፍል ፪
የተከበራችሁ የግቢ ጉባኤያት ድረ ገጽ ተከታታዮች “እንዴት እንጹም” በሚል ርእስ በክፍል አንድ ዝግጅታችን ከሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ስለ ጾም በጥቂቱ አቅርበንላችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከምትመራባቸው የሥርዓት መጻሕፍት መካከል በፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም ከተደነገጉት መካከል በአንቀጽ ፲፭ ያገኘነውን እነሆ፡-
- ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፤ በደሉን ለማስተሥረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፣ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ፡፡
- ለክርስቲያን ሁሉ የታዘዘውም ጾም ክብር ምስጋና ይግባውና ክርስቶስ የጾመው ጾመ ፵ ነው፡፡ ፍጻሜዋ ከፍሥሕ (የአይሁድ ፋሲካ) በፊት ባለው ዐርብ የሚሆን ነው፡፡ ከዚህም ቀጥሎ የስቅለት ሳምንት ነው፡፡ እነዚህም እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ድረስ ይጾማሉ፣ ደም የሚወጣው እንስሳ፣ ከእንስሳትም የሚገኘው አይበላባቸውም፡፡
- ዳግመኛም በየሳምንቱ ሁሉ ዐርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ፶ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ ፱ ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው፡፡
- ጾምስ የሥጋ ግብር ነው፣ ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ፣ ለነባቢትም ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡
- ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያን እንመስላለን፣ ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጸዋሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በጽኑ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው፡፡ መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን፤ ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለ አጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው፡፡
- ጾመ ፵ በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን፤ መጀመሪያውም ከሰንበቶቹ ሁለተኛ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ መጨረሻውም ከፍሥሕ አስቀድሞ ባለው በዕለተ ዐርብ ነው፡፡ ይህም ከፍሥሕ ሱባዔ በኋላ ያለ ሱባኤ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዐቢይ ጾም በኋላ የከበረ ሰሙነ ሕማማትን ትፈጽሙ ዘንድ ትጉ፡፡
- ዘወትር በዕለተ ሰንበት መጾም አይገባም፤ እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አርፎበታልና፡፡ ቅዳሜ ስዑርን ብቻ ሊጾሙ ይገባል እንጂ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ በመቃብር ውስጥ አድሮበታልና፡፡
- በሊህ በስድስቱ ቀኖች ከቂጣ፣ ከጨው፣ ከውኃ ብቻ በቀር አይብሉባቸው፤ በሊህ ቀኖች ከወይን፣ ከሥጋ ተለዩ የኀዘን ቀኖች ናቸውና የደስታ ቀኖች አይደሉም፡፡ ዐርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡ የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጨኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው፣ ሰውየው ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻለው ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም፡፡
- ዐቢይ ጾምንና ዐርብን፣ ረቡዕን የማይጾም የታወቀ ደዌ ያለበት ካልሆነ በቀር ካህን ቢሆን ይሻር፣ ሕዝባዊ ቢሆን ይለይ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!