“በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” (ማቴ. ፲፯፥፬)

“በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” (ማቴ. ፥፬)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ በድምቀት ታከብራለች፡፡ ደብረ ታቦር ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከልም አንዱ ነው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን “የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉ አሉ፤ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አሉት፡፡ እርሱም “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ሐዋርያትን ጠየቃቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ “አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብፁዕ ነህ፤ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና …” ብሎታል፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፲፫-፲፱)

ከዚያም በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን እንደሚነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸው ጀመረ፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ግን የሞቱን ነገር ሲሰማ “አቤቱ ይህ አይሁንብህ፡ ከቶም አይድረስብህ” እያለ ይከለክለው ጀመረ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ምስጢር ተሰውሮበታልና ጌታችንን ተከላለከለው፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፲፫-፳፫) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መለስ ብሎ ጴጥሮስ “አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ ዕንቅፋት ሆነህብኛል፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታሰብምና” በማለት ገሰጸው፡፡

ከስድስት ቀን በኋላም ቅዱስ ጴጥሮስን፣ ቅዱስ ያዕቆብንና ወንድሙን ቅዱስ ዮሐንስን ይዞ ሌሎቹን ደቀ መዛሙርቱን ደግሞ በእግረ ደብር ትቶ ወደ ደብረ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በዚያም መልኩ በፊታቸው ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከሙታን፣ ሞትን ካልቀመሱት ነቢያት መካከል ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን ነቢዩ ኤልያስ መጥተው ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው፡፡

ሦስቱም ደቀ መዛሙርት ባዩት ነገር ተደነቁ፡፡ በዚያም መኖር መልካም እንደሆነ አስተዋሉ፡፡ ከመካከላቸውም ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “አቤቱ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ ሦስት ቤቶችን በዚህ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፣ አንዱንም ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ” አለው፡፡ እርሱ ገና ይህን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ አብ በደመና ውስጥ ሆኖ “የምወደው እርሱም ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ቃል መጣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ያዩትንና የሰሙትን መቋቋም አልቻሉም፣ እጅግም ፈርተው ነበርና በግምባራቸው ወድቀው ሰገዱ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ዳሰሳቸውና “ተነሡ አትፍሩም” አላቸው፡፡ ዐይኖቻቸውን አቅንተው ቢያዩ ከጌታችን በስተቀር ያዩት ሌላ ማንም አልነበረም፡፡ ከተራራውም ሲወርዱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ ከሙታን ተለይቶ እስኪነሣ ደረስ ያያችሁትን ለማንም አትናገሩ” ብሎ አዘዛቸው፡፡

እነርሱ ግን ባዩትና በሰሙት ሁሉ ተመስጠዋልና ከአምላካቸውና ከነቢያቱ ጋር በዚያ አብሮ መኖርን ናፈቁ፡፡ የረቀቀው ገዝፎ፣ የራቀው ቀርቦ ምስጢር እየተገለጠላቸው ዓለምን ንቀው ይኖሩ ዘንድ ተመኙ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ግን ጊዜው ሲደርስ በጊዜው ሁሉን ያከናውናልና ከዚህ በላይ ምስጢሩን መሸከም አይችሉምና ይዟቸው በእግረ ደብር ወዳሉት ሐዋርያት ወሰዳቸው፡፡ ከተራራው ሲወርዱም ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን እየጠየቁትና እየመለሰላቸው ምስጢር እየገለጠላቸው ወርደዋል፡፡  

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢረ መንግሥቱን ለምን በደብረ ታቦር ተራራ ገለጠ ቢሉ፡- ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡

፩. ትንቢቱን ለመፈጸም፡- በነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ምስጢረ መንግሥቱን ለደቀ መዛሙርቱ ገልጦላቸዋል፡፡ “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ ስምህን ያመሰግናሉ” እንዲል (መዝ. ፹፰፥፲፪)፡፡

. ምሳሌውን ለመፈጸም፡- ታቦር ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል አድርጎበታል (መሳ. ፬፥፮)፡፡ “የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ፡፡ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ የሠራዊቱም አለቃ ሲሣራ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና እስራኤላውያንን ሃያ ዓመት ያስጨንቃቸው ነበር፡፡ (መሳ. ፬፥፩-፫)፡፡ እግዚአብሔርም እስራኤላውያን ከዚህ ቀንበር ይላቀቁ ዘንድ አመለከታቸው፡፡ (፩ቆሮ. ፲፥፲፫)፡፡ እስራኤላውያን ወደ ፈጣሪያቸው በጮኹ ጊዜም ነቢይቱን ዲቦራን ተጠቅሞ የማሸነፊያ መላውን አመለከታቸው፡፡ እግዚአብሔር በነቢይቱ በዲቦራ በኩል ለእስራኤል ንጉሥ “ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጡ” ብሎ አዞት ነበርና ንጉሡ ዐሥር ሺሕ ብረት ለበስ ያልሆነ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ደብረ ታቦርን ተማምኖ በተራራው ላይ መሸገ፤ ጦርነቱም ሳይጀመር አለቀ፡፡ ምክንያቱም “እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ” (መሳ. ፬፥፲፭)፡፡ እስራኤላውያንም በእግዚአብሔር አጋዥነት በታቦር ተራራ ላይ የሃያ ዓመት የግፍና የሰቀቀን አገዛዝን አስወገዱ፡፡

ለምን ሦስቱን ሐዋርያት ብቻ ይዞ ወጣ?

፩. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እሞታለሁ፤ እሰቀላለሁ” ባለ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “አቤቱ ይህ አይሁንብህ፤ ከቶም አይድረስብህ” ብሎ ተቃውሞት ነበርና አብ በደመና ሆኖ “የምወደው፣ በእርሱም ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ቃል ተነግሯቸዋልና ይህ ለአንተ አይገባም አትበሉት፤ አትቃወሙት” ለማለት፡፡ (ማቴ. ፲፯፥፭-፮)

. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎት ነበርና አሁንም አብ “እመለክበት ዘንድ ለተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ለማረጋገጥ፡፡

. ለፍቅሩ ስለሚሳሱ ነው፡፡  

. በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ አንዱን ሐዋርያት ወደ ተራራ ይዞ ይሁዳን ትቶ ቢወጣ ከምሥጢር ቢለየኝ በሞቱ ገባሁበት እንዳይል ነው፡፡ ታዲያ በይሁዳ ምክንያት ስምንቱ ሐዋርያት ለምን ተከለከሉ ቢሉ፡- አልተከለከሉም፡፡ በርእሰ ደብር (በተራራው አናት) ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተገለጸው ምስጢር በእግረ ደብር (በተራራው ግርጌ) ለነበሩት ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦላቸዋል፡፡

ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን፣ ከሙታን ሙሴን ለምን አመጣቸው?

፩. ሊቀ ነቢያት ሙሴ እግዚአብሔርን፡- “አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆነ ዐውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ ይህም ትልቅ ሕዝብ ሕዝብህ እንደሆነ ዐውቅ ተገለጥልኝ፡፡ … ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም፡፡ …እስካልፍም ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፡፡ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፤ በዚያ ጊዜ ጀርባዬን ታያለህ፣ ፊቴ ግን ለአንተ አይታይም “ብሎት ነበር (ዘጸ. ፴፫፥፲፫-፳፫)፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጽሟል፡፡

፪. ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን፡- “አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ” ብሎት ነበር፡፡ ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ” ሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡

፫. በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?” ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ሙሴ ነው ይሉሃል ፤ እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል” ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ፤ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ ፤ አምላከ ሙሴ ፤ እግዚአ ኤልያስ ፤ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡

፬. አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታን እንደ ሕግ ተላላፊና የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ የሚወስድ አድርገው ያስቡት ስለ ነበረ (ዮሐ. ፱፥፲፮፤ ፲፥፴፫) ሕግን የሰጣቸው ሙሴንና ለሕገ እግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረው ኤልያስን አምጥቶ ሕግ አፍራሽ አለመሆኑን የእግዚአብሔር ተቃዋሚም አለመሆኑን ለማስረገጥ፡፡

፭. የሐዋርያቱን የወደፊት አገልግሎት ሲነግራቸው፡፡ ይኸውም ሙሴ እና ኤልያስ ለሕዝበ እስራኤል በጣም ታማኝ እንደነበሩ ሁሉ እነርሱም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ታማኝ እረኞች እንዲሆኑ፡፡ ምክንያቱም ውጊያቸው እንደ ሙሴ ከፈርዖን እንደ ኤልያስም ከአክዓብ ጋር ሳይሆን ከክፋት መናፍስት ጋር ነውና፡፡

ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ሲል ተደምጧል፡፡ ይህም የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ማለቱ “አንተ እያበላኸን እየፈወስከን፣ ሙሴ እነዚህ መከራ ያደርሱብኛል፣ ይገድሉኛል ያልካቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን እንዳይመጡ በደመና እየጋረደ፣ ቢመጡም አልያስ እሳት እያዘነመ እያባረራቸው በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” ማለቱ ሲሆን ምሥጢራዊው መልእክቱ ግን “የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት በሚታመንበት፣ ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ሰይጣን ድል በተደረገባት በታቦር ተራራ ምሳሌም በምትሆን በወንጌል ሕይወት፣ አንድም በቤተ ክርስቲያን መኖር ለእኛ መልካም ነው” ማለቱ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *