‹‹ሁሉ በአግባቡ እና በሥርዓቱ ይሁን›› ፩ኛ ቆሮ.፲፬፥፵ (ክፍል አንድ)
በዲ/ን ታደለ ሲሳይ
ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር እንዲል እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር የሚሠራበት ጊዜ አለው፡፡ ዓለምን ሲፈጥር፣ ሙታንን ሲያስነሣ፣ ድዉያንን ሲፈውስ፣ የተሰደዱትን ሲመልስ፣ ያዘኑትን ሲያረጋጋ እርሱ ጊዜ አለው፡፡ ሁሉንም በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው እንዲል ለሥራው ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር የተፈጠረ፣ እርሱ የሠራለትን ሥርዓት ተከትሎ የሚኖር እንደመሆኑ ለእንቅስቃሴው ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ የሰው ልጅ በጨለማ የኖረበት ጊዜ አለው፤ በብርሃን ውስጥ ያለፈበትም ጊዜ አለው፡፡ የሰው ልጅ በድንቁርና የኖረበት ጊዜ አለ፤ በዕውቀት ብርሃን የተመላለሰበት ጊዜ አለ፡፡ የሰው ልጅ በጥበብ ሰክኖ ፈጣሪውን ያመሰገነበት ጊዜም አለው፡፡ የሰው ልጅ ባልተጻፈ ሕግ የተመራበት ጊዜ አለው፤ በተጻፈ ሕግም የተመራበት ጊዜ አለው፡፡
አሁን ያለንበት ዘመን የሰው ልጆች ልዩ ልዩ የሆኑ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለዓለም ያበረከቱበት፣ እነርሱም የላባቸውን ውጤት እየተጠቀሙ ያሉበት ጊዜ ነው፡፡ እነዚህ የሰው ልጆች የአዕምሮ ፈጠራ ውጤት የሆኑት የቴክኖሎጂ ግኝቶች ምድራዊ ኑሮን ከማቅለል እና ቀልጣፋ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ የዕለት ከዕለት ኑሮን ከማፋጠን እና ምቹ ከማድረግ አንጻርም ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡ እንደሚታወቀው የሰው ልጅ አቅሙ ውስን እንደመሆኑ መጠን አእምሮው በሚፈልገው ፍጥነት ማከናወን አይችልም፡፡ ይህንን የአዕምሮ ፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ የወሰደው እርምጃም እግዚአብሔር የሰጠውን ብሩሕ አዕምሮ ተጠቅሞ፣ ሥራውን የሚያቀልለትን መሣሪያ መሥራት ነው፡፡ በዚህም የጥበብ አምላክ ይክበር ይመስገንና የሰው ልጅ አስደማሚ የሚባሉ መሣሪያዎችን መሥራት ችሏል፡፡ ዓለምንም ዘመናዊ እንድትባል አስችሏታል፡፡ እርሱም ዘመናዊ ሰው ተብሏል፡፡
ዘመናዊነት ማለት ታዲያ ከላይ እንደተተጠቀሰው ከዘመኑ ጋር አብረው የሚሔዱ ነገሮችን ጥበበ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ መሥራትና መጠቀም ነው፡፡ ይህም ባህልን፣ ክርስቲያናዊ ሕይወትን፣ ግላዊ ማንነትን፣ ሰዎችን ጥቅም፣ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማይፈታተን መልኩ መሆን አለበት፡፡ ዘመናዊነት ይህ ነው እንጂ ራስን እየጎዱ፣ ሌሎችን እያሳዘኑ፣ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን አደጋ ላይ እየጣሉ የሚጠቀሙት አይደለም፡፡ ይህ ዘመናዊነት ሳይሆን ራስ ወዳድነት፣ አለማስተዋልና ስግብግብነት ነው፡፡ በመሆኑም ዘመናዊነት ዘመኑን ዋጁ እንዳለው ቅዱስ መጽሐፍ ዘመኑን መዋጀት ነው፡፡
የሰው ልጅ እግዚአብሔር የገለጸለትን ጥበብ በአግባቡና በሥርዓት ሲጠቀም፣ ለሥጋው ብቻ ሳይሆን ለነፍሱም ትሩፋትን መሥራት ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ከዚህ በተቃራኒው አጠቃቀማቸው ሰብአዊ፣ ሥርዓት የለሽ እና ሥነ ምግባር አልባ ከሆነ ጉዳታቸው በጣም አስከፊ ነው፤ በሥጋ በነፍስም እንድንጠፋ ያደርጋሉ፡፡ አሁን ወጣቱ ክፉንና ደጉን ለይቶ መጠቀም ባለመቻሉ፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሕግ ሲጥስ፣ ራሱን ሲያታልል፣ ትእዛዛትን ሲያፈርስ፣ በዚህም የተነሣ በምድር ላይ በሰላም መኖር ተስኖት ሲጎዳ ይታያል፡፡ «ልጄ ሆይ ሕጎቼን አትርሳ፤ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ፤ ብዙ ዘመናትንና ረጅም ዕድሜን ሰላምንም ይጨምሩልሃልና፡፡ ምጽዋትና ሃይማኖት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሠራቸው በልብህ ጽላትም ጻፋቸው» እንዳለ ምሳ. 3፥1-4 ዘመናዊነትን ተጠቅመን፣ ሕጉን መርሳት ያስጠይቀናልና በዘመናዊነት ውስጥ በሕግ መኖርን መዘንጋት የለብንም፡፡
የሰውን ልጅ ለጥፋትም ለድኅነትም ከሚረዱ ነገሮች የመገናኛ ብዙኃን የፈጠራ ግኝቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ማኅበራዊ ሚድያዎች (Social medias) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፌስቡክ (Facebook)፤ ትዊተር (Twitter)፤ ኢንስታግራም (Instagram)፤ ፓልም ቻት (Palmchat) በስፋት አገልግሎት ላይ የሚውሉ ማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኀን ናቸው፡፡ ከነዚህ ማኅበራዊ የመረጃ አውታሮች መካከል በሀገራችን እጅግ ብዙ ተጠቃሚ ያለው ደግሞ ፌስ ቡክ የተሰኘው ማኅበራዊ የመረጃ አውታር ነው፡፡ ይህንን የመረጃ አውታር በብዛት የሚጠቀመው ደግሞ ወጣቱ እንደመሆኑ መጠን ይህንን እና ሌሎች የዘመናዊነት መገለጫ የሆኑ ነገሮችን ሲጠቀም በማስተዋልና በጥበብ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሰው ካወቀበት በሚድያ ትምህርተ ሃይማኖትን ተምሮ፣ ያሬዳዊ መዝሙሮችን ሰምቶ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብቦ፣ ዓለም የሄደበትን መልካምና ክፉ ዘመን መርምሮ፣ ዓለማዊና መንፈሳዊ ዕውቀትን ተምሮ፣ ዓለም የደረሰበትን የጥበብ ጥግ አውቆና ተረድቶ በሥጋውም በነፍሱም መጠቀም ይችላል፡፡ ካላወቀበት ደግሞ በማኅበራዊ ሚድያው ጥፋትን፣ ዝሙትን፣ ስርቆትን፣ ሰው መግደልን፣ ዘረኝነትን፣ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን መራቅን፣ ሀገርንና ሕዝብን መክዳትን ተምሮ ለነፍሱም ለሥጋዉም የሚጎዳ ተግባር ይፈጽማል፡፡
እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች ወጣቱ በሥርዓት ከመጠቀም ይልቅ ያለ ሥርዓት ሲያውላቸው ሥነ ምግባርን፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን እና ሥነ ሥርዓትን ያልጠበቀ ይሆናል፡፡ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዛኝ ሆኖ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ አሁን እስካለችበት ዘመን ድረስ ብሎም ለወደፊት እስከ ዓለም ፍጻሜ በሕግና በሥርዓት እየተመራች እንዲሁም ምእመኖቿ ሕግጋተ እግዚአብሔርን እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያከበሩ፣ ሥርዓተ አምልኮአቸውን እየፈጸሙ በአግባቡ እና በሥርዓቱ እንዲኖሩ ስታስተምር ቆይታለች፤ አሁንም በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!