‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ›› ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ
በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳርማእከል
የመጨረሻው …ክፍል -፬
፰.መስቀል በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ሀገራችን ከቤተ እስራኤል ቀጥላ እግዚአብሔርን በማምለክ ከሌሎቹ ሀገራት ቀዳሚ እንደሆነች ታሪክ ያስረዳል፡፡ ሌሎቹ ሀገራት ለጣዖት ሲሰግዱ ሲንበረከኩ መሥዋዕት ሲሠው ኢትዮጵያ ሀገራች ግን በሦስቱም ሕግጋት (በሕገ ልቡና፣በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል) እግዚአብሔርን በማምለክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እያቀረበች ብሉይን ከሐዲስ አንድ አድርጋ ይዛ ኑራለች፡፡ ወደ ፊትም በዚህ መልካም ሥራዋ ጸንታ ትኖራለች፡፡ ኢትዮጵያ አምልኮተ ጣዖትን ተጸይፋ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ የምትማጸን በመሆኗ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የኾነው ቅዱስ መጽሐፍ ክብሯን ከፍ በማድረግ ከ፵ ጊዜ በላይ የከበረ ስሟን ለዓለም ሕዝብ ያስተዋውቃል፡፡
ኢትዮጵያ ባላት የሃይማኖት ጽናት የክርስቲያን ደሴት፣ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ምዕራፈ ቅዱሳን ተብላ ትጠራለች፡፡ የክርስቲያን ደሴት ሀገረ እግዚአብሔር ከመባሏም በላይ የእግዚአብሔር ቸርነት ያልተለያት የበረከትና የረድኤት ሀገር ናት፡፡ የበረከት ሀገር የክርስቲያን ደሴት እንድትባል ያደረጋት የቃል ኪዳኑን ታቦትና የዓለም ቤዛ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለሙን ያዳነበትን ሥጋውን የቆረሰበትን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበትን ግማደ መስቀሉን ይዛ በመገኘቷና ባላት የሃይማኖት ጽናት ነው፡፡
፱ .ግማደ መስቀሉ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ መጣ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የመጣው በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ታሪክ ይናገራል የመጣበትም ምክንያት በሀገራችን በተደጋጋሚ ረኀብ በሽታ ተክሥቶ ስለ ነበር በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ ዳዊት ረኀብና በሽታው እንዲቆም ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ችግሩ ሊወገድ የሚችለው የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሲመጣ እንደሆነ በራእይ ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ወደ ኢየሩሳሌም ቅድስት ዕሌኒ አስቆፍራ ካስወጣችው ከጌታ ግማደ መስቀል ከፍለው እንዲልኩላቸው ለገጸ በረከት የሚሆን ብዙ ወርቅ እና አልማዝ አስጭነው ወደ ኢየሩሳሌሙ ፓትርያሪክ ላኩ፡፡
ፓትርያሪኩ መልእክቱን ተቀብሎ የመስቀሉን ክፋይ አክሊለ ሦክ ቅዱስ ሉቃስ የሣላትን የእመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳን ሥዕለ አድኅኖ ጨምረው ላኩላቸው፡፡ መልክእተኞችም ይህን ተቀብለው የሲና በረሃ አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከመግባታቸው በፊት የክብር አቀባበል ሊያደርጉላቸው ሲሄድ የተቀመጡበት ባዝራ ጥሏቸው በክብር ዐረፉ እርሳቸው ቢሞቱም በኢትዮጵያውያን ጀግኖችና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ ጥረት በጌታ ፈቃድ ግማደ መስቀሉ ወደ ሀገራች ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ መጥቶም የኢትዮጵያን ምድር ተዟዙሮ ከባረከ በኋላ መቀመጫውን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራእይ ገለጸላቸው ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ›› ካላቸው በኋላ አፈላልገው ቦታውን አግኝው አሁን ካለበት ቦታ ላይ በወሎ ክፍለ ሀገር በግሸን አንባ ወይም ደብረ ከርቤ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በክብር አስቀምጡት፡፡ ከዚያ ዕለት ጀምረው ብዙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቦታው ድረስ ሄደው መስቀሉን ተሳልመው ቦታውን ረግጠው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ሲያገኙ ኖረዋል ወደ ፊትም ይኖራሉ፡፡
፲. የደመራው ምሥጢር
ደመረ ሰበሰበ አከማቸ አንድ ላይ አደረገ በአንድነት አቆመ ማለት ሲሆን ደመራ ማለት ደግሞ መደመር አንድ ማድረግ ማቆም ማለት ነው፡፡ ይህም ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ያሳየናል፡፡
አንደኛ በዓለ መስቀልን ለማክበር ከአራቱም አቅጣጫ በአንድነት ከታናሽ እስከ ታላቅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተሰበሰቡትን የቆሙትን ኦርቶዶክሳውያን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለመስቀል በዓል ከመድረሱ ፊት ከጫካ ተቆርጦ ተለቅሞ ተሰብስቦ መጥቶ እርጥቡ ከደረቁ፣ ደረቁ ከእርጥቡ በአንድነት ተሰብስቦ የሚቆመውን የደመራ እንጨት ያመለክታል፡፡
በእኛ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ደመራ የሚከመርበት ምክንያት ቅድስት ዕሌኒ የተቀበረውን መስቀል ከማውጣቷ በፊት እንጨት ከምራ ወይም ጨምራ ስለነበረ ያን አብነት በማድረግ በዓለ መስቀልን ለማክበር እንጨት እንጨምራለን እንከምራለን፡፡ በደመራው ፊት ለፊት ካህናቱ ጸሎተ አኮቴት ጸሎተ ምሕላውን ከጨረሱ በኋላ በዲያቆኑ ምስባኩ ከተሰበከ የዕለቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላና ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ የተደመረውን ደመራ ሊቃውንቱ ‹‹መስቀል አብርሃ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርአየ እያሉ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ ምእመናኑም ‹‹እዮሃ አበባየ መስከረም ጠባየ›› እያሉ ምእመናን በዕልልታና በዝማሬ ደመራውን እየዞሩ በተመረጡ አባቶች ይለኮሳል፡፡ የደመራው እንጨት ነዶ ከአበቃ በኋላ የተጸለየበትና በአባቶች የተባረከ ስለሆነ ምእመናኑ ወደ ቤታችው ይወስዱታል ሰውነታቸውን ይቀቡታል ልጆቻቸውን ከክፉ መንፈስ እንዲ ጠብቅላቸው ከአንገታቸው ላይ ያሥሩታል፡፡
፲፩. መስቀሉ ለኦርቶዶክሳውያን
ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔርን መስቀል ያላመኑበት ሰዎች አይጠቀሙበትም፡፡ የምናምንበት እኛ የተዋሕዶ ልጆች ግን ከሕይወታችን ጋር የተሳሰረ ከደማችን ጋር የተዋሐደ በልቡናችን ውስጥ ሥር የሰደደ ነው፡፡ ይህንን ስንልም ከአእምሮአችን አንቅተን ከልቡናችን አመንጭተን አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን ነው እንጂ፡፡ ስለሆነም፡-
፩ኛ. ቅዱስ መስቀል ለኦርቶዶክሳውያን አጥር ነው፡-አጥር ከዘራፊ ከቀጣፊ ከወራሪ እንደ ሚከለክል ሁሉ ቅዱስ መስቀልም ከሰይጣን ደባ ከአጋንንት ድብደባ የሚከላከል አጥር ነው፡፡ ይህንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል ይገልጻል ‹‹መስቀል ምጽንዓተ ቅጽርነ መስቀል ፀሐይ ሠርጐ ነገሥት ሠናይ፤ መስቀል የአንባችን ማጽኛ አጥር ነው መስቀል የተወደደ የነገሥታት ሽልማት ነው፡፡ መስቀል ፀሐይ ነው፡፡›› በማለት ለሰው ልጆች ሁሉ አጥር መሆኑን ገልጧል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የመስቀሉን አጥርነትና ኃይል አምነን እንዲህ በማላት ዘወትር ይማጸናሉ ‹‹መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ›› በማለት መስቀሉ አጥር ቅጥር መሆኑን እንመሰክራለን፡፡
፪ኛ. ቅዱስ መስቀል ለኦርቶዶክሳውያን መመከቻና ጠላትን ማጥቂያ ነው፡- አባቶቻችን ጠላት ሲነሣባቸው ፈተና ሲገጥማቸው በመስቀሉ ኃይል ተመክተው ድል ያደርጉ ነበር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ የሆነው ቅዱስ ያሬድ የቅዱስ ዳዊትን ቃል መነሻ አድርጎ በዜማ ድርሰቱ ላይ እንዲህ ሲል ይዘምራል ‹‹ብከ ንወግኦሙ ለኵሎሙ ፀርነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል ዘተሰቅለ ዲቤሁ ቃለ አብ ወበስምከ ነኀሥሮሙ ለእለ ቆሙ ላዕሌነ ወካይበ ይቤ ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቅስት ወይድኃኑ ፍቁራኒከ ወንሕነኒ ንትፈሣሕ ዮም ወንግበር በዓለ በዛቲ ዕለት፤ዳዊት በትንቢት መንፈስ ጠላቶቻችን ሁሉ በአንተ እንወጋቸዋለን በዚህ ዕፀ መስቀል ላይ የተሰቀለ የአብ አካላዊ ቃል ነው፡፡በላያችን ላይ የቆሙትን በስምህ እናጎሳቁላቸዋለን ዳግመኛም ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኻቸው ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ እኛም በዚች ዕለት ደስ ይበለን በዓልንም እናድርግ አለ›› በማለት እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚያመልኩ የጠላት መመከቻና ማጥቂያ እንደሆነ አስረግጦ ተናግሯል፡፡
በገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ከመክስምያኖስ ጋር ጦርነት በገጠመ ጊዜ ሊሸነፍ ሳለ በሰማይ በፀሐይ ብርሃን ላይ ተቀርጾ በራእይ ‹‹በዚህ መስቀል ጠላትህን ድል ታደርጋለህ›› የሚል ጽሑፍ አነበበ ቆስጠንጢኖስም ሳይጠራጠር በመስቀሉ ኃይል አምኖ በፈረሱና በበቅሎዎቹ ልጓም በጦር መሣሪያው በሠራዊቶቹ ልብስ ላይ እንዲሁም በሰንደቅ ዓላማው ላይ አስቀርጾ ቢገጥም መክስምያኖስና ሠራዊቶቹን ድል አድርጓቸዋል፡፡ ለብዙ ዘመናት ተከፋፍላ ትኖር የነበረችውን ሮምንም አንድ አደርጎ በመልካም አስተዳደር መርቷታል፡፡ እኛም የዚህ ዓለም ገዥ የሆነውን ጠላታችን ዲያብሎስ እና ሠራዊቱን በመስቀሉ ኃይል ድል እንድናደግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
፫ኛ. ምልክታችን ወይንም መለያችን ነው፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታታይ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን የሆነው ሁሉ ከሌላው እምነት የሚለየው በመስቀሉ ምልክትነት ነው፡፡መስቀል ለኛ ለተዋሕዶ ልጆች የማንነታችን መለያ የሕይወታችን አሻራ ነው፡፡ መስቀል መለያ ወይም ምልክት ይሆነን ዘንድ የሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ‹‹ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው›› (መዝ ፶፱÷፬) በመስቀሉ ምልክትነት ከዓለም ሕዝብ የለየን ለአንድ ዓላማ የጠራን እግዚአብሔር ነው፡፡ የእርስዎ መለያ ምልክት ምንድን ነው? መስቀሉ ወይስ ሌላ?
፬ኛ. መስቀል ሰላማችን ነው፡– ሰላም ስምምነት አንድነት ኅብረት ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ሰላም የሰው ልጅ ወጥቶ ሊገባ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው በሰላም በስምምነት በአንድነት መኖር እንዲችል አድርጎ ነው፡፡ ይሁንም እንጂ የሰው ልጅ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱና ከእግዚአብሔር በመለየቱ ለ፭ ሺህ ፭፻ ዘመን ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ኑሯል፡፡ የሰው ልጆች መቅበዝበዝ ያለ ሰላም መኖር ያሳዘነው ጌታ ወደ ዚህ ዓለም መጥቶ የሰላምን ወንጌል አስተምሮ የተበተነውን ሕዝብ ሰብስቦ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የተነጠቁትን ሰላም ለአዳምና ለልጆቹ መለሰላቸው፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ‹‹በመስቀሉ ሰላምን አደረገ›› ሲል የዘመረው በመስቀሉ ሰላምን ኅብረትን አንድነትን ሕይወትን አግኝተናል በመሆኑም ቅዱስ መስቀል ለኛ ለተዋሕዶ ልጆች ሰላማችን ነው(ቆላ. ፬÷፲፱ ኤፌ.፪÷፲፫-፲፰)
፲፪.መስቀል ለምን እንሳለማለን ?
ሐዋርያዊት ጥንታዊት፣ ዓለም ዓቀፋዊት ኵላዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ደመ ወልደ እግዚአብሔር የፈሰሰበትን ሥጋ ወደሙ የተፈተተበትን ከዲያብሎስ ወጥመድ አምልጠን ነጻ የወጣንበት ከባዱን የዲያብሎስን ሸክም ያቀለልንበት ቅዱስ መስቀልን አክብረን እንድንሳለመው ዘወትር ታስተምራለች፡፡ የተወዳዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የተቀደሰውን ነገር አክብረን ብንሳለመው ብንዳስሰው በረከት እንደምናገኝና እንደምንቀደስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ ‹‹ሁሉንም ትቀድሳችዋለህ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱሳን ይሁናሉ›› (ዘፀ.፴÷፳፱) በማለት ያስረዳል፡፡ እኛም በቅዱስ መስቀሉ ላይ አድሮ እግዚአብሔር እንደሚቀደሰንና እንደሚባርከን አምነን እንሳለመዋለን፡፡ በአጠቃላይ መስቀል የምንሳለመው ስለ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ነው፡-
፩. ሥርየተ ኃጢአትን ለመቀበል፣
፪. መንፈሳዊ ክብርንና ፀጋን ለመቀበል፣
፫. ለመስቀሉ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ስንል መስቀል እንሳለማለን፡፡
፲፫.በመስቀል መባረክ ወይም መሳለም የተጀመረው መቼ ነው?
በመስቀል አምሳል መባረክ ወይንም መሳለም የተጀመረው በዘመነ ኦሪት ወይም በብሉይ ኪዳን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሙሴናእና ካህኑ አሮን ይባርኩ እንደነበረና እግዚአብሔርም ቡራኬያቸውን ተቀብሎ ሕዝቡን በማያልቅበት በረከት ይባርክ እንደ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ ‹‹ስትባርካቸውም እንዲህ በላቸው እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህም—–እኔምእባርካቸኋለሁ›› ‹‹አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም››(ዘሌ.፱÷፳፪) ይላል፡፡ኦሪትን ሊሽር ሳይሆን ሊያጸናት የመጣ ፈጻሜ ሕግ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርቱን ሲባርካቸውም በኋላ ወደ ዓለም ለወንጌል አገልግሎት እንደላካቸው ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ‹‹እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጁንም አንሥቶ ባረካቸው››(ሉቃ.፳፬÷፶) አባቶቻችን ካህናትም እግዚአብሔር ለሙሴ እና ለአሮን የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩ እንዲህ በሏቸው በተባሉት የቡራኬ ቃል መሠረት ይባርኩናል በረከትንም እንቀበላለን፡፡
፲፬. በዓለ ቅዱስ መስቀል
ክርስቶስ በወርቀ ደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን ምእመናን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እንዲያገኙ ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲኖሩ ለቅዱሳን ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት እንዲገልጹ በዓላትን ሰፍራ ቆጥራ ይዛ በየወሩና በየዓመቱ መታሰቢያቸውን በላቀና በደመቀ ሁኔታ ታከብራለች፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው ክርስቶስ ተሰቅሎ ፍቅሩን ለዓለም ሕዝብ የገለጠበት የከበረ ሥጋውንና ደሙን ለልጆቹ ያደለበት መስከረም ፲፯ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የመስቀል በዓል ተጠቃሽ ነው፡፡
ሀገሯ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቧ ሕዝበ እግዚአብሔር ምድሯ ምዕራፈ ቅዱሳን በሆነችው በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በሊቃውንቱ ያሬዳዊ ዝማሬ በእናቶች ዕልልታ በወጣቶች ሆታ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ዝማሬ ተውበውና ደምቀው ከሚከበሩ መንፈሳዊና ዓመታዊ በዓላት መካከል አንዱ በዓለ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡
ይህን መንፈሳዊ በዓል ለማክበር ኦርቶዶክሳውያን እንደ ሰማያውን መላእክት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው በልብሳቸውም መስቀሉን አስጠልፈው ለቅዱስ መስቀል ያላቸውን ፍጹም የሆነ ፍቅር ይገልጻሉ፡፡ ይህን በዓል ለማክበር ነገሥታት ከዙፋናቸው ጳጳሳት ከመንበራቸው መነኮሳት ከገዳማቸው መምህራን ደቀመዛሙርት ከጉባኤ ቤቶቻቸው ካህናት ዲያቆናት ምእመናን በአንድነት በአራቱም መዓዝናት ወጥተው እንደ ቅድስት ዕሌኒ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነውና ታምነው በመስቀሉ ፍቅር ተማርከው በፍጹም ደስታ በየዓመቱ በአደባበይ ያከብሩታል፡፡
ምእመናን ይህን በዓል ሲያከብሩ በዓይነ ሕሊና የመስቀሉን ቅርጽ ብቻ ሳይሆን በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች ሲል በችንካር የተቸነከረ ደሙን ያፈሰሰ የክርስቶስን ውለታ በዓይነ ሕሊና ስለው በአዕምሯቸው ቀርጸው በልቡናቸው አንግሠው አንደበታቸውን በዝማሬ ያከብሩታል፡፡ ቅዱስ መስቀል በኢትዮጵያ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳ መስቀል የሌለበት ቤተ ክርስቲያን ባይኖርም በተለይ በቅዱስ መስቀል ስም በታነፁት አብያተ ክርስቲያናት ዘወትር ክብረ መስቀል ይነገራል፡፡
ከዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላትም አንዱ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ይሄውም በየዓመቱ መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት ከ፪፻ ዓመት በላይ ተቀበሮ ከኖረ በኋላ ተቆፍሮ የወጣበትን ምክንያት በማድረግ በከተማም ይኹን በገጠር በላቀና በደመቀ ሁኔታ ይከበራል፡፡ግማደ መስቀሉ በተቀመጠበትም በግሸን ደብረ ከርቤ መስከረም ፳፩ ቀን ብዙ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች በተገኙበት ይከበራል፡፡ እኛም መስቀሉን አክብረን በመስቀሉ ኃይል አምነን ዲያብሎስን ድል ነሥተን ስለእኛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተውን ክርስቶስን አምልከን በተዋሕዶ ሃይማኖት ጸንተን የመንግሥተ ስማያት ዜጎች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡ወለወላዲቱ ድንግል፡ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!