‹‹ሁሉ በአግባቡ እና በሥርዓቱ ይሁን›› ፩ኛ ቆሮ.፲፬፥፵ (ክፍል ሁለት)
በዲ/ን ታደለ ሲሳይ
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክታት መካከል ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ እንዳስቀመጠው፡ ‹‹ነገር ግን ሁሉ በአግባብ እና በሥርዓት ይሁን›› 1ኛ ቆሮ. ፲፬፤፵ ብሏል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን መልእክት መሠረት አድርጋ ልጆቿን ታስተምራለች፡፡ በሁሉም የአምልኮ ዘርፍ ሥርዓት መሥርታ ሕግጋተ እግዚአብሔርን እያጣቀሰች ምእመናን በቀና መንገድ እንዲመሩ ታሳስባለች፡፡ ያላመኑትን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በማምጣት፤ ያመኑትን በእምነት በማጽናት፤ የጸኑትን ደግሞ በመባረክ እና በመቀደስ ለማያልፈው ዘለዓለማዊ መንግሥት እንዲበቁ የንስሓ ትምህርትን በማስተማር ለንስሓ ሕይወት ታዘጋጃለች፡፡ ከሕግ እና ከሥርዓት ብሎም ከትክክለኛ አስተምህሮዎቿ የሚርቁ፤ የሚሸሹ እና የሚቃወሙትን ደግሞ በምክረ ካህን ታስተምራለች፤ እምቢ አሻፈረኝ ያሉትን ደግሞ ታወግዛለች፡፡
ከጥንት ጀምሮ በሕግና በሥርዓት ስትመራ የቆየችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘመን በተቀያየረ ቁጥር የሚከሰቱ ዓለማዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምእመኖቿን ከአምልኮተ እግዚአብሔር እና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዳያርቃቸው ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ማኅበራዊ የመረጃ አውታሮችንም ሆነ ሌሎች የዘመናዊነት መገለጫ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሚጠቀምበት ጊዜ እንዲሁም ሃይማኖታዊ መልእክቶችን በሚያስተላልፍበት ጊዜ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ እና ሃይማኖታዊ፤ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴቶችን የማይጋፋ፤ የማይጻረር በሆነ መልኩ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ማኅበራዊ የመረጃ አውታሮችን በምንጠቀምበት በማንኛውም ጊዜ ክፉ ከሆነ አስተሳሰብ፤ ከጥላቻ መንፈስ፤ ከዘረኝነት እና ሥርዓትን ከሚጋፉ አመለካከቶች የጸዳ ሊሆን ይገባል፡፡ የግለሰቦችን ስም እየጠቀሱ የማይገቡ ወይም ከእውነታ የራቁ ሐሜቶችን፤ ስድቦችን እና አላስፈላጊ ሥነ ምግባርን የተላበሱ ወቀሳዎችን ማራመድ ፍጹም ክርስቲያናዊ ምግባር አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለን ሐሜት በወንድሞች መካከል ያለን ፍቅር ያጠፋል፤ አላስፈላጊ ጥላቻን ያሰፍናል፤ ከእግዚአብሔር ሕግም ያርቀናል፡፡ ‹‹ወንድሞች ሆይ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ፡፡ ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል፣ በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም፡፡ ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ፤» እንዲል፡፡ ያዕ. ፬፤፲፩-፲፪ ፡፡በመሆኑም በምናውቀውና በማናውቀው ቴክኖሎጂው ስላገዘን ብቻ አባቶቻችንንና ወንድሞቻችንን፣ እኅቶቻችንንና እናቶቻችንን ከመዝለፍና ከመፍረድ ይልቅ፣ በማስተዋልና በጥበብ ፍርድን ለእግዚአብሔር መተው ወሳኝና ጠቃሚ ነው፡፡
ከላይ በተቀመጠው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የምንረዳው እርስ በርስ መተማማት ሕግን ማማት እና በሕግ ላይ እንደመፍረድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕግን እንደ መጣስ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንደተናገረው፣ የሚፈርድ፣ የሚገሥጽ፣ ፍትህና ርትዕ በሥልጣኑ የሚኖሩ እግዚአብሔር ብቻ ነውና፤ ሁሉን ለርሱ ሰጥቶ ራስን መግዛትና ለሕግ ማስገዛት ተገቢ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ በፌስቡክም ሆነ በስልክ ወጣቱ ትልቅ ጥፋትን ሲያጠፋ ይታያል፡፡ ይህም እግዚአብሔር አክብሮ የፈጠረውን ሰው ልጅ መስደብ ነው፡፡ ስድብ ኃጢአት እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጾ እያለ ይህንን ማድረግ ከሥርዓት መውጣት ነው፡፡ እንደ ልቤ የተባለ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ክፉ ነገር ከአንደበታችን መውጣት እንደሌለበት ሲናገር፣ ‹‹አንደበትህን ከክፉ ከልክል፣ ከንፈሮችህንም ሽንገላን እንዳይናገሩ›› በማለት አስቀምጧል፤ መዝ. ፴፫(፴፬)፤፲፫ ይህ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ትእዛዝ ነው፡፡ እንደዚህ ባታደርጉ ይሻላል ሳይሆን ያለው አታድርጉ ነው፡፡ በመሆኑም በየትኛውም ዓይነት መንገድ መሳደብና ክፉ ነገርን መናገር ትእዛዝን መተላለፍ ነውና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ መለያየትም ከቶ አላስፈላጊ እንደሆነና ባንድ ልብ እና ሐሳብ እንድንተባበርም ያዝዘናል፡፡ ይኸውም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን ባስቀመጠው መልእክቱ ላይ የተቀመጠ ነው፡፡
‹‹ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ ባንድ ልብና ባንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይኖር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› እንዲል፡፡ ፩ኛ ቆሮ. ፩፤፲
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!