ቅድስት

መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ

የማቴ.6፥16-24 ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜ
ቁ.16. በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፡፡ እነዚያ ፊታቸውን አጠውልገው ግንባራቸውን ቋጥረው ሰውነታቸውን ለውጠው ይታያሉና፡፡ እንደ ጾሙ ሰው ያውቅላቸው ዘንድ የወዲህኛውን ውዳሴ ከንቱ አገኙ የወዲያኛውን ዋጋቸውን አጡት ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ፡፡ 

ቁ.17. እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ ራሳችሁን ተቀቡ ፊታችሁን ታጠቡ የተቀባ የታጠበ እንዳይታወቅበት አይታወቅባችሁ ሲል ነው፡፡ ይህስ በጌታ ጾም ምን ውዳሴ ከንቱ አለበት ይኸውስ በከተማ ነው በገዳም ቢሉ በከተማ ነው እንጂ በገዳምማ ምን ውዳሴ ከንቱ አለበት ይህም ሊታወቅ ዳንኤል እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ማለፊያ እንጀራ አልበላሁም ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም ዘይትም አልተቀባሁም ብሏል፡፡ እናንተስ ራሳችሁን ተቀቡ /ፍቅርን ያዙ/ ፊታችሁን ታጠቡ፣ ንጽሐናን ገንዘብ አድርጉ ወይም ትሕትናን ያዙ፣ በንስሓ እንባ ታጠቡ፡፡

ቁ.18. እንደ ጾማችሁ ሰው እንዳያውቅባችሁ ሁሉን መርምሮ ከሚያውቅ ከሰማያዊ አባታችሁ በቀር ነው እንጂ ተሠውራችሁ ስትጾሙ ተሰውሮ የሚያያችሁ ሰማያዊ አባታችሁ በጻድቃን በመላእክት በኀጥአን በአጋንንት መካከል ዋጋችሁን ይሰጣችኋል፡፡

በእንተ ምጽዋት
ቁ.19. እህሉን ነዳያን ከሚበሉት ብለው አኑረውት ነቀዝ ቢበላው፣ ልብሱን ነዳያን ከሚለብሱት ብለው አኑረውት ብል ቢበላው ወይም ነቀዝ ቢያበላሸው ምቀኝነት ነውና ዳግመኛ ለክፉ ቀን ይሆነኛል ብሎ ማኖር እግዚአብሔርን ከዳተኛ ማድረግ ነው፡፡ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ አይመግበኝም ማለት ነውና አንድም ምንም እጅ እግር ባያወጡለት ገንዘብ ማኖር ጣዖት ማኖር ነውና ኅልፈት ጥፋት ያለበትን ምድራዊ ድልብ አታድልቡ፣ ብል የሚበላውን ነቀዝ የሚያበላሸውን ሌቦች ግንቡን አፍርሰው ግድግዳውን ምሰው የሚወስዱትን ከሚወስዱበት ቦታ አታድልቡ፡፡

ቁ.20. ኅልፈት ጥፋት የሌለበትን ሰማያዊ ድልብን አድልቡ እንጂ፡፡ ብል የማይበላውን ነቀዝ የማያበላሸውን ሌቦች ግንቡን አፍርሰው ግድግዳውን ምሰው የማይወስዱትን ከማይወስዱበት ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፡፡

ገንዘባችሁ ካለበት ዘንድ ልቡናችሁ ከዚያ ይኖራልና አንድም ውዳሴ ከንቱ ያለበትን ምጽዋት አትመጽውቱ አጋንንት በውዳሴ ከንቱ የሚያስቀሩባችሁን ሳይሆን የማያስቀሩባችሁን ምጽዋት መጽውታችሁ፣ ምጽዋታችሁ ካለበት ልቡናችሁ ከዚያ ይኖራልና፡፡

ቁ.22. የሥጋህ ፋና ዓይንህ ነው ማለት የሥራህ መከናወኛ ዐይንህ ነው፡፡ ዓይንህ ብሩህ የሆነ እንደሆነ አካልህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል ዐይንህ የቀና እንደሆነ ሥራህ ሁሉ የቀና ይሆናል፡፡

ቁ.23. ዐይንህ የሚታመም የሆነ እንደሆነ አካልህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል ማለት ዐይንህ ግን ያልቀና እንደሆነ ሥራህ ሁሉ ያልቀና ይሆናል፡፡ ባንተ ያለ ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማህ እንደምን ይሆን? በተፈጥሮ የተሰጠህ ዓይንህ የታመመ ከሆነ ጨለማ እንደምን ይጸናብህ ይሆን የታመመው ዓይንህ እንደምን ያይልሃል?

ቁ.24. አንድ ባሪያ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻለውም፡፡ ከፍለን መጽውተን ከፍለን ብንኖር ምነዋ ትሉኝ እንደሆነ ይህም ባይሆን ማለት እገዛለሁም ቢል አንዱን ይወዳል ሌላውን ይጠላል፣ ላንዱ ይታዘዛል ለሌላው አይታዘዝም እንጂ፡፡ እንደዚህም ሁሉ እናንተም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ /መታዘዝ/ መገዛት አይቻላችሁም፡፡

ቁ.25. ስለዚህ ነገር ለነፍሳችን ምን እንበላለን ምን እንጠጣለን ለሥጋችን ምን እንለብሳለን ብላችሁ አታስቡ መብል መጠጥን ለነፍስ ሰጥቶ ተናገረ የበሉት የጠጡት ደም ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ነፍስ ከሥጋ ተዋሕዳ ትኖራለችና፣ ልብስን ለሥጋ ሰጥቶ ተናገረ ምንም የምታፍር ነፍስ ብትሆን አጊጦ ከብሮ የሚታይ ሥጋ ነውና ነፍስን እምኀበ አልቦ አምጥቼ ሥጋን ከአራቱ ባሕርያት አዋሕጄ የፈጠርኋችሁ ለእናንተ ምግብ ልብስ እንደምን እነሳችኋለሁ ለማለት እንዲህ አለ፡፡

ቁ.26. ከፍለን መጽውተን ከፍለን ካላኖርን ምን እንመገባለን ትሉኝ እንደሆነ ዘር መከር የሌላቸውን በጎታ፣ በጎተራ፣ በሪቅ የማይሰበስቡትን ሰማያዊ አባታችሁ የሚመግባቸው አዕዋፍን እዩ ማለት አዕዋፍን አብነት አድርጉ ከተፈጥሮተ አዕዋፍማ ተፈጥሮተ ሰብእ አይበልጥምን? ለኒያ ምግብ የሰጠ ለእናንተ ይነሣችኋልን?

ዘወረደ

መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ

የዮሐ.3፥10-21  ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜ

ቁ.11. ራሱን ከዮሐንስ አግብቶ፡፡ ያየነውን፣ የሰማነውን እናስተምራለን ብዬ እንድናስተምር በእውነት እነግርሃለሁ፡፡ ምስክርነታችንን ግን አትቀበሉም፡፡

ቁ.12. ምድራዊ ልደታችሁን ስነግራችሁ ብነግራችሁ ያልተቀበላችሁኝ ሰማያዊ ልደታችሁን ብነግራችሁ እንደምን ትቀበሉኛላችሁ፡፡ ለዚህ ምክንያት አለው በጥምቀት፣ በንፍሐት ይሰጣል፡፡ ለዚያ ግን ንቃሕ ዘትነውም ባለው ነው፡፡ ምክንያት የለውምና፡፡  

ቁ.13. ወደ ሰማይ የወጣ የለም፣ ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡ ይህንስ ለምን ይሻዋል ቢሉ የወጣውም የወረደውም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው ለማለት ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ የለም፣ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀት ገንዘብ ያደረገ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡

ቁ.14. ሙሴ እባብ በምድረ በዳ እንደ ሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ጌታ መሰቀሉ ስለምን ነው ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊደርስ ሊፈጸም፡፡ ጌታ እስራኤልን መና ከደመና አውርዶ ውኃ ከጭንጫ አፍልቆ ቢመግባቸው ከዚህ ምድሩ ብቅ ሰማዩ ዝቅ ቢልለት፣ ከደጋ ላይ ቢሆንለት የወርጭ ሰደቃ እያበጀ ውኃውን እያረጋ መና መገብኳችሁ ይላል እንጂ ይክልኑ እግዚአብሔር ሠርዓ ማዕድ በገዳም ቆላ ቢሆንማ ባልተቻለውም ነበር ብለዋል፡፡ ጌታም የርሱን ከሃሊነት የነርሳቸውን ሐሰት ለመግለጥ ሙሴን አውርዶሙ ቆላተ ሐራሴቦን አለው፡፡ ነቅዐ ማይ የሌለበት በረሐ ነው፡፡ ይዟቸው ወርዷል መናም ዘንሞላቸዋል፣ ውኃውም ፈልቆላቸዋል፡፡ ነገር ግን ነዘር የሚባል እባብ እየነከሰ ይፈጃቸው ጀመር፡፡ ሙሴን ከኛ ስሕተት ኃጢአት አይታጣምና ወደ እግዚአብሔር አመልክትልን አማልደን አሉት፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክትላቸው ድሩቶን ብርት /ነሐስ/ አርዌ /እባብ/ አስመስለህ ሠርተህ ከሚገናኙበት አደባባይ ከእንጨት ላይ ስቀልላቸው ያልጸናባቸው መልኩን አይተው የጸናባቸው ድምጹን ብቻ ሰምተው ይዳኑ አለው እንዳዘዘው አደረገው፡፡ ያልጸናባቸው መልኩን አይተው የጸናባቸው ድምጹን ብቻ ሰምተው ድነዋል፡፡ አርዌ ምድር የዲያብሎስ፤ አርዌ ብርት የጌታ ምሳሌ፤ በአርዌ ምድር መርዝ እንዳለበት በዲያብሎስም ፍዳ ኃጢአት አለበት፡፡ በአርዌ ብርት መርዝ እንደሌለበት በጌታም ፍዳ ኀጢአት የለበትም፡፡ ጽሩይ እንደሆነ ጌታም ጽሩየ ባሕርይ/ በባሕርዩ ንጹሕ/ ነው፡፡ አርዌ ብርት በአርዌ ምድር አምሳል መስቀሉ፣ ጌታም በአርአያ እኩያን ለመስቀሉ ምሳሌ፡፡ ተቅለቈ ምስለ ጊጉያን ከክፉዎች ተቆጠርኩ እንዲል፡፡ ይህንም ሊቁ ከመ ይደምረነ ምስለ ነፍስ ጻድቃን ከጻድቃን ነፍስ ይደምረን ዘንድ ብሎ ተርጉሞታል፡፡ መልኩን አይተው ድምጹን ሰምተው የዳኑ በአካል ያዩ ከቃሉ ሰምተው ያመኑ የዳኑ ድምጹን ብቻ ሰምተው የዳኑ ከርሱ በኋላ በተነሡ መምህራን ሰምተው ያመኑ የዳኑ የምእመናን ምሳሌ፡፡

ቁ.15. በእርሱ ያመነ ሁሉ እንዳይጎዳ ለዘለዓለም ይድን ዘንድ እንጂ፡፡ አይጎዳም ይድናል እንጂ፡፡

ቁ.16. አንድ ልጁን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ እስከ መስጠት ደርሶ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና፡፡ በእርሱ ያመነ ሁሉ እንዳይጎዳ የዘላለም ደኅንነት ያገኝ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ በርሱ ያመነ ሁሉ አይጎዳም የዘላለም ደኅንነት ያገኛል እንጂ፡፡

ቁ.17. እግዚአብሔር በዓለሙ ሊፈርድበት ልጁን ወደዚህ ዓለም አልሰደደውም፡፡ እርሱ ስለካሠለት ያድነው ዘንድ እንጂ አስቀድሞ ያልተፈረደበት ሆኖ ሊፈርድበት አልሰደደውም፡፡ ተፈርዶበታልና ከተፈረደበት ፍርድ ሊያድነው ነው እንጂ፡፡ በሥጋው ሊፈርድበት አልላከውምና ተኀደገ ለከ ኀጢአትከ ተኀደገ ለኪ ኀጢአተኪ እያለ ሥርየተ ኀጢአትን ሊሰጥ ነው እንጂ፡፡

ቁ.18. በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፡፡ በእርሱ ባላመነ ግን ፈጽሞ ይፈረድበታል፡፡ በአንድ በእግዚአብሔር ልጅ አላመነምና፡፡

ቁ.19. ፍርዱም ይህ ነው ብርሃን ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶአልና፡፡ ሰውም ከብርሃን ጨለማን፣ ከዕውቀት ድንቁርናን ከክርስቶስ ሰይጣንን፣ ከወንጌል ኦሪትን ወዷልና እስመ እኩይ ምግባሩ፡፡

ቁ.20. ምግባሩ ክፉ የሆነ ሰው ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ወደ ብርሃን አይመጣም ሥራው እንዳይገለጥበት ሥራው ክፉ ስለሆነ ሥራው በጎ የሆነ ሰው ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ ሥራው ይገለጥ ዘንደ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራዋልና ሥራቸው ክፉ የሆነ ጸሐፍት ፈሪሳውያን፣ አይሁድ፣ አሕዛብ ጌታን ይጠላሉ በጌታ አያምኑም ሥራቸው እንዳይገለጥ ሥራቸው ክፉ ስለሆነ ሥራቸው በጎ የሆነ ሐዋርያት፣ አይሁድ አሕዛብ ግን በጌታ ያምናሉ ሥራቸው ይገለጥ ዘንድ ሥራቸው በጎ ስለሆነ፡፡

ቀዳም ሥዑር

ሚያዝያ 6፣2004 ዓ.ም.

ቅዳሜ፡

ቀዳም ሥዑር ይባላል፡፡ በዚች ዕለች ከድሮው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፡፡

የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /የተሻረች/ ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም በቀዳም ሥዑር  ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

 

ለምለም ቅዳሜ፡- ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ በዚህ ተሰይሟል፡፡ ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡

በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡  

የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡

ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡

ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብሏል፡፡

ምእመናን ሆይ፣ በአጠቃላይ ሥርዓተ ሕማሙን፤ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና ስያሜ ከማወቅና ከመረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃየማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ የስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሚያዝያ 2004፣ አዲስ አበባ፡፡

ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ሊቶስጥራ

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}Sekelete2{/gallery}

ሰሙነ ሕማማት(ዘረቡዕ)

በመምህር ኃይለማርያም ላቀው

 

በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አዘጋገብ መሠረት ሦስት ነገሮች በዕለተ ረቡዕ ተደርገዋል፤ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.    የካህናት አለቆች÷ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ  ተማክረዋል፤

2.    ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡

3.    ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ 30 ብር ተመዝኖለታል፡፡

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምንት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ “ሲኒሃ ድርየም” ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲሆኑ የተቀሩቱ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ 72 አባላት የነበሩት ሲሆን የሚመራው በሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ነበር፡፡

 

በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደ ሚገድሉት መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ በጸሐፍት ፈሪሳውያንና በካህናት አለቆች ዘንድ ይጉላላ የነበረውን ጥላቻ ያውቁ ስለነበር “ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተዋውሏል፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት ከተለያዩ ሰዎች የሚገባውን ገንዘብ ሰብሳቢ /ዐቃቤ ንዋይ/ ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡  “ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር” በማለት ያቀረበው ሐሳብ “አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች” እንደ ሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶ ከፈሰሰ የሚተርፈው የለም፡፡ ይህ በመሆኑ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ስላጣ ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሄዶ ተዋዋለ፡፡ ብር 30 ተመዘነለት፡፡ ይህ አሳዛኝ ታሪክ በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ጥቅሶች ቀጽፎ እናገኛለን፡፡ ማቴ.26÷3-16፤ ማር.14÷1-11፤ ሉቃ.22÷1-6 ይመልከቱ፡፡

 

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን እግር ስር ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ የተለያዩ ገቢረ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ሁሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎቹ ሁሉ ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፤ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታውን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ “የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል÷ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት እንደ ተባለ፡፡” ማቴ.26÷24፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ “ገንዘብ የኃጢአት ስር ነው” ተብሎ አንደ ተነገረ ይህ የኃጢአት ስር የክርስቲያኖችን ሕይወት ሊያደርቅ ስለሚችል ለገንዘብ ያለን ፍቅር በልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰው ይህን ህልም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

 

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረሃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይሆን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ሆነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡

ሰሙነ ሕማማት ( ዘሰሉስ)

ማክሰኞ

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ናቸው፡፡ ጥያቄውም በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?€ የሚል ነበር፡፡ የካህናት አለቆች ያቀረቡት ጥያቄ ነበር፡፡ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማድረጉን ተያይዞ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ሰኞ ከቅጠል ብቻ በቀር ፍሬ ያላገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፤ በማስከተል ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል፡፡ ማቴ.21:23-25፤ ማር.11:27፣ ሉቃ.20·1-8፡፡ ከላይ እንደ ተገለጸው ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩት ተአምራትና የኃይል ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀናቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡

ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ በአንድ አገር የንግድ ቦታን የሚያጸድቅ መንግሥት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡት ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልመለሰም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሷል፡፡ በመባሕተ መኑ ትገብር ዘንተ፤ በማን ሥልጣን ነው ይህን የምታደርገው? ነበር ያሉት፡፡ በራሴ ሥልጣን ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡

ጌታችን እኩይ የሆነውን የፈሪሳውያንን አሳብ በመረዳት œየዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ከሰማይ ያልነው እንደ ሆነ ለምን አላመናችሁበትም ይለናል:ከሰው ያልነው ከሆነ ሕዝቡ ይጣላናል፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው፡፡ ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አተውት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋና በጥርር ስለተሞላ እንጂ፡፡ 

በማቴ.21፡28፤ 25፡46፤ ማር.12፡2፤ 13፡37፤ ሉቃ.20፡9፤ 21፡38 የሚገኙት ትምህርቶች ሁሉም የማክሰ ትምህርት ባላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ባላል፡፡ ክርስቲን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃማኖት ትምህርት ሲማር ሲይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

ዛሬም ቢሆን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊሆን እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን ዐሳባችን ከዓለም ዘንድ የተገላቢጦሽ ነገር እንደ ሚጠብቀን ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ ይህ በመሆኑ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልን ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

ሰሙነ ሕማማት

ሚያዝያ 1/2004 ዓ.ም. 

መምህር ኃይለ ማርያም ላቀው

ፍቅር የተከፈለ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ደኅንነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለ ካሠልን “ቅዱስ ሳምንት” ተብሏል፡፡ በተጨማሪም “የመጨረሻ ሳምንት” ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሙዓለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

 

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፣ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፣ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ እንዲሁም ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ፡፡

 

በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ እንዲከበር ይተላለፋል፡፡ ይህ ብያኔ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ ሆኗል፡፡ “ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ ከዓመፀኞችም ጋር ተቆጠረ፡፡ እርሱ ግን ግፍን አላደረገም ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፡፡” /ኢሳ.53÷4-12/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ ምእመናን ክርስቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መሆኑን በማዘከር በሰሙነ ሕማማት ከማንኛውም የሥጋ ሥራ መታቀብ ዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር በኀዘን ልናከብረው ይገባል፤ ብድራትን የማያስቀረው አምላክም መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ ያደርገናልና፡፡

 

ሰሙነ ሕማማት አስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከጾሙ ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር፡፡ በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም ሕማማቱም ትንሣኤውም ተያይዘው እንዲከበሩ ተደረገ፡፡ ምዕራባውያን ከአርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል፡፡ የምሥራቃውያን /ኦሪየንታል/ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን አርባውን ጾም ጨርሰን ከኒቆዲሞስ በኋላ ያለውን ተከታዩን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን፡፡ከእነዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት /በሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ/ ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

ሰኞ

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሳዕና ማግሥት ጌታችን ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ነገሮችን አድርጓል፡፡ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል፡፡/ማቴ.21÷12-17፤ ማር.11÷17፤ ሉቃ.19÷45-46፡፡/ በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ “በማግሥቱ ተራበ” የሚል ቃል እንመለከታለን፡፡

 

ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም” /ኢሳ.46÷25/ ይላል፡፡ በቅዱስ ወንጌልም “በመጀመሪያ ቃል ነበር” ይላል፡፡ ያ ቃል ቀዳማዊ እንደ ሆነ፣ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበር፣ ያም ቃል እግዚአብሔር ነው ተብሎ ተጽፏል፡፡ ዮሐ.1÷1-2፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱም ሲያስተምር “የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፡ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው” /ዮሐ.4÷34/ ሲል ተናግሯል፡፡ ነቢዩ እግዚአብሔር እንደማይራብ ተናግሯል፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

 

ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፣ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፡ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ ፤ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከ5000 የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ተራበ! ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በእርግጥ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመሆኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረሃብ ንዴት ያለበትና የአንዲት የበለስ ዘለላ ረሃብ አይደለም፡፡ ረሃቡ የበለስ ፍሬ ሳይሆን “በለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱ” እንዲል የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባርን ፍሬ የሻ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “በአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት” ብሏል፡፡

 

እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የአመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመሆን መብቃታቸውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡- “አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሶኩሰ ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኽውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፡፡” ብሎ ተርጉሞታል፡፡ እሾኽ የእርግማን ምሳሌ ነው፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡ ዛሬ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይሆን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ ይለናል፡፡ ማቴ.3÷8፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እናፍራ፡፡ ገላ.5÷22፡፡ ጌታችን በዳግም ልደት ሲመጣ ከሰው ልጅ ሃይማኖት መገኘቱ አጠራጣሪ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ “የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይሆንን?” ቀጣይ ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን ከእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ ፍቅሩን ለማትረፍ እንትጋ፡፡

የዐብይ ጾም ስብከት /ክፍል 7/

መጋቢት 26/2004ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤


ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በአዲስ አበባ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊ፤ቀደም ሲል በዚሁ ደብር አስተዳዳሪ ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ውስጥ ለማጠቃለያ ከሰበኳቸው በርካታ የወንጌል ስብከቶች መካከል የተወሰደ፡፡/መጋቢት 21 ቀን 1985 ዓ.ም./

እውነት እውነት እልሃለሁ፡- ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የተናገረው ለኒቆዲሞስ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ የሃይማኖት ሊቅ ነው፡፡ ብዙ የተማረ ብዙ ያወቀ ሰው ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ሊቅ – ምሁር – አለቃ ተብሎ ተጠርቶአል፡፡ በጊዜው ከነበሩ ሰዎች ከፍ ያለና የላቀ ዕውቀት የነበረው ሰው ነበር፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር ነበር፡፡ የማታ ተማሪ ነበር፡፡ ቀን – ቀን የምኩራብ አስተማሪ ሆኖ ብዙ ሰዎችን ያስተምር ስለ ነበረና እርሱ የሚያስተምራቸው አይሁድ ጌታን ስላልተቀበሉ ቀን ለቀን መጥቶ የሚማርበት አመቺ ጊዜ አልነበረውም፡፡

በአይሁድ ሕግ ጌታን የሚከተልና የሚቀበል ሰው ከምኲራብ የሚባረር ስለሆነ እነርሱን ላላማስቀየም ማታ ነበር የሚማረው፡፡ ኒቆዲሞስ ለጌታ ከሰው ችሎታ በላይ የሆኑ ተአምራትን ስለምትሠራ እኛን ለማስተማርና ለመምከር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከህ የመጣህ ነህ ብሎ መስክሮለታል፡፡ ጌታም ለእናንተ ተልኬ የመጣሁ ከሆነና እናንተን ለማስተማር እንደ መጣሁ ከተረዳህ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም አለው፡፡

ኒቆዲሞስ ስላልገባው እኔ አርጅቼአለሁ፤ እንዴት ነው ወደ እናቴ ማኅጸን ተመልሼ የምገባውና ዳግም የምወለደው? ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ጌታም፡- ሰው ከሰው ከተወለደ ሥጋዊ ነው፤ የሰው ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን በመንፈስ መወለድ አለበት፡፡ ከእግዚአብሔር መወለድ ነፋስ ከየት ተነሥቶ ወዴት እንደሚነፍስ እንደማይታወቅ ያለ ረቂቅ ምሥጢር ነው አለው፡፡ አሁንም ያ ሊቅ፤ ያ አዋቂ አልገባኝም አለ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- አንተ የእስራኤል ሊቅና አዋቂ ሆነህ እንዴት ይህን አታውቅም አለው፡፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የሚወጣ የለም፤ የምናውቀውንም እንናገራለን ካለው በኋላ ጥያቄውን በዚህ ገታ፡፡

ኒቆዲሞስ  ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ መማሩ የምያስመሰግነው ተግባር ነው፡፡ አይሁድ ወገኖቹ ጌታን ሳይከተሉት እርሱ ጌታን መውደዱ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የሚያመሸው ከጌታ ጋር ነበር፡፡ ባለችው ትርፍ ጊዜው ሁሉ ወደ ፈጣሪው ይሔድ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ቀን ሲያስተምርና ሲደክም ስለሚውል ማታ – ማታ ማረፍ ይገባው ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ቤቴ ገብቼ ልረፍ አላለም፡፡ ባለ ሥልጣንና ባለጸጋ ስለ ነበር ደጅ የሚጠናው ሕዝብና መሰል ባልንጀሮቹ ይፈልጉት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከእነርሱ ጋር አላመሸም፡፡

ከዚህ አባት ታላቅ ትምህርት ልንማር ያስፈልጋል፡፡ እኛ ዛሬ የምናመሸው የት ነው? የምናመሸውስ ከማን ጋር ነው? ምን ስናደርግ ነው የምናመሸው? ኒቆዲሞስ ቤቱ አልነበረም የሚያመሸው፤  ከእውነተኛው መምህር ጋር እንጂ፡፡ ኒቆዲሞስ ጽድቁንና በረከቱን እየያዘ ነበር ወደ ቤቱ ይገባ የነበረው፡፡ እኛ ወደ ቤታችን የምንገባው እየከበርን ነው ወይ? ጸድቀን ነው የምንገባው ወይስ ጎስቁለን?

የዛሬው ሰው እየሰከረ፣ እየጨፈረ፣ እየደማ፣ እየቆሰለ አብዶ ነው የሚመለሰው፡፡ በቤት ያሉትም እንቅፋት ያገኘው ይሆን? ይሞት ይሁን? እያሉ እየተሳቀቁ ነው የሚያመሹት፡፡ የሚሞትም አለ፡፡ ማምሸት እንደ ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ነው እንጂ! ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በማምሸቱ ፈጣሪውን አወቀ፡፡ ጌታን ማወቅ ብቻ ደግሞ አይበቃም፡፡ ማወቅማ አጋንንትም ያውቁታል፡፡ ከመንፈስ መወለድ መወለድ ያስፈልጋል፡፡

ሰው ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ተነጥቆ ነበር፡፡ ጌታ መጥቶ ዳግም ሰው እስከሚያደርገን ድረስ የሰይጣል ልጆች ሆነን ነበር፡፡ ከዚያም በአርባና በሰማኒያ ቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደናል፡፡ አባታችን የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ከእርሱ ከተወለድንና ልጅነትን ካገኘን እንደገና ልጅነታችንን ካገኘን እንደገና ልጅነታችንን እንዳናጣ አክብረን እንያዘው፡፡ መጀመሪያም አላወቅንበትም ነበር፡፡ አዳም ከገነት የሚወጣ አልመሰለውም ነበር፡፡ ሰይጣን አታሎታል፡፡ እኛም እንደገና እንዳንታለል ልጅነታችን እንዳይሰረዝ እንጠንቀቅ፡፡

የብዙዎቻችን ልጅነት ዛሬ እየተወሰደ ነው፡፡ ልጅነታችንን እያስነጠቅነው ነው፡፡ እነ ኤሳው እየነጠቁን ነው፡፡ ብዙዎች እንደ ያዕቆብ ልጅነታችንን ሊወስዱብን አሰፍስፈዋል፡፡ ሰይጣን እንደ አዳም ሊነጥቀን አሰፍስፏል፡፡ ዛሬ በጣም አርጅተናል፡፡ ኒቆዲሞስ አርጅቶ ነበር፡፡ በጥምቀትና በንስሓ ግን አዲስ ሕይወት አግኝቶአል፤ ታድሷል፡፡ ያረጀው ሕይወቱ ለመለመ፡፡ ያረጀው ሰውነታችንን በሥጋውና በደሙ በንስሓ እናድሰው፡፡ ይህ ከሆነ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርሰው፡፡

 

 

የዐብይ ጾም ስብከት /ክፍል 6/

መጋቢት 20/2004 ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

 

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ውስጥ የምናነበው ወንጌል የሚያሳስበን ስለ በጎና ታማኝ አገልጋይ የተነገረውን ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ንባብ ውስጥ ጌታ በምሳሌ አድርጎ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ሰዎች እንደ ሥራቸው እንደሚዳኙ በሰፊው አስተምሯል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ አንድ ጌታ ለሦስት ባሮቹ ለእያንዳንዳቸው እንደ አቅማቸው ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለአንዱ ሁለት መክሊትና ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ከሰጣቸው በኋላ ነግዱና አትርፉ በማለት እርሱ ወደ ሌላ አገር መሄዱ ተገልጦአል፡፡ በዚህም መሠረት አምስት መክሊት የተቀበለው የመጀመሪያው ባሪያ በተሰጠው አምስት መክሊት ቆላ ወርዶ ደጋ ወጥቶ ከነገደ በኋላ አምስት ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ አኖረ፡፡ ሁለት መክሊቶችን የተቀበለው ሁለተኛው ባሪያም በተሰጡት አምስት መክሊቶች ከነገደ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አስቀመጠ፡፡ ሦስተኛው ባሪያ ግን ከእነዚህ ሁለት ባሪያዎች በተለየ ሳይወጣና ሳይወርድ፣ ሳይደክምና ሳያተርፍ በአቅሙ መጠን በተሰጠው አንድ መክሊት ሥራ ሳይሠራ እንዲሁ ወስዶ ጉድጓድ በመቆፈር ቀበረው፡፡

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ለእነዚህ ሦስት ባሪያዎች በመጠን የተለያዩ መክሊቶችን ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር ሄዶ የነበረው ጌታቸው ወደ እነርሱ ተመልሶ መጣ፡፡ ከዚያም እያንዳንዳቸው በየተራ ወደ እርሱ እያስገባ በተሰጧቸው መከሊቶች ምን እንደሠሩ ይጠይቃቸውም ይቆጣጠራቸውም ጀመር፡፡ በዚህ መሠረት አምስት መክሊቶችን የተቀበለው የመጀመሪያው ባሪያ በጌታው ፊት ቀርቦ በተሰጡት አምስት መክሊቶች ሌሎች ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ በድምሩ አሥር መክሊቶችን ለጌታው አስረከበ፡፡ ሁለተኛውም እንዲሁ በተሰጡት ሁለት መክሊቶች ሌሎች ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አሁን በእጁ ላይ ያሉትን አራት መክሊቶች ለጌታው አስረከበ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነዚህ ሁለት ባሪያዎች ጌታ በእነርሱ ደስ በመሰኘት ለሁለቱም አንተ መልካም፣ በጎና ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ ስለምሾምህ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ በማለት ወደ መንግሥቱ አስገባቸው፡፡

ምንም ሥራ ሳይሠራና ሳያተርፍ የተሰጠውን አንድ መክሊት ጉድጓድ ውስጥ የቀበረው ሦስተኛው ባሪያ ግን ባዶ እጁን መቅረቡ ሳያንሰው በድፍረት ጌታ ሆይ፡- ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ስለማውቅና ስለ ፈራሁ መክሊትህን ጉድጓድ ቆፍሬ በመቅበር አቆይቼልሃለሁና እነሆ ተረከበኝ የሚል መልስ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ስለ ተቆጣ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፤በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰው መሆኔን ታውቃለህን? ካወቅህ ደግሞ ገንዘቤን ለሚነግዱበት ወይም ለሚለውጡ ሰዎች በመስጠት እነርሱ እንዲያተርፉበት ማድረግና እኔ ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ ከእነርሱ መቀበል እንድችል ማድረግ ትችል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ሳታደርግ ጭራሹኑ በድፍረት እነዚህን በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ክፉ ቃላትን ስለ ተናገርህ ቅጣት ይገባሃል በማለት ለወታደሮቹ፡- ያለውን መክሊት ውሰዱና አሥር መክሊት ላተረፈው ጨምሩለት፤ ላለው ይሰጠዋል ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ ስለዚህ የማይጠቅመውን ባሪያ ወደ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ውጪ አውጡት በማለት አዘዛቸው፡፡

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሳለ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ ትምህርቱን ቃል በቃል ወይም በሰምና ወርቅ ወይም በምሳሌ አስተምሮአቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት እርሱ ይህን ትምህርት ያስተማረው በምሳሌ ነው፡፡ ጌታ ትምህርቱን በምሳሌ ያስተምር የነበረው አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት «አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ፡፡» (መዝ 77፥2) ተብሎ የተነገረውን የትንቢት ቃል ለመፈጸምና ቃሉን የሚሰሙት ተማሪዎቹ የሚማሩት ትምህርት ሳይገባቸው እየተጠራጠሩ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ለማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ከሰባት በማያንሱ ምሳሌዎች ስለምትመጣው መንግሥቱ በስፋት አስተምሯል፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌልን ቃል በዚህ ዓለም ላይ ሲዘራ ዘሩ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ በተሠማሩ ሰዎች ልብ ውስጥ በተለያዩ ምሳሌዎች አማካኝነት ይዘራ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም ጌታ ቃሉን ለገበሬዎች በዘርና በእንክርዳድ እንዲሁም በሰናፍጭ ቅንጣት፣ ለእናቶች በእርሾ፣ ለነጋዴዎች በመዝገብና በዕንቁ፣ ለዓሣ አጥማጆች በመረብ. . . ወዘተ እየመሰለ በምሳሌ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በአሥሩ ቆነጃጅት፣ በሰርግ ቤት፣ በበግና በፍየል. . . ወዘተ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለ መንግሥቱ በስፋት በምሳሌ አስተምሯል፡፡ ጌታ ይሁን ያደርግ የነበረው ትምህርቱ ለተማሪዎቹ እንዲብራራላቸውና ግልጽ እንዲሆንላቸው ነበር፡፡

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ሰንበት ውስጥ የምናነበው ንባብ፣ የምንሰበከው ስብከትና የምንዘምረው መዝሙር የሚነግረንም ስለ አንድ በጎናና ታማኝ ባሪያ በምሳሌ የተነገረውን ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የወንጌል ቃል መሠረት «ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው» ተብሎ የተጠቀሰው ሰው በዳግም ምጽአቱ ወደዚህ ምድር ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ወደ ቀደመ ክብሩ የተመለሰውን ቅን ፈራጅ አምላካችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት ባሪያዎች የሚወክሉት ምዕመናንን ወይም እኛን ነው፡፡ መክሊት የተባለው በጎ የሚያሰኘው በጎና መልካም ሥራ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች የሚመሰሉት ሥራን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረው የያዙትን ጻድቃን ሲሆን መክሊቱን ጉድጓድ በመቆፈር የቀበረው ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ደግሞ ምግባርና ሃይማኖት የሌላቸው የኃጢአተኛ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት በመካከላችን ተገኝቶ ስለ መንግሥተ የምትናገረውን ወንጌል ከሰበከልን በኋላ ለእያንዳንዳችን አንድ፣ ሁለትና አምስት መክሊቶችን በመስጠት ለፍርድ እስከምመጣ ደረስ ነግዳችሁና አትርፋችሁ ጠብቁኝ ብሎን በዕርገቱ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ  ሄዷል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ከእግዚአብሔር የተለያዩ መክሊቶችን ተቀብለናል፤ እንድንነግድባቸውና እንድናተርፍባቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «ለአንዱ ጥበብን መነገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፤ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፤ለአንዱም ትንቢትን መናገር፤ለአንዱም መናፍስትን መለየት፤ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፤ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል፡፡» 1ኛ ቆሮ.12፥8-11፡፡

እግዚአብሔር ለልጆቹ የሰጣቸው መክሊት ይህ ብቻ አይደለም፤ለአንዱ መስበክ ለሌላው የማስተማር ለሌላው የመቀደስ ለሌላው የመዘመር ለሌላው የመባረክ ለሌላው የማገልገል. . . ወዘተ መክሊቶችን ወይም ስጦታዎችን ሰጥቶአል፡፡ በፍርድ ቀን ሁሉም ሰው የሚፈረድበት በተሰጠው መክሊት ትርፍ መሠረት ነው፡፡ አንድ ሰው የሚሰጠው አንድ መክሊት ብቻ አይደለም፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ መክሊቶች ሊሰጡት ይችላል፡፡ እንደ ምሳሌ አድርገን ብንወስድ ለመጥምቀ መለኮት የተሰጡት መክሊቶች ብዙ ናቸው፤ በብሕትውና መኖር፣ ማጥመቅ፣ ነቢይነት፣ ንስሓ ተቀባይ ካህን፣ ስብከት፣ የሰዎችን ልብ ለጌታ የተስተካከለ መንገድ አድርጎ ማዘጋጀት፣ . . .፡፡ ዮሐንስ በተሰጡት በእነዚህ ሀብቶቹ ወይም መክሊቶቹ የብዙዎችን ልብ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ እጅግ ስላተረፈ ጌታ ስለ እርሱ «ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤. . .» (ማቴ.11፥11) በማለት መስክሮለታል፡፡

ይህን ስብከት ስለ ታማኝ አገልጋይ የሚናገረውን የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ስብከት ሳዘጋጅ ከሦስት ቀናት በፊት በሞት የተለዩንን በጎና ታማኝ አገልጋይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ መንፈሳዊ ሕይወት እያሰብሁ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለእኚህ ታላቅ አባት ብዙ መክሊቶችን ስለ ሰጧቸው በእነዚህ መክሊቶች ብዙ ሰዎችን ለእግዚአብሔር አፍርተውለታል፡፡ ይህን በማስመልከት ስለ እርሳቸው የአገልግሎት ዘመናት በሚናገር መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተብሎ የተጻፉትን ቃላት አንብቤያለሁ፡- «ከምንም ነገር በላይ ቅዱስነታቸው ታታሪ ሰባኪ፣ እጅግ ጎበዝ መምህር፣ ጥበበኛ ጸሐፊ፣ ተሰጥኦ ያላቸው ገጣሚ፣ መናኝ መነኩሴ፣ የዋህ ባሕታዊ፣ የሚያነቃቁ ጳጳስ፣ ታላቅ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናንን በስብከቶቻቸው ያነሣሡና በታላላቅ ሥራዎቻቸው የሚመሩ ብሩህ ኮከብ ናቸው፡፡» መክሊት ተቀብሎ በተቀበለው መክሊት ሌሎች መክሊቶችን የሚያተርፍ ሰው በፍርድ ቀን በኢየሱስ ክርስቶስ «መልካም፤ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙም እሾምሃለሁ፤ወደ ጌታህ ደስታ ግባ. . .» ይባላል፡፡ መክሊቱን መሬት ቆፍሮ የሚቀብረው አገልጋይ ግን በውጪ ባለው ጨለማ ውስጥ ተጥሎ በዚያ በልቅሶና ጥርስ በማፋጨት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ዛሬ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉም አንድ ከሆነው ከእግዚአብሔር መንፈስ የተለያዩ ስጦታዎችን ወይም መክሊቶችን ተቀብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም መክሊቱን ቆፍሮ ስለ ቀበረ ለእግዚአብሔር ምንም ሊያተርፍ አልቻለም፡፡ በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ የተሰጠውን መክሊት ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራበት ወይም ሳይነግድበት ወይም ሳያተርፍበት በመሬት ውስጥ ቆፍሮ በማስቀመጡና ጌታው ሲመጣ በማስረከቡ በዚህ ዘመን ከምንገኝ ሰዎች እጅጉን ይሻላል ብዬ አስባለሁ፤እኛ መክሊቶቻችንን ጠብቀን በማቆየት ለእግዚአብሔር ማስረከብ እንኳ አልቻልንምና፡፡ ዛሬ የተቀበለ ሁሉ ቀብሯል ወይም ጥሏል፡፡ አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ በተሰጠው የመቀደስ መክሊት መቀደስ ሲገባው የሚዘፍን ከሆነ መክሊቱን ጥሏል፡፡ አንድ የመዘመር መክሊት የተሰጠው አገልጋይ ለእግዚአብሔር መዘመር ሲገባው ሰዎችን የሚያማ ወይም የሚሳደብ ከሆነ መክሊቱን ጥሏል፡፡   ትክክለኛውን የወንጌል ትምህርት እንዲያስተምርና ሰዎችን በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስገባ የማስተማር መክሊት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለ ሰው በዚህ መክሊቱ የኑፋቄ ስብከት በመስበክ የዋህ የሆኑ ሰዎችን ወደ ሲዖል ለመምራት የሚያስተምርበት ከሆነ መክሊቱን ሙሉ ለሙሉ ጥሎታል ወይም አጥፍቶታል እንጂ አልቀበረውም፡፡ በተሰጠው የመባረክ መክሊት ወይም ሥልጣን ምዕመናንን መባረክና ኃጢአታቸውን መናዘዝ ሲገባው ለጥንቆላ ሥራ ተቀምጦ እፈርዳለሁ የሚል ከሆነ መክሊት የተባለ ክህነቱን አቃሎአታል አጥፍቷታልም እንጂ አልቀበራትም፡፡ በእግዚአብሔር መድረክ ላይ ወንጌልን መናገር ሲገባው ተራ ወሬ ወይም ፖለቲካ የሚደሰኩር ከሆነ ይህ ሰው መክሊቱን ጥሏል፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ለዚህ ነው በዚህ ዘመን ውሰጥ ያለን ሰዎች መክሊቱን ከቀበረው ሰው የምናንስ ክፉና ሃኬተኛ ሰዎች ነን እንጂ ከእርሱ የምንሻልበት ምንም ዓይነት ነገር የለንም የምንለው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ በወንጌል እንደ ተነገረለት ለጻድቃን ሊፈርድላቸውና በኃጥአተኞች ላይ ሊፈርድባቸው ይመጣል፡፡ ከፍርዱ በፊት ሁላችንንም በሰጠን መክሊቶች መጠን ይቆጣጠረናል፡፡ አንድ መክሊት የተሰጠው ሰው ሁለትና ከዚያም በላይ ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ሁለት የተሰጠው ደግሞ ሁለት ወይም ከዚያም በላይ የሆኑ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ አምስት የተቀበልነው ደግሞ አምስትና ከዚያም የሚበልጡ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ እኛ ያተረፍነው ምንድር ነው? በዕርቅ ፋንታ ጠብን የምናባብስ ስለሆንን በመክሊታችን ሰዎችን አጉድለናል እንጂ ማትረፍ አልቻልንም፡፡ በመመረቅ ፋንታ የምናረገም ከሆንን መክሊታችንን ጥለናል፡፡ በመጸለይ ፋንታ ለመደባደብ የምንጋበዝ ከሆንንም የተሰጠንን መክሊት አጥፍተናል፡፡ ታዲያ የገብርኄርን ሰንበት ዛሬ ስናከብር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ እያንዳንዳችንን ታተርፉበት ዘንድ የሰጠኋችሁን መክሊት እስከነ ትርፉ አስረክቡኝ ቢለን ምንድር ነው የምናስረክበው? የምንሰጠውስ መልስ ምንስ የሚል መልስ ነው?

በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ያ ሃኬተኛ ባሪያ መክሊቱን መቅበሩ ሳያንሰው  ለጌታው የሰጠው ክፉ መልስ ለከፍተኛ ቅጣት ዳርጎታል፡፡ እርሱ ለጌታው «ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፡፡» የሚል መልስ ነበር የሰጠው፡፡ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ከዚህ ባሪያ ጋር የሚመሳሰል ጠባይ አላቸው፤ እነርሱ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምንም ነገር ሳያውቁ የእግዚአብሔርን ጠባይና እውቀት በእነርሱ የእውቀት ሚዛን ላይ ይሰፍራሉና፡፡ አንድ ሰው በጠና ሕመም ከታመመ ወይም ከልጆቹ አንዱ በሞት ቢለየው ወይም ንብረቱን በእሳት ቃጠሎ ቢያጣ ይህን አደጋ ያደረሰበት እግዚአብሔር እንደ ሆነ አድርጎ ለእርሱ በእርሱ ላይ ለእርሱ የማይገባ ቃላትን የሚሰነዝር ሰው አለ፡፡ ከዚህ አንጻር እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ሕልውና ላይ በመምጣት «እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ ይህ ሕመም ወይም አደጋ በእኔ ላይ አይደርስም ነበር፡፡» ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ «እግዚአብሔር እንደዚህ የጨከነብኝ ምን አድርጌው ነው;» እያሉ እግዚአብሔርን እንደ ሃኬተኛው ባሪያ ጨካኝ የሚያደርጉት ሰዎች አሉ፡፡ እግዚአብሔርን «የለህም» ወይም «ጨካኝ» ማለት ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨለማ የሚያስገባ ክፉ መልስ ነው፡፡ ሰዎች ሁለት ጊዜ ሳያስቡና አንድ ጊዜ ሳያውቁ በቸልተኝነት በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዝሩአቸው ቃላት ከባድ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡

የጻድቁ የኢዮብ ሚስት እርሷ በእግዚአብሔር ላይ በልቧ ስትሰነዝራቸው የነበሩትን ቃላት ባሏም እንደ እርሷ ይሰነዝራቸው ዘንድ «እግዚአብሔርን ስደበውና ሙት» በማለት በእርሱ ላይ ልታነሣሣው ሞክራ ነበር፡፡ ሊነቀፍ ወይም ሊወገዝ ወይም ሊኮነን የሚገባው ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቸር፣ ርኅሩኅ፣ ታጋሽ፣ ይቅር ባይ፣ መዓቱ የራቀና ምሕረቱ የበዛ አምላክ ነው እንጂ «ጨካኝ» አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ያልዘራነውን የጽድቅ ፍሬ እንድንዘራና እንድናጭድ፤ያልበተንነውንም መልካም ዘር በመበተን በፍርድ ቀን ምርቱን እንድንሰበስብ የሚፈልግ ጌታ ነው፡፡ እኛ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ በማፍራት የእነዚህ ፍሬዎችን ምርት በመሰብሰብ ሰማያዊ መንግሥቱን እንድንወርስ ስለሚፈልግ «ጨካኝ» አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ ለሚያምኑትና ለሚታመኑት ሁሉ የሚታመን ታማኝ ጌታ ነው እንጂ የሚያምኑትን የሚክድ «ጨካኝ» ፈጣሪ አይደለም፡፡ ካልዘራበት የሚያጭድና ካልበተነበት የሚሰበስብ ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፤ ጨካኝ፣ ከሀዲና የማይታመንም ሰው ነው፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር በጎና ታማኝ አገልጋይ አጥቶአል፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታመን አገልጋይ አጥታለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ «ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም፡፡» (መዝ 13፡3) ተብሎ የተነገረው ለዚህ ዘመን አገልጋዮች ነው፡፡ ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔርና ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ ሊሆን አልቻለም፡፡ በጥቂቱ ታምኖ በብዙ ላይ ሊሾም የሚችል ሰው ስለ ጠፋ እግዚአብሔር አምላክ የሰው ያለህ እያለ ነው፤ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ፡፡ አገልጋዩም ሆነ ምዕመኑ በአንድነት ተባብሮ ከዳተኛ ሆኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቃሉ የሚገኝ ሰው ማግኘት ተቸግራለች፡፡ ሁሉም የተሰለፈው የቤተ ክርስቲያንን ሙዳይ በመቦጥቦጥ የግል ብልጽግናውን ለማዳበር እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምዕመናን መዳንና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ሲል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አገልጋዮችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሾማቸውና የሚሾማቸው ግን ራሳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያንንና መንጋውን ከጥፋት እንዲጠብቁ ነው፤ ሐዋ.20፥28፡፡ ለመጠበቅ ተሾሞ የሚያጠፋ ጠባቂ ዕድል ፈንታውና ዕጣ ተርታው ትሉ በማያንቀላፋበትና እሳቱ በማይጠፋበት ዘላለማዊ ሲዖል ውስጥ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ አገልጋይ ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑን ከወዲሁ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ እርሱ ጌታው በዳግም ምጽአቱ እስከሚገለጥ ድረስ መንጋውን በመመገብ፣ ውኃ በማጠጣትና በማሳረፍ ፋንታ ለራሱ ብቻ የሚበላና የሚጠግብ፤ የሚጠጣና የሚሰክር፤የሚያርፍና ዘና የሚል ከሆነ ጌታው ባላሰባት ሰዓት ተገልጦ ከሁለት ይሰነጥቀዋል፤ዕድሉንም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ባለበት ጨለማ ውስጥ ያደርግበታል፤ ማቴ. 24፥45-51፡፡ ዛሬ ጌታ አይመጣም ወይም ይዘገያል ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በተለያያ መልኩ የሚዘርፍና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን አገልጋይም ሆነ ተገልጋይ ከዚህ ጠባዩ ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡  የቤተ ክርስቲያን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለው ለዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በጥፊ የተመታላት፣ ርኩስ ምራቅ የተቀበለላት፣ የሾህ አክሊል የተቀዳጀላት፣ የተንገላታላትና ሞተላት ለዚህች ቤተ ክርስቲያንና ለዚህ ምዕመን ነውና አገልጋዮች በጎና ታማኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡

ይቆየን፡፡

በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