ታቦት ምንድን ነው?

…በመ/ር ማዕበል ፈጠነ…

ሕገ እግዚአብሔር በወረቀት ላይ መጻፍ ሲጀምር በብዙ ቁጥር የሚቆጠሩ ምሥጢራት በእግዚአብሔር አንደበት ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ተነግረዋል፡፡ ነቢዩ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል በቃል ከተነጋገረባቸው አንዱ ምሥጢር ደግሞ ‹‹እንደ ቀደመው የድንጋይ ጽላት ቅረፅ›› የሚለው ትእዛዝ ነው፡፡ ይህም ‹‹እግዚአብሔር ሙሴን አለው ‹‹ሁለት የድንጋይ ጽላት እንደ ፊተኛው አድርገህ ቅረፅ፤ ወደእኔም ወደ ተራራው ውጣ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ›› ይላል፡፡ ዘጸ. 34÷1-2

  ከመጽሐፍ ቅዱሱ ንባብ ውስጥ በማያሻማ መልኩ እንደ ተመለከትነው ሙሴ በቀደሙት ጽላት ፋንታ ሌላ ጽላት እንዲቀርፅ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡  ዝቅ ብሎም  ‹‹ወወቀረ ሙሴ ክልኤተ ጽላተ ከመ ቀዳምያት፤ ሙሴም ሁለት ጽላት እንደ ቀደመው አድርጎ ቀረፀ፤ ሲል ይደመድመዋል፡፡ ዘጸ. 34÷4

እንግዲህ ይህን ቃል እንዲሁ በዓይነ ሥጋም ሆነ በዓይነ ነፍስ ለተመለከተው እግዚአብሔር በአንደበቱ ታቦት ቅረፅ ብሎ ለሙሴ ሲናገር ሙሴም ‹‹አሜን››  ብሎ ትእዛዙን ሲፈጽም ያሳያል

  ይህም ብዙ ዐውደ ምሥጢር እንዳለው ግልፅ ነው፡፡ ለምን ቢሉ?

  1. ታቦት እንዲቀርፅ ሙሴ መታዘዙ ታቦት ለጊዜው ለእስራኤል ዘሥጋ የሥርዐተ አምልኮ መፈጸሚያና መማጸኛ እንዲሆን ነው፡፡
  2. የፊተኛው ታቦት ከተሰበረ በኋላ ሁለተኛ ታቦት እንዲቀርፅ አባታችን ሙሴ መታዘዙ ታቦት ለትውልደ-ትውልድ እንደሚያስፈልግ ለመግለጽ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የቀደሙት ጽላቶች በጣዖት ምክንያት  ከተሰበሩ በኋላ ሁለተኛ እንዲቀረፁ ማዘዙ ታቦት አንድ ጊዜ ብቻ ለአምልኮት የሚፈለግ ከዚያ በኋላ የሚጣል እንዳልሆነ ለማስተማር ነው፡፡

 የዚህ ሁሉ የምሥጢር ቁንጮ ግን ታቦቱ በብሉይም ሆነ በሐዲስ እንዲሁም እስከ ወዲያኛው ሊኖር ከእግዚአብሔር መሰጠቱን እንድናውቅ ይረዳናል፡፡

  ይህም ‹‹ወእጽሕፍ ውስተ ውእቶን ጽላት ዝክተ ነገረ፤ እንደ ቀደሙት ሁሉ ዐሠርቱ ቃላትን በዚህ ላይ እጽፋለሁ›› ማለቱ ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ታቦቱ ላይ ዐሥሩ ቃላት መኖራቸው ነው፡፡ ከዐሥሩ ቃላት አንዱ ደግሞ ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ›› የሚለው ነው፡፡ ዘጸ 20÷3

እናም ከታቦቱ ላይ የእሱ ስም እንጂ የጣዖት ስም የለበትም፡፡ ለታቦት መስገዳችንም ይህን ሥርዐተ ምሥጢር በማወቅ እንጂ ባለማወቅ ለቅርፃ ቅርፅ ወይም ለጣዖት እየሰገድን አምልኮ ባዕድ እየፈጸምን አይደለም፡፡

ያለ ትርጓሜ ሠረገላ በጥሬው አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ለሚመሩም ሆነ ዐሠረ አበውን ተከትለው የሊቃውንትን መጽሐፍ ተቀብለው፣  የውስጡን ምሥጢር ተረድተው ለሚኖሩ ቤተ እምነቶች ሁሉ ታቦት ክቡር መሆኑን እንዲያውቁ የሚፈለገው ከታቦቱ ላይ ስመ- አምላክ ወይም ትእዛዙ ተጽፎ መኖሩን ማወቅ ነው፡፡ ይህንን በሚገባ ከተረዳነው ታቦቱ ማኅደረ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ማደሪያ) መሆኑን ማመን የግድ ነውና፡፡

   እንግዲህ ‹ስሙ›› ስመ አምላክ ከሆነ ትእዛዙም ጣዖታዊ ሳይሆን አምላካዊ ከሆነ በእግዚአብሔር አንደበት ታቦት እንዲቀርፅ ለሙሴ መለኮታዊ ትእዛዝ ከታዘዘ ታቦት የስሙ ማረፊያ ሆኖ ሊኖር እንጂ በዘመን ሊሻር የሚችል አይደለም፡፡ ለምን ቢሉ በሊቀ ነቢያት ሙሴ ጊዜም ሆነ ዛሬ ከታቦቱ ላይ የታተመው ስመ-አምላክ ነውና ነው፡፡

  ለሙሴ ታቦት ተሰጠው፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሲፈጽምበት ኑሮ አረፈ፡፡ ደቀ መዝሙሩ ኢያሱም እንደ መምህሩ ሙሴ ካህናቱን ታቦት አሸክሞ ወደ ምድረ-ርስት ገባ፡፡ ኋላ ዳዊት ከአቢዳራ ቤት ወደ ኢያቡስ አስመጥቶ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ዘመረ፡፡

   ምድራዊቷ ሴት ሚልኮል ግን ተቃወመች፤ እግዚአብሔር ግን የዳዊትን ዝማሬ ተቀብሎ ሚልኮልን ናቃት፡፡ ከዳዊት ክብር የታቦቱ  ክብር ይበልጣልና፡፡ በሌላ አነጋገር ቤተ-አቢዳራ (የአቢዳራ ቤት) በታቦቱ እንደ ከበረ ዳዊትም በታቦቱ ሊከብር መፈለጉ የታቦቱን ክብር በመንፈሰ ትንቢት አውቋልና ነው፡፡ ስለዚህ ከሙሴ እስከ ዳዊት ከዳዊት እስከልደተ-ክርስቶስ ታቦት የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ሆኖ ሲሰገድለት ኑሯል፡፡