ምኲራብ

                                                                                                                ገብረእግዚአብሔር ኪደ

ምኲራብ ማለት ቤተ ጸሎት ማለት ሲሆን ናቡከደነፆር ቤተ መቅደስን አፍርሶ አይሁድን ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን ለመማርና ለጸሎት በየቦታው የሰሩት ቤት ነው፡፡ በኢየሩሳሌም ብቻ ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ ማንም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ አምልኮውን መፈጸም ግዴታው የነበረ ሲሆን፥ በምኵራብ ግን በየዕለቱ እየተገናኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነቡ፤ ይተረጕሙና ይሰሙም ነበር (ሕዝ.፲፩፥፲፮፣ ሐዋ.፲፭፥፳፩)፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ፥ በልብ መታሰቡ፣ በቃል መነገሩ፣ በቅዱሳት መጻሕፍትም መዘከሩ ከፍ ከፍ ይበልና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራበ አይሁድ እየተገኘ እንዳስተማረ፣ ድውያንን እንደ ፈወሰ፣ በዚያ ይነግዱ የነበሩትንም ማስወጣቱን አስመልክቶ በዐቢይ ጾም ከሚገኙት ሳምንታት መካከል ሦስተኛውን እሁድ ምኵራብ ብሎታል፡፡ “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖትም ቃል አስተማረ፡፡ ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ፡፡ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ አላቸው፡፡ የአባቴን ቤት የሸቀጥ ቦታ አታድርጉት፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ ወደ ምኵራብ ገብቶ ተቈጣቸው፡፡ ዝም እንዲሉም ገሠጻቸው፡፡ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩንም ጣዕም የንግግሩንም ርቱዕነት አደነቁ” በማለትም ይዘምራል – በጾመ ድጓው ! ከዚህም መረዳት እንደምንችለውም፡-

አንደኛ ቅዱስ ያሬድ ምኲራብን “የአይሁድ ምኵራብ” ብሎ እንደ ጠራው እንመለከታለን፡፡ በዕለቱ በሚነበበው ወንጌል ላይም፥ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቀርቦ የነበረውን ፋሲካ “የእግዚአብሔር ፋሲካ” (ዘጸ.፲፪፡፥፲፩) ማለትን ትቶ “የአይሁድ ፋሲካ” ብሎ እንደ ጠራው እናያለን (ዮሐ.፪፥፲፪)፡፡ ሊቁ ራሱ ቀጥሎ እንደ ነገረን፥ አይሁድ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ብለው እንደ ነበረ፥ ጌታችን ግን የሰው ሥርዓትንና ወግን ሳይኾን “የሃይማኖትን ቃል” ወይም ወንጌልን እንዳስተማራቸው እንገነዘባለን፡፡

ምንም እንኳን ከላይ እንደ ተናገርነው አይሁድ በዚያ በምኵራብ በየዕለቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነበቡ የነበሩ ቢኾኑም፥ በገጸ ንባባቸው ብቻ ድኅነት የሚገኝ ይመስላቸው ስለ ነበረ ጌታችን “የሃይማኖትን ቃል” አስተማራቸው (ዮሐ.፭፡፥፴፱)፡፡ ዳሩ ግን ምን ያደርጋል፤ አብዛኞቹ ይህን አልተቀበሉትም፡፡ ይህን የተመለከተው አፈ ጳዝዮን ዮሐንስ አፈወርቅ በልደት ድርሳኑ ላይ እንዲህ አለ፡- “በአይሁድ ዘንድ ድንግል እንድትፀንስ ተነገረ፤ በእኛ ዘንድ ግን እውነት ኾነ፡፡ ትንቢት ለምኵራብ ሃይማኖት ለቤተ ክርስቲያን ነውና፡፡ ያቺ ትንቢትን ገንዘብ አደረገች፤ ይህችም ሃይማኖትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ምኵራብ ምሳሌን ሰጠች፤ ቤተ ክርስቲያን አመነችበት፡፡ ምኵራብ ትንቢት አስገኘች፤ ቤተ ክርስቲያን ተቀበለችው፡፡ ምኵራብ ትንቢቱን በምሳሌ አስተማረች፤ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ጸናችበት፥ ረብሕ ጥቅም አደረገችው፡፡ ከዚያም የወይን ሐረግ (መስቀል) ተተከለ፤ በእኛ ዘንድ ግን የጽድቅ ፍሬ ተገኘ፡፡ ያቺ ወይንን በዐውድማ ረገጠች፤ አሕዛብ የምሥጢሩን ገፈታ ጠጡ፡፡ ያቺ የስንዴ ቅንጣትን ዘራች፤ አሕዛብ በሃይማኖት ሰበሰቡት፡፡ አሕዛብ ጽጌረዳን በቸርነቱ ሰበሰቡ (ሃይማኖትን ገንዘብ አደረጉ)፤ እሾኹ ግን በአይሁድ ዘንድ ቀረ፡፡ ይኸውም ክሕደት ኑፋቄ ነው፡፡ ትንሽ ወፍ ሰነፎች ተቀምጠው  ሳሉ  ጥላውን  ጥሎባቸው  ይኼዳል፡፡  አይሁድም በብራና የተጻፈውን መጽሐፍ ተረጎሙ፤ አሕዛብ ግን ምሥጢሩን ተረዱ” እያለ እንዳመሠጠረው (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐ.አፈ.፣ ፷፮፥፳፩-፳፬)፡፡

ሁለተኛ ቅዱስ ያሬድ “እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን” እንደሚወድ ነግሮናል፡፡ ይኸውም አብዛኛው አይሁድ ጌታችን እንደ ተናገረ ከአፍ ብቻ ሃይማኖታውያን የነበሩ በውስጣቸው ግን እንዳልነበሩ የሚያመለክት ነው (ማቴ.፳፫፡፳፯)፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚፈልገው የልብ መታደስን፣ የሕይወት መዓዛ መለወጥን፥ በአጭሩ እግዚአብሔር መምሰልን ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን “የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ” እያለ ይህን ያስተምራቸው ዘንድ ወደ “አይሁድ ምኵራብ” እንደ ገባ እንመለከታለን፡፡ ምሕረት በሦስት መልኩ የምትፈጸም ስትሆን እነርሱም ምሕረት ሥጋዊ፣ ምሕረት መንፈሳዊና ምሕረት ነፍሳዊ ይባላሉ፡፡ ምሕረት ሥጋዊ የሚባለው ቀዶ ማልበስ ቈርሶ ማጉረስ ነው፡፡ ምሕረት መንፈሳዊም መክሮ አስተምሮ ክፉን ምግባር አስትቶ በጎ ምግባር ማሠራት ነው፡፡ ምሕረት ነፍሳዊ ደግሞ ክፉን ሃይማኖት አስትቶ በጎ ሃይማኖት ማስያዝ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን ከየትኛውም ዓይነት መሥዋዕት ይልቅ ደስ ብሎ የሚቀበለው ይህን እንደ ሆነ ከዚህ እንማራለን፡፡

ሦስተኛ፥ ቤተ መቅደሱ ቤተ ምሥያጥ ሆኖ እንደ ነበረ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነግሮናል፡፡ ቤተ መቅደሱ ከተመሠረተበት ዓላማ ርቆ፣ የገበያና የንግድ ቦታ ሆኖ፣ “ተዉ” ብሎ የሚቈጣ ሰው ጠፍቶ፣ “ርግብ ሻጮች” በዝተው እንደ ነበረ በዕለቱ ከሚነበበው ወንጌልም እንመለከታለን (ዮሐ.፪፥፡፲፬)፡፡ ስለዚህ ጌታችን ይህን ያደርጉ የነበሩትን ሲገለባብጥባቸው፥ አንደኛ- ዓላማቸውን ስለ መሳታቸው ሲነግራቸው፣ ሁለተኛ- መሥዋዕተ ኦሪትን ሲያሳልፍ፣ ሦስተኛ- ዛሬም ጭምር ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በሚፈተትበት ሥፍራ ይህን የሚያደርጉትን “ከቶ አላውቃችሁም” እንደሚላቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ዳግመኛም “ርግብ ሻጮች” የተባሉት በተጠመቁ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ የተቀበሉትን መንፈሳዊ ሀብት ለምድራዊ ሥራ ለኃጢአት ንግድ የሚጠቀሙበትን “ከእኔ ወግዱ” እያለ በፍርድ ቃሉ ጅራፍ ወደ ውጭ ጨለማ እንደሚያወጣቸው የሚያስተምር ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ሌላው የነገረንና በአራተኛ ደረጃ ልናየው የምንችለው፥ ክብር ይግባውና ጌታችን ሲያስተምራቸው ሁሉም እንደ ተደነቁ እንመለከታለን፡፡ ይኸውም እንደ ነቢያት “እግዚአብሔር እንዲህ አለ”፣ “ሙሴ እንዳዘዘ”፣ “ሳሙኤል እንደ ተናገረ” በማለት ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን እንደ ሠራዔ ሕግ “እኔ ግን እላችኋለሁ” እያለ ያስተምራቸው ስለ ነበረ ነው፡፡ ይህም የባሕርይ አምላክነቱን የሚገልፅ ነው፡፡

እግዚአብሔርን የምትወዱት፥ ይልቁንም እግዚአብሔር አብልጦ የሚወድዳችሁ ሆይ ! እንግዲያውስ እኛም እንፍራ፡፡ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ብለን መቅደስ ሰውነታችን የእግዚአብሔር ሳይሆን “የአይሁድ ምኵራብ” እንዳይባል እንፍራ፡፡ ደገኛ ዘር ይኸውም የወንጌል ዘር ተዘርቶብን ሳለ የክፋት ፍሬ ተገኝቶብን ያን ጊዜ እንዳናፍር አሁን እንፍራ፡፡ ምሕረት ሥጋዊን፣ ምሕረት መንፈሳዊንና ምሕረት ነፍሳዊን በቃል ያይደለ፤ እንደ ዓቅማችን በተግባር እንፈጽም፡፡ በእውነት ያለ ሐሰት ብርሃናችን በሰዎች ሁሉ ፊት በርቶ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔር የሚከብረው፥ እግዚአብሔርም እኛን የሚያከብረን ያን ጊዜ ነውና፡፡ ቤተ መቅደሱንና ቤተ መቅደስ ሰውነታችን ቤተ ምሥያጠ ኃጢአት አድርገነው እንደ ኾነ ወይም እንዳልኾነ ቆም ብለን እንይ፡፡ ርግብ ሻጮች ሆነን እንዳንገኝና ሥርየት የሌለው ኃጢአት እንዳያገኘን እንፍራ፡፡ ይህን ያደረግን እንደ ሆነም ጌታችን ዳግም በመጣ ጊዜ “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን” ከሚላቸው ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ክብርና ጌትነት የባሕርይ ገንዘቡ የሚሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለጋስነቱና ሰውን በመውደዱ ይህን ለማግኘት የበቃን ያድርገን፥ አሜን !

  ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› (ዘሌ.፲፱፥፪)

 

መምህር ኃይለሚካኤል ብርሀኑ

የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት (ሰንበት) ቅድስት ይባላል፡፡ ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ሲሆን የመዝሙሩ ርዕስ የጾመ ድጓው መክፈያ ሆኖ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ከቅድስት ሰኞ ጀምሮ ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንትም ስለ እግዚአብሔር ቅድስና የሚያነሱ መዝሙራት ይቀርባሉ፤ እኛም እግዚአብሔርን መቀደስ (ማመስገን) እንዳለብን የሚገልጹ ምንባባት ይነበባሉ፣ትምህርት ይሰጣል፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ ቅድስናውም ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት፣ቅዱሳን ጻድቃን፣ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ቅዱሳን አበው፤ ቅዱሳት አንስት፤ ቅዱሳን ሊቃውንት፣ቅዱሳን ጳጳሳት፣ ቅዱሳን መነኮሳት፣ ቅድስናን ያገኙት በባሕርዩ ቅዱስ ከሆነው ከአምላካችን ከቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ቅዱስ የሚለውን ቃል ስንመለከት ምስጉን፣ክቡር፣ንጹሕ፣ የተለየ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ስንልም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ የሚመሰገን፤ የቅድስና ምንጭ በቅድስናው የተቀደሰ፤ ቅዱሳንን የሚቀድስ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው፤ኢሳ (፮፥፩)፡፡

ፍጡራንስ ቅዱስ ተብለው መጠራታቸው እንዴት ነው? ብለን ብንጠይቅ  እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ሁሉ የተለየ ቅዱስ ስለሆነ ወደ እርሱ የተጠሩና የመጡ ለእርሱ ክብር የተለዩ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ይህም ማለት  ቅድስናን በጸጋ አግኝተው እንዲያጌጡበት የተጠሩት ሰውና መላእክት ሲሆኑ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የዋሉ የመቅደሱ ዕቃዎች አልባሳቶች በአጠቃላይ ንዋያተ ቅዱሳቱ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እኛም እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ መንግሥቱ ሲጠራንና ልጅነትን ሲሰጠን ለእግዚአብሔር ተለይተን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች እንሆናለንና፤ቅዱሳን ተብለን እንጠራለን፡፡

 እግዚአብሔር ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› ብሎ እንደተናገረው ንጽሕናን ቅድስናን በጸጋ እግዚአብሔር ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ እንዲሁም ሰውና መላእክት የሚገናኙባት፣ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምታስገኝ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ስንል ለእግዚአብሔር አምልኮ የተለየች ክብርትና ንጽሕት ናት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ለራሱ ትሆን ዘንድ የለያት ነፍሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እስከ መስጠት የወደዳት ፣ በደሙ የዋጃትና በቃሉ ያነጻት የክርስቶስ አካሉ ቤተ ክርስቲያን ንጽሕት ናትና ክርስቶስ ክቡር እንደሆነ ክብርት፣ ንጹሐ ባሕርይ እንደሆነ ንጽሕት፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ የኖረች የክርስቶስ ሙሽራ ናት  ማለታችን ነው፡፡

ፍጡራን የቅድስናቸው ምንጭ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፤ ከላይ እንዳየነው እርሱ የቅዱሳን ቅዱስ ነውና፡፡ በሙሴ መጽሐፍ እንደ ተጠቀሰው እስራኤልን እግዚአብሔር ከግብጻውያን እጅ እንዳዳናቸውና ግብጻውያንም እንደሞቱ በባሕር ዳር አዩ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረጋትን  ታላቂቱን እጅ አዩ፡፡ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም አመኑ፤ ባሪያውንም ሙሴን አከበሩ፡፡ በአንድነትም በዝማሬ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ በዝማሬያቸውም የእግዚአብሔርን ቅድስና እንዲህ ሲሉ ገለጹ ‹‹አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤ ቀኝህን ዘረጋህ ምድርም ዋጠቻቸው›› (ዘፀ ፲፭፥፲፩) በማለት መስክረዋል፡፡

አምላከ አማልክት፤ እግዚአ አጋዕዝት ጌታ በቅድስና የከበረ ነው፡፡ ምስጋናውም ቅዱስ እንደሆነ ያየውና የሰማው ኢሳይያስ ስሙን ቅዱስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ ‹‹እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?›› (ኢሳ ፵፥፳፭) ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር፡፡

  ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ እንደተናገው ‹‹አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ›› ብለው መላእክት በሰማይ በባሪያው በሙሴ መዝሙር እንደሚያመሰግኑት ጽፎልናል፡፡ ‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ መንገድህ ጻድቅና እውነት ነው፤ ጌታ ሆይ አንተን የማይፈራና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፡፡  በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለህ አንተ ነህ፤ አቤቱ ፍጥረትህ ሁሉ በፊትህ ይሰግዳሉ፤ ፍርድህ ተገልጦአልና››፤ (ራእ.፲፭፥፫) ይላል፡፡

በአፈ መላእክት ቅዱስ ተብሎ የሚጠራውና የሚቀደሰው በልሳነ ሰብእም ይትቀደስ ስምከ (ስምህ ይቀደስ) እየተባለ የሚጠራ ስሙ ቅዱስ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ስሙን እየጠሩ እንደሚያመሰግኑት ሲመሰክር “አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ሲል ገልጾታል(ኢሳ.፮፥፫)፡፡

ቅዱሱን የወለደች እመ አምላክ ድንግል ማርያምም “ወቅዱስ ስሙ፤ስሙ ቅዱስ ነው ብላ መስክራለች” (ሉቃ.፩፥፶)፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለ ራሱ ቅድስና ሲናገርም “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ.፲፱፥፪) ብሏል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ ቅድስና እንድንቀደስ እንደሆነ ሲገልጽ “የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ይላል (፩፥፲፭)፡፡

የጠራን እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ በቅድስና መኖር ያስፈልጋል፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለድንበት ምሥጢረ ጥምቀት የቅድስናችን መጀመሪያ ስለ ሆነ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ለመሆን ተሠራን፡፡ ነገር ግን ከቅድስና የሚያጎድሉንን ክፉ ተግባራት ስንፈጽም እንበድላለንና በጸጋ ያገኘነውን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እናጣለን፡፡ ስለዚህ እንዳንበድልና ቅድስናን እንዳናጣ ተግተን በእውነት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር ያስፈልጋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ጾመ?

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ  

በገዳም ቆሮንቶስ ፵ ቀንና ለሊት የጾመው

ሀ/ ሕግን ሊፈጽም

የሕግ ሁሉ ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ጾምን ለአዳም የሰጠው ጥንታዊው ሕግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ዋጋ የሚያገኝበት ጸንቶ እንዲቆም የሚያስችለውና ከክፉ የሚጠብቀው መንፈሳዊ መከላከያው መድኃኒት ሆኖ የተሰጠው ፤  ኦሪትም የተሰራችው በጾም ነበር፡፡ አባታችን ሙሴ ኦሪት ዘዳግም  ፱፥፱ ላይ “ሁለቱን የድንጋይ ጽላት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃልኪዳን ጽላት እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ በተራራውም አርባ ቀንና አርባ ለሊት ተቀምጬ ነበር፤ እንጀራ አልበላሁም፤ ውሃም አልጠጣሁም”፤ አለ፡፡ በዚህም ሙሴ የኦሪትን ሕግ ተቀበለ፤ እናም ሕግን ለመቀበል በቅድሚያ መጾም ያስፈልጋል ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግን ሲፈጽም በቅድሚያ የወንጌል መጀመሪያ ያደረገው ጾምን ነው፤ የማቴዎስ ወንጌል ፬፥፩-፲፩ ላይ “እኔ ሕግ ልሽር ሳይሆን ልፈጽም ወደ ምድር ወርጃለሁ”፤ አለ፡፡

ለ/ዕዳችንን ሊከፍል (ካሳ ሊሆነን)፤

እግዚአብሔር ለአባታችን አዳም “ይህንን ዕፀ በለስ አትብላ፤ የበላህ እንደሆነ ትሞታለህ”፤ ብሎት የነበረውን ትእዛዝ ተላልፎ በራሱ ፍቃዱ ተጠቅሞ የተከለከለችዋን ፍሬ በላ፤ ሕግንም ጣሰ፡፡ ስለዚህ አዳም በመብላት ያመጣውን ሞት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ  ለ፵ ቀን ለ፵ ለሊት ባለመብላት ባለመጠጣት ዕዳችንን ከፈለ፡፡ ደሙን አፍሶ፤ ሥጋውን ቆርሶ፤ በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ አዳምን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሲኦል ወደ ገነት መለሰው፡፡

ሐ/ለአርያነት፤ የመንፈሳዊና የበጎ ምግባር ሁሉ መነሻው ጾም ነው፡፡  የዕለተ ዐርብ የማዳኑን ሥራ በጾም ጀመረ፤ የወንጌል ሥራ መጀመሪያም አደረጋት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ  ሥራውን በጾም እንደ ጀመረ ሐዋርያትም ስለተረዱ እርሱን በመምሰል ሥራቸውን በጾም ጀመሩት፡፡ አባቶቻችን ጾምን የትምህርት መጀመሪያ አደረጓት፤ በዚህም ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር በመንግሥቱ እንዲኖሩ በር ስለከፈተላቸው ለአርአያነት ነው ብለን ተቀበልነው፡፡ ሆኖም ሳይጾም ጹሙ አላለንም፤ በምድር እስካለንና እርሱ አርአያ እስከሆነን ድረስ  ከመዓትና ከዘላለም እሳት ለመዳን በጾምና ጸሎት ልንኖር ያስፈልጋል፡፡፡

መ/ሊያስተምረን፤ የተፈቀደውን እየፈጸምን፤ የተከለከልነውን በመተው ሕግ እያከበርን በትምህርተ ወንጌል ድኅነትን እንድናገኝና የነፍሳችን ቁስል እንዲፈወስ ለክርስቶስ ሕይወታችንን መስጠት አለብን፡፡ እንዲሁም ለመጾም ድፍረት ያላት ነፍስ ቀጣይነት ባለው መንፈሳዊ ልምምድ ራስን መግዛት ለሥጋ ፈቃድ የሚያስፈልገውን ምግብና መጠጥ በመተው የሥጋ ፈቃድን ድል በመንሣት ለነፍስ ፈቃድ ማስገዛት ይቻላል ፡፡ ይህቺ ነፍስ ክርስቶስ ያስተማራትን ከተገበረች የሚመጣባትን ከባድ ነገር ሁሉ እስራቱንና ግርፋትን መቋቋም ይቻላታል፡፡ ስለዚህ መጾም በኃጢአታችን እንድንጸጸትና ወደ አግዚአብሔር እንድንመለስ (እንድንቀርብ )ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንድንችል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡

ሠ/ ዲያብሎስን ድል ለመንሣት፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ፬፥፩-፲፩ ላይ መዋዕለ ጾሙ ሲፈጸም ሰይጣን በሦስት ነገር ማለትም በስስት፣ በትዕቢትና በፍቅረ ንዋይ ተፈታተነው፡፡ በስስት ቢፈትነው በትዕግስት፣ በትዕቢት ቢቀርበው በትሕትና፤ በፍቅረ ንዋይ ሊያታልለው ቢሞክር በጸሊአ ንዋይ ድል ነሣው፡፡ ዛሬ እነዚህን ማሳቻ መንገዶች ለይተን ጠላታችንን ድል መንሣት እንችላለን፤ ክርስቶስ ሳጥናኤልን ስለ እኛም ተዋጋው፤ በገሃነም ጣለው፡፡ በዮሐዋንስ ወንጌል ፲፮፥፴፫ ላይ “ስለዚህ እኔ ዓለምን ድል ነስቼዋለኹና ድል ንሱ” ያለበት ምክንያትም ጾም ደዌ ነፍስን ትፈውሳለችና፡፡ የሥጋ ምኞትን አጥፍታ የነፍስን ረኃብ ታስታግሳለችና፤ ከዲያብሎስ ቁራኝነት በማላቀቅ ከክርስቶስ ጋር አንድ ታደርጋለች፡፡

እኛ ለምን እንጾማለን?

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጾም ለነፍሳችን ካሳ እንደሆነን ሁሉ እየጾምን፤ ጠላታችን ሳጥናኤልን ድል ነሥተን አባቶቻችን የወረሱትን ርስት እንድንወርስ እንጾማለን፡፡ ጾም በመንፈሳዊ ሕይወት የመበልጸጊያና የሰውነት መሻትን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ የማቅረቢያ መንገድ ነው፡፡ በዚህም ጾም የወንጌልና የበጎ ሥራ ሁሉ መጀመሪያና የትሩፋት ጌጥ እንደሆነ ሁሉ፤ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፤ አልፋና ኦሜጋ ልዑል እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው የመጀመሪያ ትእዛዙ ነው፡፡ ዘፍጥረት ፪፡፲፯ ላይ “ነገር ግን መልካሙንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”፤ ብሎ ያዘዘው ትእዛዝ ይህ ነውና፡፡

ጾም ስንል፤ ፩ኛ እግዚአብሔርን የምንፈራበትና ከእግዚአብሔር ምሕረት የምንለምንበት መንገድ ነው፡፡

ዕዝራ ፰፡፳፫ ላይ “ስለዚህም ነገር ጾምን ወደ እግዚአብሔር ለመንን፤ እርሱም ተለመነን”፤ በማለት ጾም እግዚአብሔርን መለመኛ እና ጸሎታችንን እንዲሰማን የምናደርግበት መሣሪያችን መሆኑን በተግባር እንዳገኙ እንረዳበታለን፡፡

፪ኛ ኀዘናችንን እና ችግራችንን ለእግዚአብሔር የምንነግርበትና  የምናቀርብበት መንገድ ነው፡፡

ነቢዩ ኢዩኤልም ሕዝበ እስራኤልን ሐዘን በገጠማቸው ጊዜ፤ በመከራም ሳሉ ትንቢተ ኢዩኤል ፩፥፲፬ ላይ የነገራቸው ቃል “ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔር ጩኹ”፤ በማለት ወደ እግዚአብሔር መጸለይ እንደሚገባ ነግሮናል፡፡ ትንቢተ ኢዩኤል ፪፡፲፪ ላይም “እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም፣በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ”፤ በማለት ነግሮናል፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር በመብላት፣ በመጠጣትና በሥጋ ፍላጎት ሆነን የፍላጎታችን፣ የሰላማችንንና የአንድነታችን መሻት መጠየቅ የለብንም፡፡ መጀመሪያ እራሱ ክርስቶስ ማድረግ ያለብንን የተግባር ሥራ እንድንሰራ የነገረን ከችግራችንና ከሐዘናችን ለመላቀቅ በምድር ለምንኖር ሁሉ መጾም እንዳለብን እራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር በነቢያት አድሮ ነግሮናል፡፡

፫ኛ ስብራታችን የምንጠግንበትንና መልካም የሆነ ትውልድ የሚታነጽበት መሣሪያ ነው፤

ትንቢተ ኢሳያስ ፶፰፡፲፪ ላይ “ከድሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎችህ ይሠራሉ፤ መሠረትህም ለልጅ ልጅ ዘመን ይሆናል፤ አንተም ሰባራውን ጠጋኝ የመኖሪያ መንገድንም አዳሽ ትባላለህ”፡፡ እንዲሁም በቁጥር ፭ ላይ “እኔ ይህንን ጾም የመረጥሁ አይደለሁም”፤ እንደዚችም ባለች ቀን ሰው ራሱን ማሳዘን እንደሌለበትና በዚህም ጾም ራሱን ቢያስገዛ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ይታመናል፤ በምድርም በረከት ላይ ይኖረዋል፤ እግዚአብሔርም በያዕቆብም ርስት ይመግበዋል፤ እርሱ እግዚአብሔር ተናግሯልና”፡፡

፬ኛ የአምልኮ መንገድ ነው፤

የሐዋርያት ሥራ ፲፫፡፩-፪ ላይ እንደተገለጸው መንፈስ ቅዱስ ለሥራ የጠራቸውን በርናባስንና ሳውልን ያሰናበቷቸውም በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ በዚያም ጊዜም ከጾሙ፤ ከጸለዩ፤ እጃቸውንም ከጫኑ በኃላ አሰናበቷቸው፡፡ አንድ ሰው የአምልኮ መንገድ ሲጀምር መጾም መጸለይ እንዳለበት እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፤ ጾም የአምልኮ መንገድ ስለሆነች ነው፡፡ ሐዋርያትንም የጠፋውን ትውልድ ለመፈለግ ሐዋርያዊ ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት ጾመዋል፡፡

፭ኛ አጋንትን የምናወጣበት እና ርኩሳን መናፍስትን የምንዋጋበት መሣሪያችን ነው፤ማር ፱፡፳፱  ጌታችን ደቀመዛሙርቱ ማውጣት አቅቷቸው የነበረውን ጋኔን እርሱ ካወጣው በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው “እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለምን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ ስለ እምነታቸው ማነስ መሆኑን ነገራቸው:: “ይህ ወገን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም’ ነው ያላቸው፡፡ ስለሆነም ያለ ጾምና ጸሎት አጋንንት ማውጣት አይቻልም፡፡ ጾምን እየነቀፉና እያጥላሉ እንዲሁም በተግባር ሳይጾሙ አጋንንት እናወጣለን ማለት፤ የአጋንንት መዘባበቻና መጫወቻ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ፤ ከላይ(ከሰማይ) የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤(ቅ/ያሬድ)

 

 

ዲያቆን አቢይ ሙሉቀን

በቦታ የማይወሰነው አምላክ ሥጋን በመዋሕዱ ወረደ፤ ተወለደ፤ ተሰደደ፤ ተራበ፤ ተጠማ፣ ተሰቀለ እየተባለ ይነገርለታል፡፡ የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በመወሰን ተወለደ፤ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ዞሮ አስተማረ፤ በመስቀል ላይ መከራን ተቀበለ፤ ሞተ፤ተቀበረ፤ተነሣ፤ ዐረገ፡፡ ዘለዓለማዊ አምላክ በመሆኑም በሁለም ስፍራ ይኖራል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዐቢይ ጾም እግዚአብሔር ሊመሰገንበት የሚገባውን ምስጋና በጀመረበት ክፍሉ “ሃሌ ሃሌ ሉያ ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘያሐዩ በቃሉ፤ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፤ ከላይ (ከሰማይ) የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤” ብሏል፡፡ ነገር ግን  አላወቁም፤ በቃሉ የሚያድን የሁሉ ጌታ ነውና” በማለት ጾመ ድጓ በሚባለው ድርሰት ይገልጸዋል፡፡

በዚህ ክፍለ ንባብ ሊቁ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር እንደ ሆነ፣ እንዲሁ ስለ ልዕልናው በሰማያት የምትኖር ይባላልና ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት አለ፡፡ እርሱ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ የጸሎት ሥርዓት ሲያስተምራቸው “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር…” ብላችሁ ጸልዩ ብሎ የእርሱ አባትነት ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነና ከምድራዊ አባት የተለየ እንደሆነ በማስረዳት “በሰማያት የምትኖር በሉኝ” አለ፡፡ ሊቁም ይህን መሠረት አድርጎ “ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት” አለን፡፡

ከሰማይ የወረደው ቅድመ ዓለም አብ ያለ እናት በማይመረመር ጥበቡ የወለደው ድኅረ ዓለም ድንግል ማርያም ያለ አባት በማይመረመር ጥበብ የወለደችው ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ነው፡፡ ሥጋዊ ልደት የሆነ እንደሆነ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ይወለዳል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ግን ከአብ ያለእናት፤ ከእናት ያለአባት ሲሆን  እንዲህ ነው ተብሎ አይመረመርም፡፡ በማይመረመር ልዩ ጥበብ ስለተወለደ ስለልዕልናው በሰማይ የምትኖር ይባላል፡፡ ዘበእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት፤ ስለልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ እንዲል፤ ስለዚህ ከላይ ከሰማይ የወረደውን ማለት በልዕልና ያለውን የሚኖረውን አምላክ አይሁድ ሰቀሉት፡፡

የአይሁድን ግብዝነት የጌታን ሁሉን ቻይነትም ሲያስረዳን፤  “ምንም አላወቁም፤ የሰቀሉት በቃሉ የሚያድነውን የሁሉን ጌታ ነው” ይለናል፡፡ በማቴዎስም ወንጌል ፱፥፲፰ ታሪኩ ተመዝግቦ እንደምናገኘው የመቶ አለቃው ልጁ በታመመበት ጊዜ “እባክህ አድንልኝ” በማለት ተማጸነው፤ “እኔ መጥቼ አድንልኃለሁ” ብሎትም ነበር፡፡ የመቶ አለቃውም በበኩሉ ፍጹም እምነትን የተሞላ ስለነበር “ሁሉ ይቻልሃል፤ በቃልህ ብቻ ተናገር ልጄ ይድናል” ብሎ ስለሁሉን ቻይነቱ  በምሳሌ ተናገረ፡፡ ጌታም የመቶ አለቃውን እምነት አድንቆ እንደወደድክ ይደረግልህ አለው፤ ልጁም ተፈወሰ፡፡ ይህንም የሚያውቀው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “እግዚአ ኵሉ ዘየሐዩ በቃሉ የሚያድን የሁሉ ጌታ” በማለት ገልጾታል፡፡

እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ጌታ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱን፣ መሰደዱን፣ መጠመቁን፣ በገዳመ ቆሮንቶስ መጾሙን በአጠቃላይ የነገረ ድኅነት ጉዞ ብላ ትገልጸዋለች፡፡ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ፵ መዓልት  ፵ ሌሊት ጾመ፡፡ የዐቢይ ጾም ሳምንት መግቢያ የሆነውን የመጀመሪያውን ሳምንት “ዘወረደ፤ ከሰማይ የወረደው አምላክ” በማለት ታስበዋለች፡፡

በዚህም ሳምንት ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱን፣ ለዓለም ቤዛ ሲል መከራ መቀበሉን የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ጾመ ሕርቃል በመባልም ይታወቃል፡፡ ጾመ ሕርቃል የተባለበትም ምክንያት ጌታችን የጾመው ፵ መዓልት ፵ ሌሊት ሲሆን እኛ ግን ፶፭  ቀናት እንጾማለን ፡፡  ይህም የሆነበት ምክንያት ጌታ ከጾመው ፵ ቀን በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድ ለብቻው ተቆጥሮ አንድ ሳምንት፡፡ በመጨረሻ ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመሆኑ በመጀመሪያ ያለው አንድ ሳምንት ደግሞ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሐዋርያት፡- ጌታ ፵  መዓልት ፵  ሌሊት ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ ነው የጾመው፤ እኛ ደግሞ እሑድና ቅዳሜ አንጾምም በማለት በመጀመሪያ ያለውን አንድ ሳምንት ጨምረው ጹመውታል፡፡

ሌላው በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭ እንደምናገኘው በ፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ፎቃ፣ በሮም ደግሞ ሕርቃል የሚባሉ ነገሥታት ነበሩ፡፡ ይህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ፎቃ ጨካኝና ለክርስቲያኖች የማይራራ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ፤ ለሮሙ ንጉሥ “እባክህ ከእንዲህ ካለው ጨካኝ ንጉሥ አድነን፤ እኛ ላንተ እንገዛለን” በማለት ይልኩበታል፡፡ እርሱም ለጊዜው ቸል ብሏቸው ቆይቶ ነበር፡፡ከዕለታት አንድ ቀን “ግዙራን ይነሥእዋ ለመንግሥትከ፤ ክርስቲያኖች መንግሥትህን ይወርሷታል” የሚል ራእይ አይቶ፤ ይህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ነው በማለት እንደገና የላካችሁብኝን ነገር አልረሳሁትም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያት ነፍስ ያጠፋ ዕድሜ ዘመኑን ይጹም ብለዋልና፤ ያን ብፈራ ነው እንጂ አላቸው፡፡ እነሱም የአንድ ሰው ዕድሜ ፸ ፹ ነው፤ እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን ብለውት ጠላታቸውን አጥፍቶላቸዋል፡፡ እነሱም ተከፋፍለው አንድ ሳምንት ጹመውታል፡፡

ስለዚህም በንጉሡ በሕርቃል ምክንያት ስለተጾመ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ታሪክ ያላወቁት አንድ ጊዜ ብቻ ጾሙ፡፡ ታሪክ ያወቁት ደግሞ ቀድሞም ሐዋርያት ጹመውታል በማለት መጾም ቀጥለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህን መሠረት አድርጋ ከጌታ ጾም መግቢያ ላይ እንዲጾም ሥርዓት ሠርታለች፤ በመሆኑም ምእመናን ከጾሙ በረከት ያገኙ ዘንድ እንዲጾሙ ታስተምራለች፡፡ በዘመኑ ክርስቲያኖች ከጨካኙ ግዛት የዳኑበት ነው፡፡ ዛሬም ምእመናን ከጨካኙ ዲያብሎስ ፈተና፣ መከራና የጭካኔ አገዛዝ ነጻ የሚወጡበት ነውና ሊጾሙት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ይህ ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማየ ሰማያት መውረድ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድና ወደዚህ ዓለም መምጣት የሚታሰብበት ስለሆነ “ዘወረደ” ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “እስመ ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ ወታጸምም ኵሎ ዘሥጋ ፍትወታተ፤ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች፤ የሥጋን ፍላጎትንም ታስታግሳለች፡፡” ጾመን፤ ጸልየን፤ የሚታገለንን የሥጋ ፍላጎት ለማስታገሥ፣ ነፍሳችንን ለማዳን፣  ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ የኃጢአት ስርየት ለማግኘት ይህን ጾም በመጾም በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

የነነዌ ሰዎች እምነት ንስሓና የጾም አዋጅ

 

መ/ር ቢትወደድ ወርቁ

ትንቢተ ዮናስ አራት ምዕራፎች ያሉት፤ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነሣ ትውልድ ሁሉ ሊማርበትና ራሱን ሊያስተካክልበት የተጻፈ ታላቅ የትንቢት መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ የነቢዩ ዮናስ መጽሐፍ የተጠቀሱት ነቢዩ ዮናስን ጨምሮ የነነዌ ሰዎች ፣ንጉሡ ፣ዮናስ በየዋህነት ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ሊኮበልልበት የተሳፈረበት መርከብ ባለቤቶች /መርከበኞች/ እና ሌሎች ፍጥረታት ዓሣ አንበሪው፣የባሕር ማዕበሉ፣እግዚአብሔር ነቢዩ ዮናስን ያስተማረበት ትልና ቅሉ ሁሉ የነነዌ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት ከመጣባቸው የጥፋት ዋዜማ አንስቶ ከኃጢአት ተመልሰው መዓቱ በምሕረት ቊጣው በትዕግሥት እሰከ ተለወጠላቸውና ከቅጣቱም እስከዳኑበት ጊዜ ድረስ የነበራቸው ተግባርና እግዚአብሔር የሠራላቸው የቸርነት ሥራዎች የተገለጡበት መጽሐፍ ነው፡፡

  መጽሐፉም እያንዳንዱ ቢዘረዘር ትልቅ መጽሐፍም ሊወጣው የሚችል ከመሆኑ አንጻር ያን ወደ ቤተክርስቲያን መጥተን ሊቃውንቱንና መምህራንን በመጠየቅ እንዲሁም ሌሎች ምሥጢራትን የሚያብራሩ  ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ መረዳት እንችላለን፡፡ አሁን ግን ባለንበት ወቅት በግላዊ፤ ቤተሰባዊና ሀገራዊ አኗኗራችን ከገባንበትና ሊገጥመን ከሚችሉ ችግሮች አንጻር የነነዌ ሰዎችን ታሪክ መስተዋት አድርገን ራሳችንን እንመለከትበት ዘንድ ታሪካቸውን በአጭሩ መቃኘትና የንስሓ መንገዳቸውን መከተል ተገቢ ይሆናል ፡፡ በመጽሐፍ ያለው ታሪክ በሙሉ የተጻፈልን ለፍጹም ትምህርትና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን እንሆን ዘንድ እንዲሁም ለተግሣጽ ልባችንንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ጥበብ ይጠቅማልና (፪ጢሞ ፫÷፲፮-፲፯)

                የነነዌ ሰዎች የጥፋት ዋዜማ

ለነነዌ ሰዎችና ለከተማይቱ ጥፋት ምክንያት ሊሆን የነበረው  ምን እንደነበር መጽሐፍ ሲነግረን “የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፤ ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸውም ወደፊቴ ወጥቶአልና፤ በእርሷ ላይ ስበክ”(ዮናስ ፩÷፪ )ይላል፡፡ የነነዌን ከተማ “ታላቂቱ ከተማ” ያሰኛት ብልፅግናዋና እድገቷ ብቻ ሳይሆን በሥሯ የነበሩ ሰዎች ይፈጽሙ የነበረው ታላቅ ክፋት ነበር፡፡ስለዚህም የነዋሪዎቿ ክፋት እግዚአብሔርን አሳዝኖት ከክፋታቸው እንዲመለሱ የክፋት ሥራቸውን እንዲተውና ንስሓ እንዲገቡ ይነግራቸው ዘንድ ነቢዩ ዮናስን ወደ እነርሱ እንዲሄድ ላከው ፡፡ ባዕድ አምልኮትንና ጣዖትን ማስፈን፤ ለጣዖታት መስገድና መሠዋት ፣ ጥንቆላን ማስፋፋት ፣ሥር እየማሱ ቅጠል እየበጠሱ የሰዎችን አኗኗር ማጎሳቆልና ማዘበራረቅ ፣በዘፈንና አስረሽ ምችው ሰክሮ ዝሙትንና ሌሎች የሥጋ ፈቃዳትን በራስና በሌሎች ላይ ማንገሥ ነው፤ (ገላ ፭÷፲፯-፲፱)፡፡  የኃጢአት ሥራ  ከእግዚአብሔር ይልቅ ደስታና ተድላን በመውደድ ለዚያም በሰዎች መካከል ጠብን ከመዝራትና እንዲጋጩ ከማድረግ አንስቶ የራስን ጥቅም ብቻ በመመልከትም ማታለልን ሰዎች የሚጠፉበትንም መንገድ መቀየስና ለዚያም ቀንና ሌሊት በመትጋት ወደ ፍጻሜ ማድረስ ነው፤(ምሳ ፮÷፲፮-፲፱)፡፡ ክፉ ሰዎች የሚጠፉበትንና እግዚአብሔር የሚያሳዝኑበትን ሐሳብ ንግግርና ተግባራትን አጠቃሎ ይይዛል፡፡

   ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር  ዘንድ የተጠላ ነው፤ ዘዳ ፳፭÷፲፭፡፡  የነነዌ ሰዎችንም ለጥፋት ያቀረባቸውና ከተማይቱንም “በሦስት ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” (ዮናስ ፫÷፬) እስከ መባል ያደረሳት ክፋታቸው ነው፡፡ ሰው ልቡናውን ከክፋት ካላራቀ ራሱም ይጠፋል፡፡ ክፋቱም በዙሪያው ላሉት ሁሉ ተርፎ ሌላ ጥፋትን ይወልዳል ፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቀድሞው ዘመን ለእስራኤል ዘሥጋ ” ኢየሩሳሌም ሆይ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ”፤ (ኤር ፬÷፲፬ ) ማለቱም ለዚህ ነው፡፡ ዛሬም ከራሳችን አንስቶ ዙሪያችንን ስንመለከት እግሮቻችን ወደ ክፋት የሚሮጡ፤ እጆቻችንም ደምን ለማፍሰስ የሚፋጠኑና በራሳችንም የክፋት ሐሳብ እየተራቀቅን ጠቢባን ሆነናል የምንል ሰዎች በዝተናል (ምሳ ፩÷፲፮)፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት እንደተናገረውም “ከኃጢአታችን ተመልሰን ንስሓ ካልገባን ክፋታችን ይገድለናል”፤(መዝ ፴፫÷፳፩)፡፡ የነነዌ ሰዎች ጥፋታቸው እስኪነገራቸው ድረስ በኃጢአት ሥራ ጸንተው ይኖሩ እንደ ነበር፤ ዛሬም በክፉ ሐሳብ ንግግርና ተግባር ላይ ካለን እኛም በጥፋት ዋዜማ ላይ እንደሆን ልንረዳ ይገባናል ፡፡

                  የእግዚአብሔር ቸርነትና የንስሓ ጥሪ

የነነዌ ሰዎች በመጥፎ ምግባራቸውና ኃጢአታቸው ምክንያት ሊጠፉ ሲገባቸው የቸርነት ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር እንዳይጠፉ በነቢዩ ዮናስ አንደበት የቸርነቱን የንስሓ ጥሪ አሰምቷቸዋል፡፡ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት”(ዮናስ ፫÷፪) እንዲል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን እኛ ከኃጢአታችን ከተመለስን ከስሕተታችን ተምረን ለመታረምና ሕይወታችንን ለማስተካከል ከፈቀድን እንደ ወጣችሁ፤ እንደ ጠፋችሁና እንደ ረከሳችሁ ቅሩ አይልም፡፡ በበደላችንና በኃጢአታችን ካሳዘነው ይልቅ በኃዘንና በጸሎት ፍጹም በሆነ ንስሓ ከተመለስን ይደሰታል፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን ቅዱሳን መላእክቱም በሰማይ ይደሰታሉ፤ “ንስሓ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ ምክንያት በሰማይ መላእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ ይሆናልና”(ሉቃ ፲፭÷፲) እንደተባለ፡፡ ስለሆነም ዛሬም በገባንበት የጥፋት መንገድ ፣ ተመቻችተንና ተደላድለን እየኖርን ካለንበት የኃጢአት መንደር በመውጣት ንስሓ በመግባት ሰላማዊ አኗኗርንና መንግሥተ ሰማያትን ገንዘብ እንድናደርግ ያስተምረናል ፡፡ “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአትም እንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ተመለሱ፤ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ስለምን ትሞታላችሁ ? የሟቹን ሞት አልፈቅድምና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ” (ሕዝ ፲፰÷፴-፴፪ )እንዲል፡፡ዛሬም ቢሆን በኃጢአት እየኖርን የሚታገሠን ንስሓ እንድንገባ ነው፤ (፪ጴጥ ፫÷፱) ንስሓ ካልገባንም ቅጣት መምጣቱ የማይቀር መሆኑን ልብ ማለት ይገባናል፤(ሮሜ ፲፩÷፳፪)፡፡

የነነዌ ሰዎች መመለስ

የነነዌ ሰዎች ንስሓ እንደማይገቡና በልባቸው ትዕቢት ሞልቶ፤ ከጀመረ ይጨርሰኝ ካፈርኩ አይመልሰኝ፤ብለው በበደላቸው ጸንተው እንደሚኖሩ ሰዎች አልሆኑም ፡፡ ኃጢአታቸውና በደላቸው እንዲሁም ንስሓ ካልገቡ ሊመጣ ያለው ጥፋት ሲነገራቸው በዙፋን ካለው ንጉሥ በዐደባባይ እስካለው ችግረኛ ሁሉም በአንድነት ሆነው ነቢዩ ዮናስ የሰበከውን የንስሓ ስብከት በልቡናቸው አምነው ተቀበሉ፡፡ ማመናቸውንም ከንጉሣቸው ጋር በመሆን ለጾም አዋጅ በመንገር ገለጡ፡፡ እምነታቸውንና ጾማቸውንም በንስሓ አጅበው አለቀሱ፡፡በዚህም እግዚአብሔር ቊጣውን በትዕግሥት መዓቱን በምሕረት ለወጠላቸው ፡፡

 “የነነዌ ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፤ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጎናጸፊያውን አውልቆ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ” (ዮናሰ ፫÷፭-፮) ተብሎ እንደ ተነገረ፡፡ ኃጢአታቸውን አምነው ንስሓ በማይገቡ ሰዎች እግዚአብሔር “የወደቁ አይነሡምን ? የሳተስ አይመለስምን ? ምን አድርጌሃለው ብሎ ከኃጢአቱ ንስሓ የገባ የለም …”(ኤር ፰÷፬) በማለት ይገረማል፤ ይደነቃልም፡፡ የነነዌ ሰዎች ግን በእምነታቸው፤በንስሓቸውና በጾማቸው እግዚአብሔርን አስደሰቱት፡፡ በዚህም በሐዲስ ኪዳን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንስሓ በማይገቡ ላይ እንደሚፈርዱ ሲመሠክርላቸው “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና ብሏል”፤ (ማቴ ፲፪÷፵፩)፡፡ ስለሆነም ከጥፋት እንድንድን ከክፉ ሐሳባችን፤ ንግግራችንና ተግባራችን ተመልሰን ንስሓ እንግባ ፡፡ “የንስሓ ኃዘን መዳንን፤ የዓለምም ኃዘን ሞትን ያመጣልና”፤(፩ ቆሮ ፯÷፲) እምነትን፤ ንስሓንና እውነተኛ ጾምን ገንዘብ አድርገን ለክብር ለመብቃት እንድንችል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ እመቤታችንም በምልጃዋ፤ ቅዱሳንም ሁሉ በጸሎታቸው አይለዩን አሜን!!

ሆሳዕና

ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም

በመምህር ኃለ ማርያም ላቀው

ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ሆሼዕናህ የሚል ሲሆን ትርጉሙም እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፡፡ መዝ.117፡25-26 የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ /Palm Sunday/ ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኟትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብፃውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ ጊዜ፣ እንዲሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ /ሉቃ.22፤18/ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል፡፡ እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም አስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ /ጸበርት/ በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡

ሕፃናትና አእሩግ ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል፡፡ እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ ሲል መልሶላቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያንም የዋህ የሆነው ሕዝብ ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው በዕለተ ሆሳዕና እሑድ ዘንባባ ይዘው የዘመሩለትን ጌታ ዓርብ ይሰቀል ዘንድ ይገባል ብለዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡ ዘካ.9፡9፤ ማቴ.21፡4፤ ማር.11፡1-10፤ሉቃ.19፡28-40፤ ዮሐ.12፤15፡፡ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መላእክት በዕለተ ልደቱ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል በምድር ሰላም ለሰው ሁሉ ይሁን /ሉቃ.2፡13/ እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ሰላሜን እሰጣችኋለሁ /ዮሐ.14፡27/ ብሎ እንዳስተማረ ያን ሰላም የሚሰጥበትን ዕለት መቅረቡን ለማመልከት ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፣ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜያችን ሳትጠልቅ በእምነት እንፈልገው፡፡ አሞጽ4፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፣ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም፡፡ ኢሳ.66፡2፤ መዝ.50፡17፡፡

ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የኅሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ንስሐ ገብተን ጌታችንን ሆሳዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡ ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ 1996 ዓ.ም

005siklet

ሕማማተ እግዚእነ በልሳነ አበው /የጌታችን መከራ በሊቃውንት አንደበት/

ሚያዝያ 1 ቀን 2007 ዓ.ም.

005sikletየእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ አለ

ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፣ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡

ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፡፡ አይራብም፣ አይጠማም፣ አይደክምም፣ አያንቀላፋም፣ አይታመምም፣ አይሞትም ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ፡፡

ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የወልድን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ

እጆቹን፤ እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማስተስረይ መከራ ተቀበለ እንዳለ፤ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲሆን በሥጋ የታመመ ነው፡፡ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል አለ፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው ሁሉ መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፡፡

የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ከላከው ሲኖዶሳዊ መልእክት የተገኘ

እርሱ መቼም መች ከመለኮቱ ሳይለይ የሰውነትን ሥራ ሁሉ ገንዘቡ አደረገ፡፡ ይኸውም መራብ፣ መጠማት፣ መንገድ በመሔድ መድከም፣ በመስቀል ላይ መሰቀል፣ በብረት ችንካር መቸንከር ነው፡፡ በሰውነቱ መቸም መች ሰው ነው፣ በአምላክነቱም ሰውን የፈጠረ ነው፡፡ ግን ከማይከፈል ተዋሕዶ በኋላ መከፈል የለበትም፡፡ ሰው እንደ መሆኑ ስለ እኛ የታመመው የሞተው እርሱ ነው፡፡ በመለኮቱ ግን መቸም መች አይታመምም አይሞትም፣ ሕማምንና ሞትንም አይቀበልም፡፡ በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፡፡ ሲኦልንም የበዘበዘው እርሱ ነው፡፡

የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ አለ

ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡

ሲኦል ተነዋወጠች፣ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፣ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ ክብርት ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት በርሷ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ፡፡

ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል እንደተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፤ ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡

ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሊቃውንት በአንድ ልብ እንዲህ አሉ

ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ ያይደለ፣ በባሕርዩ ከአባቱ ጋር አንድ የሚሆን፡፡ ሁሉ የተፈጠረበት ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፣ በሰማይ በምድር ያለውም ቢሆን፡፡

እኛን ስለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ፡፡

የሠላሳ ዘመን ጎልማሳ ሆኖ በጶንጦስ ሰው በጲላጦስ የሹመት ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፣ ስለ እኛም ታመመ ሞተ ተቀበረ፡፡

የቂሣርያ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ባስልዮስ እንዲህ አለ

ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፣ ተጠማ እንጂ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን ከመጸብሐን ጋር በላ ጠጣ፣ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፣ እጁን እግሩን ተቸነከረ፣ ጎኑን በጦር ተወጋ፣ ከእርሱም ቅዱስ ምስጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ /ወጣ/፡፡

የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዲህ አለ

የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፣ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም ሁሉ የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፣ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፡፡

ሰማዕት የሆነ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ፊልክስ እንዲህ አለ

በሥጋ መወለድ፣ በመስቀል መከራ መቀበል፣ መሞት መነሣት፣ ገንዘቡ የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ሳለ ከጥንት ጀምሮ በመቃብር ያሉ ሙታንን ሁሉ አስነሣ፡፡

የሮማ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ አቡሊዲስ እንዲህ አለ

ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፣ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፣ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሁሉ ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለሁሉ ሕይወትን ሰጠ፡፡

የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አዮክንድዮስ እንዲህ አለ

በመስቀል በሥጋ ተሰቅሎ ሳለ ለመለኮት ከሥጋ መለየት የለበትም፡፡ አንዲት ሰዓትም ቢሆን የዐይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ ቢሆንም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፣ በመቃብር ውስጥ በሰላም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፡፡

የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤራ ቅሊስ እንዲህ አለ

ከአብ ጋር አንድ እንደ መሆንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ ከእኛ ጋር አንድ እንደመሆንህ በፈቃድህ የሞትክ አንተ ነህ፡፡

በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፣ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፡፡ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርክ አንተ ነህ፣ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡

ከሙታን ጋር የተቆጠርክ አንተ ነህ፣ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፣ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርክ አንተ ነህ፣ በዘመኑ ሁሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፡፡

በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ የእግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፡፡

የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ

ኃጢአታችንን ለማሥተሰረይ በሥጋ እንዲህ ታመመ፣ እንደሞተ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ እናምናለን፡፡

የቆጵሮስ ደሴት ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንዲህ አለ

ነብይ ዳዊትም ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም አለ፡፡ ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፣ የቀና ልቡና ዕውቀት በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ፡፡ ዳዊት እንደተናገረው እውነት ሆነ፣ ነፍስ መለኮትን ተዋሕዳ ወደ ሲኦል ወርዳለችና፣ ሥጋም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ሳለ መለኮት ከሥጋ አልተለየም፡፡ አምላክ ሰው የመሆኑን እውነት ያስረዳ ዘንድ፣ መለኮት ነፍስን ተዋሕዶ በአካለ ነፍስ የሲኦል ምስጢርን ገልጦ ፈጽሟልና በሲኦልም በቁራኝነት አልተያዘምና፡፡

ምንጭ ስምዐ ተዋሕዶ፤ ሚያዝያ 1-5 ቀን 2007 ዓ.ም.

ሆሳዕና በአርያም

መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን ሚኪያስ አስረስ

ሰውን ከወደቀበት የበደል ጉድጓድ ያወጣው ዘንድ እግዚአብሔር ክንዱን ወደ ዓለም ላከ፡፡ ሰው ሆኖ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክንድ በጉድጓድ ተጥሎ የነበረን በዚያም በሥጋ በነፍስ፤ በውስጥ በአፍአ ቆስሎ የነበረ አዳምን በትህትና ሁለተኛ አዳም ሆኖ በሥጋ የቆሰለውን በለበሰው ሥጋ ቆስሎ;በነፍስ የታመመውን በትምህርት አዳነ፡፡ ከእርሱ አስቀድሞ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከባርነት ወደ ነፃነት የሚያመጣ ባለመኖሩ እርሱ ሁሉን የፈጠረ ሁሉን የሚያኖር እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ለሰው መድኃኒት ሆነ፡፡ በሞቱም መድኃኒትነትን አሣየ፡፡ በነቢይ መድኃኒተ ፈነወ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ መድኃኒትን ሰደደ፡፡ (መዝ.110፡9) ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፡፡

ክርስቶስ ባለ መድኃኒት ሆኖ በኃጢአት ለታመሙ ደቂቀ አዳም ሁሉ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ወደዚህኛው ዓለም መጣ፡፡ በምድራዊ ሥርዓት እንደምናየው መድኃኒትና ባለ መድኃኒት እንደሚለያዩ አይደለም፡፡ ሁለቱም እርሱ በመምጣቱ (ሰው በመሆኑ) ፈጸ እንጂ፡፡ መድኃኒት አድርጎ ሥጋውን ደሙን የሰጠ እርሱ ነው፡፡ በካህናት አድሮ ሰው በንስሐ ሲመለስ መድኃኒት ወደሆነው ወደ ራሱ የሚመራ እርሱ ነው፡፡

ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ በእመቤታችን ማኅፀን የተጀመረው የእርሱ መድኃኒትነት እና ፍቅሩ ፍፃሜውን ያገኘው በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ መሐሪ ንጉሥ እርሱ መሆኑን ይገልጥ ዘንድ በፈቃዱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ከመግባቱ አስቀድሞ ከኢየሩሳሌም 16 ያህል ምዕራፍ በምትርቀው በቤተፋጌ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡

ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን (ማለትም ጴጥሮስን እና ዮሐንስን) በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ ወዲያውም ወደ እርሷ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበትን ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ፡፡ (ማር 11፡2) በማለት አዘዛቸው፡፡ ዳግመኛም ሰው ወዳልገባባት የተዘጋች የምሥራቅ ደጅ ወደ ምትባል ወደ ድንግል መጥቶ ዘጠኝ ወር ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ እንደኖረ፤ ማኅየዊት ከምትሆን ሕማሙ በኋላም ሰው ባልተቀበረበት መቃብር እንደተቀበረ፤ አሁንም ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ማንም ሰው ያልተቀመጠባቸውን በሌላ መንደር የሚገኙ አህያንና ውርንጫን እንዲያመጡ ደቀመዛሙርቱን አዘዘ፡፡

የፍጥረት ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ እስትንፋሷን የገበረችለትን አህያ አሁን ደግሞ በፈቃዱ ስለ ሰው ሁሉ ሊሞት ሲል ንጉሥነቱን ሊያስመሰክርባት ወደደ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ካለው 16 ምዕራፍ አሥራ አራቱን በአህያ ላይ ሳይቀመጥ በእግሩ ሄደ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ምዕራፍ በአህያ ላይ በመቀመጥ ከተጓዘ በኋላ የኢየሩሳሌምን መቅደስ ሦስት ጊዜ በውርጫዋ ላይ በመሆን ዞረ፡፡ በዚህም ለሰው ሁሉ ያለው ቸርነቱ፣ ሕግ የተሰጣቸው አይሁድ እና ሕግ ያልተሰጣቸው አሕዛብ ላይ እኩል ቀንበርን መጫን እንዳይገባ አጠየቀ፡፡

ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ ብዙ ሰዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፣ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቆረጡ ያነጥፉ ነበር፡፡ (ማር. 11፡8)፡፡ ከዚያም ሰዎች ሆሣዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው (ማር. 11፡9) በማለት አመሰገኑ፡፡ ይህም ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን እኛ ክርስቲያኖች ቡሩክ ስሙ ለእግዚብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ስሙ ምስጉን ነው፡፡ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ እርሱ ክርስቶስም ምስጉን ነው በማለት የአብ እና የወልድን መስተካከልን ገልጸን ጌታን እናመሰግናለን፡፡ ጌታን የሚከተሉት ሰዎች ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር (ማር.11፡10) ይኸውም በልዕልና፣ በሰማይ ያለ መድኃኒት፣ ከሰማይ የመጣ መድኃኒት ማለት ነው፡፡

የእግዚአብሔር ፍቅር እና መሓሪ መሆን በክርስቶስ ሕማም እና ሞት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተገልጧል፡፡ ክርስቶስ የተቀበለው ሕማም እና ሞት የእርሱን አምላክነት እና ንጉሥነት አልሸሸገውም፡፡ እንደውም ዙፋኑን መስቀል በማድረግ ንጉሥነቱን በመድኃኒትነቱ ገልጿል እንጂ፡፡ በነቢይ እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር፣ እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ መዝ. 73፤12 ተብሎ የተነገረው እግዚአብር ድኅነትን በፈጸመበት ማዕከለ ምድር ሲሰቀል በመድኀኒትነቱ ንጉሥነቱን መግለጡን ያመለክታል፡፡ ዳግመኛም አንሰ ተሰየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ በጽዮን በደብረ መቅደሱ፤ እኔ ንጉሥ ሆኜ ተሸምኩ በተቀደሰው ተራራ ላይ(መዝ.2፡6) ተብሎ የተነገረው ኦርቶዶክሳውያን አበው እነርሱ (አይሁድ) ሰቅለነው ገድለነው ኋላ ፈርሶ በስብሶ ይቀራል ይሉኛል እንጂ እኔ ደብረ መቅደስ በምትባል በመስቀል ላይ ነግሻለሁ በማለት ይተረጉሙታል፡፡

ጌታ ንግሥናው ክብሩ የተገለጠበት ሆነ እንጂ መታመሙ እና መሞቱ ውርደት ክብሩንም የሚሸሽግ አይደለም፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማት ወልዱ ክብረ ወስብሐት፣ የልጁን ሕማማት ክብርና ምስጋና አድርጎ የሰየመ እግዚአብሔር ይመስገን አለ፡፡ እኛን ያከበረበት በመሆኑ ሕማሙ ክብር እንደተባለ እናስተውል፡፡ በመስቀል ላይ ሆኖም በቀኝ የተሠቀለው ወንበዴ አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ (ሉቃ 24 ) በማለት ንጉሥነቱ መስክሮለታል፡፡ ለዚህ ነው ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም በምስጋና መግባቱ መድኃኒትነቱን እና ንጉሥነቱን ያሳያል ያልነው፡፡ ዳግመኛም ሁሉን የያዘ ጌታ በአህያ ላይ መቀመጡ ትህትናው ያስረዳል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል ዲባ ዕዋለ አድግ ነበረ፡፡ በማለት ሰማያዊ ልዑል አምላክ ትሑት ሆኖ እንደተገለጠ ተናገረ፡፡

ጌታ ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ድንቅ የሆኑ እና ተአምራትን ለሰዎች አሳየ (ገለጠ)፡፡ እም ሆሳዕናሁ አርአያ ተአምረ ወመንክረ (ቅዳ. ጎርጎ.ዘኑሲስ) እንዲል፡፡ ይኸውም በአህያ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አእምሮ ጠባይዕ ያልቀናላቸው ሕፃናት ዕውቀት ተገልጾላቸው ሆሳዕና በአርያም እያሉ ጌታ በማመስገናቸው ነው፡፡ ዳግመኛም በከሃሊነቱ መናገር ለማይችሉ ዕውቀት ለሌላቸው ድንጋዮች ዕውቀት ተሰጥቷቸው መናገር ችለው ጌታን አመስግነዋል፡፡ እርሱ የባሕርይ አምላክ መሆኑ በሰውነቱም ቀድሞ በበደል ምክንያት ለሰው ከመገዛት ውጪ የሆኑ ፍጥረታት ዳግመኛ ሥጋዌ ለሰው እንደተገዙ ከዚህ ሁሉ ማስተዋል ይገባል፡፡

ጌታ ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ልጅነት እና ተአምራት ማድረግን ገለጸ፡፡ እም ሆሳዕናሁ አርአያ ጸጋ ወኅይለ እንዲል (ቅዳሴ ጎርጎ. ዘኑሲስ)፡፡ የእርሱ ማዳን ከሰው ተወስዶበት የነበረ የጸጋ ልጅነት እንዲመለስለት አድርጋ በልጅነት ላይ ገቢረ ተአምራት (ተአምራትን ማድረግ) ገልጿል፡፡ ይኸውም እርሱ በረድኤት አድሮባቸው ድንቅ ተአምራትን ሚያደርጉ ቅዱሳን መሠረት ነው፡፡ በተጨማሪም ልጅነትን ካገኙ በኋላ በበደል ሲገኙ ለንስሓ የሚሆን እንባን ሠጠ፡፡ እምሆሳዕናሁ ወሀበ ፈልፈለ አንብዕ ለኅጥአን እንዲል (ቅዳሴ ጎርጎ. ዘኑሲስ) ይኸውም የበደሉትን ያከብራቸው ዘንድ፣ ኀጥአንን ከኃጢአታቸው ያነጻቸው ዘንድ እንዲሁም የሳቱትን በንስሐ ይመልሳቸው ዘንድ ነው፡፡

ዳግመኛም ጌታ መድኀኒት ከመሆኑ የተነሣ ለዕውራን ዳግመኛ ብርሃንን ሰጠ፡፡ ይኸውም ለጊዜው በተፈጥሮ ዐይን ተሰጥቷቸው የታወሩትን ፈውሶ በሥጋ ብርሃን መስጠቱ ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን በነፍስ ዕውቀትን ከማጣት የተነሣ ዕውራን የነበሩትን ትምህርትን; ዕውቀትን ገለጸላቸው፡፡ ይኸውም የእርሱ ገንዘቡ ስለሚሆን አንድነት ሦስትነት፣ አምላክነቱን መድኃኒት መሆኑን ገለጠላቸው ማለት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ኒቆዲሞስና አዲሱ ልደት

መጋቢት 20 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን ታደለ ፈንታው

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ ሦስት ብዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና እምነት የተቀላቀሉበት ምዕራፍ ነው፡፡ድኅነትን በትጋት ለመፈጸም የሚታገሉ ክርስቲያኖች ይሄንን ምዕራፍ ሲያነቡ ከኒቆዲሞስ ጎን መቆማቸው የሚያጠራጥር አይሆንም፤ ከጌታ ጋር ምስጢራዊ የሆነ ውይይትን መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በሕይወታቸው የተከፈተ የአዲስ ኪዳን መንገድን እንዳለ ሲገነዘቡም ጌታን ይከተላሉ፡፡ ከእርሱ ጋር ከቅዱስ መንፈሱም ጋር አንድ ይሆናሉ፡፡ አዲስ ልደትን ያገኛሉ ፤ይህም በጥምቀት የሚገኝ ልጅነት ነው፡፡

ይህ ምዕራፍ መልካም ሥነ ምግባር በነበረው ፈሪሳዊ ሕያውና መንፈሳዊ በሆነው ምንጭ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የነበረውን ውይይት ይዟል፡፡

ኒቆዲሞስ እንደ ፈሪሳዊ በአይሁድ ትውፊትና በብሉይ ኪዳን ትምህርት የታጠቀ ነው፡፡ ጠንካራ ሞራል እንደገነባ ሰው ወደ ጽድቅ የሚወስደውን ትውፊት የሚያውቅ ሰው በፈቃዱ መታዘዝ እንዳለበት የሚያምን ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ሰው በሚያደርገው ጠንካራ ትግል እንደሆነ ያምናል፡፡ይህ ትግል በሰው በጎ ፈቃድና ሕጉን በደረቁ በመተርጎም እንደሚገኝ ያምናል፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታን ያገኘው ሕጉን የሚቃወም ሆኖ ሳይሆን ሕጉን በጥልቀት የሚተረጉም አይሁዳዊ ሆኖ ነው፡፡

ስለዚህም ነው ወደ መድኀኒታችን ከተሳቡ ወገኖች መካከል ወንጌላዊው የኒቆዲሞስን ጉዳይ በትኩረት የጻፈው፡፡ በዚህ ዐውድ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ይላል፡-በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ /ዮሐ.2፡23/፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታ ከእግዚአብሔር እንደመጣ አወቀ፤ አመነም /ዮሐ.3፡2/፡፡ ነገር ግን ምናልባት ኒቆዲሞስ ጌታ ትምህርቱን ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያስተምር ሊያስብ ይችላል፡፡ የሕጉን ጥሬ ትርጉም እንጂ ፍካሬያዊ ትርጉም አልተገነዘበም፡፡ የአይሁድን ኑሮ ሊያሻሽል የመጣ ነው ብሎም ሊያስብ ይችላል፡፡

የኒቆዲሞስ አመለካከቱና ልምዱ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን አዲስ ሕይወት ለመቀበል አያበቃውም፡፡ በአዲሱ ልደት የሚገኘው የጸጋ ልጅነት አይገነዘበውም፡፡ የመንፈሳዊው ሕግ ጥቅም ግን ይህ ነበር፡፡ ሥጋዊውን ከመንፈሳዊ ምድራዊውን ከሰማያዊ መለየት ያስችላል፡፡ ጌታ የኒቆዲሞስን አሳቡን፣ ልቡን፣ ስሜቱን፣ ዕውቀቱን ሁሉ ወደ ሰማያዊ ነገር እንዲያሸጋግረው ፈቀደ፡፡ ይህን በማድረግ ከሰማይ የወረደው እርሱም የሰው ልጅ በሰማይ የነበረው€ እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ ወደ ሰማይ መውጣትም የሚቻለው እርሱ ነው፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ወገኖችን ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው ከፍ ያለውንም ነገር እንዲመለከቱ የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡

የኒቆዲሞስና የጌታ ግንኙነት ትኩረታችንን ወደ ክርስቶስ እንድናደርግ ያደርገናል፡፡ ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ነፍስ መዳን ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ከእያንዳንዱም ወገን ጋር ሲነጋገር ያለውን ትህትናም እንገነዘባለን፡፡ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲወያይ የአዲሱን ልደት ጠባይ ዘርዝሯል፡፡ ኒቆዲሞስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማወቅ ፈልጓል፤ ይሄንን መንግሥት ለማወቅ በውኃና በመንፈስ ይጠመቅ ዘንድ ግድ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ይህ ሁኔታ አስፈላጊ ነው፤ ክርስቲያን ዘወትር የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ እንዲኖር ያስችለዋልና ይጠመቅ ዘንድ የግድ ነው፤ በመንፈሱም እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ጌታ ከምድራዊ ነገሮች ያወጣና አሳባችን ሰማያዊ በሆነው ጉዳይ እንዲያዝ ያደርጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የምንችለው ከሰማያዊው ጋር ሕብረት ስንፈጥር መሆኑን ይነግረናል፡፡

ጌታ ጥምቀቱን ከመስቀሉ ጋር አያይዞታል ፡፡ እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለውን እውነተኛ ፍቅር የገለጠበት፣ የባሕርይ ልጁን ወደ ዓለም በመላክ ዓለሙ ዘላለማዊ ሕይወትን ያገኝ ዘንድ ልጁ ከፍ ከፍ ያለበትም የነገሠበትም ዙፋኑ ነውና፡፡ አዲሱን ልደትን በማንሣት ጌታ ከፍርሃት ባርነት አውጥቶ መለኮታዊ የሆነውን ብርሃን እንድንመለከት ያደርገናል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ጌታ ሲጠመቅ የነበረውን ሁኔታ ሲነግረን ለሚያምኑ ወገኖች ያለውን አንድምታም ሲገልጽ ደስታው ፍጹም ነበር፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ

1.ስለ አዲሱ ልደት ገለጻ /1፡13/

2.አዲሱ ልደትና የመስቀሉ ሥጦታ /14-17/

3.አብርሆትና እምነት /18-21/

4.በጌታ ጥምቀት ጊዜ የዮሐንስ ሁኔታ /22-36/ ተዘርዝሯል፡፡

ስለ አዲሱ ልደት ገለጻ

ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንደ ሰው ነበረ /ቁ.1/€ ኒቆዲሞስ የአይሁድ ስም ሲሆን ትርጓሜው ሕዝብን ያሸነፈ€ ማለት ነው፡፡ የአይሁድ አካል የሰንሃድሪን አይሁድ ሸንጎም አባል ነው፡፡ መለኮታዊው ጥሪው መላውን የሰው ልጆች ያካተተ ነው፡፡ የመደብ ልዩነት አልተደረገበትም፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ሓላፊነት ከነበሩ የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎች መካከል ለዚህ ጥሪ መልስ የሰጡ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ከፈሪሳውያን መካከል እጅግ ጥቂቶች፤ ከጥቂቶቹ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡

ጌታን ሊያነጋግር የመጣው ብቻውን ነው፡፡ ምናልባት አንድ ወይም ሁለት አጃቢዎች ሳይኖሩት አይቀሩም፡፡ በአይሁድ ሸንጎ የተከበረ ሰው ነበረ፡፡ ጌታ ግን ይህችን አንዲት ለመዳን የወሰነች ነፍስ ዝቅ አላደረጋትም፤ ሞትን የተቀበለው ስለ እያንዳንዱ ነፍስ ነውና፡፡ ፈሪሳውያን ለመለኮታዊው እውነት የሰጡት መልስ ጥላቻና የዓመጽ መንፈስን የተመላ ነው፡፡ ነገር ግን ከተማሩ አይሁድ መካከል ጌታን ለማግኘት የቸኮሉ በሩም ተከፍቶ የጠበቃቸው ጥቂቶች ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ በተማሩም ባልተማሩም ወገኖች ላይ ይሠራል፡፡ በተራውም ሕዝብ፣ በአለቃውም፣ በየዋኁም፣ በዓመጸኛውም ላይ ይሠራል፡፡

ኒቆዲሞስ ደረጃው ከአመጸኞቹ ቢሆንም ወደ ጌታ መጣ፤ ጊዜው ሲደርስ የቻለውን ያህል ይጠይቅና ያውቅ ዘንድ ሞከረ፡፡ በጥያቄ ላይ እንደነበረ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ለደቀ መዛሙርቱ ያልተቻለው ለዚህ ሰው ተቻለ፡፡ ከጲላጦስ አስፈቀዶ አዲስ ባሳነጸው መቃብር ላይ እንዲቀበር አደረገ፡፡

ቤን ረጊን በአይሁድ ታሪክ መጽሐፍ ስለ ኒቆዲሞስ ሲናገር ይህ ሰው በጣም ሀብታም ከመሆኑ የተነሣ በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙዎችን ለብዙ ዓመታት ይረዳ ነበር ይላል፡፡

እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን /ቁ.2/አለው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ኒቆዲሞስን በብዙ ቦታዎች ጠርቶታል፡፡ ጌታን ማታ ማታ ይጎበኝ እንደነበረ ተገልጧል፤ ይህ ሁኔታ ሦስት ጊዜ ያህል ተጠቅሷል /ዮሐ.ዮሐ.3፡2፣ 7፡50፣ 19፡39/

ስለምን ወደ ጌታ በምሽት መጣ

1.የመጀመሪያው ምክንያት ጌታችን በአደባባይ የሚያስተምረውን ትምህርት ከሰዎች መስማቱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ጌታ በአደባባይ የሚያደርገውን ምልክት በሕዝብ መካከል በግልጽ መጥቶ ማየት አልወደደም፡፡ ድኅነትና ነፍስን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በጥሞና ከጌታ ሥር ቁጭ ብሎ መነጋገር ልቡ ፈቅዷል፡፡ቃሌስ በቅንነት ለሚሄድ በጎ አያደርግምን /ሚክ.2፡7/ ተብሎ እንደተጻፈ የቅንነትን መንገድ መርጦ ወደ ጌታ ቀርቧል፡፡

ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ይነጋገር ዘንድ ወደደ፡፡ ጌታ እንኳን ከሕዝቡና ከደቀመዛሙርቱ ተለይቶ ከአብ ጋር ሲነጋገር የሚያድርበት ጊዜ ነበር፡፡ እኛማ ሌሊቱን በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር እንደምን መነጋገር ይገባን ይሆን፡፡ በተለይ በሌሊት ሁሉንም ነገር ትተን ከጌታ ጋር የግል ጭውውት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አዲሱን ሕይወትና የዚህን ሕይወት ባህርይ፣ በዚህ ሕይወትም ውስጥ ካለች ከመንፈስ ሕብረት ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ይገባናል፡፡

2.ሁለተኛው ምክንያት ምናልባት ጥበብን ለመማር የማታው ጊዜ የተሻለ እንደሆነ በመረዳቱ ነው፡፡ ጌታ ቀን ቀን ሕዝቡን በማስተማር ተይዞ እንደሚውል ያውቃል፡፡ ስለዚህ ኒቆዲሞስ ምሽት እስከሚመጣ ድረስ ጠበቀ፡፡ ጌታን ለማግኘትና የድኅነት ጨዋታን ይጨዋወቱ ዘንድ ወደደ፡፡

3.ሦስተኛው ምክንያት አንዳንድ ምልክቶችን ከተመለከተ በኋላ ጌታን ለማግኘት የመጀመሪያውን ዕድል በምሽት አግኝቶ ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰው ሲተኛ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ የሆነች ምሽትን ማሳለፍ ፈልጎ ይሆናል፡፡ ምናልባትም እንዲህ አይነት ዕድል ወደፊት ሊገጥመው እንደማይችል ሥጋት አድሮበት ሊሆን ይችላል፡፡

4.አራተኛው እንደ ነቢዩ ዳዊት ምሳሌውን ሊከተል ፈልጎ ::ዳዊት ሌሊቱን ለምስጋና ይጠቀምበት ነበርና /መዝ.36፡6፤119፡148/

5.አምስተኛው ምናልባትም ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ ዘንድ እየሄደ መማሩ ለካህናት አለቆች ወሬው ሊደርስ ይችላል ብሎ ከፍርሃት የተነሣ ሊሆን ይችላል፡፡

6.ስድስተኛው ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ ዘንድ መድረሱን አይሁድ ቢያውቁ ጌታችንን ለመዋጋት ቁጣቸውን ይጨምርላቸዋል፡፡ ኒቆዲሞስን ራሱን ለመጉዳት አይሁድ ፈሪሳውያን ሊነሳሡበት ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን በጌታ ትምህርት የተሳበ ቢሆንም በቀን እንዳይሄድ እምነት አንሶት ሊሆን ይችላል፡፡

7.ሰባተኛው ምክንያት ከምንም በላይ ጌታ የዓለም ብርሃን መሆኑን በእርግጠኝነት አለመረዳቱ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ነው፤ የእስራኤል መምህር ነው፡፡ ሰማያዊውን ደስታ ገንዘብ ያደርግ ዘንድ አዲስ ልደት የሚያስፈልገው ሰው ነው፡፡ በምሽት ሲመጣ ደካማ የሆነ እምነትን ይዞ ነበር የመጣው፤ ነገር ግን የጌታ በር ተከፍቶ አገኘው፡፡ ጌታ ስሜቱን ሊጎዳው አልወደደም፡፡

ሁሉ ነገር የሚቆጠረው እምነት እንደሰናፍጭ ቅንጣት ቀስ በቀስ በልቡ ውስጥ እንደሚያድግ ነበር፡፡ ጌታ የፈለገው ያች ቅንጣት አብባ፣ አፍርታ፣ ጌታ በሚሰቀልበት ጊዜ ትልቅ ዛፍ ትሆን ዘንድ ነበረ፡፡ እንደዚያ ሲሆን ነው በዚያ እምነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው በድፍረት የጌታን ሥጋ የቀበረው፡፡

ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በተገናኘ ጊዜ የአይሁድ ድካም በእርሱም ላይ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ አስቀድመን እንዳልነው በብርሃን ሳይሆን በጨለማ የመምጣቱም ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ነገር ግን መኃሪው አምላክ አልጠላውም፤ ትምህርቱንም አልከለከለውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ጌታ በጉጉት ከእርሱ ጋር ተነጋገረ፤ ከፍ ያለውንም ምስጢር ገለጠለት፡፡ በርግጥ ለኒቆዲሞስ የተሰወረ ነበረ፡፡ ጌታ ግን አብራራለት፤ ክፉ አሳብ ከነበራቸው ወገኖች አንጻር ሲመዘን ይህ ሰው ይቅርታን ያገኝ ዘንድ እንደሚገባው ጌታ ቆጥሯልና፡፡ ክፉ ሰዎች ይቅርታ የላቸውም፡፡

ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ ከአይሁድ የተለየ ቢሆንም ጌታን የቆጠረው ሰው አድርጎ ነው፡፡ ይናገረው የነበረው እንደ ነቢይ ነው፡፡ ያደረገውን ምልክት እያደነቀ ነበር የጠየቀው፡፡

መምህር ሆይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን /ቁ.2/ አለው፡፡

ታዲያ ኒቆዲሞስ ሆይ ስለምን በምስጢር በምሽት መጣህ? ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ የእግዚአብሔር የሆነውንም ነገር እንደሚናገር እያወቅህ፡፡ ስለምን ከእርሱ ጋር ነገሮችን በግልጽ አልተወያየህም? ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስን እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን አልጠየቀውም፡፡ አልወቀሰውምም፡፡ ነቢዩ እንዲህ ይላል €œአይጮኸም፤ ቃሉንም አያነሣም፣ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም፡፡ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፣ የሚጨስንም ክር አያጠፋም€ /ኢሳ.42፡3/ ጌታ ራሱ እንዲህ ብሏል፡፡ ዓለሙን ላድን እንጂ በዓለሙ ልፈርድ አልመጣሁም፡፡ /ዮሐ.12፡47/

€œእግዚአብሔር ከርሱ ጋር ከሆነ በስተቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና /ቁ.2/

የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና ተመልከቱ! እንዲህ አላለም €œእኔ ሁሉን በራሴ ማድረግ ይቻለኛልና የማንም እርዳታ አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ የያዝኩት ኀይል የአባቴን ኀይል ነው፤ ይህንን ቢል ለሚያዳምጡት ወገኖች ከባድ በሆነ ነበር፡፡

ነገር ግን ድርጊቱን ሲፈጽም በተመሳሳይ መንገድ አልነበረም፤ ምልክትን ሲያደርግ በኀይል ነው፤ ስለዚህም እንዲህ አለ €œልትነጻ እወዳለሁ /ማቴ.8፡3/ ጣቢታ ተነሽ /ማር.5፡4/ እጅህን ዘርጋ /ማር.3፡5/ ኀጢአትህ ተሠረየችልህ /ማቴ.9፡2/ ፀጥ በል /ማር.4፡39/ አልጋህን ተሸከምና ሂድ /ማቴ.9፡6/፤ አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ /ማር.5፡8/፤ ማንም ስለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት ማር.11፡3/፤ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ /ማር.23፡43/፡፡ ለቀደሙት አትግደል እንደተባለ ሰምታችኋል የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል እኔ ግን እላችኋለሁ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፡፡ /ማቴ.5፡21-22/ ተከተለኝ ሰውን አጥማጅ አደርግሃለሁ /ማቴ.1፡17/፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ታላቅ ሥልጣኑን እንመለከተዋለን፡፡ ስለዚህ ሲሠራ ማንም ወገን በርሱ ላይ ስህተትን ማግኘት አይቻለውም፡፡ ነገር ግን ሊያጠምዱበት የሚቻላቸው በአንድ መንገድ ብቻ ነው እርሱም በንግግሩ ብቻ ነው፤ ማለት ንግግሩን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡-

ስለዚህ ነው ጌታ ኒቆዲሞስን በግልጥ ያናገረው፤ ነገር ግን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን በመግለጽ አልጀመረም፤ ምልክት የሚያደርገው በተመሳሳይ ሥልጣን መሆኑን አልገለጠለትም፡፡

ኒቆዲሞስ በሥሙ ከሚያምኑ ከጌታ ጋር ግን ግንኙነት ከሌላቸው ወገኖች አንዱ ነበረ፡፡ ስለዚህ በምሽት ወደ ጌታ ዘንድ መጣ፡፡ የመጣው ወደ ብርሃን ቢሆንም በጨለማ መጣ፡፡

ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ የመጣው ወደ ጌታ ቢሆንም የመጣው በምሽትና የሚናገረው በጨለማ ነፍሱ ነበር፡፡ ስለዚህ በሰው ሁሉ ላይ የሚያበራውን ብርሃን የሚናገረውን መልእክት ሊረዳው አልተቻለውም፡፡

ኒቆዲሞስ መምህር ነበረ ወደ እውነተኛው ብርሃን በጨለማ የመምጣቱ ምስጢርም ምናልባት ለክብሩ ተጠንቅቆ ነው፡፡ የሚናገረውን ማንነት ገና አላወቀምና፤ መማሩ እንዲያፍር አደረገው፤ በግሌ እኔ መምህርን ማዳመጥ እንጂ ሰዎች እንደመምህር ሲያዳምጡኝ አይደለም የምጠቀመው፡፡ የመጀመሪያ በመሆን ፍላጎትና ዝንባሌ ያላቸውን ወገኖች ጌታ እንዲህ ብሎ ሲገሥጻቸው አውቃለሁ፡፡ እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ መምህራችሁ አንድ ነውና /ማቴ.23፡8/

በማንኛውም ሁኔታ ኒቆዲሞስ በምሽት ወደ ጌታ የመጣው ለመጠመቅ አልነበረም ለመማርና የጌታ ደቀመዝሙርም ለመሆን አይደለም፡፡

በአይሁድ ትውፊት መሠረት ማንም ወገን በምሽት ወደ አይሁድ እምነት፣ ለመገረዝ ወይም ለመጠመቅ አይመጣም፡፡ ይህ ሕግን መተላለፍ ነው፡፡ እንደ ተማሪ ከጌታ ሥር ቁጭ ብሎ ለመማር ሳይሆን የጌታን አሳብ ለማወቅና በጎዳናውም ይጓዝ ዘንድ ነው፡፡

ለአንድ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቄ አውቃለሁ ለሚል የአይሁድ መምህር ረቢ ብሎ ጌታን መጥራት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሕዝብ አለቃ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰው በትህትና ረቢ ብሎ ሲናገር መመልከት በርግጥም ያስደንቃል፡፡€œመምህር ሆይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን/ቁ.2/ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ቢሆንም የተናገረው ፖለቲካ ወይም የአገር ጉዳይ አይደለም፡፡ ነፍሱ ስለምትድንበት ሁኔታ ብቻ ነው የጠየቀው፡፡

ኒቆዲሞስ ስለ ጌታ አንድ ነገር ያውቃል፤ ጌታ በአይሁድ ምሁራን ወይም በታወቀ የአይሁድ ትምህርት ቤት ገብቶ የተማረ አይደለም፡፡ ትምህርቱ ከሰማይ ነው፡፡ ጌታ የያዘው የእውነትን ኀይል እንጂ የሰይፍን ኀይል አለመሆኑን ተገነዘበ፡፡ የሰውን ጥበብ ባለፈ ፍጹም መለኮታዊ ጥበብ እንደሚናገር ተገንዝቧል፡፡ የሚያደርገው ምልክት በመለኮታዊ ኀይል መሆኑን ተገንዝቧል፡፡

በጣም አስደናቂው ንግግሩ €œእናውቃለን€ የሚለው ነው፡፡ ምናልባት ከርሱ ጋር ሌሎች ሰዎች እንዳሉ ያመለክታል፤ ወይም ፈሪሳውያንን ወክሎ እየተናገረ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ምግባቸውም መጠጣቸውም ወሬአቸውም ክርስቶስ ሆኗልና፡፡ ከእነርሱ መካከል ኒቆዲሞስ የሚያምነውን እምነት የሚያምኑ ፈሪሳውያን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ መካከል ጌታን በግልጥ ወይም በስውር ሊያገኘው የፈለገ ወገን የለም፡፡

ኢየሱስም መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው /ቁ.3/€

ኒቆዲሞስ ምልክትን ማድረግ ለክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ለማመኑ ማሣያ አድርጎ ቆጥሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ረበናት እምነትን ምልክት ከመሥራት ጋር አያይዘውታልና፡፡ ስለ ክርስቶስ ማንነት ለመመስከር ከዚህ ወንዝ ባሻገር ያቋረጠው የለም፡፡ ስለዚህ ጌታን ዕሤተ በጎነት ያለው መምህር፣ የእግዚአብሔር ሰው አድርጎታል፡፡ እግዚአብሔር ይስሐቅን €œአትፍራ እኔ ከአንት ጋራ ነኝና /ዘፍ.26፡24/ እንዳለው ሰው ዓይነት አድርጎ ገምቶት ነበር፡፡ ወይም እንደ መበለቲቱ ልጅ ኢያሱ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ከአንተም ጋር እሆናለሁ /ኢያ.1፡5/ ያለው ዓይነት ነቢይ ነበር ጌታ ለኒቆዲሞስ፡፡

ሌሎች ብዙ አለቆችና ነቢያት ተመሳሳይ ልምድ ነበራቸው፤ ነገር ግን ኒቆዲሞስ ምንም እምነትን ይዞ ቢመጣም ከፈሪሳውያን ጠባብ አስተሳሰብ ልጓም እንዳይወጣ የሚያደርግ አዕምሮ ነበረው፡፡ የተማረውም ይኼንን እውነታ ነው፡፡ በጌታና በኒቆዲሞስ መካከል የነበረው ውይይት የሚከተሉት ነጥቦች የትኩረት አቅጣጫዎቹ ነበሩ፡፡

1.የዳግም ልደት አስፈላጊነት እርሱም ውስጣዊው ዓለም የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ እርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡ ይህ አባባል በቅብጥ፣ በሶርያ፣ በላቲን በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፍ የተካተተ ነው፡፡ ዮስጢኖስ፣ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ፣ ጠርጡለስ፣ አውግስጢኖስና፣ ዠሮም ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ጌታችን ኒቆዲሞስን እንደገና እንዲወለድ እንደጋበዘው ተረድቷል፡፡ ይህ አስደነቀው፡፡ አሳቡ በልቡ ውስጥ መዳህ ጀምሯል፡፡ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል አለ፡፡

2.አዲሱ ልደት ከላይ ነው ሰማያዊ ነው /3/ ይህ ድርጊት በቅዱሱና በሰማያዊው የእግዚአብሔር መንፈስ ብቻ የሚፈጸም ነው፡፡ የሰውን አሳብ ሁሉ ያለፈ ስጦታ ነው፡፡

3.አዲሱ ልደት የሚፈጸመው በውኃና በመንፈስ ነው /5/

4.ይህ ልደት በኀይል ያለ በነፍስ የተመሰለ ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ምስጢሩን ሊገነዘበው አይችለም፡፡

በአይሁድ ጽሑፍ እውነት የሚለው ቃል መደገሙ በእውነት ቅዱስ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ጌታችን የሚናገረው ነገር በጣም ጠቃሚና ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ለመናገር ይጠቀምበታል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ በርጋታ ለኒቆዲሞስ የገለጸለት ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ መምህር መሆኑን ማመን ብቻውን በቂ አለመሆኑን፣ ተአምራቱንም ማድነቅና የተለዩ መሆናቸውን ማወቅ በራሱ ግብ አለመሆኑን ነው፡፡ በርግጥም የሚያስፈልገው እንደገና መወለድ ነው፡፡ እርሱም ሰማያዊ የሆነ ልደት ነው፡፡ ሰማያዊ መንፈሳዊ የሆኑ ጉዳዮችን ለማየት ያስችላልና፡፡ በእናቱ ማኅፀን ያለ ፅንስ በዚህ ዓለም እየሆነ ስላለው ነገር የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት መመልከት አይቻለውም፡፡ እንደገና ከተወለደ ብቻ ነው የአዲሱን ዓለም ብርሃን መመልከት የሚችለው፡፡

ሊያይ የሚለው ጌታችን አጽንዖት ሰጥቶ የተናገረው ግሥ ለእውነተኛ ክርስቲያን አስፈላጊ ነው፡፡ አዲሱን ልደት ያጣጥም ዘንድ ስለተወለደ እንዲመካ አይደለም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊመለከት ለመንግሥቱም እንደሚገባ ሊመላለስ ይገባዋል እንጂ፡፡

ይህ ማለት አዕምሮውና ልቡ ሰማያዊ በሆነ ነገር ላይ ማተኮር አለበት ማለት ነው፡፡ ከሰማያዊ ሕግ ጋር አብሮ የሚሄድ ሕግን ያለማወላወል ሊከተል ይገባዋል፡፡ አዲስ ግብ፣ አዲስ ተስፋ አዲስ ኀይልን ገንዘብ አድርጎ፡፡

በአዲሱ ልደት ክርስቲያን በአይነቱ የተለየ ኑሮን መኖር ይጀምራል፤ አሮጌውን የሰውነቱን ሕንፃ አፍርሶ መሠረቱ ክርስቶስ የሆነውን አዲስ ሕንፃ በማነጽ አሮጌው ሰዋችን ተወግዶ የክርስቶስን መልክ የያዘው አዲሱ ሰው ሊታይ ይገባዋል፡፡

አስቀድመን ኀጢአት ጥንተ ተፈጥሮአችንን ስላጠፋው፣ የልባችንም ጥልቅ በኀጢአት ተይዞ ስለኖረ፣ ሥጋውያን በሥጋ ሕግና ፈቃድም የምንመራ ሆነናል፡፡ የምንመራውም የመልካም ነገር ጠላት በሆነ በዲያብሎስ ነበረ፤ ስለዚህ አዲሱ ልደት ልንሸሸው የማይገባ ጠቃሚ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ የሚለው የጌታ ቃል ለዚህ እውነት ማሣያ ነው፡፡

የእግዚአብሔር መንግሥት ምንድነው? ከሰማያዊው መሲሕ ሌላ መመልከት እንደሌለብን የምታሳስብ መንግሥት አይደለችምን! በእኛ መካከል መንግሥቱን መሥርቶ ይኖራል፡፡ ከእርሱ ጋር አንድነትን ፈጥረን የምናየው፣ የምንኖረው ሁሉ ለዚህ ሕይወት እንደሚገባ ነው፡፡ እርሱ ቅዱስ ስለሆነ እኛም ቅዱሳን እንሆናለን፡፡ በእኛ የሚኖረው የእግዚአብሔር መንግሥት ትክክለኛ ትርጉምም ይኼው ነው፡፡ ጌታ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንሥሐ ግቡ /ማቴ.4፤17/ አለ፡፡ እንደገናም መንግሥተ ሰማያት በመካከላችሁ ናት /ሉቃ.17፡21/ ብሏል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ያለንን ሥፍራ ሲናገር፡፡ ጌታ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ /ራዕ.1፡6/ ይላል፡፡

ይህ መንግሥት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረትን የምንፈጥርበት መንግሥት በመሆኑ እንዲህ ተብሏል፡-€œየእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም€ /ሮሜ.14፡17/

ይህ መንግሥት ለዘላለማዊ ሕይወት ዋስትና ነው፡ ወደ ሰማይ እንድንጓዝ ጌታ በጌትነቱ ሲመጣ አስደናቂውን ክብር እንድንካፈል ያደርገናል፡፡ ከምንም በላይ አሳባችንን ከፍ ከፍ አድርጎ ውስጣዊ ነፍሳችንን የመጨረሻውን ቀን እንድትመለከት ጌታ ሲመጣ ሰማያዊ ዘውድን ደፍተን ያለፍርሃት በፊቱ እንቆም ዘንድ የሚያስችለንን ጸጋ እንይዝ ዘንድ ያስችለናል፡፡

የጌታን ቃል እንደገና በሌላ አባባል እንግለጠው ብንል ዳግመኛ ካልተወለድህ ከመንፈስ ጋር ኅብረት ካልፈጠርህ በጥምቀት ልጅነትን ካላገኘህ እኔን በተመለከተ ትክክለኛ የሆነውን አሳብ አታገኝም´የሚል ይሆናል፡፡

€œኒቆዲሞስም ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? /ቁ.4/ በማለት ጠየቀ፡፡

የኒቆዲሞስ ጥያቄ የእውቀት ድካሙን ይገልጣል፡፡ ጌታ የሚናገረው በመንፈሳዊ ቋንቋ ነው፡፡ የኒቆዲሞስ ልብ ነገሮችን የሚያገናኘው ቁሳዊ ዓለማዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ነው፡፡ ቁሳዊ ነገሮችን ከልቡናው ከአእምሮው ካላወጣ መንፈሳዊና ሰማያዊ የሆኑ ምስጢራትን እንደምን ሊገነዘብ ይችላል? ያኔ ነው ወደ እውነት መድረስ የሚቻለው፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስ አዲስ መንፈሳዊ ጉልበትን ይዞ ምስጢርን መረዳት የሚቻለው፡፡

ኒቆዲሞስ ጌታ በተናገረው አዲስ ልደት ተደንቋል፤ ልክ እንደ ሌሎች አይሁድ ዘመዶቹ የአብርሃም ዘር በመሆኑ የሚመካ ነው፡፡ ጌታ ደግሞ እንደገና ተወለድ እያለው ነው፤ አይሁድ ለእግዚአብሔር የተመረጡና የተወደዱ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር፡፡

በነቢያትና በተስፋው ቃል ኪዳን የተቀደሱ ሕዝቦች ነን ይሉ ነበር፡፡ ከምንም በላይ እግዚአብሔር ከእነርሱ አባቶች ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር፡፡ ልዩ መቅደስና መሥዋዕትም ነበራቸው፡፡ ኒቆዲሞስ እስራኤላዊ ብቻ አልነበረም ፈሪሳዊም ጭምር እንጂ፡፡

ምን ዓይነት ከዚህ የበለጠ ልደት ጌታ ይሰጠኛል ብሎ ሊያስብ ይችላል? አይሁድ መሲሑ ሲመጣ የእስራኤል መንግሥት እንደሚያምንበት እንደገናም እንደሚወለዱ ይገምታሉ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ በነበራቸው ኩራትና ትምክህት አንጻር ሲመዝኑት ይህ የሚሆን አይመስላቸውም ነበር፡፡ እነርሱ አሁን ከያዙት የአብርሃም ልጅነት የከበረ ልደት ያለ መስሎ አይታያቸውም ነበር፡፡ ስለ ትውልድ ሀገራቸው ይመኩ ነበር፤ ስለዚህ ሌላ ልደት መስማት የሚሆንላቸው አይደለም፡፡

ይህ ሁሉ ነገር እያለ ኒቆዲሞስ ጀርባውን ለጌታ አልሰጠም፤ እርሱ የጎደለው አንድ ነገር እንዳለ አምኖ ትምህርቱን ቀጥሏል፡፡ በግብሩ ምንም እንኳን መምህርና አለቃ ቢሆንም በትሕትና እውነተኛ የሆነ ነገርን ለመማር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጧል፡፡ ነገር ግን ጌታ የሚለው አዲስ ልደት የማይቻል እንደሆነ ገምቷል፡፡ አስደናቂ ሰው ነው፡፡ ረጅም ዘመን የትምህርትና የአመራር ልምድ ያለው ሰው ከጌታ እግር ሥር ተንበርክኮ አዲስ ነገርን ሲማር መመልከት ያስደንቃል፡፡ ለእውነተኛ አለቃ ጌታ የሰጠው ምሳሌ አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል፡፡ አሁን ኒቆዲሞስ ስለ ትምህርትና ስለ አመራር ልምዱ ሲመካ አንመለከተውም፡፡ እስከመጨረሻው እስትንፋሱ ድረስ ሲማር እንጂ፡፡ አምብሮስ እንዲህ ይላል፡- የኒቆዲሞስ ሁኔታ የሚያሳየን መማር የማያስፈልገው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው ይላል፡፡

ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጣ፤ ከፍ ያሉ ነገሮችን አዳመጠ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ተራ ሰው የሚገልጣቸው አይደሉም፡፡ ማንም ሰውም ከዚህ አስቀድሞ ሰምቷቸው አያውቅም፡፡ በቅፅበት ኒቆዲሞስ ወደ ከፍታ ወጣ፤ ነገር ግን መረዳቱ ጨለማ ነበር፡፡ ነገር ግን በራሱ ማስተዋል ገና የቆመ በመሆኑ ሊሸከማቸው ስላልቻለ ወደቀ፤ የጌታን ቃል እንዴት ሊሆን ይችላል? በማለት ጠየቀ፡፡ ጌታ የተናገረውን ነገር እንዲያብራራለት ሰው ከሸመገለ በኋላ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን በማለት ማብራሪያ ጠየቀ፡፡

ኒቆዲሞስ ስለ መንፈሳዊ ልደት ሰምቷል፡፡ ነገር ግን በመንፈስ አልተለማመዳቸውም /አያውቀውም/፡፡ኒቆዲሞስ ትውክልቱን ያደረገው ቁሳዊ መረጃ ላይ ነው ፤ይህንን ትልቅ ትርጉም ለመረዳትና ለመተርጎም ምሳሌ አድርጎ ያቀረበው የሰውን የሥጋ ልደት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል €œለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም€ /1ቆ.2·14/

በዚህ ሁሉ ነገር ኒቆዲሞስ ክብርና ጉጉት ይታይበታል፡፡ ጌታ የነገረው ነገር አላስቆጣውም፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ የማይቻል መሆኑን አስቦ ጥያቄ ጠይቆ ዝም አለ፡፡ ሁለት ነገሮችን ተጠራጥሯል፡፡ ምን አይነት እንደገና መወለድ እና የእግዚአብሔር መንግሥት፡፡ አይሁድ በየትኛውም ጊዜ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የተናገሩት ነገር የለም፡፡ ስለ ዳግም ልደትም እንዲሁ፡፡ ስለነዚህ ነገሮች ሰምተውም አያውቁም፡፡ ኒቆዲሞስን ያስደነቀውም ነገር ይህ ነው፡፡

ቅዱስ አውግስጢኖስ እንዲህ ይላል፡- ይህ ሰው ከአዳምና ከሔዋን የሚደረግ ልደትን ሰምቷል፤ ከእግዚአብሔርና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሚደረገው ልደት ግን አያውቅም፡የሚያውቀው ዘርን የሚተኩ ወላጆች በሞት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ነው፡፡ ነገር ግን ሕይወትን ስለሚሰጠው ስለ አዲሱ ልደት ያለው ግንዛቤ ከመረዳት በታች ነው፡፡ ንብረታቸውን የሚወርሱ ልጆችን የሚወልዱ ቤተሰቦች ያውቃል፡፡ ነገር ግን ዘወትር የሚኖሩ ልጆችን የሚወልዱ የማይሞቱ ወላጆችን በተመለከተ እውቀት የለውም፡፡ ሁለት ዓይነት መወለድ አለ፡፡ አንደኛው በምድር የሚደረግ ሁለተኛው ሰማያዊ፡፡ የመጀመሪያው ከሥጋና ከደም ሁለተኛው ከውኃና ከመንፈስ፤ የመጀመሪያዎቹ ለሞት የተጋለጡ ናቸው የኋለኞቹ ዘላለማውያን ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የተወለዱት ከወንድና ከሴት የኋለኞቹ ከእግዚአብሔርና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ኒቆዲሞስን በተመለከተ የሚያውቀው አንድ ልደትን ብቻ ነው፡፡

ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ /5/

ጌታ ይህንን እውነት ዝቅ አድርጎ እንዳይመለከተው በማሰብ አስቀድሞ የተናገረውን ነገር ደገመለት ፡፡ በርግጥ የእግዚአብሔር ቃል አዎ አይደለም ከሚለው አፍአዊ ነገር በዘለለ መልስን የሚጠይቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ ከመረዳት አቅሙ በላይ ቢሆንም ጌታ እንደገና መወለድ ትምህርቱ ላይ ጠንከር ብሎ ሄዷል፤ ያለዚህ ልደት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየትም ለመግባትም የሚያስችል መንገድ የለም፡፡

ሰው ከውኃና ከመንፈስ መወለድ አለበት ይላል፤ ስለምን ውኃን ይጠቀማል? ውስጣዊ የመንፈስ መታጠብን ለማመልከት ነው፡፡ /ቲቶ.3፡5፣ 1ቆሮ.6፡11፣ ሕዝ.36፡25/ €œ

ይህ ውስጣዊ የመንፈስ መታጠብ በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም ነው፡፡ እርሱ ብቻ ያጥባል ያነጻል ውስጣዊ ልባችንን አዲስ ያደርጋል፡፡ ጌታ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን በመቀየር በሰርጉ ቤት ለነበሩ ዕድምተኞች ደስታን እንደሰጠ በመንፈሱ የሰጠው ውጫዊ የሰውነት መታጠብ አይደለም፡፡

ይህ ውኃ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ ይጠጣ በማለት ለሳምራዊቷ ሴት የነገራት የሕይወት ውኃ ነው፡፡ በያዕቆብ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለው ውኃ አይነት አይደለም ያዕቆብ፣ ልጆቹና፣ ከብቶቹ የጠጡት ውኃ የሚያረካው የሥጋን ጥማት ነው፡፡ ጌታችን የሚሰጠን ውኃ ግን የነፍስን ጥማት የሚያረካ ነው፡፡

በአዲሱ ልደት ውኃ አስፈላጊ ሆኗል፤ ጥምቀት የሚፈጸመው በመዘፈቅ ነውና፡፡ ይህም ሞትን የመቀበልና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመቀበር ምልክት ነው፡፡ ከእርሱ ጋር እንነሣ ዘንድ የግድ ያስፈልገናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡-

እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፣ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን€

ከውኃና ከመንፈስ መወለድ የአሮጌውን ሰው መሞትና የአዲሱን ሰው ትንሣኤ ይጠይቃል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሆነውን አዲስ ሕይወትም መቀበል ነው፡፡ እርሱም የትንሣኤ መንፈስ ነው፡፡ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር የሚያደርገንን አዲሱን ሰው የመፍጠር ሂደት ነው፡፡ በፈጣሪያችን መልክ የተፈጠረውን አዲስ ሰው መመልከት ነው፡፡

በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምነው መስቀሉን ሊሸከሙ የሚወዱ ወገኖች በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ አለባቸው፡፡ የጌታ ቃል ትርጉም ለኒቆዲሞስ ምንድነው ብላችሁ ብትጠይቁኝ መልሴ የሚሆነው ጌታ ከሥጋ ትውልድ ወጣ ብሎ መንፈሳዊውን ትውልድ እንዲያስብ ሳበው የሚል ይሆናል፡፡

ጌታ እንዲህ በማለት የነገረው ይመስላል፡፡ ኒቆዲሞስ ሆይ እየተናገርሁህ ያለሁት ስለ ሌላ ልደት ነው፡፡ ስለምን ነው ንግግሬን ወደ ምድራዊ ነገር የምታወርደው፡፡ ስለምን የምነግርህ ነገር በተፈጥሮ ሕግ እንዲገዛ ታደርጋለህ? ይህ ትውልድ /ልደት/ በአይነት በሥጋ /በምጥ/ ከሚደረገው ትውልድ የተለየ ነው፡፡ አጠቃላይና የተለመደ ከሆነ ልደት ራስህን አውጣ፤ እኔ ሌላ ልደት ወደሚገኝበት መንፈሳዊ ዓለም ሾሜሃለሁና፡፡ ሰዎች ሁሉ ከዚህ አዲስ ልደት እንዲወለዱ እወዳለሁ፡፡ አዲስ ዓይነት ልደትን ይዤ ወደ ምድር መጥቻለሁ፡፡ ሰውን የፈጠርሁት ከምድር አፈርና ከውኃ ነበር፡፡ ይህ ያገለግለኛል ብዬ የፈጠርሁት ምርጥ ዕቃ የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቶ አግኝቸዋለሁና እንደገና ከአፈርና ከውኃ ልሠራው አልፈቅድም እንደገና በውኃና በመንፈስ እንዲወለድ እፈቅዳለሁ እንጂ፡፡

ምናልባት ከመካከላችሁ አንዱ እግዚአብሔር ሰውን እንዴት ከውኃ ፈጠረው ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ እኔ መልሼ እጠይቀዋለሁ፡፡ ሰውን እንዴት ከምድር አፈር አበጀው? ጭቃን እንደምን አድርጋችሁ ወደተለያየ ክፍል ትከፋፍሉታላችሁ? አጥንት፣ ነርብ፣ የደም ሥር፣ የደም ቧንቧ ከየት ተሠሩ? ቆዳ፣ ደም፣ ጉበት ከየት ተሠሩ? ይህ ታላቅ ሥራ ለምን የተከናወነ ይመስላችኋል? የተለያየውስ ቀለም? እነዚህ ሁሉ አይነቶች ውሁዶች ከየት ተገኙ? እነዚህ ሁሉ ነገሮች የምድርም የጭቃም አካል አይደሉምና፡፡

ምድር ዘርን ስትቀበል እንዴት አድርገው ሥር ይሰድዳሉ? ነገር ግን በእኛ አካል ውስጥ ሲሆኑ እነዚህ ዘሮች ይፈጫሉ፡፡ ምድር ዘርን ምን መግባ ዘር ፍሬ እንዲያፈራ ታደርጋለች? እንደገናስ ሰውነታችን እንዴት በእነዚህ ዘሮች ይገነባል? ምድር ውኃን ትቀበላለች ወደሚያፈራ ወይንም ትቀይረዋለች፡፡ የእኛ ሰውነት ግን ወይንን ተቀብሎ ወደ ውኃ ይቀይረዋል፡፡ በአሳብ የምትሰጠው ፍሬ ሁሉ የእርሷ ውጤት መሆኑን በምን በምን በምን መንገድ ነው የሚለውን ግን ማስረዳት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ምድር በፍሬዋ ሰውነታችንን ታጠግባለች፤ በእግዚአብሔር ላይ ያለኝ እምነት ብቻ ነው እነዚህ ሁሉ ነገሮች የምድር ውጤቶች ናቸው ብዬ እንድቀበል የሚያደርገኝ፡፡

አሁን እነዚህ ሁሉ ዓይነት ተጨባጭ ነገሮች በየቀኑ የሚከሰቱ ስለሆነ እምነት የሚይጠይቁ ስለሆነ መንፈሳዊ የሆነው ጉዳይ በቂ የሆነ ትኩረትና ቅድምና ማግኘት እንደሚኖርበት ትገነዘባላችሁ፡፡ የማይንቀሳቀሰው ምድር ለእግዚአብሔር ፈቃድ መልስ ይሰጣል ምድር የምትሸከመው ይህ ሁሉ ነገር የተገኘው ለዚህ ፈቃድ ነውና፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከመረዳታችን በላይ የሆነ ጽንፍ የያዘ ብዙ ምልክት ይፈጠራል፤ መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ በኖረ ጊዜ ምን ተከሰተ?

ምናልባት ከመካከላችሁ አንዱ ውኃ ለዚህ ልደት ለምን ያስፈልጋል? ብሎ ቢጠይቀኝ መልሴ የሚሆነው ይህ ልደት አምላካዊ ጠቀሜታ አለው የሚል ነው፡፡ መቃብር፣ መቀበር እምነት፣ ሕይወትና፣ ትንሣኤ እነዚህ ሁሉ ምሥጢራት በጥምቀት ጊዜ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ጭንቅላታችንን ውኃ ውስጥ እንነክራለን፤ ወደመቃብር እንደምንወርድ ሁሉ አሮጌውን ሰዋችን እንቀብር ዘንድ ጭንቅላታችንን ስናነሣ አዲሱ ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ ይገኛል፡፡

ከመንፈስ የሚወለድ እርሱ ማነው €œእንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዶ በአእምሮው መንፈስ ከሚታደስ ሰው በስተቀር€ /ኤፌ.4፡23/ በእርግጥ ይህ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደገና የተወለደ ሰው ነው፡፡

ይህ በዘላለማዊ ሕይወት የመተማመን ውጤት ነው፡፡ ይህም በጥምቀት አማካኝነት የሚፈጸም ነው፡፡ በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ሰው እንደምሕረቱ መጠን በአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብም በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ /ቲቶ.3፡5/ መንፈሳዊ ልጅነትን የተቀበለ ነው፡፡ በሌላ ንባብ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ይላል €œበመንፈስ ቅዱስ ስም ትጠመቃላችሁ€ /ሥራ.11፡16/፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ከተወለደ ወገን ውጭ በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቀ ማነው? እውነት እውነት እላችኋለሁ ከውኃና ከመንፈስ ከተወለደ ወገን ውጭ በመንፈስ ቅድስ የተጠመቀ ማነው? እውነት እውነት እላችኋለሁ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻላችሁም፡፡

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተጠመቀ ሰው ላይ ያደረ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን ምስጢር ይናገራል፡፡ ጥምቀት €œለአዲስ ልደት የሚሆን መታጠብ /ቲቶ.3፡5/ ተብሏል በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን መታደስ ነው፡፡

በምስጢረ ጥምቀት የኀጢአት እሥራት ይፈታል ስለዚህ ምክንያት ሕፃናት ሳይቀሩ ይጠመቃሉ፡፡€

€œሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይቻለውምና፡፡

ጥምቀት ኀጢአታችን ሁሉ ያጥባል፡፡ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ሰማያዊ ተፈጥሮአችንን ያድሳል ይህም በመንፈስ ቅዱስ ግብር የሚፈጸም ነው፡፡

በቅዱስ ጥምቀት ሰው ከሰይጣን ኀይል ነጻ ይሆናል፤ እንደ አርባ ቀን ሕፃንም ይሆናል፡፡ ይህም በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወን ነው፡፡ የተጠመቀውን ሰው የሚቀድስና የሚያነጻ መንፈስ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሰው ላይ ሰይጣን የወደደውን ያደርግበት ዘንድ አቅሙ አይኖረውም፡፡

ሰው በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድነትን ሲፈጥር እንደገና ከመወለዱ ባሻገር ክርስቶስን በሁለንተናው ይለብሰዋል /ገላ.3፡27/ ይህን በንባብ ብቻ የምንረዳው አይደለም፡፡የፍቅር መግለጫ ነውና፡፡ይህንን የምንረዳው ጌታ ሥጋችንን ተዋሕዶ በእኛ መጠን መወለዱና ስለእኛም ሲል ለአብነት በመወለዱ ነው፡፡

ምኩራብ(የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)

የካቲት 20 ቀን 2007 ዓ.ም.

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡

 

ትርጉም:- ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡)፡ ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።

 

ምንባባት

መልዕክታት

(ቆላ. 2÷16-ፍጻ.)፡- እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ÷ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር፡፡ ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት÷ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት÷ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት በሚሞላበትም በራስ አይጸናም፡፡

 

ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርሰቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ÷ ይህን አትንካ÷ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና፡፡ ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት÷ ለሥጋም ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም፡፡

(ያዕ. 2÷14-ፍጻ.)፡- ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ÷ “በሰላም ሂዱ÷ እሳት ሙቁ÷ ትጠግባላችሁም” ቢላቸው÷ ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡

 

ነገር ግን አንድ ሰው÷ “አንተ እምነት አለህ÷ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” ይላል፡፡ አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም፡፡ አንተ ሰነፍ ሰው÷ እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደ ሆነች ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ÷ በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር÷ በሥራውም እምነቱ እንደ መላችና ፍጽምት እንደ ሆነችም ታያለህን?

 

መጽሐፍ÷ “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት” የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጒበኞችን ተቀብላ÷ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ÷ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡

 

ግብረ ሐዋርያት

(የሐዋ.10÷1-8)፡- በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ÷ “ቆርኔሌዎስ ሆይ÷” አለው፡፡ ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና÷ “አቤቱ÷ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው÷ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል፡፡ አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ፡፡ እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል፡፡ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡” ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት÷ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ፡፡

 

ምስባክ

መዝ.68፡9፡- እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ ትዕይርቶሙ ለእለይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፤ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

ትርጉም፦ የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፡፡

 

ወንጌል

(ዮሐ. 2÷12-ፍጻ.)፡- ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ÷ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡ የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን÷ ርግቦችንም የሚሸጡትን÷ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን÷ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡ ርግብ ሻጮችንም÷ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም÷ “የቤትህ ቅናት በላኝ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ፡፡

 

አይሁድም መልሰው÷ “ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳያለህ?” አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም÷ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው፡፡ አይሁድም÷ “ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?” አሉት፡፡ እርሱ ግን ይህን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለ ተባለ ሰውነቱ ነበር፡፡ ከሙታን በተነሣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደ ነገራቸው ዐሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃልና ጌታችን ኢየሱስ በነገራቸውም ነገር አመኑ፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳለም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በስሙ አመኑ፡፡ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ግን አያምናቸውም ነበር፤ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና፡፡ የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም፤ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