lideteEgzie

እድለኞቹ እረኞች /ለሕፃናት/

ጥር 3/2004 ዓ.ም

በእኅተ ፍሬስብሐት
lideteEgzie
በአንድ ምሽት በቤተለሔም አካባቢ እረኞች በጎቻቸውን ተኩላዎች እንዳይበሉባቸው ይጠብቁ ነበር፡፡ እኩለ ሌሊት ሲሆን በዚያ አካባቢ ልዩ ብርሃን ታየ፡፡ እረኞቹ ያንን ብርሃን ሲያዩ በጣም ተገረሙ፡፡ በዚያም መልአክ መጣ እና በዚያች ሌሊት የዓለም መድኀኒት የሚሆን ሕፃን መወለዱን፤ ያም ሕፃን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ለእረኞቹ ነገራቸው፡፡ እረኞቹም ተደሰቱ ፈጥነው ሕፃኑ ወደ ተወለደበት ወደ ቤተልሔም ሔዱ፡፡ መልአኩ ቦታውን ነግሯቸው ነበር፡፡ በዚያም ሲደርሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕፃኑን ታቅፋ አገኟት፡፡ በአጠገቧም አንድ ሽማግሌ ሰው ቆሞ ነበር፡፡ ያ ሽማግሌ እመቤታችንን ይጠብቃት የነበረው ዮሴፍ ነበር፡፡ እረኞቹም ወደ ሕፃኑ ቀርበው ሰገዱለት ምስጋናም አቀረቡ፡፡
yesemayu_bm

የሰማዩ ቤተ መንግሥት (ለህጻናት)

15/04/2004 ዓ.ም

በእኅተ ፍሬስብሐት

 

በህንድ ሀገር ታከሻሊላ በተባለ ከተማ ጎንዶፓረስ የተባለ ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ስለ ነበረው የንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት ዝና እየሰማ እርሱም በሀገሩ ማሠራት ይፈልግ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነጋዴዎች በየሀገሩ ሲጓዙ የታወቀ ግንበኛ  እንዲያመጡለት አዘዛቸው፡፡

 

ይህንን መልእክት ከሰሙት ነጋዴዎች መካከል አንዱ ፋርስ ወደሚባለው ሀገር ተጓዘ ከዚያም ያ ነጋዴ አንዱ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን አገኘው፡፡ ነጋዴው ቶማስ ከኢየሩሳሌም እንደመጣ ሲሰማ የግንበኝነት ሙያ ይችል እንደሆነ ጠየቀው፤ ሐዋርያው ቶማስ ወደ ህንድ ሄዶ ማስተማር ይፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህም ይህንን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ለመሔድ “በኢየሩሳሌም ሳለሁ ህንፃ በመገንባት እኖር ነበር፡፡” አለው፡፡

ነጋዴውም በጣም ተደስቶ ቶማስን ወደ ህንድ ወሰደው፡፡ ንጉሡም የቶማስን ሙያ ሲሰማ በጣም ደስ አለው፡፡ ከዚያም ከከተማው አጠገብ ወደሚገኘው ሔዶ ቶማስን ወሰደውና በጫካ የተሞላውን ሜዳ እያሳየ ቤተ መንግሥቱ በዚያ ቦታ ላይ እንዲሠራ ነገረው፡፡ ቅዱስ ቶማስ የቤተ መንግሥቱን አሠራር ሲነግረው ንጉሡ ተሠርቶ እስከሚያየው ቸኮለ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሡ ለህንጻው መሥሪያ ብዙ ገንዘብ ለቅዱስ ቶማስ ይልክለት ጀመር፡፡

 

ቅዱስ ቶማስ ግን ገንዘቡን ሲያገኝ የሚሔደው ወደ ድሆች መንደር ነበር፡፡ በዚያም ለተራቡት ምግብ፣ ልብስ ለሌላቸው ልብስ፣ መጠለያ ቤት ለሌላቸው ደግሞ ቤት እየገዛ መስጠት ጀመረ፡፡ የታመሙትን እያዳነና እየስተማረ ይኖር ጀመረ፡፡

 

yesemayu_bm

 

ንጉሥ ጎንዶፓረስ ለሕንፃው መሥሪያ የመደበው ገንዘብ እና ጊዜ እንዳለቀ፣ ቤተ መንግሥቱን ሊጎበኝ መጣ፡፡ ወደ ቦታው ደርሶ ቢመለከት እንኳን ሕንፃው ሊሠራ ጫካው አልተነካም፡፡ ንጉሡም በዚያ የሚያልፍ መንገደኛ ጠርቶ ቶማስ የታለ? ሲል ጠየቀው፡፡

 

“ቶማስ በድሆች መንደር የተቸገሩትን እየረዳና እያስተማረ ይገኛል፡፡” ሲል መንገደኛው መለሰለት፡፡ “እርሱስ ጥሩ ግን የሰራልኝ ቤተ መንግሥት የታለ?” ብሎ መንገደኛውን ጠየቀው፡፡ መንገደኛውም “በድንጋይ የተሠራ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፤ ጌታዬ፤ ነገር ግን ሕዝብዎ በጣም እንደተደሰተ መመልከት ይችላሉ፡፡” አለው፡፡

 

በዚህ ጊዜ ንጉሡ ያ ሁሉ ገንዘብ እንደባከነበት መጠራጠር ጀመረ ወዲያው ወታደሮቹ ቶማስን ፈልገው እንዲያመጡ ላካቸው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ተይዞ እንደመጣ “ቤተ መንግሥቴን ለምን አልሠራህልኝም ጫካው እንኳን መቼ ተነሣ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ቶማስም “በእርግጥ በምድር ላይ የድንጋይ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን በሰማይ ላይ ቤተ መንግሥት ሠርቼሎታለሁ፡፡” አለው፡፡

 

ያን ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ፤ ቶማስን እጅ እግሩን እንዲያሰቃዩት አዞ እስር ቤት አስገባው፡፡ በዚያች ሌሊት የንጉሡ ወንድም ልዑል ጋድ በድንገት ታሞ ሞተ፡፡ የጋድ ነፍስ በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማያት ወጣች፡፡ የጋድን ነፍስ ካጀቧት መላእክት አንዱ ብዙ ቤተ መንግሥታትን እያሳያት “እንድትኖሪበት ደስ ያለሽን ምረጪ፡፡” አላት፡፡ የጋድ ነፍስም ከቤተ መንግሥታቱ ሁሉ የሚያምረውን መረጠች “ይህ ቤተ መንግሥት የአንቺ አይደለም፤ ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፓረስ የሠራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው፡፡”

 

ጋድ ሊቀብሩት በተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነሣ፡፡ ከዚያም ያየውን ሁሉ ለንጉሡ እና ለተሰበሰቡት ሰዎች ነገራቸው፡፡

 

ንጉሡ ይህን ሲሰማ በቶማስ ላይ በሠራው ሁሉ አዘነ፣ ያሰበው ቤተ መንግሥት መሠራቱን ሲሰማ ቶማስን ከእስር ቤት አስመጣው፡፡ እራሱ እና ቤተሰቡም በክርስቶስ አምላክነት አምነው ተጠመቁ፡፡ ለቶማስም ያለውን ገንዘብ ሁሉ “ሌላም ቤተ መንግሥት ሥራልኝ” እያለ ይሰጠው ጀመር፡፡ የሀገሩ ሰዎችም እንደርሱ ያደርጉ ጀመር፡፡

 

የተቸገሩትን መርዳት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መልካም ሥራ ነው፡፡ የተቸገሩ ሰዎችን የምንረዳ ከሆነ ደግሞ በምድር ላይ አይተነው የማናውቀውን እጅግ በጣም ያማረ ቤት ያሰጠናል፡፡

 

ደጉ ሰው (ለሕፃናት)

