የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እና የምክክር መርሐ ግር ተካሄደ

በማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ አዘጋጅነት ለማእከላት ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ ለመደበኛ አስተባባሪዎች እና በዋናው ማእከል ለግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባሪያ አባላት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እና የምክክር መርሐ ግብር ከኅዳር ፫-፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ተካሄደ፡፡

በማኅበሩ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ሥልጠናም አዲሱን የማኅበሩን ተቋማዊ ለውጥ በተመለከተ በመጋቤ ሀብታት ታደሰ አሰፋ እና አቶ ግዛቸው ሲሳይ ለአንድ ቀን የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡ በዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ውጫዊና ውስጣዊ ከባቢያዊ ሁኔታን መሠረት አድርጎ አሁን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በማጤን ተቋማዊ ለውጡ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡ የማኅበሩ ለውጥ ከየት ወደ የት ትንተና የቀረበ ሲሆን አዲሱ የማኅበሩ ርእይ፣ ተልእኮ፣ ዕሴት እና ዓላማም በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በቀረበው ገለጻ መነሻነትም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ የተሰጣቸው ሲሆን፤ የቡድን ውይይት፣ እንዲሁም ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ የልምድ ልውውጥ እና የምክክር መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

እሑድ በነበረው መርሐ ግብርም “ውጤታማ መሪነት እና የመሪነት ችሎታ፤ Effective leadership & leadership skill” በሚል ርእስ በመጋቤ ሀብታት ታደሰ አሰፋ እንዲሁም “ተግባቦት፤ Communication” በሚል ርእስ በዶ/ር ወርቁ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተሰጡት ሥልጠናዎች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበው በጥናት አቅራቢዎቹ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በሥልጠናው ላይ ተሳታፊዎች ከነበሩት አባላት መካከል ቆይታቸውን በተመለከተ ሲገልጹ “ከአቀባበሉ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው መልካም ጊዜን አሳልፈናል፡፡ ተቋማዊ ለውጡ ላይ ያለንን ብዥታ ያጠራንበት፣ በሌሎቹም በተሰጡን ሥልጠናዎች በቂ ዕውቀት መጨበጥ ችለናል፡፡ በተለይም ያካሄድናቸው የልምድ ልውውጦች ለአገልግሎት እንድሣሣ እና እንድንበረታ የሚያደርጉን ናቸው” በማለት ገልጸዋል፡፡

በዚህ መርሐ ግብር ከ፴፩ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት የተውጣጡ ፵፫ ተሳታፊዎች የተካፍለዋል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *