የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት ክፍል ሁለት

ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ባለፈው ዕትማችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጪ/ ያደረገችውን ረዥም ሐዋርያዊ ጉዞ የሚዳስስ ጽሑፍ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

2. አፍሪካ
የኢ.ኦ.ተ.ቤ. የጥቁሩን ሕዝብ መወከል የሚያስችላት ታሪካዊ አጋጣሚ ቢኖራትም ከዓለም ቀድማ በተመሠረተችበት አህጉር ለሚገኘው ሕዝቧ የሰጠችው አገልግሎት ሰፊ የሚባል አይደለም፡፡ እሷ አገልግሎት ባለመስጠቷ ጥቁሩ ሕዝብ ባሕሉና ልማዱ በፈጠረው ሀገረ ሰብአዊ እምነት ተይዞ ከአሚነ እግዚአብሔር ርቆ ለረጅም ዘመናት እንዲቆይ ሆኗል፡፡ አፍሪካውያን ከብዙ ሺሕ ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ በእጅጉ ዘግይተው ወንጌልን የተቀበሉ አውሮ¬ውያን ያስተማሯቸውን ተቀብለዋል፡፡ ይልቁንም ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ሕዝቡ መሔዷ ቀርቶ ራሱ ሕዝቡ እሷን ፈልጎ እንዲመጣ ኾኗል፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያናችን ቀደም ባሉት ጊዜያት እስከ ሱዳንና ሱማልያ ተስፋ ፍታ እስልምና እስከሚቀማት ድረስ በርካታ አፍሪካውያንን በሃይማኖት ይዛ እንደቆየች የሚያስረዱ የታሪክ መዛግብት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በአፍሪካ ያላት የሳሳ ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

2.1 ኬንያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1967/68 ዓ.ም ጀምሮ በናይሮቢ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች፡፡ በ1978 ዓ.ም የተመሠረተው የደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንም ለምእመናን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስደተኞች ካምፕ የመድኃኔዓለምና ለኬንያዎች የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በስደተኞተ ካምፕ አካባቢ እንዳለ ይነገራል፡፡

 
2.2 ሱዳን
በካርቱም ከተማ ቤተ ክርስቲያን ተቋቁማ ከ1932 ዓ.ም ጀምሮ አገል ግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡

2.3 ደቡብ አፍሪካ
ይህች ሀገር ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ ለኢትዮጵያና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያኗ ልዩ ፍቅር ያላቸውና የኢ.ኦ.ተ.ቤ. ተከታዮች ነን ብለው የሚያምኑ ሰዎች በብዛት የሚኖሩባት ናት፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህንን እምነታቸውን በተግባር ለመተርጎም እ.ኤ.አ. ከ1872 ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ አድርገው እ.ኤ.አ. በ1892 ዓ.ም. የተወሰኑ ምእመናን ከነበሩበት የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ተለይተው በመውጣት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” ብለው አቋቋሙ፡፡ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት በጣልያኖች ላይ የተቀዳጀችው የድል ዜና እንቅስቃሴያቸውን የበለጠ እንዲጎለብትና ማኅበራቸው እንዲጠናከር አድርጓል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በነበሩባት ውስጣዊ ችገሮች የተነሣ የፈለጉትን ያህል ልታጠናክራቸው ባትችልም አልፎ አልፎ በሚያገኙት ዕርዳታና የአይዞአችሁ መልእክት ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው ላለው ሕዝብ አገልግሎት ስትሰጥ እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ በ1993 ዓ.ም ደግሞ በስደት ወደ አካባቢ የሔዱ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከደቡብ አፍሪካውያኑ የእምነት ወንድሞቻቸው ጋር በመተባበር የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አቋቁመዋል፡፡

3. አውሮፖ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እግሯ አውሮፖን የረገጠው /በጊዜው በኢጣልያ ፍሎሬንስ በተደረገው ዓለም ዐቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ከኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ተመርጠው በተላኩ ልኡካን አማካይነት /ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ  እንደኾነ ታሪክ እማኝነቱን ቢሰጥም በይፋ በተደራጀ መልኩ ተቋቁማ አገልግሎት መስጠት የጀመረችው በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣልያን በተወረረችበት ጊዜ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሎንዶን ካደረጉት ስደት ጋር ለአጭር ጊዜም ቢሆን በተሰጠው አገልግሎት ጀምሮ በ1964 ዓ.ም በትውልደ ጃማይካውያን የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች አማካይነት ተቋማዊ መልክ ይዞ እንዲቀጥል የተደረገው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በታላቋ ብሪታንያ አምስት ያህል አብያተ ክርስቲያናትና ከሦስት በላይ የጽዋ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡

ከእንግሊዝ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያና ችን የደረሰችበት ሀገር ጀርመን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው እንቅስቃሴ የጀመረችው በወቅቱ ለትምህርት ወደዚህ ሀገር መጥተው በነበሩት መልአከ ሰላም ዶ/ር መርዐዊ ተበጀና ዶ/ር በዕደ ማርያም አማካይነት ሲኾን በአሁኑ ወቅት ሰባት ያህል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ከሦስት የማያንሱ የጽዋ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ15 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በግሪክ /አንድ/፣ በጣልያን /ሦስት/፣ በስዊዘርላንድ /ሦስት/ በስዊድን /ሁለት/፣ በኖርዌይ /ሁለት/፣ በቤልጅየም /አንድ/፣ በኦስትርያ /አንድ/፣ በፈረንሳይ /አንድ/ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ለማደግ ክትትል እየተደረገላቸው ያሉ ጽዋ ማኅበራት በተለያዩ የአውሮ¬ፖ ሀገራት አሉ፡፡

4. አውስትራሊያ
በዚህ አህጉር የቤተ ክርስቲያናችን እንቅስቃሴ ጥንታዊ የሚባል አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን እንደዚሁ በጽዋ ማኅበርነት የተደራጁ የምእመናን ኅብረቶች አሉ፡፡

5. ሰሜን አሜሪካ
የቤተ ክርስቲያናችን የሰሜን አሜሪካ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ሲኾን ቤተ ክርስቲያን በኦፊሴል የተመሠረተችው ግን በ1951 ዓ.ም በአቡነ ቴዎፍሎስ ተባርኮ ኒውዮርክ ላይ በተቋቋመው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ነበር፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን የተቋቋመው በወቅቱ የኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝብ አርአያነት አምነው ያስተጋቡ ለነበሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ በተቋቋመበት ዕለት 275 አፍሪካ አሜሪካውያን በመጠመቅ የቤተ ክርስቲያን አካል እንደሆኑ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ዓይነት በርቀት ለናፈቃት ጥቁሩ ሕዝብ ፓ-ስፊክን አቋርጣ የተቋቋመችለት ቤተ ክርስቲያን እየዋለ እያደረ በልዩ ልዩ ምክንያት ሀገሩን ትቶ ወደ አህጉሩ የሚሰደደው ሕዝብ ቁጥር እየበዛ ሲሔድ እሷም እየተስፋፋች ዛሬ ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በአህጉሩ ከ90 በላይ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ 

 
6. ካናዳ
በካናዳ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተጀመረው በቶሮንቶ ከተማ በአንድ ምእመን ድጋፍ በተገዛ ሕንፃ ውስጥ በ1964 ዓ.ም ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመላ አህጉሩ ከሃያ አምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡

7. ካሪብያን ሀገሮች
በዚህ ትሪንዳድ ቶቤጎን ጉያናንና ጃማይካን በሚያጠቃልለው አካባቢ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የጀመረችው በ1964 ዓ.ም. በአባ ገብረ ኢየሱስ /በኋላ አቡነ አትናቴዎስና አቶ አበራ ጀንበሬ አማካይነት ሲኾን በአሁኑ ወቅት ከአምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡

8. ትሪንዳድና ቶቤጎ
ቤተ ክርስቲያን በቅኝ ገዥዎቹ በደረሰበት ተፅዕኖ በማንነት ፍለጋ ይናውዝ ለነበረው ለዚህ አካባቢ ጥቁር ሕዝብ አገልግሎት መስጠት የጀመረችው ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተደረጉ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ነፍሳት በጥምቀት ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ተወልደው በቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እየገቡም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ አካባቢ ከአምስት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡  

9. ጃማይካ
በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ የነጻነታቸው ተስፋ ምድራዊ ርስት አድርገው ይቆጥሯት ለነበረችው ኢትዮጵያ አጋርነታቸውን ለማሳየት “ራስ ተፈሪያን” የሚል ቡድን መሥርተው ነበር፡፡ ንጉሡ በ1958 ዓ.ም በጃማይካ ይፋ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የመሆን ፍላጎት እያየለ በመምጣቱ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን በኪንግስተን ጃማይካ ተቋቋመች፡፡ ከዚያም በኋላ ግንቦት 6 ቀን 1962 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ጃማይካ ሲገቡ ብሔራዊ አቀባበል በተደረገላቸው ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ አማካይነት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥታ ዛሬ ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡

II. አስተዳደራዊ መዋቅር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከላይ በቀረበው መልኩ ዓለም ዐቀፋዊ አገልግሎት ስትሰጥ እንደየዘመኑ ሁኔታ የራሷን አስተዳደራዊ መዋቅር እየዘረጋች ሲሆን ዛሬ ባለችበት ደረጃ የዝርወት እንቅስቃሴዋን በመምራት ላይ ያለችው 12 ያህል አህጉረ ስብከትን በማቋቋም ነው፡፡ እነዚህም የመላ አፍሪካ ሀገረ ስብከት፣ የአውስትራሊያ ሀገረ ስብከት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት፣ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት፣ የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገረ ስብከት፣ የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት፣ የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ የካሪብያን ሀገራት ሀገረ ስብከትና የካናዳ ሀገረ ስብከት ናቸው፡፡

 
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ ማለፍ የሌለበት ቤተ ክርስቲያናችን በልዩ ልዩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት መካከል ማኅበራዊ መረዳዳትንና ቅርርብን ዓላማው አድርጎ በ1948 ዓ.ም በአምስተርዳም የተመሠረተው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት /World Council of Cherches/ ሲመሠረት በመሳተፍ ከመሠረቱ ሀገራት አንዷ መሆኗ ነው፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ደረጃ በ1963 ዓ.ም ናይሮቢ ኬንያ ላይ የተቋቋመው የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መሥራች አባል ናት፡፡ ከያዝነው ርእስ አንጻር የቤተ ክርስቲያኗ የእነዚህ ጉባኤያት አባል መሆን ብዙም የጠቀማት አይመስልም፡፡ ወይም ጉባኤያቱን በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም፡፡ 

    
III.  ችግሮች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ ሰማያዊ እንደመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የዓላማዋ ተፃራሪ በሆነው ዲያብሎስ ስትፈተን ኖራለች አሁንም በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ አካባቢ ያለችዋ ቤተ ክርስቲያናችንም ከምሥረ ታዋ ጀምሮ ልዩ ልዩ ችግሮች አጋጥመዋታል፡፡ ዛሬም እነዚሁ ችግሮች ሰማያዊ አገልግሎቷን በስፋት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው በጉያዋ ለተሰበሰቡ ስዱዳን ልጆቿ እንዳትሰጥ ያደርጓታል፡፡

በአካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያሉባትን ችግሮች ውስጣዊ እና ውጫዊ ብለን ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ውስጣዊ ስንል በየደረጃው ካሉ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኗ አካላት፣ ካህናት፣ ምእመናን፣ ሰበካ ጉባኤያት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ወ.ዘ.ተ.፣ የሚመጡ ችግሮችን ሲሆን ውጫዊ ስንል ደግሞ ከቤተ ክርስቲያኗ ውጭ ካሉ አካባቢያዊ ነባራዊ ሁናቴዎች የሚመጡትን ችግሮች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት

ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጭ/ ያደረገችውን ረጅም ሐዋርያዊ ጉዞ በአጭሩ በመዳሰስ፤ ጉዞዋ ዛሬ የደረሰበትን ምዕራፍ መቃኘት ነው፡፡ የዛሬው ከታየ ዘንድ ግን ጽሑፉ በመጠኑም ቢሆን ጥናታዊ መልክ ይኖረው ዘንድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ በውጭው ዓለም ለምትሰጠው አገልግሎት እንቅፋት ናቸው ተብለው ሊጠቀሱ ከሚችሉ ችግሮች ዋና ዋና የሚባሉትን በማቅረብ የይሁንታ አሳብ ይሰነዝራል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እምነትን በተመለከተ የግንኙነት መስመሯን ወደ ውጭ መዘርጋት የጀመረችው ቅድመ ክርስትና ከ1000 ዓ.ዓ. ገደማ ጀምሮ ነው፡፡ በቃልም በመጣፍም የቆየን የሀገራችን ወፍራም የእምነት ታሪክ እንደሚነግረን ንግሥተ ሳባ በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን ሲያመልክ የነበረ ሕዝቧን በመወከል ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ከንጉሡ ከሰሎሞን ጋር በመወያየት እግዚአብሔር ለእሱና ለሕዝቡ የገለጠውን ሕገ ኦሪት ይዛ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡ ሕዝቧንም በዚሁ የኦሪት ሕግና እምነት እንዲመራ አድርጋለች፡፡ እሷ የጀመረችው ግንኙነትም በኋላ የመንፈሳዊ ጥበብ ፍለጋ ጉዞዋ ሌላ ውጤት በሆነው ልጇ ቀዳማዊ ምንልክና እሱ ባመጣቸው ሌዋውያን ካህናት አማካይነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከክርስትና በፊት የነበረውን ድዮስጶራዊ እንቅስቃሴና ግንኙነት በዚሁ እንተወውና የክርስቶስ መወለድና ታላቅ የማዳን ሥራ ለዓለም ከታወጀበት ወዲህ ያለውን ታሪክ እንመልከት፡፡ መግቢያ ይሆነን ዘንድ የዝርወት እንቅስቃሴዋን የምናይላት የኢ.ኦ.ተ.ቤ. እንዴት እንደ ተመሠረተች በሌላ አገላለጥ ክርስትና ወደ ሀገራችን እንዴትና መቼ እንደገባ በአጭሩ እንመልከት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከክርስትና ጋር የተዋወቅንበትን ጊዜ አስመልክቶ ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአበው ያስቆጠረው ሱባኤ ሞልቶ፣ በነቢያት ያስነገረው ትንቢት እውነት ሆኖ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ይህንን ታላቅ ዜና በጥበብ ተረድተው፣ በኮከብ እየተመሩ ቤተልሔም ደርሰው በመስገድ ለንጉሠ ሰማይ ወምድርነቱ ወርቅ፣ ለክህነቱ ዕጣን፣ አዳምን ለማዳን በመስቀል ላይ ስለሚቀበለው ሕማምና ሞት ከርቤ እጅ መንሻ አቅርበው ወደ ሀገራቸው ከሔዱት ነገሥታት አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው የሚል ታሪክ አለ፡፡

በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምኖ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስስም ተጠምቆ ክርስትናን በመያዝ ወደ ሀገራችን የገባው የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬ በጅሮንድ /የገንዘብ ሹም/ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው፡፡ እንደኦሪቱ ሥርዐት ማንኛውም የብሉይ ኪዳንን እምነት የተቀበለ ወንድ የሆነ ሁሉ በዓመት የሚያከብራቸው በዓላት ነበሩ፡፡ እነዚህም በዓላት በዓለ ናዕት /የቂጣ በዓል/፣ በዓለ ሰዊት /የእሸት በዓል/፣ በዓለ መጸለት /የዳስ በዓል/ ይባሉ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ኢትዮጵያውያን የእምነታቸው ሥርዐት በሚያዝዘው መሠረት ከበዓለ ፋሲካ ሰባት ሱባኤ በኋላ የሚከበረውን በዓለ ሰዊትን ወደ ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ ያከብሩ ነበር፡፡ /ሶፎ. 3፥10/፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ መዝግቦት በምናገኘው ታሪክ መሠረት ሐዋርያት በጌታ ልደት የተበሰረችውን ወንጌል ያለፍርሐትና ያለመሰቀቅ ዓለምን ዞረው ያስተምሩ ዘንድ አጽናኝ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን የላከላቸው በ34 ዓ.ም በዓለ ሰዊት በተከበረበት ዕለት ነበር፡፡ /ሐዋ. 3፥10/ በዚህም መሠረት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው በየሀገሩ ቋንቋ ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በመደነቅ ከሰሙት ምእመናን መካከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበት እንደነበረ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዓለ ሐምሳን አስመልክቶ በሰጠው ስብከቱ መስክሯል፡፡ /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘበዓለ ሃምሳ/፡፡

በዚሁ በዓል ተሳትፎ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር እየመረመረ ወደ ሀገሩ በመመለስ ላይ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከወንጌላዊው ፊል ጶስ ጋር ተገናኘ፡፡ ፊልጶስም ያነበው የነበ ረውን የትንቢት መጽሐፍ ለክርስቶስ እንደተነገረ አምልቶ አስፍቶ ተረጎመ ለት፡፡ ጃንደረባውም በትምህርቱ አመነ፡፡ ተጠመቀ፡፡ በዚህ ዓይነት ክርስትናን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ እሱም በተራው ይኸንኑ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ዜና ለሕዝቡ አሰማ፡፡ /ሐዋ. 8፥26-40/ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ 2ኛ መጽሐፍ ቀ. 1/፡፡ በዚህ ዓይነት እንደ ሕገ ኦሪቱ ሁሉ በቤተ መንግሥቱ በኩል አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስትና በዐራተ ኛው መ.ክ.ዘ. ተቋማዊ መልክ ይዞ በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም ኢትዮ ጵያዊ ጉዞውን ጀምሯል፡፡

ከላይ ከቀረበው ታሪክ የምንረ ዳው ሀገራችን ኢትዮጵያ አስቀድሞ ከሕገ ኦሪት ኋላም ከሕገ ወንጌል ጋር የተዋወቀችው በዘረጋችው የውጭ ግንኙነት አማካይነት እንደሆነ ነው፡፡

I. የአገልግሎት ጉዞ ከትላንት እስከ ዛሬ
ቤተ ክርስቲያኗ እንደ መንፈሳዊ ተቋም ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በዝርወት ያደረገችውን እንቅስቃሴ እንደሚከተለው በወፍ በረር በክፍል በክፍል እናየዋለን፡፡

1. በመካከለኛው ምሥራቅ   
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭው ዓለም ካላት ሐዋርያዊ ጉዞ ታሪክ ሰፋ ያለውንና ቀዳሚውን ምዕራፍ የሚወስደው በመካከለኛው ምሥራቅ የጻፈችውና ያጻፈችው ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ኢትዮጵያ ከአካባቢው ሀገራት ጋራ ካላት መልክአ ምድራዊ መቀራረብ እንዲሁም የባሕልና የእምነት መዛመድ የተነሣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በዚህ አካባቢ ያደረገችው እንቅስቃሴና አስቀምጣ ያለፈችው የታሪክ አሻራ በወግ አልተጠናም፡፡ የሆነው ሆኖ የሚታወቀውን እንቅስቃሴዋን በሀገራቱ በመከፋፈል ለማየት እንሞክር፡፡

1.1 በኢየሩሳሌም
ኢትዮጵያ እምነትን በሚመለከት ከኢየሩሳሌም ጋር ያላት ግንኙነት ከንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንደሚሔድ ተመልክተናል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሀገራችን ከእስራኤል ጋር ባላት ቅርርብ መሠረት በተለያዩ ጊዜ ያት ልዩ ልዩ ገዳማትን በማቋቋም ስታገለግልና ስትገለገል ቆይታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በኢየሩሳሌም የራሷ ሀገረ ስብከት ያላት ሲሆን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የበላይ ጠባቂነት የሚተዳደሩ ሰባት ቅዱሳት መካናት አሏት፡፡

1.2 በግብፅ
ቤተ ክርስቲያኗ ከምሥረታዋ ጀምሮ ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ከሆነችው የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራት፡፡ ለ1600 ዓመታት ያህል ግብፃውያን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገራችን በመምጣት ቤተ ክርስቲያኗን መርተዋል፡፡ የዚያኑ ያህል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና አባቶችም ወደ ግብፅ እየሔዱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከሐዋርያዊ አገልግሎቷ መካከል ለግብፃውያኑ ስለእምነት ነፍስን አሳልፎ መስጠት /ሰማዕትነት/ ተጠቃሽ ነው፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም ወደ ግብፅ በመሔድ ልዩ ልዩ ተጋድሎ ሲፈጽም ቆይቶ መነኮሳትን ለማጥፋትና ገዳማቸውን ለማቃጠል አረማዊ ሠራዊት በመጣ ጊዜ ከግብፃውያኑ ቀድሞ ሰማዕትነት ተቀብሏል፡፡ ይህ አባት ሰማዕትነትን እንዲቀበሉ ያጸናቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሐዋርያ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ የዚህ ሐዋርያ ተግባር ተሰዐቱ ቅዱሳንን ወደ ኢትዮጵያ እንደሳበ በስፋት ተመዝግቦ የሚገኝ ታሪክ ነው፡፡

በ11ኛው መ.ክ.ዘ. በአስቄጥስ በረሃ በሚገኘው ዮሐንስ ሐፂር ገዳም ውስጥ የኢትዮጵያውያን መነኮሳት እንደነበሩ፤ በ1330 በ1330 አቡነ ብንያም 2ኛ የተባሉት የግብፅ ፓትርያርክ የዮሐንስ ሐፂርን ገዳም በጎበኙ ጊዜ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያን መነኮሳት በዝማሬ እንደ ተቀበሏቸው፣ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በገዳመ አስቄጥስ ጉብኝታቸው ወቅት በገዳመ ዮሐንስ ሐፂር ቆይታ ማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕል በ1517 ዓ.ም በአቡነ መቃርዮስ ገዳም ለጎብኝዎች ማረፊያ በተሠራው ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ መገኘቱ፤ እንዲሁም በግብፅ ውስጥ ዴር አል ሱርያን ተብሎ በሚታወቀው በሶርያውያን ገዳም ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ይኖሩ እንደ ነበርና አንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት እንዳቋቋሙ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በደቡብ ግብፅ በሚገኘው የቁስቋም ገዳም ከ14ኛው እስከ 17ኛው መ.ክ.ዘ. ድረስ ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ገዳም ነበራቸው፡፡ በዚህ ዘመን የተጋድሎን ሕይወት ለግብፃውያኑ ካስተማሩት ኢትዮጵያ ውያን አበው መካከል አቡነ አብደል ጣሉት አል ሐበሽና አቡነ አብደል መሢሕ /ገብረ ክርስቶስ/ በመባል የሚታወቁት ሁለት አበው ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ግብፅ በስደት በመግባታቸው በግብፅ የአባስያ ሰንበት ት/ቤት አቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

1.3 በሀገረ ናግራን
በዛሬዋ የመን ደቡብ ዓረቢያ ይገኝ የነበረ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሲሆን በዚህ ቦታ ቤተ ክርስቲያን ለ300 ዓመታት አገልግላለች፡፡ በዚህ አካባቢ ጻድቁ ዐፄ ካሌብ በአይሁድና አረማውያን እንግልት የደረሰባቸውን ክርስቲያኖች በማዳን ታላቅ ተጋድሎ ከመሥራታቸውም ባሻገር አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀው ቤተ ክርስቲያኗ የተገፉትን በመጠበቅ የተበተኑትን በመሰብሰብ በኩል ሰፊ አገልግሎት እንድትሰጥ አድርገው ተመልሰዋል፡፡  

1.4 በሶርያ
በዚህ አካባቢ ቤተ ክርስቲያናችን የሰጠችው ሰፊ አገልግሎት በወግ ስላልተጠና ሰፊ ሐተታ ማቅረብ ባይቻልም ዛሬም ድረስ ሙሴ አል ሐበሻ በመባል የሚታወቀው ገዳምና የዐፄ ገብረ መስቀል ልጅ አባ ሙሴ እንደ መሠረተው የሚነገረው ገዳም መገኘቱ ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው ያላትን ታሪካዊነትና ጥንታዊነት ይመሰክራል፡፡  

1.5 አርመን
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ኤዎስ ጣቴዎስ፣ አባ ባኪሞስ፣ አባ መርቆ ሬዎስና አባ ገብረ ኢየሱስ የተባሉ ደቀ መዛሙርታቸውን አስከትለው ግብፅ ወርደው የግብፁን ፓትርያርክ አቡነ ብንያምን አነጋግረው ወደ ኢየሩሳሌም ከሔዱ በኋላ በአርመን በተለይም ዛሬ ቱርኮች በያዟት ሲሲሊያ በተባለች ቦታ ለ14 ዓመታት ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡   

1.6.  በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ
ቤተ ክርስቲያናችን ጥንት ቀይ ባሕርን ተሻግራ በመካከለኛው ምሥራቅ የሰጠችውን አገልግሎት በዚህ ዓይነት ካየን ዘንድ በአሁኑ ወቅት በየመን፣ በሰንዓ፣ በዓረብ ኢምሬቶች፣ በሊባኖስ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ተቋቁመዋል፡፡ በዓረብ ኢምሬቶች ውስጥ በሻርጂያ፣ ዱባይ፣ አቡዳቢ እና አል ዓይን ከተሞች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት እንቅስቃሴው ተጀምሯል፡፡  

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 19 ከሰኔ 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.
abune endrias

አቡነ እንድርያስ ገዳም/አቡነ እንድርያስ ዋሻ

ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አባላት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ሰብከቶች በመንቀሳቀስ የአድባራትና ገዳማት እንቅስቃሴዎችን ቃኝተን  ከተመለስን ሰነባበትን፡፡ ክፍል ስድስት ድረስ ጸበል ጸዲቅ በሚል ርዕስ ስናቀርብ መቆየታችን ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ቀጣዮቹን ክፍሎች ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡  

የቴሌቪዥን ክፍል አዘጋጁ ቶማስ በየነ ከቪዲዮ ካሜራ ባለሙያው ሙሉጌታ ቢሆነኝ እኔን ጨምሮ ሊቀ መንኮራኩር ነብያት መንግሥቴ /ማዕረግ የራሳችን/ ሾፌራችን አብራሪነት ከአዲስ ዘመን ከተማ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ወደ አቡነ እንድርያስ ዋሻ ገሰገስን፡፡

የአስፋልቱን መንገድ አገባደን ኮሮኮንቹን ጥቂት ወደ ቀኝ ታጥፈን እንደተጓዝን ከፊት ለፊታችን እንደ ጦር የሾሉ ንጣፍ ድንጋዮች አጋጠሙን፡፡ ሊቀ መንኮራኩር ነብያት መኪናውን በንዴት አቁሞ “እንዴት በዚህ መንገድ ላይ ሂድ ትሉኛላችሁ?`ለመኪናው አስቡ እንጂ!” በማለት ከመኪናው ወርዶ በኩርፊያ ከፊት ለፊት ከሚታየው ትልቅ ድንጋይ ላይ ቁጭ አለ፡፡

ያለን አማራጭ በእግር መጓዝ ስለነበር ለቪዲዮ ቀረጻ የሚያገለግሉንን መሣሪያዎች ከመኪናው ላይ አውርደን በመከፋፈል ተሸክመን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ ከአርባ ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ አቡነ እንድርያስ ዋሻ ደረስን፡፡  የአቡነ እንድርያስ ገዳም ከአዲስ ዘመን ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ ከተራራ ሥር የሚገኝ የዋሻ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በአካባቢው በተለምዶ አቡነ እንድርያስ ዋሻ በመባል ይታወቃል፡፡

abune endriasገዳሙ አራት በሮች ሲኖሩት እያንዳንዳቸው ከአንድ  ወጥ እንጨት ተጠርበው የተሠሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ደረጃና የበሩ መቃን በጣና ደሴት ውስጥ ከሚገኙት ከደብረ ሲና ማርያም፤ ከደብረ ገሊላ ኢየሱስ አቡነ ዘካርያስ ገዳም፤ ማን እንደ አባ ያሳይ መድኀኔዓለም ገዳም፤ . . . ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ገዳሙ ምንም ዓይነት እድሳት ያልተደረገለት ሲሆን ጥንታዊነቱን ጠብቆ የሚገኝ የዋሻ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡  

ቀሲስ ቢራራ በላቸው ይባላሉ፡፡ የገዳሙ አገልጋይና ቁልፍ ያዥ ናቸው፡፡ ስለ ገዳሙ ካጫወቱንና በገዳሙ ውስጥ ከሚገኘው ከአቡነ እንድርያስ ገድል ካገኘነው በጥቂቱ ላቅርብላችሁ፡፡

ቦታው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ899 ዓ.ዓ. በዐፄ ባዚን ዘመነ መንግሥት የተመሠረተና የአካባቢው ሰዎች በእንጨት ምስል ቀርጸው ጣዖት እያመለኩ ቆይተውበታል፡፡ ለ440 ዓመታትም የኦሪት መሥዋዕት ሲሠዋበት የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ዋሻው ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ባልና ሚስት  ዘንዶዎችን እርጎ እየመገቡ ያመልኳቸው እንደነበር በገዳሙ ውስጥ የሚገኘው ገድለ አቡነ እንድርያስ ይገልጻል፡፡

በሩን አልፈው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሰፊውን ቅኔ ማኅሌት ያገኛሉ፤ ከፊት ለፊት ቅድስትና መቅደሱ፤ እንዲሁም በትልቁ የተሳሉ የአቡነ እንድርያስ ስዕሎች ጎልተው ይታያሉ፡፡ በቤተ መቅደሱ ግራና ቀኝ ሰልፋና ደፈር በተባሉ ሰዎች በጥርብ ድንጋይ የተከለሉ ቦታዎች አሉ፡፡ /ሰልፋና ደፈር የዘንዶዎቹ ቀላቢዎች/ እንደነበሩ ገድለ አቡነ እንድርያስን በመጥቀስ አባቶች ይናገራሉ፡፡

ገዳሙ ከክርስቶስ ልደት በኋላም የአካባቢው ሕዝብ ዘንዶዎቹን በማምለክ የቆየ ሲሆን አቡነ እንድርያስ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት በደቀመዛሙርትነት ተመርጠው ምድረ እንፍራንዝ /የአሁኑ ሊቦ ከምከም ወረዳ አካባቢ/ ሄደው ክርስትና እንዲያስተምሩ፤ ህዝቡንም እንዲያጠምቁ ተልከዋል፡፡

አቡነ እንድርያስ ተልእኳቸውን ለመፈጸም ወደ አካባቢው ሲመጡ ረድአቸውን አቡነ ቶማስን አስከትለው ስለነበር አካባቢውን እንዲቃኙና ለጸሎabune endrias 2ት የሚመች ቦታ እንዲፈልጉ ላኳቸው፡፡ ይህ ዋሻ በአቡነ እንድርያስ ረድእ በነበሩት በአቡነ ቶማስ አማካይነት የተገኘ ሲሆን ዘንዶዎቹን ሲመለከቱ በመፍራታቸው ቦታው እንደማይሆናቸውና የዘንዶዎቹን አስፈሪነት ለአቡነ እንድርያስ ይገልጹላቸዋል፡፡ አቡነ እንድርያስም “በእግዚአብሔር ኃይል እናሸንፋቸዋለን” በማለት መጥተው በመስቀላቸው በማማተብ በእግዚአብሔር ስም ይገስጿቸዋል፡፡ በዚህ ቅጽበት አቡነ እንድርያስ የያዙት መስቀል ከመሬት ወድቆ የቀኝ በኩል ክንፉ በመሰበሩ ወደ እግዚአብሔር ቢጸልዩ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንደነበረ አድርጎ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዘንዶዎቹ አንዱ ከአካባቢው ማዶ ተምዘግዝጎ ግራርጌ ጉበያ ማርያም ከሚባል ቦታ ላይ ወድቋል፡፡ አንደኛው ግን እስከ ዛሬ ድረስ የደረሰበት ባይታወቅም ወደ ዋሻው ውስጠኛ ክፍል ገብቶ እንደቀረ ይነገራል፡፡

አቡነ እንድርያስ ገዳሙን አቅንተው የአካባቢው ምእመናንን ክርስትና በማስተማር ታላቅ ተድጋሎ የፈጸሙበት ቅዱስ ስፍራ ነው፡፡ ወደ ገዳሙ በተአምራት አብረዋቸው የመጡ አራት በግምት አንድ ሜትር ቁመት ያላቸውና ከ20 እስከ አሥራ አምስት ሣንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው ድንጋዮች መካከል ሁለቱ በደወልነት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ሲደወሉ ወፍራምና ቀጭን ድምጽ ስለሚያወጡ የወንድና የሴት ደወሎች ይባላሉ፡፡ በአገልግሎት ወቅት ዋሻው ድምጽ እያስተጋባ ስለሚያስቸግር አቡነ እንድርያስ ገስጸውት እስከ ዛሬ ድረስ ዋሻው ምንም ዓይነት ድምፅ አያስተጋባም፡፡

በገዳሙ ውስጥ ዜና ማርያም የተባለችው ቅድስት እናት ለ25 ዓመታት በጸሎት ተወስና ቆይታበታለች፡፡ ከእንጨት ተፈልፍሎ በቁመቷ ልክ በተሠራ ገንዳ ውስጥ ገብታ የገንዳውን ግራና ቀኝ በደረቷ አቅጣጫ በመብሳት በጠፍር በማሰር ትጸልይ ነበር፡፡/ ዜና ማርያም ትጸልይበት የነበረው የእንጨት ገንዳ ዛሬም በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡/

በገዳሙ ውሰጥ በጥንቃቄ ጉድለት እየተበላሹ የሚገኙት ቅርሶች እንደ አልባሌ እቃዎች ተጥለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ዘንዶው እርጎ ይጠጣበት የነበረው ገንዳ፤ የዜና ማርያም መጸለያ ገንዳ፤ በእንጨት የተሠራ የኦሪት መሠዊያ፤ የመሥዋዕተ በግዕ ሥጋ ማስቀመጫ፤ የደሙ ማኖሪያ፡ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ለገዳሙ ከሰጧቸው 6 ነጋሪቶች መካከል ሁለቱ፤  ብዛት ያላቸው የሰው አጽሞች ይገኛሉ፡፡ ከአጽሞቹ መካከል አንዱ ሙሉ ለሙሉ ሳይፈርስ ከራስ ቅሉ እስከ እግር ጥፍሩ በዘመናዊ ሳጥን ተደርጎ ከላይ በመስታወት ታሽጎ ይታያል፡፡ የአጽሞቹን እድሜ መገመት እንደማይቻልና ቀድሞም እንደነበሩ ቀሲስ ቢራራ በላቸው ይገልጻሉ፡፡

የአቡነ እንደርያስ የእጅ መስቀል በገዳሙ ውስጥ በቅርስነት ተጠብቆ ይኖር እንደነበር፤ ብዛት ያላቸው ምእመናን በመስቀሉ ታሽተው ከያዛቸው ደዌ ይድኑ እንደነበር ቀሲስ ቢራራ በላቸው የዐይን ምስክር እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በአንድ ግለሰብ የአቡነ እንድርያስ መስቀል መዘረፉንና የግለሰቡ ማንነት ታውቆ ክስ ተመሥርቶበት በቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ ገልጸውልናል፡፡ የአቡነ እንድርያስን ዋሻ ቆይታችንን አጠናቀን ስንወጣ የገዳሙ አበምኔት የክሱን ሁኔታ ለመከታተል ከሔዱበት ሲመለሱ አግኝተናቸው ነግረውናል፡፡

abune endrias 1ገዳሙ ለስርቆት የተጋለጠ በመሆኑ የገዳሙ ጥንታዊ መጻሕፍት ተሰብስበው በአንድ ታማኝ በሆነ ግለሰብ ቤት ውስጥ እንዲቀመጥ መደረጉንም ቅርሶቹን ለማየት በጠየቅንበት ወቅት ከተሰጠን ምላሽ ለማወቅ ችለናል፡፡ የብራና መጻሕፍት ገድለ ሠማእታት፤ ስንክሳር የዓመት /2/፤ ጸሎተ እጣን፤ ግንዘትና . . . ሌሎችም ንዋያተ ቅዱሳት በዚሁ ታማኝ ነው በተባለው ሰው እጅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በየዓመቱም ቆጠራ እንደሚካሔድ በስፍራው ከነበሩት አባቶች ተገልጾልናል፡፡

ምእመናን ተጠምቀው ከተያዙበት ደዌ የሚፈወሱበት ጸበል ከገዳሙ በስተ ደቡብ ይገኛል፡፡ ጸበሉ በምንጭነት የሚፈልቅ ሲሆን ምንም ዓይነት ከለላ ስላልተደረገለት ለከብቶችና ለአራዊት የተጋለጠ ነው፡፡

የኢየሱስ፤ የቅዱስ ሚካኤልና የአቡነ እንድርያስ ታቦታት፤ እንዱሁም የአቡነ እንድርያስ መቃብር በዚሁ ዋሻ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አቡነ እንድርያስ ግንቦት 20 ቀን 1246 ዓ.ም. ወደ ገዳሙ እንደገቡ ገድላቸው የሚገልጽ ሲሆን ዓመተ ምሕረቱን ባይገልጽም ጳጉሜ 3 ቀን እንዳረፉ ይጠቅሳል፡፡ገዳሙ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ የሌለው ሲሆን አገልጋዮቹ የራሳቸውን የእርሻ መሬት እያረሱ በሚያገኙት ይተዳደራሉ፡፡

ስዱዳን ለስዱዳን

ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ባለፈው ጽሑፌ በገባሁት ቃል መሠረት በባዕድ ምድር የሚኖሩ ወገኖች፤ የስደት ሕይወትን ከጀመሩበት አንሥቶ የጠበቁትን በማጣታቸው ችግር ውስጥ የገቡትን ወገኖቻቸውን እንዴት መርዳት እንዳለባቸው ለመጻፍ አሳቦቼን እያብላላሁ ነበር፡፡ ግንቦት ሃያ ቀን ምሽት እኔና ቤተሰቤ አልፎ አልፎ በምናየው የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ ቃለ ምልልስ ተመለከትኩ፡፡ ቃለ ምልልሱን ያደረገችው በጣቢያው «ሄለን ሾው» የተሰኘ ሳምንታዊ ፕሮግራም ያላት ሄለን አሰፋ ነበረች፡፡ የዕለቱን ውይይት ያደረገችው ትእግሥት ከተባለች በመካከለኛው ምሥራቅ ነዋሪ ከሆነች ኢትዮጵያዊት ጋር ነበር፡፡ ትዕግሥት በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ትገኛለች፡፡

እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊት ወጣት ሠርታ ለመለወጥና ቤተሰቦቿን ለመለወጥ ወደ ዐረብ አገር ተሻግራ ለዓመታት የቆየች ናት፡፡ ትዕግሥት ከሄለን ጋር ባደረገችው ውይይት እንደገለጸችው ወደ የመን ከተሻገረች በኋላ እንደ አብዛኛዎቹ እኅቶቻችን በሰው ቤት ተቀጥራ ብዙ ችግሮችን አልፋለች፡፡ በአሠሪዎቿ ምግብ ከመነፈግና ከመራብ ጀምሮ እስከ መደብደብና መታሠር፤ በመጨረሻም እስከ መባረር ደርሶባታል፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ በዐረብ አገር የሚሠሩ እኅቶቻችንን ሥቃይ አልፋበት ያየችው ትዕግሥት ላቧን አንጠፍጥፋ ያጠራቀመቻትን ገንዘብ ይዛ በእሷ የደረሰ እንዳይደርስባቸው የኢትዮጵያውያን እኅቶቻችንን ሥቃይ ቢቻል የሚያጠፋ ባይቻል ደግሞ የሚያቃልል ድርጅት ለማቋቋም ትወስናለች፡፡ በዚህ እንቅስቃሴዋ ላይ አንድ መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገ በስደተኞች ላይ የሚሠራ ድርጅት ጋብዟት ወደ አሜሪካ እንደተሻገረች በቃለ መጠይቁ ገልጻለች፡፡

ትዕግሥት በዐረብ አገር ስለሚገኙ እኅቶቻችንና ሳይፈልጉ ስለሚወልዷቸው ሕጻናት ሥቃይ ስትገልጽ በዕንባም ጭምር ነበር፡፡ በዚያ የሚኖሩ እኅቶች በአጋጣሚ ስሕተት ወይም ተገደው የሚወልዷቸው ሕጻናት የመማርና እንደ ሕፃን የመጫወት መብት ተነፍጓቸው ከወላጆቻቸው ጋር እንደሚመቱ፣ እንደሚራቡና እንደሚታሰሩ ስትገልጽ ሐዘን በሰበረው ድምፅ በዕንባ እየታጠበች ነበር፡፡ ይህች እኅት እነዚህን በከፋ ችግር ላይ ያሉ ሕፃናትና ወላጆቻቸውን ለመርዳት በምታደርገው እንቅስቃሴ በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምን እንዲረዷት እንደምትፈልግ ተጠይቃ አጽንኦትና ትኩረት ሰጥታ የተናገረችው ከወላጆቻቸው ጋር እየተሠቃዩ ያሉ ሕፃናት መጠለያ የሚያገኙበትን፣ ተምረውና እንደ ልባቸው የሚያድጉበትን ዕድል እንፍጠር፤ ወላጆቻቸውንም እንርዳ የሚል ነበር፡፡

ይህ የትዕግሥት መልእክት የዚህ ጽሑፍም የመጀመሪያ መልእክት ነው፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ የስደት ሕይወታቸው የሠመረላቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው በልዩ ልዩ ምክንያት ተሰደው ወደሚኖሩበት አገር ሲመጡ በግልም በማኅበርም ሆነው መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ደግሞ በየሚኖሩበት አገር በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ተሰባስበው የሚገለገሉና የሚያገለግሉ ምእመናን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ የተቸገሩትን ስለመርዳት፣ ሀገርና ወገንን ስለመውደድና ስለ ፍቅር አብዝታ በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ናቸውና፡፡

ባለፈው ጽሑፋችን እንዳየነው በልዩ ልዩ ምክንያት አገር ወገናቸውን ትተው ወደ ባዕድ ምድር የሚሔዱ ወገኖች ስለሚሰደዱበት አገር ነባራዊ ሁኔታ መረጃ አይሰበስቡም፡፡ በብዛት እንደ ሚታየው ከሔዱም በኋላ በቀላሉ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያገኙበት ዕድል የላቸውም፡፡ እንዴትና የት ሥራ እንደሚያገኙ፣ ኑሮአቸው እስከሚ ስተካከልና ራሳቸውን እስከሚችሉ አገሩ ያዘጋጃቸው የዕርዳታ ዕድሎች መኖር አለመኖራቸውን፣ ቋንቋ የትና እንዴት በቀላሉ መማር እንደሚችሉ ወዘተ ቀድመው የሔዱ ኢትዮጵያውያን በግልም በማኅበርም ሆነው ለአዳዲስ ስዱዳን ወገኖቻቸው ማካፈል ይገባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በውጭው ዓለም በነበረው ቆይታ ያረጋገጠው ለአዳዲስ ስዱዳንም ሆነ እዛ በቆዩ ኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ነገር ወደፊት መሻሻል አለበት፡፡ ወገኗን ብቻ ሳይሆን ባዕዳኑን በየዘመኑ በአክብሮት እየተቀበለች፣ ከገጠማቸው ችግርም እየታደገች ከኖረችና ካለች አገር የሔዱ መሆናቸውን ሊያስታውሱ ይገባል፡፡

የስደት ሕይወት እስከሚለምዱት ድረስ ከባድ ነው፡፡ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ፣ ባሕልና ቋንቋ ተለይተው፣ ከቤተሰብ ሙቀትና ክብካቤ ርቀው የሚጀምሩት ሕይወት ነውና፡፡ በብዙ ቦታዎች እንደሚታየው በዚህ ፈታኝ ወቅት ተገቢውን ዕርዳታ ያገኙ ወገኖች በስደት ሕይወታቸው ሁሉ ከወገናቸው ርቀው የሚኖሩ፣ በመንገዳቸው እንኳን ኢትዮጵያዊ ካዩ ወይ መንገድ ቀይረው የሚሔዱ ካልሆነም ሰላምታም ሳይሰጡ የሚያልፉ፣ በጥቅሉ የተገለሉ ናቸው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ መንገዶች እንደ ሰማነው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ረጅሙን በረሐ በሕገ ወጥ መንገድ አቋርጠው፤ ከዚያም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውቅያኖስን አቋርጠው ወደ ጣልያንና ሊባኖስ ይሻገራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ከሚሔዱት ሩብ ያህል የሚሆኑት በመንገዳቸው በሚገጥማቸው አደጋ የበረሃና የውኃ ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ፡፡ እግዚአብሔር ጠብቋቸው በረሃውን አልፈው፣ ውቅያኖሱን ዘልቀው ጣልያን የሚደርሱት ወገኖች የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው እንደነበር የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አስተውሏል፡፡ ከሚገጥሟቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ በዚያ በሚኖሩ መናፍቃን የሚፈጠርባቸው ችግር ተጠቃሽ ነው፡፡ የጽሑፉ አዘጋጅ በቅርበት እንደተመለከተው በተለይ ጣልያን ያሉ ኢትዮጵያውያን ፕሮቴስታንት አዳዲስ ስዱዳን ወገኖቻችንን በልዩ መንገድ እየተቀበሉ፣ በችግራቸው እየገቡ እምነታቸውን ያስለውጧቸዋል፡፡ ከብዙ ድካምና ሰቀቀን በኋላ ወደማያውቀው አገር የገባ ሰው እንኳን በመልክ የሚመስለው ቋንቋውን እያወራ ልርዳህ ብሎ የቀረበው ሰው አግኝቶ ማንንም ቢሆን መቀበሉ አይቀርም፡፡

በዚህ የተነሣ በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ተወልደው የእናት ቤተ ክርስቲያንን ጡት እየጠቡ ያደጉ ወገኖች፤ በደጇ ተመላልሰው ዕንባቸውን እያፈሰሱ ያደጉባትን ቤተ ክርስቲያን ትተው ሔደዋል፡፡ እየሔዱም ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዚያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን አስተባብራ፣ ስዱዳን ልጆቿን ተቀብላ ማጽናናትና ማስተናገድ አለመቻሏ ነው፡፡

በደሙ የመሠረታት አምላክ የተመሰገነ ይሁንና ዛሬ ቤተ ክርስቲያችን በዓለም ሁሉ የተበተኑ ልጆቿን እየተከተለች ያልደረሰችበት የዓለም ክፍል የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ይህንን ሥርጭት ያደረገችው በምናውቃቸው ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች አልፋና እያለፈች እንደሆነ ቢታወቅም ሐዋርያዊ ጉዞዋ ካለው ችግር አንጻር ሲመዘን የሚያስደስት እንጂ የሚያሳዝን አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ሁሉም ናቸው ባይባልም በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎታቸው በቤተ መቅደስ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ነገር ግን ቤተ  ክርስቲያን ሐዋርያዊ እጇ ረጅም መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም ወደ አካባቢዋ የመጡ ልጆቿን ወዳሉበት ሔዳም የመሰብሰብ አገልግሎት መፈጸም ይጠበቅባታል፡፡ ይህ ተልእኮዋ በተለይ አዲስ ስዱዳንን በመሰብሰብና ከወገናቸው ጋር እንዲተዋወቁ፣ የሀገሩን ባሕልና ቋንቋ እንዲለምዱ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በባዕድ ምድር ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ደገኛና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነ ተግባር እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸውን ዕቅድና አሠራር መዘርጋት አለባቸው፡፡

ማጠቃለያ
በጽሑፉ እንደተመለከትነው ሕይወታቸውን በስደት መሥርተው የቆዩ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው የሚመጡ ስዱዳንን በመቀበል ሊኖራቸው የሚገባቸውን ሚና በአጭሩ ተመልክተናል፡፡ ከምእመናኑም በተጨማሪ የእነሱ ኅብረት የሆነች ቤተ ክርስቲያንና አስተዳደሯ ይህንኑ ደገኛ ተግባር በመፈጸም ረገድ ልትከተለው የሚገባትን አቅጣጫ አሳይተናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ከተሰነዘሩት ጥቂት አሳቦች የበለጠ ኑሮአቸውን በስደት ካደረጉ ወገኖች ሊቀርቡ የሚችሉ አሳቦች እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡

በመሆኑም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ይህ ዓምድ የተከፈተው ከዝግጅት ክፍሉ ከሚጻፉ ትምህርቶች በተጨማሪ ኑሮአቸውን በውጭው ዓለም ያደረጉ ምእመናን የሕይወት ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን በመለዋወጥ እንዲማሩ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ወገኖቻችን ይህንን ዕድል በመጠቀም አገልግለው በረከት እንዲያገኙ ዛሬም ግብዣችንን እናስተላልፋለን፡፡
 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት 18 ከሰኔ 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.

የስደት ጦስና ተስፋ

ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ወቅቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ብላቴ የውትድርና ማሠልጠኛ ጣቢያ እንዲሔዱ የተገደዱበት ነበር፡፡ ተማሪዎቹ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ባዘዘው መሠረት ወደ ማሠልጠኛ ጣቢያው ሔደው ለወራት የውትድርናውን ትምህርትና ሥልጠና ወሰዱ፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጥበቃ ሥልጠናው አልቆ ወደ ጦር ግንባር መወሰጃ ጊዜአቸው ሲደርስ ያዘመታቸው መንግሥት በኃይል ሥልጣኑን ለቀቀ፡፡ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በአውቶቡስ ተጉዘው ብላቴ በረሃ የከተሙት ተማሪዎች መንግሥት ሲፈርስ የእነሱም ካምፕ ፈረሰ፡፡ ግማሹ ወደየመጣበት ሀገሩ፤ ግማሹ ደግሞ ከሚወዳት እናት ሀገሩ ተለይቶ ወደ ኬንያ ተሰደደ፡፡

ወደ ኬንያ ከተሰደዱት ተማሪዎች አንዱ ክብረት /ትክክለኛ ስሙን ቀይሬዋለሁ/ ነበር፡፡ ክብረት ወደ ኬንያ የተሰደደው ጠላ ጠምቀው በቆልት አብቅለው በመሸጥ ያስተማሩትንና የሚወዳቸውን እናቱን ለመለየት እየጨነቀው ነበር፡፡ ምንም እንኳን ምርጫቸው እንደ አብሮ አደግ ጓደኛቸው ክብረት ወደ ኬንያ መሔድ፤ ከዚያም አውሮፓ¬ ወይም ካናዳ ከተቻለም አሜሪካ መግባት የነበረ ቢሆንም፤ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከብዙ ድካምና ረሃብ በኋላ አገራቸው የገቡት የክብረት ሁለት የሠፈር ልጆች፤ እንደደረሱ ለክብረት እናት በማለዳ ሔደው “እትዬ አበባ /ስማቸው አይደለም/ እንኳን ደስ አለዎት እኛ ፈሪዎች ወደ አገራችን ስንመጣ ደፋሩና ነገን ያሰበው ልጅዎ ኬንያ ገባ፡፡ ራሱን ለውጦ ይለውጥዎታል” ይሏቸዋል፡፡ ይህ አባባላቸው የክብረት ጓደኞች እንዳሰቡት ለእትዬ አበባ የምሥራች አልነበረም፡፡ ድንጋጤው ኡኡታውና ደረት ድቂው ዕድሜ የጎሰመውን አካላቸውን አዝለፍልፎ ለጣላቸው እትዬ አበባ መርዶ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለእትዬ አበባ ስደት ማለት ሞት ነው፡፡ እንኳን ጠላ ጠምቀው በመሸጥ ላሳደጉት ብቸኛ ልጃቸው ለማንም ኢትዮጵያዊ ተመኝተውትም አያውቁ፡፡

ይህ በቅርቡ ሃያ ዓመት የሞላው እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ትላንት የእኛ እናቶች ስደትን እንደሞት ያዩ ነበር፡፡ ተሰደደ/ች ሲሏቸው ሞተ/ች ብለው ያለቅሱ፤ ይጮኹ ነበር፡፡ ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦም ያስተዛዝን ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተቀይሯል፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባል እንኳን ሔደ ተብሎ፤ የደስታ ድግሱ ፌስታው የሚጀመረው ገና የግብዣ ወረቀት ሲላክ ነው፡፡ የስደት ጉዞው እውን ሲሆን ቪዛ ሲመታለትማ /ሲመታላትማ/ ሰርግና ምላሽ ነው፡፡ ትላንት እነ እትዬ አበባ ልጅዎ ውጭ አገር ሔደ ሲባሉ ልባቸው በሐዘን ተወግቶ ቀሪ ዘመናቸውን በለቀሶና በቁዘማ ፈጽመው ወደ መቃብር ይወርዱ ነበር፡፡ ዛሬ እናት ወይም አባት የልጃቸውን መሰደድ በኩራትና በደስታ ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ ለዛሬው ወጣት ወንድሜ ወይም የፍቅር ጓደኛዬ ውጭ አገር ነው ማለት በኩራት የሚናገሩት ስኬት ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ) አንባብያን አሳባችሁን ስጡ፡፡

በየትኛውም መንገድ ወይም ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ትተው በስደት ሕይወታቸውን እንደሚገፉ እርግጥ ነው፡፡ ቁጥራቸው ውጭ ካሉት ወገኖቻችን ቢልቅ እንጂ የማያንስ ኢትዮጵያውያንም እነሱም ውጪ እንዳሉት እንዲሰደዱ ሲጸልዩ፣ ሲሳሉ፣ ገንዘባቸውን ሲያባክኑ፣ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሲጥሉ እንደሚኖሩ ምስክሮች ነን፡፡ “የውጭ ጉዞዬ እንዲሳካ ቤቱ መጥቼ አልቅሼ ነበር፤ ተሳክቶልኝ አሁን እዚህ እገኛለሁና እልል በሉልኝ” የሚሉ ማስታወቂያዎች በየዐውደ ምሕረቱ እንሰማለን፡፡ “ይህ ደላላ ቪዛ ሊያስመታልኝ ይህን ያህል ሺሕ ብር ሰጥቼው ካደኝ” የሚሉ ፕሮግራሞች በኤፍ ኤም ሬድዮዎቻችንም ጭምር እናደምጣለን፡፡ “ሊቢያ ለመግባት በረሃ አቋርጠው ሲጓዙ የበረሃው ዋዕይ ሕይወታቸውን ቀጠፋቸው፤ የመን ለመግባት በጀልባ ተጭነው ሲቀዝፉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ጀልባቸው በሞገድ ተመትታ በመስጠሟ ሁሉም አለቁ” የሚሉ ዜናዎች በየጊዜው እናነባለን፣ እንሰማለን፡፡ “በዚህ ዐረብ አገር ትሠራ የነበረች ኢትዮጵያዊት በአሠሪዋ አሲድ ወይም የፈላ ውኃ ተደፋባት፤ ከፎቅ ተወረወረች፤ አስከሬኗ መጣ” የሚሉ መርዶዎች መስማት ልማዳችን ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነብን) አንባብያን አሳባችሁን፤ ገጠመኞቻችሁን የደረሰባችሁን ሁሉ ወደ ዝግጅት ክፍሉ ላኩ፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያት ከሀገር ወጥተው ከውቅያኖሱ ባሻገር ከሚኖሩት ወገኖቻችን በዕውቀታቸውና በሙያቸው አገሩ ፈልጎአቸው በስኬት የሚኖሩ ያሉትን ያህል፤ ኑሮ ከሀገሩ እንግዳ ባሕልና የአየር ጠባይ የበለጠ ከብዶአቸው በምሬትና በመሳቀቅ የሚኖሩ፤ አልፎ አልፎም ራሳቸውን የሚያጠፉ እንዳሉ እንሰማለን፤ እናያለንም፡፡ ይህ ችግር በተለይ ገና የስደቱን ኑሮ አሐዱ ብለው በጀመሩት ይበዛል፡፡ ከብዙ ጸሎትና ድካም በኋላ ያሰቡት ተሳክቶ የሔዱ ወገኖች የቅርብና የልብ ወዳጅ ዘመድ ካጠገባቸው ከሌለ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው ገና እንደሔዱ የሚያጋጥማቸው ችግር ሕሊናቸውን ከመጉዳቱ ባሻገር ጠባሳው በስደት ሕይወታቸው ሁሉ ዘልቆ ኑሮአቸውን ከባድ ያደርግባቸዋል፡፡

የሥነ ልቡና ምሁራን አንድ ሰው የጠበቀውን እና የጓጓለትን ነገር ሲያጣ የሚያጋጥመውን ሥነ ልቡናዊ ስብራት ሥነ ልቡናዊ መራቆት /Psychological Crisis/ ይሉታል፡፡ በአገራቸው ምድር ሳሉ ሁሉም ለምለም ሆኖ በምናብ ይታያቸው የነበረ የባዕድ ምድር፤ ምድሩ ላይ ቆመው ሲያዩት ልምላሜው በቀ ላሉ ምግብ የማይሆን ሆኖ ሲያገኙት፤ በአጭሩና ካለ ብዙ ድካም በኪስ እንደሚታጨቅ ያሰቡት ገንዘብ ብዙ ድካምና ራስን ዝቅ ማድረግ እንደሚጠይቅ ሲረዱ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ጭንቀታቸው በርትቶም የጤና እክል ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ የጤና ችግር ደግሞ በስደቱ ምድር በጉልበታቸው ሮጠው በዕውቀታቸው ተወዳድረው ሕይወታቸውን እንዳያሻሽሉ ዕንቅፋት ይኾንባቸዋል፡፡ ለመሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን የስደትን ሕይወት ሲጀምሩ ከፍተኛ መደናገጥ፣ መታመምና አልፎ አልፎም ኅልፈተ ሕይወት የሚያጋጥማቸው ለምንድን ነው) የተወሰኑትን ምክንያቶች ከዚህ በታች እናያለን፡፡

1. የተሳሳተ መረጃ
ሀገር ቤት ያለን ኢትዮጵያውያን ስለውጭው ዓለም የምንረዳው በዋና ነት በዚያ ከሚኖሩ ወገኖቻችን ነው፡፡ ምንም እንኳን የባዕድ ሀገር ሕይወት ምን ዓይነት እንደሆነ ካዩትና ከደረሰባቸው እውነቱን የሚናገሩ ቢኖሩም፤ በአብዛኛው በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዕረፍት ወደ ሀገራቸው ሲመጡም ሆነ እዚያው ባሉበት ሆነው ለወዳጅ ለዘመዳቸው የሚያስረዱት፤ በእጅጉ እንደሚመች፣ ሰው ዐቅሙ እስካለው ድረስ ሥራ አማርጦ በመሥራት ገንዘብ እንደሚዛቅበት ነው፡፡ ለዚህ ከእውነት የራቀ ምስክርነታቸው ማስረጃ ለማድረግም ብዙ ደክመው /በግሌ እንዳየሁትም/ ለራሳቸው በአግባቡ ሳይመገቡና ሳይለብሱ ያጠራቀሟትን ገንዘብ ወደዚህ ሲልኩ ጥቂቷና በብዙ ድካም ያገኟት ገንዘብ በሀገራችን ምንዛሬ በርክታ ከወዳጅ ዘመድ እጅ ስትገባ የስደት ሀገሩን ለምለምነት ትሰብካለች፡፡ በፎቶ ግራፍ ተቀርጾ የሚላከው በረጅሙ ወርኃ በረዶ ወቊር የገረጣ ፊት ሀገር ቤት ለሚኖረው ሰው የባዕድ አገር ሕይወትን ምቾት የሚሰብክ ነው የሚመስለው፡፡

በሀገራችን የዲዮስጶራ ሰርግ የሚባል አለ፡፡ የዲዮስጶራ ሰርግ አንድ ወይም ሁለቱ ተጋቢዎች ከውጭ መጥተው ጋብቻቸውን የሚፈጽሙበት ሰርግ ነው፡፡ ይህንን ሰርግ ልዩ የሚያደርገው /ሁሉም ማለት አይደለም/ ወጪው በእጅጉ የበዛ፤ የሰርጉ ታዳሚዎች እስከሚሰለቻቸው ድረስ መብል መጠጡና የመናፈሻው ሥርዓት የበዛ፣ ሙሽሮች የሚሞሸሩበት መኪናም ጭምር ከሰማይ የወረዱ እስከሚመስል ድረስ ለታዳሚ ዓይን ግራ የሚያጋባ፤ በጥቅሉ “የናጠጠ” ሰርግ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ያየ ወጣት ታዳሚ በሀገሩ በድሎት የሚኖርም ቢሆን እንኳ እሱም ባሕር ማዶ ተሻግሮ በመሥራት በልጽጎ በመመለስ በተመሳሳይ ሁኔታ ማግባትን ይመኛል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የብዙዎች ዲዮስጶራ ተጋቢዎች የውጭ ሕይወት እዚህ መጥተው ሰርጋቸውን ድል ባለ ሁኔታ እንደደገሱለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ያላቸውን ካሟጠጡ በኋላ ከሌላውም ተበድረው ድል ያደርጉታል፡፡ ይህ ከእውነታ ውጭ የሆነ የዲዮስጶራ ወገኖቻችንን የውጭ አገር ገለጻና ካላቸው በላይ ገንዘብ መርጨት ሲያዩና ሲሰሙ የቆዩ ወገኖች እነሱም ዕድሉን አግኝተው ሲሔዱ፤ ያ በርቀት የሳሉት የባዕድ ምድርና ሕይወት እንዳልጠበቁት ሆኖ ሲያገኙት ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ያጋጥማቸዋል፡፡

2. የገቡት ቃል
ኢትዮጵያውያን የስደት ሕይወት እንደጀመሩ ለከፍተኛ የመንፈስ ስብራት የሚዳርጋቸው ሌላው ምክንያት ሀገራቸውን ከመልቀቃቸው በፊት ለወዳጅ ዘመዳቸውና ጓደኛቸው ገብተውት የሚሔዱት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ከላይ ባየነው መልኩ ወደ ውጭ እንደሔዱ በገንዘብ ባሕር ላይ የሚሰጥሙ ይመስላቸውና ለቪዛው ፕሮሰስና ለትራንስፖርት እንደሁም ለሽኝት ድግስ ብዙ ብር ይበደራሉ፡፡ ወደውጭ ለሚሔድ የሚያበድር አይጠፋምና፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አብረዋቸው ሲቸገሩ ለኖሩት ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ከፍተኛ የዕርዳታ ተስፋ ይሰጣሉ፡፡

ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው የስደት ሕይወት እንደተጀመረ ከተሻለ ኑሮ ላይ አያፈናጥጥም፡፡ ተሰዳጁ ሥራ ያዘም አልያዘ ከገባበት ቀን ጀምሮ ውጭ ስላለው ሕይወት አስቀድሞ በመረዳት ራስን አሸንፎ መሠረት ለማስያዝ ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ በዚህ ስደት ተሰዳጁ ሀገሩ ትቶት የመጣውን ቃልኪዳን እያሰበ፤ አብረውት ሲቸገሩ የነበሩ ቤተሰቦቹን ጉጉትና ጠኔ በሕሊናው እየሳለ ይጎዳል፡፡ ጉዳቱም የመንፈስ ስብራት ይሆንና ሠርቶ ሊያገኝበት ከሀገሩ ይዞት የሔደው ጉልበት እየደከመ በሽታ ላይ ይወድቃል፡፡ ይህ ጉዳት እንዲደርስበት ያልፈለገ ደግሞ ገንዘብን በአቋራጭ ለማግኘት ሲል ኢትዮጵያዊ መልኩና የሀገሩ ሕግ በማይፈቅድለት ተግባር ተሠማርቶ የባሰ ችግር ላይ ይወድቃል፡፡

3. አለመዘጋጀት
እንኳን ለቀዋሚ ኑሮ ይቅርና ለጊዜያዊ ዕረፍት ወይም ሥራ የሚደረግ ጉዞ ከፍተኛ ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡ ከዝግጅቶቹ ውስጥ ስለሚሔዱበት ሀገር ባሕል፣ ቋንቋና አሠራር ማወቅ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው በርካታ ወገኖቻችን ወደ ውጭ የመሔድ ዕድል ሲያጋጥማቸው፤ ለራሳቸውና በዚያ ለሚያገኟቸው ዘመ ዶች የሚያካፍሉት ሽሮና በርበሬ እየሸ ከፉ በአውሮፕላን ገብተው የሚበሩባትን ቀን በጉጉት ከመጠበቅ ባለፈ ሁኔታ ዝግጅት አያደርጉም፡፡ በዚህም የተነሣ እንደሔዱ ከፍተኛ ድንጋጤና ሥነ ልቡናዊ ጫና ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሥራ ለመፈለግ የሀገሩን ቋንቋ በሚገባ አላወቁም፣ በነጻነት ለመንቀሳቀስ አስቀ ድመው ስለሀገሩ አነዋወርና ሕግ አላጠኑም፡፡ ይህ ዓይነት ችግር በተለይ ኢትዮጵያውያን በማይበዙባቸው ሀገራት ጎልቶ ይታያል፡፡

ኑሮአቸውን በስደት የሚጀምሩ ወገኖች ለወዲያው ለሚያጋጥማቸው የሕሊና ስብራት ምክንያቶቹ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህል ከተጠቁሱት የምንገነዘበው ግን የስደት ሕይወት ሀገር ላይ ተቀምጦ እንደሚያስ ቡት የተመቻቸ /የተደላደለ/ እንዳልሆነና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንዳሉ በመረዳት ተዘጋጅቶ መሔድ እንደሚገባ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዕትም በተለይ የስደት ሕይወትን የሚመሩ ወገኖች ከሚደርስባቸው ሥነ ልቡናዊ ስብራት ለመታደግ በዚያ ካለችው ቤተ ክርስቲያንና ምእመናኗ ምን ይጠበቃል) የሚለውን እንመለከታለን፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ምእመናን የሕይወት ተሞክሯችሁንና ለሌላው ትምህርት ይሆናል የምትሉትን በዝግጅት ክፍሉ የስልክና የፖስታ ሳጥን ቁጥር፣ በኢሜይል እንዲሁም በአካል እየመጣችሁ እንድታደርሱን በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡

መፍትሔዎች፡-

  1. በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለሚኖሩበት ምድርና ሕይወት ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እውነቱን በአገር ቤት ለሚኖሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ይግለጹ፡፡ ሥራ ለማግኘት ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዙ፣ ከብዙ ድካም በኋላ ስለሚያገኙት ገንዘብ፣ በወር ስለሚሸፍኑት ቢል ብዛት፤ ስለአየር ጠባዩ፣ ስለ አሠሪና ሥራ ግንኙነት፣ ስለ ቤተሰብ ሕይወት ወዘተ. . . በግልጽ ቢናገሩ ወገኖቻችን በመጓጓትና ትልቅ ነገርን በመጠበቅ ሔደው ከመደንገጥ፣ ከበሽታ ነጻ ይሆናሉ፡፡

  2. በተለያየ ምክንያት ሀገራቸውን ለቀው የሚሔዱ ሰዎች በተቻላቸው መጠን የሚሔዱበትን ሀገር እንደሀገራቸው ሁሉ የራሱ ተግዳሮት የሌሉት፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደሆነ አድርገው መሣል የለባቸውም፡፡ ይህንን ካደረጉ ለቀሪ ዘመዶቻቸው የሚገቡት ቃል አይኖርም፡፡ ቢኖርም ሊያጋጥም የሚችለውን ተግዳሮት ግንዛቤ ውስጥ የከተተ ይሆናል፡፡

  3. ኑሮአቸውን በባዕድ ምድር ለማድረግ ወስነው የሚሔዱ ወገኖች አስቀድሞ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ማድ ረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እዚያ ሲሔዱ ከሚበሉትና ከሚጠጡት በተጨማሪ ሀገሩ ምን ዓይነት የአየር ጠባይ አለው) ቋንቋውን በሚገባ አውቀዋለሁን) ሕግጋቱና የአነዋወር ይትበሃሉ ሁሉ ምን ይመስላል) ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መያዝ /ማዘጋጀት/ ይገባቸዋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር  

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት 17 ከግንቦት 16-30 ቀን 2005 ዓ.ም.

በባዕድ ምድር እስከመቼ?

ሰኔ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

የስምዐ ጽድቅ ዝግጅት ክፍል በዝርወት ለሚኖሩት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የእናት ቤተ ክርስቲያናቸውን አስተምህሮ፣ ምክርና ተግሳጽ ይሰሙ ዘንድ ዓምድ በከፈተላቸው ጊዜ፤ መጀመሪያ ወዲያውም ዓምዱን ማስተዋወቂያ  ቢሆን ብዬ የጻፍኩት ጽሑፍ ዐራት እትሞች ዘልቆ ተፈጸመ፡፡ ጽሑፉን አስመልክቶ ከተለያዩ ጓደኞቼ ካገኘሁአቸው አስተያየቶች በመነሣት እንደ አብርሃም ሁሉ የያዕቆብን የስደት ሕይወት በመመርመር ለዛሬዎቹ ስዱዳን አርኣያ በሚኾን መልኩ በአጭሩ ለማቅረብ መረጥኩ፡፡ ጽሑፉ ይኸውና፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን ኑሮአቸውን በስደት ያደረጉ ወንድሞችና እኅቶች ዕለት ከዕለት ከሚያጋጥማቸው ችግር በመነሣት ጽሑፎችን አዘጋጅተው ወደ ዝግጅት ክፍሉ በመላክ ቢማማሩ መልካም ነው፡፡

ሕይወተ ያዕቆብ
ከአያቱ አብርሃምና አባቱ ይስሐቅ ቀጥሎ ሦስተኛው የሕዝበ እስራኤል አባት /3rd Patriarch/ ተብሎ የሚታወቀው ያዕቆብ ወላጆቹ ይስሐቅና ርብቃ በጋብቻ በተጣመሩ ሃያኛው ዓመት ላይ ተወለደ፡፡ እሱ ሲወለድ አባቱ የ60 ዓመት ጎልማሳ ነበር፡፡ /ዘፍ. 25ሚ20፤ 25ሚ26/፡፡ ይስሐቅና ርብቃ በሃያ ዓመት የጋብቻ ሕይወታቸው ወልደው ለመሳም አልታደሉም ነበር፡፡ በዚህ የተነሣም የአብራካቸው ክፋይ የሆነ ፍሬ ይሰጣቸው ዘንድ አምላክን ይማጸኑ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ጩኸታቸውን ሰምቶ በርብቃ ማኅፀን ያዕቆብና መንትያው ኤሳው ተፀነሱ፡፡ ነገር ግን በልመናና በጩኸት የተፀነሱት ያዕቆብና ኤሳው ገና በማኅፀን ውስጥ ሳሉ እየተገፋፉ እናታቸውን ይሠቃዩ ጀመር፡፡ በዚህ የተሠቃየችው ርብቃ እንደ ገና ፅንሱን ወደ ሰጣት አምላክ ምሕረትን በመለመን ጮኸች፡፡ በዚህ ጊዜ በማኅፀኗ የተቀረጹ ልጆቿ እስከሚወለዱና ከተወለዱም በኋላ ዕድሜ ልካቸውን የሚጣሉና አንዱ በሌላው ላይ እየተነሣ እንደሚጥለው በራእይ ተረዳች፡፡ ይህንን ምስጢር በልቡናዋ ያዘችው እንጂ ለባሏ አልነገረችውም ነበር፡፡ ሕፃናቱ ሲወለዱ እንደተነገረው ትንቢት አንዱ ከሌላው የማይመሳሰል ሆነው ተወለዱ፡፡ በኲሩ ዔሳው እንደ ጽጌረዳ አበባ ሰውነቱ ሁሉ ቀይና ጸጉራም ሆኖ፣ በኋላ የተወለደው ያዕቆብም የወንድሙ የዔሳውን እግር ይዞ ወደዚህ ዓለም መጡ፡፡ የኋለኛው በዚህ ግብሩ ያዕቆብ ተብሏል፡፡

 

ያዕቆብ ብሂል አኀዜ ሰኰና አዕቃፄ ሰኰና ማለት ነው፤ ሲያድጉም ዔሳው የበረሃ ሰው አርበኛ አዳኝ ሲሆን ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበር፤ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር፡፡ ዔሳው አድኖ በሚያመጣለት ምግብ የተነሣ የአባቱን ከፍ ያለ ፍቅር ሲያገኝ ያዕቆብ ደግሞ ከቤት ውሎ እናቱን ስለሚያጫውትና ስለሚታዘዛት የእናቱን ከፍ ያለ ፍቅር አገኘ፡፡ አባታቸው ይስሐቅ በእርጅና ምክንያት ጉልበቱ ደክሞ ዓይኑ ደግድጎ ከቤት በዋለ ጊዜ አንድ ቀን የሚወደውን ልጁን ዔሳውን እኔ እንደ ምወደው አድርገህ የምበላው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ ሳልሞት ሰውነቴ /ነፍሴ/ እንድትመርቅህ /እንድትባርክህ/ ወደ ዱር ሄደህ አድነህ አምጣልኝ አለው፡፡ ይህንን የሰማች ርብቃም የምትወደውን ልጇን ያዕቆብን እንደ ዔሳው አስመስላ አልብሳ አባቱ ይስሐቅ የጠየቀውን ምግብ እንደሚወደው አድርጋ አዘጋጅታለት ይዞ ወደ አባቱ እንዲገባና የአባቱን በረከት እንዲቀበል የምትችለውን ሁሉ በማድረግ አዘጋጀችው ዔሳውን መስሎ ወደ አባቱ በመግባትም የአባቱን በረከት ለመቀበል በቃ፡፡ በረከት በመቀበል እንደቀደመው የተረዳው ወንድሙ ዔሳውም “በጽድቅ ተሰምየ ያዕቆብ እስመ ፪ ጊዜ አዕቀጸኒ  ቀዳሚ ብኲርናየ ነሥዓኒ ወናሁ ዮምኒ ወዳግመ በረከትየ፤ ያዕቆብ በእውነት ስያሜውን አገኘ፡፡ አንደኛ ብኲርናዬን ሁለተኛ በረከቴን ወስዶብኛልና ሁለት ጊዜ አሰነካክሎኛ” በማለት ምሬቱን ገልጿል፡፡ /ዘፍ.27፥6/ ያም ሆነ ይህ ሁሉም በፈቃደ እግዚአብሔር የተከናወነ ሆነ፡፡

ምክንያተ ስደቱ
ለያዕቆብ ስደት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ትዳር ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ አባቱ ይስሐቅ ያዕቆብን ጠርቶ መርቆ “ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስት አታግባ፡፡ ተነሥተህ በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል ወደሚኖር ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሒድ፡፡ ከናትህ ወንድም ከላባ ልጆች ሚስት አግባ ብሎ አዘዘው፡፡ ፈጣሪዬ ካንተ ጋራ በረድኤት ይኑር፡፡ ያክብርህ ያግንህ ያብዛህ፡፡ ብዙ የብዙ ወገን ያድርግልህ አለው፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ምድር ከነዓንን ትወርሳት ዘንድ የአባቴ የአብርሃምን በረከት ይስጥህ፡፡ ካንተ በኋላ ላሉ ለልጆችህም ይስጣቸው” አለው፡፡ /ዘፍ.28፥1-5/

ከያዕቆብ ሕይወት ምን እንማራለን?
ሀ. የእግዚአብሔርን ውለታ እያሰቡ ፍቅርን በሥራ መግለጽ
ያዕቆብ በስደት ሕይወቱ እግዚአብሔር በተለያዩ ጊዜያት እየተገለ ጠለት መክሮታል፤ አበረታቶታል፤ ሲያጠፋም ገሥጾታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ “ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስት አታግባ፤ ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሒድ፤ ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክም ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ እንድትሆን ይባርክህ ያፍራህ ያብዛህ ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን እግዚአብሔርም ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአብርሃምን በረከት ለአንተ ይስጥህ ለዘርህም እንዲሁ እንደ አን” ብሎ ምክር ያዘለ ትእዛዝ በሰጠው መሠረት ከቤርሳቤህ ተነሥቶ የርብቃ ወንድም ላባ ወደ ሚገኝበት በሁለቱ ወንዞች መካከል ወደምትገኝ ወደ ሶርያ ጉዞ ጀመረ፡፡ ሲጓዝ ውሎ ሎዛ ተብላ ትጠራ ከነበረች ቦታ ሲደርስ መሸበት፤ ደከመውም፡፡

 

በዚያውም ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ፡፡ በሕልሙም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ በመሰላሉም የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡበትና ሲወርዱበት ተመለከተ፡፡ በመሰላሉ ላይ የቆመው እግዚአብሔርም “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤ ይከብራሉ፡፡ ያዕቆብን ያከበረ ያክብርህ እየተባባሉም ይመራረቃሉ፡፡ ካንተም በኋላ በልጅህ ይመራረቃሉ፡፡ በምትሔድበት መንገድ ሁሉ በረድኤት ጠብቄ ወደዚህ አገር እመልስሀለ” አለው፡፡ /ዘፍ.28፥13-ፍጻ/ 

ይህ አምላካዊ ቃል ኪዳን ከወላጅ ከዘመድ ተለይቶ የስደት ጉዞ ላይ ለነበረው ያዕቆብ ታላቅ ቃል ኪዳንና የምሥራች ነበር፡፡ በመሆኑም ያዕቆብ ይህንን ቃል ኪዳን ለሰጠው አምላክ ውለታውን እያሰበ ፍቅሩን ለመግለጽ ፈጣን ነበር፡፡ ያ ታላቅ ሕልም ያየበት ሌሊት ሲነጋ ተነሥቶ የእግዚአብሔር ስም ማስጠሪያ ይሆን ዘንድ ተንተርሶት ያደረውን ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤ በላዩም ዘይት አፈሰሰበት፡፡ ስሙንም ቤቴል ብሎ ጠራው፤ ቤተ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ በዚህም ብቻ አላበቃም፡፡ ስእለትም ተሳለ፡፡ “እግዚአብሔር በረድኤት ከኔ ጋራ ካለ በምሔድበትም ሀገር ሁሉ በረድኤት ከጠበቀኝ የዕለት ጉርስ ያመት ልብስ ከሰጠኝ ወደ አባቴም ቤት በደኅና ከመለሰኝ እግዚአብሔር ፈጣሪዬ ይሆንልኛል አለ፡፡ ፈጣሪውስ የግድ ፈጣሪው ነው እወደዋለሁ አመልከዋለሁ ሲል ነው፡፡ አንድም ይህን የሰጠኝ እግዚአብሔር አምላኬ ነው ማለት እሱን ብቻ አመልካለሁ ሌላ አላመልክም ማለት ነው፡፡ ይህችም የተከልኋት ደንጊያ የእግዚአብሔር ማደሪያ ትኾንልኛለች አለ፡፡ የሰጠኸኝን አሥራቱንም ሁሉ ላንተ ካሥር አንድ እሰጣለ“ አለ፡፡/ዘፍ.28፥20-ፍጻ/

በስደት በምንኖርበት ጊዜ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ የቸርነት ሥራውን ይሠራልናል፡፡ በበረከቱ ይጎበኘናል፡፡ በዚህ ጊዜ አባታችን ያዕቆብ እንዳደረገው ያንን ላደረገ እግዚአብሔር ውለታውን መክፈል ባይቻልም ፍቅራችንን በሥራ ለመግለጽ የተጋን መሆን አለብን፡፡ በያለንበት ክፍለ ሀገር ስሙ የሚቀደስበት መንግሥቱ የሚሰበክበት አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ማድረግ፤ በተቋቋመበት ቦታ የምንኖር ከሆነም እንዲጠናከሩ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር አብዝቶ ከሚሰጠን በረከትም አሥራት ማውጣት ይኖርብናል፡፡          

ለ. በስደት ሕይወት ትዕግሥት ማድረግ
አባቱ የመከረውን ምክርና የሰጠውን ትእዛዝ በመቀበል ያዕቆብ ወደ ሶርያ ሔዶ የሕይወት ጓደኛውን ራሔልን ቢያገኝም እንዳሰበው አገር አቋርጦ የመጣላትን የትዳር አጋሩን ይዞ ወደ አገሩ በቶሎ መመለስ አልቻለም፡፡ ይልቁንም አባቷ ላባ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ መሠረት ለሰባት ዓመታት የበግ ጠባቂው ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ከተሰደደ በኋላ አይቶ የወደዳትን ራሔልን በእጁ ያስገባ ዘንድ ሰባቱን ዓመት አገልጋይ ሆኖ የቆየው ያዕቆብ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ጨርሶ ልሂድ ብሎ ሲነሣ የራሔል አባት አልፈቀደለትም፡፡ ራሔልን ይዞ ለመሔድ ከፈለገ ሌላ ሰባት ዓመታትን እያገለገለ መቆየት እንዳለበት ነገረው፡፡ ያዕቆብ በተገባለት ቃል መሠረት ሰባት ዓመት ሲጠናቀቅ መሔድ ባለመቻሉ ቢያዝንም የመጣበት ዓላማ ግድ ይለዋልና ሌላ ሰባት ዓመታት ጨመረ፡፡ የእናቱ ፍቅር የወንድሙን የዔሳውን ብኲርናና ምርቃት መውሰድ እስኪያስችለው በፍቅርና በክብካቤ ያደገው ያዕቆብ ለ14 ዓመታት በግ ጠባቂ እረኛ ሆኖ በቀን ፀሐይና በሌሊት ቊር ሲሠቃይ ቢቆይም ተስፋ በመቁረጥ ተማሮ ወደ እናቱ አልሔደም፡፡ እርጅና ተጫጭኖት ሞት አፋፍ ላይ ሳለ ትቶት የመጣው አባቱ አሳስቦትና ናፍቆት ልሒድ አላለም ዓላማውን ማሳካት ነበረበትና በትዕግሥት ቆየ፡፡

ዛሬ በልዩ ልዩ ምክንያት በስደት የምንኖር ወገኖች ተወልደን ያደግንበ ትን ሀገርና ባሕል ትተን ስንመጣ ይነስም ይብዛ ይዘነው የመጣነው ዓላማ አለን፡፡ ይሁን እንጂ በስደት ሕይወት በሚያጋጥሙን ችግሮች የተነሣ ከዓላማችን የምናፈነግጥ ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የሚገቡት በዋናነት በሁለት ምክንያት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሲመጡ በአዕምሮአቸው ሥለውት የመጡት ነገርና ሲደርሱ የሚያጋጥማቸው የተለያየ መሆን ነው፡፡ ሲመጡ ውጭ አገር ገንዘብ በቀላሉ የሚታፈስ እንደሆነ አስበው ይመጡና ካሰቡት ቦታ ደርሰው ሲያዩት እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር ይደናገጡና ከሀገራቸው የወጡበትን ቀን ይረግማሉ፡፡ ተስፋም ቆርጠው ሕይወታቸውን በአግባቡ መምራት ይሳናቸዋል፡፡

ነገር ግን ከአባታችን ከያዕቆብ የስደት ሕይወት የምንማረው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ አባቱ ተነሥተህ ወደ ወገኔ ሒድና ሚስት የምትሆንህን ይዘህ ና ሲለው ምናልባት በወጣትነት አእምሮው እንደ ደረሰ በዓይኑ ዐይቶ የፈቀዳትንና የወደዳትን ይዞ እንደሚመለስ አስቦ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሶርያ ሲደርስ ያጋጠመው ሌላ ነገር ነው፤ የ14 ዓመታት የእረኝነት ሕይወት፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ደንግጦ ወይም ተበሳጭቶ ወደ አገሬ ልመለስ አላለም፡፡ በዚያው ሲቆይም ዕለት ዕለት ሲበሳጭና ተስፋ ሲቆርጥ እንደነበረ መጽሐፍ አያስነብበንም፡፡ ስለዚህ በስደት ሕይወት ስንኖር ባልጠበቅነው ሁኔታ በሚያጋጥመን ችግር የተነሣ ሳንሳቀቅ ከሀገራችን ስንወጣ ይዘነው የወጣነውን ዓላማ አጽንተን ለስኬታማነቱ እየታገልን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ያንን ያደረግን እንደሆነ ያዕቆብ ራሔልን ከነአገልጋዮቿ ይዞ አገሩ እንደገባ እኛም በዕውቀት በልጥገን በገንዘብ ከብረን አገራችን እንገባለን፡፡

ሌላው ምክንያት የወጡበትን ዓላማ በአግባቡ ለመረዳት አለመቻል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደ ውጭ የሚወጡት በተረዳ ነገር ሰፍረው ቆጥረው በዕቅድ ያወጡትን ዓላማ ሳይዙ ነው፡፡ ያ ባለመሆኑም በስደት ሕይወታ ቸው በሚያጋጥማቸው ችግር በቀላሉ መደናገጥና መማረር ብሎም ተስፋ መቁረጥ ያጋጥማቸዋል፡፡ በስደት ሕይወት ይቅርና በየትኛውም ሕይወቱ ቢሆን ሰው የሚመራበት የሕይወት ዓላማ ያስፈልገዋል፡፡ ዓላማ የሌለውና ዓለማውን በአግባቡ ያለተረዳ ሰው በየመንገዱ በሚፈጠሩ ችግሮች /መሰና ክሎች/ በቀላሉ ለመውደቅ የተመቻቸ ይሆናል፡፡ ዓላማ ያለውና በአግባቡ ዓላማውን የተረዳ ሰው ግን በጥንካሬ የሚጓዝ፣ በቀላሉ የማይወድቅና ቢወድቅም ፈጥኖ የሚነሣ ሰው ነው፡፡ አባታችን ያዕቆብ ከሀገሩ የወጣበትን ዓላማ ያልተረዳ ቢሆን ኖሮ በፍጹም አስቦትና ሆኖት የማያውቀውን ሕይወት ለ14 ዓመታት ይቅርና ለ4 ቀናትም ቢሆን ታግሦ ሊቆይ አይችልም ነበር፡፡  

    
ሐ. ያሰቡትን ካገኙ በኋላ ወደ ተወለዱበት ሀገር መመለስ
ያዕቆብ ከ21 ዓመታት አገልግ ሎት በኋላ ራሔልን ሲያገኝ ራሔልንና በስደት ያጠራቀመውን ሀብት ይዞ ወደ ተወለደበት ሀገር ሊመለስ ወሰነ፡፡ ዓላማውን ካሳካ በኋላ በባዕድ ምድር ተጨማሪ ዓመታትን በባዕድነት መቆ የት አልፈለገም፡፡ ፈጣሪው እግዚአ ብሔርም ተመለስ አለው፡፡ /ዘፍ.31፥3/ እሱም ተመለሰ፡፡

ሰዎች በስደት ሕይወት ሲኖሩ ከሀገር ይዘውት የሚመጡት ግልጽና የጸና ዓላማ ሊኖር እንደሚገባ ሁሉ ዓላማቸውን ከግብ ካደረሱ በኋላ ሊኖር ስለሚገባው ሕይወት ማሰብ አግባብ ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ከሀገራቸው ከወጡ በኋላ ረጅም ጊዜ በስደት የኖሩ ሰዎች ዓላማቸውን ካሳኩ በኋላም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የማያስቡ ይኖራሉ፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ የሚያደርጓቸው በቂ ምክንያቶች የሚኖሯቸውም አይጠፉም፡፡

ዓላማን ከግብ ካደረሱ በኋላ ወደ ሀገር መመለሱ ለተመላሹ ከሚሰጠው የአእምሮ ዕረፍትና የተረጋጋ ሕይወት ባሻገር ከተመላሹ በሚገኘው ዕውቀት፣ ልምድ፣ ሀብትና ጥረት ወገንና ሀገር እንዲጠቀም ያስችላል፡፡ ያዕቆብ ዓላማውን ካሳካ በኋላ በመመለሱ ሕዝበ /ሀገረ/ እስራኤልን በአዕማድነት የመሠረቱ ልጆች ለማፍራት ችሏል፡፡

በዚህም ዘመን ሰፊ ራእይ ሰንቀን ሩቅ አልመን ወደተለያዩ ሀገሮች የተሰደድን ኢትዮጵያውያን በከፈልነው መሥዋዕትነትና በእግዚአብሔር አጋዥነት ዓላማችን ከተሳካልን በኋላ ወደ ሀገራችን ልንመለስ ያስፈልጋል፡፡ “ሠናይ ለብእሲ ለእመ ይከውን መቅበርቱ ውስተ ርስቱ፤ የሰው ሞቱ፤ መቃብሩም በሀገሩ /ርስቱ/ ቢሆን መልካም ነው“ እንደተባለ መመለስ የማያስችለን መሠረታዊ ችግር ከሌለ በስተቀር የተሰደድንበት ዓላማ ከተሳካ በኋላ በባዕድ ምድር ውሎ ከማደር ይልቅ ባካበትነው ቁሳዊና አእምሮአዊ ሀብት ሀገርንና ወገንን በመጥቀም ለመጠቀም ቤተሰብን ይዞ፤ ሀብትንም ሸክፎ ርስት ሆና ወደ ተሰጠችን ምድረ ኢትዮጵያ ለመግባት ማመንታት የለብንም፡፡ ያዕቆብን ተመለስ ብሎ ያዘዘው እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ወደሀገራችን እንድንመለስ ፈቃዱ እንደሆነም እንረዳለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት 16 ከግንቦት 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.

የ ቆሙ መቃብሮች

መጋቢት 16 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ስምዓኮነ መላክ

መቃብር ሰዎች ሲሞቱ ወይም ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሲለይ በክብር የሚያርፍበት ቦታ መቃብር ይባላል፡፡ መቃብር የሚላው ቃል የጎደጎደ ምድር ተብሎ ይተረጎማል፡፡ መዝ.14፥4፣ ኢሳ.22፥16 ሲዖልንም መቃብር ሲል ይገኛል፡፡ መትሕተ ታሕቲት ናትና፡፡

በማን ጊዜ እንደተጀመረ ባይታወቅም የሚቀበሩት በርስትነት በያዙት ቦታ ነበር ዘፍ.13፡፡ ያ ልማድ ሆኖልን ዛሬም በአዲስ ኪዳን የምንኖር ክርስቲያኖች እንደ አባቶቻችን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንቀበራለን፡፡ ስለምን ቢሉ ሥጋውን ደሙን የበላንበትና የጠጣንበት ብቸኛዋ ርስታችን በምድር ቤተ ክርስቲያናችን ናትና ነው፡፡

የቀደመው ርስት በዋጋ ይገዛ ነበር የዛሬዋ የምእመናን ርስት ቤተ ክርስቲያን ዋጋዋ የክርስቶስ ደም ነውና ደሙ በነጠበበት ቦታ ብቻ ስትሠራ ትኖራለች የምእመናን መቃብር በጌታ ደም የተገዛ እንጂ በሰቅል በተመዘነ ወርቅ የተገዛ አይደለም፡፡ ይህም የጌታ ደም ከሁሉ በላይ የከበረ እንደሆነ የምእመናንም መቃብር የከበረ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ለዛሬው ግን መቃብርን ያነሣነው ከአቤል ሞት ጀምሮ እስከ ጌታ ዳግም ምፅአት የማያቋርጥ ታሪክ ያለውን ጀግና ባለ ታሪክ መቃብርን ታሪኩን ለትውልድ ልናስተዋውቅለት ሳይሆን መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለቆሙ መቃብሮች የተናገረውን ቃል ማስታወስ ስለሚገባ ነው፡፡

መድኀኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት በጀመረ በመጨረሻው ዓመት በመቅደስ ተገኝቶ ለሕዝቡና ለደቀመዛሙርቱ ተናገረ፡- “ታላቅ ሸክም ማሰር ሰለሚችሉት መሸከም ግን ስለማይወዱት ስለ ጻፎችና ፈሪሳውያን ነበር የተናገረው፡፡

ለብዙዎች ብዙውን ኀጢአታቸውን በፍቅር የሸፈነው ጌታ ስለ ወንጀለኞች ሲጠየቅ ዝም የሚለው አምላክ ዮሐ.8፥11፣ ሉቃ.7፥47 በቤተ መቅደሱ አደባባይ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል የእነዚህን ታላላቅ የኦሪት አገልጋዮች በደል መዘርዘር ጀመረ፡፡ ተመክሮ ያልተመለሰን ሰው በአደባባይ ሊወቅሱት ይገባልና ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረው “ቢሰማህ ብቻውን አድርገህ ብቻህን ሆነህ ምከረው ባይሰማህ ካንተ ጋር ሁለት ሆናችሁ ምከረው….. እነርሱንም ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት” ማቴ.18፥15-17 ብሎ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይም የማይገባ ነገርን አድርገዋልና መገሰጽ ስለሚገባቸው በታላቅ ቃል ገሰጻቸው 1ቆሮ.5፥5 በመጽሐፍ ቃልህ እውነት ነው ተብሎ የተነገረለት መምህር ነውና ዮሐ.17፥17 እነርሱን ከውስጥ እስከ ውጭ ሊገልጹ በሚችሉ የተግሣፅ ቃላት ገሰፃቸው፡፡

በዘመኑ የነበሩ መምህራን አባቶቻቸው በሠሩት ኀጢአት የተጸጸቱ ለመመሰል አባቶቻቸው የገደሏቸው የነቢያትን መቃብር በኖራ እየለሰኑ ይሠሩና ያሠሩ ነበርና ያንኑ የሠሩትን ልስን መቃብር እየተመለከተ “የተለሰነ መቃብር የምትመስሉ” ሲል ተናገራቸው ይህ መቃብር ቢከፍቱት ለአፍንጫ የሚከረፋ ለዐይንም የሚከፋ ነገር አይታጣበትም፡፡ ሥጋው ተልከስክሶ አጥንቱ ተከስክሶ፣ እዡ ፈሶ ሲታይ ከውጭ የተለሰነ ውበቱን ያጠፋዋል፡፡  አብረውት እንዳይኖሩ ያስገድዳል በዚህ ረጅም ዕድሜው እንደላዩ ሁሉ ውስጡ አምሮ አያውቅም፡፡

ዘመኑን ሁሉ ሕይወት በሌላቸው ነገሮች የተሞላ ሆኖ ይኖራል እንጂ፡፡ ከዕለታት ባንዱ ስንኳን ንጹህ ነገር ክርስቶስን ቢያገኝ በሥጋ የሞተው በመንፈስ ግን ሕያው የሆነው ጌታ በትንሣኤ አሸንፎት ይዞ ማስቀረትም አይቻለው ብሎ ባዶውን ቀርቶ ይሄው እስከዛሬ ያለ ክርስቶስ ይኖራል፡፡ በእውነት ክርስቶስ በመቃብር መስሎ የተናገረበት ነገሩ ምን ይመስላችኋል? ለጊዜው የሚያመለክተው በዚያ ዘመን እስከ ክርስቶስ ወደ መቃብር መውረድ ድረስ በሰው ልጆች ላይ ሙስና መቃብር በሥጋቸው ወደ ሲዖል መውረድ በነፍሳቸው የግድ የነበረባቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡

በዘመኑ ባለ ጊዜ ሆኖ ሞት ውጦ መቃብር ተረግጦ የማስቀረት ኀይል ነበረውና፡፡ ያንን የሚገልጽ ሲሆን ፍጻሜው ግን ከውጭ ለሰው መልካም መስለው ስለሚታዩት ከውስጥ ግን ለእግዚአብሔር የሚመች በጎ ተግባር የሌላቸው ሰዎች እንዲገሰጹበት የተጻፈ ነው፡፡

ከውጭ ሲያዩአቸው ይጸልያሉ ይጾማሉ በጾምና በጸሎት ብዛት በገድልና በትሩፋት ጠውልገው ይታያሉ ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው ይምላሉ ሐሰቱን እውነት ያስመስላሉ በልባቸው የሌላውን የእግዚአብሔር ቃል አንሥተው ሲናገሩ በቂሳርያ ከተመሰገነው ጴጥሮስ ይበልጣሉ ዝምነታን በማያውቀው አንደበታቸውም ደግመውና ደጋግመው ስሙን ሲጠሩ ከጳውሎስ በላይ ሰባኪ ይመስላሉ ከውስጣቸው ግን እንዲህ አይደሉም፡፡ አመጽንና ሽንገላን ተሞልተዋል፡፡ በክፉ ምኞታቸውና አስቀያሚ በሆነው መሸታቸው የገዛ ነፍሳቸውን ገለው የገዛ ሥጋቸውን መቃብር አድርገው ቀብረዋል፡፡

በወይንና በአረቂ አልሰከሩም እንጂ በኀጢአት ሰክረው ወድቀዋል፡፡ ከመብልና ከመጠጥ እንጂ ክፉ ተግባራቸውን ከመተው የማይከለክሉ ይልቁንም በሞተ ሥራ የተሞሉ የቆሙ መቃብሮች ሆነዋል ስለዚህም መቃብር ውስጥ ያሉ ሙታንን ስንኳን የማይጠላ ጌታ ለተለሰኑ መቃብሮችም በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆሞ አሳምረው የለሰኑአቸው ልስን መቃብሮችን አሻግሮ እየተመለከተ ሁሉም ወደ መዳን የሚደርሱበትን ሕያው መልእክቱን አስተላለፉ፡፡

ወንድሜ ሆይ! አንተስ እንዳምን ነህ? ከውስጥህስ ምን ይገኛል? እግዚአበሔር አንተን ክርስቲያን አድርጎ ሐዋርያት ከሰበሰቧት አንዲት ማኅበር አባል ሲያደርግህ ምን ዓይነት ዓላማ እንደነበረው ታውቃለህ? ጨለማውን ዓለም ካንተ በሚወጣው የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ሊሞላው፣ ሕይወት አልጫ ለሆነችባቸው ማጣጫ ሊያደርግህ ማቴ.5፥12-13 በአሕዛብ መካከል ስሙን አሸክሞ ሊልክህ ሐዋ.9፥5 ዓላማ ስላለው ነው፡፡

የታመሙትንና በአጋንንት ተይዘው የሚሰቃዩትንም የሚፈውሳቸው ለምጻሞችን የሚያነጻቸው የረከሱትን የሚቀድሳቸው አንተን መሣሪያ አድርጎ እንደሆነ ታውቃለህ? አንተ ግን ለዚህ ዓላማ የተጠራህ መሆንህን የረሳህ ትመስላለህ፡፡ በአለባበስህና በከንፈርህ ብቻ እግዚአብሔርን ታመልካለህ ቀን ቆጥረህ ደማቅ በሆኑ የዓመትና የወር በዓላት ብቻ ለእግዚአብሔር ትዘምራለህ በሌላው ቀን ግን ትጠፋለህ ቃሉን ታውቃለህ እንደ ቃሉ መኖር ግን ተስኖሃል ከውጭ እንጂ ከውስጥ የሚታይ ነገር የሌለህ መጥፎ ሰው ሆነሃል፡፡ በክፉ መሻትህ እየወጋህ ሕያዊት ነፍስህን ገለህ የቆመ መቃብር ሆነሃታል፡፡

የማይታይ የተሰወረ የማይገለጥ የተከደነ አለ ይመስልሀልን? ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ቆይታ በኋላ ተከድኖ ይኖር የነበረ መቃብር መገለጡን በጌታ ደም ድብቅ ምሥጢሩን ከረጅም ዓመታት በኋላ ማጣቱን እንዳትረሳ ማቴ.27፥57 አንተ ሆይ! ሳይነግሩት የሰውን ማንነቱን የሚያውቅ ጌታ አንተንስ ቢገልጥህ? ዮሐ.2፥25 ከላይ የተለሰነ ኖራህን ቢያነሳብህስ? የቆመው መቃብርነትህ በጌታ ቃል የሞተውን ሳይሆን ሕያው የሆነ አልዓዛርን የሚያስገኝ ይመስልሃል? ብታምን የልቡናህን ትንሣኤ ዛሬ ታየ ዛሬም የተለሰነው መቃብር በር ላይ ቆሞ ይጣራል በውስጥህ ያሉት ሙታን አካሎችህ ዛሬ ድምጹን የሚሰሙበት ጊዜ ደርሷል እርሱም አሁን ነው ዮሐ.5፥25፡፡

የሚያሳዝነው ነገር ተዘግቶ ተለስኖ መቀመጡ ነው እንጂ የተከፈተ መቃብርማ ለብዙዎች የሚያስገርም ምስጢር ተገኝቶበታል እኮ! ሉቃ.24፥12 መላእክቱ የከበቡት የጌታ ደቀ መዛሙርት የጎበኙት ያ ቅዱስ መቃብር ባዶም ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ትንሣኤውን የሰበከ እርሱ ነበር፡፡

ወንድሜ ሆይ! የቆመ መቃብር ብትሆንም ለእግዚአብሔር ቃል የተከፈተ ልብ ካለህ እውነት እልሃለሁ ስላንተ ወዳንተ ወደመቃብሩ መላእክቱን ያዝልሀል ለደቀ መዛሙርቱ ሳይቀር የሚደንቅ ጥበብን ይገልጥብሃል ለጌታችን ቃል የተከፈተ ልብህ ዝቅ ብለው ቢያዩትስ የጌታ ልብስ ብቻ እንጂ ሌላ ምን ይገኝበታል፡፡ ከእውቀት፣ ከጥበብህ ከቅድስና የተለየሁ ባዶ ሰው ነኝ ብለህ ብታምን እንኳን እግዚአብሔር ባዶነትህን ለምስክርነት ይሻዋልና ከላይህ ላይ ያለ ልስንህን አስወግደው፡፡

አለበለዚያ የክፉዎች አጋንንት ማደሪያ መሆንህን አትርሳው፡፡ ማቴ.8፥28 ከዚያ በፊት ግን አሁን ዕድል አለህ፡፡ እንደውጪ ሁሉ ውስጠኛውንም የመቃብር ክፍል ማጽዳት ትችላለህ፡፡ አንተ እኮ! ዕድለኛ ነህ፡፡ የአባትህ ድምጹ እስከመቃብር ድረስ ዘልቆ ይሰማል ቅዱስ የሆነው ደሙ በመቃብር ያሉትን ሳይቀር መቃብራቸውን ከፍቶ ይቀድሳል እንዳትረሳ! ይሄ ዕድል ላንተም ተሰጥቶሃል፡፡ ደግሞም አንድ ነገር አለ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባው ቃል ኪዳን አለ መቃብሩን ከፍቶ ለሞቱ አጥንቶች ሕይወትን ሰጥቶ የሚያኖርበት ጊዜ አለ ይሄ ቃል ኪዳን ላንተም የተገባ ቃል ኪዳን ነውና አትፍራ ምን አልባትም ይሄ ቃል ኪዳን ላንተም የተገባ ተስፋ አትቁረጥ፡፡

በዙሪያህ ሆነው ከመቃብሩ ደጃፍ ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል የሚሉም ይኖራሉ ድንጋዩ ታላቅ ቢሆንም ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር መላኩን ልኮ አንተ ባልጠበቅከው ሰዓት ሊያነሣው እንደሚችል አትጠራጠር፡፡ መቃብር ብዙ ኀያላንን ይዞ ማስቀረቱ የተገለጠ ነው፡፡ እነ ዳዊት እነሶምሶን፣ ዮፍታሔ፣ ጌዴዎን ሌሎችም ኀያላን መቃብር ያድራሉ ደራሲዎቹ የደረሱላቸው ተራኪዎቹ የተረኩላቸው ዜመኞቹም ያዜሙላቸው ጀግኖች ሁሉም ከመቃብር አላመለጡም ምድራዊ ፍጥረት ሥጋዊ ደማዊ ሰውነት ሁሉም የመቃብር ምርኮኞች ሆነዋል፡፡

አንተ ሆይ! ባንተም ውስጥ ስንት ኀያላን የእግዚአብሔር ቃላት ተቀብረው ቀርተዋል መሰለህ? እነ አባ ጳውሊ ከዓለም ወጥተው የኮበለሉባቸው እነ አባ እንጦንስ ሥርዓተ መላእክትን የተላመዱባቸው ይሄ ግዙፍ ዓለም የተከናወነባቸው እነዚያ ሰባሪ ቃላቶች አንተ ዘንድ ሲደርሱ ግን ሳይሠሩ ቀብረህ አስቀርተሃቸዋል፡፡

እውነት እልሃለሁ አዲስ ሆነህ የምትሠራው በቅዱስ ቃሉ ነውና ቃሉን ጠብቅ ብታምንም ባትምንም በክፋት ብትሆን ሳትወድ በግድ “መቃብር ሆይ ይዞ ማስቀረትህ ወዴት አለ?” ሆሴ.13፥14፣ 1ቆሮ15፥55 ተብለህ መጣልህ አይቀርምና ይህ የፈጣሪህ ድምጽ ወዳንተ ባደረበት ቅጽበት ወዲህ በፈቃድህ ንስሓ ግባ ይሄ ጊዜ ለሌላ ለምንም የተመደበ አይደለም የንስሓ ብቻ ነው፡፡

“እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ ወደ እስራኤል ምድርም አገባችኋለሁ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” ሕዝ.37፥12-13፡፡

ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ዘፍ.35፥1

የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

ዲ/ን ሰለሞን መኩሪ

ይህንን የተናገረ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ የተነገረው እስራኤል ለተባለ ያዕቆብ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩ ተጽፎ እንደምናገኘው ከወንድሙ ከዔሳው ሸሽቶ የአባቱን የይስሐቅን በረከት ተቀብሎ ወደ አጎቱ ወደ ላባ ሲሄድ ሎዛ ከምትባለው ምድር ሲደርስ ጊዜው መሸ፡፡ እርሱም ደክሞት ስለነበር ድንጋይ ተንተርሶ ተኝቶ ሳለ ሌሊት በራእይ እግዚአብሔር ተገለጠለት ራእዩም የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ በመሰላሉ መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በዙፋኑ ተቀምጦ ነበር፡፡

 

ያዕቆብንም “እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ አትፍራ፣ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፡፡ በአንተ በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ፡፡ እነሆም እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፡፡ የነገርኩህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህም” አለው፡፡ ያዕቆብም ከእንቅልፍ ተነሥቶ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ አላወቅሁም ነበር፡፡

 

ይህ ሥፍራ እንዴት ያስፈራል? ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህችም የሰማይ ደጅ ናት፡፡ ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ ተንተርሷት የነበረችውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆማት፤ በላይዋም ዘይት አፈሰሰባት፡፡ ያዕቆብም ያን ሥፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው አስቀድሞ ግን የዚያ ከተማ ስም ሎዛ ነበር፡፡ ያዕቆብም ስዕለትን ተሳለ፡፡ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድበት መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላውን እንጀራ የምለብሰውን ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ አገር በሰላም ቢመልሰኝ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፡፡ ለሐውልት ያቆምኳት ይህች ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ትሆንልኛለች፤ ከሰጠኸኝ ሁሉ ለአንተ ከአስር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ አለ፡፡ እግዚአብሔርም ስእለቱን ሰምቶ ሁሉንም ፈጸመለት ወደ አጎቱ ወደ ላባ ደርሶ ሚስት አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ እንዲሁም ብዙ ባሮችን እና ሀብት ንብረት አፍርቶ ወደ አባቱ ሀገር ሲመለስ እግዚአብሔር አምላክ ተገለጠለትና “ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር” ብሎ አዘዘው ዘፍ.28፥10-20፣ ዘፍ.35፥1፡፡

x

 

ለመሆኑ ይህች ቤቴል ማን ናት? እግዚአብሔር አምላክ ለጊዜው ያዕቆብና ቤተሰቡ እንዲኖሩባት ለፍጻሜው ሁላችንም እንድንኖርባት የታዘዝንባት ቤቴል ምስጢራዊ ትርጉሟ ምን ይመስላል? አባቶቻችን እንዲህ ይተረጉሙታል፡፡

 

1.    ቤቴል የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡

አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ባየው ራእይ እግዚአብሔር አምላክ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር ገልጾለታል፡፡ ይኸውም የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ተተክሎ በመሰላሉ መላእክት ከላይ ወደ ታች ሲወርዱ እና ሲወጡ ተመልክቷል፡፡ በመሰላል የላዩ ወደ ታች እንዲወርድ አምላክ ሰው ለመሆኑ የታቹ ወደ ላይ እንዲወጣ ሰው አምላክ ለመሆኑ ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ መሰላሉ ደግሞ ወርቅ ነበር፡፡

 

ወርቅ ፅሩይ ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በማሰብ፣ በመናገር፣ በመተግበር፣ በመዳሰስ፣ በማሽተት ወ.ዘ.ተ. ሰው ሁሉ ኀጢአት በሚሠራበት ህዋስ ሁሉ ያልተዳደፈች፣ ንጽሕት፣ መልዕልተ ፍጡራን /ከፍጡራን በላይ/ መትሕተ ፈጣሪ /ከፈጣሪ በታች/ ናት፡፡ ከነገደ መላእክት ከደቂቀ አዳም በክብር የሚመስላት በጸጋ የሚተካከላት የለም፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ ሲገልጽ “የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎሙ ቅዱሳን” “የማርያም ክብር ከቅዱሳን ክብር ይበልጣል” ብሏል፡፡

 

በወርቁ መሰላል መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ መታየታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምዕራገ ጸሎት እንደሆነች በእመቤታችን ምልጃ የሰው ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንደሚቀርብ የእግዚአብሔርም ቸርነት ለሰዎች እንደሚሰጥ ያመለክታል፡፡ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ “አልቦ ጸሎት ወአልቦ ትንባሌ እንበሌኪ ማርያም ዘየዓርግ ሎዓሌ” ብሎ አጉልቶታል በወርቁ መሰላል ጫፍ ዙፋን ነበር፡፡ በዙፋኑም ላይ እግዚአብሔር ተቀምጦ ለያዕቆብ ተገልጦለታል፡፡ ባርኮታል፤ ዙፋን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል የማኅፀኗ ምሳሌ ነው፡፡ በማኅፀኗም ፍጥረቱን ለማዳን እግዚአብሔር ሰው እንደሆነ ማለትም በማኅፀነ ድንግል መፀነሱን ያመለክታል፡፡ ከዚያም በአጭር ቁመት በጠባብ ደርት በሰው መጠን መገለጹን ያስረዳል፡፡ ያዕቆብን እንደባረከው ርስት እንደሰጠው ሁሉ በእመቤታችን ሥጋ ተገልጦ በበደሉ ምክንያት የተረገመውን ሰው እንደባረከው አጥቶት የነበረውን ርስት ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንደሰጠው ያመለክታል ዮሐ.14፥2፡፡ “በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያ አለ ቦታ  አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፡፡ ዳግመኛም እመጣለሁ እናንተም እኔ ባለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ” እንዲል፡፡ ፍጥረቱም ሁሉ ፈጣሪው እግዚአብሔር ተመለከተው፡፡

 

ፍጥረት ማለትም መላእክትና ደቂቀ አዳም ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን ለመመልከት የቻሉት በእመቤታችን ሥጋ በመገለጡ ነው፡፡ ያዕቆብ ተንተርሶት የነበረው ድንጋይ እመቤታችን በትንቢተ ነቢያት ጸንታ መኖሯን ያመለክታል፡፡ እንግዲህ ይህችን ነቢያት በትንቢታቸው ደጅ ሲጠኗት የነበረችውን እግዚአብሔር የተገለጠባት የእግዚአብሔር ዙፋን ጸሎትን መሥዋዕትን ሁሉ የምታሳርግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅ መጠጊያ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡ ያዕቆብ በቤቴል እንዳደረ እኛም በአማላጅነቷ ከልጇ ዘንድ በተሰጣት የከበረ ቃል ኪዳን ልባችንን እንድናኖር ያስፈልጋል መዝ.47፥12፡፡ “በብርታቷ ላይ ልባችሁን አኑሩ” እንዲል፡፡ የእመቤታችን ምልጃ ለሁላችንም ይደረግልን፡፡

 

2.    ቤቴል የተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

አባታችን ያዕቆብ ባየው ራእይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር እግዚአብሔር ገልጦለታል፡፡ ያዕቆብ የጳጳሳት የቀሳውስት ምሳሌ ነው፡፡ ቦታው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ የተንተራሰውን ድንጋይ ዘይት አፍስሶበታል፡፡ ለጊዜው ቦታው እንዳይጠፋበት ለምልክት ለፍጻሜው ሊቃነ ጳጳሳት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅብዐ ሜሮን እንደሚያከብሯት የመንፈስ ቅዱስ የጸጋው ግምጃ ቤት እንደሚያደርጓት ማሳየቱ ነው፡፡ ሐዋ.20፥28፡፡ የወርቁ መሰላል ምሳሌዋ የሆነ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና ክብር አማላጅነት የሚነገርባት እግዚአብሔር የታየባት ዙፋኑ የተዘረጋባት ይኸውም የታቦቱ ምሳሌ ነው፡፡ መላእክት የእግዚአብሔርን ቸርነት ወደ ሰው ልጆች የሚያመጡባት የሰው ልጆችን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርጉባት ዘወትርም በኪዳን በቅዳሴ በማኅሌት በሰዓታት የማይለያት የምሕረት አደባባይ አማናዊት ቤቴል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

 

አምላካችን እግዚአብሔር ለቅዱስ ያዕቆብ “ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር” ሲል አዞታል፡፡ ምክንያቱም ሕይወት የሚገኝባት በሥጋ በነፍስ የምንጠበቅባት ስለሆነ ነው፡፡ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በደብረ ታቦር የጌታችንን ብርሃነ መለኮቱን በተመለከቱ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ማቴ.17፥4 እንዳለ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እርሷንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ …. ቤተ መቅደሱንም አገለግል ዘንድ እንዳለ መዝ.26፥4፡፡ ቅዱስ ዳዊት መንግሥቱ እንዲደላደልለት ዙፋኑ እንዲጸናለት ያይደለ በእግዚአብሔር ቤት መኖር እንዲገባ አጥብቆ እግዚአብሔርን የለመነበት ልመና ነው፡፡ ይህም የተወደደ ሆኖለታል፡፡ እንግዲህ በእግዚአብሔር ቤት በአማናዊት ቤቴል ለመኖር እንዴት ሆነው ተዘጋጅተው መውጣት /መሄድ/ እንደሚገባቸው ያዕቆብ ለቤተሰቡ አስገነዘባቸው እንዲህ አላቸው፡፡

 

1.    እንግዶች አማልክትን ከእናንተ አስወግዱ አላቸው፡፡

አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቦቹና ከእርሱ ጋር ላሉት “ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶችን አማልክት ከእናንተ አስወገዱ” አላቸው አምላካችን እግዚአብሔር በአምልኮቱ የሚገባበትን አይወድም በሊቀ ነቢያት በሙሴ አድሮ ሲናገር “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን አታምልክ” ዘጸ.20፥3 ብሏል፡፡ ሰማይና ምድርን በውስጧ ያሉትን የሚታየውንና የማይታየውን ፈጥሮ በመግቦቱ በጠብቆቱ የሚያስተዳድር እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ሌላ አምላክ አጥንት ጠርቦ ድንጋይ አለዝቦ፣ በጨሌ፣ በዛፍ፣ በተራራ፣ በጠንቋይ ወ.ዘ.ተ. ማምለክ አይገባም፡፡ እንዲህ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣው ትነዳለችና ዘጸ.20፥4፡፡ ዛሬም በዘመናችን ከወገብ በላይ ታቦት ከወገብ በታች ጣዖት ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ጠዋት ቤተ ክርስቲያን መጥተው ኪዳን አድርሰው ቅዳሴ አስቀድሰው ለእግዚአብሔር የሚገባውን እጣኑን ጧፉን ዘቢቡን ሌላም ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን ሰጥተው ሰግደው አምልኮታቸውን ፈጽመው ደግሞ ሲመሽ ሰው አየኝ አላየኝ ብለው ጨለማን ተገን አድርገው ጫት፣ ሰንደል፣ ቡና፣ ቄጤማ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን በሄዱበት እግራቸው ወደ ጠንቋይ ቤት የሚሄዱ በዚያ የሚሰግዱ በቤታቸውም ጠንቋዩ ያዘዛቸውን ጨሌ የሚያስቀምጡ ቀን እና ወር ለይተው ጥቁር በግ ገብስማ ዶሮ ወ.ዘ.ተ.

 

የሚያርዱ እህል የሚበትኑ እንደዚህ ባለ በሁለት እግር በሚያነክስ ልብ ወይም ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ ሊወጣ የሚመኝ ሰው ከእግዚአብሔር አንዳች ነገር አያገኝም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሰይጣናዊ ልምድ አስወግዶ ማለትም ከዚህ የኀጢአት ሥራ ንስሐ ገብቶ ተለይቶ በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ እግዚአበሔርን ብቻ በማምለክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ያስፈልጋል፡፡ የያዕቆብ ቤተሰቦች የአባታቸውን ምክር ሰምተው የጣዖት ምስል ተቀርፆባቸው የነበሩ በእግራቸውና በእጃቸው በጆሮአቸውም የነበሩትን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት እርሱም እንዳያገኟቸው አድርጎ አርቆ ቀበራቸው፡፡ እስከ ዛሬም አጠፋቸው ዘፍ.35፥4 እንዲል፡፡ ያዕቆብ የቀሳውስት ምሳሌ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ የምእመናን ምስሎቹን አምጥቶ ለያዕቆብ እንደመስጠት ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ከአምልኮ ጣዖት እንደመለየት ሲሆን ያዕቆብ ወስዶ እንደ ቀበራቸው በቀኖና ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ምሳሌ ነው፡፡ ከአምልኮ ጣዖት ተለይተን እግዚአብሔርን ብቻ እያመለክን በቤቱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድንኖር የቅዱሳን አምላክ ይርዳን፡፡

 

2.    ንጹሐን ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ አላቸው፡፡

አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ እንግዶችን አማልክትን እንዲያስወግዱ ካዘዙ በኋላ እነርሱም ካስወገዱ በኋላ የሰጣቸው መመሪያ “ንጹሐን ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ” አላቸው፡፡ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ አፍአዊ /የውጭ/ ንጽሕናውን እንዲሁም ውስጣዊ /የልብ/ ንጽሕናውን መጠበቅ እንደሚገባው አስተማረ ዘሌ.11፥44 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ ንጹሐንም ሁኑ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፡፡” ይላል ስለዚህ ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር ወደ ክብሩ ዙፋን ወደ ጸጋው ግምጃ ቤት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ለመገናኘት ንጹሕ ልብስ ለብሰን ደግሞ በንስሐ ታጥበን ሕይወታችንን አድሰን ሊሆን ይገባል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝ.50፥7 “በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡” እንዲል፡፡

 

አንዳንድ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ የልብስ ንጽሕና መጠበቅ የሚገባ የማይመስላቸው ወደ አንድ ሰርግ ወይም ድግስ በሰው ፊት ለመታየት የሚያደርጉትን ጥንቃቄ እና የአለባበስ ሥርዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን ግን ሲመጡ አልባሌ ሆነው መምጣት የሚገባ የሚመስላቸው አሉ አንዳንዶችም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ሰውነትን የሚያራቁት /የሚያስገመግም/ ልብስ ለብሰው የሚመጡ አሉ ይህ የሚገባ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጸሎት የመጣውን ሰው አእምሮ የሚሰርቅና የሚያሰናክል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምስጢሩ ግን አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ ንጹህ ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ ማለቱ በንስሐ ሕይወት ተዘጋጅታችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በእግረ ልቡና ውጡ ለማለት ነው፡፡ ለዚህም የቅድስት ሥላሴ ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ፈጣን ተራዳኢነት የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ አይለየን ይርዳን አሜን፡፡

“ወበ እንተዝ ኢየኃፍር እግዚአብሔር ከመ ይትበሃል አምላኮሙ” (ክፍል 2)

ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቀሲስ ይግዛው መኰንን

4.    ሰማያዊውን ሕይወት ናፋቂዎች ስለሆኑ

ክቡር ዳዊት “በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘለዓለምም ያመሰግኑሃል፡፡ አቤቱ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው፡፡” በማለት ሰማያዊውን መናፈቅ እንደሚያስመሰግን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ተናገረ፡፡ መዝ. 83፥4 ቅዱስ ጳውሎስም የሚጠበቅበትን አገልግሎት ካከናወነ በኋላ “ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤” በማለት ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ሕይወት ምን ያህል እንደሚናፈቅ ገልጿል፡፡ ፊል.1፥23 ለዚህ ነው ቅዱሳን በሥጋ የምኞት ፈረስ እንዲጋልቡ፥ በኀጢአት ባሕር እንዲዋኙ፥ በክፉ አሳብ ጀልባ እንዲቀዝፉ የሚፈታተናቸውን ርኩስ መንፈስ በመልካም ሥራቸው በመቃወም ድል የሚያደርጉት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ፡፡” በማለት የአሁኑን ችግርና ፈተና ከሚመጣው ጋር በማመዛዘን የተናገረው፡፡ ሮሜ.8፥18

 

ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴ ማርያም ጸሎቱ “ሰማዕታት በእውነት የዚህን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ስለ እግዚአብሔርም ሲሉ ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለመንግሥተ ሰማያትም ሲሉ መራራ ሞትን ታገሡ፡፡” በማለት የዚህን ዓለም መከራ መታገሥ ሰማያዊውን ክብር በማስታወስና የሚገኘውን ዋጋ በማመን እንደሆነ ገልጿል፡፡ /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/ ለዚህም ነው ሰማእታት እሳቱን ስለቱን፣ ጻድቃን ግርማ ሌሊቱን፥ ጽምፀ አራዊቱን፣ ጸብአ አጋንንቱን ታግሰው ሥጋቸውን ለነፍሳቸው አስገዝተው የኖሩበት ዐቢይ ምሥጢር፡፡ ሰማዕታት የሚታሰሩበትን ገመድ፣ የሚሰቀሉበትን ግንድ ይዘው ወደ ሞት ሲነዱ ጻድቃንም አስኬማቸውን ደፍተው፣ ደበሎአቸውን ለብሰው፣ ከምግበ ሥጋ ተለይተው ርሃቡን ጥሙን ችለው ሲኖሩ ደስ ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከፈጣሪያቸው እንደሚያገኙ ያውቃሉና ነው፡፡ መሬት ፊቷን ወደ ፀሐይ ስታዞር ብርሃን እንደምታገኝ፣ ፊቷን ስትመልስ ደግሞ ጨለማ እንደሚሆን ሳይንሱ ይነግረናል፡፡ የሰው ልጅም ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ካዞረ ብርሃን ይሆንለታል፤ ፊቱን ከፈጣሪው ካዞረ ግን ይጨልምበታል፡፡ ኑሮው፣ ትዳሩ፣ መንገዱ ሁሉ የተሳካ እንዲሆን፣ የውስጥ ሰላምን እንዲያገኝ፣ በሚያገኘው ተደስቶ እንዲኖር፣ ሰላም፣ ጤና በረከት ከቤቱ እንዳይርቁ፣ አሸሼ ገዳሜ በሉ፣ አይዟአችሁ ጨፍሩ የሚለውን የጥንት ጠላት የአጋንንት ስብከት በመልካም ሥራ በዝማሬ በማኅሌት በሰዓታት በቅዳሴ፣ በኪዳን ተጠምዶ መቃወም ያስፈልጋል፡፡ መቼም የሰይጣን የዘወትር ስብከት “ሥጋችሁ በነፍሳችሁ ላይ ትንገሥ” የሚል ስለሆነ እኛ ግን ነፍሳችንን በሥጋችን ላይ ልናነግሣት እንደ አባቶቻችን ቅዱስን ሰማያዊውን ናፋቂዎች ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፣ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡” እንዲል፡፡ 2ቆሮ.5፥1

 

5.    ለሌላው አሳቢዎች በመሆናቸው

ለሌላው ማሰብ፥ ለሌላው መጨነቅ፥ ከሚደሰቱ ጋር መደሰት፥ ከሚያዝኑ ጋር ማዘን፥ ችግር የወደቀባቸውን ሰዎች የችግራቸው ተካፋይ መሆን ፈጣሪን መምሰል ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ፣ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፡፡ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን፡፡” በማለት ከራስ ይልቅ ለሌላው ማሰብን እንድናስቀድም ያስተምረናል፡፡ ፊልጰ.2፥1 ታላቁ ሊቅም በሰቆቃወ ድንግል ላይ “ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፡፡ ኢየሱስ ግፉዕ ምስካዮሙ ለግፉዓን፡፡ እግዚአብሔር ማኅደር ዘአልቦ ከመ ነዳያን..” በማለት የጌታችን መሰደድ የተሰደደውን የሰውን ልጅ ለመመለስ እንደሆነ፤ ጌታችን ያለ በደሉ የተገፋው የተገፋ የሰውን ልጅ ሊያድን እንደሆነ፤ እግዚአብሔር ተስፋ፣ ላጡ ተስፋ ማረፊያ ቤት ለሌላቸው ማረፊያ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን ከራሳቸው በላይ ለሌላው ያስባሉ፡፡ “ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ አለ፡፡” የሚለውን የታላቁን ሰው የሙሴን ልመና ስንመለከት ምን ያህል ለሌላው ማሰብ እንደሚገባ እንማራለን ዘፀ.32፥32 ዛሬ ቢሆን ምናልባት ሌላውን ደምስሰህ እኔን ጻፍ ሳይባል ይቀራል ትላላችሁ፡፡ ቅዱሳን ግን እንደፈጣሪያቸው ለሌላው አሳቢወች በመሆናቸው “እግዚአብሔር አያፍርባቸውም” ተባለ፡፡

 

ዛሬም ሰው ለድሃ እጁን ሲዘረጋ እግዚአብሔር ደግሞ የምሕረት እጁን ይዘረጋለታል፡፡ የወደቀ ባልንጀራውን ሲያነሣ እግዚአብሔር እርሱን ከወደቀበት ያነሣዋል፡፡ የተጨነቀውን ሲያጽናና፥ የተጨቆነውን ነጻ ሲያወጣ ተስፋ ለቆረጠው ሲደርስለት በእውነት ዋጋው አይጠፋበትም፡፡ ለዚህ ነው ክቡር ዳዊት “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ ሕያውም ያደርገዋል፡፡” በማለት ያስተማረን፡፡ መዝ. 40፥1 ስለዚህ በዘመናችን ያለውን የወገንተኝነት፥ የትዕቢትና የሥጋዊነትን አስተሳሰብና አመለካከት በወንጌል መሣሪያነት አፈራርሶና ንዶ ለራስ ነጻ በመውጣት ለሌላውም መትረፍ ያስፈልጋል፡፡ ከነዚህ ክፉ ተግባራት ካልተለየን ገና ዛሬም በጨለማ ውስጥ ስላለን እንጠንቀቅ፡፡

 

“ልጄ ድሃውን ምጽዋቱን አትከልክለው ከሚለምንህ ከድሃውም ዓይኖችህን አትመልስ፡፡ የተራበች ሰውነትን አታሳዝን ያዘነ ሰውንም አታበሳጭ፡፡ ያዘነ ልቡናን አታስደንግጥ፣ የሚለምንህን ሰው አልፈኸው አትሂድ፡፡ የሚገዛልህ ቤተ ሰብህን አትቆጣ፤ ከድሃም ፊትህን አትመልስ፡፡” ካለ በኋላ ቀጥሎ “ከሚለምንህ ሰው ፊትህን አትመልስ፤ በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ ፈጣሪው ልመናውን ይሰማዋልና፡፡” በማለት ምስካየ ኅዙናን፣ ረዳኤ ምንዱባን የሆነ እግዚአብሔር የድሃውን ኀዘን ሰምቶ እንደሚበቀል ይነግረናል፡፡ ሲራ.4፥2 ስለዚህ የነዚህ ቅዱሳን ልጆች የሆን እኛ ፍትሕ ተጓድሎባቸው የሚሰማቸው አጥተው የሚገባቸውን፣ ተነፍገው፣ መከበር ሲገባቸው ተዋርደው ከሰው በታች ሆነው ለሚቆዝሙ ወገኖች ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ “ሳትሞት ለባልንጀራህ በጎ ነገርን አድርግ፡፡” ተብለን ተመክረናልና፡፡ ሲራ.14፥13

 

6.    ለመከራ ራሳቸውን ያዘጋጁ በመሆናቸው

ከላይ እንዳየነው እምነታቸው በማዕበል ቢመታ የማይፈርስ እውነተኛ እምነት ስለሆነ ለመከራ አይበገሩም፡፡ ከእሳቱ ከሰይፉ ከመከራው በስተጀርባ የሚወርድላቸው አክሊለ ሕይወት ስለሚታያቸው ወደሞት ሲነዱ ደስ እያላቸው ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸውን ለሞት ራሳቸውን ለስቅላት፣ ራሳቸውን ለእንግልት አዘጋጅተው በሃይማኖት ስለሚኖሩ፣ ፈጣሪ ያዝንላቸዋል፡፡ ደስ ይሰኝባቸዋልም፡፡ ያለ መከራ ዋጋ እንደማይገኝም ስለሚያውቁ “አቤቱ ቅጣኝ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቁጣ አይሁን፡፡” እያሉ ድሎትን ሳይሆን መከራ ሥጋን ይለምናሉ፡፡ ኤር.1፥24 ሥጋ ሲጎሰም ለነፍስ እንደሚገዛ ይረዳሉ፡፡ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሃብ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፣ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጥረን” ተብሎ እንደተጻፈ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በወደድን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ ግዛትም ፍጥረትም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፡፡” የሚለው የቅዱስ ጳውሎስም ትምህርት የሚያስተምረው ራስን ለመከራ ማዘጋጀትን ነው፡፡ ሮሜ.8፥35

 

ገበሬ ብርዱን፣ ዝናቡን፣ ፀሐዩን ታግሦ እሾሁን ነቅሎ መሬቱን አለምልሞ ተክል የሚተክለውና ከበቀለም በኋላ የሚኮተኩተው የሚያርመው ፍግ እያስታቀፈ የሚንከባከበው ውኃ እያጠጣ፣ ፀረ ተባይ መድኀኒት እየረጨ ከተባይ የሚጠብቀው፣ ቅጥር ምሶለት፣ አጥር አጥሮለት ከእንስሳት የሚያስጠብቀው በአጠቃላይ ብዙ የሚደክምለት መልካም ፍሬን  ለማግኘት ነው፡፡ እንዲህ ከለፋ በኋላ አመርቂ ውጤት ቢያገኝ በልፋቱ ይደሰታል፡፡ በሚቀጥለውም ከመጀመሪያው የበለጠ እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡ ካልሆነ ግን ያዝናል፡፡ ተክሉ ፍሬ አልባ ቢሆን ወይም ደግሞ ጣፋጭ ፍሬን እየጠበቀ መራራ ፍሬን ቢያፈራ ከማዘንም አልፎ እንዲቆረጥ ያደርገዋል፡፡ ዮሐ.15፥5፣ ማቴ.21፥18

 

ሰውም የእግዚአብሔር ተክል ነው፡፡ በቃለ እግዚአብሔር በምክረ ካህን ተኮትኩቶ በረድኤተ እግዚአብሔር አጥርነት ተጠብቆ የሚኖር የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ስለሚያውቁ ቅዱሳን መልካም ፍሬን አፍርተው በመገኘታቸው እግዚአብሔር ተደስቶባቸዋል፡፡

 

ፍሬአቸው መራራ የሆኑ ተክሎች /ሰዎች/ ጨለማን ተገን አድርገው ሰው አየን አላየን ብለው ኀጢአትን የሚፈጽሙትን ያህል በእግዚአብሔር ቤት የተተከሉ፣ ፍሬአቸው ያማረ ቅዱሳን ጨለማው ሳይከለክላቸው ጽድቅን ሲሠሩበት ያድራሉ፡፡ በዓለም ላይ ለ5 ሲሕ 5 መቶ ዘመናት ኀጢአት በዓለም ላይ ነግሦ ይኑርም እንጂ በዚህ ኀጢአት በነገሠበት ዘመን ጽድቅን ሲሠሩ የኖሩ አባቶችና እናቶች ነበሩ፡፡ ዛሬም ኀጢአት በዓለማችን ላይ ጠፍንጎ ይዞ እያስጨነቀን እንዳለ ብንረዳም የነዚህ የቅዱሳን አበው በረከት ያደረባቸው በየገዳማቱ ወድቀው ለጽድቅ ራሳቸውን ሲያስገዙ እንመለከታለን፡፡

 

ማጠቃለያ

አንድን መንፈሳዊ ሥራ መጀመር ብቻውን የጽድቅ ምልክት አይደለም፡፡ ከላይ ያየናቸው የቅዱሳን ሕይወት ጽድቃቸው ከሰውም አልፎ በእግዚአብሔር የተመሰከረላቸው ከመጀመሪያው ይልቅ መጨረሻቸው በማማሩ ነው፡፡ ጀምረው ያቋረጡማ የሚነገርላቸው ማቋረጣቸው እንጂ ጽድቃቸው አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ሳጥናኤል የመላእክት አለቃ ነበር፡፡ አርዮስ ካህን፣ ይሁዳ ከሐዋርያቱ ጋር ተቆጥሮ የነበረ፣ ዴማስ ከአርድዕተ ክርስቶስ ከነ ሉቃስ ጋር ተደምሮ የነበረ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች የጀመሩትን መንፈሳዊ አገልግሎት ችላ ማለታቸው ከሰማይ ወደ ምድር፣ ከክብር ወደ ውርደት፣ ከሹመት ወደ ሽረት፣ ከማግኘት ወደ ማጣት ተወረወሩ እንጂ ምን ጠቀማቸው? በትናንት ማንነት ብቻ ድኅነት አይገኝም፡፡ ዛሬ የማያሳፍር ሥራን መሥራት እንጂ፡፡

 

ትናንት ዘመነኞች፣ ቅንጦተኞች፣ ኩሩዎች፣ የነበሩ ነገሥታት ወመኳንንት ዛሬ የት አሉ? በሀብታቸው የሚኩራሩ፣ በሥልጣናቸው የሚንጠራሩ፣ ፊታቸውን ከፈጣሪ ያዞሩ ሁሉ ጊዜ አልፎባቸው ገንዘባቸው፣ ሥልጣናቸው፣ ወገናቸው አላድናቸው ብሎ በጸጸት አለንጋ ከመገረፍ ውጪ ምንም አላገኙም፡፡ ስለዚህ ከዚህ መማር የዘመኑ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ በሃይማኖት ቁመው ከተጠቀሙት በሃይማኖት የመቆምን ጥቅም፣ ወድቀው ከተጎዱት የመውደቅን አስከፊነትና ጉዳት መማር እንችላለን፡፡ ስለዚህ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡ በየመሥሪያ ቤታችን የምንሠራው ሥራ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነው ወይስ የሚያሳዝን፣ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ በተለይ በሐዲስ ኪዳን “ከአሁን በኋላ ባሮች አልላችሁም፣ ልጆች ብያችኋለሁ፡፡” በማለት ያቀረበውን ፍጹምም የወደደውን የሰው ልጅ እንዴት እያየነው ነው? እውነት የምንሠራው ሥራ አሳፋሪ ነው ወይስ የሚያስደስትና የሚያስከብር? የሚለውን ጠይቀን ለራሳችን ምላሽ ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ ያለ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ መልካምን ማድረግም አይቻልምና ለመልካም ሥራ እንዲያነሣሣን ኃይሉን ብርታቱንም እንዲሰጠን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ledet04

የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር

ኅዳር 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ሰሎሞን መኩሪያ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ledet04በቤተ እስራኤል ስም ጠባይን፣ ግብርን፣ ሁኔታን እንደሚገልጥ ሁኖ ይሰየማል፡፡ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ማርያም” የሚለውን ስያሜ ከማየታችን በፊት ስለ ድንግል ማርያም አባቶቻችን በነገረ ማርያም ያሉትን ጥቂት እንመለከታለን፡፡ “ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ በም.1፥9 ላይ እንደተናገረ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር፡፡” እንዳለ በኦ.ዘፍ.ም.19፥1 ጀምሮ እንደተጻፈ የሰዶምና የገሞራ ሰዎች በበደላቸው ምክንያት እንደተደመሰሱ /እንደጠፉ/ እናነባለን፡፡ አዳምና ልጆቹ በሲዖል ባህር ሰጥመን እንዳንቀር እግዚአብሔር በቸርነቱ ንጽህት የሆነች ዘር መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እያማለደች የምታሰጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባያስቀርልን ከእርሷም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ በሞቱ ሞታችንን ባይደመስስ ወደ ሕይወት ባይመልሰን ኖሮ መኖሪያችን ሲዖል ነበር፡፡

 

ለፍጥረት ሁሉ መዳን ምክንያት ያደረጋት ንጽሕት ዘር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትውልዷ በአባቷ በኩል ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፡፡ በእናቷ በኩል ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ወገን ነው፡፡ የአባቷ ስም ቅዱስ ኢያቄም የእናቷ ስም ቅድስት ሐና  ይባላል፡፡ ሁለቱም በሕግ በሆነ ቅዱስ ጋብቻ ሲኖሩ ለብዙ ዘመን ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጠናል በማለት ተስፋ እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት ደጅ እየጸኑ ኖሩ እንጂ፡፡ በዘመኑ ልጅ ያልወለደ ኀጢአተኛ፣ እግዚአብሔር የተጣላው ተደርጎ ይወሰድ ስለነበረ ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚያመጡትን መብዓ አይቀበሏቸውም፤ ይሰድቧቸው፣ ያሽሟጥጧቸውም ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ታግሰው ሲኖሩ እግዚአብሔር ትእግሥታቸውን ተመልክቶ የሚወልዷትን የድንግል ማርያምን ነገር በህልም ገለጸላቸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሲጠብቁ እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተፀንሳለች፡፡ በተፀነሰች ጊዜ ብዙ ተአምራት ተደርጓል፡፡ የሃናን ማሕፀን እየዳሰሱ፡- ብዙ እውራን አይተዋል፣ ድውያን ተፈውሰዋል፣ ምውታን ተነሥተዋል፡፡ ይህንን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ ኢያቄምን እና ቅድስት ሐናን በድንጋይ ወግረው በእሳት አቃጥለው ሊገድሏቸው በጠላትነት ሲነሡ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሊባኖስ ወደ ሚባል ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሳሉ በግንቦት 1 ቀን ከፀሐይ 7 እጅ የምታበራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመኀልይ በም.4፥8 ላይ እንደተናገረ “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ነይ…. ከአንበሶች ጉድጓድ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች፡፡” እንዳለ ይህ ትንቢት ተፈጸመ በተወለደች በ8ኛው ቀን ስሟን “ማርያም” ብለው አወጡላት ለመሆኑ ማርያም ማለት ምን ማለት ነው?

 

ሀ. ማርያም ማለት ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝ.126፥3 ላይ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፡፡” ብሎ እንደተናገረ አባቷ ቅዱስ ኢያቄም እናቷ ቅድስት ሐና ከእግዚአብሔር የተሰጠችን ስጦታችን፣ ሀብታችን ናት ብለው “ማርያም” አሏት፡፡ ለጊዜው ለእናት እና ለአባቷ ስጦታ ሁና ትሰጥ እንጂ ለፍፃሜው ለፍጥረት ሁሉ እናት አማላጅ ሆና ከእግዚአብሔር የተሰጠች ናት በተለይ ለክርስቲያኖች በእምነት እናትነቷን እና አማላጅነቷን ለሚቀበሉ በዮሐንስ ወንጌላዊ አማካኝነት እናት ሁና የተሰጠች ልዩ ስጦታ ናት አምላካችን ክርስቶስ በቀራኒዮ አደባባይ በመስቀል ተሰቅሎ ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ ለድኅነታችን እንደሰጠን ሁሉ እናቱንም እናት ትሁናችሁ ብሎ ሰጥቶናል፡፡” ዮሐንስ ወንጌላዊ ወደ ቤቱ እንደወሰዳት እኛም ወደ ቤተ ልቦናችን ልናስገባት ጣዕሟን በአንደበታችን ፍቅሯን በልቦናችን ልናሳድረው ያስፈልጋል፡፡ ዮሐ.19፥26 የድንግል ማርያም ጣዕሟ በአንደበታችን ፍቅሯ በልቦናችን ይደር፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ከእግዚአብሔር ተልኮ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መጥቶ እያመሰገናት እየተሳለማት የነገራት ነገር ቢኖር እርሷ “ምልዕተ ጸጋ ወክብር” እንደሆነች ነው፡፡ ሉቃ.1፥28 እንግዲህ መልአኩ ከእግዚአብሔር አግኝቶ የእመቤታችንን ነገር እንደነገረን የጐደለባት ጸጋ የሌለ እመቤት ናት እና እኛ ደግሞ ብዙ ነገር ጐድሎብናልና ከተትረፈረፈ ጸጋዋ እንድታድለን ምልዕተ ጸጋ ምልዕተ ውዳሴ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልንማፀናት ይገባል፡፡ እመቤታችን ጸጋ በረከት ታድለን፡፡

 

ለ. ማርያም ማለት ፍፅምት ማለት ነው፡ “ፍፅምት” ማለት እንከንና ጉድለት የሌለባት ማለት ነው፡፡ እመቤታችን ለጊዜው መልክ ከደምግባት ጋር አስተባብራ በመገኘቷ ፍፅምት ተብላለች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በባሕርይው ቅዱስ ነው፡፡ ዘሌ.19፥2 ቅዱስ እና ንፁሐ ባሕርይ የሆነ እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በወደደ ጊዜ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንደተናገረ “እግዚአብሔር በሰማይ ሁኖ ምሥራቁን እና ምዕራቡን ሰሜኑን እና ደቡቡን ዳርቻዎችን ሁሉ ተመለከተ እንዳንቺ ያለ አላገኝም የአንቺን መዓዛ ወደደ፤ ደምግባትሽን ወደደ፤ የሚወደውን ልጁን ወደ አንቺ ሰደደ” እንዲል፡፡ ንፁሐ ባሕርይ እግዚአብሔር ለማደሪያነት /ለተዋሕዶ/ እመቤታችንን መረጠ እርሷም ፍፅምት ናት የአዳም መርገም ያልወደቀባት /ጥንተ አብሶ/ የሌለባት ጠቢቡ ሰሎሞን በመኀል.4፥7 ላይ እንደተናገረ እንዲህ ብሎ “ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውር የለብሽም፡፡” እንዲል እንኳን የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቀርቶ ወዳጆቹ ቅዱሳን እንኳን አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ሲያደርጉ ከፍፁምነት ማዕረግ ይደርሳሉ ይህንንም ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክርላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ኖኅ በትውልዱ ጻድቅ ፍፁምም ሰው ነበር  ዘፍ.6፥9፡፡ ኢዮብም ፍጹምና ቅን እግዚአበሔርንም የሚፈራ ከክፋትም የራቀ ነበር ኢዮብ 1፥1፡፡ ይላል፡፡ የኖኅን እና የኢዮብን አምላክ የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍፅምትነቷ አያጠራጥርም፡፡ የድንግል ማርያም ጸጋ በረክት ይደርብን፡፡

 

ሐ. ማርያም ማለት የሕያዋን እናት ማለት ነው፡፡ ዘፍ.3፥20 ላይ “አዳምም ለሚስቱ ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና፡፡ ይላል በእርግጥ ሔዋን ለሕያዋን ሁሉ ማለትም ለፍጥረት ሁሉ እናት ናት ግን ፍጥረትን ሁሉ አስጐድታለች ማለትም አትብሉ ተብሎ ከእግዚአብሔር የታዘዘውን ዕፀ በለስን በልታ ለባሏ ለአዳም በማብላቷ በሰው ልጆች ላይ የሞት ሞት እንዲመጣ /እንዲፈርድባቸው/ ምክንያት ሁናለች ከእርሷ ምክንያተ ስህተትነት የተነሣ የገነት ደጃፎች ተዘጉ በምትገለባበጥ የኪሩብ ሰይፍ እንድትጠበቅ ሆነ፡፡ ዘፍ.3፥24 በዚህ የተነሣ በሰው ልጆች ላይ 5500 ዘመን ሞት ሰለጠነ፡፡ አዳም ግን “ሔዋንን” የሕያዎን ሁሉ እናት ብሎ በትንቢት የተናገረላት ሔዋንን ሳይሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ “በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኀወ ለነ” ይላል ትርጉሙም “ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ ዳግመኛ ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን” ማለት ነው፡፡ ሔዋን ሕያዋንን ሁሉ አስጐዳች ዳግማዊት ሔዋን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ ለሕያዋን ሁሉ እናት ሆና ፍጥረቱን ሁሉ ለማዳን ምክንያት ሆነች፡፡

 

ሕያዋን የሚባሉት ጥምቀተ ክርስትና ያላቸውን ወልድ ዋሕድ ብለው በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የሚያምኑትን ክርስቲያኖችን ነው፡፡ እነዚህ ሕያዋን  ናቸው፡፡ ጌታ በቅዱስ ወንጌሉ “በወልድ ያመነ የዘለዓለም ሕይወት አለው ያላመነ ግን አሁን ተፈርዶበታል፡፡” እንዲል ዮሐ.3፥37 ደግሞም ሰው ሰው ተብሎ በሕይወት ለመኖር ከእናት ከአባቱ መወለድ ግድ እንዲሆንበት ክርስቲያንም ክርስቲያን ይባል ዘንድ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት መወለድ አለበት ዮሐ.3፥5፡፡ የእነዚህ እናታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ አንድም ሕያዋን የሚላቸው ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃቸውን የነፍስ ሥራ ሠርተው በጽድቅ የተሸለሙ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ናቸው የእነዚህ እናታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናትና ስማን “ማርያም” አሉት፡፡

 

መ. ማርያም ማለት ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች የከበረች ደግ ፍጥረት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሚታየውንና የማይታየውን ብዙ ፍጥረት ፈጥሯል ከእነዚህ ፍጥረታት መካከል ግን ሰው እና መላእክት ክብሩን እንዲወርሱ ስሙን እንዲቀድሱ ለይቶ ፈጥሮአቸዋል፡፡ ከሰው መላእክት በቅድስና ለእግዚአብሔር የቀረቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መላእክት መካከል ስድስት ክንፍ ያላቸው ብዙ ዐይኖች ያሏቸው የእግዚአብሔርን ዙፋን የሚሸከሙ እግዚአብሔርም በዘፈቀደ ለወዳጆቹ ሲገለጽ የሚታይባቸው ክብር ያላቸው ናቸው፡፡ በፈጣሪያቸው ፊት ግን ሲታዩ ትእምርተ ፍርሐት አላቸው ከዙፋኑ የሚወጣው እሳት እንዳያቃጥላቸው በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን ይሸፍናሉ፤ ገጽህን ማየት አይቻለንም ሲሉ፤ በሁለት ክንፋቸው ከዳርቻ እስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣሉ ይወርዳሉ ባህርይህን ተመራምሮ መድረስ አይቻልም ሲሉ፡፡ እንዲህ ባለ ፍርሐት ፈጣሪያቸውን “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ምሉዕ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ” እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ ራዕ.4፣ ኢሳ.6 እነዚህ ከፍጡራን ሁሉ የከበሩ ለእግዚአብሔርም የቀረቡ ናቸው ከእነዚህ ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትበልጣለች፡፡ ምክንያቱም እነርሱ እንዲህ ከሚንቀጠቀጡለት ከሦስቱ ቅዱስ አንዱን ቅዱስ ወልደ እግዚአብሔርን ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች አዝላ የተሰደደች በማስተማር ዘመኑ ያልተለየች እስከ እግረ መስቀል ድረስ የነበረች የአምላክ እናት ናትና ስለዚህም ቅዱስ ኤፍሬም ሲናገር “ይእቲ ተዓቢ እም ኪሩቤል ወትፈደፍድ እም ሱራፌል እስመ ኮነት ታቦተ ለአሐዱ ዘእም ቅድስት ሥላሴ” ብሏል በእውነትም ከኪሩቤል እና ከሱራፌል ትበልጣለች ከቅድስት ሥላሴ አንዱን ወልደ እግዚአብሔርን በሕቱም ድንግልና ፀንሳ በሕቱም ድንግልና ወልዳዋለችና ይህ ጸጋ ለእመቤታችን እንጂ ከፍጡራን መካከል ለሌላ ለማንም አልተሰጠምና ከነገደ መላእክት ከደቂቀ አዳም በክብር የሚመስላት በጸጋ የሚተካከላት የለም፤ ከፍጡራን በላይ ያሰኛታል፡፡ “ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ….. ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ ነው፡፡ የልዑል እግዚአብሔርም ልጅ ይባላል፡፡” ሉቃ.1፥28፣ ሉቃ.1፥35 እንዲል፡፡

 

ሠ. ማርያም ማለት መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው /መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታስገባ/ ማለት ነው፡፡ የቀደመው ፍጥረት የታደሰባት ወደ ቀደመ ርስቱ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ምክንያተ ድሂን የሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ዛሬም ያለው ፍጥረት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የድንግል ማርያም ምልጃ ያስፈልገዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን መርቶ መንግሥተ ሰማያት የምታስገባ የመሆኗን ነገር በምሳሌ እንዲህ ስትል ታስተምራለች፡፡ በዘፀ.ም.32 እና 34 ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ሙሴ በደብረ ሲና 40 መዓልት 40 ሌሊት ከጾመ ከጸለየ በኋላ እግዚአብሔር ተቀብሎ ከተራራው ሲወርድ እስራኤል ጣዖት አቁመው ሲሰግዱ ተመለከተ በዚህ ጊዜ ፍቅረ እግዚአብሔር ቢያቃጥለው በፅላቱ ጣዖቱን መታው ፅላቱ ተሰበረ ጣዖቱ ደቀቀ፡፡ ወደ እግዚአብሔር ሲያመለክት ከማይነቅዝ እንጨት ሠርቶ ወደ ተራራው እንዲወጣ በዚያም እንደ ቀድሞው እንዲጾም እንዲጸልይ እግዚአብሔር አዘዘው እርሱም እንደታዘዘው አደረገ እግዚአብሔርም በተሰወረች ጣት ትዕዛዛቱን ጻፈበት ለሙሴም ሰጠው ሙሴም ይህንን ይዞ ከተራራው ሲወርድ ብርሃን ተሳለበት እስራኤል በዚች ፅላት እየተመሩ የዮርዳኖስን ባህር ከፈሉ ኢያሱ.3፥14-17 የኢያሪኮን ቅፅር ናዱ /አፈረሱ/ ኢያ.6፥8 ምድረ ርስት ከነዓን ገብተው ርስት ተካፈሉ፡፡ በዚህ ምሳሌ የቀደመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሙሴ የተሰጠው የእንቁ ፅላት የአዳም የፅላቱ መገኛ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ ለአዳምም እናትና አባት መገኛ የሚሆን የለውም ወድቆ መሰበሩ ሕግ ትዕዛዝ በመተላለፉ ከፈጣሪው መለየቱን ያመለክታል፡፡ ፅላቱ እንደተሰበረ ይቅር እንዳላለ አዳምም እንደወጣ ይቅር አላለም በንስሓው ተቀብሎታልና፡፡ ሁለተኛይቱ ፅላት እመቤታችን ሙሴ ሠርቶ መውሰዱ እመቤታችን በዘር መገኘቷን ከቅድስት ሐና ከቅዱስ ኢያቄም መወለዷን ያመለክታል፡፡ ከማይነቅዝ እንጨት መሥራቱ እመቤታችን በሐልዮ /በማሰብ/ በነቢብ /በመናገር/ በገቢር /መሥራት/ ኀጢአት እንዳልፈጸመች ንፅናናዋን ቅድስናዋን ያመለክታል፡፡ በፅላቱ ላይ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በማሕፀነ ድንግል የተቀረጸው የአብ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ዮሐ.1፥1 “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነው” ዮሐ.1፥14 የቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” እንዳለ፡፡ በዚያች ፅላት እስራኤል ባህር እንደተከፈለላቸው፣ ቅፅር እንደተናደላቸው ተመርተው ርስት እንዲወርሱ ጥንተ ጠላታትን ዲያብሎስ ተሸንፎ በእመቤታችን በተሰጣት ቃል ኪዳን አማላጅነት ከገቡ መውጣት ካገኙ ማጣት የሌለባት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ እድል አገኘን፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ከላይ የተጠቀሰውን አልን እንጂ ስለ እመቤታችንስ የተነገረው ብዙ ነው፡፡ የድንግል ማርያም ጣዕሟ በአንደበታችን ፍቅሯ በልቡናችን ይደርብን በአማላጅነቷ ለርሥተ መንግሥተ ሰማያት ታብቃን አሜን፡፡