ሰሙነ ሕማማት

ሰሙነ ሕማማት ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ጀምሮ እስከ ቀዳም ስዑር ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ሳምንት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር የተገለጠበት፣ የመሥዋዕትነት ሥራ የተሠራበት፣ የሰው ልጆች ድኅነት የተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም በመስቀል ተሰቅሎ ለእኛ ቤዛ መኾኑ በስፋት የሚነገርበት ሳምንት በመሆኑ ቅዱስ ሳምንት ይባላል፡፡ እንዲሁም የመጨረሻ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ይህንን ወቅት አስመልክቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤ እኛም እንደ ታመመ እንደተገረፈም ቆጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፣ ስለበደላችንም ታመመ፤ የሰላማችን ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ በማለት የሕማማቱን ምሥጢር አስቀድሞ ተናግሮአል፡፡ በዚህም መሠረት በኋለኛው ዘመን እግዚአብሔር ወልድ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ሲል ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ በፈቃዱ ሰው ሆኖ በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀበለ፡፡ በመስቀሉም ላይ ሳለ በፈቃዱ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ በዚህም መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መስቀሉን የተቀበለበት ሳምንት ስለሆነ ሳምንቱ ሰሙነ ሕማማት ተብሏል፡፡ (ኢሳ.፶፫፥፬-፭ ፤ ማቴ. ፰፡፲፯ ፤ ዮሐ. ፩፥፳፱)

በዚህ ልዩ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠለስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆነው ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ግብረ ሕማማት መጽሐፍ እንዲሁም ከሌሎች ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይና አብዝተው በመስገድ ሕማሙንና ሞቱን ይዘክራሉ፡፡

በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፣ ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡

የሰሙነ ሕማማት ዕለታት

ሰኞ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሣዕና ማግሥት ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አንደኛ፡- ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ፡- ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፯፤ ማር. ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፭-፵፮)፡፡

ፍሬ ያልተገኘባት በለስን ረግሟል፡

በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ በማግሥቱ ተራበ የሚል ቃል እንመለከታለን፡፡ “በነጋም ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ፡፡ በመንገድም አጠገብ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትም፡፡ “ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ” አላት፤ ያን ጊዜም በለሲቱ ደረቀች፡፡ (ማቴ. ፳፩፥፲፰-፲፱) ነቢዩ ኢሳይያስም “እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም” ይላል፡፡ (ኢሳ. ፵፮፥፳፭)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልንን በምድረ በዳ መና ከሰማይ አውርዶ የመገበ፤ በመዋዕለ ሥጋዌው የሚከተሉትን ከአምስት ገበያ የሚበልጡ ሰዎችን በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ የመገበ ጌታ “ተራበ” ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ የክርስቶስ ርኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይሆን ከሰው ልጆች ዘንድ የሃይማኖት እና የመልካም ሥነ ምግባር ፍሬ ማጣቱን ለማመልከት “ተራበ”ተባለ፡፡ ከበለሲቱም ፍሬ በማጣቱ ረገማት፡፡ ይህንንም መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሰሙነ ሕማማት ሳምንት ሰኞን ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ የረገመበት ቀን መሆኑን በማሰብ ልጆቿ በሃይማኖት በምግባር ጸንተው ይኖሩ ዘንድ ታስተምራለች፡፡

 

የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ከቤተ መቅደስ አስወጥቷል፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ አይሁድ የጸሎት ቤት የሆነውን ቤተ መቅደሱ የገበያ አደባባይ አድርገውት አገኘ፡፡ እርሱም አይሁድ ያደረጉትን የማይገባ ሥራ ያስወግድ ዘንድ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ እየገረፈ አስወጣ፡፡ “በቤተ መቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም መደርደሪያ፣ የርግብ ሻጮችንም ወንበር ገለበጠ፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፣ ተብሎ ተጽፎአል እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” እንዲል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፫)፡፡ ይህም ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን ኃጢአት ሰፍኖበት ቢያገኘው ራሱ ተገርፎ፣ ተገፍፎ መከራ መስቀልንም ሁሉ ተቀብሎ ከሰውነታችን ኃጢአትን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሉቃ.፲፱፥፵፮)

ይቆየን

 

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *