ታቦት በቅዱስ ጳውሎስ አንደበት

…በመ/ር ማዕበል ፈጠነ…

ታቦት ከእግዚብሔር ለእሥራኤል ዘሥጋ የተሰጠ ስመ አምላክ የተጻፈበት ሰው በእግዚአብሔር ትእዛዝ ውስጥ መሆኑን የሚያመለክት ምሥጢራዊ ሀብት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለእስራኤል ዘሥጋ የሰጠውን ታቦት ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሐዲስ ኪዳን ጠቅሶ ሲያስተምርበት እንመለከታለን፡፡ እንደሚታወቀው ቅዱስ ጳውሎስ  ዓለምን በሚያስተምርበት መዋዕለ ስብከቱ  ታቦትን ከጣዖት  ለይተው ያላወቁ  ጥሬ ደቀ መዛሙርት ነበሩ፡፡ ይኸውም በቅዱስ ጳውሎስ አነጋገር ታውቋል፡፡ ያም ማለት ‹‹ለመሆኑ  ታቦተ እግዚአብሔርን  ከጣዖት ጋር አንድ የሚያደርግ ማን ነው›› ብሎ ታቦትን ከጣዖት ለይቶ ማስተማሩ  ነው፡፡  ይህን ሊል የቻለው ቅድመ ኦሪት የነበሩ እስራኤል ዘሥጋ  በከነዓናውያን ፍቅረ ጣዖት እየተሳቡ ወደቤተ ጣዖት ይገሠግሡ ነበር፡፡ ያን እንዲተዉ ጌታ በሙሴ እጅ ታቦትን ሰጣቸው፡፡

  ኋላም በሐዲስ ኪዳን ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ በመስቀል ተሰቅሎ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት አድሮ ተነሣ፡፡ ተነሥቶ ሲያርግ መምህራንን ሹሞላቸው አረገ፡፡

   ከዚህ በኋላ አበው ሐዋርያት አስተማሩ፡፡ በአንድ ቀን ትምህርት  በእልፍ የሚቆጠሩ ምእመናን አመኑ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የቆሮንቶስ ምእመናን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የቆሮንቶስ ምእመናንም አምነው ከተጠመቁ ከጨለማ ከወጡ በኋላ የለመዱት ልማድ እንዲህ ቶሎ ሊለቅ አይችልምና በቅዱስ ጳውሎስ መዋዕለ ስብከት  እየተሾለኩ ወደቤተ ጣዖት  መሔዳቸው አልቀረም፡፡

    ያን የሰማው ቅዱስ ጳውሎስ የታቦትን ቅዱስነት የጣዖትን ርኩስነት ሲገልጽ ታቦቱን ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር›› ብሎ  ጣዖቱን ‹‹ርኩስ››  በማለት ገለጸው፡፡  ይኸውም ‹‹መኑ ዘይዴምር ታቦተ እግዚአብሔር ውስተ ቤተ ጣዖት፤ የእግዚአብሔርን ታቦት በጣዖት ቤት ውስጥ የሚጨምር ማን ነው ብሎ ካነጻጸረ በኋላ ወደ ጣዖት የሚገሰግሱ ባዕዳንን ሲመክር ‹‹ወኢትቅረቡ ኀበ ርኵሳን፤ ወደረከሱት አትቅረቡ›› ሲል መከራቸው፤ አስተማራቸው፡፡  እንግዲህ ርኩሳን ሲል መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ርኵስ›› ብሎ  የነቀፈው ጣዖቱን ሲሆን ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር›› ብሎ የገለጸው  ደግሞ ታቦቱን ነው፡፡ እንግዲህ ታቦትና ጣዖት በቅዱስ ጳውሎስ አንደበት እንዲህ የሰማይና የምድርን ያህል ርቀት አላቸው፡፡

  በሐዲስ ኪዳን ታቦት አያስፈልግም ለሚሉ ሁሉ ይህ ‹‹ታቦተ-እግዚአብሔር›› ተብሎ በቅዱስ ጳውሎስ አንደበት የተመሰከረለት ታቦት ለመኖሩ በቂ ምስክር ነው፡፡ 2ቆሮ 6÷15

  በሌላ አገላለፅ በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን ጣዖት እንደነበረ ታቦትም ነበረ፡፡ ባይኖር ኑሮማ ታቦት ድሮ ነበረ፡፡ ነገር ግን አለፈ ብሎ በማስተማር ፋንታ ታቦቱን ከጣዖት ክርስቶስን ከቤልሆር ለይቶ አያስተምርም ነበር፡፡

   እሱ ግን ‹‹ክርስቶስና ቤልሆር በማንኛውም ነገር ኅብረት እንደሌላቸው ታቦትና ጣዖትም እንዲሁ ናቸው›› ብሎ ታቦቱን ‹‹ታቦተ እግዚአብሔር›› ጣዖቱን ‹‹ርኵስ›› ብሎ ለይቶ አስተማረ፡፡ እንግዲህ ይህ ቃል አማናዊ እንጂ የምሳሌ ትምህርት ስላልሆነ በብሉይም ሆነ  በሐዲስ ኪዳን  ታቦት መኖሩን በሚገባ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታቦቱ መኖሩ በዚህ ቃል መሠረት ነው እንጂ አላዋቂዎች እንደሚሉት በስሕተት አይደለም፡፡