አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ ጌታችን ጾመ፡፡ (ቅዱስ ያሬድ)
በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ
ጾም በብሉይ ኪዳንም፣ በሐዲስ ኪዳንም በፈጣሪ መኖር ለሚያምኑ የፈጣሪያቸውን ስሙን ጠርተው ለሚማጸኑ የተሰጠ አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በነቢያት የተጾሙ፣ ለሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ያገለገሉ አጽዋማት እንዳሉ መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ “ሙሴም ወደ ተራራው ወጣ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ቆየ” (ዘጸ.፳፬፥፲፰) እንዲል፡፡ ሙሴ በተራራው የቆየው እየጾመ ነበር፡፡
ነቢያት በጾም ከፈጣሪያቸው ጋር ተገናኝተውበታል፡፡ ምንም እንኳን ድህነተ ነፍስን ማግኘት ባይችሉም በመጾማቸው አባር ቸነፈርን ከሕዝቡ አርቀዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ያሉ አጽዋማት በሙሉ በፍጡራን የተጾሙ ናቸው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ጾም ግን የተጀመረው በጌታ ጸዋሚነት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን አጽዋማት ረድኤተ እግዚአብሔር የሚገኝባቸው እና የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መነሻና ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከላይ በርእሱ የነገረን የጌታችን ጾም የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ጾም የአጽዋማት ሁሉ በኵር ነው፡፡ በኃጠአት ብዛት በመርገም በጠወለገ ሰውነት የተጾሙ አጽዋማትን አድሷል፣ ቀድሷልም፡፡ ውኃ ከላይ ደጋውን፣ ከታች ቆላውን እንዲያለመልም የጌታም ጾም ከላይ ከመጀመሪያ የነበረ የአበውን ጾም ቀድሷል፣ ጉድለቱን ሞልቷል፡፡ ከእርሱ በኋላ የተነሡ የሐዋርያትን፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታትን፣ የደናግል፣ የመነኮሳትን፣ የምእመናንን ጾም ቀድሶ የሰጠ ነው፡፡ በአጠቃላይ የጌታችን ጾም እንደ በር ነው፡፡ በር ሲከፈት ከውጭ ያለውን እና ከውስጥ ያለውን ያገኛል፡፡ የጌታችን ጾምም ከፊት የነበሩትን የነቢያትን አጽዋማት ኋላ ከተነሡ ከሐዋርያት አጽዋማት ጋር ያገናኘ ነው፡፡ በመርገም ውስጥ የነበሩትንና ከመርገም የተዋጁትን ያስተባበረ ጾም ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ እንደነገረን “ጌታችን የጾመው ለምን ነው?” የሚለውን ትልቅ ጥያቄ መልሶልናል “አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ” በማለት፡፡ ጌታችን የጾመው እንደ ፍጡራን ክብር ለመቀበል ኃጠአት ኖሮበት ስርየት ለማግኘት አይደለም፡፡ የጌታችን ጾም እርሱን ከመጥቀም በታች ነው፤ ለእኛ ጥቅም ጾመ እንጂ፡፡ አርአያነቱን አይተን፣ ፍለጋውን ተከትለን ልንጠቀምበት ጾምን ቀድሶ ሰጠን፡፡ ጾም ዲያብሎስን ድል የምንነሳበት ጋሻ፣ ከኃጢአት የምንሰወርበት ዋሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ መሆኗን አርአያ ሆኖ ሊያሳየን ጾመ፡፡ የጾምንም ጥቅም በግብር በትምህርት በሚገባ አስረዳን፡፡
ይህ ዐቢይ ጾም(ታላቁ ጾም) ሁዳዴ፣ አርባ ጾም፣ የጌታ ጾም እየተባለ ይጠራል፡፡ ዐቢይ ጾም ማለት ከግሱ እንደምንረዳው እጅግ ትልቅ ጾም ማለትን ያሳያል፡፡ በእርግጥ የጾም ትንሽ የለውም፤ አንድም ቀን ይሁን ሳምንት ጾም ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጾም ዐቢይ(ትልቅ) የተባለበት ምክንያት፡-
የታላቆች ታላቅ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ሁሉ ጌታ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ስለጾመው ነው፡፡
የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት ሁሉ በኩር በመሆኑ ነው፡፡
ስምንት ሳምንታትን፤ ኀምሳ አምስት ቀናትን በውስጡ የያዘው በቁጥር እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ በቁጥር ከአጽዋማት ሁሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ሁዳድ(የመንግሥት እርሻ)፡- በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ ሕዝቦች በሙሉ በግዳጅ ወጥተው የሚያርሱት፣ የሚያጭዱት የሚሠሩት እንደሆነ ሁሉ ይህም ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የመንግሥቱን የምስራች በምትነግር ወንጌል ያመኑ ምእመናን በአዋጅ በአንድነት የሚጾሙት በመሆኑ ነው፡፡
አርባ ጾም አያሻማም ግልጽ ነው፡፡ ጌታችን የጾመው አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ነው፡፡ “አርባ መዓልት እና አርባ ሌሊት ጾመ”(ማቴ.፬፥፪) እንዲል፡፡ ጾሙ ስምንት ሳምንታትን ኀምሳ አምስት ቀናትን ያካተተ ነው ብለናል፡፡ ጌታችን የጾመው አርባ ቀን ነው ለምን ኀምሳ አምስት ቀናትን እንጾማለን? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጣችን ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡ ጌታችን በጾመው አርባ ቀን ላይ ቅዱሳን ሐዋርያት ከመጀመሪያው አንድ ሳምንት፣ ከመጨረሻው አንድ ሳምንት ጨምረውበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾሙ ከስድስት ሳምንታት ወደ ስምንት ሳምንታት፣ ከአርባ ወደ ኀምሳ አምስት ቀናት ከፍ ሊል ችሏል፡፡ ለምን ብለን ጥያቄ ማንሳት የለብንም፡፡ ምክንያቱም የጨመሩት ከጌታችን ጋር ፣ በቃልም፣ በተግባርም ከጌታ የተማሩ፣ የምሥጢር ደቀ ማዛሙርት የሕግ ምንጮች እኛ ወደ ክርስቶስ በምናደርገው ጉዞ መሪዎች የሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡ አምነን ከመቀበል ውጭ ምንም ልንል አይቻለንም፡፡ እኛ የክርስትና ተቀባዮች እንጂ ጀማሪዎች ወይም መሥራቾች አይደለንም በቅዱሳን ሐዋርያት መሠረትነት ላይ የተመሠረትን እንጂ፡፡
“እናንተስ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ተመሥርታችኋል”(ኤፌ.፪፥፳) እንዲል የብሎኬት ድርድር መሠረት አያስፈልገኝም ሊል አይችልም፡፡ መሠረቱ ከተናደ ድርድሩ የት ሊቆም ይችላል? እኛም የሐዋርያትን ካልተቀበልን የማንን እንቀበላለን?
ቅዱሳን ሐዋርያት ከመጀመሪያው የጨመሩት የጌታችን ጾም መግቢያ መቀበያ ንጉሥ ሲመጣ በሠራዊት እንዲታጀብ፣ በብዙ ሕዝብ እንዲከበብ፣ ከፊት ከኋላ ተከብቦና ታጅቦ በክብር እንደሚቀበሉትና እንደሚሸኙት ሁሉ የንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ሲመጣ የሚያጅቡ፣ የሚከቡ፣ የሚያከብሩ ዘወረደን ከመጀመሪያው፣ ሕማማትን ከመጨረሻ ጨምረዋል፡፡ ደግሞስ መቀነስ እንጂ መጨመር አያስቀጣ፡፡ በክርስትና ሕይወት የተቀበሉትን መክሊት መቅበር እንጂ አትርፎ ማቅረብ ገብርኄር ያሰኛል፣ ያሾማል፣ ያሸልማል ሐዋርያትም የጨመሩት ገብርኄር ለመሰኘት ነው፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ (ከመጋቢት ፩-፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!