ክርስቲያናዊ ሕይወት

መጋቢት 19/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

 • “ለማኅበረ ቅዱሳን አማርኛ መካነ ድር ዝግጅት ክፍል፡፡ መንፈሳዊ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፡፡ እባካችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝን ምክር ለግሱኝ?”

ውብ አንተ


የተከበርክ ወንድማችን ውብ አንተ ክርስቲያናዊ ሕይወትህ እንዲበረታ መንፈሳዊ ምክር ፈልገህ ስለጻፍክልን እናመሰግናለን፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት ይህ ነው ወይም ያ ነው ብሎ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጊዜና ቦታ ይገድበናል፡፡

 

ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝ ምክር እፈልጋለሁ የሚለውን ዐሳብህን ብቻ ነጥሎ ማየት አሁን ያለህበትን የሕይወት ደረጃ ብናውቀው ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም ጥምቀተ ክርስትናን ተቀብለህ በክርስቶስ ክርስቲያን እንደተባልክ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም እንደ ክርስቲያን መኖር ያለብህን ሕይወት ስላልኖርክ በውስጥህ የሚወቅስህ ነገር አለ፡፡ ይህ ወቃሽ ኅሊና በልቡናህ ስለተሳለ እግዚአብሔርን አመስግነው፡፡ እንዲህ ዐይነቱ የሚጸጸት፣ የሚጨነቅ የሚተክዝ ልቡና ያለው ሰው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ያልተለየው ነው፡፡ ሐዋርያው ይህን ሲመሰክር እንዲህ አለ “…መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይናገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና” ሮሜ.8፥26-27

መንፈስ ቅዱስ አካሉ አንድ ሲሆን ጸጋው ብዙ ነው፡፡ ጸጋው የማይመረመር ረቂቅና ምሉዕ  ስለሆነ በጎ ችሎታዎች ሁሉ ከእሱ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሰማዕታትን ለእውነትና ምሥክርነት የሚያዘጋጅ፣ ሐዋርያትን ለስብከት የሚያሰማራ መነኮሳትን በገዳም የሚያጸና ተነሳሕያንን ለንስሐ የሚያነሣሣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ከእኛ ጋር ሲሆን ለጸሎት እንነሣለን ለምጽዋት እጆቻችንን እንዘረጋለን ለምሥጋና አፋችንን እንከፍታለን፡፡ ለአምልኮ ወደ ቅድስናው ቦታ እንገሰግሳለን፡፡

 

ይህ በመሆኑ ኀጢአት ስንሠራ ከቤተ መቅደስ ስንለይ ከቃለ እግዚአብሔር ስንርቅ የምንጨነቀው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሲሆን ብቻ ነው፡፡

 

ክርሰቲያናዊ ሕይወት በጣም ጥልቅና ሰፊ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ክርስቲያናዊ ሕይወት ተመክረን ከምንሰማው ተጽፎልን ከምናነበው ይልቅ በሕይወታችን የምንቀምሰው በሒደት የምንማረው ሕይወት ነው፡፡ ሒደት ደግሞ መውደቅና መነሣት፣ ማዘንና መደሰትን ማልቀስና መሳቅ፣ ማጣትና ማግኘትን ይመለከታል፡፡ ክርስትና ስናገኝ የምንደሰትበት ስናጣ የምናዝንበት ስንወድቅ ተስፋ የምንቆርጥበት ሕይወት አይደለም፡፡ ክርስትና በትናንቱ ጥንካሬያችን የምንኩራራበት የትዝታ ሕይወት ሳይሆን አሁን የምንኖርበት ቤት የምንጓዝበት ጎዳና ነው፡፡

ክርስትና ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 38 የተጻፈውን እንመልከት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ሲያስተምር በርካታ ሰዎች ልባቸው ተነክቷል፡፡ በትምህርቱም ተመስጠው ወደ 3ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች አምነዋል፡፡ እነዚህ ያመኑትን ሰዎች በሕይወታቸው የፈጸሙት በርካታ ቁም ነገር ነበር፡፡

1. የሚያስተምረውን ትምህርት በሚገባ አደመጡት ስለሆነም ልባቸው ተነካ፡፡

አሁንም ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሔድ ቅዱሳት መጻሕፍት ስናነብ መዝሙር ስናዳምጥ በማስተዋል መሆን አለበት፡፡ ሳናቋርጥ ሁል ጊዜ ቃለ እግዚአብሔርን በማስተዋል የምናዳምጥ ከሆነ አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ይከፍታል፡፡ በመቀጠልም ወደ እውነተኛው የሕይወት አቅጣጫ ይመራናል፡፡ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ይመራችኋል” /ዮሐ.16፥13/ ብሎ ሐዋርያው እንደጻፈልን እውነት ወደ ሆነው ክርስቶስ ያደርሰናል፡፡

 

2. ምን እናድርግ? አሉ፡፡

ሰው የሚማረውን ከተረዳው በኋላ ቀጣዩ ጥያቄ ምን ላድርግ? ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሊያሳድድ ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት የሚያደርገው ሥራ እግዚአብሔርን ስላሳዘነው የመውጊያውን ጦር ብትቃወመው ለአንተ ይብስብሃል አለው፡፡ የምቃወምህ አንተ ማን ነህ? ብሎ ጥያቄውን አቀረበ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለው ታዲያ ምን እንዳደርግ ትወዳለህ” ብሎ ተናገረ፡፡ የምታደርገውን በከተማ የምታገኘው ሰው ይነግርሃል ብሎ አምላካችን ፈቃዱን ገለጠለት፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ሕይወቱ ተለውጦ እግዚአብሔርን እያገለገለ ኖረ፡፡ /ሐዋ.9፥1/

 

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ሐዋርያው ፊልጶስን ክርስቲያን እንዳልሆን የሚከለክለኝ ነገር ምንድን ነው?” /ሐዋ.8፥36/ ብሎታል፡፡

 

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባቦች የሚያስረዱት እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ሰዎችን ሲያስተምር ከልባቸው የተነኩ ሰዎች የመጀመሪያው ግብረ መልሳቸው “ምን ላድርግ?” የሚል ነው፡፡

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እነዚህን አዲስ አማንያን “ንስሐ ግቡ ኀጢአታችሁም ይሠረያል” አላቸው፡፡ ስለዚህ ስረየተ ኀጢአትን ለማግኘት ንስሐ መግባት ያስፈልጋል፡፡

 

3. በጸሎት በረቱ

በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ያመኑት ምእመናን ንስሐ ገብተው ከተጠመቁ በኋላ በጸሎት ይተጉ ጀመር፡፡ ያላቸውን ሀብት ሸጠው በአንድነትና በኅብረት በጥሩ ልብ ይተጉ ነበር፡፡ ይላል እነዚህ ሁሉ ሒደቶች ለክርስትና ሕይወታችን ጥሩ የሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡

 

ወደ ክርስትና ሕይወት ለመመለስ እና በዚሁም ለመጽናት የአባቶቻችንን ሕይወት የሚያብራሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይጠቅማል የእግዚአብሔርን ቃል የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው፡፡” /ዕብ.13፥7/ እንዳለው ሐዋርያው የቅዱሳን ሐዋርያትን፣ ሰማእታትን ጻድቃንን ሕይወት ስንመለከት በሃይማኖት እንበረታለን፡፡

 

ጠያቂያችን ውብ አንተ፡፡ ዋናው እና ትልቁ ነገር አንተ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ያለህ የልብ ፍላጎት ነው፡፡ ፍላጎትህ ስሜታዊ ሳይሆን ልባዊ ከሆነ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ያስተምርሃል፡፡ ስለዚህ ሳታቋርጥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ ቅዳሴውን አስቀድስ ቃለ እግዚአብሔርን ተማር መዝሙርን አዳምጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ ሊቃውንት አባቶችን ቅረባቸው ቅዱሳት መካናትን ተሳለም፡፡ የበለጠ ፍቅሩ እያደረብህ ጣእሙ እየገባህ ሕይወቱ እየናፈቀህ ይሔዳል፡፡ ሁሉም የሚሆነው በፈቃደ እግዚአብሔር ስለሆነ በሃይማኖት እንድትጸና አምላክህን በጸሎት ጠይቀው፡፡

 

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔ ተማሩ በነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” /ማቴ.11፥28-30/

 

ወስብሐት ለእግዚብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

መውደቅ አዳማዊ ነው፤ ወድቆ አለመነሣት ግን ዲያብሎሳዊ ነው”

መጋቢት 3/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባየ
“ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ”

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው መተርጉማን፣ ሰባኪያንና የእምነት አርበኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የተመለሱ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተብለው በተጠሩበት የሦርያ ዋና ከተማ በሆነችው በአንጾኪያ ተወልዶ ያደገው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሕይወቱ በአርአያነቱ የሚጠቀስ መንፈሳዊ አባት ነው፡፡

አንደበቱ ርቱዕ፣ እውነተኛ ሰባኪ ምግባሩ የታረመ መና ባሕታዊና የቤተክርስቱያን መሪ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ የዚህ ዓለም የእንግድነት ቆይታውን ጥሎ ከተሰናበተ በኋላ ወደ 5ተኛው መቶ ዓመት ማጠናቀቂያ አካባቢ በትምህርቱ የተደነቁ በጽሑፉ የተማረኩ ከሕይወቱ የተማሩ ምእመናን “አፈወርቅ የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውታል፡፡ “አፈወርቅ” በግሪክኛ Chyrysostomos በእንግሊዝኛው Golden mouth ተብሎ ይጠቀሳል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በ347 ዓ.ም. ተወልዶ በ407 ዓ.ም. ይህቺን ዓለም እስኪሰናበት ድረስ የተሰጠውን የክህነት አገልግሎት የተወጣ የብዙ ብዙ መጻሕፍትን የደረሰ አባት ነው፡፡ በስብከቱና በጽሑፉ የተማረከ አንድ ጸሐፊ “He terrified the comforted and comforted the terrified ዝንጉዎችን ያስደነግጣል የተጨነቁትን ደግሞ ያጽናናል” ብሎ ጽፎለታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ክፍለ ትምህርቶች በርካታ ስብከቶችን ሰብኳል፤ ከእነዚህም ውስጥ “አጋንንት በሰው ሕይወት ላይ ሥልጣን አላቸው” ብለው ለሚናገሩ ሰዎች የሰጠው ትምህርት ይጠቀሳል፡፡ ይህን ስሕተት የሆነ አመለካከት እንዲያስተካክሉ በሦስት ተከታተይ ክፍል ትምህርቱን አቀረበ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በነበረበት ዘመን ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚጠላለፉበት የሞራል ውድቀት የበዛበት፣ ነገሥታቱ በቤተ ክህነት ላይ እጃቸውን እያስገቡ የስልጣናቸው ማራዘሚያ ያደረጉበት እጅግ ፈታኝ ወቅት እንደነበረ በታሪክ መስታወት እንመለከታለን በአሚነ ልቡና እንዘክረዋለን፡፡

አጋንንት በሰው ሕይወት ላይ ሥልጣን አላቸው ማለት ራስን ከተጠያቂነትና ከዘለዓለማዊ ፍርድ ነጻ እንደሚያደርግ ሳይፈራና ሳይታክት አስተማረ፡፡ ከአጋንንት የሚመጣውን ፈተና በፍጹም ተጋድሎ በነጻ ፈቃድ መመከት እንደሚችል፡፡ ሰበከ “ክፋት /ኀጢአት/ የሰው የተፈጥሮ ጠባይ /ባሕርይ/ ገንዘብ” ነው እያሉ የተሳሳተ መረዳት የነበራቸውን ሰዎችን አስተካከላቸው አብሮ የተፈጠረ /የባሕርይ ገንዘብ/ የሆነ ሥራ ሊታረም እንደማይችል እያሳሰበ ኀጢያት በንስሐ በምክር፣ በተግሳጽ፣ በጾም በጸሎት በተጋድሎ ሊወገድ እንደሚችል ያስገነዝባል፡፡ ኀጢአት የሚመጣው ከራስ ድካም ካልቆረጠ ኅሊና ከሰነፈ ልቡና ከላሸቀ ኅሊና ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከራሳቸው ድካም ተነሥተው ኀጢአትን ሠሩ እንጂ ሰይጣን እጃቸውን ጠምዝዞ እጸ በለስን ቆርጦ እንዳልመገባቸው ይታወቃል፡፡

ለኀጢአት በር ካልተከፈተ እንዝህላልነት ከታረቀ በዓቂበ ልቡና ከተተጋ አጋንንት የወደቁና የታሠሩ ጠላቶቻችን እንጂ በእኛ ላይ ምንም ኀይል የላቸውም “ሰይጣን ታስሯል እአስራቱ የሚፈቱት ፈቃዱን የሚፈጽሙ ሰዎች ናቸው” እንደሚበላው ፈቃደ ሥጋን መፈጸም በዓለሙ ብልጭልጭ ነገር መሳብ ያለልክ መብላትና መጠጣት መጠን የሌለው ሥጋዊ ደስታና ከንቱ ቅዥት አጋንትን ኀይል ያስታጥቃል፡፡

ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው ዮሐንስ ተጸጽተው ንስሓ የገቡ አባቶችን ለአብነት በመጥቀስ የእግዚብሔርን መሐሪነት አስተምሯል፡፡ እምቢ ብለው ሕይወታቸውን ከንስሐ ያራቁ ሰዎች ደግሞ በጥፋት ጎዳና መጓዛቸውን ሰበከ፡፡ በመጨረሻም “መውደቅ አዳማዊ ነው ወድቆ አለመነሣት ግን ዲያብሎሳዊ ነው” ብሎ አባታዊ ምክሩን ለገሣቸው፡፡

/ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ 1999፥108/ “መውደቅ አዳማዊ ነው” እንዴት፥?

ከተፈጠርንበት ሰባት ባሕርያት አንዱ አፈር ነው አፈር ሲታጠብ ቢውል እንደማይነኀጻው የሰዎች ጠባይ በተለያዩ ምክንያቶች ሊጎድፍ ይችላል፡፡ ሰው እንደውሎው እንደ አካባቢው እንደ ግንዛቤው ለሚቀርቡለት ጥያቄ የራሱ የሆነ ግብረ መልስ ይኖረዋል፡፡ በቅድስና ሕይወታቸው የሚታወቁ አባቶቻችን በስሕተት መንገድ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ለዚህም ነው አባቶቻችን “ሰው ሆኖ የማይበድል እንጨት ሆኖ የማይጨስ የለም” የሚሉት፡፡

“ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል” /ምሳ.24፥16 ብሎ ጠቢቡ መናገሩም በምድር ላይ ያለን እኛ በሥጋ ፈቃድ ተታለን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በስሕተትም ይሁን በድፍረት ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ዋናው ጥያቄ ለምን ወደቅን? ሳይሆን ለምን አልተነሣንም ነው፡፡

ብዙ ሰዎች ለውድቀታቸው ምክንያት ማቅረብ ይወዳሉ ከተጠያቂነት ለመሸሽ /ለማምለጥ/ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ምክንያት ጠቃሚ ቢሆን ኖሮ አዳም ሔዋንና እባብ ከተፈረደባቸው ፍርድ ባመለጡ ነበር፡፡ ምክንያት ረብ /ጥቅም/ የሌለው በመሆኑ ለበደሌ ለውድቀቄና ለሽንፈቴ ምክንያቱ እኔ ነኝ ማለትን መለማመድ አለብን፡፡

ነቢዩ ዳዊት “አንተን ብቻ በደልሁ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ /መዝ.50፥4/ ብሎ መጸለዩ ተጠያቂነቱን በራሱ አድርጎ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስም የመርከቧ መታወክ የሞገዱ ማየል የነፋሱ ንውጽውጽታ በእኔ ምክንያት የሆነ ነው፡፡ ብሎ ስሕተቱን አምኗል፡፡ ነቢዩ ሙሴ እኔ አንደበቴ ኮልታፋ ነው የፈርዖን አምላክ የእሥራኤል መሪ እንዴት ታደርገኛለህ ብሎ ደካማነቱን አመነ፡፡ ለዚህ ያደረስከኝ እኔ ማን ነኝ ቤቴስ ምንድን ነው? እያሉ መጻተኛነታቸው ያመኑ ጉስቁልናቸውን የተረዱ አባቶች ራሳቸውን በመንፈስ ድኀ አድርገዋል፡፡ ቀራጩም ሲጸልይ “እኔ ኀጢያተኛውን ማረኝ” ብሎ ነበር /ሉቃ.18፥13/

መውደቅ እጅን ለዲያብሎስ መስጠት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር መለየት ነው፤ ከቅዱሳኑ ኅብረት መገለል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመጀመሪያው ሞት ነው፡፡ በመጀመሪያው ትንሣኤ /ትንሣኤ ልቡና/ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ሁለተኛው ሞት /ሞተ ነፍስ/ ይፈረድባቸዋል፡፡ /ራዕ.20፥14/

 

 • አዳም ወደቀ በአምላካችን ቸርነት ተነሣ
 • ነቢዩ ዳዊት ሳተ እግዚአብሔር ይቅር አለው
 • ቅዱስ ጴጥሮስ ካደ መሐሪው አምላክ ይቅር አለው

የአባቱን ሀብትና ንብረት ከፍሎ የኮበለለው ወጣት ወደ ልቡ ሲመለስ አባቱ በይቅርታ ተቀብሎታል፡፡ እኛም መውደቃችን ሳይሆን አለመነሣታችን ሲያሳስበን ይገባል፡፡
መውደቅ /መሳሳት/ አዳማዊ ጠባይ በመሆኑ በመውደቃችን አይፈረድብንም ማንኛውም ሰው ኀጢአትን የመሥራት ዝንባሌ ሊታይበት ይችላልና፡፡ እኛን የሚያስፈርድብን በኀጢአት ላይ አቋም ይዘን በንስሓ አለመነሣታችን ነው፡፡

ዲያብሎስ ስሕተቱን ማመን አልቻለም ስለዚህ ወድቆ ቀረ በበደል ወድቀው በንስሓ ያልተመለሱ ሰዎት የግብር አባታቸውን የዲያብሎስን ፈቃድ ፈጻሚዎች በመሆናቸው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ መውደቅ አዳማዊ ጠባይ ነው ይለናል፡፡

ዲያብሎስን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል እግዚአብሔርን እሺ በሉት ወደ እናንተ ይቀርባል፡፡ /ያዕ.4፥8/ ዲያብሎስን መቃወም ፈቃዱን አለመፈጸም ነው፡፡ ዲያብሎስን መቃወም የምንችለው በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሳይጸልዩ ወደ ዕለት ሥራቸው የሚሔዱትን ሰዎች እንዲህ እያለ ይመክራቸዋል፡፡ “ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተህ እግዚአብሔርን ለአምላክነቱ እንደሚገባ አምልከህ ከዚያ በኋላ ወደ ሥራህ ብትሔድ የምትሠራው ሥራ የተባረከና የሰመረ እንደሚሆንልህ አታውቅምን? የሚያስጨንቅህ የዚህ ዓለም ገዳይ አለብህ? እዚህ በምታሳልፈው ጊዜ የእግዚአብሔርን ርዳታና ምሕረት ታገኝ ዘንድ በመረጋጋትና በመጽናናት መንፈስ ሆነህ ትሔድ ዘንድ ስለዚህ ምክንያት ወደዚህ ና፡፡

እርሱ ኀይልህ ጋሻህ ይሆን ዘንድ በሰማያዊ ሥልጣን በመጠበቅ ለጠላቶችህ ለአጋንንት የማትሸነፍ ትሆን ዘንድ ወደዚህ ወደ ጸጋው ዙፋን ና፡፡ በአባቶች ከሚደርሰው ጸሎት ሲታርፍ ካለህ በማኅበር ጸሎት ከተሳተፍክ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ከሰማህ የእግዚአብሔርን ርዳታ ካገኘህ እነዚህን መሳሪያዎች ከታጠቅህ የትም ብትሔድ እንደአንተ ያሉ ሠሪጋ የለበሱ ጠላቶችህ  ክፉዎች ሰዎች ይቅርና ዲያብሎስ ራሱ ፊትህን ማየት አይችልም ነገር ግን ከቤትህ እንደተነሣህ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳትመጣ ወደ ገበያ ወደ ሥራ ወዘተ ብትሔድ ብቻህን ያለምንም መንፈሳዊ ትጥቅና ጸጋ እግዚአብሔር ስለምትሆን ሁሉም ነገር በአንተ ላይ ይበረታብሀል፡፡ ጠላቶችህም በቀላሉ ያጠቁሃል፡፡ በቤታችን ውስጥም ሆነ በውጭ ብዙ ነገሮች እንደ ጠበቅነው ሳይሆን በተቃራኒው የሚሆኑብን አስቀድመን ለመንፈሳዊ ነገር ቅድሚያ ስላልሰጠንና ሌላውን የዚህ ዓለም ነገር ከዚያ በኋላ ማድረግ ሲገባን እኛ ግን ቅደም ተከተሉን ስለ ስለምናገለባብጥ ነው፡፡ ስለዚህ ነገሮች ዝብርቅርቃቸው ይወጣል” ይለናል፡፡

ዲያብሎስ ሆይ ብወድቅ እነሣለሁና በጨለማ ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ደስ አይበልህ /ሚክ.7፥8/ ማለት የምንችለው በንስሓ ወደ አባታችን ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ ነው፡፡ ኀይልን በሚሰጠን በክርስቶስ ሁሉን ስለምንችል ክፉ ሥራውን እንጂ ዲያብሎስን አንፈራውም፡፡ የሠራዊት አምላክ አቤቱ መልስን ፈትህንም አብራ እኛም እንድናለን” መዝ.79፥7

ለንስሓ ሞት
ለአዘክሮ ኀጢአት
ለቅዱስ ቊርባን የበቃን ያድርገን
“ሁሉ ከእርሱና በእርሱ በእርሱም ነውና ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን አሜን” ሮሜ.11፥36

የገዳማውያኑ ጸሎትና አንድምታው /በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/!!

በገብረእግዚአብሔር ኪደ

የካቲት 3/2004 ዓ.ም

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ሲመጣ ለሁሉም እንደሥራው ያስረክባል” /ማቴ.16፡27/ ብሎ ሲናገር እኔም ንግግሩን ስሰማ የድል አክሊልን ከሚቀዳጁ ቅዱሳን ወገን ስላልሆንኩኝ ተብረከረክኩ፡፡ ይህን ፍርሐቴንና ጭንቀቴን ሌሎች ሰዎችም እንደሚጋሩኝ አስባለሁ፡፡ ይህን ሁሉ በልቡ እያሰበ የማይደነግጥ ማን ነው? የማይንቀጠቀጠውስ ማን ነው? ከነነዌ ሰዎች በላይ ማቅን የማይለብስና አብዝቶ የማይጾምስ ማን ነው? ምክንያቱም ይኸን ሁሉ  የምናደርገው ስለ አንዲት ከተማ መገለባበጥ ተጨንቀን ሳይሆን ዘለዓለማዊውን ቅጣትና ትሉ የማያንቀላፋ እሳቱም የማይጠፋውን ነበልባል ለማለፍ ነው፡፡

በየበረሀውና በየገዳማቱ የሚኖሩት አበው ወእማት ይኸንን ቃል ከሌላው ሰው በበለጠ አኳኋን ስለ ገባቸው እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለሁ፤ አደንቃቸውማለሁ፡፡ ምክንያቱም እራታቸውን ከቀማመሱ በኋላ፣ እንደውም እራታቸውን ሳይሆን ምሳቸውን ከተመገቡ በኋላ (ምክንያቱም አብዝተው የሚጾሙና የሚያዝኑ ስለሆነ እራት የሚባል ነገር አያውቁም በዜማ አምላካቸውን ያመሰግኑና መዝሙር ይዘምራሉ፡፡ እናንተም መዝሙሩን መስማት ከፈለጋችሁ ላስታውሳችሁ እና ደጋግማችሁ ዘምሩት፡፡ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን፣ ሥጋ ለባሽን ሁሉ የምትመግብ ቡሩክ እግዚአብሔር ሆይ! መልካሙ ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን፡፡ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ይገባኻል! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህም የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተመላን አድርገን፡፡”

ይህ ዝማሬ በተለይም የመጨረሻው ስንኝ አንክሮ የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም መብል በባሕርይው የድካምና የመወፈር ስሜትን የሚያመጣ ቢሆንም በመነኰሳቱ ዘንድ ግን በነፍስ ላይ ሲያበራና ነገረ ምጽአትን ሲያሳስብ እንመለከተዋለን፡፡ እነዚህ ሰዎች እስራኤል ሰማያዊው መና ከተመገቡ በኋላ ምን እንዳገኛቸው ተምረዋል፡፡ እንዲህ እንደተባለ፡- “የተወደደውን ጥጋብ አቀናጣው፤ ሰባ፤ ወፈረ፤ ሰፋ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ” /ዘዳ.32፡15/፡፡ ዳግመኛም ሙሴ፡- “በበላህና በጠገብህም ጊዜ… እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ” እንዲል /ዘዳ.6፡11-12/፡፡

እስኤላውያን የተወደደውን ምግብ ከበሉ በኋላ አሳፋሪ ነገርን ለማድረግ ጀመሩ፡፡

እናንተስ ይኼን የመሰለ ነገር በእናንተ ዘንድ እንዳይሆን ትገነዘባላችሁን? ምንም እንኳን ለድንጋይ፣ ወይም ለወርቅ ምስል በግ ወይም ከብት ባትሠዉም የራሳችሁን ነፍስ ስለሠዋችሁ መዳናችሁን እንዴት እንደምታጥዋት እና እንዴት ያለ ቁጣ እንደሚደርስባችሁ ተመልከቱ፡፡ እነዚህን መነኰሳት ስንመለከት ይኼን የመሰለ ውድቀት በእነርሱ እንዳይደርስ በመፍራት ምግባቸውን ከተመገቡ በኋላና በጊዜ ጾማቸው መካከል ሁሉ ስለዚያች አስፈሪ ቀን እና ስለ አስጨናቂው የፍርድ ወንበር ያስባሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ መነኰሳት እንኳን በጾም ሌሊቱን ሁሉ በመሬት ላይ ተኝተው እንቅልፍን በማጣት በንቃትና ማቅን በመልበስ እልፍ ጊዜ እየደጋገሙ ስለዚያች ቀን በማሰብ የሚተጉ ከሆነ የምግብ ክምር በጠረጴዛችን ላይ ከምረን ስንጀምርም ስንጨርስም የማንጸልይ ትሩፋተ ሥጋ ትሩፋተ ነፍስ የሌለን እኛስ ይኼን የምናደርገው መቼ ይሆን?

ስለዚህ ምግበ ሥጋ ብቻ በምግብ ጠረጴዛች እንዳንከምር ይኼን የመሰለ ጣዕመ ዝማሬ እና ትርጕሙን እንናገር፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቅሙን እየተመለከትን በማዕዳችን ዙርያ እንድናመሰግን እና ለሆድ ብቻ ብለን የምናደርገውን ሩጫ በማስወገድ የመላእክትን ሥርዓት ወደ ቤታችን እናስገባ፡፡ ከመብላታችሁ በኋላ መልካም እንዲሆንላችሁ ይኸን ታደርጉ ዘንድ ይገባችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ብያንስ እንኳን ለምነግራችሁ ቃል ፈቃደኞች ስላልሆናችሁ ይኸንን ጣዕመ ዝማሬ አድምጡና ከዛሬ ጀምራችሁ ከማዕዳችሁ በፊትም ይሁን በኋላ ምስጋናን ተለማመዱ፡፡
“ብሩክ እግዚአብሔር ሆይ!” ነው ያሉት፡፡ እነዚህ መነኰሳት የሐዋርያትን ትእዛዝ ሲፈጽሙ እንመለከታቸዋለን፡፡ ሐዋርያት እንዲህ ብለው ነበርና፡- “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” /ቈላ.3፡17/፡፡

ሲቀጥሉ ደግሞ የእግዚአብሔር መግቦት ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለሁል ጊዜ እንደሆነ ሲናገሩ፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን” ነው ያሉት፡፡ ይኼን ትእዛዝ ደግሞ፡- “እግዚአብሔር ምግባችሁን ይሰጣችኋልና አትጨነቁ” ማለት ነው፡፡ እናንተ ከአንድ ንጉሥ ጋር እየኖራችሁ ንጉሡ ምግባችሁን ሁሉ ከግምጃ ቤት እያወጣ የሚሰጣችሁ ከሆነ በጭራሽ ስለምትበሉት ነገር አታስቡም፤ ምግብ እንደሚሰጣችሁ ተስፋችሁን ሁሉ በንጉሡ ላይ ጥላችሁታልና፡፡ እንግዲያስ ከዝናብም በላይ በእናንተ ላይ እነዚህን ነገሮች ሊያዘንም የሚችለውን እግዚአብሔር በበለጠ አኳኋን ተስፋ እያደረጋችሁ ስለ አንዳች ነገር ልትጨናነቁ አይገባችሁም፡፡ አዎ! እነዚህ መነኰሳት ራሳቸውንና በእግራቸው ለሚተኩት ደቀመዛሙርቶቻቸው ያስተምሩ ዘንድ ይኼን መዝሙር ደጋግመው ይዘምራሉ፡፡

ከዚህ በኋላ እነዚህ መነኰሳት ለራሳቸው ብቻ ያመሰግናሉ እንዳይባል፡- “ሥጋ ለባሽንም ሁሉ የምትመግብ” ይላሉ፡፡ ስለዚህ በዓለም ሕዝብ ፈንታ እነርሱ ያመሰግናሉ፤ እንደ ዓለም ሁሉ አባቶች እግዚአብሔርን ይባርካሉ፤ ጽኑ ፍቅረ ቢጽን /የወንድም ፍቅርን/ ይለማመዳሉ፡፡ ወንድሞቻቸውን እግዚአብሔር ስለመገበላቸው ያመሰግናሉ እንጂ አይጠሉም፡፡

እንግዲህ በቀደሙትና በእነዚህ የምስጋናቸው ቃል እንዴት አመስጋኝነትን፣ እንደገለጹና ዓለማዊ ምቾትን እንዳራቁ ተመለከታችሁን? እግዚአብሔር ሥጋ ለባሹን ሁሉ የሚመግብ አምላክ ከሆነ የሚያመሰግኑትን ደግሞ የበለጠ ይመግባቸዋል፤ በዓለም ኑሮ ለተወጠሩት እንኳን የሚመግብ ከሆነ ከዓለማዊ ምኞት ራሳቸውን ላራቁ ደግሞ ይበልጥ ይመግባቸዋል፡፡

ይኼን ግልጽ ያደርግ ዘንድ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ከብዙ ድንቢጦች እናንተ አትበልጡምን?” /ሉቃ.12፡7/፡፡ በዚህም እምነታችንን በሀብትና በምድር ፍሬ እንዳንጥል አስጠንቅቆናል፡፡ ምክንያቱም ምግባችንን የሚሰጡን እነዚህ ሳይሆኑ እግዚአብሔር ነውና /ዘዳ.8፡3፣ ማቴ.4፡4/፡፡…

ተሐራምያኑ ልመናቸውን ይቀጥሉና አምላካቸውን፡- “ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን” ይሉታል፡፡ ይህን ማለታቸውስ ምን ማለት ነው? በዚህ ዓለም ደስታ ይሆን? በፍጹም! ይኸን የለመኑ ቢሆን ኖሮ ራሳቸውን በየፍርኩታው፣ በየገደሉ፣ በየበረኻው ማቅ ለብሰው ባልተመላለሱ ነበር፡፡ ስለዚህ እየለመኑት ያለው ደስታና ሐሴት ከዚህች ዓለም ደስታ ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት የሌለው ይልቁንም የመላእክትን ሐሴት የሆነውና ሰማያዊውን ደስታ ነው፡፡

አጠያየቃቸውን እንኳን ተመልክተን ከሆነ ቀለል ባለ አገላለጽ “ስጠን” ሳይሆን “ሙላልን”፤ “እኛን” ሳይሆን “ልባችንን” ነው የሚሉት፡፡ የልብ ሐሴት ማለት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆኑት ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም የመሳሰሉ ናቸውና /ገላ.5፡22/፡፡

ስለዚህ ኀጢአት ሐዘንን ስለምታመጣ ያለዚህም ደስታ ስለማይገኝ በዚሁ ደስታ አማካኝነት ጽድቅን እየለመኑ ነው ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው፡- “እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጐ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” ይላል /2ቆሮ.9፡8/፡፡ እነዚህ መነኰሳት በዚህች አጭር ምስጋናቸው “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” የሚለውን የወንጌሉን ቃል እንደ ተገበሩትና እነዚህን ሁሉ ለመንፈስ ፍሬ እንዴት እንደ ፈለጓቸው ተመልከቱ፡፡ ምክንያቱም፡- “በጐው ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ ልብ በሉ! “ሥራችንን እንፈጽም ዘንድ፣ በጐ ምግባርን እንሠራ ዘንድ” ብቻ ሳይሆን “ይበዛልን ዘንድ” ነው እያሉ ያሉት፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ዘንድ ትንሽዋን ፈቃድ ሲፈልግብን እነዚህ መነኰሳት ግን ከዚህም በላይ የሆነ መታዘዝን ነው ያሳያት፡፡ ይህ አባባል የመልካም ባሮች እና ራሳቸውን የሚገዙ የጠንቃቃ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡

በመቀጠል ይኸን መልካም ሥራ የሚሠሩት በራሳቸው አቅም እንዳልሆነ እና ደካማነታቸውን ለመግለጽ፡- “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ገር ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን” ይላሉ፡፡ በምስጋና የጀመሩት ልመናቸው በምስጋና ያሳርጉታል፡፡

ከዚህ በኋላ አዲስ ምስጋና የጀመሩ ቢመስሉም ያንኑ ምስጋናቸውን ተከትሎ የሚመጣ ተጨማሪ ሐሳብ ይቀጥላሉ፡፡ ይኼም ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶቹን ሲጀምር፡- “እንደ አባታችንና እንደ አምላካችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፡፡ ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን አሜን” ገላ.4፥5 ብሎ በምስጋና ጀምሮ ተመልሶ ወደ መጀመርያው ሐሳብ እንደሚመለስ የመሰለ ነው፡፡ በሌላ ቦታም ቅዱስ ጳውሎስ ፡- “በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው አሜን” ሲል ቃሉን ፈሞ ሳይሆን እንደገና እንደጀመረ /ሮሜ.1፡25/፡፡

እንግዲያስ እኛም እነዚህን መነኰሳት ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደገና ጀመሩ ብለን የምንወቅሳቸው አይደለንም፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያቱ በምስጋና ጀምረው በምስጋና ጨርሰው ዳግመኛ መልእክታቸውን እንደሚቀጥሉ ሁሉ እነዚህ መነኰሳትም ይኼን በመሰለ መንገድ ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡

ስለዚህ፡- “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እገዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና” ይላሉ፡፡

ምስጋናን ማቅረብ ያለብን ስለ ትልልቅ ጉዳዮቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ጥቃቅኑም ጭምር መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መነኰሳት የተባሕትዎን ኑሮ የሚንቁትን ሁሉ ያሳፍሩ ዘንድ ስለ ጥቃቅኑም ጭምር ያመሰግናሉ፡፡ እነዚህ መነኰሳት መናፍቃን እንደሚያወሩት  ማለትም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ከመጥላት ወይም ጋብቻን ከማንቋሸሽ አንጻር ሳይሆን ቁጥብነትን፣ ራስን መግዛት ይለማመዱ ዘንድ ይኼን ያደርጋሉ፡፡

ምስጋናቸው ደግሞ እግዚአብሔር ከዚህ አስቀድሞ በሰጣቸው ሁሉ የተገደበ ሳይሆን ፡- “በመንፈስ ቅዱስ ሙላን” እያሉ ወደ ሰማያዊ መሻት እንደሚወጡና ያንን ሕይወት እንደሚናፍቁ ልብ በሉ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔር ካልረዳው በስተቀር ማንም ሰው ታላለቅ ሥራዎችን መሥራት አይችልም፤ ቢሠራ እንኳን ታላላቅ መሆን ያለባቸውን ያህል ታላላቅ አይሆኑም፡፡

ስለዚህ፡-“ በጐ ሥራችን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” እንዳሉ ሁሉ አሁንም “በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በቅዱስ መንፈስህ ሙላን” ይላሉ፡፡

እንግዲህ ስለአሁኑ ዓለም ኑሮዋቸው ጸሎት ሳይሆን ምስጋናን ብቻ እንዳቀረቡና ከመንፈስ ቅዱስ ለሚሆነው ነገር ግን ጸሎትም ምስጋናም እንዳቀረቡ ተገነዘባችሁን? ጌታም ያስተማረው ይኼንኑ ነበር፡- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” እንዲል /ማቴ.6፡33/፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ መነኰሳት ዘንድ ያለውን ከፍተኛ መልካምነት ልብ በሉ፡፡ ምክንያቱም ሲጸልዩ፡- “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ እንዲህ ማለታቸውም ነበር፡- “በብዙዎች ዘንድ የሚደርስብን ማንኛውም የሚያሳፍር ነገር አያስጨንቀንም፤ ሰዎች በእኛ ላይ የወደዱትን ሁሉ ቢናገሩ፣ ቢስቁብን፣ ቢታበይቡን ለእኛ ቁብም አይሰጠንም፡፡ የእኛ ጭንቀትና ናፍቆት በፊትህ የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ ብቻ ነው፡፡” በዚሁ ጸሎታቸውም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ደግሞም መንግሥቱን ለሚያወርሳቸው ያዘጋጀውን መልካሙን ሁሉ እና የእሳቱን ባሕር በሚገባ አስቀምጠውታል፡፡

ሲጸልዩም፡- “እንዳንቀጣ” ሳይሆን “በአንተ ፊት የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ” ነው ያሉት፡፡ ይኸውም እኛ ሁላችን ከገሃነም አስፈሪነት ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት መቆምን እንድንፈራ ሲያስተምሩን ነው፡፡

ታድያ እነዚህ መጻተኞች፣ ስደተኞች፣ የበረሀው ከዚያም በላይ ደግሞ የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች የሆኑት እነዚህ መነኰሳት ምን ያህል እንደጠቀሙን ተመለከታችሁን? እኛ በዚህ ምድር ሐሳብ ስንፏቀቅ እነርሱ ግን በተቃራኒው ከዚህ ዓለም ተቃራኒ በመቆም የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች ሆነዋል፡፡

ዝማሬአቸውን ከጨረሱ በኋላ ስለ ኃጢአታቸው በማዘንና በማያቋርጥ የእንባ ጅረት ካለቀሱ በኋላ ለቀጣዩ ቀን ራሳቸውን እንደ አዲስ ይዘጋጁ ዘንድ ትንሽ ዕረፍት ይወስዳሉ፡፡ እንደገና ተነሥተውም ሲያመሰግኑ ደግሞም መዝሙረ ዳዊታቸውን እየደገሙ ሌሊትን ቀን ያደርጉታል፡፡
የሚደንቀው ነገር ደግሞ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ የተፈጥሮ ደካማነታቸውን በትጋት በማሸነፍ ይኼን ራስን የመካድ ኑሮ የሚፈጽሙት ሴት መነኰሳየያትም ናቸው፡፡

እንግዲያስ እኛም ወንዶች ስንሆን የእነዚህን ሴት መነኰሳይያትን ትጋት እየተመለከትን በራሳችን የምናፍር እንሁን፡፡ እንደ ጥላ ከሚያልፉት፣ እንደ ሕልም ከሚረሱትና እንደ ጢስ ከሚተጉት ከዚህኛው ዓለም ጉዳዮች ጋር እንታሠር፡፡ ብዙዎቻችን በዚሁ ድንዛዜ ተይዘን ዕድሜአችን ያልቃልና፡፡

የአብዛኞቻችን የዕድሜአችን የመጀመርያው አጋማሽ በዚሁ ስንፍና የተሞሉ ናቸው፡፡ ወደ ሁለተኛው የዕድሜአችን አጋማሽ ከገባን በኋላም ትንሽ ደስታን አጣጥመን መልሰን በርኩሰት፣ በድካምና በሌሎች የማይረቡ ነገሮችን እንታነቃለን፡፡

ስለዚህ ሌባ የማይሰርቃቸውንና ዘላለማውያን የሆኑትን /የማያልፉትን/ ሀብታት እንዲሁም ማርጀት (ሽምግልና) የሌለበትን ሕይወት ትሹ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡

አንድ ሰው በከተማ ውስጥ ሆኖም እንደ እነዚህ መነኰሳት ራስን መግዛት መለማመድ ይችላል፡፡ አዎ! ሚስት አግብቶ፣ በቤትና በኑሮ ጉዳዮች የተጠመደ ሰው እንኳን መጸለይ፣ መጾምና ስለ ኃጢአቱ ማልቀስ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ከሐዋርያት የተማሩትም ምንም እንኳ በከተማ ቢኖሩ በበረሃ የሚኖሩትን ሰዎች ንጽሕናና ቅድስና ይዘው ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ብዙ ሠራተኞች የነበሯቸውም እንዲሁ አድርገዋል፡፡

ነቢያቱም እንዲሁ ሚስትና ቤት ነበራቸው እንደ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤልና ሊቀ ነቢያት ሙሴ፡፡ እነርሱ ከበጎ ምግባርና ትሩፋት የተነሣ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡

እንግዲያስ እኛም እነዚህን ሁሉ እየመሰልናቸው እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ እናመስግን፤ በጊዜውም ያለጊዜውም በመዝሙር እንቀኝለት፤ ትዕግሥትንና መልካም ምግባርን ሁሉ ገንዘብ እናድርግ፡፡ በገዳማውያኑ የተለመደውን ራስን የመግዛት የሕይወት ልምምድ ወደ ምንኖርበት የከተማ ሕይወት በማምጣት በእግዚአብሔር ፊት የተገባን ሆነን እንገኝ፡፡ ብርሃናችንም በሰው ፊት ይብራ፡፡ ሊመጣ ያለውን በጎ ስጦታ ሁሉ እንውረስ፡፡

ይህንን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ያድለን፡፡ ምስጋና ክብርና ለእርሱ በእርሱ ለአብ ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!

የድርሳንና የገድል ልዩነት ምንድን ነው?

ጥር 30/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

“በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ጊዜ ድርሳንና ገድል ሲባል እሰማለሁ፡፡ እኔም የድርሳንና የገድል ልዩነት ብዙ ጊዜ አይገባኝም፤ እባካችሁ የድርሳንና የገድልን አንድነትና ልዩነት አስረዱኝ”

ገብረ እግዚአብሔር
ከዲላ

ውድ ጠያቂያችን በእርግጥ እርስዎ እንዳሉት ድርሳንና ገድል በቤተ ክርስቲያን የማይነሡበት ጊዜ የለም፡፡ “የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው” ዕብ.13፥7 እንደተባለው በሃይማኖትና በምግባር ለመጠንከር ገድለ ቅዱሳንን የያዙ መጻሕፍትን እናነባለን፤ እንጸልይባቸዋለን፡፡ የቅዱሳን መላእክትንም ጠባቂነት፣ የሊቃውንትን ተግሣጽ ትርጓሜና ምክር የዕለተ ሰንበትን ክብር እና የኢየሱስ ክርስቶስን የቤዛነት ሥራ የሚናገሩ ድርሳናትን ሁል ጊዜ እናነባለን እናደርሳለን፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለው መጽሐፋቸው “ድርሳን” የሚለውን ቃል እንዲህ ብለው ይፈቱታል “ድርሳን በቁሙ “የተደረሰ፣ የተጣፈ፣ ቃለ ነገር፣ ሰፊ ንባብ፣ ረዥም ስብከት፣ ትርጓሜ፣ አፈታት፣ ጉሥዐተ ልብ፣ መዝሙር፣ ምሥጢሩ የሚያጠግብ፣ ቃሉ የተሳካ፣ ጣዕመ ቃሉና ኃይለ ቃሉ ደስ የሚያሰኝ ልብ የሚነካ” ማለት ነው፡፡

ድርሳን ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ተራዳኢነት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ክብርና ጸጋ፣ ስለ ዕለተ ሰንበት ክብርና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚናገሩ /የሚያትቱ/ መጻሕፍት ማለታችን ነው፡፡

እስከ 2000 ዓ.ም በተደረገው ጥናት ወደ 138 የሚሆኑ በድርሳን ስያሜ የሚጠሩ መጻሕፍት እንዳሉ ታውቋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 11ዱ የመላእክት ድርሳናት ሲሆኑ  የ11ዱ መላእክት ስምም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ አፍኒን፣ ቅዱስ ፋኑኤል፣ ቅዱስ ሳቁኤል፣ ቅዱስ ሱርያል፣ ቅዱስ ሱራፌልና ቅዱስ ኪሩቤል ናቸው፡፡

የመላእክትድርሳናት በአብዛኛው ተመሳሳይነት ባሕርይ አላቸው፡፡ የውስጥ ይዞታቸውም በ5 ይከፈላል፡፡ እነሱም መቅድም፣ ድርሳን፣ ተአምራት፣ አርኬና መልክእ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ድርሳን የምንለው የባለ ድርሳኑን መልአክ ግብር በፈጣሪው ዘንድ ያለውን ሞገስ የሠራቸውን ተአምራት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እያጣቀሰ የሚያብራራ ክፍል ነው፡፡ በአጠቃላይ ድርሳንን በ4 መክፈል ይቻላል፡፡

 1. ድርሳነ መላእክት የሚባለው ድርሳነ ሚካኤል ድርሳነ ገብርኤልን የመሳሰሉትን ነው፡፡
 2. ድርሳነ ሰንበት ስለ ዕለተ ሰንበት ክብር የሚያብራራ መጽሐፍ ድርሳነ መስቀል ደግሞ የመስቀሉን ታሪክና አመጣጥ ይተርካል፡፡
 3. ድርሳነ ሊቃውንት ደግሞ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ የእነ ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን የሚባለው ነው፡፡ ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን ዘቅዱስ ቄርሎስንም ያጠቃልላል፡፡
 4. ድርሳነ ማኅየዊና ድርሳነ መድኀኔ ዓለም የመሳሰሉት ድርሳናት የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ የሚያዘክሩ ድርሳናት ናቸው፡፡

 

ገድል፡- “በቁሙ ትግል ፈተና ውጊያ ሰልፍ ድልና አክሊል እስ    ኪገኝ ድረስ የሚደክሙት ድካም የሚሠሩት ሥራ የሚቀበሉት መከራ ማለት ነው” ሲሉ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ፍቺያቸው አስቀምጠውታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ገድል ማለት ጻድቃንና ሰማዕታት በሕይወት ዘመናቸው እያሉ የሠሩትን ሥራ የሚናገር መጽሐፍ እንደሆነ አብራርተዋል /ደስታ ተክለ ወልድ 2036፣ አለቃ ኪዳለ ወልድ ክፍሌ 301/ የገድል መጻሕፍት ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትእዛዘ እግዚአብሔር እንዲከበር ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ ከአላውያን ነገሥታት፣ ከቢጽ ሐሳውያን፣ ከጠላት ዲያብሎስና ከፈቃደ ሥጋ ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያወሱ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሃይማኖታቸው በኑሮአቸው እንዴት እንደተገለጠ የሚያሳዩን የሕይወታቸው መስተዋቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ገድል ስንል የቅዱሳን ታሪክ፣ ተአምራት፣ ቃል ኪዳንና መልእክት የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ይህ እንዲህ ይሆናል ይቻላል ተብሎ የተነገረው ቃል በእውነት የሚኖር በቃልና በሥራም የሚገለጥ እንደሆነ የምናየው በቅዱሳን ገድል ነው፡፡ /ማቴ.10፥37፣ ሉቃ.14፥27፣ 1ቆሮ.11፥26-28/

ገድል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው /2ቆሮ.11፥23-22 ዕብ.11፥32-40/ ራሱ የሐዋርያት ሥራ የምንለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሐዋርያትን ግብር /ሥራ/ ገድልና ዜና የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳንም መጽሐፈ ጦቢት መጽሐፈ አስቴር፣ መጽሐፈ ሶስና፣ የመሳሰሉት በሰዎቹ ኑሮ የተገለጠውን የእምነታቸውን ፍሬ የሚያሳዩ የገድል መጻሕፍት ናቸው፡፡

ገድላት በ3 ይከፍላሉ እነሱም፡-

 1. ገድለ ሰማዕታት፡- ለምሳሌ ገድለ ጊዮርጊስ፣ ገድለ ፋሲለደስ፣ ገድለ ኢየሉጣ
 2. ገድለ ሐዋርያት፡- በአንድነት የተሰበሰቡ የሐዋርያት አገልግሎት ተአምራት መከራ የያዙ መጽሐፍት
 3. ገድለ ጻድቃን፡- ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስና የመሳሰሉትን ነው፡፡

ውድ ጠያቂያችን ምላሹን ለማጠቃለል ድርሳን ሲባል የመላእክትን ግብር በፈጣሪያቸው ዘንድ ያላቸውን ሞገስና የሠሯቸውን ገቢረ ተአምራት እየዘረዘሩ የሚናገሩ፣ ስለ ዕለተ ሰንበትና ቅዱስ መስቀል ክብር የሚያስረዱ ድርሳነ ሰንበትንና የድርሳነ መስቀል፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ ምክርና ተግሣጽ እንዲሁም ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት የመሰከሩበት የሊቃውንት መጻሕፍት፣ በመጨረሻም የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ የሚያስታውሱ እንደእነ ድርሳነ ማኅየዊ ያሉት መጻሕፍት በድርሳን ሥር ይጠቃለላሉ፡፡

ገድል ደግሞ ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ጥበብ የቅዱሳንን መከራ ተጋድሎ፣ ተአምራትና ቃል ኪዳን የያዙ የቤተ ክርስቲያን ሕያውነት የሚገለጥባቸው መጻሕፍትናቸው፡፡ ድርሳናትም ሆኑ ገድላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይጋጩ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ የሚተረጉሙና የሚተነትኑ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሰፋ የለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ሐመረ ተዋሕዶ 1999፥61፣ ሐመር ጥር/የካቲት 2000፥27 አዋልድ መጻሕፍት ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሜጋ ማተሚያ ቤት 1995፣ የኢዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ዛሬና ነገ፣ ብራና ማተሚያ ቤት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ 1995፥16 የሚሉ መጻሕፍትና መጽሔቶችን ቢያነኳቸው መልካም ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በመላእክት ተራዳኢነት በቅዱሳን ጸሎት ሁላችንንም ይጠብቀን፡፡

ራስን የመግዛት ጥበብ


ጥር 29/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ “ፍልስፍና ማለት ጥበብን ማፍቀር ማለት ነው፤ ጥበብ ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህም ፍልስፍና ማለት እግዚአብሔርን ማፍቀር ማለት ነው”ብሎ ያስተምራል፡፡ እኛም በበኩላችን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ሰውም በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል የተፈጠረ ስለሆነ ሰው ፍቅር የሚገዛው ፍጥረት ሆነ እንላለን፡፡ አንድ ጸሐፊ ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲያስተምር፡- “እግዚአብሔር ሰውን ከፍቅር አፈር አበጀው፡፡ ስለዚህም ሰው ፍቅር የሚገዛው ፍጥረት ሆነ፤ ስለዚህም ሰው ፍቅር ሲያጣ እንደ በድን ሬሳ ሲቆጠር በፍቅር ውስጥ ካለ ሕያው ነው፡፡ ሕይወቱም እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔርም ፍቅር ነው፡፡” ስለዚህም ክርስቲያናዊ ፍልስፍና ፍቅርን መሠረት ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ለፍልስፍና ትምህርታችን መንደርደሪያ የሚሆነን ፍቅር የሆነውን ተፈጥሮአችንን በሚገባ ማወቃችንና መረዳታችን ነው፡፡

ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረውን ሰውን ትንሹ ዓለም ይለዋል፡፡ እንዲህም ያለበት ምክንያት ሰማያዊና ምድራዊ ተፈጥሮ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ረቂቅ በሆነችው የነፍስ ተፈጥሮው በኩል ረቂቃን ከሆኑ መናፍስት ጋር አኗኗሩን ሲያደርግ፤ ግዙፍ በሆነችው ሥጋዊ ተፈጥሮው በኩል ደግሞ በምድር ፍጥረታት ላይ ገዢ ሆኖ ጠቅሟቸውም ተጠቅሞባቸውም ይኖራል፡፡ ስለዚህም ነው ሰው በሁለት ዓለማት እኩል የሚኖር ፍጥረት ነው መባሉ፡፡ ወይም ሰው የሁለት አካላት ውሕደት ውጤት ነው፡፡ ነፍስ የራሱዋ የሆነ አካል ያላት ስትሆን በዚህ ተፈጥሮዋ መላእክትን ትመስላቸዋለች፣ እንደ ምግባሩዋ ከቅዱሳን ወይም ከርኩሳን መናፍስት ጋር ኅብረትን ትፈጥራለች፡፡ በነፍስ ሕያው ሆና የምትኖር ሥጋችንም ከዚህ ዓለም ጋር ተመጋግባና ተግባብታ ለመኖር የሚረዳት የራሱዋ የሆነ አካላዊ ተፈጥሮ ያላት ናት፡፡ መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ለመንፈሳዊያንና(በእርሱ ዘንድ ረቂቃን አይደሉም) ለምድራዊያን ፍጥረታት ሕይወትን ሰጥቶ እንደሚያኖራቸው እንዲሁ ነፍስም ለሥጋ ሕይወትን ሰጥታ ታኖራታለች፡፡ በዚህም ተፈጥሮአችን አምላክን እንመስለዋለን፡፡ “ሠዓሊ ቀለማትን አዋሕዶ የራሱን መልክ እንዲሥል እንዲሁ እግዚአብሔር ነፍስና ሥጋን በማዋሐድ የራሱን መልክ በመሳል ሰው አድርጎ ፈጠረው፡፡”(ቅዱስ ኤፍሬም)

 

ነፍስ ከሥጋ ተፈጥሮአዋ ሳትለይ ከመንፈሳዊያን ፍጥረታት ጋር ኅብረትን መፍጠር ይቻላታል፡፡ ሥጋም ከነፍስ ሳትለይ ነፍስ ሕይወት ሆኗት ለራሷ ሕልውና ጠቃሚ የሆኑትን ተግባራት በምድር ላይ ታከናውናለች፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አድርጎ ሰውን ከፈጠረው በኋላ የሕይወት እስትንፋስ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን በአፍንጫው እፍ አለበት፡፡ (አክሲማሮስ ገጽ.156) መንፈስ ቅዱስም ለነፍሳችን እውነተኛ እውቀትን በመግለጥ፤ ነፍስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሥጋዋን እንድትመራት ይረዳታል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንዲህ አድርጎ ፈጠረው፡፡ ስለዚህም ሰው ማለት ሥጋው ለነፍሱ፣ ነፍሱም ለመንፈስ ቅዱስ የሚገዙለት ፍጥረት ማለት ነው፡፡

 

አንድ ሰው ይልቁኑ አንድ ክርስቲያን ይህ ሰብአዊ ተዋቅሮውን ካወቀ እግዚአብሔር እርሱን ለምን ዓላማ እንደፈጠረው ይረዳል፡፡ ስለዚህም ነው የትምህርት መጀመሪያው ራስን ማወቅ ነው ብለው ቅዱሳን አባቶች ማስተማራቸው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም “ማንነትህን የማታውቅ ከሆነ የፈጣሪህን ቃል መስማት እንዴት ይቻልሃል?”ሲል፣ ቅዱስ ባሲልዮስ ዘቂሳርያ ደግሞ “ከትምህርቶች ሁሉ የሚልቀው ትምህርት ራሰን ማወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱን ከአወቀ እግዚአብሔርን ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔርን ከአወቀ ደግሞ እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል” ብሎ ያስተማረው፡፡ ራስን ማወቅ የመንፈሳዊ ሕይወታችን መሠረት ነው፡፡

 

ቅዱሳን አባቶቻችን ራስን የማወቅ ጥበብን በሦስት የእውቀት እርከኖች ከፋፍለው ያስቀምጡታል፡፡ የመጀመሪያው እርከን ማንነትን መረዳት ነው፡፡ ይህ እርከን ተፈጥሮአዊ መዋቅርን የመረዳት እርከን (carnal stage) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ያም ማለት የራስን ተፈጥሮዊ ጠባይ ማወቅ ማለት ነው፡፡ ሰው ራሱን ካወቀ ራሱን ለመግዛትና እንደ ፈጠሪው ፈቃድ ለመመላለስ መሠረት ይጥላል፡፡ ራሳችንን ካወቅን በኋላ የሚቀጥለው የእውቀት እርከን መንፈሳዊያኑንና ምድራዊያኑን የስሜት ሕዋሳቶቻችንን ተጠቅመን አካባቢያችንን መረዳት ነው፡፡ በዚህ እርከን ውስጥ ስንገኝ በዙሪያችን ያሉትን ረቂቃን መናፍስትንና ግዙፋን ፍጥረታትን ወደ መረዳትና ከእነርሱ ጋር ግንኙትን ወደ መጀመር እንመጣለን፡፡ ይህም የለብዎ እርከን(sensual stage) ይባላል፡፡  ሦስተኛውና የመጨረሻው እርከን መንፈሳዊያን ሆነን የምንመላለስበት እርከን ሲሆን መንፈሳዊ እርከን ተብሎ ይታወቃል (spiritual stage)፡፡ ይህ የቅዱሳን መላእክትንና የአጋንንትን ንግግር የምንለይበትና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የምንመላለስበት የእውቀት ወይም የቅድስና እርከን ነው፡፡ ይህን እርከን ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም፡፡ እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን”በማለት ይተነትነዋል፡፡(1ቆሮ.2፡15-16)

 

አንድ ሰው መንፈሳዊ ነው የምንለውም እነዚህ የእውቀት እርከኖችን አልፎ የመንፈስ ቅዱስን መልእክት ማዳመጥና መለየት ወደሚችልበት እርከን ሲሸጋገር ነው፡፡ ይህን ለማስረዳት ቅዱሳን “በክርስቶስ ያመነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ዘመኑ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ነው፤ ነገር ግን በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ፤ እግዚአብሔር ያውቃል ያ ሰው እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ነጥቀው ወሰዱት” (2ቆሮ.12፡2) ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረውን ይጠቀማሉ፡፡ እንደ ቅዱሳኑ አስተምህሮ ሦስቱ ሰማያት የተባሉት ቅዱሱ ያለፈባፋቸውን ሁለቱን የእውቀት እርከኖችንና በስተመጨረሻ የደረሰበትን የእርሱን የእውቀት ከፍታን ነው፡፡ በዚህ የእውቀት እርከን ውስጥ የሚገኝ ቅዱስ በዚህ ምድር ሳለ የትንሣኤን ሕይወት ጣዕም መቅመስ ይጀምራል፡፡ ይህም ማለት  ከአምላክ ጋር፣ ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጋር ለመነጋገር የበቃ ይሆናል፣ የአጋንንትንም ምክርና አሳብ ይለያል፣ በሰው ልቡና የሚመላለሰውን ክፉም ይሁን በጎ አሳብ ማወቅና መረዳት ይችላል፣ መጪውን ያውቃል፡፡ እነኝህን ሁሉ ግን የምናገኘው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ነው፡፡

 

ነፍስ ለሥጋ ብርሃኗ እንደሆነች ለነፍስም ብርሃኗ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ ረቂቁንና መንፈሳዊውን ዓለም መረዳት አይቻለንም፡፡ በዚህም ላይ ጨምረን ነፍሳችንን ከኃጢአት ንጹሕ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ ያለበለዚያ እውር ድንብራቸውን እንደሚመላለሱ ወገኖች እንሆናለን፡፡ ይህን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው” ብሎ ይገልጸዋል፡፡ (ዮሐ.5፥25) ወንድሜ ሆይ በዚህ ቦታ ሙታን ያላቸው ነፍሳቸው የተለየቻቸውንና ወደ መቃብር የወረዱትን ወገኖችን ነውን ? ስለሰማያዊው አኗኗራቸው ፈጽመው የማያቁትን አይደለምን ? ይህ ኃይለ ቃል ምን አልባት ግልጽ ላይሆን ይችላል፤ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን እርሱን ለሚከተል ደቀመዝሙር የተናገረውን እስቲ እናስተውለው፤ “ኢየሱስም፡- ተከተለኝ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው”(ማቴ.8፥22) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ በቁም ሳሉ ሙታን እንደሆኑ አሳወቀው፡፡ የሞተ ሰው በዚህ ዓለም ምን ይፈጸም ምን አንዳች የሚያውቀው እንደሌለ እንዲሁ እነዚህም ወገኖችም ለሰማያዊው ዓለም እንደምውት ናቸውና ስለሰማያዊ አኗኗራቸው የሚያቁት አንዳች ነገር የላቸውም፡፡ ነገር ግን ሕያዋን እንደተባሉት በሁለቱም ዓለማት ታውረው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ሙታን አላቸው እንጂ በሥጋማ መሰሎቻቸውን ሊቀብሩ ተፍ ተፍ እያሉ እኮ ነው!

 

ቅዱሳን “አካሔዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አደረጉ” ሲባልም ምድራዊ አኗኗራቸውን ትተው ከረቂቃኑ ፍጥረታት ጋር ኖሩ ማለት እኮ አይደለም፡፡ ሄኖክ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ ሲባል አኗኗሩን ከምድራዊው አኗኗር ለየ ማለት ሳይሆን ሁለቱንም ዓለማት በአግባቡ ኖረባቸው ሲለን ነው፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ቤተሰብ መሥርቶ ልጆችንም ወልዶ ይኖር ነበር፡፡ በኋላም አምላኩ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወሰደው፡፡ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ የተባለለት ቅዱስ ነው፡፡ በምድራዊ ሕይወቱም በቅድስና ተመላለሰ፡፡ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሕያዋን የተባሉ ቅዱሳን ናቸው (ማቴ.22፥31-32)፡፡ ይህም የሚያሳየው በረቂቁም በግዙፉም ዓለም እኩል ሕያዋን ሆነው ይኖሩ እንደነበር ነው፡፡

 

በእዚህ የእውቀት እርከን ውስጥ ያሉ ቅዱሳን ሕይወት ምን እንደሚመስል ሶርያዊ ቅዱስ ዮሴፍ (ባለራእይው ዮሴፍም ይባላል) እንዲህ ይገልጸዋል፡- “መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሰውነት ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምንረዳው አእምሮአችን ፍጹም ብሩህ በሆነ የማስተዋል ብርሃን ሲሞላ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ በልባችን ጠፈር ላይ የሰንፔር ድንጋይን የመሰለ ሰማይ ተዘርግቶ ከልባችን ጠፈር ልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት ያሉዋቸው ብርሃናት (እውቀቶች) ሲፍለቀለቁ ይታየናል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ማራኪ የሆኑ ብርሃናት በልቡናችን የሚፍለቀለቁት ሥላሴ በልቡናችን ውስጥ የባሕርይ የሆነውን ብርሃን ሲያበራልን ነው፡፡ በሥላሴ ብርሃን እገዛ የሚኖረን እውቀት ፍጥረታዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀውና እንድንረዳው የሚያደርገን ሲሆን ከዚህ አልፈን መንፈሳዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀው ያበቃናል፡፡ በመቀጠልም ስለ እግዚአብሔር ቅን ፍርድና መግቦት ወደ ማወቅ እንመጣለን፡፡

 

በዚህ መልክ ከፍ ከፍ በማለት ከክርስቶስ የክብሩ ብርሃን ተካፋዮች ለመሆን እንበቃለን፡፡ ከዚህ ቅዱስና ግሩም ከሆነው እይታ ስንደርስ እጅግ ውብ አድርጎ በፈጠራቸው ዓለማት በእጅጉ እንደነቃለን፡፡ ከእነርሱ የምናገኘው ማስተዋል እጅግ ታላቅ ነው፡፡ በዚህ ድንቅ በሆነ የእውቀት ከፍታ ውስጥ ስንገኝ ስለ ሁለቱ ዓለማት ያለን እውቀት እንደ ጅረት ውኃ ከአንደበታችን ሞልቶ ይፈሳል፡፡ የሚመጣውን ዓለም በዚህ ዓለም ሳለን ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ እጅግ ውብ የሆነውን የመላእክትን ማስተዋል ገንዘባችን እናደርጋለን፡፡ ደስታቸውን፣ ምስጋናቸውን፣ ክብራቸውን፣ ዝማሬአቸውንና ቅኔአቸውን እንሰማለን፡፡ መላእክትን ከእነ ማእረጋቸውና ከእነ ክብራቸው እንመለከታቸዋለን፣ እርስ በእርሳቸው  ያላቸውንም አንድነት እንረዳለን፣ ቅዱሳን ነፍሳትን ለመመልከት እንበቃለን፣ ገነትን ማየት፣ ከሕይወት ዛፍ መመገብን (መላእክት የሚመግቡትን የፍቅር ማዕድ ማለቱ ነው)፣ ከቅዱሳን ነፍሳትና መላእክት ጋር መነጋገርና ከዚህም ባለፈ ልዩ ልዩ በረከቶችን ለማግኘት የበቃህ እንሆናለን፡፡” ወደዚህ የቅድስና ወይም የእውቀት ከፍታ ለመወጣጣት ግን አስቀድመን እንደጻፍንላችሁ የራስን ማንነትን ማወቅ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

 

ከላይ ነፍሳችን በሁለቱም ዓለማት አኩል ተሳትፎ እንዳላት ተመለክተናል፡፡ ይህች ረቂቅ የሆነች ተፈጥሮአችን ሥራዎቹዋን የምታጠናቅርበት አካል አላት፡፡ ይህን ረቂቅ አካል እኛ አእምሮ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ይህች ነፍስ ሁለት ወገን የሆኑ የስሜት ሕዋሳት ሲኖሩዋት አንደኛው ወገን ረቂቁን ዓለም የምናስተውልበት ሲሆን ሁለተኛው ወገን ግን ግዙፉዋን ዓለም የምንረዳበት ነው፡፡ ነፍስ ረቂቁን ዓለም እና ግዙፉን ዓለም በምትረዳባቸው የስሜት ሕዋሳት በኩል መረጃዎችን ረቂቅ ወደሆነው የአእምሮዋ ክፍል ታስገባለች፡፡ አእምሮም በስሜት ሕዋሳቱ በኩል ያገኛቸውን  ጠቃሚ መረጃዎች ወደ ውስጠኛው የአእምሮ ክፍሉ አስገብቶ ያኖራቸዋል፡፡

 

እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ አእምሮአችን ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ አንደኛው ልዩ ልዩ አሳቦችን የሚያኖርበት ላይኛው የአእምሮአችን ክፍል እንለዋለን፡፡ ሌላኛው ክፍል ደግሞ አእምሮአችን በላይኛው የአእምሮ ክፍላችን ከሚመላለሱት ዐሳቦች ይጠቅሙኛል ያላቸውን ዐሳቦች የሚያኖርበት ክፍል ነው፡፡ አንድ ዐሳብ ወደ ታችኛው የአእምሮ ክፍላችን ከመግባቱ በፊት በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል ረዘም ያሉ ሒደቶችን ያሳልፋል፡፡ እነዚህ ሒደቶች አንድን ሰው ከስህተት ጠብቀው በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ መልካም ሆኖ እንዲመላለስ ይረዱታል፡፡

 

ሰው ሁለት ወገን ከሆኑት የስሜት ሕዋሳቱ ከመንፈሳዊው ዓለምና ከግዙፉ ዓለም መረጃን ወደ ላይኛው የአእምሮአችን ክፍል ያስገባል፡፡ አእምሮም ለሁለቱ አካላት ማለትም ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም መስለው ወደ ታዩት ይሳባል ወይም ይረዳቸው ዘንድ ወደ እነርሱ ያዘነብላል፡፡ ይህ ዝንባሌ አጥብቆ መሻት(passion) ይባላል፡፡ አእምሮአችን በአንድ ነገር በመሳቡ ብቻ ዐሳቡን ወደ ተግባር ይመልሰዋል ማለት ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ልክ በካሜራ ምስልን እንደምናስቀር እንዲሁ ለበለጠ መረዳት የተሳበበትን ነገር ምስል በውስጡ ያስቀረዋል፡፡ ይህ ምስልን በልቡና ውስጥ ማስቀመጥ “ምናብ” (imagination) ተብሎ እንጠራዋለን፡፡ በምናብ መልክ በአእምሮአችን ውስጥ ያስቀመጠውን ዐሳብ አእምሮአችን ደግሞ ደጋግሞ ጠቀሜታውንና ጉዳቱን እንዲሁም እውነተኝነቱን ይመረምራል፤ ያሰላስለዋል፡፡ በዚህም አንድ አቋምን ወደ መያዝ ይመጣል፡፡ ይህ ወደ አንዱ ማድላት አቋም (opinion) ይባላል፡፡ ከዚህም በኋላ አእምሮአችን ዐሳቡ ለሰብእናችን የሚጠቅም ሆኖ ሲያገኘው ሊተገብረው ፍላጎት ያድርበታል፡፡ ይህ ፍላጎቱ ፈቃድ (will) ይባላል፡፡ በመጨረሻም ወደ ትግበራ ይመጣል፡፡

 

አእምሮአችን ወደ ተግባር ሊመልሰው የመረጠውንም ዐሳብ ለአተገባበር  እንዲመች ወደ ውስጠኛው የአእምሮአችን ክፍል ያስገባዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እግዚአብሔር ወደ ተግባር ለማምጣት በፈቀድነው ፈቃዳችን የሚፈርድብን ወይም የሚባርከን፡፡ ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ለእግዚአብሔር የቃል ኪዳኗ ታቦት መቅደስ ለመሥራት አሰበ፡፡ ዐስቦም አልቀረም ወደ ተግባር ለመግባት ነቢዩ ናታንን አማከረው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዳዊት ቤቱን እንዲሠራለት ፈቃዱ አልነበረም፤ ቢሆንም ቅን ስለሆነው ዐሳቡ እግዚአብሔር ባረከው እንዲህም አለው “እግዚአብሔር ቤት እንደምትሠራለት ይነግርሃል፤ እሠራለታለሁ ብለሃልና፡፡ ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አዘጋጃለሁ፡፡ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል ዙፋኑን ለዘለዓለም አጸናለሁ” ብሎ ባረከው፡፡ (2ሳሙ.7፡) ይህ ከእርሱ ወገን ክርስቶስ እንዲወለድ የሚያሳይ ዘለዓለማዊ በረከት ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጁ ሰሎሞን ለዘለዓለም ነግሦ አላየነውምና፡፡ ለዘለዓለም በዳዊት ዙፋን ላይ የነገሠው ከዳዊት ወገን ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ሉቃ.1፡31) ክፉን ዐሳብ ዐስቦ እርሱን ለመተግበር ፈቃዱ ያለው ሰው ምንም እንኳ ድንጊቱን በተግባር አይፈጽመው እንጂ ልክ ድርጊቱን እንደፈጸመው ተደርጎ ይፈረድበታል፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ ሴት ያየ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ አመነዝሮአል” ብሎ አስተማረን፡፡(ማቴ.5፡28)

 

ከላይ የዘረዘርናቸውን ሒደቶች የሚፈጸሙት በኅሊናችን መሣሪያነት ነው፡፡ ኅሊናችን ውስጥ እውነትን ከሐሰት የምንለይበት ሚዛን አለ፡፡ እርሱም እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ በኅሊናችን ያኖረው ሕጉ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “… አሕዛብ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ … ኅሊናቸው ሲመሰክርላቸው ኅሊናቸው እርስ በእርስ ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግን ሥራ ያሳያሉ፡፡”(ሮሜ.2፡15) ብሎናል፡፡ ስለዚህም በሁለቱ ወገን የስሜት ሕዋሳቶቻችን ወደ አእምሮአችን የሚገቡ ዐሳቦች ሁሉ እኛን በደለኞች አያሰኙንም፡፡ ነገር ግን እነርሱን በአእምሮአችን ውስጥ አልምተን ወደ መተግበር ፈቃድ ስንመጣ ፍርዱ የዛን ሰዓት በእኛ ላይ ይፈጸማል፡፡

 

ዲያብሎስ ክፉ ዐሳቦችን ከእኛ የመነጩ አድርጎ በአእምሮአችን ውስጥ ሊዘራብን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ስጋት ሊፈጠርብን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእርሱ የመነጨውን ክፉ ዐሳብ በጽኑ በመቃወም የእግዚአብሔር ወገን ከሆኑት ቅዱሳን መላእክት ጋር ልንወግን ይገባናል፡፡ ይህን ትምህርት የምንቋቸው ባሕታዊው ዮሐንስ የሚባለው ሶርያዊ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የጻፈልንን ድንቅ የሆነ ጽሑፍ በመመልከት ይሆናል ፡፡ እንዲህ ይለናል፡- “በልቡናህ የሚመላለሱትን ዐሳቦችን በጥንቃቄ ተከታተላቸው፡፡ ክፉ ዐሳብ በልቡናህ ዘልቆ ቢገባ አትረበሽ ይህ ዐሳብ ከአእምሮህ የመነጨ እንዳልሆነ ከአእምሮህ በላይ ያለውን የሚውቅ ጌታህ ይረዳዋል፡፡ እርሱ የሚመለከተው ጥልቅ ከሆነው የአእምሮህ ክፍል በመነጨ ክፉ ዐሳብ ደስተኛ የሆንክ እንደሆነ ነው፡፡ የሚጠሉ ክፉ ዐሳቦች በላይኛው የአእምሮህ ክፍል ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡

 

ቢሆንም እግዚአብሔር የሚመረምረው የተጠሉ ክፉ ዐሳቦችን ለይቶ ማስወገድ የሚችለውን ጥልቁን የአእምሮአችንን ክፍል ነው፡፡ በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል በሚመላለሱት በተጠሉ ክፉ ዐሳቦች የተነሣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አይፈርድብንም፡፡ ነገር ግን ከጥልቁ  የአእምሮአችን ክፍል የሚመነጩ የተጠሉ ዐሳቦች ስውር በሆኑ እጆቹ የማስወገድ ችሎታው ካለው  እእምሮ ክፍል የሚመነጩ ከሆኑ ግን ፍርድ ይጠብቀናል፡፡ ከጥልቁ የአእምሮችን ክፍል አመንጭተን ለምናመላልሳቸው ክፉ ዐሳቦች እግዚአብሔር በእኛ ላይ ከመፍረድ አይመለስም፡፡ በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል የሚመላለሰው ዐሳብም ወደ ውስጠኛው የአእምሮአችን ክፍል እንዳይገባ መከላከል ስንችል ወደ ውስጥ እንዲገባ ከፈቅድንለት እግዚአብሔር ፍርዱን ከዚህ የተነሣ ይሰጣል፡፡ እንዳውም ክፉ ዐሳብ በውስጥህ ጎጆውን ቢሠራና ብዙ ቀንም በአእምሮህ ቢሰነብት፣ ከእዛም አልፎ ወደ ውስጠኛው ክፍል ቢገባ፣ ነገር ግን ውስጠኛው የአእምሮው ክፍል ያለማቋረጥ ላለመቀበል የሚሟገተውና ከአንተም ትእዛዝ የማይወጣ ከሆነ፣ አትረበሽ ይህ ክፉ የሆነው አሳብ ተነቅሎ መወገዱ አይቀርም፡፡ በዚህም ከእግዚአበሔር ዘንድ የምትቀበለው አንዳች ፍርድ የለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከጥልቁ አእምሮህ የመነጨው መልካሙ ዐስተሳሰብህ ከእግዚአብሔር አምላክህ ዘንድ ታላቅ ዋጋን ያሰጥሃል፡፡ ክፉ ዐስተሳሰብን የሚቃወም የለመደ አእምሮንም ገንዘብህ ታደርጋለህ፡፡”

 

እንግዲህ እግዚአብሔር አምላክ እንዴት እጹብና ድንቅ አድርጎ እንደፈጠረን እናስተውል፡፡ ነገሮችን በአግባቡ እንድናከናውን እግዚአብሔር በአእምሮአችን ውስጥ ልዩ የሆነ ሥርዐትን ዘርግቶልናል፡፡ በእነዚህም የአእምሮ ሥርዐታት አምላክንና ሰውን ሳንበድል ፍቅርን አንግሠናት በዚህ ዓለም በአግባቡ ያለስህተት መመላለስን በሚመጣው ዓለም ከቅዱሳን ጋር የርስቱ ወራሾች ለመሆን እንበቃለን፡፡ እግዚአብሔር ይህን በመረዳት ወደ ተግባር መልሰነው ለመመላለስ ማስተዋል ያድለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

30

እረኝነት እንደ አፍርሃት ሶርያዊ አስተምህሮ

ታኅሣሥ 24/2004 ዓ.ም

ትርጉም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መግቢያ

አፍርሃት ያዕቆብ ዘንጽቢን እና “የፋርሱ ጠቢብ” በሚሉ ስያሜዎቹ የሚታወቅ አባት ሲሆን በዐራተኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የተነሣ ሶርያዊ ተጠቃሽ  ጸሐፊ ነው፡፡ በእርሱ ዘመን ማኅልየ ማኅልይ ዘሶርያና የቶማስ ሥራ የሚባሉት ሥራዎች እንደሚታወቁ ይታመናል፡፡ ስለአፍራሃት የሕይወት ታሪክ ብዙ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አንዳንድ ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊያን አፍራሃት በአሁኑዋ ኢራቅ ትገኝ በነበረችው ማር ማታያ ተብላ በምትታወቀው ገዳም ሊቀ ጳጳስ እንደነበረ ጽፈው ይገኛሉ፡፡ ይህ ግን ተቀባይነት የለው፡፡ አፍራሃት ሃያ ሦስት ድርሳናትን የጻፈ ሲሆን እነርሱም የተለያዩ ርእሶች ያሉዋቸው ናቸው፡፡ እርሱ ከጻፈባቸው ድርሰቶች መካከል ስለእምነት ፣ ስለፍቅር፣ ስለጾም ፣ ስለጸሎት፣ በዘመኑ ስለነበረው የቃልኪዳን ልጆችና ልጃገረዶች፣ ስለትሕትና ጽፎአል፡፡ አፍርሃት ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር ለሶርያ ሥነ ጽሑፍ ፋና ወጊ የሆነ ጸሐፊ ነው፡፡  እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በእረኝነት ላይ የፃፈውን እንመለከታለን፡፡

እረኞች የሕይወት ምግብን ይሰጡ ዘንድ በመንጋው ላይ የተሾሙ አለቆች ናቸው፡፡ መንጋውን የሚጠብቅና ስለእነርሱ የሚደክም እረኛ እርሱ መንጋውን ለሚያፈቅረውና ራሱን ስለመንጎቹ ለሰጠው መልካም እረኛ እውነተኛ ደቀመዝሙር ነው፡፡ ነገር ግን መንጋውን ከጥፋት የማይመልስ እርሱ ለመንጋው ግድ የሌለው ምንደኛ ነው፡፡

እናንተ እረኞች ሆይ በጥንት ጊዜ የነበሩትን ቅዱሳን እረኞችን ምሰሉአቸው፡፡ ያዕቆብ የላባን በጎች ያሰማራ፣ በትጋትና በድካም ይጠብቅ30 ነበር፡፡ በዚህም ከአምላኩ ዘንድ ዋጋ አግኝቶበታል፡፡ አንድ ወቅት ያዕቆብ ለላባ  “ሃያ ዓመት ሙሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፤ እኔ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፤ በቀንም በሌሊትም የተሰረቀውን ከእጄ ትሻው ነበር፡፡ የቀን ሀሩር የሌሊት ቁር ይበላኝ ነበር ፤ እንቅልፍ ከዐይኔ ጠፋ”(ዘፍ.፴፩፥፴፰-፴፱)ብሎት ነበር፡፡  እናንተ እረኞች ይህን እረኛ ለመንጎቹ ምን ያህል እንዲጠነቀቅ  አስተዋላችሁን? በሌሊት እንኳ እነርሱን ለመጠበቅ በትጋት ያለእንቅልፍ የሚተጋ እነርሱንም ለመመገብ በቀን  የሚደክም  እውነተኛ እረኛ ነበር፡፡

ዮሴፍና የእርሱ ወንድሞች ሁሉ እረኞች ነበሩ፤ ሙሴ የበጎች እረኛ ነበር፤ ዳዊትም እንዲሁ እረኛ ነበር፡፡ አሞጽም ላሞችን ያግድ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ መንጎቻቸውን በመለመለመ መስክ ማሰማራት የሚያውቁ እረኞች ናቸው፡፡ ወዳጄ ሆይ  እግዚአብሔር እነዚህን እረኞች አስቀድመው በጎችን በኋላም ሰዎችን እንዲጠብቁ ስለምን እንዳደረጋቸው ተረዳህን? መልሱ ግልጽ ነው፤ መንጎቻቸውን እንዴት መጠበቅና ስለእነርሱ ሲሉ ምን ያህል መድከም እንዳለባቸው ሊያስተምራቸው በመፈልጉ ነበር፡፡ ይህንን የእረኝነት ሓላፊነት ከተማሩ በኋላ ለእረኝነት ተቀቡ፡፡ ያዕቆብ የላባን በጎች በብዙ ድካምና ትጋት ጠበቀ፤ በለመለመ መስክም አሰማራ፡፡ ከዛም ልጆቹን በአግባቡ ወደ መምራት ተመለሰ፣ የእረኝነት ሙያንም ለልጆቹ አስተማረ፡፡ ዮሴፍ በጎችን ከወንድሞቹ ጋር በመሆን  ይጠብቅ ነበር፡፡ ስለዚህም በግብጽ እጅግ ብዙ ሕዝብን ይመራና ልክ እንደ መልካም እረኛ ያሰማራ ዘንድ ተሾመ፡፡ ሙሴ የአማቱን በጎች ይጠብቅ ነበር፡፡

 

በመቀጠል ወገኖቹን ይመራ ዘንድ ተመረጠ፡፡ እርሱም እንደ መልካም እረኛ ሕዝቡን በለመለመ መስክ አሰማራ፡፡ ሕዝቡ የጥጃ ምስልን ሠርቶ እግዚአብሔር አምላክን በማሳዘናቸው ምክንያት ሊያጠፋቸው ቆርጦ ሳለ ሙሴ ስለሕዝቦቹ ተገብቶ እግዚአብሔር አምላክ ይቅር እንዲላቸው ዘንድ “አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ እኔን ደምስሰኝ” (ዘጸአ.፴፪፥፴፪) ብሎ ጸለየ፣ እግዚአብሔር አምላኩን ተለማመነው፡፡ በመንጎቹ ፈንታ ነፍሱን የሚሰጥ እርሱ እጅግ መልካም እረኛ ነው፡፡ ስለሚመራው ሕዝብ ነፍሱን የሚሰጥ እርሱ ትክከለኛ መሪ ነው፡፡ እርሱ ስለመንጎቹ ደጀን ሆኖ የሚጠብቅና የሚመግብ ርኅሩኅ አባት ሊስኝ የሚገባው፡፡ መንጋውን እንዴት ማሰማራት እንደሚችል የሚያውቀው አስተዋዩ እረኛ ሙሴ እጁን ጭኖ መንፈሱን ላሳደረበት ለመንፈስ ልጁ ለኢያሱ ወለደ ነዌ፣ የእግዚአብሔርን መንጋ እንዲያሰማራ የእስራኤልንም ሠራዊት እንዲመራ የእረኝትን ሙያ አስተምሮት ነበር፡፡ እርሱ ጠላቶቹን ሁሉ ድል በመንሳትና ሀገራቸውንም በመውረስ፣ የመሰማሪያ መስክ በመስጠትና ምድሪቱንም ያርፉባትና ለበጎቻቸውም ማሰማሪያ ያገኙ ዘንድ አድርጎ አካፈላቸው፡፡

 

እንዲሁ ንጉሥ ዳዊት የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር፡፡ ከዚህም ነው ሕዝቡን ይመራ ዘንድ የተቀባው፡፡ እርሱ ከልቡ ሕዝቡን ወደ አንድነት መራ፤ በእጁም ጥበብ መንጋውን አሰማራ፡፡ ዳዊት መንጎቹን ወደ መቁጠር በመጣ ጊዜ በእነርሱ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ነደደ፤ ሕዝቡም እግዘአብሔር ባመጣው ቸነፈር ምክንያት ማለቅ ጀመረ፡፡ ዳዊት ግን በመንጎቹ ምትክ እርሱና ቤቱ ላይ ቅጣቱ እንዲፈጸም ጠየቀ፡፡ በጸሎቱ ስለእነርሱም “ጌታ ሆይ እኔ በድያለሁ፤ ጠማማም ሥራ አድርጌአለሁ፤ እነዚህ በጎች ግን እነርሱ ምን አደረጉ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ አንድትሆን እለምንሃለሁ፡፡”(፪ሳሙ.፳፬፥፲፯)ብሎ እግዚአብሔር አምላክን አጥብቆ ተማጸነ፡፡ ነገር ግን ስለመንጎቻቸው ግድ ስለሌላቸው እረኞች፣ ለእነዚያ እራሳቸውን ብቻ ስለሚያሰማሩ እረኞች ነቢዩ እንዲህ ይወቅሳቸዋል “መንጎቼን የምታጠፉና የምትበትኑ እናንተ እረኞች ሆይ የጌታን ቃል ስሙ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል፡፡ እረኛ መንጎቹን እንዲጎበኝ አንዲሁ እረኞችን የምጎበኝበት ጊዜ ይመጣልና ወዮላችሁ፡፡  በዚያን ጊዜ በጎቼን ከእጃችሁ እፈልጋቸዋለሁ፡፡

 

እናንተ ሰነፍ እረኞች ሆይ ከበጎቼ ፀጉር ለበሳችሁ፡፡ ከሰባውም ተመገባችሁ በጎቼን ግን አላሰማራችሁም፣ የታመመውን አላዳናችሁም፣ የተሰበረውን አልጠገናችሁም፣ የደከመውን አላበረታችሁም የጠፋውንና የባዘነውን አልፈለጋችሁም፣ ብርቱውንና የሰባውን አሰማራችሁ ነገር ግን እነርሱን በግፍ አጠፋችኋቸው፡፡ እናንተ የሰባውን ገፋችሁ በላችሁ፣ ከእግራችሁ ሥር ያለውን ረገጣችሁ፡፡ እናንተ ከጥሩ ውኃ ትጠጣላችሁ ከእናንተ የተረፈውን ውኃ ግን በእግራችሁ ታደፈርሳላችሁ፡፡ የእኔ በጎች እናንተ ባጠፋችሁት መስክ ታሰማሯቸዋላችሁ፡፡ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትንም ውኃ ታጠጧቸኋላችሁ” ይላል፡፡ (ዘካ. ፲፩፥፲፭-፲፯)  እነዚህ እረኞች ስስት የሠለጠነባቸው፣ የማያስተውሉ እረኞች እና ባለሙያተኞች ናቸው፡፡ እነዚህ መንጎቻቸውን አይመግቡም ወይም አይጠብቁም ወይም ለተኩሎች አሳልፈው የሚሰጡ ጨካኝ እረኞች ናችው፡፡ ነገር ግን የእረኞች አለቃ ይመጣል፤ መንጎቹንም በየስማቸው ይጠራል፤ ይጎበኛቸዋል፤ ስለመንጎቹም ደኅንነት ይመረምራል፡፡ የበጎቹንም እረኞች ከፊቱ ያቆማቸዋል፤ እንደ በደላቸውም መጠን ይከፍላቸዋል፤ እንደሥራቸውም መጠን ይመልስባቸዋል፡፡

መንጎቻቸውን በመልካም ላሰማሩ እረኞች ግን የእረኞች አለቃ ደስ ያሰኛቸዋል፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትንና ዕረፍትን ይሰጣቸዋል፡፡ አንተ የማታስተውል ሰነፍ እረኛ ሆይ ሰለመተላለፍህ ቀኝ ክንድህንና ቀኝ ዐይንህን ታጠፋታለህ፡፡ ምክንያቱም ስለበጎቼ የሚሞተው ይሙት፤ የሚጠፋውም ይጥፋ ቅሬታም ካለው ሥጋውን እቀራመተዋለሁ የምትል ሆነሃልና፡፡ ስለዚህም ቀኝ ዐይንህን አጠፋዋለሁ ቀኝ እጅህንም ልምሾ አደርገዋለሁ፡፡ መማለጃን የሚጠብቁትን ዐይኖችህ ይጠፋሉ፤ በጽድቅ የማይፍርደውም እጆችህም የማይጠቅሙ ልሙሾዎች ይሆናሉ፡፡  ብታስተውለው እንደ አንተ በመስኩ ላይ የተሰማሩት በጎቼ የሰዎች ልጆች ናቸው፡፡ እኔ ግን ያንተ ጌታ የሆነኩ አምላክህ ነኝ፡፡ እነሆ በዛ ጊዜ መንጎቼን በለመለመ መስክ በመልካም አሰማራቸዋለሁ፡፡ “መልካም እረኞ ነፍሱን ስለበጎቼ አሳልፎ ይሰጣል፡፡” እንዲሁም “ወደዚህ የማመጣቸው ሌሎች በጎች አሉኝ፡፡ እናም አንድ መንጋ ይሆናሉ፡፡” አንድም እረኛ ይኖራቸዋል፡፡ አባቴ ስለሚያፈቅረኝ ስለበጎቼ ራሴን አሳልፌ እሰጣለሁ፡፡” እንዲሁም “እኔ በር ነኝ ሁሉም በእኔ በርነት ይገባል በእኔም ምክንያት በሕይወት ይኖራል ፡፡ እናም ይወጣል ይገባል ይወጣል ይላል ጌታ፡፡…”

Sebe

ሕንፃ ሰብእ ወይስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይቀድማል?

ታኅሣሥ 16/2004 ዓ.ም

ትርጉም፡- በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

Sebe

“የጌታን ቤት በወርቅ ወይም በብር ባለማስጌጣቸው ከጌታ ዘንድ በሰዎች ላይ የሚመጣ አንዳች ቅጣት የለም”


ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴ.14፥23 ያለውን ንባብ በተረጎመበት ድርሳኑ ከሰው የሚቀርብላቸው ከንቱ ውዳሴን ሽተው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስጌጡ የሚታዩ ነገር ግን እንደ አልዓዛር ከደጃቸው የወደቀውን ተርቦና ታርዞ አልባሽና አጉራሽ ሽቶ ያለውን ደሃ ገላምጠው የሚያልፉትን ሰዎች ይገሥፃል፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን አንዳንድ ባለጠጎች ደሃ ወገናቸውን ዘንግተው ከእግዚአብሔር ዋጋ የሚያገኙ መስሎአቸው ቤተ ክርስቲያንን የወርቅና የብር ማከማቻና መመስገኛቸው አድርገዋት ነበር፡፡ ይህ ጥፋት በአሁኑ ጊዜ መልኩን ቀይሮ በሕንፃ ኮሚቴ ሰበብ ምዕመኑን ዘርፎ የራሳን ሀብት ማከማቸት በአደባባይ የሚሰማና የሚታይ ምሥጢር  እየሆነ ነው፡፡ እነዚህን በዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን ከተነሡት ጋር ስናነጻጽራቸው እነዚያ ከእነዚህ በጣም ተሸለው እናገኛቸዋል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እነዚያን እንዴት ብሎ እንደሚወቅሳቸው እንመልከትና በዚህ ዘመን የሚፈጸመው ዐይን ያወጣ ዘረፋ ምን ያህል አስከፊ ቅጣትን ሊያመጣ እንደሚችል እናስተውለው፡፡

… ሰው ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕፃናትንንና ረዳት ያጡ ባልቴቶችን ከልብስ አራቁቶ በወርቅ የተለበጠ ጽዋ ለቤተ ክርስቲያን በማበርከቱ ብቻ የሚድን እንዳይመስለው ይጠንቀቅ፡፡ የጌታን ማዕድ ማክበር ከፈለግህ ስለእርሷ የተሠዋላትን ነፍስህን ከወርቅ ይልቅ ንጹሕ በማድረግ በእርሱ ፊት መባዕ አድርገህ አቅርባት፡፡ ነፍስህ በኃጢአት ረክሳና ጎስቁላ አንተ ለእርሱ የወርቅ ጽዋ በማግባትህ አንዳች የምታገኘው በረከት ያለ አይምሰልህ፡፡ ስለዚህም በወርቅ የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳትን መስጠት የእኛ ተቀዳሚ ተግባር አይሁን፡፡ ነገር ግን የምናደርገውን ሁሉ በቅንነት እናድርግ እንዲህ ከሆነ ከእግዚአብሔር የምናገኘው ዋጋ ታላቅ ይሆንልናል፡፡ ሥራችንን በቅንነት መሥራታችን ከወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረ ዋጋ አለው፤ እንዲህ በማድረጋችንም ከቅጣት እናመልጣለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን የወርቅና የብር ማምረቻ /ፋብሪካ/ ወይም ማከማቻ አይደለችም፡፡ ነገር ግን የመላእክት ጉባኤ እንጂ፡፡ ስለዚህም የነፍሳችንን ቅድስና እንያዝ አምላካችንም ከእኛ የሚፈልገው ይኼንኑ ነው፡፡ ስጦታችን ከነፍሳችን ይልቅ አይከብርም፡፡

 

 

ጌታችን ከሐዋርያት ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ ሥጋውን በብር ዳሕል ደሙንም በወርቅ ጽዋ አድርጎ አልነበረም ያቀረበላቸው፡፡ ነገር ግን በማዕዱ የነበሩት ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ እጅግ የከበሩና ማዕዱም ታላቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ማዕዱ ሲቀርብ ሐዋርያት በመንፈስ ነበሩና፡፡ ለጌታችን ቅዱስ ሥጋና ደም ተገቢውን ክብር መስጠት ትሻለህን? አስቀድመህ ደሃ ወገንህን አስበው፥ መግበው፥ አልብሰው፥ የሚገባውን ሁሉ አድርግለት፡፡ እንዲህ ስል ቅዱስ ሥጋውን አታክብረው ማለቴ አለመሆኑን ልትረዳኝ ይገባሃል፡፡ አንተ በዚህ ማዕድ ቅዱስ ሥጋውን በሐር ጨርቅ በመክደንህ ያከበርከው ይመስልሃል፡፡ ነገር ግን ይህን አካል /ቅዱስ ሥጋውን/ በሌላ መንገድ አራቁተኸዋል፤ ለብርድም አጋልጠኸዋል፡፡ጌታችን ኅብስቱን አንሥቶ “ይህ ሥጋዬ ነው” ሲለን “ስራብ አላበላችሁኝም ስጠማ አላጠጣችሁኝም” ያለው አካሉን አይደለምን? ስለዚህም ጌታችን “እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁ ለእኔም አላደረጋችሁትም” በማለትም ጨምሮ አስተማረን፡፡

ድሆች ወገኖቻችን ለመኖር የሚያስችላቸውን መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ሁሉ ልናደርግላቸው ይገባናል፡፡ ይህን ማድረግ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ግዴታችን ነው፡፡ በዚህ መልክ ክርስቶስ ኢየሱስ ከእኛ እንደሚሻው በመሆን ሕይወታችንን ቅዱስ በማድረግ ወደ ማዕዱ እንቅረብ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩን ሊያጥበው በቀረበ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “እግሬን በአንተ ልታጠብ አይገባኝም” በማለት ተከላክሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ የእርሱ መከላከል ከአክብሮት ይልቅ ታላቅ በረከትን ሊያሳጣው የሚችል መከላከል እንደሆነ አልተረዳም ነበር፡፡ ቢሆንም ከጌታ ዘንድ “ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” የሚለውን ቃል ሲሰማ እርሱ ያሰበው ነገር ተገቢ እንዳልነበረ ተረዳ፡፡ እንዲሁ እኛም እንደታዘዝነው ለድሆች ወገኖቻችን ቸርነትን እናድርግ፤ እርሱን ማክበራችንም የሚረጋገጠው በፍቅረ ቢጽ እንጂ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን በማስጌጥ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በወርቅ ሳይሆን ከወርቅ ይልቅ ንጽሕት በሆነች ነፍስ ደስ ይሰኛልና፡፡ እንዲህ ስል ግን ስጦታዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳታምጡ ማለቴ እንዳልሆነ ልትረዱኝ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ከስጦታዎቻችሁ በፊት ትእዛዙን መፈጸም ይቀድማል፡፡

በእርግጥ በተሰበረ ልብ ሆናችሁ ስጦታዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ብታመጡ እርሱ አይባርካችሁም እያልኩ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ድሆችን ከረዳችሁ በኋላ ስጦታን ለእርሱ ብታቀርቡ ታላቅ ዋጋን ታገኛለችሁ፡፡  በዚያኛው ስጦታ አቅራቢው ብቻ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህኛው ግን ቸርነትን የተደረገለት ወገንም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አንድም የወርቅና የብር ዕቃን ስጦታዎች ማድረጋችን ከሰዎች ምስጋናን ለማግኘት ብለን የፈጸምነው ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥም ደሃ ወገንህ ተርቦና ተጠምቶ እንዲሁም ታርዞ አንተ እንዲህ ማድረግህ ከዚህ ውጪ ሌላ ምክንያት የለውም፡፡ ደሃው ወገንህ በርሃብ እየማቀቀ አንተ የጌታን የማዕድ ጠረጴዛ በወርቅና በብር እቃዎች ብትሞላው ምንድን ነው ጥቅምህ? ነገር ግን አስቀድመህ ደሃውን አብላው አጠጣው እንዲሁም አልብሰው፡፡ በመቀጠል የጌታን ማዕድ (መንበሩን) በፈለግኸው መልክ በወርቅም ይሁን በብር አስጊጠው፡፡

ለድሃ ወገንህ ለጥሙ ጠብታ ታክል ቀዝቃዛ ውኃ እንኳ ሳትሰጠው የወርቅ ጽዋን ስጦታ አድርገህ ለእግዚአብሔር ታመጣለታለህን? እንዲህ ማድረግህ ጌታን ያስደስተዋልን? አካሉን የሚሸፍንበትን እራፊ ጨርቅ ለደሃ ወገንህ ነፍገኸው፣ መንበሩን በወርቅ ግምጃ ጨርቅ በማስጌጥህ ከጌታ ዘንድ የረባ ዋጋ አገኛለሁ ብለህ ታስባለህን? እንዲህ በማድረግ ጌታ አምላክህን በስጦታህ ልትሸነግለው ትፈልጋለህን? በዚህስ ድርጊትህ በአንተ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ አይነድምን? ወገንህ አካሉን የሚሸፍንበት እራፊ ጨርቅ አጥቶ በብርድ እየተጠበሰና በመንገድ ዳር ወድቆ የወገን ያለህ እያለ አንተ የቤተ ክርስቲያን ዐምዶች በወርቅ በመለበጥህ ጌታ በአንተ ደስ የሚለው ይመስልሃልን? ይህል ከባድ ኃጢአት አይደለምን?… ኦ እግዚኦ አድኅነነ እም ዘከመ ዝ ምግባር አኩይ!!

kidase

የምእመናን መሰባሰብ፤ የቅዳሴ ቀዳሚ ምስጢር

ታኅሣሥ 13/2004 ዓ.ም

በዲ/ን በረከት አዝመራው

ቅዳሴ የአንዲቷ ሰማያዊት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ገጽ እንደሆነ ሁሉ የምእመናን መሰባሰብ ደግሞ የቅዳሴ የመጀመሪያ መሠረት ነው፡፡ kidaseበመሰባሰብ የፈጸመው የቅዳሴ ሥርዓታችን አስቀድሞም በቅዱሳን መላእክት ዓለም የነበረና በምድር ባለች መቅደሱም በምእመናን መሰባሰብ የሚፈጸም ነው፡፡ “እኔ በመካከላቸው እሆናለሁ” ብሎ ደስ የሚያሰኝ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን የገባልን ጌታችን፣ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት” በማለት መሰባሰባችን ጸጋና ረድኤቱን እንድናገኝ ምክንያት መሆኑን ነግሮናል /ማቴ.18፥20/ በዚህ ርዕስም የጌታን ቃል በታላቅ ትጋት በፈጸመች ሰማያዊ ሥርዓቷን ከቅዱሳን መላእክት ዓለም ያገኘች፣ የምስጋና ሥርዓቷም በትውፊት ደርሶ ለቤተ ክርስቲየን መሠረት በሆነው በጠንታዊት /በሐዋርያት ዘመን/ ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን መሰባሰብ ይሰጥ የነበረውን ትኩረትና ምስጢራዊ እይታ እንመለከታለን፡፡

 

የምእመናን መሰባሰብ በቅዳሴ ጥንታዊ ትውፊት

ተሰባስቦ እግዚአብሔርን ማመስገን መሥዋዕትን ማቅረብ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳንም በምሳለ የቆየ ቢሆንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት ጋር በቤተ አልዓዛር የአይሁድን ፋሲካ ሲያከብር የአማናዊው ቅዳሴ መሠረት ተጣለ /ሉቃ.22፥7/፡፡ የቤተ እስራኤል ጉባኤ መሠረት ይሆኑ ዘንድ ዐሠራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች የመረጠ እግዚአብሔር እስራኤል ዘነፍስ የተባሉ የምእመናን ጉባኤ የሆነች የቤተ ክርስቲያን መሠረቶች የሆኑ ሐዋርያትን ሰብስቦ በመንግሥተ ሰማያት ማዕድ ላይ አስቀመጣቸው /ሉቃ.22፥29-30/፡፡ በዚህም በሐዋርያት በኩል የቤተ ክርስቲያን አንድነት መመሠረቱን እንመለከታለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መምጣት /ጸጋውን ረድኤቱን በመቀበል/ የጌታን ምስጢር ሁሉ የተረዱት ሐዋርያት አባቶቻችንም የቅዳሴን ምስጢር ምእመናንን ሰብስበው በአንድነት የሚፈጽሙ ሆነዋል /የሐዋ.20፥2/፡፡
ይህ ሥርዓት በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በእርግጥም የጸና ሆኗል፡፡ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና” የሚለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ “በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ…” በማለት በእርሱ ዘመን የምእመናን መሰብሰብ ለዐበይት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ቅድመ ሁኔታ እንደነበረ ይናገራል /1ቆሮ.11-18/፡፡ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና” በማለቱም ይህ በሥርዓተ ቅዳሴ በቤተ ክርስቲያን የመሰባሰብ ምስጢር ከዚያ በኋላ ሥርዓቱን ጠብቆ በትውፊት የሚተላለፍ ሆኗል፡፡
የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑ አበውም ይህን የሐዋርያት ትውፊት ተቀብለው በቀጥታ ለትውለድ አስተላልፈዋል፡፡ ይህንንም “ትምህርታችን ከቅዳሴ ጋር የተስማማ ቅዳሴያችንም ትምህርታችንን የሚያጸና ነው” ብለው አጽንተውታል፡፡ /St. Iranaeus, Against Heresies 4:18-5/ /ማቴ.18፥ 20/፡፡

በዚህ ዘመን ምእመናን ሁሉ በቅዳሴ ተገኝተው ሁሉም ሥጋወደሙ ተቀብለው ይሔዱ ነበር፡፡ የታመመ እንኳ ቢኖር ሔደው ያቀብሉት ነበር፡፡ ያለሕማምና ከባድ ችግር ቅዳሴ የቀረ ሰው ራሱን አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን እንደለየ ይቆጠር ነበር /fr.Alexander Schmemann, Eucharist, pp.24/፡፡

ሥርዓተ ቅዳሴ የሁሉም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃም ይህን ለማስፈጸም አመቺ ተደርጐ ይሠራ ነበር፡፡ ይህ ጥንታዊ የሕንፃ ቤተ ክርስትያን አሠራር ትውፊት አሁንም በቤተ ክርስቲያናችን በግልጽ ያለ ነው፡፡ ቅዳሴ ወንዶች፤ ሴቶች፣ ሕፃናት ሁሉ ሊሳተፉት የሚገባ ምስጢር ባይሆን በቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ወንዶች፣ ሴቶች የሚቆሙበት ቦታ ለይቶ ማዘጋጀት ለምን ያስፈልግ ነበር? ይህ የሆነው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የክርስቶስ አካል የሆነች የምእመናን አንድነት ማሳያ ስለሆነ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት ስንል ሁሉንም ምእመናን አቅፋ የያዘች መሆኗን እንደሚገልጽ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የዚህ መገለጫ ከሆነ ሁሉን ሊይዝ ይገባዋልና፡፡

በቅዳሴ ጊዜ ስላለው የምእመናን ኅብረት /ስብስብ/ የጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን እይታ ከዚህም የመጠቀ ነበር፡፡ በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምእመናን ስብስብ ምድራውያንን ብቻ ሳይሆን ሰማያውያንንም ያጠቃለለ እንደሆነ ይታመን እንደነበር በምርምር በተገኙ ጥንታውያን ሥዕሎች ይታያል፡፡ በልባዊ እምነታቸው በጥልቀት ያለውን የእነርሱን እና የሰማያውያንን ኅብረት በሥዕል ያሳዩ ነበር፡፡ አንድ የነገረ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ ይህን ሲገልጹ “በብዙ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሥዕላቱ ከማኅበረ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚሳተፉ፣ የዚህን ምስጢር ትርጉም የሚናገሩ፣ ዘላለማዊ እንቅስቃሴውንና መስመሩን የሚያሟሉ እንደሆነ እንረዳለን” ይላሉ /Alexander schememann. The Euchrist pp.21/
ይህ ሥርዓት አሁንም በቤተ ክርስቲያናችን ይታያል፤ ይጠበቃልም፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ ትውፊት መሠረትም ቅዱሳት ሥዕላት ቅድስትና መቅደሱን በሚለየው ግድግዳ ላይ ይሣላሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌላ ምስክር አለን፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴአችን ይዘቱና አፈጻጸሙ እንደሚያመለክተን እያንዳንዱ የካህን ጸሎት እየንዳንዱ የዲያቆን ትእዛዝ በምእመናን መልስ /አሜን/ ይጸናል፤ ይፈጸማል፡፡ በመጽሐፈ ቅዳሴ የምናነበው “ይበል ካህን፣ ይበል ሕዝብ…” የሚሉት ትእዛዛትም ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ በዚህም ሥርዓተ ቅዳሴ የካህናት ብቻ ሳይሆን የምእመናንና የካህናት የአንድነት ምስጢር መሆኑን እንረደለን፡፡

ይህንን የአንድነት ምስጢር ለማጽናት በፍትሐ ነገሥቱ ስለቅዳሴ በተነገረበት ክፍል “ምእመናን ሳይሰበሰቡ ቅዳሴ የሚጀምር አይኑር” የሚለው መልእክት እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡

በዘመናችን የሚታየው የቅዳሴን ለካህናትና ለተወሰኑ ሰዎች መተው፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና የሕይወት ልምድ እንግዳ የሆነ ስርዋጽ ነው፡፡ አንዳንዶች ሥርዓተ ቅዳሴ በዋነኝነት የካህናት ሥራ እንደሆነ እና እነርሱ ግን ቢኖሩም እንኳን አዳማጭ፣ አዳማቂ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከውስጧ ከሚሰሟት ሕመሞች አንዱ ነው፡፡ አንዳንዴ ለሚታየው በሥርዓተ ቅዳሴ በንቃት አለመከታተል፣ ከዚህም የተነሣ የመንፈሳዊ ሕይወት መድከም፣ አንዱ ምክንያት መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

የመሰባሰባችን ምስጢር

የምእመናን አንድነት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፡፡ እያንዳንዱ ምእመን ደግሞ የክርስቶስ ብልት ነው /1ቆሮ.12፥27/፡፡ እንግዲህ በምእመናን መሰባሰብ፣ ከምድራዊ አስተዳደራዊ ተቋም በተለየ የላቀች ቅድስት የሆነች የክርስቶስ አካል፣ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ የቅድስናዋ ታላቅ መዓርግ /ፍጻሜ/ ይሆናል፡፡

“የቤተ ክርስቲያን ፍፁምነት” ማለትም ቅድስት የሆነች የቤተ ክርስቲያን በሰማያዊ ገጽታዋ መገለጥ ማለት ነው፡፡ የምእመናን ስብሰብ እንደማንኛውም ምድራዊ ስብስብ የሺህዎች “ድምር” ማለት ሳይሆን የክርስቶስ ሰማያዊ አካል /በስሙ በማመን ብልቶቹ የሆኑ ምእመናን ኅብረት/ መገለጥ ነውና፡፡

ብዙ የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊ ትውፊቶች የማይቀበሉ አዳዲስ የሥነ መለኮት አስተምህሮዎች ብቅ ብቅ ባሉበት በዘመናችን ይህን ጠንቅቀን ማወቅ ይገባናል፡፡ እነዚህ ምድራውያን አስተምህሮዎች ለአምልኮ ሥርዓት ግድ የሌላቸው፣ ቢኖራቸው እንኳ አንዱን የቅዳሴ ክፍል ከሌላው የሚያበላልጡ፣ አንዱን በጣም አስፈላጊ አንዱን ደግሞ ብዙም የማያስፈልግ አያደረጉ መመደብ የሚቀናቸው ናቸው፡፡ ስለቅዳሴ ብንጠይቃቸው ሕብስቱና ወይኑ የሚለወጥበትን ጊዜ አጉልተው ሌላውን አሳንሰው የሚናገሩ ናቸው፡፡ ሕብስቱና ወይኑ የመለወጡን ነገርም ቢሆን በኦርቶደክሳዊና ሰማያዊ መንገድ ሳይሆን በሳይንሳዊና ምድራዊ መንገድ ለማረጋገጥና ለመተንተን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህ አስተምህሮዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው፡፡

ይህን ሰማያዊ ምስጢር የምታውቅ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የአንድ ምእመን ከቅዳሴ መቅረት በጣም ያስጨንቃት ነበር፡�The Eucharist, pp21/

የቤተ ክርስቲያን ቅድስና ይህ ነው፤ የክርስቶስ አካል መሆኗ፡፡ እያንዳንዳችን ምንም ያህል ኀጢአተኞች ልንሆን እንችላለን፤ ነንም፡፡ የምእመናን አንድነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግነ ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡ ይህም ከእኛ የመጣ ቅድስና ሳይሆን አካሉ በሆነች በቤተ ክርስቲየን “ራሷ” ሆኖ በመካከላችን ካለው ክርስቶስ የተገኘ ነው፡፡ ከኀጢአት የማንጠራ /የማንርቅ/ ጎስቋሎች ብንሆንም በመሰባሰባችን “የምትመሠረት” ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን በእውነት ንጽሕት ናት፤ የሕመሟ መድኀኒት፣ የቅድስናዋ ምንጭ በመካከሏ ነውና፡፡ በምእመናን መሰባሰብ “የተገነባች” ቤተ ክርስቲያን “ቅዱስ ሕዝብ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተመረጠ ዘር….” መባል ይገባታል፤ የመረጣት ከኀጢአት ባርነት አውጥቶ ያከበራት የቅድስናዋ አክሊል በመካለሏ ነውና /1ጴጥ.2፥9/፡፡ ለዚህ ነው በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ምእመናን “ቅዱሳን” ይባሉ የነበሩት፤ በመሰባሰብ ይኖሩ ነበረና /ፊልሞ.1፥7/፡፡

ይህ መሰባሰብ የቅድስና መዓዛ ነው፡፡ ይህ ሰማያዊ ደስታ ነበረ መራራውን መከራ በደስታ እንዲቀበሉት ያስቻላቸው፡፡ ይህ የቅድስና ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ደስታ ነበር፡፡ በአስቸጋሪው ዓለም ክርስትናን በቆራጥነት እንዲሰብኩ ያስቻላቸው ታላቅ አንድነት ከዚህ የመነጨው ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ፍፃሜ ማኅበርሃ ለቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክርስቲያን የማኅበሯ ፍጻሜ” ይህ ነውና፡፡

የምእመናን መሰባሰብ የክርስቶስን አካል እንደሚገልጥ፣ ቅዳሴውን የሚመራው ካህን ራስ የተባለ የክርስቶስን ክህነት ይገልጣል፡፡ /ኤፌ.5፥23፣1ቆሮ.11፥3/ በጸጋ በተሰጠው ሥልጣነ ክህነት ውስጥ ሆኖ /እያገለገለ// የክርስቶስን የባህርይ /ዘላለማዊ/ ክህነት ይመሰክራል፡፡ ካህኑ የሚለብሰው የክህነት ልብስ፣ ክርስቶስ በውስጧ ያደረው የቤተ ክርስቲያን መገለጫ ነው፡፡ ለዚህ ነው በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ምእመናን ሳይሰበሰቡ ልብሰ ተክህኖ መልበስ የተከለከለው፡፡ /መጽሐፈ ቅዳሴ/ በካህኑ ራስ ላይ ያለው አክሊል እንደ መልከ ጸዴቅ ሥርዓት ያለውን ዘለዓለማዊውን የክርስቶስ ክህነት ይመሰክራል፡፡ /ዕብ.7፥20-22፣ መዝ.109፥4፣ ዕብ.7፥1/ እንግዲህ የጌታችን ዘለዓለማዊ ክህነት በዘለዓለማዊና ሰማያዊ መቅደሱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን /በምእመናን መካከል/ በዚህ መልኩ ይገለጣል፤ ቅዱስ ጳዉሎስ “እርሱ ግን የማይለወጥ ክህነት አለው” እንዳለ /ዕብ.7፥25/፡፡ ስለዚህ መሰባሰባችን ክርስቶስን በመካከላችን አድርገን ነው፡፡ ስለዚህ በቅዳሴ መሰባሰባችን በመካከላችን ካለው ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በእውነት ታላቅ ነው፡፡

በመጨረሻ፣ እግዚአብሔር በማያሳየው ምድር በደስታ ይኖር ዘንድ አብርሃም ወገኖቹንና የአባቱን ቤት እንዲተው ከታዘዘ ወደ እግዚአብሔር መገለጫ፣ ወደ ጽዮን ተራራ ስንወጣ፤ የበኩራትን ማኅበር ልንመሠርት ስንሰባሰብ እንዴት ዓለማዊ ጣጣችንን አንተው? እስራኤል በሲና ተራራ በሚያስፈራ ሁኔታ የተገለጠውን እግዚአብሔርን ለመስማት ሦስት ቀን ከተዘጋጁ፤ ልብሳቸውን ካጠቡ፤ በሚያስደንቅ የመሥዋዕትነት ፍቅሩ ስለኛ የተሰቀለውን አምላካችንን ለማየት ብቻ ሳይሆን ለመብላት ለመጠጣት ስንሰባሰብ ምን ያህል መዘጋጀት፣ ልብሳችን ብቻ ሳይሆን ሥጋውንና ደሙን ሰውነታችንን ምን ያህል በንስሐ ማጠብ ይገባን ይሆን? /ዘፍ.12፥1፣ ዕብ.12፥22-24፣ ዘፀ.19፥14-15/ ሕፃኑ ሳሙኤል በቤተ መቅደስ ለሚጠራው ቃል በንቃት መልስ ከሰጠ፤ በእውነተኛ ቤተ መቅደሱ የተሰበሰብን እኛ በቅዳሴ ሰዓት በልዩ ልዩ መንገድ ለሚሰማው የእግዚአብሔር ድምፅ ምን ያህል በትጋትና በንቃት መልስ መስጠት ይኖርብን ይሆን? /1ኛ. ሰሙ.3፥1-14/ በእውነት እግዚአብሔር ከዚህ ሰማያዊ ጉባኤ አይለየን፡፡ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ሐመር 17ኛ ዓመት ቁጥር 6 ኅዳር/ታኅሣሥ 2002

 

ስሞት እጸልይላችኋለሁ

በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ

“ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ!”2ኛ ጴጥ.1÷13-15

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሥርቶአል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ “አንተ ዓለት ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲኦልም ደጆች ሊያናውጿት አይችሉም፡፡” በማለት ቤተ ክርስቲያንን በሐዋርያት መሠረት ላይ መሠረተ/ማቴ.16÷16-18/፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በአምሳ አምስት ዓመቱ ወደ ሐዋርያት የተጠራ፣ በሁሉም ስፍራ በሐዋርያት ስም ዝርዝርም፣ መልስ በመስጠትም፣ በመካድም፣ ንስሓ በመግባትም ፈጣን እንደነበር ቅድመ ትንሣኤ ክርስቶስ የተጻፈው ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ከትንሣኤ በኋላ ሦስት ጊዜ ክዶት መጸጸቱን የተመለከተለት ጌታ አንዳች የሚቆጠቁጥ የወቀሳ ቃል ሳይኖረው በጭቃ ላይ የወደቀ ዕንቁን ወልውለው ወደ ቦታው አንደሚያስቀምጡት ወደ ክብር ስፍራው መለሰው፡፡ አልፎ ተርፎም ለምሕረቱ ወሰን የሌለው አምላክ ይህን ሐዋርያ “ ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ” ብሎ ምእመናንን ከሕፃናት እስከ አረጋውያን አደራ ሰጠው /ዮሐ.21÷15-17/፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በተቀበለበት ዕለት በአንድ ቀን ሦስት ሺህ ነፍሳትን በትምህርቱ ማርኮ “ምን እናድርግ?” በማሰኘት ጠብቅ አሰማራ የተባለውን መንጋ ወደ በረቱ ማስገባት ጀመረ፡፡ /ሐዋ.2÷31/ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ምእመናንን በአፍም በመጽሐፍም ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ በኋላም ጠብቃቸውና አሠማራቸው የተባለውን ግልገሎች፣ ጠቦቶችና በጎች ሲጠብቅና ሲያሠማራ ከተኩላ ታግሎ ነፍሱን ሰጠ፡፡ የእረኝነት ሥራውን ሊፈጽም ቁልቁል ተሰቅሎ “የእረኞች አለቃ” /1ኛጴጥ.5÷4/ ብሎ በመልእክቱ የጠራውን የጌታውን ፈቃድ ፈጸመ፡፡

ይህ ሐዋርያ በመልእክታቱ ምእመናንን ሲገሥጽና ሲመክር ሲያስተምር የኖረ ሲሆን በሁለተኛይቱ መልእክቱ ላይ ግን ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነ ኃይለ ቃልን ጽፏል፡፡ “ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ብትጸኑ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡ ሁል ጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና፡፡ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” /2ኛጴጥ. 1÷13-15/

ብታውቁም፤ ብተጸኑም ማሳሰቤን ቸል አልልም!

ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክታቱ ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትና ስለ ሰው ልጅ ብሎ ስለተቀበለው መከራ፣ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው ስለሚገባ መንፈሳዊ አኗኗር፣ አለባበስ፣ ስለ ጋብቻና ቤተሰባዊ ጉዳዮች፣ በምእመናን ላይ ስለሚመጡ መከራዎችና የዲያብሎስ ውጊያዎች፣ ድል ሲያደርጉም ስለሚያገኙት ጸጋና ዋጋ፣ ስለሚደርሱበት መዓርግ በአጠቃላይ በቀላሉ ተዘርዝሮ የማያልቅ ሰፊ ትምህርትን በመልእክቱ አስተምሯል፡፡ ይሁንና ሐዋርያው አውቀውታል፣ ጸንተዋል ብሎ ማሳሰቡን አላቆመም፡፡ ሰው ከመንገድ የሚስተው በእውቀት ጉድለት ብቻ አይደለም፡፡ እያወቁ መሳት፣ ጸናሁ ሲሉም መጥፋት አለ፡፡ ስለዚህም “አሳስባችሁ ዘንድ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መንጋውን ጠብቅና አሰማራ የተባውን አደራ የማይረሳ፣ በጥበቃ ተሰላችቶ ቸል የማይል፣ ትናንት የበሉት የጠጡት ይበቃቸዋል የማይል በመሆኑ ያውቁታል ብሎ ከመናገር ሳይቆጠብ “ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡

በዚህ ማደሪያ ሳለሁ!

ሥጋ የነፍስ ማደሪያ ናት፤ አዳሪዋ ነፍስ ከማደሪያዋ ሥጋ ስተለይ ሰው ያን ጊዜ ሞተ ይባላል፡፡ “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ ነው” እንዲል /ያዕ.2÷26/ ጻድቁ ኢዮብም “ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ÷ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፡፡” ኢዮ.19÷26/ ያለው ሥጋ ጊዜያዊ ማደሪያ መሆኑን ሲያስረዳና ራሱን ከነፍስ አንጻር አድርጎ በሞት ሥጋውን ጥሎ እንደሚሄድ ሲናገር ነበር፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ ማደሪያዬ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ ይገባኛል፡፡” ሲል በሥጋዬ ሳለሁ፣ ነፍሴ ሳትወሰድ ማለቱ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ቀሪ ዕድሜውን በችኮላ የሚጠቀመው ለሌላ ሥጋዊ ተርታ ጉዳዮች ሳይሆን ምእመናን ያስተማረውን ትምህርት እንዳይገድፍና አንዳይጠፉበት በማሳሰብ ማንቃት ነው፡፡

ጌታዬ እንዳመለከተኝ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁ!

“በእግዚአብሔር ፊት የቅዱሳኑ ሞት የከበረ” ስለሆነ ሞት ለቅዱሳን ድንገተኛና ያልተጠበቀ አይሆንባቸውም፡፡ እርግጥ ነው ሰው ሁሉ ሟች እንደ ሆኑና የሞትን አይቀሬነት በመጥቀስ ሁሉም ሰው እንደሚሞት ያውቃል ሊባል ይችላል፡፡ ቅዱሳን ግን የሚሞቱ መሆናቸውን የሚያውቁት ሞት አይቀርም ብለው ሳይሆን የሚሞቱበትን ጊዜና ሁኔታ ለመረጣቸው ለባሪያዎቹ የሚያደርገውን የማይሠውር እግዚአብሔር ገልጣላቸው ነው፡፡ የሚከተሉት የሊቀ ነቢያት ሙሴንና የቅዱስ ጳውሎስን ንግግሮች እንመልከት፡-

“እኔ ግን በዚህች ምድር እሞታለሁ ዮርዳኖስንም አልሻገርም” /ዘዳ.4÷22/

“በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና የምሄድበትም ጊዜ ደርሷል” /2ኛጢሞ.4÷6/

እነዚህ ታላላቅ ቅዱሳን የሚሞቱ መሆናቸቸውን ብቻ ሳይሆን የሚሞቱበትን ቦታ ጊዜ አስቀድመው መናገራቸው ከእግዚአብሔር ስለተነገራቸው ነው፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችንን እና የቅዱሳት እናቶቻችንን ገድላት ስንመረምር ቅዱሳን ዕለተ እረፍታቸው ቀድሞ በእግዚአብሔር እንደሚነገራቸው እንረዳለን፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ሰው እንደመሆኑ “መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ” ብሎ ጌታ ለሁሉ ካመለከተው ጥሪ በተጨማሪ ከቅዱሳን አንዱ እንደመሆኑ ከመሞቱ በፊት እንደሚሞት ያውቅ ነበር፡፡ ጌታችን ከዕርገቱ በፊትና ከዕርገቱ በኋላ ሁለት ጊዜ ተገልጦ ስለሞቱ ነግሮታል፡፡

ከዕርገቱ በፊት ከላይ የጠቀስነውን የእረኝነት አደራ ከሰጠው በኋላ “እውነት እውነት እልሃለሁ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል፡፡” ብሎታል፡፡ ወንጌልን ጽፎ በብዙ ቦታዎች የጻፈውን ሲተረጉምና ሲያትት የምናገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ትርጓሜን ሳንሻ ንባቡ ላይ “በምን ዓይነት ሞት  እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ፡፡” ብሎ የጌታን ንግግር ትርጓሜ አስከትሎ ጽፎልናል፡፡

በእርግጥም ቅዱስ ጴጥሮስ በሸመገለ ጊዜ እጆቹን በተዘቀዘቀ መስቀል ላይ ዘርግቶ ቁልቁል መሰቀል ትንቢተ ክርስቶስን ፈጽሟል፡፡

ጌታችን ከዐረገ በኋላ ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሲያስተምር “ልበ ንጹሖች ብጹዓን ናቸው፡፡” ብሎ ባስተማረው ትምህርት ሚስቶቻችንን አሸፈተብን ያሉ ሰዎች ተነሡበት፡፡ በዚህን ወቅት ሴቶቹ ተማክረው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲሸሽ ነገሩት ከከተማይቱ ወጥቶ ሊሄድ ሲል ጌታችን ተገልጦ ታየው “ጌታ ሆይ ወዴት ትሄደለህ” ቢለው “ዳግም በሮም ልሰቀል” በማለት ነገረው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ልቡ ተነክቶ ወደ ሮም ተመለሰና የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ “ጌታችን እንዳመለከተኝ” ያለው ይህን ነበር፡፡

ከመውጣቴም በኋላ አንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ!

ከላይ የተመለከትናቸው ሃሳቦች ቅዱስ ጴጥሮስ ጊዜ ሞቱ እንደቀረበ አውቆ መናገሩን እና ምእመናን የተማሩትን በማሳሰብ ሲያነቃቸው እንደነበር የሚያስረዱ ናቸው፡፡ እስካሁን የተመለከትናቸው የሚያወሱት ይህ ሐዋርያት በሕይወት ሳለ ስለሚያደርጋቸው ነገር ነበር፡፡ በመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ግን “ከመውጣቴ በኋላ የሚል ሐረግ እናገኛለን፡፡ “ከመውጣቴ በኋላ” ሲል ምን ማለቱ ነው?

ቀደም ባሉት ዐረፍተ ነገሮች እንደሚሞትና ይህንንም ጌታችን እንዳመለከተው ተናግሮ ነበር፡፡ ስለዚህ መውጣቴ ያለው ሞቱን እንደ ሆነ እሙን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሞት መውጣት ተብሎ ሲነገር የቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በታቦር ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ስለመነጋገሩ በተጻፈበት ስፍራ “በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር” ይላል፡፡ በኢየሩሳሌም የተፈጸመው መውጣቱ ደግሞ ሞቱ ነው፡፡ /ሉቃ.9÷31/ ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ ባስተማርኳችሁ እንድትጸኑ “ከሞትኩም በኋላ እተጋለሁ!” እያለ ነው፡፡ “ከሞትኩ በኋላ” የሚለውን እናቆየውና “እተጋለሁ!” የሚለውን ቃል በጥቂቱ እናብራራው፡፡

ትጋት ምንድርን ነው? ትጋት አንድ ነገር ያለማቋረጥ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ያለመታከት ማድረግ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ታካች ሰው ምንም አደን አያድንም፤ የሰው የከበረ ሀብቱ ትጋት ነው” በማለት ትጋት የታካችነት ተቃራኒ መሆኑንና ጥቅሙን ተናግሯል /ምሳ.12÷27/፡፡ ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ብሎ ገሥጿቸው ነበር /ማቴ.26÷30/፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ግን ሐዋርያት ትጉሐን ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ መሰከረላቸው “ወደዚህም ወደ ተሰፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው” /ሐዋ.26÷7/ በዚህ ሁሉ ትጋት አለመታከት፣ አንድን ነገር ሌሊትና ቀን ማድረግ መሆኑን ተረዳን፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” ሲል የሚተጋው በምንድርን ነው? እየዞረ በማስተማር ይሆን? ይህማ ቢሆን ከመሄዴ በፊት  ላሳስባችሁ ባላለን ነበር፡፡ ደግሞም ማስተማሩን በሚገባ ፈጽሞ በሰማዕትነት አርፏል፡፡ ታዲያ ከሞተ ወዲያ የሚተጋው ምን በማድረግ ነው? የትስ ነው የሚተጋው? መቼስ በመቃብር ያለሥጋው ሊተጋ አይችልም፡፡ “የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን ይናገራሉን?” ብሏል ቅዱስ ዳዊት /መዝ.87÷15/ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም “ከማደሪያዬ እለያለሁ፡፡ ብሎ ከሞተ ወዲያ እኔ የሚላት ነፍሱን እንደሆነ አስረድቶናል፡፡ ታዲያ በነፍሱ በሰማይ ምን እያደረገ ይሆን የሚተጋው? መቼስ በሰማይ እርሻ ቁፋሮ፣ ጽሕፈት፣ ድጒሰት የለም፡፡ ሐዋርያው በምን ይሆን የሚተጋው? በጸሎት ነዋ!

ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ “እንደተማራችሁት መኖርን እንዳትዘነጉ በየጊዜው /አንድ ጊዜ ብናስብ አንድ ጊዜ መዘንጋት አለና/ ትችሉ ዘንድ ከሞትኩም በኋላ ያለማቋረጥ ያለመሰልቸት ስለ እናንተ በመጸለይ እተጋለሁ! ማስተማርና መልእክትን ጽፎ መተው ብቻ ሳይሆን በተማራችሁት መገኘት እንድትችሉ በአጸደ ነፍስም ብሆን እለምናለሁ፣ እማልዳለሁ! እያለ ነው፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ዓለትነት የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ስለእርሷ የተጻፋላት፣ በደሙ የዋጃት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሷ ነው፡፡ እርሱ በሁሉ የሞላ ሲሆን “ሁሉን በሁሉ ለሚሞላ ለእርሱ ሙላቱ የሆነች” አካሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት /ኤፌ.1÷22/፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ስትሆን ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራሷ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሰውነት አካል ክፍሎች ነን፡፡ “እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁ የአካሉ ክፍሎች ናችሁ፡፡” ተብለናል /1ኛቆሮ.12÷27/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሕይወትን የሚሰጡ ጥምቀትን፣ ንስሐን፣ ቊርባንን የመሳሰሉ ምስጢራትን በመፈጸም ራሳችን ከሆነው ከመድኃኔዓለም ጋር አንድ እንሆናለን፡፡

ክርስቲያኖች ሲሞቱ ከዚህ ኅብረት ይነጠላሉ ማለት አይደለም፡፡ ራሷ ክርስቶስ በሰማይም በምድርም ስላለ ቤተ ክርስቲያንም በምድርም በሰማይም አለች፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ ወደ ሰማያዊቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ የሰማይዋ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ድል በነሱ ቅዱሳን የተሞላች ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ ሥርዓት ያለባት፣ ሥጋዊ ደማዊ አሳብ የማይሰለጥንባት ናት፡፡ ከእኛ ተለይተው ወደዚያ ኅብረት የተደመሩ ወገኖቻችን በላይ ያሉ የክርስቶስ አካላት ናቸው፡፡ ከእኛ በምድር ካለነው የክርስቶስ አካላት ጋር አንድነታቸው አይቋረጥም፡፡ የክርስቶስ አካል አይከፈልማ! ስለዚህ በሰማይ ካሉት ድል የነሡ ቅዱሳን ጋር እኛ ደካሞቹ በጸሎት እንገናኛለን፡፡

“ዐይን እጅን አልፈልግሽም ልትላት አትችልም፤ ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁንም የሚያስፈልጉህ ናቸው፡፡ ተብሎ እንደተነገረ እኛ ኃጢአተኞቹ የቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎች ብንሆንም ቅዱሳኑ ስለ እኛ ይጸልያሉ /1ቆሮ.12÷21/፡፡ ምክንያቱም ደካማ ብንሆንም ለቅዱሳን እናስፈልጋቸዋለን፡፡ ቅዱሳን ኃጥአንን ካልወደዱ ቅድስናቸውን ያጣሉ፡፡ እኛን ካልወደዱ “እኔ ክርስቶስን እንደመሰልሁ እናንተም እኔን ምሰሉ” “አሁን እኔ ሕያው ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፡፡” ብለው ለመናገር እንደምን ይችላሉ? /ገላ.2÷20/  

እኛ በሥጋ ድሆች የሆኑ ነዳያንን በመመጽወት እንደምንከብር ቅዱሳንም በነፍስ ድሆች የሆንን እኛን በአማላጅነት ጸሎታቸው እየመጸወቱ ይከብራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉን ነው፡፡” ይላልና በምግባር ድሆች ለሆንን ለእኛ መራራት የቅዱሳን ግብር ነው፡፡ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል” ተብሎ እንደተነገረላቸው ቅዱሳን ክቡር ሆነን ሳለን ለማናውቅ እንደሚጠፉ እንስሶች ለመሰልን ለእኛ ለኃጢአተኞች ይራራሉ፤ ይማልዱማል /ምሳ.12÷10፣ 14÷21/፡፡

ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ መከራን ታግሠው ስለ ሌሎች በደል ይለምናሉ፡፡ ሳይበድሉ ራሳቸውን በኃጢአትኛው ቦታ አርገው፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆነው ይማልዳሉ፡፡ ታዲያ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይታ “ሲሄዱና ከክርስቶስ ጋር ሲኖሩ” /ፊል.1÷23/ ምንኛ ይለምኑ ይሆን?

በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሕይወተ ሥጋ ለሌሉና ወደ ሰማዩ ኅብረት ለሄዱ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐትን፣ መታሰቢያን በማድረግ፤ ለዚያ የሚያበቃ ቅድስና ያላቸውን ደግሞ በዓላቸውን በማክበር ታስባቸዋለች /2ጢሞ.1÷17-18/፡፡ በሰማይ ያሉት ቅዱሳን ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው ስለ እኛ ይተጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መከራና የምእመናንን ስቃይም በዝምታ አይመለከቱም፡፡ በዙፋኑ ፊት ቆመው “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” እያሉ ያማልዳሉ፡፡ /ራእ.6÷10/ የቅዱስ ጴጥሮስ በረከቱ አይለየን! አሜን፡፡

/ምንጭ፡ ሐመር  ሐምሌ 2002 ዓ.ም./

ክርስቶስን መስበክ እንዴት?

ሚያዚያ 25፣ 2003ዓ.ም

/ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ሚያዝያ 2003ዓ.ም/

ፕሮቴስታንቶችና ፕሮቴስታንታዊ መንገድ የሚከተሉ አንዳንዶች  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን አልሰበከችም የሚል ክርክር ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን ለመመለስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በምላሹ እንዲሳተፉበት ጋብዘናል፡፡ ለዚህ እትም የያዝነውን እነሆ!

ሊቀ ጠበብት ሐረገወይን አገዘ“ቤተክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ወንጌል ነው”

ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ ሁለት ሺሕ ዓመታት አልፏታል። ይህንንም ሊቃውንቱ ምእመናንም ያስረዱትና የተረዱት ነው። ወንጌል ካልተሰበከ ክርስቲያኖች እንዴት ለአሁን ዘመን ደረሱ? ወንጌል መሠረት፣ በጎ እርሾ ሳይሆነው፣ ወንጌል ብርታት ሳይሆነው ይህን ሁሉ ዘመናት አቆራርጦ፣ ድልድዩን አልፎ እንዴት እዚህ ደረሰ? ወንጌል ቤተ ክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ነው፡፡

 

በቤተክርስቲያን ሊቃውንቱ የሚያነቧቸው፣ የሚተረጉሟቸው፣ ምእምናን የሚሰሟቸው፣ የሚታነጹባቸው ድርሳናት፣ ተአምራት ወንጌል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት ወንጌልን የሚፈቱ፣ የሚተረጉሙ፣ የሚያመሰጥሩ ናቸው። ከዚህ ውጭ የሆኑ መጻሕፍት በቤተክርስቲያን አይነበብም፣ አይተረጎምም፣ አይሰማም። ቤተክርስቲያን ወንጌልን የምትሰብከው በቃል፣ በመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው። ጥምቀት ወንጌል ነው። ቤተክርስቲያንም ጥምቀት የዘወትር ሥራዋ ነው። ወንጌል ስለ ጥምቀት ነው የሚነግረን። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙም በየዕለቱ ይቀርባል፤ ይህ ወንጌል ነው። ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን የተቀደሰውን ጋብቻቸውን በተቀደሰው ቦታ፣ በተቀደሰው ጸሎት በምስጢረ ተክሊል ይፈጽማሉ። ይህም ወንጌል ነው። እናቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን ከዚህ ዓለም ሲሸኙ በሥርዐተ ፍትሐት፤ ብሉያትና ሐዲሳት እየተነበቡ፣ ያሬዳዊ ዜማ እየተዜመ ነው። ይህ ወንጌል ነው። አላዛርን ከመቃብር ተነሥ እንዳለው፤ የታሰረበትን ፍቱት እንደተባለ እንደተ ፈታ ሁሉ፤ ካህናትም ከኃጢአት እስራት እየፈቱ ሕዝባቸውን መሸኘት፤ “አቤቱ እግዚኦ ይቅር በለው ሲያውቅ፣ ሳያውቅ በሠራው ኃጢአት ይቅር በለው” እያሉ መሸኘት ወንጌል ነው።

ቤተክርስቲያን ራሷም፣ እግሯም፣ መሠረቷም፣ ጉልላቷም ወንጌል ነው። ይህን በቅንነት፣ በበጎ ነገር፣ በምስጢር፣ በትርጓሜ ለሚያዩት ነው። በጥላቻ ካዩት ነጩም ጥቁር ነው፤ ብርሃኑ ጨለማ ነው፤ በጥላቻ ማየትና በፍቅር ማየት፤ በሐሰት መናገርና በእውነት መናገር መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። የቤተክርስቲያን ጥንተ ጠላቶች ለቤተክርስቲያን በጎ ይመሰክራሉ ብለን ከጠበቅን የተሳሳትን ይመስለኛል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን “እግዚአብሔር ከእናንተ  ምስክርነትን አይፈልግም” ነው ያላቸው። ጸሐፍት ፈሪሳውያን ስለ ክርስቶስ በጎ ስለማይመሰክሩ ስለማይናገሩ ነው። ምክንያቱም በጭፍን፣ በቅናት፣ ስለጠሉት ነው። ቤተክርስቲያንም ከጠላቶቿ የእውነት ምስክርነትን አትጠብቅም፤ በበጎ ለሚያዩአት ግን ምስክርነቱ በእጅ የሚጨበጥ (የሚዳሰስ) በዐይነ የሚታይ ነው።

ቤተክርስቲያን ወንጌል ያልሰበከችበት ዘመንም፣ ጊዜም የለም። ወንጌል አልተሰበከም ለሚሉ ሰዎች ትናንት አለነበሩም፣ ዛሬም የሉም። ለነገሩስ የት ሆነው ያዩታል? ቢኖሩም አይገባቸውም፤ ውስጣቸውም በብዙ ችግር የተተበተበ፤ በቅራኔ የተሞላ ነው። በቅራኔ የተሞላ ደግሞ ከውጭ የሚነገረውን በጎ ነገር ለመቀበል ዝግጁ አይደለም።

 

ሊቀ ትጉኀን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ“ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው”

ሰው በተሰጠው የፈቃድ ነጻነት መሠረት የፈለገውን የመናገር መብት አለው። ፍሬ ነገሩ እውነቱ የቱ ነው? ሐሰቱስ? የሚ ለው ነው። ዲያብሎስ ስለ ቅዱስ ሚካኤል የብርሃን መላክነት አይመስክርም፤ ሊመሰክርም አይችልም። «ሚካኤል ደካማ ነው» እያለ የፈለገውን መናገር ይችላል። የዲያብሎስን ምስክርነትም ሚካኤል አይፈልገውም፣ አይቀበለውምም። ዲያበሎስ የፈለገውን ቢናገር ሚካኤልን አይከፋውም፤ ከጠላቱ ቡራኬ ስለማይጠብቅ። እንደዚሁ ሁሉ የእኛም ቤተክርስቲያን የሌሎችን ቤተእምነቶች ምስክርነትም ሆነ ክስ አታደንቀውም፤ አትደነግጥበትምም የእኛ ቤተክርስቲያን ጨርቅ ሰጥታ ጉቦ ሰጥታ እንዳልተስፋፋች ሁሉም ያውቁታል፤ ታዲያ ወንጌልና ክርስቶስን ሳትሰብክ ቤተክርስቲያን ሆና ሁለት ሺሕ ዓመታትን እንዴት ተሻገረች? አሸናፊ ስለሆነች በእውነቷ ብቻ ቆማ የምትኖር ናት። ጉቦ አይከፈልባትም፣ ማባበያም አትጠይቅም።

 

ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ልብን አሻክሮ ምላስን አለዝቦ በማነብነብ አይደለም፤ በድርጊት በማሳየትም እንጂ። በአንድ ታላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓል በአንድ ቤተክርስቲያን በአንድ ቀን ብቻ የምናደርገው ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ስብከቱ፣ ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ዋዜማው በተግባርም ታቦት ይዘን ቆመን ያስተላለፍነው ትምህርት በጠቅላላው መናፈቃኑ ለአንድ ዓመት ከጮኹበት፣ ብዙ ነገር ካወጡበት «አገልግሎት» እጅግ ብልጫ አለው። የዚህ አጠቃላይ አገልግሎታችን ዋነኛ ማእከልም ወንጌልና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ድኅነት ነው፡፡ ንዋያተ ቅድሳቶቻችን በሙሉ ስብከቶች ናቸው። በቅዳሴ ላይ ቄሱ፣ ዲያቆኑ መስቀል ይዞ የሚዞረው ምን  ለማሳየት ነው? ቀሳውስት ዕጣን እያጠኑ “ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ” እያሉ ሲያመሰግኑ ምስጢረ ሥላሴ እና ምስጢረ ሥጋዌን መስበከ፣ ማስተማራቸው ነው። ልብሰ ተክህኖዎቹ ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅድሳቱ ሁሉ መስቀል የሚደረግበት ለጌጥ አይደለም። ይህ ስብከት አይደለም እንዴ? መቅደስ ውስጥ ስንቀድስ በአራቱ ማእዘን የምንቆመው ጽርሃ አርያምን እያሳየን ነው። እነርሱ የማያስተውሉትን ሰባቱ ሰማያትን አምጥተን መቅደሱ ላይ ቁጭ አድርገን የምናሳያቸው ለስብከት ነው። ኪሩቤል እንዴት አድርገው ጌታን እንደተሸከሙት ታቦቱን መንበሩ ላይ አስቀምጠን ስንቀደስ እናሳያለን። በተጨባጭ እያሳየን እያሰተማርን ነው።

 

ደስ ሊለን ይገባል፤ ለሁለት ሺሕ ዘመን ወንጌል ሳይነበብባት በተለያየም መንገድ ሳይሰበክባት የማትውል የማታድር እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ቤተክርስቲያንም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነች። ቢያንስ በቅዳሴ ላይ ሰባኪ ያልቆመባቸው፣ ወንጌል ያልተሰማባቸው፣ ሃይማኖት አበው የማይነበብባቸው ገዳማትና አብያተክርስቲያናት የሉም። ስለዚህ ስብከት መንዘፍዘፍና ዓላማ የሌለው ጩኸት አይደለም። በእርጋታ፣ በማስተዋል፣ በጥንቃቄ የሚፈጸም በብዙ ዓይነት መንገድ የሚከናወን፤ ያልነበሩትን የምናመጣበት የነበሩትን የምናጸናበት አገልግሎት መሆኑን ሁሉም ይረዳ።