kuskuam 01

ጎንደር – የቅዱሳት መካናት ማኅደር

ሚያዚያ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ጸበል ጸዲቅ /ክፍል ሦስት/


ጎንደር ገብተናል፡፡ ዞር ዞር እያልኩ ለመቃኘት ጊዜ አልወሰድኩም፡፡ የምችለውን ያህል እግሬ እሰከመራኝ ተጓዝኩ፡፡ ጎንደር ውስጥ አንድ ቤተ ክርስቲያን ለማግኘት አንድ ኪሎ ሜትር መጓዝ አይጠበቅብዎትም፡፡ ቀና ብለው አካባቢውን በዓይንዎ መቃኘት ብቻ ይበቃዎታል፡፡  ከሰሜን ወደ ደቡብ፤ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ቢመለከቱ በእርግጠኝነት የቤተ ክርስቲያን የጉልላት መስቀል እንዳሻዎት ያገኛሉ፡፡ በቃ ወደ ተመለከቱበት አቅጣጫ ማምራት፡፡ 44ቱ ተቦት የሚለው አባባል ቀድሞ በጎንደር 44 ታቦታት ስለነበሩ አይደል?

ወቅቱ የዐብይ ጾም በመሆኑ ከሌሊት ጀምሮ ስብሐተ እግዚአብሔር እንደ ጅረት ውኃ ያለማቋረጥ ከሊቃውንቱ አንደበት ይፈስሳል፡፡ ተኝተውም ይሁን ሥራ ላይ ሆነው አብረው ለማዜም ይገደዳሉ፡፡ ይህንን ዓለም አስረስተው ሰማያዊውን መንግሥት በተመስጦ ያስባሉ፡፡ ነፍስዎ በሚደርሰው ስብሐተ እግዚአብሔር ይለመልማል፡፡

ከጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት፤ ከዚያም እስከ 9፡00 ሰዓት ምግብ ቤቶች፤ ሆቴሎችና ሻይ ቤቶች ሳይቀር ወንበሮቻቸውን ታቅፈው የሰው ያለህ ማለታቸው ጎንደር ውስጥ በጾም ወራት የተለመደ ነው፡፡ አንገቱ ላይ ክር ያላሰረ ለማየት ይቸግራል፡፡ ጎንደር ፈካ ደመቅ ማለት የምትጀምረው ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ሥርዓተ ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡ ጎንደር! የታላላቅ ቅዱሳት መካናት፤  የሊቃውንት ማኅደር፤ የነገሥታት አሻራ ያገዘፋት ከተማ!!

የጋዜጠኞቹ ቡድን ጎንደርን ተከፋፈልናት፡፡ በውስጧ ሸሽጋ ያኖረቻቸውን የአብያተ ክርስቲያናት ታሪክ፤ የሊቃውንቱ የሕይወት ተሞክሮ ለሌሎች ለማቃመስ ቸኩለናል፡፡ ለዛሬ ጎንደር ካቀፈቻቸው ቅዱሳት መካናት መከካል አንዱን ከብዙ በጥቂቱ እንካችሁ ጸበል ጸዲቅ ቅመሱ፡፡

የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም
kuskuam 01የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም ከጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ተራራው አናት ላይ በጥንታዊ ስልጣኔ አሻራ ባረፈበት ግንብ አጥር ታቅፎ ለሚያየው ውስጡን ይመረምሩ ዘንድ ይጋብዛል፡፡ ዓይኔም ልቦናዬም አርፎበታልና ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንና ቤተ መንግሥት ለማወቅ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ አቀበቱን እንደወጣሁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአብነት ትምህርት ተማሪዎች ጎጆዎችን አገኘሁ፡፡ ከተማሪዎቹ መካካል አንዱን እንኳን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ወደ ገዳሙ የሚያስገባው መንገድ እየተሠራ በመሆኑ አንዱን ሠራተኛ ጠየቅሁት፡፡ ወደ ጫካ ለቅኔ ቆጠራ ሄደዋል አለኝ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ ተጠጋሁ፡፡ ከሦስት ሜትር በላይ እርዝመት ያለውና በኢትዮጵያውያን  ጠቢባን በድንጋይ የተገነባ ግንብ ጥንታዊነቱን በሚመሰክር ሁኔታ እርጅና ቢጫጫነውም ጥንካሬው ጎልቶ ይታያል፡፡ አጥሩ በዐፄ ፋሲል ግንብ ዲዛይን የተሠራ ነው፡፡   

ተሳልሜ ደጀ ሰላሙን እንዳለፍኩ አባቶችን ሳፈላልግ የገዳሙ የሙዝየም አስጎብኚና የቅኔ መምህሩ የኔታ ዳንኤል ኃይሉን አገኘሁ፡፡ የመጣሁበትን አስረድቼ፤ የተጻፈልኝን የፈቃድ ደብዳቤ በማሳየት ለምጠይቃቸው ጥያቄ ይመልሱ ዘንድ ፈቃደኛ በመሆናቸው አንድ ጥግ ያዝን፡፡ የነገሩኝን እንዲህ አዘጋጀሁት?!

አመሠራረቱ፡-
የደብረ ጸሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም በ1930ዎቹ ዓ.ም በአፄ በካፋ ባለቤት በእቴጌ ምንትዋብ አማካይነት የተሠራ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ አመሠራረቱም ዐፄ በካፋ ከሞቱ በኋላ እቴጌ ምንትዋብ ልጃቸውን ኢያሱን አንግሠው ከዐፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት ግቢ በመውጣት ይህ ዓለም ይቅርብኝ፡ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም በስደት በግብፅ በደብረ ቁስቋም ተራራ ላይ እንደተገኘች ሁሉ እኔም ለብቻዬ ልቀመጥ በማለት ቤተ መንግሥታቸውን ጥለው ቤተ ክርስቲያኑን በማሠራት ተቀመጡ፡፡  ከዚሁ ጋር በማያያዝም ቤተ መንግሥታቸውን አሠሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንና ቤተ መንግሥቱን ለማሠራት አንድ ሺሕ ግንበኞችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን ለሁለት በመክፈል አምስት መቶው ሠራተኞች አንድ ቀን ሲሠሩ ሌሎቹ ደግሞ እያረፉ በየተራ ሠርተውታል፡፡ቤተ ክርስቲያኑንም ስደታቸውን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስደት ጋር በማያያዝ በደብረ ቁስቋም ሰየሙት፡፡ ከሁለት ሃምሳ በላይ ቀሳውስትና ካህናት አገልጋዮች ነበሩት፡፡

እቴጌ ምንትዋብ ሲያርፉም በቤተ ክርስቲያኑ ምድር ቤት ውስጥ ባሠሩት መቃብር ቤታቸው አስከሬናቸው እንዲያርፍ የተደረገ ሲሆን ልጃቸው ኢያሱና የኢያሱ ልጅ ኢዮአስkuskuam 03 ሲያርፉም አብረው በእቴጌ ምንትዋብ መቃብር ቤት ተቀብረዋል፡፡

በ1881 ዓ.ም. ደርቡሽ ጎንደርን ሲወርር ጎንደር የሚገኙትን ብዙዎቹን ቤተ ክርስቲያናት ስያቀጥልና ሲያወድም ካህናቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታቦት ወደ በለሳ በማሸሽ አስቀመጡት፡፡ ደብረ ቁስቋም ቤተ ክርስቲያንም ሙሉ ለሙሉ ወደመ፡፡ ቤተ መንግሥቱንም ደርቡሽ አፈራረሰው፡፡ አብዛኞቹ ቅርሶችም ተቃጠሉ፡፡ የተረፉትም ቢሆን ተዘርፈው ተወሰዱ፡፡ ካህናቱም ወደተለያዩ ቦታዎች ተበተኑ፡፡

ቅርሶች፡- ከጦርነቱ በኋላ ታቦቱን ወደነበረበት በመመለስ ቀድሞ እቃ ቤት የነበረውን  ቤት ቤተ መቅደስ በማድረግ በጥቂት ካህናት ብቻ ለሰማኒያ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በ1960ዎቹ ዓ.ም. ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሁን ያለውን ቤተ ክርስቲያን አሠሩት፡፡ የእቴጌ ምንትዋብና የልጃቸው ኢያሱ፤ እንደሁም የኢያሱ ልጅ ኢዮአስን ዓፅም በአንድ ላይ በመሰብሰብ በሳጥን ውስጥ እዲቀመጥ ተደረገ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሙዝየሙ ውስጥ ከሚጎበኙ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡

በሙዝየሙ ውስጥ የእቴጌ ምንትዋብና የልጆቻቸው በእንጨትና በጠፍር/ቆዳ/ የተሠራ አልጋ፤ በቀርከሃና በቆዳ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎች ማስቀመጫ ሻንጣዎች፤ ሚዛን፤ የደርቡሽ ጦር ካወደማቸው ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት የተረፉት ወንጌል ቅዱስ፤ ተአምረ ኢየሱስ፤ ግንዘት፤ ስንክሳር፤ ነገረ ማርያም፤ ሃማኖተ አበው፤ አሥራ አራቱ ቅዳሴያት፤ ግብረ ሕማማት፤ ገድለ ሠማዕታት፤. . . ከበሮ፤ የተለያዩ መጠን ያላቸው መስቀሎች፤ ነጋሪት፤ ከሙዝየሙ ውጪ በሩ አጠገብ የእቴጌ ምንትዋብ የድንጋይ ወፍጮ፤ . . .  ይገኛሉ፡፡

kuskuamቅዱሳት ሥዕላት፡- በሙዝየሙ ውስጥ በቅርስነት ከተያዙት ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስለ ፍቁር ወልዳና የቅዱስ መርቆርዮስ ቅዱሳት ሥዕላት ይገኙበታል፡፡

ቤተ መንግሥት፡- ቤተ መንግሥቱ ሰባት በሮች አሉት፡፡ የእቴጌ ምንትዋብ መኝታ ቤት፤ የገላ መታጠቢያ ቤት፤ ሣሎን፤ በዘመኑ የነበረው ታሪክ ጸሐፊው ጀምስ ብሩስ ይኖርበት የነበረው ክፍል፤ ካህናቱና ቀሳውስቱ የሚመገቡበት የግብር ቤት፤ ቤተ ክርስቲያኑንና ቤተ ክርስቲያኑን ያነጹት ባለሙያዎች ማረፊያ ክፍሎችና ዕቃ ማስቀመጫ ክፍሎች፤ . . . ፈራርሰው ይታያሉ፡፡

ጉባኤ ቤት፡- ጥንት የድጓ፤ የቅኔ፤ የአቋቋም፤ የቅዳሴ ጉባኤ ቤቶች እንደነበሩና ደርቡሽ ቤተ ክርስቲያኑን ካፈረሰ በኋላ ግን ጉባኤ ቤቶቹkuskuam 08 ተፈትተው ለረጅም ዘመናት ሳይተከሉ ኖረዋል፡፡ ጉባኤ ቤቱ በተደራጀ መልኩ ከተተከለ ሃያ ዓመታት ብቻ አስቆጥሯል፡፡ የቅኔ፤ የአቋቋም፤ የድጓና የቅዳሴ ጉባኤ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከ500 በላይ ተማሪዎች ሲኖሩ 280 የሚደርሱት የቅኔ ተማሪዎች ናቸው፡፡

መረጃዎቻችንን እንዳሰባሰብን ያመራነው ወደ ጉባኤ ቤት ነው፡፡ ከየኔታ ዳንኤል ኃይሉ ጋር ተያይዘን ስንሄድ የቅኔ ተማሪዎቻቸው ከያሉበት ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ሌሊት ዕለቱን በማስመልከት የኔታ ካስረዷቸው በኋላ ለቅኔ ቆጠራ ይሠማራሉ፡፡ የኔታ በተማሪዎቻቸው ተከበቡ፡፡ የነገራ ሰዓት በመሆኑ ለጥቂት ደቂቃዎች እንድታገስ ጠየቁኝ፡፡ አላመነታሁም፡፡ ተማሪዎቹ ወንበር አውጥተው እንዲቀመጡ ካመቻቹላቸው በኋላ በአእምሯቸው ሲያመላልሱት የቆዩበትን ቅኔ ቆጠራ መዝረፍ ጀመሩ፡፡ ሲሳሳቱ እያረሙ፤ ያልተሳካለትን እየገሰጹ ቆዩ፡፡

 
የተማሪዎቹን የውድድር ስሜትና ለትምህርቱ ያላቸው ፍላጎት እያስገረመኝ ከተማሪዎቹ መካከል አይኖቼ ድንገት በለጋነት እድሜ ክልል የሚገኙ መነኩሲት ላይ አረፉ፡፡ ላነጋግራቸውም ወሰንኩ፡፡

የኔታ ከዚህ በላይ ሊያስቆዩኝ አልፈለጉም፡፡  ጉባኤውን አቋረጡት፡፡ እኔም እማሆይን ለመጠየቅ በመፍጠን ማንነታቸውን፤ ለምን መማር እንደፈጉ ጠየቅኋቸው፡፡

kuskuam 07“እማሆ ወለተ መድኅን እባላለሁ፡፡ ከአክሱም ነው የመጣሁት፡፡ በልጅነት ከመነኮስኩ አይቀር ጉባኤ ቤት መግባት አለብኝ ብዬ ስለወሰንኩ እዚህ እየተማርኩ እገኛለሁ፡፡ ትምህርቱንከጀመርኩ አንድ ዓመት ሆኖኛል፡፡ ጉባኤ ቃና፤ ዘአምላክየ፤ ሚበዝኁ፤ ዋዜማ፤ ሥላሴ፤ ዘይእዜ፤ ክብር ይእቲ፤ እጣነ ሞገርን አልፌ መወድስ ላይ ደርሻለሁ፡፡ እግዘአብሔር ቢፈቅድ ትምህርቴን አጽንቼ በመያዝ እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንደ እማሆይ ገላነሽ ለመሆን ነው ምኞቴ” አሉኝ፡፡ ምኞታቸው እንዲሳካ ተመኘሁ፡፡

ከቀደሙት ነገሥታት የሃይማኖት ጽናትንና ቅርስን ለትውልድ ማቆየትን ተማርኩ፡፡ ከጉባኤ ቤቶቹ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የማይነጥፍ የሊቃውንት ምንጭ እንዳላት ተገነዘብኩ፡፡   
የኔታንና ተማሪዎቹን ተሰናብቼ ሌላ መረጃ ልቆፍር ተጓዝኩ፡፡

ይቆየን

tsebele tsedeke 3

ጸበል ጸዲቅ /ክፍል ሁለት/

ሚያዚያ 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ደብረ ገነት ሸረት መድኀኔዓለም ገዳም
ሚያዚያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

tsebele tsedeke 3ከንጋቱ 12፡30 ደምበጫ ከተማ ላይ ካረፍንበት የማኅበረ ቅዱሳን ከራድዮን ምግብ ቤት ተነስተን ከወረዳ ማእከሉ ወንድሞቻችን ጋር ሆነን ወደ ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በማምራት ጸሎት አደረስን፡፡ በያዝነው እቅድ መሠረት ዲያቆን ቴዎድሮስ ኃይሉና ዲያቆን ዮሴፍ ይኩኖ አምላክ የጽርሐ አርያምን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲሰሩ እዚያው ትተናቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ቶማስ በየነ፤ የቪዲዮ ካሜራ ባለሙያው ሙሉጌታ፤ ዲያቆን ታደለ ሲሳይና እኔ ሆነን የደብረ ገነት ሸረት መድኀኔዓለም ገዳምን ለመዘገብ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን እግዚአብሔርን ተስፋ አድረገን በሾፌራችን ነብያት መንግስቴ እየተመራን የ47 ኪሎ ሜትሩን መንገድ ተያያዝነው፡፡

ዋድ የገጠር ከተማን፤ ዋድ ኢየሱስ፤ ዋድ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያናትን አልፈን፤ ደግን ወንዝን ተሻግረን፤ ዘለቃን የገጠር ከተማን አልፈን ወደ ገዳሙ መግቢያ ደረስን፡፡ ከተራራው አናት ላይ ሆነው ወደ ገዳሙ ሲመለከቱ እልም ባለ በረሃ ውስጥ ለብቻው ለምልሞ የተገኘ የምድር ገነት ያስመስለዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ እግዚአብሔርን ደጅ በመጥናት በጸሎትና በልማት አገልግሎት ላይ የተጠመዱት መነኮሳትና መነኮሳይያት ማረፊያ ቤቶች፤ የመድኀኔዓለምንና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያናትን በመክበብ እጅብ ብለው ደምቀው ይታያሉ፡፡  

አርባ ሰባት ኪሎ ሜትሩን ለማገባደድ 2፡30 ሰዓት ፈጅቶብን የደረስነው ከጠዋቱ 3፡00 ላይ ነው፡፡ ከመኪናችን ወርደን በእድሜ ጠገብ ዛፎች፤ ጥላ ተጋርደን የሙዝ፤ የፓፓያ፤ የብርቱካን፤ የአቦካዶ፤ . . . ዘርዝረን በማንጨርሳቸው የፍራፍሬዎችና የሸንኮራ አገዳ ተክሎችን እያለፍን ጸበል መጠመቂያ ሥፍራ ላይ ደረስን፡፡ ከተለያዩ የገዳሙ አቅራቢያ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በመጡ ተጠማቂዎች ሕጻናትን ጨምሮ ተሞልቷል፡፡

ከተራራው ሥር የሚፈልቁ ምንጮች መውረጃ ቦይ ተዘጋጅቶላቸው አትክልቶቹን ያለመሰልቸት ያጠጣሉ፡፡ ጸበሉም ተጠማቂዎች ከተጠመቁ በኋላ ወደ አትክልልቶቹ መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡ በግዮን፤ ኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች የተከበበ እስኪመስል ድረስ የንጹህ ውኃ ጅረቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በልምላሜ በተሞላው ገዳም ተውጠው ይቀራሉ፡፡ የሚባክን ውሃ የለም፡፡ ድካማችን ሁሉ ከላያችን ላይ ተገፍፎ በብርታት፤ በእርካታና በተመስጦ ተሞልተናል፡፡ የምናያቸው፤ የምንሰማቸው ድምጾች ሁሉ አዳምና ሔዋን የኖሩባንት ገነትን tsebele tsedeke 5በዓይነ ሕሊናችን እንድናስብ አስገድዶናል፡፡ ደብረ ገነት ሽረት መድኀኔዓለም በምድር ላይ ያለች የገነት ተምሳሌት ሆና ታየችን፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ስንገባ በገዳሙ ውስጥ በምናኔና ገዳሙ በሚያከናውናቸው የልማትና የአስተዳደር ሥራዎች አበምኔቱን በማገዝ ላይ የሚገኙት አባ ዳዊትን ከሌሎች መነኮሳት ጋር በመሆን የእለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ አገኘናቸው፡፡ ቡራኬ ተቀብለን በገዳሙ ሥርዓት መሠረት አባቶች አደግድገው እግራችንን አጠቡን፡፡

የገዳሙ መሥራችና አበምኔት አባ ገ/ኢየሱስ አካሉ ወደ ገዳሙ የሚያስገባውን ጥርጊያ መንገድ ለማሰራት ዘለቃ ወደሚባለው ከተማ በመሔዳቸው የምንፈልገውን መረጃ አባ ዳዊት ሊሰጡን እንደሚችሉ ተስማማን፡፡

አጭር መረጃ ስለ ገዳሙ፡- tsebele tsedeke 4
የደብረ ገነት ሸረት መድኀኔዓለም ገዳም በአባ ገ/ኢየሱስ አካሉ በ1969 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1973 ዓ.ም. በሣር ክዳን ተተከለች፡፡ ሥፍራው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ የነበረ ሲሆን አንበሳ፤ ነብርና ዘንዶ በብዛት ይገኙ እንደነበር አባ ዳዊት ይገልጻሉ፡፡ ቀስ በቀስ ገዳማውያን እየተበራከቱ የልማት ሥራው እየሰፋ ሲሔድ የገዳሙ ይዞታም ሊሰፋ ችሏል፡፡ የክልሉ መንግስት በገዳሙ ውስጥ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰፊ የእርሻ መሬት ለገዳሙ ተሰጥቷል፡፡ ዳጉሳና በቆሎ እንዲሁም የሸንኮራ አገዳ በስፋት ይመረትበታል፡፡  

በሁለት ቦታዎች ላይ ሞፈር ቤቶች፤ ተራራው ላይ በስተደቡብ አቅጣጫ የአቡነ አረጋዊ ገዳም ቋርፍ ቤት ይገኛል፡፡ በገዳሙ ውስጥ 600 መናንያን ሲኖሩ 320ዎቹ መነኮሳት፤ 280ዎቹ ደግሞ መነኮሳይያት ናቸው፡፡ መነኮሳቱ በወንድ ሊቀ ረድእ፤ መነኮሳይቱ በሴት ለቀ ረድእ ይመራሉ፡፡ የእለት ተእለት ሥራቸውንም በሊቀ ረድኦቻቸው አማካይነት እየተመደቡ ያከናውናሉ፡፡ አረጋውያኑ ደግሞ በጸሎት፤ ቤተ ክርስቲያኑን በመጠበቅ፤ አትክልቶቹን ከአውሬ በመከላከል ገዳሙን ይረዳሉ፡፡ የገዳማውያኑ የጸሎት፤ የሥራና የምግብ ሰዓታትም የተወሰኑ ናቸው፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ የቅዱስ ሚካኤል፤ የአቡነ አረጋዊና የአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ታቦት በዚሁ ገዳም ይገኛሉ፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጣሪያው በሣር ክዳን የተሸፈነ ሲሆን ሳይፈርስ በቅርስነት እንዲያዝ በመወሰኑ ከመድኀኔዓለም ክርስቲያን በስተምእራብ አቅጣጫ ከተራራው ሥር ከሚገኘው ቋጥኝ ድንጋይ እየተጠረበ ቤተ ክርስቲያኑ በመገንባት ላይ ነው፡፡

የዮርዳኖስ ጸበል፤ የአቡነ አረጋዊ፤ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የቅዱስ ሚካኤል ጸበል በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ሕሙማን እየተጠመቁ ፈውስ በማግኘት ላይ ናቸው፡፡  የዮርዳኖስ ጸበል አፈሩን ከኢየሩሳሌtsebele tsedeke 6ምና ከዋልድባ ገዳማት እንደመጣም አባ ዳዊት ገዳሙን እያስጎበኙን ነግረውናል፡፡

የአብነት ትምህርት ገዳሙ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ከ1975 ዓ.ም. እስከ 1977 ዓ.ም. በጉባኤ ቤቱ ቅዳሴን ከአባ ገብረ ማርያም ተምረው በማጠናቀቅ አባ ገብረ ማርያም ሌላ ገዳም ለማቅናት በመሄዳቸው ጉባኤውን የተረከቡት መምህር ገብረ ሥላሴ ፈንታ ለ28 ዓመታት የቅዳሴ ትምህርት በማስተማር ላይ ናቸው፡፡ ከሁለት መቶ በላይ ደቀመዛሙርትም እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ ታላላቅ ሊቃውንትንም አፍርተዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ በአባ ገብረ ማርያም ከተማሩት አባቶች መካከልም ብፁዕ አቡነ አብርሐም አንዱ ናቸው፡፡

ይቆየን

ጸበል ጸዲቅ (ክፍል አንድ)

ሚያዚያ 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች ቡድንን የያዘና ሰባት አባላትን ያቀፈው ልዑክ በምዕራብ ጎጃም፤ ደቡብ ጎንደርና ሰሜን ጎንደር የተመረጡ ቅዱሳት መካናትና አድባራትን ለመዘገብ ሃያ ሁለት ቀናት ቆይታ ለማድረግ ከሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሰናል፡፡ በተጓዝንባቸው ቦታዎች ያጋጠሙንና እያከናወንናቸው ያሉትን ሥራዎች ለአንባቢያኑ እናቀርባለን፡፡ ሂደቱን በተመጠነና በቅምሻ መልክ የምናቀርብ በመሆኑ ከዚህም ከዚያም የምናገኛቸውን መረጃዎች ለአንባቢያን እናደርሳለን፡፡ በዚህም ምክንያት የጉዞ ማስታወሻችንን ጸበል ጸዲቅ በሚል ሰይመነዋል፡፡

መነሻ :-
መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፤ በእርሱም ታመን፤ እርሱም ያደርግልሃል /መዝ.36፥5/ እንዲል ቅዱስ ዳዊት መንገድ ከመጀመራችን በፊት በማኅበሩ ጽ/ቤት አሸኛኘት ተደርጎልናል፡፡ እስካሁን ማኅበሩ ካደረጋቸው የጋዜጠኞች የሕብረት ተልእኮ አንጻር ይህ ልዑክ በብዛት ሆኖ መጓዙና ብዛት ያላቸው ቅዱሳት መካናትን በማካለል ረገድ ለየት እንደሚያደርገው የተገለጸለት ሲሆን በጉዞው የተለያዩ ፈተናዎች ቢገጥሙት እንኳን በትዕግሥትና በጥበብ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ተልእኮውን አሳክተን እንድንመለስ  አደራውን ተቀብለን በአባቶች ምክር፤ ጸሎትና ቡራኬ ተደርጎልን ተንቀሳቅሰናል፡፡

ከረፋዱ 4፤05 ሰዓት መነሻንን ብናደርግም ከመኪና ጥገና ጋር በተያያዘ ለተወሰኑ ሰዓታት በመቆየት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጥገናውን በማጠናቀቅ ጉዞውን ጀመርን፡፡ ጫንጮ፤ ደብረ ጽጌ፤ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ደብረ ሊባኖስ ገዳም መገንጠያ፤ ፍቼ፤ ገደብ፤ ገብረ ጉራቻ፤ ኩዩን አልፈን  ጎሐ ጽዮን ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ደረስን፡፡ ከጎሐ ጽዮን እስከ ዐባይ ድልድይ ያለውን የ20 ኪሎ ሜትር አስፈሪውን መንገድ የመኪናችን ሾፌር ነብያት መኪናውን እየተቆጣጠረ ጠመዝማዛና ቁልቁለታማውን መንገድ ካለ ስጋት እንድንጓዝ አስችሎናል፡፡ ፍርሃትና ጭንቀት ከእኛ እንዲርቁም የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ቶማስ በየነ ፈገግታ አዘል ጨዋታዎች አግዘውናል፡፡ ቪዲዮ ቀራጩ ሙሉጌታም አልፎ አልፎ ለቴሌቪዥን ፕሮግራም ግብአት የሚሆኑ ምስሎችን ለመውሰድ መኪናውን እያስቆመ ወርዶ ይቀርጻል፡፡ ሌሎቻችን ለራሳችን በሚመቸን መልኩ ውስጣችን የተፈጠረውን ስሜት በራሳችን አገላለጽ በማስታወሻ ደብተራችን እንከትባለን፡፡

ሃያ ኪሎ ሜትሩን አገባደን አባይ ድልድይ ደረስን፡፡ የኦሮሚያንና የአማራን ክልል የሚለየውን የአባይ ድልድይ ላይ ሁላችንም ወርደን ለማስታወሻና ለዘገባችን የሚረዳንን ፎቶ ግራፍ በመነሳትና በማንሳት ተመልሰን የአባይን ድልድይ ተሻግረን ቀሪውን እስከ ደጀን ያለውን 20 ኪሎ ሜትር ተያያዝነው፡፡

የአባይን ድልድይ እንደተሻገርን በሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ የተተከለውን የአባይ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ተሳልመን አለፍን፡፡ የአባይ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጳጉሜን ሦስት ቀን በድምቀት እንደሚከበርና በእለቱም የአባይ ውኃ ወደ ጸበልነት እንደሚቀየር የቪዲዮ ባለሙያው ሙሉጌታ የሚያውቀውን ነገረን፡፡ ተራራውን እየወጣንም የኪዳነ ምሕረት፤ የቅዱስ ገብርኤል፤የአቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ እንዲሁም የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያናትን እየተሳለምን አጠናቀን ደጀን ደረስን፡፡  

ከደጀን የትመን፤ ሉማሜ፤ አምበር፤ ራባ ጫካዎች፤ ደብረ ማርቆስን አልፈን ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት ሲሆን ከአዲስ አበባ ደምበጫ ከተማ 350 ኪሎ ሜትር አጠናቀን የደምበጫ ወረዳ ማእከል አባላት ወንድሞቻችን በአክብሮት ተቀበሉን፡፡ ወዳዘጋጁልን ማረፊያም በማምራት በእንግድነት ተቀብለውናልና እግራችንን አጥበው እረፍት አደረግን፡፡ ከእራት በኋላም ውሏችንን በመገምገም እንዲሁም አርብ ስለምንሰራው ሥራ ውይይት በማድረግና ሌሊት የምንነሳበትን ሰዓት በመወሰን በአንድነት ጸሎት አድርሰን ተኛን፡፡
ሚያዚያ ሦስት ውሏችን ይህንን ይመስል ነበር፡፡ እንዲህም አለፈ፡፡

ይቆየን

liche 10

ከልቼ ቤተመንግሥት እስከ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ

ታኅሣሥ 15 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

liche 10በአብዛኛው ኢትዮጵያውን ዘንድ የሚወደዱትና “እምዬ” በሚል ቅጽል የሚጠሩት ዐፄ ምኒልክ ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ነበሩ፡፡ “እምዬ” የሚለውን ቅጽል ሕዝቡ የሰጣቸው፤ የተራበውን ሕዝብ ግብር የሚያበሉ፤ ያለ ፍርድ ሰው የማይቀጡና ደግ ስለሆኑ ነው፡፡

ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ሣህለ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ ዓ.ም. ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ከሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ በአንጎለላ መቅደላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሡ። አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የምኒልክን መወለድ ሲሰሙ “ምን ይልህ ሸዋ” በሉት ብለው ስም አወጡ። እሳቸው “…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበር ‘ምኒልክ’ የኔ ስም ነው ብለው ነበር። ሆኖም፣ በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ከዚህ በኋላ “ምኒልክ የኔ ስም አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት” ብለው አዘዙ። ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፍ ።

ምኒልክ እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ መንዝ ውስጥ ጠምቄ በሚባል አምባ ከእናታቸው ዘንድ አደጉ።አያታቸው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሲሞቱliche 7 የሸዋውን አልጋ የምኒልክ አባት ንጉስ ኃይለ መለኮት ወረሱ።ዓጼ ቴዎድሮስ በጥቅምት ወር ፲፰፻፵፰ ዓ/ም ትግራይንና ወሎን አስገብረው፣ ምኒልክ ገና የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳሉ፤ የድፍን አማራንና የወሎን ጦር አስከትተው የሸዋውን ንጉሥ ኃይለ መለኮትን ለማስገበር ሸዋ ገቡ። ሁለቱ መሪዎች ጦርነት ለመግጠም ተዘጋጅተው ሲጠባበቁ ንጉሥ ኃይለ መለኮት ባደረባቸው ሕመም ጥቅምት ፴ ቀን ፲፰፵፰ አረፉ። በዚህ ጊዜ የሸዋ መኳንንት ሕፃኑን ምኒልክን ከጠላት እጅ እንዳይወድቅባቸው ይዘው ሸሹ፤ ዳሩ ግን ዐጼ ቴዎድሮስ እንደሚከታተሏቸው ስላወቁ ኅዳር ፴ ቀን ፲፰፵፰ ዓ/ም የልጅ ምኒልክ ሠራዊትና የዐፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት በረከት በተባለው ቦታ ላይ ገጥሞ የምኒልክ ሹማምንት አቶ በዛብህ፣ አቶ አንዳርጋቸው ሁሉ ተያዙ። ልጅ ምኒልክም ለቴዎድሮስ ገቡ። ምኒልክ መቅደላ ገብተው በቁም እሥር ይቀመጡ እንጂ ከቴዎድሮስ ልጅ ከመሸሻ ጋር አብረው አደጉ። ወዲያውም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሹመው በጥር ወር ፲፰፻፶፮ ዓ.ም የዓፄቴዎድሮስን ልጅ ወይዘሮ አልጣሽን አገቡ። በዚህ ሁኔታ ፳፪ ዓመታቸው ድረስ ለአሥር ዓመታት ዐፄ ቴዎድሮስ ግቢ ኖሩ።

ዐፄ ቴዎድሮስ ምኒልክን እንደልጃቸው ያዩዋቸውና በታላቅ ጥንቃቄም ያስተምሯቸው ነበር። ምኒልክም ቴዎድሮስን እንደአባት ይወዷቸው እንደነበር ይገለጻል። ምኒልክ ከመቅደላ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፰፻፶፯ አምልጠው አንኮበር ገቡ።

 

በአንኮበር ጥቂት ወራት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ደብረ ብርሃን ወርደው አዲሱን ከተማቸውን ልቼን እያሠሩ ተቀመጡ። ዐፄ ምኒልክ የመጀመሪያ ቤተመንግሥታቸው ልቼ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናትና የልቼ ቤተ መንግሥት ፍርስራሽ ያስረዳል፡፡ በተለይም ዐፄ ምኒልክ ከየካቲት ፲፰፻፷ ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ ፲፰፻፸፰ ዓ.ም በልቼ ቤተመንግሥት እንደነበሩ በተጻጻፉት ደብዳቤ አማካኝነት ታውቋል ፡፡

ምኒልክ ከልቼ ቤተመንግሥት ሳሉ ከሀገር ውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ መልእክቶችን ተለዋውጠዋል። ከየካቲት ፮ ቀን ፲፰፻፸፰ ዓ.ም እስከ የካቲት ፲ ቀን፲፰፻፸፰ ዓ.ም ከዐፄ ዮሐንስ ጋር ልቼ ላይ ውጊያ አደርገዋል፡፡ በኋላም የካቲት ፲፪ ቀን ፲፰፻፸፰ ዓ.ም ውጊያ ለማቆም ፣የልቼ ሥልጣን ማካፈልንና በሌሎች ጉዳዮችም ለመረዳዳት ስምምነት አድርገዋል፡፡ ይህም የልቼ ስምምነት ተብሎ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

ኤስ ሩቬንደንና ሪቻርድ ፓንክረሥት እንደዘገቡት ዳግመኛ በመጋቢት ፲፰፻፸፰ ዐፄ ዮሐንስና ዐፄ ሚኒሊክ ልቼ ላይ የማዕረግ አጠቃቀምን በተመለከተ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ታሪከ ነገስት ዘዳግማዊ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው የዐጼ ምኒልክን ንግሥናና የልቼ ቤተ መንግሥትን ሥነ ሥርዓት እንዲህ ይገልጹታል ፤ “….(ምኒልክ) መስቀልን ውለው ልቼ ከተማቸው ወጡ፡፡ ከዚያም በሥርዓተ መንግሥት ዘውድ የሚደፉበት፣ አዳራሽ የሚገኙበት ጊዜ ነውና ልቼ ከተማ ከዕድሞው ግቢ ሰፊ ዳስ ተሠርቶ ግብር ለማብላት ልክ መጠን የሌለው ሁኖ ተዘጋጅቶ ነበረ፡፡ ደግሞም ከዳሱ አፋፍ ከሰገነቱ ዝቅ ያለ ሥራው ልዩ ልዩ የሆነ መንበር ተሠርቶ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ የዳሱ ጌጥ ሥራው የቆመበትም ሁሉ በልዩ ልዩ ዓይነት ግምጃ የተሸፈነ ነበር፡፡  ከዚህም አስቀድመው ባዋጅ ‘በምገዛው አገር የሚኖር ካህን ከየደብሩ መስቀልና ጥና ከአልባሳቱ ጋር እየያዘ በጥቅምት ሁለት ቀን ይግባ’ ብለው አዘውት ጠቅሎ ገባ፡፡ በዚህም ጊዜ በእስክንድርያ ሃይማኖት ሳይገዘት ሰንብቶ የነበረው ሲገዘት ሰነበተ፡፡

ከዚህም በኋላ በጥምቅት በ፫ ቀን ቅዳሜ ማታ ንጉሥ ከነሠራዊታቸው ከልቼ ተነሥተው ደብረ ብርሃን ወርደው አደሩ፡፡ ሲነጋ ንጉሡ ከመቅደስ ልብሰ መንግሥት ለብሰው መምህር ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ግርማ ሥላሴ ንጉሡን በወርቅ አልጋ አስቀመጧቸው፤ ዘውዱንም ደፉላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የመምህራኑ ጸሎት ይህ ነው፡፡ እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ ንጉሥ ምኒልክ ወብዙኅ ይትሐሠይ በአድኅኖትከ፤ ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ፤ ወስእለተ ከናፍሪሁ ኢከላእካ፤ እስመ በጻሕካ በበረከት ሠናይ፤ ወአነበርከ አክሊለ ዲበ ርእሱ ዘእምዕንቍ ክቡር፤ ሐይወ ሰአለከ ወሀብኮ፤ ለነዋኅ መዋዕል ለዓለመ ዓለም እያሉ ምስጋና እየጨመሩ በየመሥመሩ ሁሉ ንሴብሕ ወንዜምር ለፅንዕከ ብለው ይህንን መዝሙር እያደረሱ የወርቅ ሰይፍ አስታጠቋቸው፡፡ ቅንት ሰይፈከ ኃያል ውስተ ሐቌከ በሥንከ ወበላሕይከ አርትዕ ተሠራሕ ወንገሥ እያሉ ይህንን መዝሙር በእንተዝ ይገንዩ ለከ አሕዛብ እግዚኦ ለዓለም ወለዓለመ ዓለም እስከሚለው ድረስ ሲጨርሱ ካህናቱም ከቅድስት ቁመው በአንድ ቃል ተቀጸል ጽጌ ምኒልክ ሐፄጌ ተቀጸል ጽጌ አሉ፡፡ ሊቀ መኳስ አጥናፍ ሰገድ ካባ ላንቃ ለብሶ፡፡ ራስ ዳርጌ ራስ በና ራስ ወርቅ አሥረው ወጡ፡፡ ባለወርቅ መጣምር በቅሎዎቻቸው ቀረቡ፡፡ ንጉሡ ከበቅሎ ሲሆኑ ግራ ቀኝ ሰይፍ ተመዞ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለጊዜው ተሸልመው የነበሩ ቁጥር የሌላቸው ሊቃውንት ከቤተ ክርስቲያን በወጡ ጊዜ ዑደት ሲሆን እንደ ፊተኛው ተቀጸል ጽጌ ምኒልክ ሐፄጌ ተቀጸል ጽጌ እያሉ ዞሩ ስፍራው ጠቦ በሩቅ ካህናት ንሴብሖ ይሉ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ጕዞ ተጀመረ፡፡ ሲጓዝም መኳንንቱም በየማዕርጋቸው ሠራዊቱም አጊጦ ጭፍራውም በየአለቀው አምሮ ተሰልፎ ይሄድ ነበር፡፡ እንዲህም ባማረ ጕዞ ተጕዘው ልቼ ከተማቸው ገቡ፡፡ ካዳራሽ ገብተው ከዙፋን ሲቀመጡ ከአደባባዩ የነበሩ መድፎች ፳፪ ጊዜ ተተኰሱ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ከቡሎ ወርቄ ጀምሮ እስከ ሣሪያ ተሰልፎ የነበረው ከቅጥሩም ውስጥ የተሰለፈው ነፍጥ በተተኰሰ ጊዜ ከብዛቱ የተነሣ የክረምት ነጐድጓድ መሰለ፡፡ በንጉሡም ዙፋን አጠገብ በተዋረድ በልዩ ልዩ ዓይነት ሥጋጃው ወላንሣው እየተነጠፈ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

ራሶችም መኳንንቱም በየማዕርጋቸው ተቀምጠው ግርማ መንግሥት ሆኖ አዳራሽ ተገኝተው ዋሉ፡፡ …. ይህም ነገር በተደረገ ጊዜ ያየውም የሰማውም እጅግ አደነቀ፡፡ ይህም የሆነ  ፲፰፻፸፩ ዓመተ ምሕረት በዘመነ ሉቃስ በጥቅምት በአራት ቀን ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ዘውዳቸውን በደስታ በፍቅር ለእግዚአብሔርም ለሰውም አስመርቀው ለሠራዊትዎ ብዙ ቀን አዳራሽ (ልቼ) ተገኙ፡፡” ሲል፦ አክታ ኢትዮጲካ የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው ደግሞ ፲፰፻፸፪ ዓ.ም ፋዘር ማሲያ የተባለው ጣልያናዊ በዐፄ ሚኒልክ ልቼ ተጠርቶ ነበር፡፡ ይህም የሆነው የጣሊያን ጆኦግራፊ ማኅበር ወደኢትዮጵያ መግባት ስለፈለገ ፋዘር ማሲያ ማብራሪያ እንዲሰጥ ታስቦ ነው፡፡ ካርዲናል ማሲና እንደዘገበውም ፲፰፻፸፪ዓ.ም ልቼ በተደረገው የሶስት ቀን ድግስ ንጉሥ ምኒልክ ተገኝተው ነበር፡፡ ለዚህም ድግስ አዲስ የመመገቢያ አዳራሽ ተሰርቶ ነበር፡፡

በ፲፰፻፸፮ ዓ.ም የ፷፭ ዓመት አዛውንቱ ማርኬዝ ኦራሊዬ አንቲኖሪ ከጂዮቫኒ፤ ቻሪኒና ሎሬንዝ ላንዳኒ እንዲሁም ከጣሊያን ወታደሮቻቸው ጋር በመሆን በአንኮበር በኩል በጥቅምት ፯ ቀን ልቼ ደርሰው ነበር፡፡ በዚያም ከዐፄ ሚኒልክ ጋር ተገናኝተው ወደ አዳራሽ አስገቧቸው ግብዣም ተደረገላቸው ፡፡ በ፲፰፻፸፯ ዐፄ ሚኒልክ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በአውሮፓውያን ወታደራዊ ዘዴ እንዲሰለጥኑ በማሰብ አልጀሪያ የነበረ የፈረንሳይ ጦር አባል ሎያዥ ፓይተር የተባለን ሰው ልቼ መጥቶ እንዲያሰለጥን አድርገዋል፡፡ በ፲፰፻፸፯ መጨረሻ አንቲኖሪና ቻሪኒ በሴባስቲያኖ ማርቲና አንቶኒዬ ቺቺ አማካኝነት ቺሪና ቺቺ ኢትዮጵያን ለማሰሰ መጥተው ግንቦት ፲፬ ቀን ፲፰፻፸፯ ከልቼ ተነሡ ፡፡

 

የልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን

liche 3የልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የዐፄ ምኒልክ ልቼ ቤተ መንግሥት ይባል ነበር፡፡ በአሁኑ ዘመን ደግሞ የታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተበሎ ተሰይሞ በቤተ ክርስቲያን ስም ነው የሚታወቀው፡፡ ስያሜውን የሰጡት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ናቸው፡፡ ቀድሞ በደብረ ብርሃን ከተማ ዙሪያ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተመሠረቱ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ:: ኋላ በግራኝ አህመድ ከፈረሱት ከአብያተ ክርስቲያናት መካከል የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ይገኝ ነበር:: ይህንንም ስለሚያውቁ ይሆናል አቡነ ኤፍሬም በደብረ ብርሃን (ልቼ) ቤተ ክርስቲያኑ እንዲሠራ የመሠረት ድንጋይ ያኖሩት::

በድርሳነ ዑራኤል ዘሐምሌ ሁለተኛ ምእራፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው አሳብ እንዲህ ይላል “…ከዚህ በኋላ ሃይማኖቱ የቀና ዘርዐ ያዕቆብ ነገሠ እሱም መጀመሪያ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደብረ ብርሃን ላይ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሠራ ሁለተኛም ቅድስት በሆነች በእናቱ በድንግል ማርያም ስምሦስተኛም የመላእክት አለቃ በሆነ በቅዱስ ዑራኤል ስም …” በዚህ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ በአቅራቢያው ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ለቀብርም ሆነ፤ ለአገልግሎት ርቆ ለመሄድ ተገዶ ነበር:: በዚህም የተነሣ ይህ ቤተ ክርስቲያን እንዲተከል ግድ ስላስፈለገ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም መጥተው፤ ቦታውን ባርከው፣ ስሙንም የታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ብለው መሰየማቸውን መሪጌታ ክፍለ ክርስቶስ ያስረዳሉ::

እዚህ ቦታ ላይ ዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸው እንደነበረ ከመጻሕፍትና ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም መጽሐፍ በመመልከት ነው ታሪኩንliche 4 ያገኘነው:: እዚህ ቦታ ላይ የምናያቸው ተጨባጭ ነገሮች  በወቅቱ ዐፄ ምኒልክ ለችሎት በሚያስቀርቡ ጊዜ ሕዝቡ ለፍርድ ሲመጣ ድንጋዮችን ይዞ በመምጣት በመከማቸታቸው ኋላም ለአጥር አገልግሎት ውሏል፡፡ ይህም ዙሪያውን በሦስት ረድፍ የድንጋይ ካብ (እንደ አጥር ሆኖ ስፋቱ ሁለት ሜትር ቁመቱ ሶስት ሜትር) የተከበበ ነው:: ይህ የካብ ድንጋይ አረጀ እንጂ ድሮ እንደተሠራ ነው:: ቢፈርስም እንኳን ታሪኩ እንዳይጠፋ እንደዚሁ ነው የተካበው::

 

ዐፄ ምኒልክ እዚህ ቦታ ላይ በንግሥናቸውና ለኢትዮጵያ ቅን ተጠሪ ሆነው በነበሩበት ሰዓት የማይጠፋ አትክልት፣ የማይጠፋ ሀብት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስቀምጠውለት ከሄዱት አንዱ  ባሕር ዛፍ ነው:: ቦታው ረግረጋማ ስለነበር ከአውስትራሊያ የባሕር ዛፍ አምጥተው ስለነበር ዛሬ ብዙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው::

 

ልጆች በነበርንበት ሰዓት ት/ቤት ስንሄድ ቦታውን እንዲሁ እናየዋለን እንጂ ገባ ብለን በአካባቢው መጥተን የምናየው ነገር አልነበረም:: እግዚአብሔር ፈቃዱ ሲሆን ግን ተሰብስበን ይህንን ለመሥራት ወይም ደግሞ የሚሠሩትን አካል እንደ እናንተ ያሉትን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የሆኑትን ለመጥራት ተነሣሥተናል:: በወቅቱ ግን እሳቸው የሠሩትም ያደረጉትም በችሎት የተቀመጡበትም እኛን ሊያነሳሳ እና የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ እንዲፈተትበት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲውል እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፡፡ ይህን ያስቻለው የንጉሡ ቅንነት ነው ብዬ ነው እኔ  የማስበው:: ይህ ታሪክ ደግሞ የዚህ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡

licheክምር ድንጋይ የሚመስለው በሙሉ ቤት ነው ፡፡ ሁሉም የድንጋይ ቤት ነው:: ቤተ መንግሥት ሰለሆነ በብዙ ዓይነት ነው ቤቱ፡፡  ቤቶቹ ባሉበት ፈርሰው ክምር ድንጋይ ቢሆኑም አጥሩ እንደ ኢያሪኮ ግንብ ሶስት ዙር ባለበት ቢገኝም ድንጋዩም ሆነ መሬቱ የሀገር ሀብትና ንብረት ስለሆነ ማንም ግለሰብ መውሰድና ማጥፋት ሳይችል ታሪኩ እንዳይረሳ እግዚአብሔር እስከፈቀደ ድረስ መቀመጥ አለበት::

ቤተመንግሥት ሰለሆነ ብዙ ዓይነት ነው፡፡ ዋናው ቤተ መንግሥታቸውና የችሎት አዳራሽ አለ፡፡ የንጉሣዊያን ቤተሰብ  መኖሪያ ነው ተብሎ የሚገመት አለ፡፡  የግብር አዳራሽ አለ፡፡ የወታደር ሰፈር አለ፡፡ የግብር ቤት አለ፡፡ ሠራተኞች ሰፈር አለ፡፡ የእንግዶች ማረፊያ አለ፡፡liche2 የመኳንንቱ ቤት ወዘተ. ፍራሹና ግንቡ ይታያል፡፡  የችሎት ቦታቸው የነበረው ቦታ ለቤተ ክርስቲያኑ እንደ መቃኞ እያገለገለ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ፈረስ መፈተኛቸው የነበረው ሜዳ አሁንም ማንም ሳያርሰው ይገኛል፡፡ የውኃ ምንጫቸው ክረምት ከበጋ አትደርቅም አለች፡፡ የገበያ ቦታቸው የተንጣለለው ሜዳ አሁንም አለ፡፡ በማለት መሪጌታ ገልጸውልን፤ ማሳሰቢያቸውን እንዲህ በማለት አስከተሉ “ታሪኩ እንዳይረሳ እግዚአብሔር ፋቃዱ ሆኗል፡፡ ድንጋዩን ማንም ሳይጠብቀው አግኝተነዋል፡፡ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እየተሠራ ነው፡፡ እንግዲህ ተባብረን ታሪኩን እንጠብቅ ቤተ ክርሰቲያኑን እንሥራ፡፡”

liche 6ቀድሞ የንጉሥ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት የነበረው ቦታ ዛሬ የንጉሥ ክርስቶስ መመስገኛ ሥፍራ ሆኗል፡፡ ታሪካዊነቱ እንዳለ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ ወደፊት ተመራማሪዎች፣ ጎብኚዎች፣ የሃይማኖቱ ተከተዮች ልቼ ታዕካ ነገሥት ኢየሱስ ይመጣሉ፡፡ ሁሉንም እንደፍላጎቱ ማስተናገድ እንዲቻል፡፡ የሁላችንም ትኩረት ተሰጥቶት ቦታውን ማቃናት፣መጠበቅ፣ መገንባት ወዘተ. ይኖርብናል፡፡ ለዚህም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን፡፡

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት ክፍል
 
ክርስቶስ በደሙ የመሰረታት ቤተ ክርስቲያን ምንም ፈተና ቢጸናባትም በእግዚአብሔር ኃይል ጠላቶቿን ድል እየነሳች በሐዋርያት ትምህርት ጸንታ ‹‹አሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን›› በመባል አንድነቷን አጽንታ ቆይታለች፡፡