ልብሳችሁን እጠቡ
በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
ልብስ የሚለውን ቃል በቀጥታ ስንመለከተው አካል የሚሸፈንበት እርቃንን የሚሸፍን፣ ከሌሊት ቁር ከቀን ሐሩር የሚከላከል ሲሆን የሰውነት ክፍልን ከመሸፈንም አልፎ ግርማ ሞገስንና ውበትን ያላብሳል፡፡ ይህም እንደየ ሀገሩ የአለባበሱ ሥርዓት ሊለያይ ይችላል፡፡ ያም ቢሆን ግን የወንድ ልብስ እና የሴት ተብሎ ይለያል፡፡ አሁን ላይ በአንዳንዶች የምንመለከተው የአለባበስ ሥርዓት ግን ወግን ባሕልን፣ ዕሤትን፣ ሃይማኖትን ማእከል ያደረገ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ክፍል እየተሰነካከለበት ያለው አንዱ የአለባበስን ሥርዓት በማይጠብቁና ለውድቀት የሚጋብዙ የአካል መራቆቶችን በዓይኑ አይቶ በልቡ እንዲመኝ እናም እንዲያመነዝር የሚያደርጉ፣ ባሕልንና ዕሤትንም ያልጠበቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ማጠብ መታጠብ የሚለውን ቀጥታ ትርጉሙን ስንመለከት ዕድፍን፣ ቆሻሻን ማስወገድ፣ የቆሸሸን ነገር ማንጻት የሚያመለክት ሲሆን፣ ልብስ የሚለውን ቃል በሌላው ፍቺ ስንመለከት ደግሞ በሕይወታችን ወይም በማንነታችን የሚገለጠውን ውሳጣዊ እና አፍኣዊ ሥራችን ነው፡፡ ከዚሁ ተያይዞ ማጠብ መታጠብ የሚለውም በንስሓ መንጻት፣ መቀደስ፣ በደልን፣ ኃጢአትን መተው፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስን ያሳያል፡፡
አባታችን ያዕቆብ “ልብሳችሁን እጠቡ” በማለት ለጊዜው የተናገረው በሥጋ ለወለዳቸው እና በኑሮ አብረውት ለነበሩት አገልጋዮቹ በአጠቃላይ ለቤተሰቦቹ ሲሆን፣ ፍጻሜው ግን በብሉይ ኪዳን በሃይማኖት አባት ለሆነላቸው ለቤተ እስራኤል (ለእግዚአብሔር ሕዝቦች)፣ በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ነው፡፡ አባታችን ያዕቆብ ከመባረኩ አስቀድሞ ያዕቆብ እየተባለ ይጠራ የነበረ ቢሆንም ከተባረከ በኋላ እስራኤል ተብሏል፡፡ እስራኤል የሚለውም የመባረክ፣ የመመረጥ፣ የመቀደስ፣ የመክበር ስም ነው፡፡
እግዚአብሔር ሲያከብርና ሲቀድስ ስምንም ይለውጣል፡፡ ያዕቆብም ሌሊቱን ሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታገል ያደረው ባርከኝ በሚል ልመናና ጸሎት ነበር፡፡ “እግዚአብሔርም አለው ስምህ ያዕቆብ አይባል ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ” ብሎታል (ዘፍ.፴፭፥፲)፡፡ ያዕቆብ የሚለው የቀድሞ ማንነቱ የተገለጠበት ስም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የቀድሞ ማንነቱን በበረከት ቀይሮለት ከባረከው በኋላ ያለውን ማንነት የሚገልጥ አዲስ ስም ሰጠው፡፡ ያዕቆብ የሚለው የስም ትርጉም፡-አዕቃጼ ሰኮና(ተረከዝ ያዥ)፣ አሰናካይ ማለት ሲሆን ቀድሞ በዚህ ግብሩ ይጠራ ነበር፡፡ ኋላ ግን እስራኤል ተብሏል፡፡
እስራኤል ማለትም የተባረከ የእግዚአብሔር ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ሙሴ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሣው ቁጣ ለማምለጥ ወደ አጎቱ ላባ ሄዶ ብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ ብዙ ሀብትና ንብረት አፍርቶ ልጆችን ወልዶ ቆይቶአል፡፡ ወደ አባቱና እናቱ ወደ ወንድሙም ለመመለስ ሲነሣ የወንድሙን ይቅርታ እንዲያገኝ ብዙ እጅ መንሻ ይዞ ተነሣ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንዳለበት ነገረው፡፡
“ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጥሁልህ ለእኔ መሠውያን ሥራ” እግዚአብሔር ይህን ካለው በኋላ መላው ቤተሰቡ እሱ በስደት ከኖረበት አገር መውጣት እንዳለባቸው፣ ሲወጡ ደግሞ ንጹሐን ሆነው መውጣት እንዳለባቸውና ልብሳቸውን ማጠብ እንደሚገባቸው ከመካከላቸውም እንግዶች አማልክትን ማስወገድ እንዳለባቸው ነግሯቸዋል፡፡ “ያዕቆብም ለቤተሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶች አማልክትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፣ ንጹሓንም ሁኑ፣ ልብሳችሁንም እጠቡ፣ ተነሡና ወደ ቤቴል እንውጣ በዚያም በመከራዬ ቀን ለሰማኝ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ከመከራም አድኖ ላሻገረኝ ለእግዚአብሔር መሠውያን እንሥራ”(ዘፍ.፴፭፥2-፫) በማለት ነግሯቸዋል፡፡
አባታችን ያዕቆብ ሲናፍቃት ወደ ነበረችው፣ እናት አባቱ ወዳሉባት፣ ወንድሙና የአባቱ የእናቱ ቤተሰቦች ወዳሉባት፣ ተወልዶ ወዳደገባት ሀገር ለመመለስ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነለት በስደት እያለ ያፈራቸው እና ያገኛቸው ቤተሰቡ የቆዩበትን የኃጢአት ሥራ እንዲያስወግዱ ጣዖት አምልኮ ያደረጉበትን፣ በጣዖታት ፊት የተንበረከኩበትን፣ ያደፈ ልብሳቸውን እንዲያጥቡና እንዲያነጹ፤ ከዚያም ወደ አያቱ አብርሃም ወደ አባቱ ይስሐቅ መንደር (አገር) ወደተባረከችው ምድር በበረከት ወደሚኖርባት ሀገር ገብተው መኖር እንዲችሉ የሚያደርጋቸውን ቅድመ ሁኔታ በሚገባ አስተማራቸው፡፡
እነዚህም ከላይ የጠቀስናቸው ሲሆኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ በሕገ ልቡና ለቅዱሳን አበው የገለጸላቸው ናቸው፡፡ ኋላም ለሙሴ በሲና ተራራ ላይ በሕገ ኦሪት እንዳዘዘው “እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ በላይ በሰማይ ካለው በታችም በምድር ከአለው ከምድርም በታች በውኃ ከአለው ነገር የማናቸውንም ምስል ለአንተ አምላክ አታድርግ”(ዘፀ.፳፥፩) የሚል ነውና ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ ያዕቆብ እንዳለው እንግዶች አማልክትን ከመካከላቸው እንዲያስወግዱ አደረገ፡፡
ዛሬም ቢሆን በአንዳንዶቻችን ዘንድ ነውር የሆነ ጣዖት አምልኮ በተለያየ መልኩ ሰልጥኖብን እያለ ከሰዎች እይታ ለመሰወር እውነተኛ መስሎ መታየት፣ ነውሩን እንደ ክብር የመቁጠሩ ነገር ይታያል፡፡ አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ እንግዶች አማልክትን አስወግዱ፣ ንጹሓን ሁኑ፣ ልብሳችሁን እጠቡ ያለው የተስፋዋን ምድር ለመውረስ የሚናፍቁትን ቤተሰቡን እንደሆነ ሁሉ ዛሬም ተስፋ ወደምናደርጋት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ለመግባት አምልኮ ጣዖትን ማስወገድ፣ ከበደል ርቀን ንጹሃን ሆነን መኖር፣ በንስሓ ዕንባ መታጠብ እና መንጻት ያስፈልጋል፡፡
ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ “እንግዲህ ለአዲስ ቡሆ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ ከእናንተ አርቁ፣ ገና ቂጣ ናችሁና ፋሲካችን ክርስቶስ ተሠውቶ የለምን አሁንም በዓላችሁን አድርጉ ነገር ግን እውነትና ንጽሕና ባለው እርሾ ነው እንጂ በአሮጌው እርሾ በኃጢአትና በክፋት እርሾም አይደለም”( 1ኛቆሮ.፭፥7) በማለት ያስጠነቀቃቸው፡፡
ሐዋርያው እንዳስተማረን አሮጌ እርሾ ማለት የቀደመ በደላችን፣ ክፉ ሥራችን፣ በጨለማ የተመላለስንበት ማንነት፣ ከእግዚአብሔር ርቀን የኖርንበት ዘመን ነው፡፡ ለዚህም ነው በቤተ ክርስቲያን በምናደርገው ጉባኤ ላይ ተሰባስበን በኅብረትም ሆነ በግላችን የቀደመ በደላችንን አታስብብን፣ አቤቱ ይቅርታህ ፈጥኖ ይደረግልን እያልን የምንዘምረው፡፡
የቀደመ በደላችንን ለማስወገድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጅራፍ ተገረፈ፣ በጥፊ ተጸፋ፣ የእሾህ አክሊል ተደፋበት፣ በመስቀል ተሰቀለ፣ ነፍሱን በፈቃዱ ሰጠ፣ በሥጋው ተቀበረ፣ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ነጻነትን ሰበከ፣ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ቆይቶ ተነሣ፣ በዓርባኛው ቀን ዐረገ፣ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፣ ዳግመኛም ዓለምን ለማሳለፍ በምስጋና ይመጣል፡፡ ክብር ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ የሆነው የቀደመ በደላችንን ሊያጠፋ ነው፡፡ ከቀደመ በደላችን ነጻ ካወጣን በኋላ፣ ከባርነት አላቆ በልጅነት ጸጋ እንድመላለስ ካደረገን በኋላ ዳግም የኃጢአት ባሮች ልንሆን አይገባም፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ፡- “የአሕዛብን ፈቃድ ዝሙትንና ምኞትን ስካርንና ወድቆ ማደርን ያለ ልክ መጠጣትንና ጣዖት ማምለክምን ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋልና”(፩ኛጴጥ.