በራስህ ጥበብ አትደገፍ (ምሳ. ፫፥፭)
መ/ር ቢትወደድ ወርቁ
በወጣትነት ዘመናችን እጅግ ከምንቸገርባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ራስን ዐዋቂ አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ይህም በራስ ጥበብ የመደገፍ አንዱ ችግር ነው፡፡ ለሚፈጠርና ሊፈጠር ላለ ችግር “እንዲህ የሆነው እንዲህ ስለሆነ ነው፤ በዚህ ምክንያት እንዲህ ሊሆን ነው፤ እንደዚህ ያለው ለዚህ ይመስለኛል፡፡” በማለት ራስን ዐዋቂ አድርጎ ማቅረብ በራስ የመደገፍ ፍላጎትን ከፍ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም አንድ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ ለምን የሚል ጥያቄ ሲነሣ “ደስ ስላለኝ ነው፤ ስለ መሰለኝ ነው” የሚሉ መልሶች እየበዙ መምጣታቸው በራስ ጥበብ የመደገፋችንን ግዝፈት የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
ይህ አስተሳሰብ አደገኛ የሚያደርገውም የሕይወት ልምድ በሌለበት እንኳን በሕይወትና በኑሮ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃም ቢሆን የጠለቀ ዕውቀትን ገንዘብ ባላደረግንበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወጣቶች “ለራሴ የማውቀው ራሴ ነኝ፣ በሕይወቴ ጣልቃ አትግቡ…” እና የመሳሰሉ ሐሳቦችን በማንሣት ወላጆቻቸውንና ታላላቆቻቸውን ሲከሱና ሲያስጠነቅቁ ይስተዋላሉ፡፡ የሚያሳዝነው ግን እንዲህ የሚሉ ወጣቶች ራሳቸውን በሚጎዳ፣ የቤተሰቦቻቸውን አንገት በሚያስደፋ፣ ማኅበረሰባዊ ዕሴትን በሚንድ እና ጤናን በሚያናጋ ተግባር ላይ ተሰማርተው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ፍፃሜአቸው አስከፊ ይሆናል፡፡
ትልቅ ተቋም የሚባለውን ትዳር መሥርተው እንኳን የትዳር አጋራቸውን ምንም የማያደምጡ በቤታቸውና በትዳራቸው ጉዳዮች ሁሉ “እኔ አውቃለሁ፤ እንዲህ ነው መሆን ያለበት” በማለት በራሳቸው ጥበብ ብቻ በመደገፍ የሚወስኑ ሰዎችም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ እኔ ትክክል ነኝ ብለው ስለሚያስቡም በራሳቸው ጥበብ ላይ ብቻ በመንጠላጠል ከሌላው አካል የሚቀርብላቸውን ሐሳብ ለማድመጥ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡
ለዚህ ዓይነቱ ጠባይ መዳረግን የሥነ ልቡናው ዘርፍ እንደ አንድ ትልቅ እክል እንደሚመለከተው የታወቀ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ያልተመረመረ፣ ታላላቅ ሐሳብ ባላቸው ታላላቅ አባቶችና ወንድሞች ያልተፈተሸ የራስ ጥበብ ወደ ወድቀት ይመራል፡፡ እናታችን ሔዋንና አባታችን አዳም ከእግዚአብሔር የተነገራቸውን “በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ፣፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” የሚለውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (ዘፍ. ፪፥፲፮-፲፯) ተላልፈው በራሳቸው ጥበብ በመመካት እና አምላክ የመሆን ፍላጎታቸው አይሎ ለውድቀት ተዳርገዋል፡፡
በወጣትነት ዕድሜ ይቅርና በጉልምስናም ዕድሜ ቢሆን ራስን ብቻ ለራስ አዋቂ አድርጎ መቁጠር ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ሰው እንደመሆናችን መጠን አያሌ ክፍተቶች ይኖሩብናል፡፡ የዕይታ አድማሳችንም ቢሆን ፍጹም አይደለም፡፡ በራስ ጥበብ ብቻ መደገፍ የትዕቢትም መገለጫ ነው፡፡ በራስ ጥበብ መደገፍ በማንኛውም መመዘኛ ስንመዝነው ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ለምን? ቢሉ መጽሐፍ “መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትሽ” በማለት እንደገለጸው ማንኛውም አስተሳሰብ እና ዕውቀት በእግዚአብሔር ቃል መመዘንና መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ (ሰቆ. ኤር. ፫፥፵)
መንገዳችንን እንመርምር ከተባለ በምን እንመርምረው? የሚል ጥያቄ መነሣቱ ግድ ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነፃል?” ብሎ ይጠይቅና “ቃልህን በመጠበቅ ነው” በማለት ደግሞ ይመልሳል፡፡ (መዝ. ፩፻፲፰፥፱) በእግዚአብሔር ቃል የተገራ፣ በኑሮ ልምድ የተፈተነ፣ በዕውቀትና በጥበብ የተደራጀ ማስተዋል ያለው ሰው መንገዱ ይቀናለታል፣ እሾህና አሜኬላውን በአሸናፊነት ይሻገራል፡፡
በራስ ዕወቀትና አስተሳሰብ መደገፍ ብዙዎችን ሲጥል ተመልክተናል፡፡ ይህንንም ከሮብአም መማር ይቻላል፡፡ ሮብአም በነገሠበት ዘመን የእስራኤል ጉባኤ በአንድነት ተሠብስበው “አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልን እኛም እንገዛልሀለን” ብለው ተናገሩት፡፡
እርሱም መክሬ እስክወስን ከሦስት ቀን በኋላ ተመለሱ አላቸው፡፡ እርሱም ታላላቆቹን የሀገሩን ሽማግሌዎች ሰብስቦ “ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ በዚህ ዙሪያ ምን ትመክሩኛላችሁ?” አላቸው፡፡ ሽማግሌዎቹም “ለዚህ ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው በዘመኑ ሁል ባሪያዎች ይሆኑልሃል፡፡” ብለው መልካሙን ምክር መከሩት፡፡ እርሱ ግን ይህንን የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉት ብላቴኖች ጋር በነገሩ ላይ ተመካከረ፡፡ እነርሱም “አባትህ ቀንበር አክብዶብናል አንተ ግን አቃልልን ለሚሉህ ሕዝብ፡- ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፡፡ አሁንም አባቴ ቀንበር ጭኖባችኋል እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፡፡” በላቸው ብለው ማስተዋል የጎደለው ትዕቢትና ዕብሪት የተጫነው ክፉ ምክር መከሩት፡፡ እርሱም እነዚህ ብላቴኖች እንዳሉት አደረገ፡፡ ይህንም በማድረጉ ሕዝቡ ተነሥተውበት በድንጋይ ደብድበው ገደሉት፡፡ በራስም ሆነ በእግዚአብሐር ቃል ባልተቃኘ ጥበብ መደገፍ ፍፃሜው እንዲህ ነው፡፡ (፩ነገ. ፲፪፥፩-፲፱)
በራስ ጥበብ መደገፍ ስንጀምር ሁሉንም ነገር በራስ ዕውቀት ልክ ለመመዘንና ለመተንበይ እንጥራለን፡፡ ሰው እንደ ግዙፍ ተራራ ከፊቱ የገጠመውን ተግዳሮት በራሱ ዕውቀትና የዕይታ መነጽር ብቻ የሚመለከት ከሆነ በእግዚአብሔር መታመንን ያጣል፡፡ ለዚህ ነው ጠቢቡ ሰሎሞን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታምነህ ኑር፤ በራስህም ጥበብ አትደገፍ” በማለት የመከረን፡፡ (ምሳ. ፫፥፭) ችግር ሁሉ በሰው ዕውቀትና የማስተዋል ልክ ይመርመር ከተባለ ይወሳሰባል፤ መከራ ሁሉ ይከብዳል፤ ኀዘን ሁሉ ይጸናል፤ ስለሆነም በራስ ማስተዋል ከመደገፍ በእግዚአብሔር መታመን ይበልጣል፡፡
የራሳችን ማስተዋል ክፋቱ ክፉውን በክፉ መመለስ አቻ የማይገኝለት አማራጭ አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ ክፉውን በክፉ መመለስ ክፋትን አያጠፋም፡፡ በወጣትነት ዘመናችን ለብስጭታችን ሱሰኝነትን፤ ለኀዘናችን ቁዘማን እንደ መፍትሔ መውሰድ ለበለጠ ስቃይና መከራ ይዳርገናል፡፡
ስለሆነም ጥበባችን እውነተኛ ጥበብ እንዲሆን በእግዚአብሔር ቃል እንመዝነው፡፡ በታላላቆች ምክርም እንገምግመው፡፡ ተግባራችን በሌላውም ላይ ሆነ በራሳችን ላይ ሌላ ችግር እንዳያስከትል በራሳችን ጥበብ መደገፍን አቁመን በእግዚአብሔር እንታመን፣ እንደገፍም፡፡
እውነተኛ ጥበብ መመዘኛው ምንድነው? ለሚል ሰው መጽሐፍ እንዲህ ይላል “ከእናንተ ብልህና አስተዋይ ማን ነው? ከጠባዩ ማማር የተነሣ ሥራውን በቅንነትና በማስተዋል ያሳይ፡፡ ነገር ግን መራራ መቀናናትና መከዳዳት በልባችሁ ካለ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ፡፡ ይህቺ ጥበብ ከላይ የምትወርድ አይደለችም፤ ነገር ግን የምድር ናት፡፡ መቀናናትና መከዳዳት ባሉበት ሥፍራ ሁሉ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ አሉና፡፡ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ታራቂ ገር እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት፡፡ የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል፡፡”(ያዕ.፫፥፲፫-፲፰)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!