መስቀልና ስሙ
…በመ/ር ማዕበል ፈጠነ…
ታሪክ እንደሚነግረን በቀደመው ዘመን ለመስቀልና ለማርያም ስግደት አይገባም የሚሉ ባዕዳን ተነሥተው ነበር፡፡ ለዚህም ብዙ ሊቃውንት ብዙ ድርሰት ደርሰዋል፡፡ ከቅዱስ መጽሐፍ እየጠቀሱ በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ዘመን ከተደረሱት ድርሳናት አንዱ መጽሐፈ ምሥጢር ነው፡፡ መጽሐፉ የተነሣበት አላማ ደግሞ የድንግል ማርያምን ክብርና የመስቀልን ክብር ከፍ አድርጎ መተንተን እንደሆነ መጽሐፉ ያስረዳል፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሊቃውንትም በዚህ ይስማማሉ፡፡
እናም የዚህ መጽሐፍ ደራሲ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲሆኑ በሌላው ድርሰታቸው ‹‹ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ›› ሲሉ በተጨማሪም «…በእንተዝ አዘዙ መምህራነ ቅዱስ ወንጌል አምሳለ ፈጣሪ ልዑል፤ ንስግድ ለመስቀል ወለማርያም ድንግል» በማለት ለቅዱስ መስቀልና ለቅድስት ድንግል ማርያም ስግደት እንደሚገባቸው ያስተምራሉ፡፡ ይህን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር አዛምደን ስንመለከተው ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ በመሆኗ፣ ቅዱስ መስቀልም ሥጋው ስለተቆረሰበት ደሙ ስለፈሰሰበት የጸጋ ስግደት እንዲገባው ያስረዳል፡፡
ይህም በአንድ ወቅት ነቢዩ ዳዊት ‹‹ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ፤ የጌታችን እግር በቆመበት ሁሉ እንሰግዳለን›› መዝ 131 ÷7 ብሎ ከተናገረው ትንቢታዊ ቃል ጋር አንድ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ነቢዩ ዳዊት የጌታችን እግር በቆመበት እንሰግዳለን ሲል አስተማረ፡፡ ይህን ቃል እንደሊቅነቱ የተረጎመው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ደግሞ በዓይነ ሥጋ የሚያውቃቸውን ድንግል ማርያምንና ቅዱስ መስቀልን በስም ጠቅሶ ለእነዚህ ስግደት ይገባል›› ሲል አስተማረ ተረጎመ፡፡
ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብላ ለቅድስናዋ የጸጋ ስግደት ትሰግዳለች፤ ለምእመናንም በሚገባ ታስተምራለች፡፡ ለምን ቢሉ ነቢዩ ዳዊት የእግዚአብሔር እግር ከቆመበት ላይ እንሰግዳለን›› ብሎ መናገሩ ትንቢት ሲሆን በዚህ ትንቢታዊ ምሥጢር ውስጥ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ድንግል ማርያም ስለሆነች ነው፡፡
እንዲሁም ለመስቀልም ሆነ ለሥዕለ አድኅኖ የጸጋ ስግደት እንሰግዳለን፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ስመ አምላክ ስለተጻፈበት እግዚአብሔር በዚያ ላይ አድሮ ጸሎታችን ተቀብሎ መሥዋዕታችን መስዋዕተ አቤል አድርጎ ኃጢአታችን አስተስርዮ የውስጥ ልመናችን እንዲቀበለን ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር