“የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ” (ገላ. ፮፥፪)

“የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ” (ገላ.፥፪)

የክርስቶስ ሕግ ምንድን ነው? መልሱ ፍቅር ነው፡፡ “ባልንጀራውን የሚወድ በባልንጀራው ላይ ክፉ ሥራ አይሠራም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው፡፡” እንዲል (ሮሜ፲፫፥፲) በፍቅር ሕይወት መመላለስ እንዲገባን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ፍቅር የሕግ ሁሉ መሠረት ነውና “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ከክፉ ራቁ፤ በጎውንም ያዙ፤ ለጽድቅ አድሉ፤ እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፣ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” በማለት እግዚአብሔር በቅዱስ ጳውሎስ ላይ አድሮ ይመክረናል፡፡

አንድ ሰው ከሌላው ጋር በየዕለቱ በሚያደርገው ግንኙነት ሊመራበት የሚገባ፤ በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ልባዊ መዋደድና ጥልቅ መንፈሳዊ ጸጋ ነው ፍቅር። በሰዎች መካከል በሚኖረው መልካም ግንኙነት የተነሣ አንዱ ለሌላው የሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ከፍቅር የሚመነጭ ነው። ይህም በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ትልቅ ዋጋን ያስገኛል፡፡ በዕለት ተዕለት ግንኙነት ለተራበ ማብላት፣ ለተጠማ ማጠጣት፣ ለተቸገረ መርዳት፣ ያዘነን ማጽናናት ይህን የመሰለውን መልካም ምግባር ሁሉ ሰው ለሰው ካለው ፍቅር የተነሣ የሚያደርገው ነው። በዚህ መሰል ተግባር ለሌሎች መልካም ያደረጉትን ሁሉ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመጣ ጊዜ በፍጹም ፍቅር የሚወጡ የሚወርዱትን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፤ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ፡፡ … እውነት እላችኋለሁ በእኔ ካመኑ ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁትን ከሁሉ ለእኔ አደረጋችሁት” በማለት መንግሥቱን እንደሚያወርሰን በወንጌል ተናግሯል። (ማቴ. ፳፭፥፴፭-፴፮)

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ፍቅር ሲገልጽ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖርም ከእግዚአብሔር ጋር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል” ይለናል፡፡ (፩ኛዮሐ. ፬፥፲፮) ሰውን መውደድና ሰውን መርዳትም ፍቅር ነውና ከፍቅር አምላክ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ዋጋን ያስገኛል። ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ መልካም እናድርግ” ያለው በፍቅር የሚደረግ መልካም ነገር ሁሉ የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ዋጋ በሚገባ ስለተረዳ ነው፡፡ (ገላ. ፮፥፲)። ፍቅር ለሰው መልካም በመሥራት የሰውን ድካሙን ሳይቀር በመሸፈን የሚገለጥ መልካም ተግባር ነው። ከዚህ የሚበልጥ ምንም የለምና በፍቅር እንመላለስ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የማይስማማው ሲሆን መዋቲ ሥጋን ተዋሕዶ ከጽኑ ፍቅሩ የተነሣ አዳምና ልጆቹን ያድን ዘንድ በመስቀል ላይ ውሎ ሞትን በሞቱ ገድሎ ድኅነትን የሰጠን እስከ መስቀል በተከፈለ ዋጋ ነው፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ በመስቀል ላይ ፍቅሩን ገለጸ፣ እስከ ሞትም አደረሰው፡፡ መቃብር ውጦም አላስቀረውም፤ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፣ ዲያብሎስንም አስወገደው፣ በትንሣኤው ትንሣኤውን አበሠረን፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ምን አለ?! ለዚህ ነው ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍጻሜ ነው የምንለው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የፍቅርን ኃያልነት ሲገልጽ “ፍቅር ያስታግሳል፣ ፍቅር ያስተዛዝናል፣ ፍቅር አያቀናናም፣ ፍቅር አያስመካም፣ ፍቅር ልቡናን አያስታብይም፡፡ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፣ አያበሳጭም፣ ክፉ ነገርንም አያሳስብም፡፡ …” በማለት ይነግረናል። (፩ኛቆሮ. ፲፫፥፬-፯) በአጠቃላይ ሁሉንም በመውደድ፣ በጎ ምግባርንም በመፈጸም እንደ እግዚአብሔር ቃል በፍቅር መኖር ስንችል የሕሊና ዕረፍትን እናገኛለን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም እናድጋለን፡፡

በክርስትና ሕይወት ዕድገት እያመጣን ስንሄድ ዲያብሎስ ደግሞ በእርምጃን ሁሉ ፈተናን በማዘጋጀት ሊጥለን የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በተለይም በወጣትነት ዘመናችን ሁሉንም ካልሞከርኩ፣ ካላየሁ፣ ካልዳሰስኩ የምንልበት ጊዜ በመሆኑ ሥጋዊ ፍላጎታችንም ስለሚያይል ኃጢአትን ለመሥራት እንፈጥናለን፡፡ ነገር ግን ይህንን ሥጋዊ ፍላጎትና ስሜት መግታት የምንችለው ወደ እግዚአብሔር በመቅረብና ለሕግጋቱ በመገዛት ዲያብሎስን ድል መንሣት ስንችል ነው፡፡ ጠቢቡ በወጣትነት ዘመን ፈጣሪን ማሰብ ተገቢ መሆኑን ሲያስረዳ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ” ይላል፡፡ (መክ. ፲፪፥፩)

ዲያብሎስ በወጣትነት ድል ሊያደርገን የተለያዩ ማታለያዎችን በማቅረብ ራሳችንን ብቻ እንድንወድ ይፈትነናል፡፡ ነገር ግን በጾም በመጸሎት፣ መልካም ምግባራትን በመፈጸም ልናርቀው ይገባል፡፡ ሌላውን ስንወድ እግዚአብሔርን እንወዳለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ሐዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን? … ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን የለም” (ሮሜ ፰፥፴፭-፴፰) በማለት ክርስቲያን ስንሆን እነዚህ ፈተናዎች እንደሚገጥሙን፣ ነገር ግን የፍቅር ሁሉ ምንጭ ከሆነው ክርስቶስ ጋር ተጣብቀናልና በድል እንወጣዋለን፡፡ እግዚአብሔር ያለው ሁለም ነገር አለውና፡፡ 

እግዚአብሔር በአምላክነቱ ቀናተኛ አምላክ ነው፡፡ እርሱን መውደድ፣ እንዲሁም ሰውን ሁሉ መውደድ እንደሚገባን አስተምሮናል፡፡ የክርስትና መሠረትም በዚህ ላይ የተመሠረተ ነው። “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኃይልህ ውደደው፤ ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት፡፡ የምትመስላትም ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትለው ናት” እንዲል፡፡ (ማቴ፳፪፥፴፯-፴፰) ራሳችንን የምንወደውን ያህል አጠገባችን ያለውን ባልንጀራችንን የምንወድ ከሆነ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ይኖረናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ጠላታችንን እንወድ ዘንድም ታዘናል፡፡ “ባልንጀራህን ውደድ፣ ጠላትህንም ጥላ የተባለውን ሰምታችኋል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላታችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁንም መርቁ …” ተብለናል፡፡ (ማቴ.፭፥፵፫) ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ በጠላትነት ተነሥተው አሳደውታል፣ ገርፈውታል፣ ምራቅ ተፍተውበታል፣ … ጠላቶቹ ሲሆኑ በጭካኔ በመስቀል ላይ ሰቅለውት እንኳን “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል በፍቅር ዐይኖቹ እየተመለከተ ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ይቅርታን ለምኖላቸዋል፡፡ (ሉቃ፳፫፥፴፬)

እኛስ እንኳን ጠላቶቻችን ወዳጆቻችንን እንወድ ይሆን? በአፍ ከመናገር አልፈን ሁሉንም የመውደድ ግዴታ እንዳለብን ካልተረዳን በተግባርም ካልገለጥነው አጠገባችን በአካል የምናየውን ወዳጃችንን ሳንወድ የማናየውን እግዚአብሔርን እንወዳለን ማለት ራስን ማታለል ነው፡፡ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ የሚል ወንድሙን ግን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው፤ የሚያየውን ወንድሙን የማይወድ ግን የማያየውን እግዚአብሔርን እንደምን ሊወደው ይችላል?” ይለናል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ (፩ኛዮሐ. ፬፥፳) ነገር ግን እርስ በርስ የምንዋደድና በፍቅር የምንኖር ከሆነ እግዚአብሔር አድሮብን ይኖራል፡፡ “ወንድሞች ሆይ እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ከተዋደድን እግዚአብሔር አድሮብን ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል፡፡” (፩ዮሐ.፬፥፲፩-፲፪)

ስለ ኃጢአታችን ከገነት የተባረርነውን አዳምና ልጆቹን ያድነን ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ዽንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ፣ በምድር ላይ ተመላልሶ በመስቀል ላይ ያለ በደሉ የአዳምን በደል ይሽር ዘንድ ተሰቅሎ፣ ሲዖልን በርብሮ ዲያብስን ድል ነሥቶ ያድነን ዘንድ እስከ መስቀል የታመነ አምላክ ነው፡፡ በሞቱ ሞትን ገድሎ በትንሣኤው ትንሣኤአችንን አወጀልን፡፡ ይህ ሁሉ ለሰው ልጆች የተከፈለ ዋጋ ነው፡፡ “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም፡፡” እንዲል፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፲፫)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ለመንፈሳዊ ነጻነት የተጠራንበት የክርስትና እምነታችንን በተለያዩ የሥጋ ፈቃዳትና ፈተናዎች ተሰናክለን እንዳንወድቅ እና ፍሬ አልባ እንዳንሆን ሲያስጠነቅቀንም “ወንድሞች ሆይ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኃልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያት አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ” በማለት ራስን ዝቅ በማድረግና በፍቅር በመመላለስ የእግዚአብሔርን ሕግ ልንፈጽም ይገባል፡፡ (ገላ. ፭፥፲፫)

የሕግ ሁሉ ፍጻሜው ፍቅር ነውና በፍቅር ተመላለሰን፣ ንስሓ ገብተን፣ የመንግሥቱ ወራሾች ያደርገን ዘንድ የአምላክችን ቅዱስ እግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን፡፡ አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *