ክርስቶስን መስበክ እንዴት?

ሚያዚያ 25፣ 2003ዓ.ም

/ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ሚያዝያ 2003ዓ.ም/

ፕሮቴስታንቶችና ፕሮቴስታንታዊ መንገድ የሚከተሉ አንዳንዶች  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን አልሰበከችም የሚል ክርክር ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን ለመመለስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በምላሹ እንዲሳተፉበት ጋብዘናል፡፡ ለዚህ እትም የያዝነውን እነሆ!

ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ“ቤተክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ወንጌል ነው”

ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ ሁለት ሺሕ ዓመታት አልፏታል። ይህንንም ሊቃውንቱ ምእመናንም ያስረዱትና የተረዱት ነው። ወንጌል ካልተሰበከ ክርስቲያኖች እንዴት ለአሁን ዘመን ደረሱ? ወንጌል መሠረት፣ በጎ እርሾ ሳይሆነው፣ ወንጌል ብርታት ሳይሆነው ይህን ሁሉ ዘመናት አቆራርጦ፣ ድልድዩን አልፎ እንዴት እዚህ ደረሰ? ወንጌል ቤተ ክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ነው፡፡

 

በቤተክርስቲያን ሊቃውንቱ የሚያነቧቸው፣ የሚተረጉሟቸው፣ ምእምናን የሚሰሟቸው፣ የሚታነጹባቸው ድርሳናት፣ ተአምራት ወንጌል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት ወንጌልን የሚፈቱ፣ የሚተረጉሙ፣ የሚያመሰጥሩ ናቸው። ከዚህ ውጭ የሆኑ መጻሕፍት በቤተክርስቲያን አይነበብም፣ አይተረጎምም፣ አይሰማም። ቤተክርስቲያን ወንጌልን የምትሰብከው በቃል፣ በመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው። ጥምቀት ወንጌል ነው። ቤተክርስቲያንም ጥምቀት የዘወትር ሥራዋ ነው። ወንጌል ስለ ጥምቀት ነው የሚነግረን። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙም በየዕለቱ ይቀርባል፤ ይህ ወንጌል ነው። ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን የተቀደሰውን ጋብቻቸውን በተቀደሰው ቦታ፣ በተቀደሰው ጸሎት በምስጢረ ተክሊል ይፈጽማሉ። ይህም ወንጌል ነው። እናቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን ከዚህ ዓለም ሲሸኙ በሥርዐተ ፍትሐት፤ ብሉያትና ሐዲሳት እየተነበቡ፣ ያሬዳዊ ዜማ እየተዜመ ነው። ይህ ወንጌል ነው። አላዛርን ከመቃብር ተነሥ እንዳለው፤ የታሰረበትን ፍቱት እንደተባለ እንደተ ፈታ ሁሉ፤ ካህናትም ከኃጢአት እስራት እየፈቱ ሕዝባቸውን መሸኘት፤ “አቤቱ እግዚኦ ይቅር በለው ሲያውቅ፣ ሳያውቅ በሠራው ኃጢአት ይቅር በለው” እያሉ መሸኘት ወንጌል ነው።

ቤተክርስቲያን ራሷም፣ እግሯም፣ መሠረቷም፣ ጉልላቷም ወንጌል ነው። ይህን በቅንነት፣ በበጎ ነገር፣ በምስጢር፣ በትርጓሜ ለሚያዩት ነው። በጥላቻ ካዩት ነጩም ጥቁር ነው፤ ብርሃኑ ጨለማ ነው፤ በጥላቻ ማየትና በፍቅር ማየት፤ በሐሰት መናገርና በእውነት መናገር መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። የቤተክርስቲያን ጥንተ ጠላቶች ለቤተክርስቲያን በጎ ይመሰክራሉ ብለን ከጠበቅን የተሳሳትን ይመስለኛል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን “እግዚአብሔር ከእናንተ  ምስክርነትን አይፈልግም” ነው ያላቸው። ጸሐፍት ፈሪሳውያን ስለ ክርስቶስ በጎ ስለማይመሰክሩ ስለማይናገሩ ነው። ምክንያቱም በጭፍን፣ በቅናት፣ ስለጠሉት ነው። ቤተክርስቲያንም ከጠላቶቿ የእውነት ምስክርነትን አትጠብቅም፤ በበጎ ለሚያዩአት ግን ምስክርነቱ በእጅ የሚጨበጥ (የሚዳሰስ) በዐይነ የሚታይ ነው።

ቤተክርስቲያን ወንጌል ያልሰበከችበት ዘመንም፣ ጊዜም የለም። ወንጌል አልተሰበከም ለሚሉ ሰዎች ትናንት አለነበሩም፣ ዛሬም የሉም። ለነገሩስ የት ሆነው ያዩታል? ቢኖሩም አይገባቸውም፤ ውስጣቸውም በብዙ ችግር የተተበተበ፤ በቅራኔ የተሞላ ነው። በቅራኔ የተሞላ ደግሞ ከውጭ የሚነገረውን በጎ ነገር ለመቀበል ዝግጁ አይደለም።

 

ሊቀ ትጉኀን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ“ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው”

ሰው በተሰጠው የፈቃድ ነጻነት መሠረት የፈለገውን የመናገር መብት አለው። ፍሬ ነገሩ እውነቱ የቱ ነው? ሐሰቱስ? የሚ ለው ነው። ዲያብሎስ ስለ ቅዱስ ሚካኤል የብርሃን መላክነት አይመስክርም፤ ሊመሰክርም አይችልም። «ሚካኤል ደካማ ነው» እያለ የፈለገውን መናገር ይችላል። የዲያብሎስን ምስክርነትም ሚካኤል አይፈልገውም፣ አይቀበለውምም። ዲያበሎስ የፈለገውን ቢናገር ሚካኤልን አይከፋውም፤ ከጠላቱ ቡራኬ ስለማይጠብቅ። እንደዚሁ ሁሉ የእኛም ቤተክርስቲያን የሌሎችን ቤተእምነቶች ምስክርነትም ሆነ ክስ አታደንቀውም፤ አትደነግጥበትምም የእኛ ቤተክርስቲያን ጨርቅ ሰጥታ ጉቦ ሰጥታ እንዳልተስፋፋች ሁሉም ያውቁታል፤ ታዲያ ወንጌልና ክርስቶስን ሳትሰብክ ቤተክርስቲያን ሆና ሁለት ሺሕ ዓመታትን እንዴት ተሻገረች? አሸናፊ ስለሆነች በእውነቷ ብቻ ቆማ የምትኖር ናት። ጉቦ አይከፈልባትም፣ ማባበያም አትጠይቅም።

 

ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ልብን አሻክሮ ምላስን አለዝቦ በማነብነብ አይደለም፤ በድርጊት በማሳየትም እንጂ። በአንድ ታላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓል በአንድ ቤተክርስቲያን በአንድ ቀን ብቻ የምናደርገው ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ስብከቱ፣ ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ዋዜማው በተግባርም ታቦት ይዘን ቆመን ያስተላለፍነው ትምህርት በጠቅላላው መናፈቃኑ ለአንድ ዓመት ከጮኹበት፣ ብዙ ነገር ካወጡበት «አገልግሎት» እጅግ ብልጫ አለው። የዚህ አጠቃላይ አገልግሎታችን ዋነኛ ማእከልም ወንጌልና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ድኅነት ነው፡፡ ንዋያተ ቅድሳቶቻችን በሙሉ ስብከቶች ናቸው። በቅዳሴ ላይ ቄሱ፣ ዲያቆኑ መስቀል ይዞ የሚዞረው ምን  ለማሳየት ነው? ቀሳውስት ዕጣን እያጠኑ “ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ” እያሉ ሲያመሰግኑ ምስጢረ ሥላሴ እና ምስጢረ ሥጋዌን መስበከ፣ ማስተማራቸው ነው። ልብሰ ተክህኖዎቹ ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅድሳቱ ሁሉ መስቀል የሚደረግበት ለጌጥ አይደለም። ይህ ስብከት አይደለም እንዴ? መቅደስ ውስጥ ስንቀድስ በአራቱ ማእዘን የምንቆመው ጽርሃ አርያምን እያሳየን ነው። እነርሱ የማያስተውሉትን ሰባቱ ሰማያትን አምጥተን መቅደሱ ላይ ቁጭ አድርገን የምናሳያቸው ለስብከት ነው። ኪሩቤል እንዴት አድርገው ጌታን እንደተሸከሙት ታቦቱን መንበሩ ላይ አስቀምጠን ስንቀደስ እናሳያለን። በተጨባጭ እያሳየን እያሰተማርን ነው።

 

ደስ ሊለን ይገባል፤ ለሁለት ሺሕ ዘመን ወንጌል ሳይነበብባት በተለያየም መንገድ ሳይሰበክባት የማትውል የማታድር እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ቤተክርስቲያንም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነች። ቢያንስ በቅዳሴ ላይ ሰባኪ ያልቆመባቸው፣ ወንጌል ያልተሰማባቸው፣ ሃይማኖት አበው የማይነበብባቸው ገዳማትና አብያተክርስቲያናት የሉም። ስለዚህ ስብከት መንዘፍዘፍና ዓላማ የሌለው ጩኸት አይደለም። በእርጋታ፣ በማስተዋል፣ በጥንቃቄ የሚፈጸም በብዙ ዓይነት መንገድ የሚከናወን፤ ያልነበሩትን የምናመጣበት የነበሩትን የምናጸናበት አገልግሎት መሆኑን ሁሉም ይረዳ።

?

በዲ/ን እሸቱ

ሚያዝያ 26፣2003ዓ.ም

ሰው ማነው?ሰው ማነው? ብሎ ለጠየቀ “ሰው ንግግሩን ይመስላል” እንዳትለኝ ንግግሩ እምነቱን የሚያመለክት ዕውቀት አይሆነውምና ነው፡፡ ለሰው ባሕርያዊ ተፈጥሮና ዕውቀት ምስክሩ ውስጣዊ የአዕምሮ አቋምና የሕሊና ሕግ ነው ብለንም አንደመድምም፡፡ ሰው እንዲያውቅ የተመደበለት የሕግ ተፈጥሮ ዕውቀት መጀመሪያ ክፍል መልካምን ማወቅ፡፡ ሁለተኛ ክፋትን ንቆ መልካምን ገንዘብ ማድረግ፡፡ ሦስተኛ መልካምን በግብር መግለጽ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቱያን ሊቃውንት ይሁዳን ሲገልጹ “በአፍ አምኖ በልቡ የካደ” ይሉታል፡፡ ባህላችን “አፈ ቅቤ፤ ሆደ ጩቤ” እንዲል፡፡

 

የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት ያለ ትምህረት በተፈጥሮ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ሕገ ልቦና፤ ሕገ ህሊና፤ ሕገ ተፈጥሮ ወይንም ሕገ ጠብዓያዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል፤ ሕገ ሕሊናን ይተረጉማሉ፡፡ ለአብነት ብንጠቅስ አዳምና ሔዋን ቅዱስ ዳዊትና ይሁዳን፤ ከመጸጸት ክፉዎችን ከማዘን የምታደርሳቸው የሕሊና ኮሽታ ነች፡፡ በኑሮ ሂደት ሀዘን፣ ጸጸት ርትዕ በምናደርግበት ጊዜ ልዩ መንፈሳዊ ጥበብ አልያም ዕውቀት በመታደል ሳይሆን ሰው በመሆናችን በሕሊና ውስጥ የተቀረጸ በህሊና ሚዛን የሚሰጥ ፍርድ በመኖሩ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕገ ሕሊና በጽሑፍ ከተሰጡን ሕግጋት /ሕገ ኦሪት፣ ሕገ ወንጌል፣ ማሕበራዊ ሕግ/ በላይ ሰማያዊና ምስጢርን ለመጠበቅ ሲያገለግል እናገኘዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሀገር የግል ምስጢር ይጠበቅ ዘንድ መንፈሳዊ ሕግና ማህበረሰባዊ ሕግ ይደነግጋል፡፡ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ያለ ምድራዊ ሕግ አስገዳጅነት በሕገ ልቦና ዳኝነት ለሰማያዊ ምስጢር የታመነች ነበረች “እናቱ ማርያም በልቧ ትጠብቀው ነበር” እንዲል፡፡ /ሉቃ.2÷19/፡፡

 

 

ሰው ራሱ መጽሐፍ ነው” የሚለው የአነጋገር ስልት የሚያስተላልፈው ሰው ይነበባል፤ ይጠናል፤ ይተነተናል ይጸድቃል፤ ይሻራል ለማለት ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ለድርጊታችን ብያኔ ፍርድ ለመስጠት ረቂቅ የሕሊና ልጓም እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሰው በውስጡ የሚያረጋግጣት እውነት በክበበ አዕምሮ በሚጨበጥ ሕገ ባሕርይ ከመገለፅ እምቢ አትልም፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እምነት በቅድሚያ እንዲገኝ ግድ ቢሆንም በተግባር ወይንም በድርጊት ካልተዋሃደ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ፍሬ ቢስ፤ ረብ የሌለው ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ እምነታችን ከድርጊታችን ለምን ተዛነፈ? በጽናት የምናምነውን እምነት አጥቦ የመውሰድ ብቃት ያለው ሃይል ይኖር ይሆን? በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብር የምንወስናቸው መጠነ ሰፊ ጥቃቅን ውሳኔዎች ውህደ ሃይማኖት ምግባር የታሹ ወይስ የስሜት ውጤቶች ናቸው? እርግጥ ነው ስሜት አልባ ሰብአዊ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ሰማያዊ እውነት ከስሜት በላይ ነው፡፡ በገሃዱ ዓለም በብዙዎቻችን ሕይወት የሚታየው ውሳኔዎቻችን በድካም ባካበትነው ዕውቀት፤ መንፈሳዊ አስተምህሮ፤ ዓለማዊ ጥበብ፤ የቅዱሳን ሕይወት ሳይሆን ለስሜት ያጋደለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻልም የሚለውን ኃይለ ቃል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማረው ይሁዳ ለ30 ብር ሸጦታል ለምን ትለኝ እንደሆን ሰው ክፉን ነገር እስኪሰራ ሰው ልበ ሙሉ ይሆናልና ነው፡፡ ሁለተኛው የህሊና ዓይን ከነፍስ ባይለይም በኃጢአት ምክንያት ይጨልማል ይደክማልና ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ድርጊታችንን የሚቆጣጠረው በዕለቱ ስሜታችንን ያቀጣጠለው ኃይል እንጂ በጥረት ያካበትነው ትምህርት ወይም ዕውቀት ሆኖ አይታይም፡፡ ሰው ሆይ ለምን ይሆን

«የአሮጊቷ ሣራ» ወለደች ዐዋጅ ተሐድሶ ዘመቻ የጥፋት ፈትል እንደማጠንጠኛ

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በብሉያትና በሐዲሳቱም የምትነሣው ሣራ አበ ብዙኃን ሥርወ ሃይማኖት የምንለው የአብርሃም ሚስት ነች፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የብዙዎች አባት እንዲሆን ቃል ኪዳን ሳይገባለት በፊት፣ በመካንነት ታዝን፣ ተስፋም አጥታ ትተክዝ በነበረችበት ጊዜ ሦራ ትባል ነበር፡፡

ሦራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ ልጅ እንደምትወልድ ከአብርሃም በኩል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከገባላት፣ ተስፋም ከተሰጣት በኋላ ሣራ ተብላለች፡፡ እግዚአብሔርም ስለእርሷ ለአብርሃም «የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፤ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ፤ እባርካታለሁ፤ ደግሞም ከእርሷ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፤ የአሕዛብ እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ» በማለት ተናገረው /ዘፍ. 17፥15/፡፡

ሣራ ሦራ ተብላ ትጠራ በነበረበት፣ ያለተስፋ በኖረችበት የቀደመው ዘመኗ ለአብርሃም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፡፡ ሦራ ዘር ማጣት ታላቅ ሐዘን በሆነበት በዚያ ዘመን፣ መካንነት ያስንቅ በነበረበት በዚያን ጊዜ አብራም ከሌላ ይወልድ ዘንድ አዘነችለት፡፡ አብራም አጋር ወደ ተባለችው ግብጻዊት ባሪያዋ ይደርስ ዘንድ «እነሆ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ ምናልባት ከእርሷ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርሷ ግባ» አለችው፡፡ /ዘፍ.16፥2/ በትሑቷ ሦራ ምክር አጋር ከአብርሃም በፀነሰችበት ወራት ሦራን አሳዘነቻት፤ አጋርም ተመካች፤ እመቤት የነበረችውን ሦራ ስለመካንነቷ በዓይኗ አቃለለቻት፡፡ ይህ ለሦራ በእግዚአብሔር እና በባሏ በአብራም ፊት ያዘነችበት ሰቆቃዋ ነው፡፡ ሦራም ከሐዘኗ ጽናት የተነሣ አብራምን እንዲህ አለችው «መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይኗ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ» አለችው፡፡ በአብራም ፍርድም ሦራ ባሪያዋን አጋርን በመቅጣቷ አጋር ኮበለለች፡፡

እንግዲህ ከላይ አስቀድመን የጠቀስነው ለአብርሃም የተገባው ቃል ኪዳን የተሰጠው ሦራና አብራም በዚህ ሐዘን ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ያዘነችው ሦራ ከቃል ኪዳኑ በኋላ የብዙኃን እናት ልትሆን ሣራ ተብላ እርሱም የብዙዎች አባት ሊሆን አብርሃም ተብሎ የተስፋው ቃል ተነገረው «በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃልኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ» /ዘፍ.17፥19/፡፡

እግዚአብሔር ለአብርሃም ሣራ እንደምትወልድ የነገርውን የተስፋ ቃል በቤቱ በእንግድነት ተገኝቶ አጸና፡፡ «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች፡፡»/ዘፍ.18፥10/ አለው፡፡ ሁል ጊዜም ቃሉ የሚታመን እግዚአብሔር ይመስገንና እንደተባለው ሆነ «እግዚአብሔርም እንደተናገረው ሣራን አሰበ እግዚአብሔርም እንደተናገረው ለሣራ አደረገላት ሣራም ፀነሰች እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት አብርሃም ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው» /ዘፍ.21፥1/ «ሣራም እግዚአብሔር ሳቅ /ደስታ አድርጎልኛል ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች ደግሞም ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና /ዘፍ. 21፥7/፡፡

እንግዲህ መካኒቱ ሣራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ በጨዋነት ወልዳ ለአብርሃም ለዘላለም የገባው ቃል ኪዳን የሚፈጸምበትን ዘር ይስሐቅን አሳድጋለች፡፡ በቃል ኪዳን፣ በተስፋ የተወለደው ይስሐቅ ታላቅ ነውና «የዚህች ባሪያ /የአጋር/ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስም» አለች፡፡ እግዚአብሔርም ቃሏን ተቀብሎ ለአብርሃም «ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና…» አለው /ዘፍ.21፥1-12/፡፡

እንዲህ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የከበረችው ሣራ በብሉያት ብቻ ሳይሆን በሐዲሳትም ለተለያዩ ጉዳዮች እንደ አርአያና ምሳሌ ስትጠቀስ እናነባለን፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሚስቶችን ሲመክር በመልካም ትሑት ሰብእናዋ አርአያ የምትሆን አድርጎ የጠቀሳት ሣራን ነው «ጠጉርን በመሸረብ፣ ወርቅን በማንጠልጠል፣ ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጪ በሆነ ሽልማት» ሳይሆን «በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ» ተጎናጽፋ ውስጧን ያስጌጠች ብፅዕት ሚስት መሆኗን መስክሯል፡፡ «ሣራ ለአብርሃም ጌታዬ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ፡፡» /1ጴጥ. 3፥3-6/ ብሏል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የክርስቶስ የማዳኑ የምስራች ከታወጀላቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን ካልጠበቅን አንድንም የሚሉ ቢጽሐሳውያንን ቃል ሰምተው ያመኑ የገላትያን ሰዎች በገሰጸበት መልእክቱ ሣራን የሕገ ወንጌል ምሳሌ አድርጎ አቅርቧታል፡፡ በአንጻሩ ባሪያዋን አጋርን የሕገ ኦሪት ምሳሌ አድርጎ አቅርቧል /ገላ.4፥21/፡፡

የሣራን ሕይወት በዚህ ጽሑፍ ያነሣንበትንም መሠረታዊ ምክንያትም ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ምሳሌያዊ መልእክት ተንተርሰው ያለአገባቡ እየጠቀሱ የቤተ ክርስቲያናን ልጆች ምእመናንን ግራ ስለሚያጋቡ የተሐድሶ መናፍቃንና ተሐድሶአዊ ትምህርት ስለሚያስተምሩ ሰዎች ሐሳብ ለማንሣት ነው፡፡ በቅድሚያ የቅዱስ ጳውሎስ የመልእክቱን ሐሳብ በአጭሩ እናብራራና፤ ተሐድሶ የዘመቻ ማወራረጃ አድርጎ ስለሚጠቀምበት ጥራዝ ነጠቅ ቃልና አስተሳሰብ ደግሞ ቀጥሎ እናመጣለን፡፡ ሐዋርያው ስለዚህ ነገር ሲናገር የሚከተለውን ብሏል፡፡

«እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ? እስኪ ንገሩኝ፤ አንዱ ከባሪያዪቱ አንዱ       ከጨዋዪቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደነበሩት ተጽፏልና፤ ነገር ግን የባሪያዪቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዷል፤ የጨዋዪቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዷል፤ ይህም ነገር ምሳሌ ነው እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳናት ናቸውና፤ ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፤ እርሷም አጋር ናት፤ ይህቺም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጆቿ ጋር በባርነት ናትና፤ ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት፤ እርሷም እናታችን ናት… ስለዚህ ወንድሞች ሆይ የጨዋዪቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያዪቱ አይደለንም» /ገላ.4፥21-31/፡፡
በገላትያ መልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ «የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች» ስለነበሩት ከአይሁድ ወገን የሆኑ ካልተገረዛችሁ፣ ሕገ ኦሪትንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም እያሉ የሚያስተምሩ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ኦሪታዊ ሁኑ የሚሉ ሰዎችን ትምህርት እየሰሙ የወንጌልን ቃል ቸል ያሉት የገላትያን ሰዎች በግልጽ «እግዚአብሔርን ስታውቁ፣ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን ? ቀንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ…» ይላቸዋል፡፡ /ገላ.4፥9-11/
የሐዋርያው ዋነኛ ጉዳይ ሕገ ኦሪት ይጠበቅ አይጠበቅ በመሆኑም ነው «እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ?» ያላቸው /ገላ. 1፥21/፡፡ ምክንያቱም ያመኑትን ሁሉ በደሙ የዋጀ የኢየሱስ ክርስቶስ የምስራች ወንጌል ከተነገረች በኋላ ዳግመኛ ወደ ኋላ ተመልሶ ቀንና ወርን ዘመንንም እየቆጠሩ መሥዋዕተ ኦሪትን ለማቅረብ፣ ግዝረትን አበክሮ ለመጠበቅ፣ ያንንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም ወደሚል ትምህርት መመለስ ያሳፍራልና፡፡
ስለዚህ እናንተ በኦሪት እንኑር የምትሉ ሆይ! በኦሪት የተነገረውን ምሳሌ አንብቡ ብሎ የሣራን እና የአጋርን ምሳሌነት ያነሣል፡፡ በኦሪት አብርሃም አስቀድመን እንዳየነው ጨዋይቱ ከተባለችው ከእመቤቲቱ ሣራ ይስሐቅን፣ ከባሪያይቱ ከአጋር ደግሞ እስማኤልን ወልዷል፡፡ የሁለቱ ልደት ግን ለየቅል መሆኑን ይነግራቸዋል፡፡ ከባሪያዪቱ የተወለደው አጋር ሙቀት ልምላሜ እያላት ተወልዷልና፤ ከእመቤቲቱ የተወለደው ግን ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በዘጠና ዓመቷ/ ከእግዚአብሔር ብቻ በተሰጠው ተስፋ ተአምራትም ተወልዷልና፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሴቶች የሕገ ኦሪትና የሕገ ወንጌል ምሳሌ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቃሉ «ይህም ነገር ምሳሌ ነው» እንዳለ /ገላ. 4፥24/፡፡ አጋር ኦሪትን ደብረ ሲናን አንድ ወገን ያደርጋል፤ ሣራን፣ ወንጌልን ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌምን ደግሞ አንድ ወገን እያደረገ እያነጻጸረ ተናግሯል፡፡
አንዲቱ /ኦሪት/ አምሳል መርገፍ ሆና በደብረ ሲና ተሠርታለችና፤ ደብረ ሲናም ከኢየሩሳሌም ስትነጻጸር በምዕራብ ያለች ተራራ ናትና፤ ስለዚህ ይህች ምድራዊት የምትሆን አምሳል መርገፍ አማናዊት ከምትሆን ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ጋር ስትነጻጸር ዝቅ ያለች ናትና «ወትትቀነይ ምስለ ደቂቃ» አምሳል መርገፍ በመሆን ከልጆቿ ጋር ትገዛለች፡፡ ላዕላዊት የምትሆን ኢየሩሳሌም ግን ከመገዛት ነጻ ናት ብሎ «ወይእቲ እምነ፤ እርስዋም እናታችን ናት» ይላል፡፡ ይቺም እናታችን ሣራ ምሳሌዋ የምትሆን ወንጌል ናት፡፡
ስለዚህ ከሣራ የተወለደው ተስፋውን ወራሽ እንደሆነ ሁሉ እኛም ከወንጌል የተወለድን ክርስቶሳውያን በይስሐቅ አምሳል እንደይስሐቅ ተስፋውን መውረስ የሚገባን የነጻነት ልጆች ነን ማለቱ እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስተምራሉ፡፡ የባሪያዪቱ ልጅ ከእመቤት ልጅ ጋር ተካክሎ ርስት አይወርስምና በበግና በፍየሎች ደም ምሳሌያዊ ወይም ጥላ   አገልግሎት በምትሰጥ ገረድ /ሞግዚት/ የተባለች የኦሪት ልጆች አይደለንም፡፡ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ልጅ ሥጋና ደም ነጻ በምታወጣ አዲስ ኪዳን የወንጌል ልጆች ነንና፡፡
ሐዋርያው ይህንን ሁሉ ያለው ካልተገረዛችሁ አትድኑም የሚለውን የቢጽ ሐሳውያንን ትምህርት በመኮነን ሲሆን ይህንንም በግልጽ «በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና /ገላ. 5፥6/ ይላል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ ያለው ሕይወትም ፍትወተ ሥጋን አሸንፎ በመንፈሳዊ ተጋድሎ የበቁ ሆኖ በመንፈስ መራመድን ነው፡፡ ይህ ሣራ በተመሰለችባት ሕገ ወንገል ውስጥ የተጠራንበት የመታዘዝ ሕይወት ነው፡፡ ሐዋርያውም ለገላትያ ሰዎች ይህንኑ ተርጉሞ ሲናገር «የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ» /ገላ. 5፥24/ አለን፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞት ጋር የሰቀሉ መንፈሳውያን፣ በፍቅር የእግዚብሔርን ትዕዛዝ የሚፈጽመው የጨዋይቱ /የእመቤቲቱ/ የሣራ ልጆች ናቸው፤ እንጂ ሥጋዊ ሥርዓት፣ መርገፍ፣ ጥላ በሆነው ብሉይ ኪዳን ውስጥ የመገረዝ አለመገረዝ ጣጣን የሚሰብኩ፣ የሚሰበኩ በሥጋ ልማድ የወለደችው የባሪያዪቱ የአጋር ልጆች አይደሉም፡፡
እንግዲህ በነጻነት የምትመራውን ላይኛይቱን ኢየሩሳሌምን የመረጡ ክርስቶሳውያን ለ2ሺሕ ዘመናት ያህል ክርስቶስን በመስበክ በስሙም ክርስቲያን ተብለን ስንጠራ ኖረናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ገና አስቀድሞ በ34 ዓ.ም «ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ካለው ጃንደረባው ጀምረው ሠልጥና ከነበረችው ባሪያይቱ አጋር ይልቅ በተስፋው ሥርዓት የወለደችውን እመቤቲቱን ሣራ መርጠው እስከዚህ ዘመን ድረስ ኖረዋል፡፡
ከየካቲት ወር 1990 ዓ.ም ጀምሮ ግን «ተሐድሶ» በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በይፋ በጀመረው ዘመቻ ውስጥ የዘመቻው አዋጅ ማጠንጠኛ «አሮጊቷ ሣራ እኔ /እኛን/ ወለደች» የሚለው ቃል ነው፡፡ «የተሐድሶ መነኮሳት ኅብረት» የተባለው ቡድን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሆኖ ከቤተ ክርስቲያን ማዕድ እየተቋደሰ ነገር ግን በመሠሪነት ለመናፍቃን ተላላኪ ሆኖ የቆየ ሲሆን በየካቲት ወር 1990 ግን በአዲስ አበባ ከተማ በኢግዚብሽን ማዕከል በፕሮቴስታንቶች ተደራጅቶ በተዘጋጀው «ጉባኤ» በይፋ ራሱን ለይቶ የ«ተሐድሶ» ጥሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲደረግ ሲያውጅ ተገኝቷል፡፡ /ይህንን ለማጋለጥ የወጣወን ቪዲዮ ፊልም ወይም ቪሲዲ ይመልከቱ/ በዚህ አዋጅ በጉልህ የሚስማው ድምፅ ከላይ የተጠቀሰው «አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች» የሚለው ንግግር ነበር፡፡ ይህንን ቃል ደጋግሞ ሲያስተጋባ የነበረው አባ ዮናስ /በለጠ/ የተባለው «መነኩሴ» «ወንጌልን ለመስበክ ተሾምኩ፤… አሮጊቷ ሣራ ወለደች፤ አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች፣ ዘውዱን ወለደች፣ ፍስሐን ወለደች፣ ገብረ ክርስቶስን ወለደች… ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል…» ወዘተ እያለ አብረውት ለጥፋት የተሰለፉ ከሃዲ መነኮሳትን እየጠቀሰ ፎክሯል፡፡
በእነ አባ ዮናስ አዋጅ ውስጥ ያለው ግልጽ መልእክት ግን በሁለት መልኩ የሚታይ ወይም ሊተረጎም የሚችል ነው፡፡
1.    ቤተክርስቲያንን በእርጅና ዘመኗ ከወለደችው ከቅድስት ሣራ ጋር በማነጻጸር ራሳቸውን የዚህችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አድርገው በማቅረብ ከዚህች ቤተክርስቲያንም አካል የተገኙ መሆናቸውን በመግለጥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እነርሱ የሚሉት እንደሆነ አድርገው ለማደናበር ነው፡፡
2.    ሌላው የድፍረት መልእክት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በባሪያይቱ በአጋር ምሳሌ ልትጠቀስ የምትችል ኦሪታዊት፤ የጨዋይቱ የተባለች የሣራ የተስፋው ዘር ቅሪት የሌለባት፣ የወንጌል ብርሃን ያልበራባት፤ ክርስቶስን የማታውቅ፣ ጌትነቱንም የማታምን አድርገው አቅርበዋታል፡፡ ራሳቸውንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወንጌልን ለማድረስ የተሾሙ በኩራት አድርገው አቅርበዋል፡፡
የመጀመሪያውን ትርጉም ወይም መልእክት በማጉላትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም የዚህን የ«ተሐድሶ» መሠሪ አካሔድ በውል በመረዳት አውግዞ በመለየትና ውግዘት በማስተላለፍ ለ2ሺሕ ዘመናት ወንጌልን ስትሰብክ የነበረች ቤተ ክርስቲያንን ልዕልናና ክብር አጉድፎ በወንጌል ሰባኪነት ስም በማጭበርበር ፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ለመዝራት ተሐድሶ እያደባ መሆኑን አጋልጧል፡፡ ጠቅላይ ቤተክህነት ከሰጠው ሰፊ መግለጫ ውስጥ ይህን የተመለከተውን በአጭሩ እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡

 

«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» የሚል ኃይለ ቃል መናገራቸው ተዘግቧል፤ መናፍቃኑ ይህን የተናገሩት የእነሱን ከጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን አፈንግጦ መውጣት የዘጠና ዓመት እድሜ ከነበራት እና ከቅድስት ሣራ ከተወለደው ከይስሐቅ ልደት ጋር ለማነጻጸር በመፈለግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡


የይስሐቅ እናት ቅድስት ሣራ በመሠረቱ እናትና አባቱን የሚያከብርና የሚያስከብር እንጂ የሚያዋርድ፣ እናትና አባቱን የሚያስመሰግን እንጂ ሰድቦ የሚያሰድብ፣ በእናትና አባቱ እግር የሚተካ እንጂ እናትና አባቱን የሚክድ፣ በወላጆቹ የተመረቀ እንጂ የተረገመ ልጅ እናት አይደለችም፡፡


በቅድስት ሣራ አምሳል የተጠቀሰችው ጥንታዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም እንዲሁ እናቱን ለመሸጥና ለመለወጥ የሚያስማማ፣ እናቱን ሲሰድብና ሲነቅፍ ሐፍረት የማይሰማው ርጉም ልጅ እናት አይደለችም፤ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያለ ልጅ አልወለደችም፣ አትወልድምም፡፡


ጠላትና አረም ሳይዘሩት ይበቅላል እንደሚባለው፣ በአንድ የስንዴ ማሳ ላይ የበቀለ አረም ቢኖር ያ አረም ሳይዘራ የበቀለ መሆኑን ማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደማይሆን ሁሉ እነዚህ መናፍቃንም በቤተ ክርስቲያናችን የስንዴ ማሳ ላይ ሳይዘሩ የበቀሉ ጠላቶች እንደሆኑ መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በምሳሌ ዘር እንደተጠቀሰው /ማቴ.13፥24-30/ በንጹሕ ስንዴ ማሳ ላይ ጠላት የዘራው ክርዳድ ሊበቅል እንደሚችልም ታውቋል፡፡ እነዚህ መናፍቃንም የጠላት እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን አበው ተክል ባለመሆናቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተወለዱ አድርገው ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ የማን ልጆች እንደሆኑ ቢጠይቁ ዕውነቱን ለማወቅ በቻሉ ነበር፡፡


አሁንም ቢሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ «በኋላ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ገንዘብን የሚወድዱ፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ሐሜተኞች፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ የማይወዱ ከዳተኞች ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ይክዱታል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን፣ ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉትን… የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና» /1ጢሞ. 3.1-7/ ሲል እንደተናገረው እነዚህ መናፍቃን ከዚህ የትንቢት ዘመን የተወለዱ እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች አለመሆናቸውን በግልጽ መንገር ግዴታ ይሆናል፡፡ /መጋቢት 26 ቀን 1990 ዓ.ም/

ጠቅላይ ቤተክህነት የተነተነበት መንገድ እንዳለ ሆኖ የ«ተሐድሶ» ቡድን «አሮጊቷ» የሚለውን ቃል የመረጠበትን መሠረታዊ ምክንያት በውል ማጤን ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የምትሰብክን ቤተ ክርስቲያን ከቅድስት ሣራ ጋር አነጻጽሮ ባቀረበበት መንገድ አስበው ተናግረውት ቢሆንማ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አፈንግጠው የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ባዘጋጁት በዚያ የስድብ ጉባኤ ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት ትምህርትና ሥርዓት የምእመ ናንን ሕይወት ባላዋረዱ ባላናናቁ ነበር፡፡ ነገር ግን «አሮጊት /አሮጌ» የሚለውን ቃል የመረጡት ቤተ ክርስቲያን አርጅታለችና ማደስ አለብን ለሚለው አስተሳሰብ መንደርደሪያ ነው፡፡ እነዚህ የተሐድሶ መናፍቃን ተወግዘው ቢለዩም በውጪም በውስጥም ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ለመገዝገዝና አስተምህሮአቸውን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ «መምህራን» አውቀውም ሳያውቁም በየዓውደ ምህረቱ እንዲያስተጋቡ ተፅዕኖ መፍጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡

እነ አባ ዮናስ የ«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» ቃላቸውን ከአዋጁ ከ12 ዓመታት በኋላ አሁን በይፋ ደግሞ «ቤተ ክርስቲያንን አሪታዊት፣ ጨለማ ውስጥ ናት ሲሉ አሮጊቷ ሣራ ዛሬ እኔን ወለደች፣ እገሌን ወለደች፣ እገሌን ወለደች…» የሚል ከእነ አባ ዮናስ ጋር የቃልና የስሜት ዝምድና ያለው የአዋጅ ቃል በአንዳንድ ሰባኪያን ነን ባዮች ተሰምቷል፡፡ በአባ ዮናስና በእነዚህ ሰባኪያን መካከል ያለው የአቀራረብ ልዩነት የአባ ዮናስ በኤግዚቢሽን ማዕከል፣ እነዚህ ደግሞ በራሷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓውደ ምህረት ላይ ማወጃቸው ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው ትምህርት ቃሉም ትርጓሜውም የታወቀ ሆኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያናችንም ከጨዋይቱ የተወለድን ክርስቲያኖች አንድነት መሆኗ ለ2ሺሕ ዘመን የተመሰከረ ሆኖ ሳለ የአሁኖቹ «ሰባክያን» ራሳቸውንና ጓደኞቻቸውን ነጥለው «የተስፋው ወራሾች የአሮጊቷ የሣራ ልጆች» እያሉ የሚያቀርቡበት ገለጻ ትርጓሜ ይፋ መሆን አለበት፡፡

በመሠረቱ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ የተሰበከውን ምሳሌያዊ ትምህርት ይዞ ተንትኖ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ከአርባ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ባሉበት ጥንታዊት እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ራሳቸውንና እነርሱ የመረጧቸውን የቡድን አባላት አባ ዮናስ ባቀረቡበት መንገድ «የአሮጊቷ ሣራ» ብሎ የጠሩበት ቤተ ክርስቲያን እነርሱን ከመውለዷ በፊት ምን ጎድሎባት፣ ምንስ አጥታ ነበር ? ቅዱስ ጳውሎስ መካኒቱ፣ ጨዋይቱ፣ እመቤቲቱ እያለ የጠራበት ቅጽል እያለ «አሮጊቷ» የሚለውን በማስጮኽ ማቅረብስ ለምን ተፈለገ ? ቀጥተኛ ምንጩስ ማነው ? ምንድነው ? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው ናቸው፡፡ እነ አባ ዮናስ «አሮጊቷ ሣራ» ያሏትን ቤተ ክርስቲያንን ድንግል ማርያምን፣ ተክለሃይማኖትን፣ ጊዮርጊስን በልብሽ አኑረሻልና አውጪ እያሉ በአደባባይ ድፍረት ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ «ሰባክያን» የ«አሮጊቱ ሣራ» አስተምህሮ ውስጥ ያለው አንድምታስ ምንድነው ? እነ አባ ዮናስ በ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮአቸው «ቤተክርስቲያኒቱ በ4ኛው ክፍለ ዘመን አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ከሰበኩበት ጊዜ በኋላ ወንጌል አልተሰበከችም የወላድ መካን ሆና የኖረች ናት» በማለት አሁን እነርሱ ያንን ለመፈጸም የተወለዱ አድርገው አቅርበዋል፡፡ የእነዚህ ሰባክያን የ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮስ ከዚህ አንጻር ምን ይላል ?

ይህ ብቻ ሳይሆን አባ ዮናስ «ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል» ያለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዒላማ ያደረገ ፉከራው በእነዚህ ሰባክያን የመዝሙር መንደርደሪያዎች ውስጥ ከሚነገረውና «መዶሻ ያልያዘ ሠራዊት ኢያሪኮን ያፈርሳል…» ከሚሉት አዝማች ቃል ጋር ያለውንም የትርጉም ዝምድና መጤን እንዳለበት         እንድናስብ ያስገድዳል፡፡ በተመሳሳይ ይህንኑ መንገድ ተከትሎ በየደረጃው ምእመናን እነ አባ ዮናስ በግልጽ ያወጁት የ«ተሐድሶ» ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ዓውደ ምህረቶቻችን ላይ አሁንም ወደቆሙ «መምህራን» መሻገር አለመሻገሩን ቃሎቻቸውን እያጠኑ ለመመርመር ተገደዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የሚመለከታቸው አካላትም የእነዚህን «ሰባኪያን» ትምህርት መርምረው ካለማወቅ በስሕተት የቀረበ ትምህርት መሆኑን ወይም በድፍረት የቀረበ ለ«ተሐድሶ» ዘመቻ የጥፋት ፈትል ማጠንጠኛ መሆን አለመሆኑን ለይተው እንደሚያቀርቡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ምንጭ፦ ሐመር 19ኛ ዓመት ቁጥር 2

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መሠልጠን ማለት ግን ምን ማለት ነው?!

በዲ/ን ቴዎድሮስ በየነ

ሥልጣኔ ሲተነተን አንድ ገጽታ፣ አንድ መልክ፣ አንድ ወጥ ሳይሆን ብዙ መልኮች፣ ብዙ ገጽታዎች እንዳሉት ማጤን ይገባል፡፡

ሥልጣኔ የሰው ልጅ አካባቢውን ለኑሮ እንዲስማማው፣ እንዲመቸው ለማድረግና ለሕይወቱ የተመቻቸ ሥፍራ ለማድረግ የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ቀስ በቀስ የተከሰተ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሥልጣኔ ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ለወደፊትም የሚኖር የሰው ልጅ የተፈጥሮ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሆኖም ግን ስለ ሥልጣኔ ብይን ሲሰጥ፣ ስለ መግለጫው ሲነገር፣ ስለ ጥቅሙ ሲዘመር፣ ስለ ግቡ /መዳረሻው/ ሲታተት፤ ሥልጣኔ ከቁሳዊ ነገር መሟላትና ከሥጋዊ ድሎትና ምቾት ጋር ብቻ ሲያያዝ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ይመስላል የሥልጣኔን ክስተት በዓይን በሚታዩ፣ አብረቅራቂና ሜካኒካዊ በሆኑ ነገሮች ብቻ እንድናይ ከታች ጀምሮ በትምህርት ቤት እንድንማረው የሆነው፡፡ በሚዲያ ዘወትር እንድንሰማው የተደረገው፡፡ከበደ ሚካኤል ስለ ሥልጣኔ ምንነት ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡፡

“ሰዎች ራሳቸውን ለማረምና ኑሯቸውን ለማሻሻል ሲሉ በሥጋና በመንፈስ ያፈሩት ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ድረስ የተከማቸው የሥራ ፍሬ ሥልጣኔ ይባላል፡፡”

በእኚህ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ የሥልጣኔ ምንነት ገለጻ ውስጥ በዚህ ዘመን ሚዛን ላይ ያልወጡ ታላላቅ ቁምነገሮችን አምቆ ይዟል፡፡ ከነዚህም ውስጥ “በሥጋና በመንፈስ” በማለት ለሰው ልጅ የህላዌው መሠረት፣ የደስታው ምንጭ ሥጋዊ ፣/ቁሳዊ/ ነገር ብቻ እንዳልሆነ አስምረውበታል፡፡ መንፈሳዊም ፍሬም ሥልጣኔ እንደሆነ፡፡ ሥልጣኔ ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ድረስ የተከማቸ የሥራ ፍሬ ነው ሲሉም፤ ሥልጣኔ የዛሬ ሦስት መቶ ወይም አራት መቶ ዓመት ክስተት ብቻ አይደለም ማለታቸው ነው፡፡

ዘመናዊ ሥልጣኔን ከምዕራባውያን ሥልጣኔ ጋር ብቻ አያይዞ የሥልጣኔ መልክና ገጽታ በምዕራባውያን መስታወት ብቻ የሚታይ እንዳልሆነም የጸሐፊው እይታ ያሳያል ፡፡

ዛሬ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሥልጣኔ ማለት ምዕራባዊ መስሎ መቅረብ፣ የምዕራብ ቋንቋን መናገር፣ የምዕራባውያንን የአኗኗር ዘይቤ መያዝ ይመስላል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያውያን ሠርግ ሲዘፈን እንደነበረው “የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በእንግሊዝ አናግሪአቸው” የምዕራብ ቋንቋ መናገር የኩራት ምልክት፣ የሥልጣኔ ምልክት ነበር፡፡ ይህ ግን ስህተት እንደሆነ ኤቪሊንዎ የተባለ አንድ ምዕራባዊ ጸሐፊ ኢትዮጵያ ኋላቀር ነች እያሉ የሚተቹትን በነቀፈበት ጽሑፉ እንዲህ ይላል፡-

“የአንድን ኅብረተሰብ ትልቅነት የምትገምተው አውሮፓን ስላልመሰለ ወይም የ”ሰለጠኑ” አገራትን ስላልመሰለ ሳይሆን በራሱ እምነትና የእሴት ስልት ውስጥ የተቃረነ ነገር ሲሠራ ነው፡፡”

የዚህ መጣጥፍ ዐቢይ ጭብጥ ሥልጣኔ ከራስ እሴት አለመቃረን ነው የሚል ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ትውፊታችን፣ ባህላችንና ታሪካችን የኢትዮጵያውያን እሴቶች ምንነትን ይነግሩናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ እዚህ ላይ የምናየው ስለ ከበረው የዳኝነት /ፍትሕ/ ሥርዓት እሴታችን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ረዥም ዘመን ታሪካችን የዳኝነት ሥርዓት የተከበረ ነው፡፡ ፈረንጆች “the rule of law /ሕጋዊ ሥርዓት/” የሚሉትን የኢትዮጵያ ሕዝብ “የሕግ አምላክ” ይለዋል፡፡

በቆየው የኢትዮጵያ ባሕል አንድ ሰው ከመንገድ ላይ ባላጋራውን ካየ “በሕግ አምላክ ቁም” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው /ተቆራኝተው/ ያለ ፖሊስ አጀብ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡

“በቆረጡት በትር ቢመቱ፤ በመረጡት ዳኛ ቢረቱ፤ የእግዜር ግቡ ከብቱ፡፡” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በቀድሞ ዘመን “የተበደለ ከነጋሽ፤ የተጠማ ከፈሳሽ” ብለው፤ የተጠማ ውሃን እንደሚሻ ሁሉ የተበደለም ጉዳቱን ለንጉሡ አሰምቶ ትክክለኛ ፍርድ እንደሚያገኝ ያምኑ ነበር፡፡ በዚህም ምኞትና ሐሳቡን የፈጸሙ የመንፈስ ልዕልና ደረጃቸውን ያሳዩ ፈታሔ ጽድቅ /እውነተኛ ዳኞች/ በታሪኩ አይቷል፡፡ አጼ ዘርአያዕቆብ /15ኛው መቶ ክ/ዘ/፤ ልጃቸው የደሀ ልጅ ገድሎ በዳኞቻቸው ዘንድ በቀላል ፍርድ ስለ ተለቀቀ ይግባኙን ንጉሡ ወስደው የሞት በቃ ፈርደው እንዳስገደሉት ይታወቃል፡፡ ይህ ምንም ርትዕ ቢሆን፤ ከአብራክ በተከፈለ ልጅ ላይ ሞትን መፍረድ ሐቀኝነት ነው፡፡ በሌላ ዘመንና ቦታም ይህ ተመሳሳይ ታሪክ በትግራዩ ራስ ልዑል ሚካኤል ስሑል /18ኛው መ/ክ/ ተፈጽሟል፡፡ ሁለቱም ከግል ጥቅማቸው በተቃራኒ ቆመዋል፡፡ ይህ ነው ኢትዮጵያዊው መልካም እሴት፡፡ ሁለቱም መሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ሲጓደል በብርቱ እንደሚያዝን፤ ምንም የተወሰደው ሀብት ዋጋው ያነሰ ቢሆን በዳኝነት መዛባት እጅግ አድርጎ እንደሚቆጭ ያውቃሉ፡፡ “በፍርድ ከሄደችው በቅሎዬ፤ ያለ ፍርድ የሄዳችው ጭብጦዬ ታሳዝነኛለች” የሚል ጽኑ የፍትሕ ጥማት እምነቱ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ እነርሱም የርትዕ ፍርድ ታላቅነት አሳዩት፡፡

ስለዚህም የአንድ ሥልጡን ማኅበረሰብ አንዱ መገለጫው ይህን ከመሰለ ባሕላዊ እሴቱ ጋር አለመጋጨቱ፤ አለመቃረኑ ነው፡፡ ስለ ሥልጣኔ ስናወራ ለሥጋ እርካታ መገለጫ የሆነችውን የአብረቅራቂ ቁስ ሙሌትን ብቻ ይዘን መጓዝ የለብንም፡፡ የከበሩ የባሕልና የታሪክ እሴቶቻችንም የሥልጣኔ ማነጸሪያዎች ናቸው፡፡ የሰው ልጅን ማንነትና ፍላጎት በቁሳዊ ነገር ብቻ መመዘንም፤ ሰውን ከሰውነት ደረጃ ማውረድ ነው፡፡ በዚህ መተማመን ከተደረሰ አንድ ሥልጡን ማኅበረሰብ ለመገንባት በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ሥልጣኔን በግንጥል ጌጧ ሳይሆን በሙሉ ክብሯ እንረዳታለን ማለት ነው፡፡

ዛሬ ጊዜና ታሪክ በሰጡን ኃላፊነት ላይ ያለን ሁሉ “ደሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” የማንል ከሆነ፤ ከግል ጥቅም ይልቅ ለብዙኃኑ ጥቅም ካልቆምን? የሰው እንባ እሳት ነው ያቃጥላል ካላልን? ከራሳችን የእምነትና የእሴት ስሌት በተቃራኒ ስለቆምን በእውነት አልሰለጠንም፡፡

ውድ አንባቢዎች አፄ ዘርአያዕቆብና ራስ ልዑል ሚካኤል ስሑል በልባቸው ካለው የእምነትና የእሴት ስሌት በተቃራኒ ያልቆሙበት ምክንያት /ሠልጥነው የታዩበት ምሥጢር/ የሚከተሉት አራቱ ይመስሉኛል፡፡

1. እግዚአብሔር አለ፤ እሱ ይፈርዳል፤ በምንሰጠው ፍርድ እሱ ይመለከታል ብለው ማመናቸው፡፡

2.  ሕሊና አለ፤ እሱን ማምለጥ አይቻልምና ብለው ለሕሊናቸው በመገዛታቸው፡፡

3. ታሪክ አለ፤ ታሪክ ይፋረደናል፤ የምንሠራውን ነገር ለታሪክ ትተነው የምንሄድ ነን፤ ከታሪክ ማምለጥ አንችልም ብለው በጽናት መቆማቸውና፣

4.  ሕዝብ አለ፤ የተደረገውን ስለሚያውቅ ይመለከተናል፡፡ ይታዘበናል፡፡ ከእነዚህ ነገሮች ማምለጥ አንችልም ብለው በመንፈሳዊ ወኔ መቆማቸው ነው፡፡

ስለ እውነተኛ ዳኝነት ከቱባ ባሕላችን ውስጥ መዘን ስናጠና የምናገኘው የትልልቆቹን መሪዎች፣ የከበሩት አበውና፣ የሚደነቁት እመው ያልተዛባ ፍርድ ክዋኔ ምሥጢሩ፤ በምንሠራው ሥራ፤ በምንሰጠው ፍርድ እግዚአብሔር፣ ሕሊና፣ ታሪክና ሕዝብ አለ ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ከሰፈር የዕቁብ ዳኝነት እስከ ሀገር ማስተዳደር፤ ከማኅበር ሙሴነት እስከ ቤተ ክርስቲያን መምራት የቻለ ሰው በሚያስተላልፈው ውሳኔና በሚሰጠው ፍርድ ውስጥ ከላይ ያየናቸውን አራቱን የባሕላችንን እሴቶች በልቡናው ጽላት ቀርጾ በእነርሱ መመራት ካልቻለ፡፡ ፍትሕ ትጨነግፋለች፡፡ እውነት ከምድሩ ትጠፋለች፡፡ ፍቅር ጓዟን ጠቅልላ ትበናለች፡፡ ክህደት ታብባለች፡፡ ማስመሰል ትነግሳለች፡፡ ውሸት ትወፍራለች፡፡ ሥልጣኔ ቅዥት ትሆናለች፡፡

ይቆየን…..

 

” መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቁን የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች።” ማቴ.13፡45

capital C

Capital “C”

በድንቅነሽ ጸጋዬ

ሰኔ 1/2003 ዓ.ም.     

capital C

 
ዛሬ ደግሞ እንደ ሙአለ ሕፃናት ተማሪዎች Capital “C”ን እዚህ ምን አመጣት ትሉኝ ይሆናል፡፡ እኔም የትኩረት አቅጣጫዬ ስለ Capital “C” እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለ ትምህርት ሲነሣ ወላጆቻችን ሀ ብለው የጀመሩት በተለምዶ ቄስ ትምህርት ቤት ብለን በምንጠራቸው ሲሆን፥ ትምህርቱም ይሰጥ የነበረው የሁሉም አፍ መፈቻ ቋንቋ ባይሆንም አብዛኛው ሰው ይግባበት በነበረው የአማርኛ ቋንቋ ፊደል ሀሁ፣ አቡጊዳ፣ መልዕክተ ዮሐንስ ዳዊት…ወዘተ፥ ዘመናዊውን የአስኳላ ትምህርት ከመቀጠላቸው በፊት፥ እንደተማሩ እናውቃለን፡፡ ለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዋነኛ የትምህርት ማዕከል ሆና አገልግላለች፡፡
ስማቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የገነነው የእንግሊዙ “ኦክስፎርድ” እና የአሜሪካው “ሃርቫርድ” ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች መነሻቸው ከቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ በዛሬው አኳኋን ተደራጅተውና በዘመናዊ ትምህርት ተውጠው ከመገኘታቸው በፊት የሃይማኖት ትምህርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ነበሩ /የካቶሊክም ቢሆኑ/፡፡ ከዚህ የምንማረው ቁም ነገር፥ ዓለም ለደረሰበት የሥልጣኔ ቁንጮ የመድረስ ዋዜማውና መፍትሔው በሌሎች ላይ መንጠልጠል ሳይሆን በነባሩ /የራስ/ እሴት መሠረትነት ላይ ማነጹ እንደሆነ ነው፡፡ ለረጅም ዘመናት አገራችንን የመሩት ምሁራን ነገሥታቱና በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የነበሩ ቁልፍ ሰዎች መገኛቸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንደነበርም አይካድም፡፡
 
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፥ በየትኛውም አገር ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲማሩ ለትምህርት ያላቸው ፍላጎትና ተቀባይነት ብሎም የመረዳት ደረጃ ፈጣን ይሆናል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለቋንቋው እድገትና ተተኪ ለማፍራት የሚያደርገው አስተዋጽኦ ቀላል አይሆንም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ለአፍ መፍቻ ቋንቋ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት እናገኛዋለን፡፡ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ የተጻፈው ወንጌላውያኑ እንደተሰማሩበት የስብከት ቋንቋ፥ ቅዱስ ማቴዎስ በምድረ ፍልስጥኤም በዕብራይስጥ፤ ቅዱስ ማርቆስ ለሮማውያን በሮማይስጥ፤ ቅዱስ ሉቃስ ለመቄዶንያ በጽርዕ እና ቅዱስ ዮሐንስ ለኤፌሶን በዮናናውያን ቋንቋዎች መሆኑን እንረዳለን፡፡
በተጨማሪም ሐዋ.2÷1 እንደምናገኘው ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው 72 ቋንቋዎች ከተለያየ ሀገር ለበዓል የተሰበሰቡትን ሕዝቦች በየሀገራቸው ቋንቋ ወንጌልን ስላስተማሯቸው በዕለቱ 3000 ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ይህም ሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋው ሲማር ለመረዳት እና ወደ ተግባር ለመለወጥ ፈጣን እንደሆነ ያረጋግጥልናል፡፡

ሐዋርያዊት እና ዓለም አቀፋዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ለአፍ መፍቻ ቋንቋ ትኩረት በመስጠት ሁሉም ወንጌልን ተምረው ከሥላሴ ልጅነትን አግኝተው መንግሥተ እግዚአብሔርን እንዲወርሱ ባላት አቅም በሁሉም አህጉረ ስብከቶች በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ እኛስ ልጆቻችንን እንዴት እያስተማርናቸው ነው? በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው? ቢያንስ ከሀገርኛ ቋንቋዎች በአንዱ? ወይስ ጥሩ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሁኑ ከማሰብ? አብዛኛው ባለሀብትም/የትምህርት ቤት ባለቤቶች/ የወላጆች አስተሳሰብ ስለገባቸው ደረጃውን ባይጠብቅም የትምህርት ቤቱ ስም በእንግሊዝኛ ሲሆን ኢንተርናሽናል የሚል ተጨምሮበት፣ ማስታወቂያቸው በውጭ ዜጋ መሆን ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ ልክ ነዋ! በአገርኛ ቢጻፍ ማን ትኩረት ይሰጠዋል፡፡

ልጆቻችን በአፍ መፍቻቸው እየተማሩ ሌሎች የሀገራችንንም ሆነ የውጭ ቋንቋዎች ቢችሉ አይጠቅምም ባይ አይደለሁም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየሆነ ያለው ግን “የራስን ጥሎ” በአብዛኛው ትምህርት የሚጀምሩበት ቋንቋ እንግሊዘኛ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ ምን ችግር አለው የሚል አይጠፋም! ከአመታት በፊት የወንድሜን ልጆች ት/ቤት ልናደርስ እየሄድን የያዝኩትን መፍሔት ተቀብላ በፍጥነት Capital “C” አለችኝ፤ “ሐመር” ከሚለው ውስጥ “ር”ን ነጥላ በጣቷ እያመለከተችኝ፡፡ “ሐ” እና “መ”ን ግን እንደማታውቃቸው ስትገልጽልኝ በጣም ባዝንም አልፈረድኩባትም፡፡ A-for Apple, B-for Banana…. አየተባለች እንጂ በአፍ መፍቻዋ ፊደል እንድትቆጥር ከቤተሰብም ሆነ ከትምህርት ቤት እድል አላገኘችም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ብትሆንም የአማርኛ ውጤቷ እንደሌላው ትምህርት የሚደነቅ አይደለም፡፡ ታናሽ ወንድሟም ቢሆን የዚሁ ችግር ተጠቂ ስለሆነ በጥናት ወቅት የአባቱን እርዳታ የሚጠይቀው የአፍ መፍቻ ቋንቋው ለሆነው ነገር ግን ብዙም ለማይረዳው ለአማርኛ ነው፡፡ አንድ ቀን ነው “አባቢ ሐረግ ምን ማለት ነው?” አለው፡፡ አባትም የቻለውን ያህል ገለጸለትና በደንብ የተረዳ ስላልመሰለው በእንግሊዘኛ “Phrase እንደማለት” ሲለው ፈገግ ብሎ “ነው እንዴ” አለ! ይገርማል አማርኛን ለማስረዳት በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ማለት ነው፡፡
ሌላ ልጨምርላችሁ በመዲናችን ውስጥ ካሉ ስመ ጥር ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች በአንዱ የ5ኛ ክፍል መምህርት ጓደኛ አለችኝ፡፡ ተምሮ መፈተን፥ አስተምሮ መፈተን ያለነውና አማርኛ ትምህርት ልትፈትን ወደ ክፍል ዘለቀች ከተማሪዎቹ አንዱ ፈተናውን ተቀብሎ ”ጀምሩ“ ሲባል “ሚስ አልፈተንም” ብሎ እርፍ፡፡ “ለምን?” ሚስ ጠየቀች “አስኪ ተመልከችው ስትራክቸሩ /የፊደሉ ቅርጽ/ ሲያስጠላ” አላት፡፡ በዚህ አቋሙ በመጽናቱ ሚስም ሳታነብ፣ እሱም ሳይፈተን ቀረላችሁ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የአማርኛ ፊደላት በዝተዋልና ይቀነሱ” የሚሉ አስተየየቶች መነሣታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬ የፊደል ቅርጻቸው ያስጠላል ያሉን ሕፃናት ነገ ከነጭራሹ አያስፈልጉንም ላለማለታቸው ምን ያህል እርግጠኞች ነን? ቅኝ ብንገዛ ኖሮ እንግሊዝኛ እንችል ነበር ብለው በቁጭት የሚናገሩ ወገኖች እንዳሉም ባይዘነጋ፡፡ ይህን ሲሉ ግን ጣሊያን በኢትዮጵያ በነበረችባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ አንድም ጣልያንኛ ቃል ያላወቁትን አስተውለዋል? አሁንስ ቢሆን በተዘዋዋሪ የአስተሳሰብ ቅኝ ተገዢዎች መሆናቸውንስ?
የዛሬ ሕፃናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች መሆናቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የሀገራችን ባሕል ታሪክ እና የማንነታችን መገለጫ መዛግብቱ የተጻፉት ደግሞ በግዕዝ፣ በአማርኛ እና በሌሎች የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ሕፃናቱ የሀገራቸውን ባሕል፣ ታሪክ ማንነት ለመረዳት በውጭ ቋንቋ ተተርጉሞ ካልመጣ ላያነቡ ነው? ስለ እኛ በውጭ ቋንቋዎች የተጻፉትስ ምን ያህል ሚዛናዊ ሆነው ማንነታችንን ይገልጻሉ?
በሀገር ውስጥ ካሉ ሕፃናት ይህን ከተመለከትን በውጭ የኑሮ ውጥረት በበዛበት ቤተሰብ ተከታትሎ ባሕላቸውን፣ ታሪካቸውን በአጠቃላይ ማንነታቸውን እየተነገሩ ያላደጉ ሕፃናት እንዴት ይሆኑ? ይህን ስል ግን ባላቸው የተጣበበ ሰዓት በየቤታቸው እና በየአብያተ ክርስቲያናቱ ፊደል የሚያሰቆጥሩ ባሕላቸውና ታሪካቸውን የሚያስተምሩ መኖራቸውን ሳልዘነጋ ነው፡፡
ሐሳቤን ለማጠቃለል ያህል ወላጆችስ ይህ ጉዳይ አሳስቦን ያውቃል? ወይስ ጥሩ የውጭ ቋንቋ ስለተናገሩልን በቃ የዕውቀት ዳር የደረሱልን መስሎን ዝም ብለን ተቀምጠናል? የሚረከቧትን ሀገር ታሪክ፣ ባሕልና ማንነት የማያቁ ተተኪዎች እያፈራን መሆናችንንስ አስበነው እናውቃለን? እኔ ግን “ር”ን Capital “C” ስትለኝ በሁኔታው አዝኜ ዝም ባልል ኖሮ “ዘ”ን ኤች፣ “ረ”ን ኤል፣ “ጠ”ን ስሞል ኤም፣ “ዐ”ን ኦ፣ “ተ”ን ስሞል ቲ፣ “ሀ”ን ዩ፣ “ሠ”ን ደብልዩ ወዘተ ልትለኝ እንደምትችል አልጠራጠርም፡፡

“አብዝቶ የመመገብ ጣጣው”

  (በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
ግንቦት 30/2003 ዓ.ም.

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መግቢያ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዮሐንስን ወንጌል በተረጎመበት በ21ኛው ድርሳኑ “ ጌታችን በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄ በቃና ሰርግ ላይ ስለምን ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት እንደቀየረው  ከአብራራ በኋላ ከዛሬ 1500 ዓመት በፊት በአሁኑ ጊዜ እንደ አዲስ ግኝት ተደርገው የሚታዩትን አብዝቶ በመመገብ የሚመጡትን የጤና ጉድለቶች ጽፎልን እናገኛለን ፡፡ ጽሑፉ ተተርጉሞ እንዲህ ቀርቦአል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት ያኔ እንደቀየረ ዛሬም እኛን ድካማችንንና እንደ ወራጅ ውሃ በአንድ ቦታ ጸንቶ መቆየት የተሣነውን የሥጋ ፈቃዳችንን ከመቀየር አልተቆጠበም ፡፡ ዛሬም አዎን ዛሬም ልክ እንደ ወራጅ ውሃ ቀዝቃዛ ፣የፈጠነና ፣ ያልተረጋጋ ጠባይ ያላቸው ሰዎች አሉ ፡፡ እነዚህን ፈቃዶቻችንን ወደ ጌታችን እናምጣቸው ፤ እርሱ ወደ ወይንነት ይቀይራቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ውኃ ሆነው ከእንግዲህ አይቀጥሉም ፡፡ ነገር ግን ለራሳቸውና ለሌሎች ደስታን የሚሰጡ አካላት ይሆናሉ ፡፡

ባልተረጋጋ ውሃ የተመሰሉት እነማን ናቸው ? ለዚህ ከንቱ ዓለም ሕሊናቸውን ያስገዙ ወገኖች ፣ የዚህን ዓለምን ቅምጥልነት ፣ አለቅነትንና ክብርን የሚሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ፍቃዶቻችን እንደውኃ የሚፈሱ ፣ ፈጽሞ ያልተረጋጉ ፣ ለአመፃ የሚፋጠኑ ቁልቁል የሚምዘገዘጉ ውኆች ናቸው ፡፡
 
ዛሬ ሀብታም የነበረው ነገ ደሃ ይሆናል ፡፡ በአንድ ወቅት ዝናው ሲነገርለት፣ የተጌጠና የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሶ በሰረገላ ላይ የሚሄድና ብዙ አጃቢዎች የነበሩት ሰው ፣ ያለፈቃዱ ያን የተዋበ መኖሪያውን ተቀምቶ ወደ ወይኒ ተጥሎ ይገኛል ፡፡ ለሥጋው ደስታ የሚተጋው ሆዳሙ ደግሞ የሥጋ ፈቃዱን ከሞላ በኋላ ሆዱ ሳይጎድልበት ለአንድ ቀን መቆየት አይቻለውም ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምግቦች ከሆዱ ሲጠፉ ወደ ቀድሞው ምቾቱ ለመመለስ ሲል ከፊት ይልቅ አብዝቶ ይመገባል ፡፡ አመጋገቡም ሁሉን ጠራርጎ እንደሚበላ እንደጎርፍ ውሃ ነው ፡፡ በዝናብ ወቅት የሚነሣው ጎርፍ አስቀድሞ የነበረ ውሃ በከፈተለት ጎዳና ገብቶ ቦታውን ሁሉ ያጥለቀልቀዋል ፡፡ እንዲሁ በሆዳሙም ዘንድ እንዲህ ይሆናል ፡፡ አስቀድሞ የነበረው ሲጠፋ እርሱ በቀደደው ሌሎች  የሥጋ ፍቃዶች በዝተው ይገባሉ ፡፡
 
 ምድራዊው ነገር ይህን ይመስላል ፤ መቼም ቢሆን የተረጋጋ አይደለም ፡፡ መቼም ቢሆን አንዱ ሌላውን እየተካ የሚፈስ እና የሚቸኩል ነው ፡፡ ነገር ግን የቅምጥልነትን ኑሮ በተመለከተ ጣጣው በከንቱ መባከን ወይም መቻኮል ብቻ አይደለም ፡፡ ሌሎችም እኛን ከመከራ የሚጥሉን ችግሮችም አሉበት ፡፡ ቅምጥልነት ባመጣብን ጣጣ የሰውነት አቅማችን ይዳከማል ፣ እንዲሁም የነፍስ ጠባይዋም ይለወጣል ፡፡ ከባድ ጎርፍ ወንዙን በደለል ወዲያው እንደማይሞላው  ፣ ቀስ በቀስ ግን እንዲሞላው ፣ እንዲሁ ቅምጥልነትና ዋልጌነት እንደ አልማዝ ብርቱ የሆነውን ጤንነታችንን ቀስ በቀስ ውጦ ያጠፋዋል ፡፡
 
 ወደ ሐኪም ዘንድ ሄደህ ብትጠይቅ የበሽታዎች ሁሉ ምንጫቸው አብዝቶ ከመመገብ እንደሚመነጩ ይነግሩሃል ፡፡ ጠግቦ አለመብላትና ለሆድ የማይከብዱ ምግቦችን መመገብ ለጤንነት እናት ነው ፡፡ ስለዚህም የሕክምና ባለሙያዎች የጤንነት እናት ብለው ይጠሩታል ፡፡ እናም ጠግቦ አለመብላት የጤንነት እናት ከሆነ  ፣ አብዝቶ መመገብ ደግሞ የበሽታዎች ሁሉ እናት እንደሆነ በዚህ ይታወቃል፡፡ አብዝቶ መመገብ ሰውነታችንን አዳክሞ በሕክምና ባለሙያ እንኳ ለማይድን በሽታ አጋልጦ ይሰጠናል ፡፡
 
አብዝቶ መመገብ ለሪህ ፣ ለአእምሮ ውስጥ የደም መፍሰስ ፣ ለዐይን የማየት ኃይል መቀነስ ፣ ለእጅ መዛል ፣ ለአካል ልምሾነት  ፣ ለቆዳ መንጣት (ወደ ቢጫነት መቀየር  ፤ በተለምዶ የጉበት በሽታ ለምንለው ምልክት ነው ተብሎ ይታመናል ) ስጉና ድንጉጥ መሆን ፣ ለኃይለኛ ትኩሳት እና ከጠቀስናቸው በላይ ለሆኑ ሌሎች ሕመሞች ያጋልጣል ፡፡ በዚህ የሚመጡትን የጤንነት ጠንቆች በዚች ሰዓት ውስጥ ዘርዝሮ ለመጨረስ ጊዜው አይበቃም ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሕመሞች በተፈጥሮአችን ላይ የሚከሰቱት መጥኖ በመብላት ወይም በጾም አይደለም ፡፡ ነገር ግን ከሆዳምነታችንና ከአልጠግብ ባይነታችን የተነሣ የሚመጡብን ናቸው ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ በነፍሳችን ላይ የሚከሰቱብንን  በሽታዎች ብንመለከት ዋዘኝነት ፣ ስንፍና ፣ ድንዛዜ ፣ የሥጋ ፍትወቶቻችን ማየል፣ እነዚህንና የመሳሰሉ ሕመሞች ነፍሳችንን ያጠቁዋታል ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ምንጫቸው ሳይመጥኑ አብዝቶ መመገብ ነው ፡፡ ከእንዲህ ዐይነት ቅጥ ያጣ አመጋገብ  በኋላ የቅምጥሎች ነፍስ ክፉ አውሬዎች ሥጋዋን ተቀራምተው ከተመገቡዋት አህያ ያልተሻለች ትሆናለች ፡፡ ቅምጥሎችን ስለሚጠብቃቸው  ሕመሞችና ስቃዮች ጨምሬ ልናገርን ? ከብዛታቸው የተነሣ ዘርዝሬ መጨረስ አይቻለኝም ፡፡
 ነገር ግን በአንድ ማጠቃለያ አሳብ ሁሉንም ግልጽ አድርጌ ማስረዳት እፈልጋለሁ ፡፡ እንዲህ ከሚያደርጉ ከቅምጥሎች ማዕድ ማንም ደስ ብሎት አይመገብ ፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው ጾምና መጥኖ መመገብ የደስታና የጤንነት ምንጮች ሲሆኑ ያለቅጥ መመገብ ግን የበሽታና የደስታ ማጣት ሥር እና ምንጭ ናቸውና ፡፡
ሁሉ ነገር ከተሟላልን ፍላጎት የለንም ፡፡ ፍላጎት ከሌለ ደግሞ እንዴት ደስታን ልናገኛት እንችላለን ? ስለዚህም ድሆች ከባለጠጎች ይልቅ የተሻለ ማስተዋልና ጤና ያላቸው ብቻ አይደሉም ፣ ነገር ግን ታላቅ በሆነ ደስታ ውስጥ የሚኖሩ ጭምር ናቸው ፡፡ ይህንን ከተረዳን ከመጠጥና ከቅምጥልነት ሕይወት ፈጥነን እንሽሽ ፣ ከማዕዱ ብቻ አይደለም ፣ ከዚህ ሕይወት ከሚገኙት ፍሬዎች ሁሉ እንሽሽ ፡፡  እነርሱን በመንፈሳዊ ሕይወት በሚገኘው ደስታ ለውጠን በቅድስና እንመላለስ  ፡፡ ነቢዩ “ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ እርሱ የልብህን  መሻት ይሰጥሃል”(መዝ.36፥4)  እንዳለው በጌታ ደስ ይበለን ፡፡ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም በእርሱ በእግዚአብሔር መልካም ስጦታ ደስ ይለን ዘንድ የሰው ልጆችን በሚያፈቅረው በኩል ለእርሱ ለእግዚአብሔር አብ ለመንፈስ ቅዱስም ክብር ይሁን  እስከዘለዓለሙ ፡፡ አሜን !!          
   በነገራችን ላይ የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የፍልስፍና ምሁራን(ተማሪዎች) በዚህ በቅዱስ ዮሐንስ ገለጻ ላይ ምን ይላሉ ? በmkwebsitetechnique@gmail.com ጻፉልን።

በተሰደብክ ጊዜ

ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

ቅዱስ ዳዊት በወታደሮቹ ተከብቦ ብራቂም ወደ ተባለ ስፍራ በመጣ ጊዜ፤ ከእርሱ አስቀድሞ ንጉሥ የነበረው የሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው በታላቅ ቁጣ ወደ እርሱ መጣ፡፡ በንጉሡ ሠራዊትና በዚህ እንግዳ ሰው መካከል ታላቅ ወንዝ ነበረ፡፡

ይህ ሳሚ የተባለ ሰው ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ድንጋይ ይወረውርና ትቢያ ይበትን ነበር፡፡ ይህንን ተቃውሞ በሚያሰማበት ወቅት አንደበቱ አላረፈም ነበር፡፡ ይህ ሳሚ በቤተ ክርስቲያናችን የጸሎት መጻሕፍት ላይ በበርካታ ስፍራዎች በተራጋሚነቱ የሚወሳ ሲሆን በቅኔም ተሳዳቢ ሰውን ወክሎ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሠራዊት ተከብቦ ያለውን ንጉሥ ዳዊትን ከፍ ዝቅ አድርጎ እየተሳደበና እየተራገመ ነበር፡፡ ‹‹ውጣ! አንተ የደም ሰው ምናምንቴ ሂድ! በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ እነሆም አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል!›› እያለ የስድብ ናዳ አወረደበት፡፡

እርግጥ ነው ዳዊት በሳኦል ፈንታ ነግሧል፤ ይሁንና የነገሠው ተራጋሚው ሰው እንደሚለው በጉልበቱና በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ተመርጦ ነው፡፡ በዚያም ላይ ሳኦልን ሊገድል የሚችልበትን አጋጣሚ ‹እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣም› ብሎ አሳለፈው እንጂ በሳኦል ቤት ላይ ደመኛ የሚያሰኝ በደልን አልፈጸመም ነበር፡፡ ከብዙ የሕይወት ውጣ ውረዱ ላይ የገዛ ልጁ አቤሴሎም ባመፀበትና ቀን ጎድሎበት በተከፋበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ስድብና ንቀት ከአንድ ተራ ሰው መቀበል ለንጉሡ ለዳዊት በእርግጥ መራራ ነበር፡፡ ይሁንና ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፤ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው፡፡ ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች›› ብሎ እንደዘመረው ታግሦ ዝም አለ፡፡ (መዝ.88÷22) ስለተሰደበው ስድብም ክፉም በጎም መልስ አልመለሰም፡፡

 

የንጉሣቸው በአንድ ተራ ሰው መሰደብና መንቋሸሽ ያንገበገባቸው ወታደሮቹ ግን ዝም ሊሉ አልቻሉም፡፡ ከወታደሮቹ መካከል የጺሩያ ልጅ አቢሳ በቁጣ ‹‹ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሻገርና ራሱን ልቊረጠው›› ብሎ በቁጭት ጠየቀ፡፡ ይህን የሎሌውን ለጌታው መቅናት ያየው ንጉሥ ዳዊት ይህንን ወታደር እሺ ብሎ አላሰናበተውም ወይም ስለ ተቆርቋሪነቱ አላመሰገነውም፤ ተቆጣው እንጂ፡፡ ‹‹እናንተ የጺሩያ ልጆች፤ ከእናንተ ጋር ምን (ጠብ) አለኝ? እግዚአብሔር “ዳዊትን ስደበው!” ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ፤ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ የሚለው ማን ነው?›› አለ፡፡

 

በቅዱስ መጽሐፍ ስድብ ፈጽሞ የተከለከለ የአንደበት ኃጢአት ነው፡፡ የሚሳደብም ሰው ንስሓ እስካልገባ ድረስ ጽኑዕ ፍርድ እንደሚጠብቀው በግልጥ ተነግሯል፡፡ ታዲያ ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር “ዳዊትን ስደበው!” ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ›› ሲል ምን ማለቱ ነው? ተሳዳቢ ይልካልን? የሚል ጥያቄ መነሣቱ የግድ ነው፡፡ ስድብን የሚቃወምና በተሳዳቢዎች ላይ የሚፈርድ እግዚአብሔር አንድ ሰው ሌላውን እንዲሳደብ ፈልጎ ‹እገሌን ስደበው› ብሎ አይልክም፡፡ በእርግጥም እንዲህ ከሆነ ይህ ሰው ምንም አላጠፋም፤ እንዲያውም የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ ቅዱስ ዳዊት ‹ዳዊትን ስደበው ብሎ እግዚአብሔር አዝዞታል› ሲል ምን ማለቱ ነው?

 

እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ እምነታቸውንም ለመፈተን ሲል በርካታ መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ የተናጋሪዎቹን ነጻ ፈቃድ ሳይነካ እንደገዛ ፈቃዳቸው የሚናገሩትን ኃይለ ቃል በመጠቀም በመልካም ሰዎች ብቻ ሳይሆን፤ በክፉ ሰዎችም ንግግር ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ ንጉሥ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን አታለልሁ ብሎ ‹‹ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ ባገኛችሁትም ጊዜ መጥቼ እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ›› ብሎ ነበር፡፡ ይሁንና እግዚአብሔር ይህንን የሄሮድስ የሸፍጥ ንግግር የሰብአ ሰገልን እምነት ለማጽናት ተጠቅሞበታል፡፡ ምክንያቱም ሰብአ ሰገል ‹ልስገድለት› ማለቱን ሲሰሙ ለካ የሀገሩም ንጉሥ ያምንበታል ብለው እምነታቸው ጸንቶአልና ነው፡፡ የጌራ ልጅ ሳሚንም እግዚአብሔር ሒድ ተሳደብ ብሎ ባይልከውም እንደ ዳዊት ላለ መንፈሳዊ ሰው ግን ራሱን እንዲመረምር የተላከለት  ስጦታ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሳሚን የግልፍተኛነት ደካማ ጎን ተጠቅሞ ባሪያው ዳዊትን ገስጾታል፡፡

 

ንጉሥ ዳዊት በወታደሮች እና በሕዝብ ተከብቦ ያለ ኃያል ንጉሥ ሆኖ ሳለ የዚህን ተራ ሰው ስድብ ታግሦ ከመቀበልም ባሻገር ለሌላ ዓላማ ተጠቀመበት፡፡ ስድቦቹና እርግማኖቹንም እንደፍቱን መድኃኒት የኃጢአት ቍስሉን የሚሽሩ እንዲሆኑለትና ከእግዚአብሔር ምሕረት መቀበያ እንዲሆኑለት ተመኘ፡፡ ‹‹ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል›› ብሎ በተስፋ ተናገረ፡፡

ይህን ደገኛ ንጉሥ ስድብን እንዲታገስ ምክንያት የሆኑት ነገሮችም አሉ፡፡ እርግጥ በሳኦል ቤት ላይ ተሳዳቢው ሳሚ እንዳለው ያለ ግፍ አልፈጸመም ይሁንና ሚስቱን ቀምቶ በግፍ ያስገደለው የኦርዮ ደም በእጁ አለ፡፡ ስለዚህ የሳሚን እርግማን ምክንያታዊ ባይሆንም ‹የደም ሰው› አስብሎ የሚያስጠራ በደል ሠርቶ ያውቃልና ለዚያ በደሉ ሥርየት እንዲሆነው እግዚአብሔር ይህንን ቅጣት እንዲያደርግለት በአኮቴት ተቀበለ፡፡

 

የተራገመውን ሰው ለመግደል ወታደሮቹ በተነሡ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት ማስተዋልና ብስለት በተሞላበት ንግግር ነበር የከለከላቸው፡፡ በሳሚ ስድብና እርግማን ሳይበሳጭ ልጁ አቤሴሎም አሳድዶት እንደወጣ አስቦ፡- ከወገቤ የወጣው ልጄ ነፍሴን ይሻል፤ ይልቁንስ ይህ የብንያም ልጅ እንዴት ነዋ?›› በማለት የአብራኩ ክፋይ ልጁ ሊገድለው ተነሥቶ እያለ የሌላ ሰው ልጅ ሰደበኝ ብሎ ሊቆጣ እንደማይገባው ተናገረ፡፡ ‹‹ተነሣሒት በመሆኗ የምትታወቅ ነፍስ ወዳለችው ወደ ዳዊት ተመልከቱ! እነዚያን ሁሉ መልካም ነገሮች ካደረገ በኋላ ከሀገሩ ከቤቱ ሌላው ቀርቶ ከሕይወቱ እንኳን ስደተኛ ሆኖ እያለ በመከራው ጊዜ የአንድን ተራ ሰው ስድብ ታገሠ፤ መልሶ አለመሳደብ ብቻ ሳይሆን ከወታደሮቹ አንዱ ሊበቀልለት ሲነሣ ከልክሎ “እግዚአብሔር አዝዞታልና ይርገመኝ” አለ፡፡›› በማለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህን የዳዊት ትዕግሥት ያደንቃል፡፡

 

ሰላም በሰፈነበት ወቅት በሚመስልህ በሚያክልህ አቻህ መነቀፍና መሰደብ ያን ያህል አይከብድህ ይሆናል፤ የሀገር መሪ ሆነህ በተራ ሰው በአደባባይ መሰደብ ግን ለመታገስ የሚከብድህ ነው፡፡ በተለይም በዙፋን ላይ ላለ ንጉሥ ከእርሱ ቀድሞ በነገሠው ንጉሥ ዘመዶች በአደባባይ መተቸት እጅግ የሚፈታተን ጉዳይ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ክፉ ቀን በገጠመው፣ የገዛ ልጁ ዐምፆበት በሚንከራተትበትና ሆድ በባሰው ሰዓት እንዲህ ዓይነቱን እርግማን መስማት የሚቋቋመው ጉዳይ አልነበረም፡፡

 

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ንጉሥ ዳዊት ተሳዳቢውን ሳሚን ቢገድለው ኖሮ ለተሳዳቢው የሚያዝንለትም ሆነ በንጉሡ ላይ የሚፈርድበት ሰው አይኖርም ነበር፡፡ ‹እንደተራ ሰው ከፍ ዝቅ ሲያደርገው አቧራ ሲበትንበት ምን ያድርግ፤ ቀድሞ ነገር ንጉሥን በሠራዊቱ ፊት እንዲህ መዳፈር ይገባ ነበር?› እያለ የየራሱን ማስተባበያ ይሰጣል እንጂ ማንም ንጉሡን አይኮንነውም ነበር፡፡ በዚያ ላይ እግዚአብሔር የቀባውን ንጉሥ ተሳደበ የተባለ ሰው ደግሞ ሞት ቢፈረድበት ሁሉም የሚስማማበት ዘመን ነበር፡፡ (1ነገ. 20÷13፤ 2ሳሙ 19÷21)፡፡

 

ንጉሥ ዳዊት ግን ይህንን ሁሉ ትቶ ስድቡን በደስታ ተቀበለ፤ የቀረበበትን ትችት ተገቢ አለመሆኑን ለሌሎች   ለማስረዳት አልሞከረም፡፡ እኔ ሳኦልን ማጥፋት ስችል ዝም አልኩ እንጂ መች አጠቃሁት?፤ የሳኦልን የልጅ ልጅ ሜምፊቦስቴን እንኳን በገበታዬ አቅርቤው አልነበረም? ብሎ ለመናገር አልፈለገም ‹‹እግዚአብሔር አዝዞታልና ይርገመኝ››አለ እንጂ፡፡

ቅዱሳን ስድብን ታግሠዋል

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሲሰድቡን እንመርቃለን ሲያሳድዱን እንታገሣለን ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጕድፍ ሆነናል›› ብሎ እንደተናገረ ስድብን በጸጋ መቀበል የክርስቲያኖች መታወቂያ ነው፡፡ (1ቆሮ. 4÷12) በብዙ ቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ያለአግባብ መሰደብ የተለመደና በደስታ የሚቀበሉት ተግሣጽ ነበር፡፡ ቅዱሳኑ ስድብን በደስታ ይቀበሉ የነበረው ለስድብ የሚያበቃ ጥፋት ስለ ሠሩ አልነበረም፡፡ ያለ ስሙ ስም፣ ያለ ግብሩ ግብር ተሰጥቶት በዕለተ ዓርብ በአደባባይ የተሰደበውና የተተፋበትን አምላካቸውን መድኃኔዓለምን በእምነት እያዩ ‹ከእኔ ትለፍ› ያላትን የመከራ ጽዋዕ በመቅመሳቸው ደስ እየተሰኙ ነበር፡፡ ከሸንጎ ፊት ሲወጡም ጮማ እንደቆረጡ፤ ጠጅ እንደጠጡ ሁሉ ፊታቸው በደስታ በርቶ የወጡት ‹‹ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ›› ነበር፡፡ (ሐዋ 6÷41)

 

በአበው መነኮሳት ታሪክ ስድብና እርግማንን ሳያስተባብሉ በአኮቴት መቀበልን የመረጡ ብዙ ቅዱሳንን እናገኛለን፡፡ በንጽሕናቸው መላእክትን መስለው ይኖሩ የነበሩት ቅዱሳን ከዝሙት ርቀው ሳለ ዘማውያን ሲሏቸው ታግሠዋል፡፡ አባ መቃርዮስ የተባለ አባት ከአንድ ጎልማሳ የጸነሰች ወጣት ከእርሱ ነው የጸነስኩት ብላ በከሰሰችው ጊዜ እኔ አይደለሁም ሳይል ‹‹እየሠራሁ ልርዳ›› ብሎ ተቀብሏል፡፡ እስክትወልድ ድረስ ሰሌን እየሸጠ ሲረዳት ከቆየ በኋላ በምጥዋ ጊዜ ጭንቋ ሲበዛ እውነቱን ተናግራለች፡፡ ቤተሰቦቿ ይቅር በለን ሊሉት በሔዱ ጊዜ በአቱን ለቅቆ ሔዷል፡፡ (ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 27)

 

እንደ አባ መቃርዮስ ያለ ስድብን የታገሠው አባ በጥል እና በጾታ ሴት ሆና ሳለ ሴት መሆኗን ሳያውቁ በሐሰት ድንግል ሴትን አስረግዘሻል ብለው ዕድሜዋን ሙሉ የነቀፏት ቅድስት ዕንባ መሪናም ባልሠሩት መነቀፍን መታገሥ እንደሚገባን የሚያስረዱ እንደ ደመና የከበቡን ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ እውነተኛ ትሑትም ሲሰድቡት የሚታገስ ነው እንጂ ስድብን የሚያስተባብል አይደለም (ማር ይስሐቅ 6)፡፡

ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ !

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና።›› በማለት እንደተናገረ ሲሰድቡት መልሶ መሳደብ የክርስቲያን ተግባር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን ያሰኘን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሲሰድቡት መልሶ    አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤›› እንጂ (1ጴጥ.2÷23 ፣3÷9)፡፡

 

በእውነቱ ክርስቲያኖች እንሰኝ እንጂ ተሰድቦ መታገስ ግን ለብዙዎቻችን የሚዋጥ አይደለም፡፡ ተሰድቦ ዝም ማለት በብዙዎቻችን ትርጓሜ ራስን ማስናቅ፣ ፊት መስጠት፣ ፈሪነት እንጂ ትዕግሥት ተብሎ አይጠራም፡፡ አንዳንድ ዝም ያልንባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም እንኳን በትሕትና ታግሠን አለመሆኑና የዝምታችን ምክንያት ሌላ መሆኑ የመታገሣችንን ደረጃ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ተሰድበን ዝም የምንልባቸው ብዙ ምክንያቶችም አሉ፡-

•    ለተሳዳቢው ቦታ ካለመስጠት ንግግሩን ‹‹እንደ ዘፈን ቆጥሮ›› ‹ያሻውን ይለፍልፍ፣ ምን ያመጣል?› ከሚል ንቀት፤

•    ተሳዳቢው አካል በቀላሉ ልንጋፋው የማንችለው የበላያችን ሆኖ መልስ ብንሰጥ የሚመጣብንን በመፍራት፣

•    በአንደበት መልስ ከመስጠት ይልቅ ሌላ መበቀያ ምቹ መንገድ ለመፈለግ፣

•    በቃል በሚደረግ እሰጥ አገባ የተነሣ በሌሎች ሰዎች ዐይን ትዝብት ውስጥ ላለመውደቅ

በመሳሰሉ ተርታ ምክንያቶች ተሰድበን ልንታገስ እንችላለን፡፡ ይህ ግን ትዕግሥት ሆኖ ዋጋን የሚያሰጥ አይደለም፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ጊዜ ታግሠን ከቆየን በኋላ በአንድ አጋጣሚ ስንጋጭ ታግሠን ያሳለፍናቸውን ስድቦች ሁሉ ካጠራቀምንበት ልባችን አውጥተን ‹‹ታግሼ ነው እንጂ፤ ለእግዚአብሔር ሰጥቼ ነው እንጂ እንዲህ እንዲህ ብለኸኝ/ ብለሽኝ ነበር›› ብለን እናስታውሳቸዋለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት ግን በተግባር ያስተማረን ስድብን መታገስ ብቻ ሳይሆን ይገባኛል ብሎ ማመንንና ከእግዚአብሔር እንደተላከ ተግሣጽ መቀበልን ነው፡፡

 

ውድ ክርስቲያኖች! የጌራ ልጅ ሳሚ ቅዱስ ዳዊትን የሰደበው ስድብ ተገቢ አልነበረም፡፡ እኛን ግን ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚሰድቡንና የማንታገሠው ስድብ አንዳች እውነታንም ያዘለ ነው፡፡ ያለ አንዳች ምክንያትም የሚሰድበን የለም፡፡ ይሁንና ሌላው ቀርቶ ስማችንን የመጥራት ያህል ለእኛ በሚመጥን (በሚገባን) ክፉ ስም ሰዎች ሲጠሩን እንኳን ይበሉኝ ብለን ከመታገስ ይልቅ ለጠብ እንቸኩላለን፡፡ ልሳነ ወርቅ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አንድ ሰው “አንተ አመንዝራ” ብሎ ሲሰድብህ ለምን ትቆጣለህ? በሐሳብህም እንኳን ቢሆን አመንዝረህ አታውቅም? ወይም ደግሞ በክፉ የጎልማስነት ምኞት ዝለህ አታውቅም? ስለዚህ ይህንንም ስድብ ለክፉ ሐሳቦችህ እንደ ቅጣት አድርገህ ልትቆጥረው ይገባሃል፡፡››

 

‹ብልህ ሰው ከስድብ ይማራል› የሚሉት ብሂልም በእርግጥ እዚህ ላይ ሊነገር ይችላል፡፡ ‹ወንበዴ ቀማኛ› ከሚለው ስድብ ጀርባ ‹አትስረቅ› የሚል ምክር አለ፣ ‹ዘማዊ አመንዝራ› ከሚለው ነቀፋ ጀርባ ‹አታመንዝር› የሚለው ተግሣጽ አለና በምን ነቀፈው ነቀፋ መነፅርነት ራሳችንን መመልከት ይገባናል፡፡ ከስድብ ጀርባ ምክርና ተግሣጽ አለ ሲባል ግን ስድቡን ከሚሰማው ሰው አንጻር ነው እንጂ ምክርን ያዘለ ነው እያሉ ሰውን መሳደብ ይገባል ማለት እንዳልሆነ ግልጥ ነው፡፡ ላሳዝነው ብሎ ሥር ገብቶ ቤት መርምሮ ዘር ቆጥሮ መሳደብ በእግዚአብሔር ዘንድ   የሚያስፈርድ ነው፡፡ ‹‹ወዘይፀርፍሂ ላዕለ እኁሁ ፀረፈኬ ላዕለ እግዚአብሔር ልዑል፤ ወንድሙን የሚሰድብ ልዑል እግዚአብሔርን ተሳደበ›› ተብሎ እንደተነገረ ሕንፃን መንቀፍ ሐናፂውን መንቀፍ፣ ሥዕልን መንቀፍ ሠዓሊውን መንቀፍ እንደሆነ ሁሉ፤ ፍጡርን መንቀፍም ፈጣሪን መንቀፍ ነው፡፡ ፈጣሪን መንቀፍ ነው የተባለውም ሰውን የሠራ እግዚአብሔር ስለሆነ አንድም ደግሞ ሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ስለተፈጠረ ነው (ተግሣጽ ቀዳማዊ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡

 

ቅዱስ ዳዊት ‹እግዚአብሔር አዝዞታልና ይርገመኝ!› እንዳለ ሰዎች በክፉ ቃል በተናገሩን ጊዜ ቀንቶብኝ ነው፣ ተመቅኝቶኝ ነው እያሉ ራስን ከመካብ ይልቅ ‹አምላክ በዚህ ሰው አንደበት አድሮ ኃጢአቴን ሊያመለክተኝ ነው› ብሎ በትሕትና ማሰብ ይገባል፡፡ ትሕትና ማለትም ‹‹ራስን መሳደብ ሳይሆን ሌሎች ሲሰድቡን መታገሥ ነው›› ብሏል ቅዱስ ዮሐንስ በተግሣጹ፡፡

 

ተሳዳቢው ሰው የቱንም ያህል ክፉ ቢሆን፣ የምንሰደበው እኛም የቱንም ያህል ንጹሐን ብንሆን መልሶ መሳደብ አይገባም፡፡ ንጉሥ ዳዊት ስለ በደለው በደል ንስሓ የገባ ጻድቅ ቢሆንም፤ የጌራ ልጅ ሳሚም መናገር የማይገባውን የተናገረው ቢሆንም ታግሦታል፡፡ እኛም የሚሰድቡን ሰዎች ምንም ቢከፉ እኛም የቱን ያህል ብንቀደስ ለስድብ አጸፋ መመለስ አይገባንም፡፡ ከላይ ከተነሣንበት ታሪክ አንጻር ሙሉ በሙሉ ሊተረጎም አይገባም እንጂ አሁን ላነሣነው ሐሳብ የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ታሪክ ምሳሌ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ይህ ታላቅ መልአክ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ዲያቢሎስ የድፍረት ቃልን በተናገረው ጊዜ ‹‹እግዚአብሔር ይጣልህ!›› አለው እንጂ የስድብን ቃል ሊናገረው አልደፈረም፡፡ (ዘካ 3÷2፤ ይሁ 1÷9) ከመላእክት ወገን ከቅዱስ ሚካኤል በላይ የከበረ ከዲያብሎስም በላይ የተዋረደ የለም፤ ከነሠራዊቱ ተዋግቶ የጣለውን ውዱቅ መልአክ እንደ ሰው ቢሆን የጥንቱን አንሥቶ ሊያዋርደው ይቻለው ነበር፤ ይሁንና የከበረው ሚካኤል ለተዋረደው ዲያብሎስ እንኳን ክፉ ሊመልስለት አልወደደም፡፡

 

እኛም ምንም ብንከብር የቅዱስ ሚካኤልን ያህል አንከብርም፤ የሚሰድቡን ሰዎችም ምንም ቢከፉ የዲያብሎስን ያህል አይከፉምና ለመሳደብ በመቸኮል ለአንደበታችን አርነት አንስጥ! የሚገባንን ስድብ ስንሰደብ ራሳችንን በስድቡ ውስጥ እንገሥጽ፣ ያለ ጥፋታችን ስንሰደብ ደግሞ ያለ ጥፋቱ የተሰደበ አምላክ ባሪያዎች መሆናችንን እያሰብን ከቅዱስ ዳዊት ጋር ‹‹ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ›› ‹‹የሚሰድቡህ ስድብ በላዬ ወደቀ›› ብለን እናመስግን! (መዝ 88÷9)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡ሐመር ኅዳር 2003 ዓ.ም