ማኅበራዊ ሚዲያና ወጣቶች
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበራዊ ሚዲያ ስንል ሰዎች በኢንተርኔት (በይነ መረብ) አማካኝነት የሚገናኙበት ወይም የሚነጋገሩበት፣ ግለሰብን፣ ተቋማትን፣ ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ የሚያስተሳስር ዘመኑ ካፈራቸው የመገናኛ ዘዴዎች አንዱ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ሐሳብና ፍላጎትን፣ ልዩ ልዩ መረጃዎች በተለያዩ ቅርጾች ተቀናብረው ለሕዝብ የሚቀርቡበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ወዘተ የመሳሰሉት ሲሆኑ በተለያዩ ቋንቋዎች በጽሑፍ፣ ድምጽ ወምስል፣ በድምጽ መረጃን ለመለዋወጥ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
የሚቀርቡት መረጃዎች እውነትና በእውነት ላይ ተመሥርተው የሚቀርቡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ መረጃዎች ሁሉ ስለ ተጻፉ ወይም ስለተነገሩ ብቻ እውነት (የተጨበጡና የተረጋገጡ) ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በተጨማሪም መረጃዎቹ ጥሩም መጥፎም መረጃዎችና መልእክቶች ያዘሉ ሊሆኑ ስለሚችሉ በሚያነቡት፣ በሚሰሙትና በሚያዩት ሰዎች ዘንድ የተለያዩ ስሜቶችን የማሳደር አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ አዎንታዊም፣ አሉታዊም በሆነ መልኩ ማለታችን ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መረጃዎች በሕፃናት፣ በታዳጊዎች፣ በወጣቶች፣ በጎልማሶችና በአረጋውያን ዘንድ ጥሩም መጥፎም ተጽእኖ መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ በተለይም በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ለማድረግ የምንሞክረው ወጣቶች (የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች) ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንዴት ነው የሚጠቀሙት? ጥቅምና ጉዳቱስ ምንድነው? እንደ መፍትሔም እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው መጠቆም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ቅድሚያ ሰጥተን ማኅበራዊ ሚዲያ በወጣቶች ወይም በሰው ልጆች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ወይም የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ጥቂት ነጥቦችን እናነሣለን፡፡
ሀ. የማኅበራዊ ሚዲያ ተግዳሮቶች፡-
ማኅበራዊ ሚዲያ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ ጉዳቶችም አሉት፡፡ መረጃ ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ውስጥ የፈለግነውን መረጃ ምንነት ያለመረዳት፣ አንዱን ስናገኝ ሌላውን የመፈለግ፣ ጥቅሙንና ጉዳቱን ባለመረዳት ጊዜያችንን እናጠፋለን፡፡ ይህም ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን እንዳንከተል በማድረግ እንድንባክን ያደርገናል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች በተመለከተ ጥቂቶቹን እንዳስሳለን፡፡
፩. ጊዜን በከንቱ ያባክናል፡- ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚተላለፉ መረጃዎች ጥሩም ይሁኑ መጥፎ የማወቅ ጉጉታችንን ስለሚጨምር ከአንዱ ወደ አንዱ በመሸጋገር ጊዜአችንን በማባከን ከዕቅዳችንና ከዓላማችን ሊያስወጣን ይችላል፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ሱስ በመቀየር መሥራት የሚገባንን ሳንሠራ ቁጭ ብለን ውለን እንድናድር የማድረግ ዐቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሊሄድ ይቸላል፡፡
የምንፈልገውን መረጃ በአጭር ደቂቃ ውስጥ ዐይተን ወይም አንብበን ለምንፈልገው አገልግሎት ማዋል ሲገባን ተጨማሪ መረጃ በመፈለግ ጊዜአችን እንዲባክን እናደርጋለን፡፡ ቆይቶም ጊዜአችንን በከንቱ ማባከናችንን ስንረዳ ወደ ጸጸት ያስገባናል፡፡ ደግመን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ላለመቀጠል እንገዘታለን ወይም እንወስናለን፤ ነገር ግን ለማቆም እንቸገራለን፡፡ በዚህም ምክንያት የሚጠሙንና የማይጠቅሙን መረጃዎችን መምረጥ እያቃተን ቀኑን ሙሉ በኢንተርኔት (በይነ መረብ) ላይ የሚሰራጩ መረጃዎችን ስንቃርም እንድንውል ያደርገናል፡፡
፪. ለባዕዳን የባህል ወረራ ያጋልጣል፡- ሀገራችን ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ትውፊትና ሥርዓት እንዲሁም ቅርሶች ያሏት ሀገር እንደሆነች የቀደምት ታሪኮቿ ምስክሮች ናቸው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ከውጪ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ግን ቀስ በቀስ የራሳችንን እየተውን የውጪው ባህል ላይ ትኩረት በማድረጋችን ለከፋ የሃይማኖትና የባህል ወረራ ተጋልጠን እንገኛለን፡፡
በዘመናዊነት ስም እጅግ ጸያፍ የሆኑ ድርጊቶች ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ በጦርነት፣ በመንግሥታት ተወካዮች፣ በጎብኚዎች፣ በዲፕሎማቶች፣ በመምህራን አማካይነት ለመግባት ቻሉ፡፡ እነዚህም መረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕዝቡን አዳዲስ ባህሎችን በማስለመድ በቀላሉ ወጣቶችን በመማረክ ኢትዮጵያዊ የምንላቸውን ባህሎች ወደ መሸርሸር ተሸጋገረ፡፡ ቴክኖሎጂው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀ በመምጣቱም “ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት እንቀይራለን” የሚለውን አስተሳሰባቸውን ለማስፋፋት ተጠቀሙበት፡፡
በዚህ ዘመንም የባህል ወረራው እየተስፋፋ ከቁጥጥር ውጪ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያው ለዚህ የባህል ወረራ ግንባር ቀደም በመሆን እየመራ ይገኛል ማለት እንችላለን፡፡ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን፣ ጎልማሶችንና አረጋውያንን ሳይለይ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መረጃዎች ከመስማት አልፎ ወደ ተግባር ለመለወጥ በሚደረግ ቅጥ ያጣ ነፃነት ስም ብዙዎች የችግሩ ሰላባ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
፬. ከቤተሰብ ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ ያሳጥራል፡- ማኅበራዊ ሚዲያን መከታተል ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳቱም እጅግ የከፋ ነው፡፡ በተለይም ማኅበራዊ ሕይወትን በመገደብ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እስከ ማበላሸት ይደርሳል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በቤተሰብ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነትን በማላላት ለቤተሰባችን የምንሰጠውን ጊዜ በማሳጠር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመጣድ ግላዊ ሕይወትን እንድንመራ ያደርገናል፡፡ በቤተሰብ መካከል መተጋገዝን፣ ውይይትን፣ የጋራም ሆነ የግል ችግርም ይሁን ደስታ ለመካፈል እንዳንችል እንቅፋት ይሆነናል፡፡
ለሉላዊነት ራስን አሳልፎ በመስጠትም በዓለም ላይ የሚከናወኑ ከሥነ ምግባር ያፈነገጡና ባህልን የሚጻረሩ መረጃዎችን እንድንመለከት በማድረግ ከኢትዮጵያዊው ባህል እያፈነገጥን የሕይወታችንን የጉዞ አቅጣጫ ቀስ በቀስ ያስቀይረናል፡፡
ከቤተሰብ ጋር በአንድነት ተቀምጦ ሁሉም ከሞባይሉ በሚተላለፍ መልእክት ስለሚሳብ በተመስጦ ቤተሰብን እንረሳለን፡፡ ይህ ድርጊት የቤተሰብ አባላት የሆኑትን ሕፃናትም የችግሩ ተጠቂ እንዲሆኑ ያበረታታል፤ የጋራ የሚባልን ነገር በማስቀረት ለተለያዩ ሥነ ልቡናዊ ቀውሶች አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ በተለይ ለሕፃናት ሞባይልም ይሁን የተለያዩ ጣቢያ ያላቸውን የቴሌቪዥን ሥርጭቶችን በመግዛት ወይም ማየት የሚገባቸውን እንዲያዩ መርጦ ከመስጠት ይልቅ “ልጆቼ በነፃነት ማደግ አለባቸው” በሚል ፈሊጥ ከሥነ ምግባር እንዲወጡ፣ እግዚአብሔርን መፍራት በልቡናቸው እንዳያድር በማድረግ ራሳቸውም፣ ለቤተሰብም ሆነ ለሀገር የማይጠቅሙ ዜጎች ሆነው እንዲወጡ መንገዱን እናመቻቻለን፡፡ ስለዚህ ቤተሰብ በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል፡፡
