ትጉኀኑ የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎች …
ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ እንደየደረጃው ሲያስተምሯቸው የነበሩ ተማሪዎችን የሚያስመርቁበት ጊዜ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችም ለተማሪዎቻቸው ዓመቱን ሙሉ የደከሙበትን ውጤት አብስረው ተማሪዎቻቸውን የሚያሰናብቱበት፣ እነርሱም ለሚቀጥለው ዓመት ዝግጅት የሚያደረጉበት ጊዜ ነው፡፡
ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂ ተማሪዎች በማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አማካይነት ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመማር በሁለት ወገን የተሳሉ ስለት ሆነው በመውጣት ሀገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጅት የሚጀምሩበትም ነው-ወቅቱ፡፡
ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ደግሞ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከትምህርት ክፍላቸው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዋንጫና ሜዳልያ ተሸላሚ የሚሆኑት ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በየዓመቱም ከፍተኛ ውጤት በማመምጣት የተሸለሙትን ዋንጫና ሜዳልያ “እግዚአብሔር ረድቶን ውጤታማ እንድንሆንና ቤተ ክርስቲያናችንን እንድናውቃት፣ በሃይማኖታችንም እንድንጸና ያስተማረን ማኅበረ ቅዱሳን ነውና ለውጤታማነታችን ድርሻው ከፍተኛ ነው” በማለት ሽልማቶቻቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን ማበርከታቸው የተለመደ ነው፡፡
እንደተለመደው በ፳፻፲፬ ዓ.ም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችም ዋንጫውንና ሜዳልያውን ለመውሰድ ችለዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ፡- ከነቀምት፣ ከደብረ ማርቆስ፣ ከሐዋሳ፣ ሐረር፣ መቱ፣ ዋቸሞ፣ ሻምቡ፣ አሰላ፣ … እና ከሌሎችም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ውጤት በመመረቅ ተሸላሚዎች መሆናቸውን መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ከ፲፱፻፹፬ ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤያት ውስጥ በማስተማር እንዳስመረቀ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!