ስኬት

…በዳዊት አብርሃም…

“ስኬት” የሚለውን ቃል የማይወድ ሰው ያለ አይመስልም:: በተለይ ራእይ ያላቸው ወጣቶች ስኬታማ መሆንን አጥብቀው ስለሚፈልጉ ብዙ ይጨነቃሉ፡፡ ወደ ስኬት የሚያመሩ መንገዶችን ይጠቁማሉ የተባሉ መጻሕፍትን ያነባሉ፡፡ ብዙ ጊዜም ታላላቆችንና ባለሙያዎችን ስለዚሁ ጉዳይ ምክር ይጠይቃሉ፡፡ እርስ በርስ ይወያያሉ፡፡ ብቻቸውን ሲሆኑም ከራሳቸው ጋር የሚመክሩት ጉዳይ ቢኖር እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ነው፡፡ በርግጥ ስኬት ለማንኛውም ሰው ወሳኝ መሆኑ ግልጽ ስለሆነ ወጣቶች ያን ያክል አጥብቀው ቢፈልጉት የሚያስገርም አይሆንም፡፡ አሳዛኙ ነገር ብዙ ጊዜ ወደ ስኬት ያደርሳሉ ተብለው በአንዳንድ ዓለማውያን አማካሪዎች የሚነገሩ አሳቦች በትክክል ስኬታማ ማድረግ መቻላቸው አስተማማኝ አለመሆኑና ዘዴዎቹ ወጥነት የሚጎድላቸው እንዲሁም በጣም ብዙና አንዳንዴም የሚቃረኑ መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ የትኛውን ዘዴ መጠቀም እንደሚሻል ማወቅ ብቻ ፈታኝ ይሆናል፡፡

ስለሆነም አንድ ክርስቲያን ወጣት ለችግሮቹ መፍትሔን ሊፈልግ የሚገባው ከቤተ ክርስቲያን ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የሚገኝ መፍትሔ አለ ብሎ ማመኑ ብቻውን በተለያዩ የአሳብ ወጀቦች እየተላጋ ካለምንም ተጨባጭ ውሳኔ እንዳይባክን ይረዳዋል፡፡ በተጨማሪም ከአንድ ምንጭ የሚገኝ ምክር ወጥና ጥቂት በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ ቀላል ይሆናል፡፡ በዓለም ሳላን ከዓለም ባንሆንም ኑሮአችንን ለማሸነፍ እግዚአብሔር ጥበብ ከሰጣቸውና ካስገኙልን መልካም ተሞክሮ እየቀሰምን ሕይወትን ቀላል በሆነ መንገድ ብንመራ ለስኬት አያበቃንም፤  እገዛም አይኖረውም፤ ትልቁ ነገር ለስኬት ወደሚወስዱን መንገዶች ስናስብ ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር ያላቸውን አንድነትና ልዩነት ማየት ተገቢ ነው፡፡ “ይከናወንለታል” “ይበዛለትማል” ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ መመሪያዋ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መሆኑ መጠን ሁሌም ቢሆን ለመልካም ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚጠቅሙ አሳቦችን ከዚሁ አንድ መጽሐፍ እየቀዳች ለልጆቿ ታቀርባለች፡ ፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግም ስኬታማ ሕይወት መምራትን በተመለከተ የሚሰጠው ምክር አዎንታዊና የተሟላ ነው፡፡ ይኸውም

መጽሐፉ ስለሰማያዊ ነገር ብቻ እየተናገረ ምድራዊ ሕይወታችንን የሚዘነጋ ስላልሆነ እንዲሁም ምድራዊ ሕይወትን በተመለከተ የሚያቀርበው መመሪያ ሁሉ በመንፈሳዊ አስተሳሰብ የተቃኘ ስለሆነ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን መዝሙረኛው “የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለታል” ሲል የገለጸው በምድራዊ ሕይወት የምናገኘውን መከናወን /ስኬት/ በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል ያለውን ቀና አመለካከት የሚጠቁም ሲሆን በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ደግሞ “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ፡፡” /ዮሐ.1ዐ፥1ዐ/ በማለት የተሟላ ስኬት መንፈሳዊ ሕይወትንም የሚመለከት መሆኑን ያሳያል፡፡ ስኬትና መንፈሳዊ ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወት ለተሳካ ሕይወት ያለው ሚና በምንም አይተካም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለታል” ሲል የገለጸው በመንፈሳዊ ሕይወቱ ብርቱ የሆነውን ሰው ነው፡ ፡ ሙሉ ቃሉም እንዲህ ይላል፡፡ “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ በኀጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ፡፡ ነገር ግን በእግዚብሔር ሕግ ደስ ይለዋል ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባለ፡፡ እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል፡፡ ”  ይህም አሳብ ቢሆን ለዓለም ዕድገት መልካም አቅጣጫንና የስኬት መንገዶችን የቀየሱትን አይቃወምም፡፡ በተቃራኒው ከመንፈሳዊው ጎዳና ስለወጡ ሰዎች ደግሞ ሲገልጽ “ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፤ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው፡፡ ” ይላል፡፡ ስለዚህ የጽድቅ ሕይወት ለሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድራዊ ሕይወት ለመባረክና የተሳካ ሕይወት ለመምራት ዋስትና መሆኑን ክፋትም ቢሆን በሰማይ የሚያስኮንነውን ያህል በምድርም ለጊዜው የጠቀመ መስሎ ቢታይ ለዘላቂው ግን የሚነቅልና ጠርጎ የሚያጠፋ መሆኑን ማወቅ አንድ የስኬት ቁልፍ ነው፡፡ ያልተሳካለት ሳውልና የተሳካለት ጳውሎስ በሳውልና በጳውሎስ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ሁለቱም የአንድ ግለሰብ ስሞች ናቸው፡፡ ልዩነታቸው ግለሰቡን በተለያየ ጊዜ ስለወከሉ ነው፡፡ ሳውል የሚያመለክተው ግለሰቡ

ምሁር የነበረበትን ጊዜ ነው፡፡ ምሁር ብቻ አልነበረም፤ በጣም የሚከበርና የሚፈራ ሰው ነበር፡፡ ለእምነቱ ቀናኢ ከመሆኑም የተነሣ የእምነቱ ጠላቶች አድርጎ የሳላቸውን ክርስቲያኖች ያሳድድ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ለመግደል እስከመቻል ድረስ መብት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሳውል ስኬታማ አልነበረም፡፡ ሳውል የማሳደድ ተግባሩን በትጋት በሚፈጽምበት አንድ አጋጣሚ እስካሁን በሕይወቱ ያልተከሰተ ነገር ገጠመው፡፡ ይህም አጋጣሚ ሳውልነቱን አስቀርቶ ጳውሎስ የሚሰኝ አዲስ ስኬታማ ሕይወቱን አመልካች ስያሜን አጎናጸፈው፡፡ አጋጣሚው የክርስቶስ መገለጥ ነበር፡፡ ምሁርና በጣም የተከበረ ባለሥልጣን የነበረው ሳውል ከአምላኩ ጋር እስኪገናኝ ድረስ በምሁርነቱ ወይም በሥልጣኑ ምክንያት ስኬታማ አልሆነም ነበር፡፡ ከአምላክ ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ግን አሮጌው የሳውልነት ሕይወቱ በስኬታማው / ዓለምን በለወጠው/ ጳውሎስ ተተካለት፡፡ ከዚህ ታሪክ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር ስኬት ማለት የደረጃ ጥያቄ አለመሆኑ ነው፡፡ በርግጥም ስኬት ከፈጣሪ ጋር መሆን እንጂ በደረጃ አንደኛ መሆን ወይም ከሌሎች በልጦ የበላይ መሆን አይደለም፡ ፡