ቅዱስ መስቀል
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡
መስቀል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ኃጢአት ያስወግድ ዘንድ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ መሰቀሉን፣ ተጣልተው የነበሩትን ሰባቱ መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን፣ መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) ያስታረቀበት ነው፡፡ በቀራንዮ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም“ (ዮሐ. ፲፭፥፲፫) እንዲል፡፡ በዚህም የመዳን ምልክት መሆኑ የተረጋገጠበት በክርስቶስ ደም የተቀደሰ፣ የጠብ ግድግዳን ያፈረሰ፣ ቅድስናና ክብር ያለው የአበው ተስፋ የተፈጸመበት፣ ሰው ከውድቀቱ መነሣቱን የተበሰረበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ታላቅ ክብር ይሰጠዋል፡፡ የመስቀል በዓልም ከጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ ሲሆን በየዓመቱ መስከረም ፲፯ ቀን ይከበራል፡፡ በዋዜማውም ደመራ በመደመር፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውነተ ቤተ ክርስቲያን መምህራን፣ ካህናትና ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እንዲሁም ምእመናን ጋር በመሆን በአደባባይ በጸሎት፣ በትምህርትና በዝማሬ በድምቀት ታከብረዋለች፡፡
የደመራው መደመር ምክንያትም ስንመለከት፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አይሁድ በምቀኝነት ተነሣስተው ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ሰውረው ቀብረውት ስለነበር የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስና ፈቃዱ ሲሆን ቦታው የተገኘበትን ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ በዓል ሆኖ ይከበራል፡፡ በ፫፻፳፮ ዓ.ም የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ፣ ኪራኮስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት ደመራ አስደምራ በዕጣን ጢስ ተመርታ ጢሱ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ማመልከቱን በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን መስከረም ፲፮ ቀን የደመራ በዓልን ታከብራለች፡፡
ንግሥት ዕሌኒ በጭሱ ምልክትነት መስቀሉ ያረፈበትን ቦታ ካረጋገጠች በኋላ መስቀሉን ለማውጣት መስከረም ፲፯ ቀን በማስጀመር ለሰባት ወራት ያህል በማስቆፈር በመጋቢት ፲ ቀን እንዳስወጣቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ታሪክ ተከትሎ እንደሆነ ሊቃውንቱና ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡
ቅድስት ዕሌኒ በምልክቱ መሠረት ተራራውን ስታስቆፍር የተገኙት ሦስት መስቀሎች ናቸው፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ሁለት ወንበዴዎች ከተሰቀሉበት መስቀል ለመለየትም ባደረገችው ጥረት የጌታችን መስቀል ድውያንን ፈውሷል፣ አንካሳ አበርትቷል፣ ጎባጣን አቅንቷል፣ የዕውራንን ዐይን አብርቷል፡፡
ስለ መስቀሉ ስናነሣ በዘመነ ብሉይ የመባረኪያ ምልክት እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን በእምነት ባርካቸው” እንዲል፡፡ በተጨማሪም ዮሴፍ አባቱ ያዕቆብ ልጆቹን ይባርክለት ዘንድ ባቀረባቸው ጊዜ “የሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፤ ኤፍሬምንም በቀኙ፣ ምናሴንም በግራው አቆማቸው፤ ወደ አባቱም አቀረባቸው፡፡ እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፣ እርሱም ታናሽ ነበረ፤ ግራውንም በምናሴ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ። ያዕቆብም ባረካቸው” ይላል፡፡ (ዘፍ. ፵፰፥፲፩፤ ዕብ. ፲፩፥፳፪)
መስቀል በብሉይ ኪዳን ለወንጀለኞች መቅጫነት አገልግሏል፣ በመስቀል የተመሰለው የሙሴ በትርም ባሕር ከፍሏል፣ ጠላት አስጥሟል፣ መና አውርዷል፣ ደመና ጋርዷል፣ ውኃ ከዐለት አፍልቋል፣ በግብፃውያን ላይ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡
በሐዲስ ኪዳንም አይሁድ ወንጀለኞችን የሚቀጡት በውግራት፣ በእሳት ማቃጠል ቢሆንም በመስቀልም ይቀጡ ነበር፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች አይገረፉም፤ በመስቀል ይቀጡ ነበር፡፡ ከተገረፉ ደግሞ አይሰቀሉም፡፡ (ዘዳ. ፳፩፥፳፩-፳፫) በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ግን ከሕጋቸው ውጭ ገርፈውታልም ሰቅለውታል፡፡
የቅዱስ መስቀሉ በረከት ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!