፬፥፫) እንዳለው ሁሉ የቀደመ ክፉ ግብራችንን ማስወገድ ያለፈውን ዘመን ከነ ክፋቱ ጥሎ ማለፍና አዲሱን ዘመን በንስሓ በታጠበ ማንነት መኖር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው አባታችን ያዕቆብ ወደ ቤቴል እንዲወጣ እና ከቤተሰቡ ጋር እንዲገናኝ በተጠራ ሰዓት በስደት ሀገር ያገኛቸው ቤተሰቡን የኖሩበትን የቀደመ በደላቸውን ትተው ልብሳቸውንም አጥበው መውጣት እንደሚገባቸው ያስተማራቸው፡፡
ውጫዊ ልብስ ሲቆሽሽ እንደሚታጠብ ሁሉ ውሳጣዊ ማንነታችንም በኃጢአት ሥራ ሲቆሽሽ በንስሓ ይታጠባል፡፡ ነገር ግን ባደፈ ልብስ ወደ ሠርግ አዳራሽ እንደማይገባ ሁሉ ንስሓ ባልገባ ማንነትም ወደ እውነተኛው ወደ ዘለዓለማዊው የሠርግ ቤት አዳራሽ መግባት አይቻልም፡፡ ንስሓ ኃጢአተኛውን ጻድቅ፣ ዘማዊውን ድንግል የሚያደርግ ነው ሲባል በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ሲመለስ በኃጢአት ይኖር የነበረ ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል፡፡ ዘማዊ የነበረውም በደሉ ተደምስሶለት ቅዱሳን ሊያገኙት ያላቸውን ጸጋና ክብር ያገኛል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ አስቀድሞ እንደሚበድል ያውቅ ነበርና የሚጸጸትና ስለ ኃጢአቱ የሚያለቅስ በጎ ኅሊና ፈጥሮለታል፡፡ ለዚህም ነው ንስሓ ለእገሌ ወይም ለነእገሌ ተብሎ ሳይሆን ለሁሉም ሰው ያስፈለገው፡፡ ምክንያቱም ሰው በተለያየ መንገድ ስለሚበድል ኃጢአትን ስለሚሠራ እሱም፡- በአሳብ፣ በቃል፣ በተግባር የሚሠራ ኃጢአት ነው፡፡
ለሁሉም እንደየ ደረጃው ንስሓ ያስፈልገዋልና ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ፡- “ይህች መከራ ስለአገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ተለይተው ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሏችኋልን አይደለም እላችኋለሁ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ ወይስ እነዚያ በሰሊሆም ግንብ ተጭኖ የገደላቸው ዐሥራ ስምንቱ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ሰዎች ይልቅ ተለይተው ኃጢአተኞች ይመስሏችኋልን አይደለም እላችኋለሁ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ” በማለት ያስተማረው(ሉቃ.፲፫፥፩)፡፡
አባታችን ያዕቆብ ልብሳችሁን እጠቡ ያለው ለጊዜው ውጫዊ ልብሳቸውን ሲሆን በፍጻሜው ግን በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስን የሚያስተምር ነው፡፡ ሰው በኃጢአትና በበደል ምክንያት ከእግዚአብሔር እንደሚርቅ ሁሉ በንስሓ ሲመለስ ደግሞ ከእግዚአብሔር የተለየበት ኃጢአቱ ይቅር ተብሎለት ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል፡፡ ይህ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየቱ የሞት ሞት መሞቱን ሲያመለክተን በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መቅረቡ ደግሞ በዘለዓለማዊ ሕይወት የሚኖር መሆኑን ያስረዳናል፡፡
ከገቡ መውጣት፣ ካገኙ ማጣት የሌለባት የማታልፈውን ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እግዚአብሔር ያወርሰን ዘንድ ያደፈው ማንነታችንን የተጎሳቆለ ሕይወታችን በንስሓ ልናጥበውና ንጹሕ ሆነን ምጽአቱን ልንጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ መቼ እንደምመጣ አታውቁምና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁኝ ብሎ የአመጣጡን ነገር እንዳስተማረን ሁሉ ተዘጋጅተን ልብስ የተባለ ሥራችንን መልካም አድርገን እንኖር ዘንድ በቸርነቱ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!