መስቀል የበረከት ዐውድ
ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ /፻፲-፻፲፭/ በነበረው ጊዜ ሰማዕትነትን ሊቀበል ሲወስዱት የሚከተለውን የኑዛዜ ቃል ተናገረ፡- “ከሶሪያ እስከ ሮም ድረስ ከአውሬዎች ጋር በባሕርና በየብስ እየተዋጋሁ እስከዚህች ሰዓት ደርሻለሁ፤ ቀንና ሌሊት በዐሥር አናብስት እጠበቅ ነበር” ብሏል፡፡ ይህ ቃል የወታደሮቹን የሚያስጨንቅ አያያዛቸውን፣ ክፋታቸውንና ጭካኔያቸውን የሚያሳይ ነበር፡፡
በመቀጠልም እንዲህ አለ፡- “እነርሱ አላስፈላጊ የሆነ መከራን ባጸኑብኝ መጠን እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ምን ማለት እንደሆነ ተምሬያለሁ፡፡ እንዲያውም መከራ ሲጨምሩብኝ የምቀበለውን የሕይወት አክሊል እያሰብሁ በርኅራኄ ሳይሆን በፍርሐት በእኔ ላይ የሚያጸኑትን መከራ እንዳይቀንሱ አሳስባቸው ነበር፡፡ እነርሱ ይኽንን ነገር በእኔ ላይ እንዲፈጽሙ ሰውነቴን ለመከራ አሳልፌ ሰጠሁ፡፡ ለእኔ የሚጠቅመኝ ምን እንደሆነ አውቄያለሁ፡፡ አሁን ደቀ መዝሙር መሆን ጀምሬያለሁ፡፡ ከዚህም በላይ የሚታይና የማይታይ መከራን ያድርሱብኝ፣ በእኔ ላይ እሳትን ያምጡ፣ መስቀሉንም ያቁሙ፣ ለአውሬዎችም ይስጡኝ፣ አጥንቴንም ይሰባብሩት፣ ከንፈሬንም ይቁረጡት፣ ሰውነቴንም በሙሉ እንዳልበረ ያድረጉት፡፡ ነገር ግን ወደ ፈጣሪዬ ክርስቶስ የማደርገውን የእምነትና የነፃነት ጉዞ ሊያስተጓጉሉ አይቻላቸውም” ብሏል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም “ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ፡፡ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጉዳይ ግን እንደሚገባ ሁኖ መከራን አይቀበል፣ ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን፡፡ /፩ጴጥ.፬.፲፫-፲፭/ የሚለውን ቃል የክርስትና ጉዞ የመስቀል ጉዞ መሆኑን ያስረዳል፡፡
የልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በቀራንዮ የተተከለውን፣ በጎልጎታ የተቀበረውን፣ በተአምራት የወጣውን የጌታችን መስቀል ስታስብ እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር ገመድ እየተጎተተ ከሊቶስጥራ ዐደባባይ እስከ ቀራንዮ ሲጓዝ በእምነት ትመለከታለች፡፡ የሕይወትና የክብር መገኛ አምላክ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ በክብር መንገሡን ትመለከታለች፡፡ የፍቅር ትርጉሙ ለሚገባቸው ሁሉ የቸርነት ተግባሩን ትናገራለች፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን የፍቅር ፍላጻው በልቡናው ውስጥ ሥር በሰደደ መጠን ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ ወዴት አለ? ሞት ሆይ መውጊያህ ወዴት አለ? እያለች የፍቅር ዜማን እያዜመች ምርኮን ሲበዘብዝ፣ ሲኦል ሲመዘበር እየተመለከተች /ኤፌ.፬.፰/ ከምድር እስከ ሰማይ በመስቀል ላይ ለነገሠው ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ጉልበት ሁሉ ሲንበረከክ ትመለከታለች፡፡ /ፊል.2.፲/፡፡
በቀደመ ርግማን ምክንያት “እሾህና አሜኬላ ያብቅልብሽ” ተብላ የተረገመች ምድር፣ በክብረ መስቀሉ ይህ የመከራ አረም ተወግዶ አዲስ የሆነ የድኅነት ተክል የተዘራባት ምድር ሆነች፡፡ ይህም ተክል ንጹሕ የሆነ የቅድስና ሕይወትን አስገኘ፡፡ እርሱም ክርስቶስ በቀራንዮ ዐደባባይ የነገሠበት የክብር ዙፋኑ ዕፀ መስቀሉ ነው፡፡
በመስቀሉ ፍጥረት ሁሉ አዲስ ሆነ፣ በመስቀሉ ሞትና ኃጢአት በመስቀሉ ሞትና ኃጢአት ተዘርቶበት የነበረው ዓለም በምትኩ ጽድቅና ሕይወት የተዘራበት ዓለም ሆነ፡፡ ጠቢቡ በምስጋናው እንዲህ አለ፡- “እነሆ ክረምትም አለፈ፣ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቁርዬው ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ፣ ወይኖች አበቡ፣ መዓዛቸውንም ሰጡ” /መኃ.2.፲፩/ እንዲል፡፡
ይኽም ማለት ቀዝቃዛው የሞት ዘመን በክርስቶስ ቤዛነት አለፈ፣ በአዲስ ሕይወት ታደሰ፣ እርሱ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ እንዳለ ፍጥረትን አዲስ አደረገ፡፡ ይኽም በመስቀል ላይ ባደረገው ቤዛነት ነው፡፡ በሥጋ ሞትን የቀመሰ በትንሣኤው አበባ ምድርን አስጌጠ፣ ፍጥረትን አዲስ አደረገ፡፡ ሙታን አዲስ ሕይወትን ለበሱ፡፡ አበቦች ስለ ጎመሩ፣ ዛፉም መልካም ፍሬን ስለሰጠ ምድረ በዳውም ልምላሜ ጽድቅን ስለለበሰ፣ ፍጥረት ሁሉ ደስ ይለዋል፡፡
ሙሽራዪቱ ቤተ ክርስቲያን ለሙሽራው መድኃኔዓለም ክርስቶስ ክብር የተዘጋጀች ሁና ልትቀመጥ ይገባታል፡፡ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ እድፍና የፊት መጨማደድ ሳይኖርባት ለሙሽራው የተገባች ሁና ያገኛት ዘንድ በጽድቅ ለሚፈርደው በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ የተሸከመውን እርሱን /፩ጴጥ.2.፳፬/ ከፍ ከፍ ታደርገው ዘንድ፡፡
ዘወትር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚፈተተው በቀራንዮ ዐደባባይ በዕለተ ዐርብ በመስቀሉ ላይ የተዘጋጀው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡ መስቀሉም በክርስቶስ ደም የታጠበ ነው፡፡ የክርስቶስ መስቀል መከራ በዓይነ ሕሊናችን ላይ በሚሣልበት ጊዜ ሁሉ መከራ የተቀበለበት መስቀልም በዓይነ ልቡናችን ዘወትር ይመላለሳል፡፡ እንደገናም ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ወገኖች በመስቀሉ ላይ የተፈተተውን ምግበ ሕይወት በመመገብ ነፍሳቸውን ያነጻሉ፡፡ ሞኞችና ማስተዋል የሌላቸው ወገኖች ዕለት ዕለት የሚፈተተውን ይህንን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደም መታሰቢያ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ጥበበኞችና ለድኅነት የተመረጡ ወገኖች ግን ይህ ቃል ከጦር ይልቅ የሚያስፈራ እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ይህ ቃል በተነገረበት ቦታ ሁሉ የሚታሰባቸው ለሰይጣንና ለመልእከተኞቹ ወደተዘጋጀ ወደዘለዓለማዊ እሳት ሂዱ የሚለውን አስፈሪ የፍርድ ቃል ነው /ማቴ.፳፬.#1/፡፡ በእርግጥ ከባድና አስፈሪ ቃል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መከራ በምትናገርበት ጊዜ ሁሉ ይኽንን የመጨረሻ የአዋጅ ቃል ታስተጋባለች፡፡
በመስቀል የተፈተነ ክርስትና
ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ የሰው ልጆች ክርስቲያን የሆኑበትን ምሥጢር ሲያስረዳ እንዲህ አለ፡- “ጌታችን በመስቀል ላይ መስቀሉን እያሰቡ፣ ልባቸውን መስቀሉ የተቀበረበትን የጎልጎታ መቃብር አድርገው በፍጹም ፍቅሩ እንዲመላለሱ ነው፡፡ ከመስቀሉ ፍቅር ይልቅ የዚህ ዓለም ፍቅሩ ያየለባቸው ወገኖች ግን በኃጢአተኞች አኗኗር ልባቸው ስለቀና የእውነትን መንገድ ተቃዋሚና እንደ በሽተኞች መዋጋትን የሚናፍቁ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የመስቀሉ ጠላት ሆነው ተነስተዋል፡፡ ይኽንንም ተቃውሞአቸውን የሚገልጹት፣ የማያምኑ መስለው ሳይሆን የሚያምኑ መስለው ስሕተታቸውን ይደግፍልናል የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተቀመጠበት ዓውድ በመለየት ለእነርሱ በሚመቻቸውና በሚፈልጉት ቦታ ላይ በማስቀመጥ ነው” ይላል፡፡
ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች በበለጠ ይወደው ዘንድ የሚከተሉት ነገሮች በእርሱ ዘንድ አሉ፡፡ የሚያምን ሰው ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራን በመቀበሉ ፍላጎቱ፣ ተስፋው፣ እምነቱ ሁሉ እንደተፈጸመ በእምነት ያውቃል/ኤፌ.፫.፲9/፡፡ የተፈቀሩ ሰዎች ግን የተፈቀሩበትን የፍቅር መጠንና ያፈቀራቸውን ማንነት፣ ስለ ፍቅራቸውም የተከፈለውን ዋጋ በትክክል የተረዱ አይመስልም፡፡ /ሉቃ.፯፤፯/፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ምን እንደተደረገላት በሚገባ ተገንዝባለችና “ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፣ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ወዴት ትመሰጋለህ? ትላለች”/መኃ.1.7/////////፡፡ መንጋዎቿንም በዕረፍት ውኃ በለመለመ መስክ ታሰማራለች፡፡ እረኛዋም የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡
በአጠቃላላይ ያለ ክብረ መስቀል ክርስትና፣ ያለ ክርስትናም ክብረ መስቀል አይኖሩም፡፡ አበው ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ዳገቱን የወጡበት፣ እሳቱን፣ ስለቱን ያለፉበት፣ መከራውን የታገሱበት፣ ተልእኮአቸውን የተወጡበት ዕፀ መስቀሉን ተመርኩዘው ነው፡፡ በመስቀሉ የተፈተኑ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የበረከት ዐውድ የሆነውን የመስቀሉን በዓል በሥርዓተ እምነታቸው መሠረት ማክበር ይገባቸዋል፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ መስከረም ፲፮-፴ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!