ወቅታዊውን የኮሮና በሽታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ የሰው ልጆችን ሕይወት በሞት እየቀጠፈ ያለው ተላላፊ በሽታ በአገራችን ኢትዮጵያም ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱ ታምኖበት ወረርሽኙም ለመቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንደምንገኝ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ባሉባት ሕዝባዊ ኃላፊነት የተነሳ ለዚሁ የመከላከል ሥራ ራሱን የቻለ የተስፋ ግብረ ኃይል በማቋቋም ኅብረተሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ ለማድረግ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ በቀጣይም ከበሽታው ራስን በተገቢው መንገድ መጠበቅ እንዲቻል ቋሚ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ በጉዳዩ በሰፊው በመነጋገር በጊዜያዊነት መዘጋት በሚገባቸው የሥራ ክፍሎች ላይ የሚከተለውን ወስኗል፡፡

  1. ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የተዘጉ መምሪያዎች

ሀ. የመንበረ ፓትርያርክ ቅርሳቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር

  • ጉብኝት
  • የንባብ አገልግሎት
  1. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ከአዲስ አበባ እስከ አህጉረ ስብከት ያሉ

ሀ. መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲዎች

ለ. መንፈሳዊ ኮሌጆች

ሐ. ሥልጠና ያልጀመሩ የካህናት ማሰልጠኛዎች

መ. መዋዕለ ሕፃናት

ረ. የአብነት ትምህርት ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ የመማር ማስተማሩ ሥራ ቁሞ ደቀ መዛሙርቱና ተማሪዎቻቸው የተማሩትን እየቀጸሉና እያጠኑ እንዲቆዩ፡-

  1. በከፊል እንዲዘጉ የተደረጉ፡-

ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ መላው አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች ለአስቸኳይ ሥራ ከሚፈለጉና ተለይተው እንዲቆዩ ከሚደረጉ ሠራተኞች በስተቀር መላው ሠራተኞች በየቤታቸው ሥራቸውን እንዲያከናውኑና ሲፈለጉና ጥሪ ሲደረግላቸው ከሚመጡ በስተቀር በቤታቸው እንዲቆዩ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝባችንን ከሕማም ሞት፣ ሀገራችንን ከልዩ ልዩ መቅሰፍትና ደዌ ይጠብቅልን፡፡

ብፀዕ አቡነ ያሬድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *