እንዴት እንጹም?
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደነገገቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት እንደአሏት ይታወቃል፡፡ እነዚህም፡- ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ፍልሰታ፣ ጾመ ድኅነት እና ገሀድ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊም በጾም ወቅት እንዴት መጾም እንዳለበት ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ይተነትናሉ፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል ከሃይማኖተ አበው፣ እንዲሁም ከፍትሐ ነገሥት ያገኘናቸውን መረጃዎች በጥቂቱ እናካፍላችሁ፡፡ በቅድሚያ ግን በሃይማኖተ አበው ሠለስቱ ምእት ምዕራፍ ፳፤፲፰-፳፱ ላይ የሰፈሩትን እናስቀድም፡-
- ጌታ ያዘዘውን ጾም አትሻር፣ እነዚህም ረቡዕ፣ ዐርብ ናቸው፡፡ ደዌ ካላገኘህ በቀር በበዓለ ሃምሳ፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ በዋሉባቸው ዕለታት (ረቡዕ፣ ዐርብ) በቀር ይኸውም ኤጲፋንያ(ጥምቀት) ነው፡፡
- ምእመናን የሚጾሙዋት ጾመ አርብዓ (ዐቢይ ጾም) ከፋሲካ የሚቀድሙ ሰባቱን ዕለታት (ሰሙነ ሕማማትን) ጾምነታቸውን በፍጹም ጥንቃቄ ጠብቅ፡፡
- አንተ ሰውነትህን ለማድከም በምትጾምባቸው ዕለታት ወንድምህ ሊጠይቅህ ቢመጣ እግዚአብሔርን ደስ በምታሰኝ በበጎ ሕሊና በፍቅር ሆነህ ከእርሱ ጋር ተመገብ፣ ይህንንም የምነግርህ የጌታ ጾም በሆኑበት ዕለታት ትበላ ዘንድ አይደለም፡፡ እሊህም ረቡዕና ዐርብ አርባውም (ዐቢይ ጾም) ቀን ናቸው፡፡ አንተ ብቻ በራስህ ፈቃድ በምትጾምበት ቀን ነው እንጂ ይኸውም ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ሐሙስ ነው፡፡
- በቅዳሜ ቀን ግን መጾም አይገባም፡፡ በቅዳሜ ቀን ፀሐይ እስኪገባ መጾም የሚገባ ሥራ አይደለም፡፡ የሚገባ ጊዜ አለ እንጂ፡፡ እስከ ስድስት ያም ባይሆን እስከ ሰባት፡፡
- እሑድ ቀን በጠዋት እጅግ ማልደህ ከሌሊቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ። ስትሔድም ልቡናህን በማባከን ወዲያና ወዲህ አትይ። በንጹሕ ቅዳሴም ጊዜ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን እያሰብክ በፍጹም ፍርሃት ቁም፡፡
- የዐርብና የረቡዕ ጾም ከቀኑ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይሁን፤ ከዚህ አብልጠህ ብትጾም ግን ለነፍስህ ጥቅም ይሆንሃል፡፡ የማሰናበቻ(ዕትዉ) እስኪፈጸም ድረስ ከቤተ ክርስቲያን አትውጣ፣ ሕማም ቢያገኝህ ነው እንጂ፣ ድንገተኛ መንገድ ቢሆን ነው እንጂ፡፡
- ሁለት ሁለት ቀን መጾም ቢቻልህ በዚህ ብትጸና ጾምህ በትሕትና ይሁን፣ ልቡናህ አይታበይ፡፡
- ትዕቢት ሰይጣን ያለማው ጦር ነውና በእርሱም ሰይጣን ከልዑል ማዕረጉ ተዋርዶዋልና በትዕቢቱ አሽከላነትም የሰውን ልጆች ሁሉ ያጠምድበታል፡፡ እንደ እርሱ ወደ ገሀነም ሊያወርዳቸው ይፈቅዳል፡፡
- በከበረች በእሑድ ቀን መቼም መቼም ትጾም ዘንድ ማንም አያስትህ፡፡ አትስገድባት፣ በዋዜማው(ቅዳሜም) ቢሆን ዳግመኛም በከበረች በፋሲካ ቀኖች (በበዓለ ሃምሳ) አትስገድ፣ ቅዳሴ በሚቀደስበትም ጊዜ ሁሉ ሥጋውን ደሙን ከተቀበልክ በኋላ አትስገድ፣ ይህ ሥርዓት ከቤተ ክርስቲያን የተገኘ አይደለምና፡፡
- በሰንበት ቀኖችም እንደ ሌሎች ቀኖች አትጹም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስኩብ በመቃብር ከነበረባት፣ ድኅነት በተደረገባትና ከፋሲካ ዋዜማ ካለች ከአንዲት ቅዳሜ ቀን (ቀዳም ስዑር) በቀር፡፡
- እሑድና ቅዳሜን የሚጾም የመርቅያን ክሕደቱ ልቡናህን አያስትብህ፣ በቅዳሴ ጊዜ ቸል አትበል፣ ሰውነትህን ለከበረ ለሥጋው ለደሙ የበቃ አድርግ። የበቃህ ሳትሆን ከእርሱ እንዳትቀበል ጽኑ ፍዳ እንዳይፈርድብህ፡፡
- ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል፣ ይህችን ሥራ ቸል የሚልዋትን ስለዚህ ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯቸዋልና ምንም ኤጲስ ቆጶሳትም እንኳ ቢሆኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና፡፡
ይቆየን
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!