ታኅሣሥ 6/2004 ዓ.ም

በእኅተ ፍሬስብሐት

በአንድ ወቅት አንድ ሰው ከሚኖርበት ከተማ ተነሥቶ ለንግድ ወደ ሌላ ሀገር ጉዞ ጀመረ በጉዞው ወቅትም ሌቦች ከሚኖርበት ዋሻ አጠገብ ደረሰ፡፡ ሌቦቹም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ከዋሻው ወጥተው ደበደቡት፡፡ የያዘውን ገንዘብ በሙሉ ቀሙት፡፡ ልብሱንም ገፈው በዚያው ጥለውት ሄዱ፡፡ የተጎዳው ሰው መንቀሳቀስ ስላቃተው በዚያ ቆየ፡፡ እየመሸ ሲሄድ አንድ ሰው በዚያ ሲያልፍ አየ፡፡ መንገደኛውን ሲያየው “እርዳኝ! እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ መንገደኛው ግን ምንም ሳይረዳው ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሌላ መንገደኛ መጣ፡፡ የተጎዳው ሰው አሁንም “እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ መንገደኛው ግን አሁንም ምንም ሳይረዳው ጉዞውን ቀጠለ የተጎዳው ሰው የሚረዳው ሰው አጥቶ ሲያዝን ሳለ ሌላ መንገደኛ መጣ፡፡ መንገደኛው የተጎዳውን ሰው ሲያይ በጣም አዘነ፡፡ ከፈረሱ ላይ ወርዶ ወደ ሰውየው ሄደ፡፡ ከዚያም በቁስሉ ላይ መድኀኒት አደረገለት እና እንዳያመው በጥንቃቄ ይዞ በፈረሱ ላይ ጫነው፡፡ ከዚያም በአካባቢው ወዳለ ቤት ወሰደው፡፡ ለቤቱ ባለቤትም እሱ እስከሚመለስ በሽተኛውን እንዲንከባከቡለት አደራ ብሎ ሰጣቸው፡፡ ለሚንከባከቡትም ገንዘብ ከፈላቸው እና ሔደ፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ሁላችሁም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፡፡ ለሁሉም ሰውም መልካም ነገርን አድርጉ፡፡”

ዓሣ አጥማጁ ስምዖን(ለሕፃናት)

በአዜብ ገብሩ

በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ ጌታችን በባህር ዳር ቆሞ ሕዝብን ያስተምር ነበር ሕዝቡም ጌታችን የሚያስተምረውን ትምህርት በደንብ ይከታተሉት ነበር፡፡ ጌታችንም ድምጹ ለብዙ ሰዎች እንዲሰማ ወደ ስምዖን ታንኳ ላይ ወጣ፡፡ በታንኳይቱም ውስጥ ተቀምጦ ሕዝቡን አስተማራቸው፡፡ ትምህርቱንም ሲጨርስ ሁሉም ሰው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ሲማሩ ከነበሩት መካከል አንዱ ስምዖን ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ሌሊቱን ሁሉ ምንም ዓሣ ስላላጠመደ ተጨንቆ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ ልጆች የስምዖን ቤተሰቦች ስምዖን የሚያመጣውን ዓሣ ይጠባበቁ ስለነበረ ነው፡፡ ስምዖን ዓሣ ሳይዝ ወደ ቤቱ ከገባ ቤተሰብ ሁሉ ሳይበላ ነው የሚያድረው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ልጆች እግዚአብሔር የስምዖን ቤተ ሰቦች ተርበው እንዲያድሩ አላደረጋቸውም፡፡

 

ሌላው ደግሞ ልጆች ስምዖን ታንኳውን ጌታችን እንዲያስተምርበት ትቶለት ነበር፡፡ በጣም ታዛዥ ስለነበር እግዚአብሔር ዝም አላለውም፡፡ ጌታችን ስምዖንን መረብህን ጣልና ዓሣ አጥምድ አለው፡፡ ስምዖንም “መምህር ሌሊቱን ሁሉ ደክሜያለሁ ነገር ግን ምንም ዓሣ አልያዝኩም አንተ ስላዘዝከኝ ግን መረቤን እጥላለሁ” አለው፡፡ ስምዖን ምንም እንኳን ይሆናል ብሎ ባያምንም ለጌታችን ግን ታዘዘው፡፡ እንዳዘዘውም ባደረገ ጊዜ መረብ እስኪቀደድ ዓሣ ያዘ፡፡ ስምዖንም ይህን አይቶ ለጌታችን ሰገደለት፡፡ ከስምዖን ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በአዩት ነገር ተደነቁ፡፡

 

አያችሁ ልጆች ስምዖን ጌታችን ያለውን ነገር ሁሉ ስላደረገ ሌሊቱን ሙሉ ማጥመድ ያቃተውን ዓሣ መረብ እስኪቀደድ ድረስ ማጥመድ ቻለ፡፡ እኛም እግዚአብሔር አምላክ የሚያዘውን ነገር ብንሠራ ከምንፈልገው በላይ ይሰጠናል፡፡

ልጆች በመጨረሻም ዓሣ አጥማጅ የነበሩት ስምዖን ያዕቆብና ዮሐንስ ዓሣ ማጥመዳቸውን ትተው ጌታችንን ተከተሉት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አትዋሹ(ለሕፃናት)

 

በአዜብ ገብሩ

በድሮ ጊዜ ክርስቲያኖች በአንድነት ይኖሩ ነበር፡፡ በመካከላቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር አንጂ “ይህ የእኔ ገንዘብ ነው” የሚል አልነበረም ከእነርሱም አንድም ችግረኛ አልነበረም፤ ቤትና መሬት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ ገንዘቡን ያመጡ ነበር፡፡

 

 

አምጥተውም በሐዋርያት እግር ስር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ሐዋርያትም ለእያንዳንዱ እንደፍላጎቱ ይሰጡ ነበር፡፡ ሐዋርያት ስሙን ዮሴፍ እያሉ የሚጠሩት በርናባስ የተባለ ሰው ነበር፡፡ የእርሻ መሬትም ነበረው፡፡መሬቱንም ሸጦ ገንዘቡን በሐዋርያት እግር ስር አስቀመጠው ከሐዋርያትም ማኅበር ተቀላቀለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ልጆች ሐናንያና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ባልና ሚስቶች መሬታቸውን ሸጡ፡፡ እርስ በርሳቸውም ተማከሩና ከሸጡት ዋጋ ግማሹን ለራሳቸው ወሰዱና የሸጥነው በዚህ ዋጋ ነው ብለው ግማሹን በሐዋርያት እግር ስር አስቀምጠው ከማኅበሩ ለማቀላቀል ይዘው ሄዱ፡፡ ያደረጉትን ማንም የሚያውቅባቸው አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ ነገር እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ውስጥ ነበርና ያደረጉትን ነገር ያውቅ ነበር፡፡

 

ቅዱስ ጴጥሮስም ለሐናንያ እንዲህ አለው “ሰውን ሳይሆን መንፈስ ቅዱስን ለምን ታታልላለህ መጀመሪያም ሳትሸጠው ያንተ አልነበረምን አሁንስ ከሸጥነው በኋላ ያንተ አይደለምን ይህንን ነገር ለምን በልብህ አሰብሀ” አለው ሐናንያም ይህን በሰማ ጊዜ ወድቆ ሞተ፤ ሰዎችም ተሸክመው ወስደው ቀበሩት፡፡ ይህ ከሆነ ከሦስት ሰዓት በኋላም ሚስቱ ሰጲራ መጣች፡፡ ባልዋ የሆነውን ሳታውቅ ገባች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “እስኪ ንገሪኝ መሬታችሁን የሸጣችሁት በዚህ ዋጋ ነውን” አላት፡፡ እርሷም “አዎ” አለች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “የእግዚአብሔርን መንፈስ ትፈታተኑት ዘንድ እንዴት ተባበራችሁ አነሆ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች በበር ናቸው አንቺንም ይወስዱሻል” አላት፡፡ ወዲያውም ወድቃ ሞተች፤ ሰዎቹም ወስደው ቀበሩአት፡፡

 

ልጆች እኛም ውሸት ስንናገር እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ሥራ እየሰራን እና የሌሎች ሰዎችን እምነት እያጣን መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ የምንዋሽ ከሆነ እግዚአብሔር በጣም ስለሚወደን ከውሸታችን እንድንመለስ ይታገሰናል፡፡ ካልተመለስን ግን በረከቱን ከእኛ ይወስድብናል፡፡ ስለዚህ ይህን ማስወገድ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እንግዳ ተቀባዩ አባ ቢሾይ(ለሕፃናት)

ሐምሌ23፣2003 ዓ.ም
                                                                               አዜብ ገብሩ

እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ጻድቅ ከሆኑ ሰዎች የተወለደ አባ ቢሾይ የሚባል አባት ነበረ፡፡ ይህ አባት ለቤተሰቦቹ ሰባተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ አንድ ሌሊት ምን ሆነ መሰላችሁ ልጆች የአባ ቢሾይ እናት ሕልም አየች የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸ፡፡ ጌታ እንዲህ ብሏል፤ “ያገለግለኝ ዘንድ ከልጆችሽ አንዱን ስጭኝ” እናቱም እንዲህ አለች “ሰባቱም ልጆቼ አሉ፤ የፈለግኸውን መርጠህ እንዲያገለግልህ ውሰድ”
መልአኩም አባ ቢሾይን ነካው፤ እናቱ ግን እንዲህ አለች “ከልጆቼ ሁሉ እርሱ ደካማ ነው፤ እግዚአብሔርን የበለጠ እንዲያገለግሉት ከሌሎቹ ልጆቼ ምረጥ” መልአኩም እንዲህ አላት “እግዚአብሔር ያገለግለው ዘንድ የመረጠው እርሱን ነው” ከዚያም አባ ቢሾይ ሃያ ዓመት ሲሆነው ወደ ገዳም ገባ፡፡ አባ ቢሾይ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነ ሰው ነበረ፡፡ ሁሌም ይጸልያል፣ ለረዥም ሰዓት ይጾማል፣ ቅዱሳት መጻሕፍን ይማራል፣ በቤቱ እንግዳ ተቀብሎ ያስተናግዳል፡፡ እግዚአብሔርን የሚያስደስት  ብዙ መልካም ሥራ ይሠራል፡፡

 

ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቢሾይ ከበአቱ በር ላይ ተቀምጦ ሳለ በጣም የደከመው ሰው ወደ እርሱ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ ከተቀመጠበት ተነሣና ያን ሰው ወደ በአቱ እንዲገባና እንዲያርፍ ጠየቀው፡፡ ከዚያም ያን በጣም የደከመው ሰው ውሃ አቅርቦ እግሩን ማጠብ ጀመረ፡፡ እግሩን እያጠበው ሳለም የእግዚአብሔር ድምጽ እንዲህ ሲል ሰማ “የተወደድክ ልጄ ቢሾይ ሆይ አንተ የተከበርክ ሰው ነህ” ወዲያውም የአምላካችንን እግር እያጠበ እንደነበር አስተዋለ፡፡ ተንሥቶም ተንበረከከ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ እግዚአብሔርም ሰላምን ሰጠው፡፡
 
አያችሁ ልጆች አባ ቢሾይ እግዚአብሔርን አየው ምክንያቱም ትሑት ስለነበረና ዝቅ ብሎ የሌሎችን ሰዎች እግር ያጥብ ስለነበረ ነው፡፡ እኛም እንደ አባ ቢሾይ ትሑት መሆንና ወደቤታችን ለሚመጡት ሰዎች ሁሉ ደግ መሆን አለብን ይህን ካደረግን እግዚአብሔር ለእኛ መልካምን ነገር ያደርግልናል፡፡ በመንግሥተ ሰማይም ስለ ሠራነው መልካም ነገር ሽልማትን ይሸልመናል፡፡

                                                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር  

የእግዚአብሔር ኃይል(ለሕፃናት)

ሰኔ15 ፣2003 ዓ.ም

ከእመቤት ፈለገ
 
በእስራኤል ሀገር ውስጥ አክዓብ የሚባል ንጉሥ ነበር፡፡ ንጉሡም በዓል የሚባል ጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን አሳዘነው፡፡ በዚሁ ሀገር ውስጥ የሚገኝ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚፈጽም ኤልያስ የሚባል ነቢይ ነበር፡፡ ንጉሡና ሕዝቦቹ እግዚአብሔርን እንዳስቀየሙት ባየ ጊዜ ዝናብ እንዳይዘንብ ጸለየ፡፡ ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረም፡፡ ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት “አክዓብ ጋር ሂድ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ” ብሎ እግዚአብሔር ለኤልያስ ነገረው፡፡ በአገሪቱም ውስጥ ከፍተኛ ረሃብ ሆኖ ነበር፡፡

አብድዩ የሚባል እግዚአብሔርን የሚፈራ የንጉሡ አገልጋይ ነበር በመንገድ ሲሄድ ነቢዩ ኤልያስን አገኘው፡፡ አብድዮም ሮጠና የአክብሮት ስግደት ሰገደለት፡፡

ነቢዩ ኤልያስም “ሂድና ለጌታህ ኤልያስ እዚህ አለልህ” ብለህ ንገረው አለው፡፡ አብድዩም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ አክአብም ነብዩ ኤልያስን እንዳገኘው “አስራኤልን የምትበጠብጠው አንተ ነህ” አለው ይህንን ያለበትም ምክንያት ዝናብ ለረጅም ጊዜ ስላልነበረ ነው፡፡ ልጆች እንደምታውቁት ዝናብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እስራኤልን ሲበጠብጧት የነበሩት ግን ሕዝቦቹና ንጉሡ ነበሩ ምክንያቱም እግዚአብሔርን ክደው ሌላ አምላክ /ጣዖት/ ማምለክ ጀምረው ነበር፡፡

ነቢዩ ኤልያስ አክአብን አራት መቶ ሃምሳ የጣዖቱን /የበአልን/ ነቢያትን እንዲጠራቸው ለንጉሡ ነገረውና በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፡፡ ከዚያም ነቢዩ ኤልያስ እንዲህ አላቸው “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍኩት እኔ ብቻ ነኝ፣ በእናንተ በኩል ግን አራት መቶ ሃምሳ ነቢያት አሉ፡፡ አንድ በሬ ውሰዱ አርዳችሁም በእንጨት ላይ አስቀምጡትና አምላካችሁን እየጠራችሁ ጸሎት አድርጉ እሳት አታንዱበት ከሰማይ አምላካችሁ እሳት አውርዶ ያዘጋጃችሁትን ነገር ከበላው እኔ በእናንተ አምላክ አምናለሁ፡፡ ይሄ ካልሆነና እኔ በአምላኬ በእግዚአብሔር ስም ጸልዬ ያዘጋጀሁትን እሳት ከሰማይ ወርዶ ከበላው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው ተስማማ፡፡

በአልን ያመልኩ የነበሩት 450 የሐሰት ነብያት ቀኑን ሙሉ ቢጸልዩ ምንም ለውጥ አላመጡም፡፡

ነቢዩ ኤያልስ እሳት ከሰማይ ወርዶ እርሱ  ያስቀመጠውን እንዲወስደው ብዙ ውሃ አደረገበት፡፡ ልጆች እንደምታውቁት ውሃ እሳትን ያጠፋል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸሎት አደረገ፡፡  እግዚአብሔር አምላክ ሆይ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህንና እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ሆይ እባክህ ስማኝ ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ እንጨቱን፣ ድንጋዩን፣ ዐፈሩን፣ ፈጽማ በላች በጉድጓድ ውስጥ ያለውን ውሃ ላሰች፡፡

ሕዝብም ሁሉ ይህን ሲያይ በግንባራቸው ተደፍተው አምላከ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው አሉ፡፡

አያችሁ ልጆች እግዚአብሔር በጣም ኃያል አምላክ ነው፡፡ እኛም የእርሱ ትእዛዛት የምንፈጽም ከሆነ ለእኛም ጥሩ ነገሮችን ማድረግ እንድንችልኃይል ይሰጠናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

አጭሩ ዘኪዮስ(ለሕፃናት)

ሰኔ11 ፣2003 ዓ.ም

አዜብ ገብሩ

ዘኪዮስ የሚባል አጭር ሀብታም ሰው ነበረ፡፡ ኢየሱሱ ክርስቶስን ለማየት በጣም ይፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ስለ እርሱ ብዙ ነገር ሲነገር ይሰማ ስለነበረ ነው፡፡ ጌታችን በዛሬው ዕለት ኢያሪኮ ወደምትባለው ከተማ ይገባል ብለው ሰዎች ሲያወሩ ዘኪዮስ ሰማ፡፡

ዘኪዮስም ይህን ሲሰማ ከቤቱ ጌታችንን ለማየት ወጣ፡፡ ከሩቅም ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ሲመጡ  አየ፡፡ “ምንድን ነው ነገሩ?” ብሎ ጠየቀ ሰዎቹም ጌታችን እየመጣ እንደሆነ ነገሩት፡፡ ዘኪዮስም ጥቂት ካሰበ በኋላ እንዲህ አለ፡፡ “እኔ አጭር ነኝ ከዚህ ሁሉ ከተሰበሰበው ሰው ለይቼ ጌታችንን እንዴት ላየው እችላለሁ?” ከዛም ወደ ተሰበሰበው ሰው ተጠጋና አንድ የሾላ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ልጆች ዛፉ በጣም ረዥም ስለሆነ ለመውጣት አስቸጋሪ ነበር፡፡

ዘኪዮስ ግን ጌታችንን ለማየት ካለው ፍላጎት የተነሳ በብዙ ጥረት ዛፉ ላይ ወጣ፡፡ የተሰበሰበው ሰው ዘኪዮስ ወዳለበት ዛፍ መጠጋት ጀመረ፡፡ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች ጌታችንን ከበውት ነበር፡፡ ጌታችንን በጣም ስለሚወዱት ከእርሱ አይለዩም ነበር፡፡ የተሰበሰበው ሰው የሾላውን ዛፍ ማለፍ ጀመረ፡፡ ጌታችን ግን ቆመ፡፡ ቀና ብሎም ዘኪዮስን ተመለከተው፡፡ “ዘኪዮስ ሆይ ና ውረድ” ብሎም ጠራው፡፡ ዘኪዮስም በደስታ ከዛፉ ላይ ወረደ ከዛም ጌታችን ለዘኪዮስ እንዲህ አለው “ዛሬ ወደቤትህ እገባለሁ፡፡ ከአንተ ጋርም ራት  እበላለሁ፡፡” ዘኪዮስም በደስታ ተቀበለው በቤቱም አስተናገደው፡፡

ልጆች ጌታችን እኛ ስለራሳችን ከምናስበው በላይ እርሱ ለእኛ እንደሚያስብልን ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡ ዘኪዮስ የፈለገው ጌታችንን ማየት ብቻ ነበር፡፡ ጌታችን ግን ከማየትም አልፎ ከእርሱ ጋር ራት እንደሚበላ ነገረው፡፡ ዘኪዮስ ካሰበው በላይ ጌታችን መልካም ነገርን አደረገለት፡፡ ሌላው ደግሞ ልጆች እንደዘኪዮስ እንግዳ ተቀባይ መሆን አለባችሁ፡፡ ዘኪዮስ ጌታችንን ደስ ብሎት እንዳስተናገደው እናንተም ወደቤታችሁ የመጣውን ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሀብታም ድሃ ብላችሁ ሳትለዩ ሁሉንም በፍቅር ማስተናገድ አለባችሁ፡፡ በሉ እንግዲህ ልጆች በሌላ ጽሑፍ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጰራቅሊጦስ(ለሕፃናት)

ሰኔ 07 2003 ዓ.

አዜብ ገብሩ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላም  አደረሳችሁ፡፡

ከትንሣኤ በኋላ ያለው ሃምሳኛው ቀን ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡ ይህ ዕለት ጌታ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ያወረደበት ዕለት ነው፡፡ ልጆች ጌታ ከሞት ከተነሣ በኋላ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት በቅዱስ ማርቆስ እናት ቤት ከሰባሁለቱ አርድዕት አና ከሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳን አንስት ጋር በመሆን ይጸልዩ ነበር፡፡ ጌታም በተለያየ ጊዜ እየተገለጸ ያስተምራቸው ነበር፡፡ አጽናኝ የሆነውን ቅዱስ መንፈስም እንደሚልክላቸው ይነግራቸው ነበር፡፡


ታዲያ ልጆች ሐዋርያት በዚያ ተሰብስበው እየጸለዩ ሳለ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ንፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፡፡ መንፈስ ቅዱስም  በእሳት አምሳል በሐዋርያት ላይ ሞላባቸው፡፡ ከዚያም ሐዋርያት በተለያየ ቋንቋ መናገር ጀመሩ፡፡ በዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሐዋርያት በተለያየ ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተው በጣም ተደነቁ፡፡ ሐዋርያትም ለተሰበሰቡት ሰዎች በየራሳቸው ቋንቋ አስተማሯቸው፡፡ ሰዎቹም በክርስቶስ አምነው ክርስቲያን ሆኑ፡፡
ልጆች ይህን ለሐዋርያት የወረደውን መንፈስ እኛም ጥምቀትን ስንጠመቅና ቅዱስ የሆነውን ሜሮን ስንቀባ እንቀበለዋለን፡፡ ይህ ቅዱስ የሆነው መንፈስም ከእኛ ጋር ሆኖ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀናል፡፡ ኃጢአት እንዳንሠራም ይጠብቀናል፡፡ እንቢ ብለን ኃጢአትን ብንሠራ ሰው ብንሳደብ፣ ለታላላቆቻችን ባንታዘዝ፣ ውሸት ብንናገር፣ የጓደኛችንን ዕቃ ብንሰርቅ፣…/ ይህ ቅዱስ የሆነው መንፈስ ከእኛ ይሸሻል፡፡ ስለዚሀ ልጆች ሁል ጊዜ መልካም የሆነ ነገር ብቻ መሥራት አለብን ማለት ነው፡፡ ይህን የመሰለ ስጦታ የሰጠንን እግዚአብሔርንም ልናመሰግነውና ልናከብረው ይገባል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እናትና አባትህን አክብር (ለህጻናት)

ግንቦት 30/2003 ዓ.ም.

                                  በአዜብ ገብሩ
“እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፣ መልካምም እንዲሆንልህ እናትና አባትህን አክብር፡፡” ዘዳግም 5÷16
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች ደህና ናችሁ የዛሬው ጽሑፋችን እናትና አባትን ስለማክበር ነው በደንብ ተከታተሉን፡፡
ልጆች ከአሥርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ እናትና አባትህን አክብር የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር እናትና አባታችንን ካከበርን ሽልማት እንደሚሰጠን ነግሮናል፡፡ ሽልማቱም በምድር ላይ ስንኖር ዕድሜያችን ረዥም እንደሚሆንና፤ በዚህ ዕድሜያችንም መልካም የሆነ ነገር እንደሚያደርግልን ነው፡፡ ለእናትና ለአባታችን ስንታዘዝ እግዚአብሔር ሽልማት እንደሚሸልመንና በእኛ እንደሚደሰት ሁሉ ካልታዘዝን ደግሞ ያዝንብናል፡፡ አዎ! እናትና አባቱን የማያከብር፣ ስድብ የሚሳደብ፣ በትዕቢት ዐይን እናትና አባቱን የሚመለከት ልጅ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝበትም፡፡ስለዚህ ልጆች እናትና አባታችን ማክበር ይገባል ማለት ነው፡፡ እናትና አባታችን ማክበር እንዳለብን ካወቅን እንዴት ነው የምናከብራቸው?
 

1.    በመታዘዝ “ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፡፡” ምሳ.1÷8
2.    ጥሩ ልጅ በመሆን
3.    አክብሮት የተሞላበት ንግግር በመናገር
4.    በመውደድ

እንግዲህ ልጆች እናትና አባትን ማክበር ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማት የሚያሰጥ መልካም ሥራ ነውና እናትና አባታችንን ልናከብር ይገባል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ራሱ እናቱ ድንግል ማርያምን  ያከብር ነበር፤ ይታዘዛትም ነበር፡፡ እኛም እርሱን ምሳሌ አድርገን ልናከብራቸውና ልንታዘዛቸው ይገባል፡፡ እርሱም እኛን ይወደናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር