ሰሙነ ሕማማት
ክፍል ሁለት
፪. ዕለተ ሠሉስ
ሀ. የጥያቄ ቀን፡– ከሰሙነ ሕማማት ዕለታት ውስጥ ዕለተ ሠሉስ የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፤ ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ ዕለት አንጽሖተ ቤተ መቅደስን ከፈጸመ በኋላ በዚህች ዕለት ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው “በማን ሥልጣን ይህ ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ “እኔም አንዲት ቃል እጠይቃችኋለሁ፣ የነገራችሁኝ እንደሆነ እኔም በምን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ” አላቸው፡፡ ጌታችንም ጥያቄውን ይመልሱለት ዘንድ “የዮሐንስ ጥምቀቱ ከየት ነው? ከሰማይ ነውን? ወይስ ከሰው?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም እርስ በርሳቸው ተነጋግረው እንዲህ አሉ “ከሰማይ ነው ብንለው እንኪያ ለምን አላመናችሁትም? ይለናል፡፡ ከሰው ነው ብንለውም ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራቸዋለን” ተባባሉ፡፡ በመጨረሻም መልስ መስጠት ስላልቻሉ “ከወዴት እንደሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም “እንኪያስ እኔም በምን ሥልጣን ይህን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፳፯ ፤ ማር. ፲፩፥፳፯-፴፫፣ ሉቃ. ፳፥፩-፰) በዚህም ምክንያት የሰሙነ ሕማማት ማክሰኞ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡
ለ. የትምህርት ቀን፡– ይህቺ ዕለት ዕለተ ትምህርት ወይም የትምህርት ቀን በመባልም ትጠራለች፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት በማስተማር የተሰጠው ስያሜ ሲሆን ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብና መክሮ መመለስ እንደሚገባን ሲገልጽልን ነው፡፡
በዚህም ትምህርቱ ሁለት ወንድማማቾችን አባታቸው ወደ ወይን ቦታ ሄደው ይሠሩ ዘንድ እንደጠየቃቸው፤ የመጀመሪያው እምቢ ቢልም ተጸጽቶ ሊሠራ መሄዱን፤ ሁለተኛውም እሺ ብሎ ነገር ግን ቃሉን አጥፎ ሳይሄድ መቅረቱን ነገራቸው፡፡ እርሱም ትምህርቱን ከነገራቸው በኋላ አስተምሮ ብቻ አልተዋቸውም፤ ጥያቄውን አስከትሏል፡፡ “እንግዲህ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመ ማንኛው ነው?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “ፊተኛው ነዋ” አሉት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ሲል ገሠጻቸው፡- “እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ እግዚአብሔር መንግሥጥ በመግባት ይቀድሟችኋል፡፡ ዮሐንስ ወደ እናንተ በጽድቅ ጎዳና መጣ፤ አላመናችሁበትም፣ ቀራጮችና አመንዝሮች ግን አመኑበት፤ እናንተም በኋላ በእርሱ ለማምነን አይታችሁ እንኳ ንስሓ አልገባችሁም” አላቸው፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፰ ፤ ፳፭፥፵፮ ፤ ማር. ፲፪፥፪ ፤ ፲፫፥፴፯ ፤ ሉቃ. ፳፥፱ ፤ ፳፩፥፴፰)
ሌላው በዚሁ ቀን በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ስለ ወይን እና ወይኑን የተከለው ባለቤት ድካም የተመለከተ ነበር፡፡ “ሌላ ምሳሌ ስሙ፤ ባለቤት ሰው ወይንን ተከለ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጭመቂያም አስቆፈረለት፤ ግንብንም ሠራለት፤ ለገባሮችም ሰጥቷቸው ሄደ፡፡ የሚያፈራበት ወራት በደረስ ጊዜም ከወይኑ ፍሬ ያመጡለት ዘንድ አገልጋዮቹን ወደ ገባሮቹ ላከ፡፡ ገባሮቹም አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን በበትር ደበደቡት፣ አንዱንም ገደሉት፣ ሌላውንም በድንጋይ መቱት፡፡” በማለት አስረዳቸው፡፡ በዚህም በብቻ አላበቃም ሌሎችን ከዚህ በፊት ከላካቸው አገልጋዮች ቁጥር በላይ ወደ ገባሮቹ ሰደዳቸው፡፡ ነገር ግን ገባሮቹ የተላኩትን አገልጋዮች ደብድበው አባረሯቸው፡፡
ባለ ወይኑ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ ልጄን ያከብሩትና ይፈሩት ይሆናል ብሎ አንድ ልጁን ከወይኑ ያመጣለት ዘንድ ወደ ገባሮቹ ላከው፡፡ ገባሮቹም ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው “እነሆ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ ተባባሉ፡፡ ይዘውም ከወይኑ ቦታ ውጭ አውጥተው ገደሉት፡፡ እንግዲህ የወይኑ ቦታ ባለቤት በመጣ ጊዜ እነዚህ ገባሮች ምን ያደርጋቸዋል?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
የካህናት አለቆችንና የሕዝቡ ሽማግሌዎችም “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ ወይኑንም በየጊዜው ፍሬውን ለሚሰጡት ለሌሎች ገባሮች ይሰጣል” አሉት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ አላቸው”… ግንበኞች የናቁአት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነች፡፡ … ስለዚህ እላችኋለሁ፡- የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች፤ ፍሬዋንም ለሚያደርጉ ለአሕዘብ ትሰጣለች፡፡ በዚያችም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፡፡፣ በላዩ የሚወድቅበትንም ትፈጨዋለች” የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ፈሪሳውያንም ይህ ስለ እነርሱ የተነገረ መሆኑን ዐወቁ፡፡
ለሦስተኛ ጊዜም ለልጁ ሠርግ ስለ አደረገው ንጉሥ በምሳሌ አስተማራቸው፡፡ እነርሱ ግን ያስተማራቸውን ትምህርት ተረድተው ወደ ንስሓ ከመመለስ ይልቅ ጌታችን መድኃነኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስን በአነጋገሩ ያጠምዱትና ይይዙት ዘንድ ተማከሩ፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፵፭ ፤ ፳፪፥፩-፳፪)፡፡
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!