ልደተ ክርስቶስ
መ/ር በትረ ማርያም አበባው
የሰው ልጅ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በልቶ በራሱ ላይ ሞትን ዐወጀ ከእግዚአብሔር ተለየ (ዘፍ. ፪፣፲፯) ቸርነት የባሕርየ የሆነ እግዚአብሔር ግን ሰውን ሞቶ እንዲቀር አላደረገውም። በከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ሰጠው። እግዚአብሔር ይህንን ቃል ኪዳን በየዘመኑ ለተነሡ ሰዎች በተለያዩ ነቢያት አስነገረ።
“ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ እምርላሃለሁ፣ይቅርታም አድርግልሃለሁ “(ቀሌም.፫፥፲፱፣ኢሳ.: ኢሳ.፱፣፮) እንዲል ጊዜው በደረሰ ጊዜም ከሦስቱ አካላት እግዚአብሔር አንዱ ወልድ ከድንግል ማርያም ተወለደ። “ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ” እንዲል (ማቴ. ፩፣፳፩-፳፫፣ሉቃ. ፪፣፮-፯፣ዮሐ. ፩፣፲፬ ፣ገላ. ፬፣፮)
ጌታችን ሁለቱ ልደታት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት።እኒህም ቀዳማዊ ልደትና ደኃራዊ ልደት ይባላሉ።
ቀዳማዊ ልደት
አብ ወልድን በዘመን ሳይበልጠው የወልድ ቃልነት የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሳይለየው ወልድን ወለደው መንፈስ ቅዱስን አሠረፀው እንላለን። ይህም ከኅሊና በላይ የሆነ በሰውና በመላእክት አእምሮ ሊመረመር የማይችል ነው። “ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድኩህ” (መዝ. ፻፱፣፫) እንዲል። ስለዚህም የአብ ግብሩ ወላዲ ይባላል። የወልድ ግብሩም ደግሞ ተወላዲ ይባላል። በቀዳማዊ ልደቱ እናት የለውም። ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ “ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት” ብሎ የገለጸው ይህንን ነው። በዚህኛው ልደት ተመትሮ የለበትም። ይህም ማለት አብ ወልድን ሲወልደው ወልድ ከአብ አልተለየም። ዘኢየኀልቅ ልደቱ ያሰኘው ይህ ነው። ወልድ ወልድ ሲባል ይኖራልና።
ደኃራዊ ልደት
ደኃራዊነቱ ለቀዳማዊው ልደት ነው። በኋለኛው ዘመን አዳምን ለማዳን ያለ አባት ከድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ነው። ይህ ልደት ያለ ወንድ ዘር፣ያለ ሩካቤ ከድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ነው። በክርስቶስ ልደት የሰው ልጆች ተስፋ ተፈጸመ። ስለዚህም እረኞች ከመላእክት ጋር የደስታ ምስጋናን አመሰገኑ። “ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር። ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ” (ሉቃ. ፪፣፲፫-፲፬ ) እንዲል ለምድር ሰላም ተሰበከላት። ሰላሟ ክርስቶስ መጣ። እሾህ አሜኬላ ይብቀልብህ ፍትወታት እኩያት ይሰልጥኑብህ የተባለ ሰው በክርስቶስ ልደት ግን “በጎ ፈቃድ ሆነለት” ። ድንግል ፈጣሪዋን በሥጋ ወለደችው። (ሃይ. አበ. ፵፯፣፪-፬)
እንዴት ሰው ሆነ
እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሲሆን እግዚአብሔርነቱን ሳይለቅ ያለ መለወጥ ነው። እግዚአብሔር የሚለዋወጥ አምላክ አይደለምና። ሰውም አምላክ ሲሆን ሰውነቱን ለውጦ አይደለም። ሰው አምላክ ሆነ እያልን ስንናገር ስለክርስቶስ ሰውነት እየተናገርን መሆኑን ማስተዋል ይገባል። አምላክ ሰው ሆነ ስንልም በተለየ አካሉ ስለ አካላዊ ቃል ወልድ እየተናገርን መሆኑን መረዳት ይገባል።
አብ እና መንፈስቅዱስ ሰው አልሆኑምና። ከዊነ ልብ እና ከዊነ እስትንፋስ ሰው አልሆኑምና። ቃል ሥጋ ሲሆን ሥጋም ቃልን ሆነ። የቃል ገንዘብ የሆነው ሁሉ ለሥጋ ሆነ። የሥጋ ገንዘብ የሆነው ሁሉ የቃል ሆነ። ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው። “እንቲኣሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲኣሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል”። የኢየሱስ ክርስቶስን ልዕልናውን በትሕትናው አወቅን። ስለዚህ ያለ መለወጥ፣ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለየት በተዋሕዶ በተዐቅቦ ሰው ሆነ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!