መናፍቃን የሚስቱባቸውና የሚያስቱባቸው መንገዶች (ክፍል አንድ)

ዳዊት አብርሃም

ነገረ ድኅነትን (የመዳን ትምህርትን) በተሳሳተ መንገድ የሚያስቡና ስሕተት የሆነን ትምህርት ከማስተማር አልፈው ትክክል የሆነውን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚቃወሙ ወገኖች እዚህ አቋም ላይ ሊደርሡ የቻሉበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ከብዙዎቹ ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹን በመለየት ቀለል ያለውን መንገድ መርጠን ለማየት እንሞክራለን፡፡ የስሕተቶቹ መነሻ በመጠኑ ሲዳሰስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

  1. በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ መመሥረት

 

በማንኛውም የትምህርት መስክ አንድ አቋም ላይ ለመድረስ በቂ የሆነ መረጃ መያዝ እንደሚያስፈልግ የጥናትና ምርምር ሕግ ግድ ይላል፡፡ ዓለማዊ ወይም ምድራዊ ነገር ይህን ያህል ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ከሆነ ሰማያዊው የነገረ መለኮት ዕውቀት ደግሞ የቱን ያህል ጥንቃቄ፣ የቱንስ ያህል ትዕግሥት ይሻ ይሆን? በተለይ የሰው ልጆችን ዘለዓለማዊ ሕይወትና ዘለዓለማዊ ጥፋት በቀላሉና በችኮላ፣ በተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ብቻ በመመሥረት ለማወቅና እውነቱ ይህ ብቻ ነው ብሎ ለመደምደም መሞከር ከባድ ስሕተት ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡ ብዙዎቹ መናፍቃን ግን በጥቂት ጥቅሶች ላይ ከመመሥረት አልፈው በሁለትና በሦስት ጥቅሶች ላይ ብቻ ተመሥርተው ይደመድማሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በጣም በሚገርም ኹኔታ በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመሥርተው ትልቅ ነገር መለኮታዊ ግንብ ለመገንባት ይጥራሉ፤ ወይም የተገነባውን ታላቅ ግንብ ለመናድ ይሞክራሉ፡፡ አንዳንዶች አንዲትን ቃል መዘው በመያዝ መዳን በጌታ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፤ ቀጥለውም ቅዱሳን ለመዳን ምንም ሚና ሊኖራቸው አይገባም በማለት ይደመድማሉ፡፡

ሌሎች መዳን በጌታ ወይም በጌታ ስም ነው በሚል የአብንና የመንፈስ ቅዱስን አዳኝነት የሚያሳንስ እምነት ያራምዳሉ፡፡ ይህም አንድን ሐሳብ በጥንቃቄ አለመግለጥ ከራስ ጋር ለሚጋጭ ሐሳብ እንደሚዳርግ የሚያሳይ ምሳሌ ነው፡፡ ፕሮቴስታንቶች በሥላሴ እንደሚያምኑ ይገልጣሉ፡፡ ‹መዳን በጌታ› የሚል የከረረ አገላለጻቸው ግን የሥላሴ እምነታቸውን ችላ ያሉና የአብንና የመንፈስ ቅዱስን የማዳን ሚና የዘነጉ ያደርጋቸዋል፡፡ አንዳንዶች ስለ ጌታ የማዳን ሥራ የተነገሩ ጥቅሶች ላይ ብቻ በመጣበቅ ለመዳን ከሰው ምንም አይጠበቅም፤ መዳን እንዲያው ያለ ሰው ጥረትና ድርሻ በነጻ፣ በጸጋው የሚገኝ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ለመዳን ማመን ብቻ በቂ ነው ይላሉ፡፡

አሁንም ሌሎች ሰዎች ሕግጋትን ስለመጠበቅና ከኃጢአት ስለመራቅ የሚያስተምሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመሰንዘር ሰው የሚድነው በመልካም ሥራው ራሱን ከኃጢአት በመጠበቅ ችሎታው ነው በማለት የክርስቶስን የማዳን ሥራ ከንቱ ያደርጋሉ፡፡ (“መዳን በጸጋው ብቻ” የሚለው የፕሮቴስታንት አንድ አስተምህሮ በዋናነት የጆን ካልቪንን ፈለግ የሚከተሉት የሚያንጸባርቁት ሲሆን አስተምህሮውም በሰውየው ስም ካልቪንያን ቴኦሎጂ ይባላል፡፡ ይህን አሳብ የሚቀናቀን የፕሮቴስታንት አስተምህሮ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ያለውን ጽንፍ በመያዝ መዳን በሰው ልጅ ነጻ ፍቃድና ሥራ የሚገኝ መሆኑን ይገልጣል፡፡ የዚህ አስተምህሮ መስራች አረሚንየስ (Jacobus Armenius, 1560-1909) የተባለ ሲሆን ፈለጉን የሚከተሉትም አርሜንያን ይባላሉ፡፡) ይህን ሐሳብ ከሚያራምዱ ወገኖች መካከል በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ፔላግዮስ የሚጠቀስ ሲሆን ምንም እንኳ ይህ ሰው በውግዘት የተለየና ትምህርቱም የተተወ ቢመስልም በአንዳንዶች ዘንድ አሁንም የሚታይ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ የተለያየ ሐሳብን የሚያራምዱ ወገኖች አንድ የሚያመሳስላቸው ነጥብ፣ ሁሉም አቋማቸው ወይም ድምዳሜያቸው የተለያየ ቢሆንም አንድ ሙጥኝ ያሉበት ጥቅስ መኖሩና ሁልጊዜም ያን ጥቅስ ካልጠቀሱ ሌላ የማስረጃ አማራጭ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ በአንድ ጥቅስ መመርኮዝ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ አይደለም፡፡ በዚህ መልክ ድምዳሜ ላይ መድረስም ኦርቶዶክሳዊ መንገድ አይደለም፡፡

አንድ ጥቅስ አንሥቶ የሆነ ሐሳብ መሰንዘር የሚፈልግ ሰው ቢያጋጥም ጥቅሱ የቱንም ያህል ግልጽ መልእክት ያለው ቢሆን እንኳ እንዲህ ለማለት ነው ተብሎ ለመደምደም አያስችልም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሰውም በተነሣው ርእሰ ጉዳይ ላይ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን እንደሚሉ ለማወቅ ይጥራል፡፡ አሳቡን የተሟላ የሚያደርጉት በጉዳዩ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጡት ሌሎች ጥቅሶች ተሟልተው ሲቀርቡ ነው፡፡ ሌሎች ጥቅሶች አንዱን ጥቅስ ግልጽና የማያሻማ እንዲሁም የተሟላ ያደርጉታል፡፡

ይህን በምሳሌ እንመልከት፡፡ “ነገር ግን ለማይሠራ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል” (ሮሜ. 4፡5) በዚህ ጥቅስ መሠረት ላይ ሆነን ሌሎቹን ሳንዳስስ ወይም ጥቅሱን በምልዓት ለመረዳት ሳንሞክር አንድ ሰው ኃጢአተኛ ሆኖ ሳለ፣ ኃጢአት መሥራቱንም ሳያቆም ወይም ንስሐ ሳይገባ ይጸድቃል ብለን መደምደም እንችላለን? ይህን ጥቅስ በትክክል ለመረዳት ጥቅሱን ግልጽ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ጥቅሶችን በማምጣት ከዚህ ጥቅስ ጎን ለጎን በማድረግ ማጥናት ይኖርብናል፡፡ (ይህንና መሰል ኀይለ ቃላት አጠቃላዩን መጽሐፍ ስናነብ የምንረዳው ቢሆንም እዚህ ላይ ጥቂት ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ጥቅሱ ኃጢአተኛ ሰው ኃጢአት ማድረጉን ሳይተው እምነት ስላለው ብቻ ይድናል የሚል እንዳልሆነ ዝቅ ብለን ስናነብ የምናገኘው ነው፡፡ ሆኖም በሥራው እንደተመጻደቀው ፈሪሳዊ የሚመካ ሳይሆን ኀጢአቱን አውቆ ምሕረትን እንደለመነው ቀራጭ የመዳኑ ተስፋ በአምላኩ እንደሆነ ለሚያምን እንደሆነ የሚያስረዳ ቃል ነው) ለምሳሌ ብዙም ሳንርቅ ከዚያው ከሮሜ መልእክት ሌሎች ጥቅሶችን እንመልከት፡፡ “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፡፡” (ሮሜ.1፡18) “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።” (ሮሜ.2፡5)

ቀጥለን ደግሞ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን መልእክት እንመልከት፡፡ “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።” (2ኛጴጥ.2፡6) ሐዋርያው ይሁዳም ከኃጢአት አለመራቅና የጽድቅ ሥራን አለመሥራት መዳንን እንደሚያሳጣ በመግለጽ ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው መልእክቱን እንደሚከተለው አስቀምጧል፡፡ “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ እነሆ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።” (ይሁዳ ቊ.14-15)

እነዚህን የመሳሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከተመለከትን በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንዲት ቦታ ላይ የጻፋትን አንዲት ጥቅስ ብቻ መዝዘን በመውሰድ ኃጢአትን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ ወደሚል ስሕተት ከመውደቅ እንጠበቃለን፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል አስተምሯልና፡፡ “ወይስ ዐመጸኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብ የሚመኙ ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡” (1ኛቆሮ.6፡9-10)

2 replies
  1. Marew Gedilu
    Marew Gedilu says:

    እግዚአብሔር ያክብራችሁ ፀጋውን ያብዛላችሁ:በርቱ ጠንክሩ የቅዱሳን ልጆች::በእውነት በጣም ደስ ይላል ደግሞ የበለጠ አማረኛ ማንብብ ለማይችሉ ምራባውያኑም እዲማሩበት በእግሊዘኛ ጭምር ተተርጉም ቢለጠፍ አገልግሎቱ ይሰፋል::

    Reply
    • Gibi Gubayeat
      Gibi Gubayeat says:

      እግዚአብሔር ይስጥልን፤ በቅርቡ በእንግሊዘኛ እንጀምራለን። ሐሳብ አስተያየተዎ አይለየን።

      Reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *