ታቦት በሐዲስ ኪዳን
…በመ/ር ማዕበል ፈጠነ…
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን ታቦተ እግዚአብሔር የሌላትን ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ናት›› ብላ አትቀበልም፡፡ በራሷ ሥርዐት እንኳ ታቦት የሌለውን ይቅርና ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተሠርቶ በሊቀ ጳጳስ ጸሎት በቅብዐ ሜሮን ካልከበረ ሕንፃውን ብቻ ቤተ ክርስቲያን ብላ አትቀበለውም፡፡ ለዚህም ‹‹ቤተ ክርስቲያን እንተ አልባቲ ጳጳስ ምሥያጥ ይእቲ፤ ጳጳስ የሌላት ስብሐተ እግዚአብሔር የማይደረስባት ቤተ ክርስቲያን ብትኖር ገበያ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ተብላ አትጠራም›› ስትል በቀኖናዋ ታስተምራለች፡፡ ታቦት ያስፈልጋል ብላ የምታስተምረውም በብሉይ ኪዳን የጌታችን በሐዲስ ኪዳን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ያለ መቆነጻጸል ተቀብላ ነው፡፡ (ፍት መን አን 1)
እንዲያም ሆኖ ምእመናን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆናቸውን ረስታ፣ ዘንግታ፣ ስታና ተሳስታ አይደለም፡፡ ይልቁንም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አኮኑ ንህነ ቤቱ ለእግዚአብሔር ሕያው፤ እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይደለንምን›› የሚለውን ቃል ተቀብላ በትሩፋታቸው የደከሙትን ሩጫቸውን የጨረሱትን ሃይማኖታቸውን የጠበቁትን እግዚአብሔር የጽድቅ አክሊል የሰጣቸውን አክብራ በስማቸው ታቦት አስቀርጻ ‹‹ቅዱሳን አበው›› ብላ ታከብራቸዋለች፡፡ እነዚህ በአፀደ ሥጋ ሳሉ አምላካችን ‹‹ወዳጆቼ›› ብሎ የጠራቸው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ›› ብሎ የገለጻቸው ንጹሓን ናቸው፡፡
እንግዲህ ታቦት አያስፈልግም ማለት በውስጡ እነዚህ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ›› ብሎ የሚጠራቸው የጽድቅ አክሊልን የተቀዳጁ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኛ›› ሲል የጠራቸውም ራሱን ጳውሎስን ጨምሮ አያስልግም እንደማለት ነው፡፡፡ እሱማ ይህ ምን ይገርማል እንኳን ጳውሎስን ክርስቶስንም ቢሆን አይሁድ አያስፈልግም ብለው ሰቅለው ገድለውታልና ይህ ዛሬም ቢደገም እግዚኦ ከማለት ውጭ ምን እንላለን?፡፡
ስለ ታቦት ብዙ መናገር ቢቻልም ለመናፍቃን መልስ ይሆን ዘንድ ታቦት እንዳለ ለማሳየት እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ማስረጃዎች በቂ ናቸው፡፡
ታቦቱና ስመ አምላክ
ከላይ እንዳነሣነው ታቦቱን ‹‹ቅርጻ ቅርፅ›› ሲሉ የስድብ አፋቸውን የሚያነሡ አሉ፡፡ ታቦቱ ግን እነሱ ከሚሉት በብዙ ነገር ይለያል፡፡
1ኛ. ታቦቱ ላይ ስመ አምላክ ታትሞበታል፡፡ ስመ አምላክ የታተመበት ‹‹ቅርጻ ቅርፅ›› ተብሎ ሊጠራ አይገባም፡፡ እርግጥ ነው ራሱ እግዚአብሔር ታቦት እንዲቀርፅ ለሙሴ በዚህ ግሥ ነግሮታል፡፡ ‹‹ቀር ከመ ቀዳምያት፤ እንደቀደመው አድርገህ ቅረፅ›› ብሎ፡፡
ይሁን እንጂ ያ ቅረፅ ብሎ ያዘዘው ሙሴም የቀረፀው ስመ አምላክ ከተጻፈበት በኋላ ታቦት እንጂ ‹‹ቅርጻ ቅርፅ›› ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተመዘገበም፡፡ ቅርፃ ቅርፅ የሚባለው ስመ አምላክ ያልተጻፈበት ተራው ነገር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም አክብሮ ታቦተ እግዚአብሔር ብሎ ጠራው እንጂ ‹‹ቅርፃ ቅርፅ›› ብሎ አላሳነሰውም፡፡ ለምን ቢሉ ስሙ ታትሞበታልና ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ስሙን በወደደው ላይ ጽፎ ማስተማር ይችላል፡፡ ደግሞም አድርጎት ይገኛል፤ በሚከተለው ክፍል እንመልከተው፡፡
መምህራችን እግዚአብሔር ለሙሴ ሲነግረው ‹‹በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ በፊቱም ተጠንቀቁ፡፡ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት›› ብሎታል፡፡ ዘጸ 23÷ 20-22
እንግዲህ ከዚህ ውስጥ እስራኤል ዘሥጋን ይመራ የነበረ መልአክ ስመ አምላክ እንደተሸከመ በመጽሐፍ ቅዱሱ ‹‹ስሜ በእሱ ስለሆነ ኃጢአት አትሥሩ›› ሲል ስሙ ካለበት ቦታ ሆኖ ኃጢአት መሥራት ነውር እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ስንመለከተው ደግሞ ታቦቱ ላይ ስሙ ታትሞበታል፡፡ ስሙ የታተመው ደግሞ የምናመልከው እግዚአብሔር ለመሆኑና የምንሰግደውም ለስመ እግዚአብሔር እንጂ ለሌላ እንዳልሆነ ምስክር ሊሆነን ነው፡፡
‹‹በመልአኩ ክንፍ ላይ ብዙ አስማተ ሥላሴ ተጽፈው እናያለን፤ እሊህም የሚከተሉት ናቸው፡፡ አልፋ፣ ወዖ፣ ቤጣ፣ የውጣ፣ ዮድ፣ አህያ፣ ሸራህያ ኤልሻዳይ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህ እየራሳቸው ትርጓሜ አላቸው ዘጸ 2÷14 ራእ 21 እነዚህም ፀረ አጋንንት ናቸው፡፡
ትንሽ ከሚመስል ቃል ብዙ ምሥጢር እንዳለ ብዙ ሰው አያውቅም፡፡ ይልቁንም በሀገራችን በሌላ ቋንቋ ሲጸልይ የተገኘ አስማተኛ ሊባል ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር ግን ስመ ሥላሴና ስመ አጋንንትን ለይቶ ማወቅ መልካም ነው፡፡ አንዳንዴ ኅቡዕ ስም በሚል የተጻፉ ከየመጽሐፉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ቃላት ስመ-አምላክ መሆናቸውን ካልተረዳን መጸለያችን ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም የምንጠራውን አላወቅንምና ነው፡፡ ስለዚህ ስሞች ኅቡዓት የሚሆኑት ላላወቀ ላልጠየቀ እንጂ ስመ-አምላክ መሆኑን ካወቅን እንጸልያቸዋለን፡፡ ማወቅ ካልቻልን ደግሞ ጸሎትነታቸው ሲረዳ በዐይን አይቶ ማመን ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ አበው ብዙ ምሥጢራቸውን በቀጥታ ጽፈው አላስቀመጡም፡፡ ይህንን ደግሞ በአብነት ትምህርት ቤት የአተረጓጎም ስልታቸውን ያነበበና የተማረ በቀላሉ ያውቀዋል፡፡
ለምሳሌ ከአበው ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው ትርጓሜ-ወንጌል ውስጥ መጽሐፈ ልደቱ ካለው አጠገብ ‹‹፩ዱ›› የሚል ቃል በምልክት ተቀምጧል፡፡ ይህንን ሊቃውንት ተራ ነገር ነው እንለፈው ብለው አላለፉትም፤ ተርጉመውት አልፈዋል፡፡ ሲተረጐም ብሂላቸው እንደ ወረደ እነሆ፤ ‹‹መጽሐፈ ልደቱ›› ባለው ቃል ‹‹፩ዱ›› ይላል፤ በጥቁር የንዑስ ምዕራፍ አኃዝ መሪ ነው፡፡ ካሉ በኋላ ወደምሥጢር ገብተው ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹መጽሐፈ ልደቱ›› ብሎ ስለ ክርስቶስ የተናገረው፣ ወንጌላዊ ማርቆስ ‹‹አንተ ውእቱ ወልድየ›› ብሎ አባቱ እግዚአብሔር ስለ ወልድ የመሰከረው፣ ወንጌላዊ ሉቃስ ‹‹ወይመስሎሙ ወልደ ዮሴፍ›› ለአይሁድ የዮሴፍ ልጅ ይመስላቸው ነበር ብሎ አይሁድን ያሳፈረበት ቃል፡፡ ነባቤ መለኮት ዮሐንስ ‹‹ቀዳሚሁ ቃል፤ያ ቃል ቅድመ ዓለም ነበር›› ብለው በጋራ የጻፉት ምሥጢር የአንድ የጌትነቱ ነገር ነውና ‹‹፩ዱ›› ተብሎ በኅዳግ (ታች) ተቀመጠ ሲሉ ለደቀ መዛሙርት ያስረዳሉ፡፡ (ትር.ማቴ.ገጽ.57)
አምላክ ነኝ ብሎ የሚመጣው ሐሳዌ መሲህ ሳይቀር ‹‹ስሜን በግምባራችሁ ጻፉ›› ሲል 666 ብለው ስሙን ግምባራቸው ላይ እንዲከትቡ ሕግ ያወጣል፤ ሥርዐት ይወስናል፡፡ ራእ13÷18 ይህ ሁሉ የሚያመለክተው አምላክችን የሠራውን አማናዊ ሥራ ሐሳዌ-መሲሕ በማስመሰል ሊጠቀምበት ስለሚፈልግ ነው፡፡
እናም አምላካችን እግዚአብሔር ከመልአኩ ክንፍ ላይ ስመ እግዚአብሔር እንዴት ጻፈ የሚል ጥያቄ ካላችሁ የወደደውን ሊያደርግ ይችላልና ‹‹ይችላል›› ብቻ ብላችሁ እመኑ፡፡ የቃል ኪዳኑን ታቦት ለሙሴ ሲሰጠው ታቦቱ ላይ ስሙ ተጽፎ ነበር፡፡ ይህም የክብሩ መገለጫ ሊሆን እስራኤል ዘሥጋ ስሙን እየጠሩ እንዲያመልኩት ነው፡፡ ዛሬም በሐዲስ ኪዳን ለታቦት እንሰግዳለን ስሙ ተጽፎበታልና፡፡ አምልኮ-ባዕድ አልፈጸምንም፡፡ ለቅዱስ ሚካኤል የጸጋ ስግደት እንሰግዳለን ስሙ ታትሞበት ይኖራልና፤ ወዲህም አቅራቤ ስብሐት ነውና ‹‹ተዉ›› ብሎ ሊገዝተን ሥርዐት ሊያስተምረን፣ መምህር ሊሆን ማንም አይምጣ፤ አስቀድመን ተምረናልና፡፡
መምህራችን ራሱ እግዚአብሔርም ለሙሴ ሲነግረው ‹‹እነሆ እኔ መልአኬን በፊትህ እልካለሁ ራስህን ጠብቅ ስማው» ካለ በኋላ በመልአኩ ላይ ስሙ እንደታተመ ሲነግረው ‹‹ስሜ በእርሱ ላይ አለ›› ብሎታል፡፡ ዘጸ. 23÷21›› ሲል ስመ-አምላክ በታቦትም ሆነ በመላእክት ክንፍ ላይ ተጽፎ እንደሚገኝ ያብራራል፡፡
በሐዲስ ኪዳን ታቦት ለመኖሩና ለታቦት መስገዳችንም ከላይ ባነሣነው ነገረ ሃይማኖት ሲሆን በአጭሩ ታቦት መኖሩን ቅዱስ ጳውሎስ ነገረን፡፡ ኋላም 318ቱ ሊቃውንት በፍትሐ ነገሥት ወይኩን ታቦት ዘይፈልስ እመካን ውስተ መካን፤ ታቦት በቅርፁ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ ሆኖ እንዲቀረፅ ወሰኑ፡፡ መስገዳችንም ስመ አምላክ ስለታጸፈበት እንደሆነ ተረዳን፡፡ እናም ‹‹ወኢትቅረቡ ኀበ ርኵሳን፤ ወደረከሱት አትቅረቡ›› ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን የረከሱትን እያስተማርን ለቅዱስ ታቦት እንደሁኔታው የአምልኮና የጸጋ ስግደት እንሰግዳለን፡፡ ይህም ‹‹ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ፤ የጌታችን እግር በቆመበት ሁሉ እንሰግዳለን ብሎ ቅዱስ ዳዊት ባስተማረን መሠረት እንጂ ባለማወቅ አይደለምና አንባቢው ያስተውል፡፡ መዝ 131÷7
በኦሪት የእግዚአብሔር ታቦት የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ሆኖ አግልግሎት ሰጥቷል፡፡ ይኸውም ስመ እግዚአብሔር ስለተጻፈበት ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ታቦተ እግዚአብሔር የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ስመ እግዚአብሔር ተጽፎበታልና ነው፡፡ ትናንት በኦሪት ዛሬም በወንጌል ክብሩ ሊገለጽ የሚችለው ስመ እግዚአብሔር ስለ ተጻፈበት ነውና፡፡ ስመ እግዚአብሔር ደግሞ ትናንት በብሉይ ኪዳን ዛሬም በሐዲስ ኪዳን አንድ ነው፡፡ አንድ ነው ማለትም ያው ስሙ ሌላ እሱ ሌላ አይደለም ማለት ነው፡፡ እናም ዛሬም ሆነ ነገ ስመ እግዚአብሔር መጥራት ለስሙ መስገድ ሃይማኖታዊ ምስጢራችን ነው፡፡ ከመ ለስሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሰግድ ኵሉ ብርክ ዘውስተ ሰማይ ወዘውስተ ምድር፤ በሰማይም ሆነ በምድር ለስሙ ጉልበት ሁሉ ይንበረከካል ይሰግዳል ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ ፊል.2
ከጥንት አባቶቻችንም ሆነ ሊቃውንት ታቦት ይቅር ብሎ ያስተማረ የለም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታቦት አያስፈልግም፤ ታቦት እኛ ነን ለማለትስ መነሣታችን ሰው ሁሉ ታቦት ነው ብሎ ማን አስተማረ? ቅዱስ ጳውሎስ እንኳ ታቦት እኔ ነኝ ሲል አልሰማንም፡፡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በስመ እግዚአብሔር የሚመጣው ሐሳዌ መሲህ ብቻ ነው፡፡