‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ›› ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ
በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳር ማእከል
ክፍል -፫
፭.ቅዱስ መስቀሉን ፍለጋ
ዕሌኒም ታሪኳን ለውጦ ሕይወቷን አስተካክሎ ለዚህ ክብር እንድትበቃ ኅዘኗን እንድትረሳ ያደረጋትን እግዚአብሔርን እያስታወሰች አይሁድ በምቀኝነት የቀበሩትን ክርስቶስ የተሰቀለበት ገነት የተከፈተበትን ዓለም የዳነበትን ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት ጉድጓድ ለማውጣት አሰበች ልጇ ቆስጠንጢኖስንም ወደ ኢየሩሳሌም ሂጄ የጌታዬን መስቀል ማውጣት እፈልጋለሁና ሠራተኛ ስጠኝ አለችው፡፡ እርሱም ብዙ ሠራዊት ሰጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ላካት፡፡ከእርሷም ጋር የተላኩት ሠራዊት ብዛት ሠላሳ ሺህ ታንከኞች፣ሠላሳ ሺህ ፈረሰኞች ሠላሳ ሺህ ብረት ለበሶች፣ሠላሳ ሺህ፣ሰይፍና ጦር የያዙ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ይህን ድርሳነ መስቀል እንዲህ ሲል ይገልጠዋል ‹‹ወለ ባዕዳንሰ ሠራዊት አልቦሙ ኁልቊ ከመ ከዋከዋክብተ ሰማይ ወከመ ኆፃ ዘንድጋገ ባሕር ብዝኆሙ፤ሌሎች ሠራዊት ብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ባሕር አሽዋ ነው››ይላል (ድርሳነ መስቀል ፲፮÷፱)
ብቻዋን ባሕር ውስጥ ተጥላ የነበረች ሴት በሠራዊት ታጅባ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ እርሷም ኢየሩሳሌም እንደ ገባች ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን በፈጸመባቸው ቅዱሳት መካናት እየዞረች ጾም ጸሎት ምሕላ ያዘች፡፡
፮.ቅድስት ዕሌኒ ሱባኤ የገባችባቸው ቦታዎች
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አርአያና ምሳሌ ሊሆነን ከቦታዎች ሁሉ መርጦ አምላካዊ ሥራ የሠራባቸው ድንቅ የሆኑ ቦታዎች አሉ፡፡ አምላካችን ቅዱስ ስለሆነ እርሱ የተናገረው እርሱ የረገጣቸው ቦታዎች ሁሉ ቅድስናን የተመሉ በመሆናቸው በእነዚህ ቦታዎች ሱባኤ መያዝ ደግሞ የተሠወረው እንደሚገለጽለት ቅድስት ዕሌኒ ስለምታውቅ ሱባኤ ይዛለች፡፡ እነዚህም ቦታወችም የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩. ክርስቶስ በተወለደበት ቅድስት ቤተ ልሔም ሰባት ቀን፤
፪. ክርስቶስ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ቀን፤
፫. ክርስቶስ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት በጾመበት በገዳመ ቆሮንቶ ሰባት ቀን፤
፬. ጌታ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት በደብረ ታቦር ተራራ ሰባት ቀን፤
፭. ጌታ ዓለሙን ለማዳን በተሰቀለበትና መከራ በተቀበለበት ቀራንዮ ሰባት ቀን፤
፮. የአምላክ እናት ድንግል ማርያም በተቀበረችባት በጌቴሴማኒ ሰባት ቀን እና
፯. አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበረባት በጎልጎታ ዐሥራ አራት ቀን ነው፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከጾመችና ከጸለየች በኋላ ጎልጎታ ላይ ሕዝበ አይሁድን ሰብስባ ድንኳን አስተክላ ጉባኤ አደረገች የጌታዬ መስቀል የተቀበረበትን አሳዩኝ አለቻቸው፡፡ እነርሱ ግን ተማምለው ስለነበረ ለማሳየት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲሰቅሉት ሲያዳፉት ጲላጦስ “ንጹሕ አነ እምደሙ ለዝ ብእሲ” ባለጊዜ አይሁድ “ደሙ ይኩን ላዕሌነ ወላዕለ ውሉድነ” ብለው ወስነው ነበርና አሁንም መስቀሉን ሲቀብሩት ይህንኑ ውሳኔ አጽድቀው ስለነበር ለማሳየት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡
ንግሥት ዕሌኒም ማስተማሪያ ይሆኑ ዘንድ መርጣ የተወሰኑትን ቀጣቻቸው፡፡ ሌሎችምንም ተመልሳ አባቶቻችሁ የጌታዬን መስቀል የት ላይ ነው የቀበሩት ንገሩኝ ብላ አጥብቃ ጠየቀቻቸው አይሁድ ግን‹‹ አባቶቻችን መስቀሉን አልቀበሩም እኛም የተቀበረ መስቀል አናውቅም›› በማለት መለሱላት፡፡ እርሷም ክፋታቸውን አይታ በርኀብና በውኃ ጥም ቀጣቻቸው አሁንም እንቢ ሲሏት ከእህል ከውሃ ተከልክላ ሱባኤ ገባች የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ የከበረ ሰላምታ አቀረበላት፡፡
እርሱንም የመስቀሉን ምሥጢር እያደነቀች አይሁድ ከምን ቦታ እንደቀበሩት ንገረኝ አለችው መልአኩም ‹‹የመስቀሉ ነገር በእኛ በመላእክት ዘንድ ጭንቅ ነው አልተገለጸልንም ሥልጣን የተሰጠው ለአንች ብቻ ነው ነገር ግን ኪራኮስና አሚኖስ የሚባሉ ሽማግሌዎች ታገኛለሽ እነርሱን ጠይቂ እነርሱ ይነግሩሻል›› ብሏት ተሠወረ፡፡ እርሷም ወደ ኪራኮስና አሚኖስ ሂዳ ‹‹መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አሳዩኝ›› በማለት ጠየቀቻችው፡፡ ይህንም ሊቁ በዜማ ድርሰቱ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል ‹‹ትቤሎሙ ዕሌኒ ለኪራኮስ ወለአሚኖስ ንግሩኒ ኀበ ሀሎ መስቀሉ ለወልድ ዋሕድ ኀሠሠት ወተረክበ ዕፀ መስቀል ኅበ ደፈኑ አይሁድ መስቀሎ በቀራንዮ ዘስሙ መካን፤ ዕሌኒ ኪራኮስና አሚኖስ የወልድ ዋሕድ መስቀሉ ያለበትን ንገሩኝ አለቻቸው ስሙ ቀራንዮ በሚባል ቦታ የተሰቀለበትን መስቀል አይሁድ የቀበሩበትን ፈለገች›› በማለት ይገልጻል፤(ድጓ ዘመስቀል)
አረጋዊው ኪራኮስ የቅድስት ዕሌኒን መቸገር አይቶ ‹‹አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም በከንቱ አታድክሚ እንጨት ሰብስበሽ ከምረሽ ዕጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዥው የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሸ በዚህም ምልክት አስቆፍሪው ታገኝዋለሽ›› አላት እርሷም ጸሎቷን ወደ እግዚአብሔር ካቀረበች በኋላ አረጋዊ ኪራኮስ እንዳላት ደመራ አስደምራ ዕጣኑን ጨምራ ደመራውን ብታቀጣጥለው የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ላይ ጢሱ ሰገደ፡፡ይህም በእጅ ጠቅሶ እንደ ማሳየት ያለ ነው፡፡ ሊቁ በዜማ ድርሰቱ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል ‹‹አረጋዊ አንገሃ ገይሰ ብእሲ ዘስሙ ኪራኮስ ዘዕጣን አንጸረ ሰገደ ጢስ በጎልጎታ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል፤ ስሙ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ ማልዶ ገሠገሠ የዕጣኑ ጢስ ሰግዶ አይሁድ በጎልጎታ የደፈኑበትን አመለከተ ዛሬ ዕፀ መስቀል ተገኘ›› በማለት ሊቁ እንደ ሻማ ጠቅልሎ እንደወርቅ አንከብሎ ገልጾታል፡፡
፯.ዕፀ መስቀሉ ተገኘ
ቅድስት ዕሌኒም ጢሱ ሰግዶ ካረፈበት ቦታ ላይ መስቀሉ እንዳለ በማመን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ማስቆፈር ጀመረች፡፡ ብዙ ጥራጊዎችንና ድንጋዮችን ሲያነሡ ጥጦስና ዳክርስ ተሰቅለውባቸው የነበሩ መስቀሎች በቀደም ተከተል ተገኙ፡፡ ቅድስት ዕሌኒም ይህ የጌታዬ መስቀል አይደለም ቁፋሮው ይቀጥል አለች፡፡ ቁፋሮውንም ቀጠሉ ብዙ ከቆፈሩ በኋላ ድንጋይ አገኙ ድንጋዩን ሲያነሡት ተቀብሮበት የነበረው ጉድጓድ ብርሃን ተመላ ሲቆፍሩ የነበሩ ሰዎች ሊነኩት አልቻሉም እየተውት ሄዱ ካህናት አብረው ስለነበሩ እነርሱ እንዲያወጡት አዘዘች ካህናቱ ሲያወጡት፡፡ ቅድስት ዕሌኒም ‹‹የጌታዬ መስቀል እሄዋ›› አለች እኛም እርሷን አብነት አድርገን ‹‹እዮሐ›› እንላልን፡፡ በኢየሩሳሌም በሙሉ አበራ ጨለማ ጠፋ ቀንና ሌሊት የማይለያይ ሆነ፡፡ ቅድስት ዕሌኒም ምኞቷን የፈጸመላትን እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ ለቅዱስ መስቀሉም የጸጋ ስግደት ሰግዳ ተሳለመችው፡፡
በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ከታናሽ እስከ ታላቅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እየመጡ ተሳለሙት አክብረውም ሰገዱለት፡፡ ሕሙማንም ተፈወሱ ዕውራን ዐይናቸው በራ ቅድስት ዕሌኒም እግዚአብሔር ያደረገላትን ቸርነት እያደ ነቀች ለልጇ ለቆስጠንጢኖስ መልእክተኞችን ላከ የመስቀሉን መገኘት እንዲነግሩት አደረገች፡፡ እርሱም ደስ አለው ወደ መስቀሉ ሄደ ሕዝቡም በዝማሬ በዕልልታ ተቀበሉት እርሱም መስቀሉን አክብሮ የጸጋ ስግደት ሰገደለት ተሳለመው፡፡ በመስቀሉ የተደረጉ ገቢረ ተአምራቶችን ተረኩለት ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጦ ወደሀገሩ ተመለሰ፡፡ በቅድስት ዕሌኒ አማካኝነት ተሠርቶ መስከረም ፲፮ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ ወደጎልጎታ እንደገባ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
እኛም እንላለን እናታችን ዕሌኒ ሆይ በፈተና በማዕበልና በሞገድ ውስጥ ሁነሽ፣ በቤተ መንግሥትም የንጉሥ ሚስት፣ የንጉሥ እናትና ንግሥት ሁነሽ የዚህ ዓለም ድሎትና ምቾት ከመስቀሉ ፍቅር ያልየሽ እንዴት የመስቀሉ ኃይል የክርስቶስ ፍቅር ቢገባሽ ነው? ያስተማረሽ መምህር እንዴት አድርጎ በመልካሙ የልቡናሽ እርሻ ላይ የወንጌሉን ዘር ቢዘራው ነው? የማያልፈውን በጎ ዕድል እንድትመርጭ አድርጎሻልና፡፡
በሰንበት ትምህርት ቤቶች በጽዋ ማኅበራት በግቢ ጉባኤያት ብዙ እኅቶቻችን ይማራሉ ይዘምራሉ ከእዚህ ውስጥ እንደ አንቺ ያሉ እኅቶችን አስነሽልን ምዕራባውያን በፍቅር ላይ ጥላቻን በቅድስና ላይ ርኵሰትን በአንድነት ላይ መለያየትን በትሕትና ላይ ትዕቢትን በጸና እምነት ላይ የጥርጣሬ ቆሻሻን ከምረውብናልና ከተቀበረበት ቆፍረው እንዲያወጡልን ፍቅር፣ ትሕትና፣ አንድነት፣በጎነት ቅድስና፣ ፍጹም መንፈሳዊነት ከተቀበሩበት ይውጡና እንደ ቅዱስ መስቀሉ ብርሃናቸውን ለዓለሙ ሁሉ እንዲለግሡ ወደ በቅድስት ሀገር እናቶቻችን እኅቶቻችን እንድታስነሽልን ነይ በረድኤት እንልሻለን፡፡
…………….. ይቆየን !
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!