“ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል?” (ዮሐ. ፫፥ ፬)
በእንዳለ ደምስስ
ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ከዓመት እስከ ዓመት ሳምንታቱን በወቅት፣ በጊዜ ከፋፍላ አገልግሎት ትፈጽማለች፡፡ በዚህም መሠረት የዐቢይ ጾም ስምንቱን ሳምንታት በቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ መሠረት ዜማውንና ምንባባቱን ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርታ ሥርዓቱን ታከናውናለች፡፡
በዚህም መሠረት የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት የአይሁድ መምህር በነበረውና ሌሊት ሌሊት በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ወንጌል ይማር በነበረው በኒቆዲሞስ ይጠራል፡፡
የአይሁድ አለቆች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ተአምራት አሳየን” እያሉ ጥያቄ ያቀርቡለት ነበር፡፡ ተአምራቱንም ድውያንን በመፈወስ፣ አንካሳውን እያቀና፣ ዲዳውን እያናገረ፣ የሥውራን ዐይን እያበራ ሲያዩት ደግሞ “ሕጋችንን ሻረ” እያሉ ይከሱት ነበር፡፡
ኒቆዲሞስ ግን የአይሁድ አለቃቸውና መምህራቸው ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላላቅ ተአምራትን ሲያደርግ ተመልክቶ እንደ አይሁድ መምህርነቱ ከመቃወም ይልቅ ከአይሁድ ተደብቆ በሌሊት ወደ እርሱ እየመጣ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ይማር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለው፡- መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና” ብሎታል፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኒቆዲሞስን ምስክርነት መሠረት አድርጎም “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” ሲል መልሶለታል፡፡ በጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ንግግር ግራ የተጋባውና ምሥጢሩ የረቀቀበት ኒቆዲሞስ ግን እንግዳ ለሆነበት አገላለጽ ምላሽ ይሰጠው ዘንድ በመሻት “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” ሲል ጠየቀ፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ቢሆንም ምሥጢር ተሰውሮበታልና በቅንነት ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጠው አላለፈም፡፡ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፣ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል ስላልኩህ አታድንቅ” በማለት ለጥያቄው መልስ ሰጥቶታል፡፡
ኒቆዲሞስም ምንም እንኳን የኦሪት መምህር ቢሆንም ይበልጥ የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልስ እጅግ ረቀቀበት፡፡ አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምሥጢር ከአምላኩ ጠይቆ ለመረዳት ወደ ኋላ ባለማለትም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ለአእምሮው የረቀቀበትን ምሥጢር ገልጾ ያስረዳው ዘንድ መልሶ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ ነገር ግን እንዴት ይህን አታውቅም? እውነት እውነት እልሃለሁ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም፡፡ በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” በማለት አስረድቶታል፡፡
ኒቆዲሞስ አሁንም ግልጽ ይሆንለት ዘንድ በመፈለግ የተከፈለበትን ምሥጢር ይረዳ ዘንድ ከአይሁድ ተደብቆ በሌሊት ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመገስገስ የቃሉን ትምህርት በመማር ተጋ፡፡
ኒቆዲሞስ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ ሌሊቱን ለምን መረጠ? ብለን ስንጠይቅ ስለ ተለያዩ ምክንያቶች ሌሊቱን መርጧል፡፡ እነርሱም፡-
ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህራቸው ስለነበር፤ መምህር ሲሆን ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ እግር ሥር በቀን ቁጭ ብሎ ሲማር ቢያዩት መምህር መባሌ ይቀርብኛል ሲል ከንቱ ውዳሴን ሽቶ፤ ሌላው ኒቆዲሞስ አይሁድ እንዳያዩት ፈርቶ፤ ሦስተኛው ከቀን ይልቅ ሌሊት አእምሮ ስለሚረጋጋ፣ በሙሉ ልብ በማስተዋል መማርን ፈልጎ ነው፡፡
ሌሊት ጨለማ ነው፤ ብርሃንም የለም፡፡ ጨለማ ደግሞ የኃጢአት ምሳሌ ነው፡፡ ኒቆዲሞስም ስለ ኃጢአቱ ንስሓን ሽቶ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በሌሊት መጥቷል፡፡ እንዲሁም ሌሊት የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው፡፡ ኒቆዲሞስም የኦሪት መምህርነቱን አምኖ ወንጌልን ከአንተ እማር ዘንድ ይገባል ሲል ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በሌሊት መጥቶ መማሩን ያመለክተናል፡፡
እኛም ክርስቲያኖች ከኒቆዲሞስ ሕይወት ልንማር ያስፈልገናል፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን ከአባቶችና ከመምህራን እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማር ሕይወታችንን እንድንመረምር፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ እንድንመለስ፣ ስለ በደላችንም ንስሓ እንድንገባ ስለሚያደረገን በጾም በጸሎት ተወስነን እንደ ኒቆዲሞስ በትጋትና በቅንነት ልንመላለስ ይገባል፡፡ እንደ ቃሉ ተመላልሰን የመንግሥቱ ወራሾች ያደርገን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን ፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!