በዓለ ጥምቀት

ጥምቀት አጥመቀ፤ አጠመቀ (ነከረ)፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውና የሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መግቢ በር ነው፡፡ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ መቶ ሃምሳው አባቶች “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት፤ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በማለት እንደመሰከሩት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት በዓልን ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት  ቀጥላ ከቅጽረ  ቤተ ክርስቲያን ወጥታ  በዱር፣ በሜዳ፣  በወንዝ፣ በባሕር  ዳርቻ  ጥር ፲፩  ቀን  በየዓመቱ  በታላቅ ድምቀት የምታከብረው በዓል ነው፡፡

ጥምቀት ሰው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆንበት ታላቅ ምሥጢር ነው (ማቴ፣ ፳፰፥፲፰)፡፡ ይህ ምሥጢር ከምሥጢራት ሁሉ የመጀመሪያ ነው። ምሥጢር መባሉም በዓይን በሚታይና በጆሮ በሚሰማ አገልግሎት በዓይነ ሥጋ የማይታይና በዕዝነ ሥጋ የማይሰማ ጸጋ ስለሚገኝበት ነው። አገልግሎቱ ሲፈጸም ይታያል፣ ይሰማል፤ ተጠማቂው ከውኃና ከመንፈስ ተወልዶ የልጅነት ጸጋ ሲያገኝ ግን አይታይም፣ አይሰማም። ይህ ምሥጢር የሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር ነው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን በወንጌል “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሏል (ዮሐ. ፫፥፯)፡፡ ይህንን ነው ጌታችን ዳግም ልደት ያለው (ዮሐ. ፫፥፫)፡፡ የመጀመሪያው ልደት ከአባት አብራክና፣ ከእናት ማኅፀን በሥጋ መወለድ ሲሆን ሁለተኛው ልደት ግን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ረቂቅ በሆነ ልደት በመንፈስ መወለድ ነው። ይህንንም ጌታችን “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” ብሎታል (ዮሐ. ፫፥፮)፡፡

ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ነው። በጥምቀት በዓል የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው። በዮርዳኖስ የተጠመቀውም ስለ ሁለት ነገር ነው፦

፩ኛ• ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ባሕር አየች ሸሸችም፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” ብሎ የተናገረውን ትንቢት በእርሱ ጥምቀት ለመፈጸም( መዝ፣፻፲፫፥፫)፡፡

፪ኛ• በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን እንደ ሰውነቱ ረግጦ፤ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ ሊደመስስልን።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ ለድኅነተ ዓለም፣ አንድም ለአብነት በፈለገ ዮርዳኖስ በዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ ተጠምቋል። በተጠመቀ ጊዜም የባሕርይ አባቱ አብ በደመና ሆኖ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ መስክሯል፤ መንፈስ ቅዱስም በፀአዳ ርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጧል። (ማቴ. ፫፥ ፲፫–፲፯)፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን ምክንያት በማድረግ ለዚህ ቅዱስ ዕለት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች፡፡ በየዓመቱም ታቦታቱ በዋዜማው ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው በአደባባይ በሊቃውንቱ እና በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም በምእመናን በዝማሬ ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመውረድ በወንዝ ዳር ወይም  በሰው ሠራሽ የውሃ ግድብ አጠገብ በዳስ ወይም በድንኳን ያድራሉ። ሌሊቱንም በማኅሌትና በቅዳሴ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ሥርዓተ ቅዳሴው ይፈጸማል። ሲነጋም በወንዙ ዳር ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል።

ጥምቀት ረቡዕ ቢውል ገሀድ ማክሰኞ፤ አርብ ቢውል ገሀድ ሐሙስ ለውጥ ሁኖ ይጦማል። ጥምቀት የሚውልባቸው አርብና ረቡዕ ስለ በዓሉ ታላቅነት ፍስክ ይሆናሉ። ጥምቀት በፍስክ ቀናት ቢውልም በዋዜማው ይጾማል።

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን ራሱ ከፈጸመ በኋላ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ በማለት ጥምቀተ ክርስትናን እንደመሠረተ፣ ሰው ዳግመኛ ከውኃና፣ ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ እንደማይችል ያመልክተናል።

በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት መሠረት ሁለተኛ መወለድ ማለት እንደገና ወደ እናት ማሕፀን ተመልሶ በሥጋዊና በደማዊ ፈቃድ መወለድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ረቂቅ ልደት /የነፍስን ልደት/ መወለድ ማለት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር የመወለድ ጸጋ የሚገኘው በጥምቀትመሆኑን ያሳየናል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን መሠረት አድርጋ ከማይጠፋ ዘር የምንወለደውን ልደት ወንድ ልጅ በተወለደ በ፵ ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ፹ ቀኗ ታጠምቃለች፡፡እንዲሁም ዘግይው የመጡትን ግን እንደ አመጣጣቸው አንድነቱን ሦስትነቱን፣ አምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ መሆኑ ተምረው ካመኑ በኋላ ታጠምቃቸዋለች። (ማር. ፲፮፥፲፮)፡፡

ይህ ከእግዚአብሔርየመወለድ ጸጋ የተገኘውም በሃይማኖት ነው። ክርስቶስን አምላክ ወልደ አምላክ ነው ብሎ በሃይማኖት ያልተቀበለ ከእግዚአብሔር መወለድ አይችልም። ለአመነና በሃይማኖት ለተቀበለ ብቻ የሚሰጥ ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ ይህንን ታላቅ የመዳን ምሥጢር እና ከእግዚአብሔር ልጅነትን የማግኘት ሥልጣን ሲያስረዳ “በስሙ ያመኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይባሉ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ዮሐ. ፩፥፲፩–፲፫) በማለት አምልቶና አስፍቶ ጽፎልናል።

ስለዚህ ጥምቀት ምሥጢር የተባለበት ምክንያት፡– 

  • ላመኑ እንጂ ላላመኑ አይሰጥምና በዐይን የሚታየው በእጅ የሚዳሰሰው ግዙፍ ነገር በመንፈስ ቅዱስ ሲለወጥ አይታይምና፣
  • ምእመናንም በጥምቀት በሚታየው የማይታየውን ጸጋ ሲቀበሉ አይታይም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግ ጠባዕያዊያን በመፈጽም፣ ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ ፴ ዓመት ሲሆነው  በዘመነ ሉቃስ ጥር ፲፩ ቀን  ማክሰኞ ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት በባሕረ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል፡፡ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል”  በማለት ሰው ሁሉ ይድን ዘንድ ተጠምቆ ተጠመቁ ሲለን አርአያ ይሆነን ዘንድ ተጠመቀ፡፡ (ማር ፲፮፥፲፮)፡፡

ጌታችን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሲሱስ ክርስቶስ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ወርዶ እንደሚጠመቅ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነጽርነት ዐይቶ በመዝሙሩ እንዲህ ሲል ተናግሯል “ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ ወአድባር  አንፈርዐጹ ከመ ሐረጊት ወአውግርኒ  ከመ መሓስአ አባግዕ ምንተ ኮንኪ ባሕር ዘጎየይኪ ወአንተኒ ዮርዳኖስ ዘገባእከ፤ ባሕር አየች ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ ተራሮች እንደ ኮርማዎች ኮረብታዎችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፡፡ አንቺ ባሕር የሸሸሽ አንቺ፣ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል? እናንተ ኮረብቶችስ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ”  (መዝ. ፻፲፫፥፫-፮)፡፡

ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሄዶ የተጠመቀበት ምክንያት፡-

፩. ትሕትናን ሲያስተምር ነው፡- ምነው ጌታ ፈጣሪ፤ እግዚእ ሲሆን ወደ ዮሐንስ ሄደ ቢሉ ሥጋ መልበሱ ለትሕትና ነውና፡፡ ይህ ባይሆን ዛሬ ነገሥታት ቀሳውስትን ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን አቁርቡን ይሉ ነበርና፡፡

፪. ትንቢቱና ምሳሌውን ለመፈጸም (ሕዝ. ፴፮፥፳፤ መዝ.፻፲፫፥፫-፮)

ጌታችን መድኃኒታችን መጠመቅ ለምን  አስፈለገው?

፩. ጥምቀት ለሚያስፈልገን ለእኛ አርአያ ለመሆን ነው፡- እርሱ ተጠምቆ ተጠመቁ ባይለን ኑሮ ጥምቀት አያስፈልግም፡፡ አስፈላጊ ቢሆንማ ጌታ ራሱ ተጠምቆ አብነት በሆነን ነበር እንዳይሉ መናፍቃን ምክንያት አሳጣቸው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዩሐንስም ”ወአርኃወ ለነ አንቀጸ ጥምቀት ከመ ንጠመቅ፤ እንጠመቅ ዘንድ የጥምቀትን በር ከፈተልን” ሲል የጥምቀትን ምስጢር ያስረዳናል፡፡

፪. ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ፡- “አቤቱ ውኃዎች አዩህ ውኃዎች አይተውህ ፈሩ ጥልቆችም ተነዋወጡ  ወኃዎችም ጮሁ  ደመኖችም ድምጽን ሰጡ  ፍላጾችም ወጡ” (መዝ.፸፯፥፲፮-፲፯) የሚል ትንቢት ነበርና ይህ እንዲፈጸም፡፡

፫. በዮርዳኖስ ውስጥ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ( ሰኞ ውዳሴ ማርያም)

፬. አንድነትና ሦስትነቱን ለማስረዳት፡- ከዚህ በፊት የሥላሴ ሦስትነት በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ ጌታ በዮርዳኖስ በሚጠመቅበት ጊዜ ግን ምሥጢረ ሥላሴ ግልጽ ሁኖ አብ በደመና ሁኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጦ ሲታይ ወልድ በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ ተገለጠ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *