የኅዳር ጽዮን በዓል አከባበር ዛሬም ቀጥሎ በድምቀት ተከብሯል።

ዲ/ን አሉላ መብራቱና በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

ኅዳር 20 ቀን ከዋዜማው ጀምሮ መከበር የጀመረው የኅዳር ጽዮን በዓል ዛሬም ቀጥሎ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

ከትናንትና ማታ 2፡00 ደወል ከተደወለበት ጀምሮ፥ ሊቃውንት ካህናትና ዲያቆናት  ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በስብሐተ ማኅሌት በማድረስ ሌሊቱን አሳልፈዋል።

ሥርዓተ ማኅሌት እንዳለቀ ዛሬ ጠዋት 1፡00 ዑደተ ታቦት ተጀምሯል። ሁለት ዓይነት ዑደት የተካሄደ ሲሆን የመጀመሪያው ዑደት በሐውልት አደባባይ ተደርጓል። በዚያም የአክሱም ሊቃውንትና የሰ/ት/ቤት መዘምራን የክብረ በዓሉን ዝማሬ አቅርበዋል። በቦታው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፥ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል።

ሁለተኛው ዑደት ቅዱስ ያሬድ የአርያም ዜማውን ባሰማበት በሙራደ ቃል ተከናውኗል። በዚህኛው ዑደት፥ ቅዱስነታቸው አቡነ ጳውሎስ ሠፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል በሁለት ቋንቋ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ሰጥተዋል። የማዕከላዊ ትግራይ አክሱም ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሰላማ በዓሉን በተመለከተ አጠር ያለ መግለጫ ሠጥተዋል። በቅዱስነታቸው ጋባዥነት ብፁዕ አቡነ ኤልሣዕ ተጨማሪ ትምህርት ያስተማሩ ሲሆን የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው እለቱን አስመልክተው በንባብ ንግግር አሰምተዋል።

ሥርዓተ ቅዳሴ የተጀመረው ከቀኑ 6፡20 ነበር። በእለቱ ሠራየ ዲያቆን ሆኖ የቀደሱትና ከማኅበረ ቅዱሳን የአማርኛ መካነ ድር ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት መ/ር ፍስሐ ጽዮን ደሞዝ እንደገለጹልን፥ በብፁዕ አቡነ ገሪማ፥ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስና በብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ የተመራው የቅዳሴ ሥርዓት በ3 መንበር የተከናወነ ሲሆን፥ ሥርዓተ ቁርባኑ በእያንዳንዳቸው በ3 አቅጣጫ በአጠቃላይ በ9 ሙሉ ቀዳሽ ተከናውኗል። የቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የጠጠር መጣያ ቦታ እስከሚታጣ ሙሉ ነበር።
እንደ መ/ር ፍስሐ ጽዮን ገለጻ፥ እርሳቸው በቀደሱበት በዋናው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩት መላው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ተሳታፊ መሆናቸው ልዩ ድባብ ፈጥሯል። በአጠቃላይ ለምእመናን ቅዱስ ቁርባን ለማቀበል ብቻ ወደ አንድ ሰአት የሚጠጋ ክፍለ ጊዜ እንደወሰደ አያይዘው ገልጸውልናል።
ከዋዜማው ጀምሮ በ100,000ዎች ለሚገመቱ ምእመናን በአራቱም አቅጣጫ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲስጥ ውሏል።  

/ከትናንት ጀምሮ መረጃዎችን ሲያደርሱን ለነበሩና ለተባበሩን ለንቡረ እድ በላይ መረሳ፣ ለመ/ር ፍስሐ ጽዮን ደሞዝና ለመ/ር ዲበኩሉ ልሳነ ወርቅ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናችንን እያቀረብን ጥንቅራችን በዚህ እንቋጫለን/

        
metshafe_bilhat.jpg

የአዳዲስ ፈጠራ ግኝቶች ማበረታቻ የሽልማት ፕሮጀክት ትግበራ ተጀመረ።

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
 
metshafe_bilhat.jpgየሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል የአዳዲስ ፈጠራ ግኝቶች ማበረታቻ የሽልማት ፕሮጀክት ትግበራ ጀመረ። በፕሮጀክቱ ትውውቅ መርሐ ግብር ላይ ለትግበራ መነሻ ይሆናል የተባለው «መጽሐፈ ብልሃትም» ተገምግሟል።
 
ፕሮጀክቱ ማኅበረ ቅዱሳንና ኢንጅነር ሙሉጌታ ዘርፉ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሠነድ መሠረት ፈጠራንና መልካም የሆነውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ማበረታት፥ ቤተ ክርስቲያንን፣ ትውልድን ፣ ሀገርን የሚጠቅም አቅም ለማሳደግ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሆነ በመርሐ ግብሩ ትውውቅ ወቅት የተበተነው ወረቀት ያስረዳል፡፡
መርሐ ግብሩን ያዘጋጀው የማኅበረ ቅዱሳን የሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል ሲሆን በፕሮጀክት ትውውቅ መርሃ ግብር ላይ የክፍሉ ሓላፊ ዶ/ር ሣሙኤል ኃ/ማርያም እንደተናገሩት ከሆነ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በየደረጃቸው መስራትና የፈጠራ ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ ማሳየት ነው፡፡ በግኝቱ ውስጥ ለሚያሸንፋ ግለሰቦች ሽልማቶችን በመስጠት ፈጠራን ያበረታታል በተጨማሪም ያለብንን የተለያዩ ችግሮች በሙያ በማገልገል በተሰጠን መክሊት አትርፈንባቸው ገብርሄር ተብለን ሰማያዊ ሽልማት እንድናገኝ ነው፡፡

በትውውቅ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙትም የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እንደገለጹት ማኅበሩ ይህንን ፕሮጀክት ለተጠቃሚ ለማድረስ ሲወስን ከዘርፉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤተ ክርስቲያንንና ሀገሩን በአካባቢያው ከሚያገኛቸው ቁሳቁሶች በማዘጋጀት እንዲጠቀም ነው፡፡ በዚህ በኩል ሁላችንም የድርሻችንን እና የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ለፕሮጀክቱ ትግበራ መነሻ ይሆናል የተባለውና በኢ/ር ሙሉጌታ ዘርፉ የተዘጋጀው መጽሐፈ ብልሃት አንደኛ መጽሐፍም ተገምግሟል፡፡ መጽሐፉ በ24 ክፍሎችና በ92 ገጾች በምርምርና ሥርዐት የተዋቀረ መሆኑን ዶ/ር ኢ/ር ብርሃኑ ይግዛው የግምገማ ግብረ መልስ /Feed back/ ሲያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

ገምጋሚው መጽሐፉ የተጻፈበትን ሥርዓትና ስልት ሲገልጹ፥ ሥልጣኔ የሚፈጥሩት እንጂ የሚቀበሉት ነገር ያለመሆኑን ያመሰጠረ መጽሐፍ ነው ብለው፥ በይዞታቸው ጥንታዊ ግኝቶች፣ በአቀራረብ ስልታቸው ግን አዲስ ሊባሉ የሚችሉ እሳቤዎችን፣ ምን አልባትም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ገና ያልተፈለሰፉ ግን ሊተገበሩ የሚችሉ ድንቅ ሀሳቦችንም እያዋዛ የሚያቀርብ መጽሐፍ ነው ብለዋል፡፡   

ስለ መጽሐፉ ጠቀሜታ በዘረዘሩበት የግምገማቸው አካል ምርምርና ሥርፀት ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያስረዳና፥ እያንዳንዱ ሰው የፈጠራ ችሎታን በተመለከተ እንዲማር የሚያደርግ ነው፡፡ እኒህም የመጠቁ ቤተ ሙከራዎችን በማይጠይቅ ሁኔታ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ኢ/ር ብርሃኑ በማጠቃለያ ሀሳባቸው መጽሐፉ ጥቂት ሊያካትታቸው ስለሚገቡ ነገሮች ጠቅሰው፥ ይህ በጎ ጀማሮ በየት/ቤቱ፣ በቤተሙከራዎች እንዲሁም በፋብሪካዎች ተሠራጭቶ በዚህ ረገድ ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ይሄው በጎ የቴክኖሎጂ መሠረታዊ ሀሳብ የሚስፋፋበትን መንገድ በመቀየስ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የማ/ቅዱሳን ሙያ አገልግሎትና አቅም ማጐልበቻ ዋና ክፍል ማኅበሩ ከተነሣለት ቤ/ክንን በሙያ በእውቀትና በገንዘብና በጉልበት ለማገልገል ካለው ዓላማ አንፃር የቤ/ክንን ልጆች በሙያ አገልግሎት ለማሣተፍ የተቋቋመ ክፍል ነው፡፡
     
   

Zimare_Mewasit.JPG

የዝማሬ መዋሥዕት አድራሾች ተመረቁ

በደረጀ ትዕዛዙ
 
Zimare_Mewasit.JPG
 
በዙር አባ አቡነ አረጋዊ ገዳም የዝማሬ መዋሥዕት ትምህርታቸውን ተከታትለው ተመረቁት ደቀ መዛሙርት ከአቡነ እንድርያስ ጋር

በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በላይ ጋይንት ወረዳ ሳሊ በተባለው ቀበሌ የሚገኘው የጽርሐ አርያም ዙር አባ አቡነ አረጋዊ ገዳም ዝማሬ መዋሥዕት ትምህርት ቤት ዐሥራ ሰባት የዝማሬ መዋሥዕት አድራሾችን አስመረቀ፡፡

የአብነት ትምህርት ቤቱ ጥር 30 ቀን 2002 ዓ.ም አድራሾችን ባስመረቀበት ወቅት ብፁዕ አቡነ እንድ ርያስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት፤ «በብዙ ጥረት እና ድካም፤ በረጅም ጊዜ ያካበታችሁትን ዕውቀት በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድታውሉት አደራ እላለሁ» ብለዋል፡፡

ምሩቃኑ ተግተው ቤተክርስቲያንን በማገልገል ሌሎችንም ተተኪ ደቀመዛሙርት ማፍራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው፤ ሀገረ ስብከታቸው ለዚህ ቅዱስ ተግባር ስኬታማነት የበኩሉን የሓላፊነት ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ ካህናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ ዝማሬ፣ ቅኔ መወድስ የአማርኛ እና የግእዝ ቅኔ ግጥሞች በተመራቂዎች መቅረቡን ከደብረ ታቦር ማእከል የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ «አድራሽ» ማለት በቤተ ክርስቲያን የአብነት ት/ቤቶች ለመምህርነት የሚያበቃቸውን ሙያ ተምረው ያጠናቀቁ ደቀመዛሙርት ማለት ነው፡፡

Semera_Kidus_Yohanes_Church.jpg

በአፋር ሰመራ ከተማ የመጥምቁ ዮሐንስ ገዳም ቅዳሴ ቤት ተከበረ

ሎጊያ ወረዳ ማዕከል
    Semera_Kidus_Yohanes_Church.jpg
 
 
 
 
 
 
 
በሰመራ ከተማ የተሰራዉ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን

በአፋር ሀገረ ስብከት ሰመራ ከተማ በሀገረ ስብከቱና በአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጥረት የተሠራው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ገዳም መቃኞ ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ግንባታው የተጀመረው ይኸው መቃኞ ቤተ ክርስቲያን፤ ቤተልሔም፣ የግብር ቤት፣ የዕቃ ቤት እና የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ እንዲሁም የካህናት ማረፊያ ቤቶችም ጭምር እንደተሠሩለት ታውቋል፡፡

ጥር 30 ቀን 2002 ዓ.ም በርካታ የአካባቢው ምእመናን፤ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች፣ ካህናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ከቀረበው መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው፤ 2001 ዓ.ም በሰመራ ከተማ የተቋቋመው ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሲቀበል የክርስቲያኖች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ይሁንና በከተማው በወቅቱ ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ማስቀደስ፣ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶችን ማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡

በዕለቱ ቡራኬ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮናስ እንደገለጹት፤ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የአምልኮ ቦታ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በአፋር ክልላዊ መንግሥት መልካም ፈቃድ 29 ሺሕ 830 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቦታው የመንበረ ጵጵስና፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያን ያካተተ ማስተር ፕላን /የይዞታ ማረጋገጫ/ የተሠራለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

«ይህ ቦታ በረሃማ ስለሆነ፤ በበረሃ የገደመው ዘ ንብረቱ ገዳም በተባለለት በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ስም፤ ቅሩበ ሳሌም ዮሐንስ መጥምቅ ገዳም ተብሎ እንዲጠራ ይሁን» ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ቅሩበ ሳሌም የሚለው ሥያሜ ዮሐንስ መጥምቅ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅበት የነበረው አካባቢ እንዲታወስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የገዳሙ ሕንፃ ቤተክርስቲያን /መቃኞ/ መሠራት እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ለሥራው የተባበሩትን ሁሉ በማመስገን ምእመናኑን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

ከሁለት ዓመት  በኋላ  ዋናውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ዕቅድ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

በሰመራ ከተማ ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የእምነት ሥርዓታቸውን ማከናወን ይቸገሩ እንደ ነበር የጠቀሰው የግቢ ጉባኤው ሰብሳቢ ዲ/ን ደጀን፤ ያም ሆኖ ተማሪው ከዩኒቨርስቲው መደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን መንፈሳዊ ትምህርት የመቀበል ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለነበረ ግቢ ጉባኤ ተቋቁሞ ትምህርቱ ይሰጥ እንደነበር አስረድቷል፡፡

«ቦታው ምድረ በዳ ከመሆኑ አንፃር በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው እጅ ተሠራ ለማለት አያስደፍርም» ያለው ሥራውን በሓላፊነት ሲከታተል የነበረው ዲ/ን ናሁሠናይ ደስታ በበኩሉ፤ «የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ከጀምሩ አንሥቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ ያደረጉ የሰመራ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሠራተኞች፣ የዱብቲ ውኃ ሥራዎች ድርጅት ሠራተኞች፣ የእመቤታችን ጽዋ ማኅበር፣ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና የአካባቢው ምእመናን ምስጋና ይገባቸዋል» ብሏል፡፡

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮናስ ከተለያዩ ምእመናን ያገኙዋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ለቤተ ክርስቲያኑ መገልገያ ማስረከባቸውንም ከማኅበረ ቅዱሳን የሎግያ ወረዳ ማእከል የተላከልን ዘገባ ያስረዳል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ የልምድ ልውውጥ አደረጉ

በይብረሁ ይጥና

ከሲዳማ ሀገረ ስብከት ሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ የስድስት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች በአዲስ አበባ የአምስት ሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ አደረጉ፡፡

ሃያ ዘጠኝ አባላትን ያቀፈው የልኡካን ቡድን፤ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መዋቅር አደረጃጀትና አሠራር፣ መዝሙራት፣ የአባላት ክትትልና አያያዝ፣ ሥነ ምግባርና የልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግም የጋራ ግንዛቤ አግኝቷል፡፡

የልኡካን ቡድኑ አስተባባሪና የሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ወጣት ብስራት ጌታቸው ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እንዳስታወቀው፤ «ከየካቲት 19 እስከ 21 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ ከመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት፣ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል፣ ጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን እና ከልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሳዊሮስ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥና ውይይት በማድረግ ሰፊ ትምህርት ቀስመናል፡፡» ብሏል፡፡ እንዲሁም፤ «በተለይ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ለማስጠበቅና የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ሰንበት ትምህርት ቤቶች በኅብረት ሆነው መሥራት ጠቃሚ መሆኑን ተረድተናል» በማለት አመልክቷል፡፡

ከአባላቱ መካከል የሀዋሳ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ዋና ጸሐፊ ወጣት ሥላስ አዲስ በሰጠችው አስተያየት፤ «ለሦስት ቀናት ባደረግነው ውይይት ጠቃሚና መሠረታዊ የሆነ ነገር አግኝተናል፡፡ ካገኘነውም ተሞክሮ ከተኛንበት እንድንነቃና ሥራዎቻችንን እንደገና እንድንፈትሽ አድርጎናል» ስትል ተናግራለች፡፡

ሌላው በሀዋሳ ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ይድነቃቸው ጥላሁንም፤ «በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ የአሠራር ልዩነትና ክፍተቶች መኖራቸውን ተረድቻለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ብዙ መሥራት እንዳለብን ተገንዝቤያለሁ፡፡ በይበልጥ መዝሙራትን በሚመለከት ችግሮች ስላሉ ከጉብኝታትን ባገኘነው ትምህርት ካለፈው በተሻለ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን እንድንሠራ ያደርገናል፡፡ በጠቅላይ ቤተክህነትም አንድ ወጥ በሆነ አሠራር አፈጻጸሙን ለመከታተል ጥረት ቢደረግ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለመቆጣጠር ይመቻል፡፡» ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ የመንበረ መንግሥት ግቢ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ደነቀ ማሞ በበኩሉ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፤ «ከሀዋሳ ከመጡ ስድስት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥ መደረጉ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መካከል የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ያስችላል፡፡ ስለሆነም ሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ይህን አርአያ ቢከተሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው» ሲል ተናግሯል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድነት ሆነው መወያየታቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት ለመጠበቅ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል፡፡

የሐይቅ ቅዱስ ዮሐንስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ እንዲጠናቀቅ የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

በደረጀ ትዕዛዙ

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሐይቅ ከተማ የሚገኘው የደብረ ናግራን ቅዱስ ዮሐንስ ፍቅረ እግዚእ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታን ለማስፈጸም የምእመናን ድጋፍ ተጠየቀ፡፡

በ1879 ዓ.ም እንደተሠራ የሚነገርለት ይኸው ቤተ ክርስቲያን ለበርካታ ዘመናት እድሳት ባለማግኘቱ አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ፈቃድ ከሰባት ዓመት በፊት ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ኮሚቴው ምእመናንን በማስተባበር፣ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመጠቀምና ጉባኤያትን በማዘጋጀት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በማሠራት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ወልደ ትንሣኤ አሳምነው ተናግረዋል፡፡

የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ገንዘብ ያዥ አቶ ካሳሁን መብራቱ በበኩላቸው፤ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ ምእመናን ያደረጉት ትብብር የሚያበረታታ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የግንባታ ዕቃ መወደድ የተነሣ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡

ስለዚህ የቆርቆሮ፣ የበርና የመስኮት የመሳሰሉት ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ቤተ ክርስቲያኑ  ለምእመናን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ድጋፍ መጠየቅ አስፈልጓል ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ለዚህም ምእመናን የተቻላቸው ትብብር እንዲያደርጉ ተማጽነዋል፡፡

Aba Entones Gedam.JPG

በዓለማችን የመጀመሪያ የሆነው የአባ እንጦንስ ገዳም በዐሥራ አራት ሚሊዮን ዶላር እድሳት ተደረገለት

ገዳሙ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታትን አስቆጥሯል

በሻምበል ጥላሁን

በዓለም የመጀመሪያው የምንኩስናና የገዳማውያን ኑሮ መሥራች የሆነው የአባ እንጦንስ ገዳም በግብፅ መንግሥት በዐሥራ አራት ሚሊዮን ዶላር ወጪ እድሳት ተደርጎለት ለአገልግሎት መዘጋጀቱን ቢቢሲ የካቲት 4 ቀን 2002 ዓ.ም ዘገበ፡፡ በግብፅ የሚገኘው የቅዱስ እንጦንስ ገዳም ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡

Aba Entones Gedam.JPG 

በግብፅ የሚገኘው የአባ እንጦንስ ገዳም 

ገዳሙ ከዕድሜ ብዛት በእርጅና ከደረሰበት ጉዳት ተጠግኖ ለቱሪስት ኢንዱስትሪው ተጨማሪ አቅም እንዲፈጥር የግብፅ መንግሥት ከዐሥራ አራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዳደረገ ዘገባው ጠቁሞ፤ ገዳሙ መንፈሳዊ እሴቱና ታሪካዊ ዳራው እንዳይጠፋ ለማደስ ከስምንት ዓመት በላይ እንደፈጀም የዜና ምንጩ አስታውቋል፡፡

የቢቢሲ ዘገባ እንዳመለከተው፤ የገዳሙ መታደስ የሀገሪቱን የቱሪስት ኢንዱስትሪ ከማስፋፋቱም በላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባትም እንደሚያስችል አመልክቷል፡፡

በግብፅ ስዊዝ ከተማ የሚገኘው የአባ እንጦንስ ገዳም መታደስ፣ አገልግሎት ላይ መዋልና ለቱሪስት መስህብነት ክፍት መሆኑ፤ ሀገሪቱ የቀድሞ ታሪኳንና ቅርሷን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያሳይ ዛሒ ሐዋስ የተባሉት የግብፅ ዋና የቅሪተ አካል ተመራማሪ መናገራቸውንም የዜና ምንጩ አስታውቋል፡፡

ገዳሙ ቅዱስ እንጦንስ በሦስተኛው መቶ ከፍለ ዘመን በቀይ ባሕር አካባቢ በሚገኘው ተራራማና በረሐማ አካባቢ ለጸሎት የመነኑበት ቦታ ነው፡፡

በመልሶ ግንባታው ወቅት በገዳሙ የሚኙት ሁለት አብያተ ክርስቲያናትና ሁለት ማማዎች በጥንቃቄ መንፈሳዊና ታሪካዊ ይዘታቸው ሳይቀየር መሠራታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የቅዱስ እንጦንስ ገዳም በግብፅ ኦርቶዶክሶችም ሆነ በአምስቱ ኦሪየንታል አኀት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ታዋቂ ነው፡፡

በገና እንደርድር

 በመ/ር መንግስተአብ አበጋዝ
ለግማሽ ምእተ ዓመት ያህል በገና ለደረደሩት መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ እሑድ የካቲት 14 ቀን 2002 ዓ.ም ልዩ ነበር፡፡ ስለዚህ በገናቸውን አንሥተው መጋቤ ስብሐት «ማን ይመራመር ማን ይመራመር ያንተን ሥራ ያንተን ግብር ማን ይመራመር …» እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለስድስት ወር ያሠለጠናቸው አርባ ስድስት የበገና ደርዳሪዎችን በሩሲያ ባሕል ማእከል የፑሽኪን አዳራሽ ተመልክተዋልና፡፡

«ለረዥም ዘመን ብቸኝነት ይሰማኝ  ነበር» ያሉት መጋቤ ስብሐት ዓለሙ፡፡ «አሁን በዝተናል» በማለት የበገና ማሠልጠኛዎችም ሆኑ ተማሪዎቹ እየጨመሩ መምጣታቸው ሀገራዊ እሴቱንም ሆነ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ለማየቆት ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመው የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት በአብነት ትምህርትና በዜማ መሣሪያዎች እያሠለጠነ ማስመረቅ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እንደ ት/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ ተፈራ ገለጻ የዛሬውን ጨምሮ አሥራ አራት ዙር አሠልጥኖ አስመርቋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ የአብነት ትምህርትና የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና እሴቶቹን ከመጠበቅ ባሻገር የሚያስገኙትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች ሲዘረዝሩ «ለምስጋና፣ ለተመስጦ፣ ጭንቀትንና ርኩስ መንፈስን ለማራቅ፣ ለትምህርት፣ እንዲሁም የሀገርን ቅርስ ከነሙሉ ታሪኩና ጥቅሙ ለማስተዋወቅ፣ ትውፊትን ለትውልድ ለማውረስና በገና ከነበረው ጥቅም አንጻር ቀጣይ አገልግሎት እንዲኖረው ማድረግ ይቆይ የማይባል አገልግሎት ነው፡፡» ይላሉ፡፡

ወጣት ሚልካ ሐጎስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአምስት ኪሎ ኢንጂነሪንግ የ4ኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ከትምህርቷ በተጓዳኝ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያን የምትከታተል የግቢ ጉባኤ ተማሪ ናት፡፡ በዚህ ሁሉ የጊዜ ጥበት ግን በአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤት የሚሰጠውን የዜማ መሣሪያ ሥልጠና ወስዳ በበገና መደርደር ተመርቃለች፡፡ ሚልካ ጊዜዋን አጣጥማ በሳምንት ሁለት ቀን ለሁለት ሰዓት ተከታትላ በስድስት ወር ያጠናቀቀችውን ሥልጠና እንዴት ትገልጠዋለች)

«ጊዜአችንን በአግባቡ የምንጠቀም ከሆነ ሕልምን እውን ማድረግ እንችላለን፡፡ ጊዜዬን ተጠቅሜ በገና ተምሬአለው፡፡ ይህ ለእኔ መንፈሳዊ ሕይወት እጅግ አጋዤ ነው፡፡ ጊዜ መድቤ ደግሞ የአብነት ትምህርቱንና ተጨማሪ የዜማ መሣሪያዎችን ለመማር አስባለሁ፡፡ እድሜዬን ሁሉ አገልጋይ ሆንኩ ማለት አይደል፡፡ በእውነት በገና መደርደር መታደል ነው፡፡» ብላለች፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ትምህርት ቤቱን ከፍቶ ኑና በገና እንደርድር ይላል፡፡

ከጋምቤላ ክልል የመጡ ሠልጣኞች ተመረቁ

በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪነት ከጋምቤላ ክልል የአኝዋክና የኑዌር ብሔረሰብ ተወላጅ ሠልጣኞች ተመረቁ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል እንደተናገሩት በክልሉ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ሠልጣኞች መጥተው ሲሠለጥኑ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ሓላፊው የሥልጠናውን ዓላማ ሲያስረዱ በአብዛኛው የጠረፋማ ቦታዎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው የሚያስተምራቸው ባለማግኘታቸው ተቸግረው ቆይተዋል፡፡ ይህንን ለማቃለል ከማኅበረሰቡ የተገኙ ወጣቶችን በማስተማር ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ተመልሰው ሕዝቡን እንዲያስተምሩና እንዲያስጠምቁ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ላሬ፣ ኝንኛንግ፣ ፒኝዶ፣ አበቦ፣ ጆር፣ ኢታንግ እና ጋምቤላ ዙሪያ ከሚባሉ ሰባት ወረዳዎች የመጡት ሠልጣኞች በቁጥር ዐሥራ ስድስት ሲሆኑ ሥልጠናው ዐሥራ አምስት ቀን እንደወሰደ ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናውን ለመሥጠት ከሰላሳ አምስት ሺሕ ብር በላይ ወጪ እንዳስፈለገ የጠቀሱት ሓላፊው ወደፊትም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ በጎ አድራጊዎች ይህንን መሰል መንፈሳዊ አገልግሎት ለማከናወን የእርዳታ እጃቸውን ከዘረጉ በርካታ የጠረፋማ አካባቢ ወገኖችን ለማስተማር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በአፍ መፍቻ ቋንቋ ተምሮ ማስተማር ውጤቱ ከፍተኛ በመሆኑም የክርስትናው እምነት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች በቋንቋቸው በማስተማር ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ሠልጣኞቹ ሥነፍጥረት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ነገረ ቅዱሳን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንና የስብከት ዘዴ በሚሉ ርእሶች ትምህርት እንደተሰጣቸው እና ወደ ክልላቸው ሔደው ምን መሥራት እንደሚገባቸው ምክክር እንደተደረገም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለገዳሙ ካህናትና ዲያቆናት መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም ሥልጠና ተሰጣቸው

በይበረሁ ይጥና
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ለስምንት ወራት በመሠረታዊ የኮምፒውተር ትምህርት ያሠለጠናቸውን አሥራ አምስት ካህናትና ዲያቆናት ጥር 30 ቀን 2002 ዓ. ም. አስመረቀ፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ ቆሞስ መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ  በምረቃው መርሐ ግብር እንደተናገሩት፤ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ማስተማር ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡ ትምህርቱን ያገኙት አባቶችም ሆኑ ዲያቆናት በኮምፒውተር ትምህርት መሠልጠናቸው የመረጃ ሥርዓትና ተዛማጅ ሥራዎች በዘመናዊ መልክ ለማከናወን እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሥልጠናውን አዘጋጅቶ አባቶች፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤቱ ወጣቶች በአንድነት እንዲሠለጥኑ ማድረጉ ቤተ ክርስቲያንን በልማት ለማሳደግ ያለውን ርእይ እንደሚያሳይ ጠቁመው፤ ወደፊትም ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን ብዙ እንደምትጠብቅ ተናግረዋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዲያቆን ደረጀ ነጋሽ በበኩሉ፤ የመጀመሪያውን ዙር መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠና ሠልጥነው ያጠናቀቁት፤ አንድ መነኩሴ፣ አሥራ ሦስት ዲያቆናትና አንዲት የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ወጣት እንደሆኑ አስረድቷል፡፡ በሥልጠናው ወቅት ያገኙትም የትምህርት ዓይነት ኤም ኤስ ዊንዶ፣ ወርድ፣ ኤክሴል፣ አክሰስና የኢንተርኔት አጠቃቀም የተመለከቱ መሆናቸውን ሰብሳቢው ጠቁሞ፣ ሥልጠናው አገልግሎታቸውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ አስታውቋል፡፡

ሥልጠናውን ለስምንት ወራት የሰጡት ቀደም ሲል በሰንበት ትምህርት ቤቱ ተኮትኩተው ያደጉ ወጣቶች ሲሆኑ፤ አሠልጣኞች በአሁኑ ጊዜ በኮምፒዩተር ሳይንስ ሙያ በተለያዩ ተቋማት የሚያስተምሩ አባላት እንደሆኑ ምክትል ሰብሳቢው አስረድቷል፡፡ ለወደፊትም ሥልጠናውን ከገዳሙም በተጨማሪ ወደ ሌሎችም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመሔድ ለአገልግሎትና ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ለመስጠት እቅድ መያዙን ተናግሯል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በተለይ ቀደም ብሎ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባል የነበሩ አባቶች በሰጡት አስተያየት አባትና ልጅ በአንድ ሆነው መማራቸው በሰንበት ትምህርት ቤቱና በገዳሙ አባቶች መካከል ያለውን ፍቅርና አንድነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ሥራውም ለሌሎች ሰንበት ት/ቤት አርአያ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ ሰንበት ት/ቤቱ ከ1950 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ 1993 ዓ. ም. ድረስ «ተምሮ ማስተማር ማኅበር» የሚል ስያሜን ይዞ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ ነበር፡፡ ከ1993 ዓ. ም. ወዲህ «የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት» በሚል ስያሜ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