፭. ውሸትን ማለማመድ፡- በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉና ሳያጣሩ ያልሆነውን ሆነ በማለት የሚቀርቡ መረጃዎች ሁሉ እውነት ነው ብሎ ማመን ከአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ሰዎች በግላቸውም ሆነ በቡድን ያልተከናወነን መረጃ በመፈብረክና በማሰራጨት በራስ፣ በማኅበረሰብና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደርጋሉ፡፡ ያልሆነውን ሆነ ብሎ ማቅረብ ከሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት በመሆኑም ማኅበራዊ ሚዲያን የሚጠቀም ሁሉ የመረጃዎችን ትክክለኛነት ሳያረጋግጥ ለሌሎች ማጋራት ተገቢ አይደለም፡፡
ውሸትን መሠረት ያደረገ መረጃ የግል ሰብእናን ከመንካት አልፎ ቤተሰብን እስከመበተን፣ ሀገርን እስከማፍረስ ሊደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የመረጃውን እውነተኛነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የሚነበብ ሁሉ አይነበብም ወይም የሚታይ ሁሉ መታየት የለበትም፤ መምረጥ ያስፈልጋል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተግዳሮቶች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት ሳይሆን ከብዙ በጥቂቱ ለመዳሰስ ነው የሞከርነው፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያ ጉዳቶች እንዳሉት ሁሉ ጥቅሞችም አሉት፡፡ ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል ጥቂቶቹን ደግሞ እንመለከት፡-
ለ. የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቅሞች
፩. በቀላሉ ተደራሽ መሆኑ፡- በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቅ መረጃ ከተለቀቀበት ቅጽበት ጀምሮ በፍጥነት ለመላው ዓለም የመሰራጨት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በአንድ ቦታና ጊዜ ውስጥ ወደ ሁሉም በመድረስ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖዎችንም ይፈጥራል፡፡ በተለይም በአግባቡና በሥርዓቱ መጠቀም ከቻልን ጠቀሜታው አያጠያይቅም፡፡ አስደሳችም ይሁን አሳዛኝ ክስተት ወይም በዓለም ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን በቀላሉ ለማዳረስ ይረዳል፡፡
፪. መረጃን በቀላል ወጪ ማግኘትም መላክም ያስችላል፡- በዘመናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ በመምጣቱ ማንኛውም ሰው መረጃን በቀላል ወጪ በማግኘት እንዲሁም መልሶም በመላክ የመረጃ ልውጥን ማሳለጥ ያስችላል፡፡ ግለሰባዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ … ሌሎችም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መረጃዎች ብዙ ሳንደክም፣ ወጪም ሳያስወጣን እናገኛለን፡፡ ርቀት ሳይገድበው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ በአጭር ሰዓትና በቀላል ወጪ በአንድ ቅጽበት ለማስተላለፍ የምናደርገው ጥረት እጅግ ቀላል ያደርገዋል፡፡
፫. ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ (የመጻፍና የመናገር) ዕድልን ይሰጣል፡- ማኅበራዊ ሚዲያ ያየነውን፣ የሰማነውን፣ ያሰብነውንና ይሆናል ብለን የምንገምተውን ሐሳብ በነፃነት ለመግለጽ በሰፊው ዕድልን ይሰጣል፡፡ ይህ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ የሚገለጽ ሐሳብ ሌሎችን ሊጠቅምም ሊጎዳም ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በተለይም ጎጂ የፈጠራ ታሪኮችን በመፈብረክ ሆነ ተብሎ አንድን ሰው፣ ማኅበረሰብን፣ ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል መረጃ እስከማጋራት ይደርሳል፡፡ በተቃሪኒው ደግሞ በጣም ጠቃሚና ሰዎች ሊማሩበት፣ ደስ ሊሰኙበትና ይህንንም መረጃ ለሌሎች በማጋራት እነርሱ የተደሰቱትን ደስታ እንዲጋሩላቸው ያደርጋል፡፡
ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ይቻላል የሚለውን እሳቤ ብቻ ይዘንም መጓዝ አደጋውን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ከመጻፋችን ወይም ከመናገራችን በፊት ማንን ይጠቅማል? ማንንስ ይጎዳል? የማጋራው መረጃስ ምንጩ ትክክል ነው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምናጋራውም መረጃ በግልጽ ኃላፊነት መውሰድ ይገባል፡፡
ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ማለት እንደፈለጉ ሳያመዛዝኑና ሌሎችን ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል መረጃን መልቀቅ ወይም ጽፎ ማጋራት ሊያስጠይቅ እንደሚችል ባለመረዳት የሚፈጽሙት እንዳሉ ሁሉ ሆነ ብለው ሰውን ከሰው፣ ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ የሚያጋጩም ግለሰቦችና ድርጅቶችም ይኖራሉ፡፡ ለዚህ ነው በማኅበራዊ ሚዲያ በየትኛውም መንገድ የሚለቀቁ መረጃዎችን ምንጩን ማጣራት የሚያስፈልገው፡፡ አንድ መረጃ ምንጩ አይታወቅም ማለት አይቻልም፤ ግለሰብም ይሁን ድርጅት ተጠያቂነት እንዳለበት መረዳት ተገቢ ነውና፡፡ ስለዚህ በማንኛውም የማኅበራዊ ሚዲያ ቅርጾችና ማስተላለፊያ መንገዶች የተላለፉትን ሁሉ ማመን አይገባም፡፡ እያንዳንዱ የምንጽፈውና የምንናገረው እንዲሁም በድምጽ ወምስል የምናጋራው መረጃ ኃላፊነትን ወስደን፣ ተጠያቂነትም እንዳለብን ተረድተን በጥንቃቄ ልናጋራ ይገባል፡፡
፬. ትውልድን ለማነጽ፡- በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጭ መረጃ ትውልድን በማነጽ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደገለጽነው ተአማኒነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ በአግባቡ ከተጠቀምንበት የዕውቀት ምንጭ መሆን የሚችል ነው፡፡ መረጃ በተለየየ መንገድ እንደሚገኝ ሁሉ የርቀት ትምህርት፣ የገጽ ለገጽ ትምህርቶች፣ በተግባር የተደገፉ የድምጽ ወምስል ትምህርቶች እንዲሁም ዕውቀትን የሚያሳድጉ ልዩ ልዩ መረጃዎችን ለማግኘት ያስችላል፡፡
ዛሬ ዓለም ወደ አንድ መንደርነት ተለውጣለች ስንል ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን ርቀት ሳይገድበን በበይነ መረብ አማካይነት ገጽ ለገጽ መማር፣ ሥራ መሥራት፣… ያስችለናል፡፡
፭. በየጊዜው አድማሱን እያሰፋ ይሄዳል፡- በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መረጃዎች በቀላሉ ከአንዱ ወደ አንዱ በፍጥነት ስለሚሰራጩ (ስለሚጋሩ) ለብዙዎች የማየት፣ የማንበብ ዕድሉን እያሰፋው ይሄዳል፡፡ በተለይም ተአማኒ መረጃዎችን በማቅረብ የሚታወቅ ማኅበራዊ ሚዲያ ከሆነ መረጃውን የሚጋራው ሰው ብዛት ከቀን ወደ ቀን ቁጥሩን በማሳደግ ዘወትር አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የሚሹ ወገኖች ቁጥርም እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
፮. በማንኛውም ቋንቋ በቀላሉ መቅረብ የሚችል ነው፡- ቋንቋ መግባቢያ እንደመሆኑ መጠን በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሳብን ለመግለጽ በመጠቀሚያነት ይውላል፡፡ በዚህም መሠረት ያለምንም ችግር መረጃ ከአንዱ ወደ ሌላው ማጋራት ስለሚያስችል ቋንቋውን መረዳት፣ መስማትና ማንበብ ለሚችል ሰው ሁሉ በቀላሉ ይዳረሳል፡፡ ስለዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው ለማለት ያስችላል፡፡
፯. በርካታ በስስ ቅጂ (Soft copy) የተጻፉ መጻሕፍትን ማግኘት ያስችላል፡- በዓለም ላይ በየጊዜው በተለያዩ ዘርፎች ለንባብ የሚበቁ መጻሕፍት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተለያዩ ድረ ገጾች በግዢና በነጻ ለአንባብያን ስለሚቀርቡ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ መጻሕፍቱ እንደ ይዘታቸው ዓይነት የትምህርት፣ የጥናታዊና የምርምር ፣ የልብ ወለድ፣ የግጥም … ወዘተ ሊሆኑ ስለሚችሉ እያንዳንዱ ሰው እንደ ፍላጎቱ ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በቀላል ወጪ፣ በአጭር ጊዜ ማግኘት ስለሚቻል ድካምን ያቀላሉ፡፡ ስለዚህ ለማንኛውም ሰው በቀላሉ ማግኘትና መጠቀም የሚያስችል ነው፡-
፰. አማራጭ የንባብ መድረኮችን ይፈጥራል፡- ማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ መረጃዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ እንደ ተመልካቹ ፍላጎትና ምርጫ አማራጮችን በመጠቀም መረጃ ማግኘት ያስችላል፡፡ ለምሳሌ፡- በፌስቡክ የምናገኘውን በትዊተር ላናገኘው ስለምንችል አማራጮችን ያሰፋልናል፡፡ የሚቀርቡ መረጃዎች ሁሉ ጠቃሚ ናቸው ባይባልም አንባቢው ወይም ተመልካችና ሰሚው መርጦ የመጠቀም ነጻነትን ይሰጠዋል፡፡
፱. ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት ማቀራረብ የቻለ ነው፡- በዚህ ዘመን መረጃ ለማግኘት ብዙ ድካም አይጠይቅም፡፡ ማንኛውንም መረጃ በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በድምጽ ወምስል መረጃዎችን እንደየፍላጎታችን ከተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ማግኘት የሚያስችል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለምን ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ በአንድ ጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት እንደመቅረቡ ሁሉ በማንኛውም ጊዜና ሰዓት እንዲሁ ማግኘት፣ መረጃውን በማውረድ ደጋግሞ ማንበብ በሚያስችል ቅርጽ ይቀርባል፡፡ በዚህም ምክንያት በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ መመልከት የሚችሉት በመሆኑ መረጃ ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት መቀየር ችሏል ማለት ይቻላል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያ ከላይ የዘረዘርናቸውን ጥቅሞች ብቻ ለማንሣት ሞከርን እንጂ ሌሎችም ጥቅሞች እንዳሉት መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ለማኅበራዊ ሚዲያ ተጋላጭ ከሆኑ የኅበረተሰብ ክፍሎች በዋነኛነት በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኘው የማኅበረስብ ክፍል ነው፡፡ ወጣትነት በራሱ የእሳትነት ዘመን እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም ልሞክር የምንልበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ማንኛውንም ነገር ጥቅምና ጉዳቱን ለይቶ ለማወቅ ከመመርመር ይልቅ በስሜታዊነት የመጓዝና ቅጽበታዊ ምላሽ የሚሰጡበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡
አንድ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ግን ከእነዚህ ስሜቶች በመራቅ በሚጠቅሙና ትክክለኛ በሆኑት ላይ ብቻ ማተኮር ይጠበቅበታል፡፡ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ” (መክ. ፲፪፥፩) እንዲል ራስን በመግዛት ከእግዚአብሔር መንገድ ላለመውጣት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በተለያዩ ክፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከነፈሰው ጋር ከመንፈስ ይልቅ ተረጋግተው መረጃውን በመፈተሽ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡
ከትምህርት ውጪም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ማለትም ለትምህርት በሚያግዙ ሚዲያዎች የሚተላለፉትን መረጃዎችን እንደ ዐውዳቸው በመለየት በአጋዥነት ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ባላቸው የእጅ ስልክ ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለያቸውን ተግባር እንዳይፈጽሙበት መጠንቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጊዜአቸውን በከንቱ እንዳያሳልፉ በእረፍት ሰዓታቸው በአገልግሎት በማሳለፍ፣ መንፈሳዊውንም ጉዳይ እየተነጋገሩ የመተጋገዝ ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ መትጋት ይገባቸዋል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያ የፈጠራ ሥራን የማገዝ ዐቅሙ ከፈተኛ በመሆኑ የማኅበረሰብንና የቤተ ክስቲያንን ችግሮች ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በመፈብረክ ለጥቅም ማዋል ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ማኅበራዊ ሚዲያ ጥቅሞችም እንዳሉት ሁሉ ጉዳቶቹም ከፍተኛ መሆናቸውን በመረዳት ጥቅሞቹ ላይ ትኩረት በማድረግ ከወጣቶች (ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች) ብዙ ይጠበቃል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር