ስንክሳር፡- መስከረም ስድስት

መስከረም 6 ቀን 2008 ዓ.ም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነብይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ዐረፈ፡፡

ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ በአምስቱ ነገሥታት ዘመን አስተማረ ትንቢትም ተናገረ፣ እሊህም ኦዝያን፣ ኢዮአታም፤ አካዝ፤ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው፡፡

በአካዝ ዘመንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ እነሆ ስለዚህ እግዚአብሔር ምልክትን ይሰጣችኋል፡፡ እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወለወዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፡፡

ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አንድ ሆነ ማለት ነው፡፡

እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቸው ወደ ሃይማኖቱም የሚያስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልንም ልጆች መስዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናትን እንደሚሾም ተናገረ፡፡

የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት በእግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምን ያጠፋው ዘንድ እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ፡፡

በዚያች ሌሊትም እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰናክሬም ሠፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺሕ አርበኞችን ገደለ፡፡ የለኪሶ ሰዎች ሲነጋ በተነሱ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አዩ፡፡

ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ እግዚአብሔር ትሞታለህ አንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው፡፡

ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ፣ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ፡፡ ይህን ከነገረው በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ነብዩ ወደ ኢሳይያስ መጣ፣ ሒደህ ለሕዝቅያስ የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፡፡ እነሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨመርኩልህ አለ በለው፡፡

ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮ ስለመመለሳቸው ትንቢት ተናገረ፡፡ የፈሳሽ ውኃን ምንጭ በማፍሰስ በእጆቹ ላይ እግዚአብሔር ምልክትን ገለጠ፡፡

ክብር ይግባውና ስለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ትንቢት ተናገረ፣ እንዲህም አለ፡፡ እርሱም በመከራው ጊዜ ነገርን አልተናገረም እንደ በግ ይታረድ ዘንድ መጣ፣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደማይናገር እንዲሁ በመከራው ጊዜ አልተናገረም፡፡

ከዚህም በኋላ ደግሞ በሕዝቅያስ ልጅ በምናሴ ላይ ትንቢት ተናገረ፣ ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሠነጠቀው፣ ምስክርነቱንም በዚህ ፈጸመ፡፡

ትንቢት እየተናገረ የኖረበትም ዘመን ሰብዓ ዓመት ከዚያም በላይ ይሆናል፡፡ እርሱም ያስተማረው ክብር ይግባውና ጌታችን ከመምጣቱ በፊት በዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከሁላችን ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ከመስከረም እስከ የካቲት፣ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ደርጅት፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ 23-25፡፡ 

ስንክሳር፡- መስከረም አምስት

መስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም አምስት በዚች ቀን የከበረች ሶፊያ ከሁለት ልጆቿ አክሶስና በርናባ ከሚባሉት ጋር በሰማዕትንት ሞተች፡፡

ይችም ቅደስት አስቀድማ አረማዊ ነበረች፣ ወላጆቿም ጣዖታትን የሚያመልኩ ናቸው፡፡ እርሷም በልቧ አስተዋለች፣ መረመረችም፣ የወላጆቿ ሃይማኖት ከንቱ እንደሆነ ተረዳች፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ መኖፌ ኤጲስ ቆጶስ ሔዳ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ታመነች፡፡ እንዲህም አለችው፤ በሕያው አምላክህ አምኛለሁና አጥምቀኝ እርሱም ሃይማኖትን፣ የቤተ ክርስቲያንም ሕግ አስተማራት፡፡ ከዚህም በኋላ ከልጆቿ ጋር በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃት፡፡

ከዚህም በኋላ የሀገር ሰዎች ለአማልእክት መስገድን ትታ ክርስቲያን እንደሆነች በገዢው በክላድያኖስ ዘንድ ወነጀሏት፡፡ ገዢውም ወደ እርሱ አስቀርቦ መረመራት፡፡ እርሷም ክብር ይግባውና በክርስቶስ አመነች እንጂ አልካደችም፣ ከልጆቿም ጋር ብዙ ሥቃይን አሠቃያት፡፡

በሥቃይም ውስጥ ላሉ ልጆቿ ታስታግሳቸውና ታጽናናቸው ነበር፣ እንዲህም ትላቸው ነበር፡፡ ልጆቼ ጠንክሩ፣ ጨክኑ የአንጌቤንዋን እመቤት ሶፍያን እመስላታለሁ፤ እናንተም ጲስጢስ፤ አላጲስ አጋጲስ የተባሉ ልጆቿን ምሰሉ፣ እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱላት፣ እናት ሆይ እኛ ፍለጋሽን እንከተላለንና ስለእኛ አትፈሪ ይህንንም በሚባባሉ ጊዜ ከእናታቸው ጋር ተሳሳሙ፡፡

ገዢውም ሲሳሳሙ አይቶ ደናግል ልጆቿ እንዲፈሩ እናታቸውን በጅራፍ ይገርፏት ዘንድ አዘዘ፡፡ ያን ጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶ እናታቸውን ከግርፋት ሲሠውራት አዩ፡፡

ዝንጉዎችም ይገርፏት ዘንድ ባራቆቷት ጊዜ በዚያን ሰዓት እንዲህ በማለት ትጮህ ነበር፡፡ ዓለሙን ሁሉ በፈጠረ በእውነተኛ አምላክ በእግዚአብሔር የማምን ክርስቲያናዊት ነኝ፣ ያን ጊዜም ገዢው ምላሷን ከሥሩ እንዲቆርጡ አዘዘ፡፡ እርሷ ግን መጮህንና መናገርን አላቋረጠችም፡፡

ከዚህም በኋላ ገዢው ወደ እሥር ቤት እንዲወስዷት አዘዘ፤ ትሸነግላትም ዘንድ ሚስቱን ወደእርሰዋ ላከ፡፡ እርሰዋ ግን ምንም አልመለሰችላትም፡፡ ራሷንም በሰይፍ ይቆርጧት ዘንድ አዘዘ፤ የድል አክሊልም ተቀበለች፡፡ አንዲት ሴትም መጥታ ሥጋዋን በጭልታ ወሰደች፣ ወደ ቤቷም አስገብታ በፊቷ መብራትን አኖረች፡፡

ከዚህም በኋላ ልጆቿን ጠርቶ እሺ ይሉት ዘንድ አስፈራራቸው፣ እምቢ ባሉትም ጊዜ እያከታተለ ራሳቸውን አስቆረጠ፣ ምሥክርነታቸውንና ተጋድሏቸውንም ፈጸሙ፡፡ ከመቃብራቸውም በሽታውንና ደዌውን ሁሉ የሚፈውሱ ብዙ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

ደግ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ የቅዱሳት ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወደ ቁስጥንጥንያ አፍልሶ ወሰደ፡፡

የሶፍያንና የልጆቿን ዜና ከመስማቱ በፊት ታላላቅና ሰፊ የሆኑ ቤቶች እንዲሠሩ በላይዋም ይቺ ቤት የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ናት ብለው ጽሑፍ እንዲቀርጹበት አዘዘ፡፡ እነርሱም ንጉሡ እንዳዘዘ ወደ ማታ ሲሆን ይጽፋሉ፣ የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ ያንን ደምስሶ ይቺ ቤት የሶፍያ ናት ብሎ ይጽፋል፡፡ የሕንፃውም ባለሙያዎች የሚያደርጉትን አጡ፣ መጻፋቸውንም ተዉ፡፡

በአንዲት ቀንም የንጉሥ ልጅ ብቻውን ሲጫወት መልአክ ተገለጸለትና የዚች ቤት ስሟ ማነው አለው፡፡ ሕፃኑም አላወቅሁም አለው፣ መልአኩም ሁለተኛ እንዲህ አለው አባትህን የሶፍያ ቤት ብለህ ሰይማት ብለህ ንገረው ሕፃኑም ተመልሼ እስክመጣ ትጠብቀኛለህን አለው፣ መልአኩ አዎን እጠብቅሃለሁ አለው፡፡

አባቱም ይህን ሰምቶ መልአክ እንደሆነ ዐወቀ፡፡ ሕፃኑንም በመጠበቅ ምክንያት ያ መልአክ ከዚያች ቦታ እንዳይሄድ ብሎ ንጉሡ ልጁን ገደለው፡፡ መልአኩም ሕፃኑን እየጠበቀ እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡

የዚያች ቤተ ክርስቲያም ርዝመቷ ሰባት መቶ ዘጠኝ ክንድ ሆነ፣ አግድመቷም ሦስት መቶ ሰባት ክንድ፣ ምሰሶዎቿም ዐራት መቶ፣ ጠረጴዛዎቿም ስምንት፣ የሚያበሩ ዕንቁቿ ዐራት ናቸው፣ ከአጎበሩ በላይ የተቀረጹ ኪሩቤልም በየሁለት ክንፎቻቸው የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ታቦት ይጋርዳሉ፡፡

ሥጋቸው በውስጡ ያለበትን የቅድስት ሶፍያንና የልጆቿን ሳጥን በታላቅ ምስጋናና ክብር ወደዚያ አስገብተው አኖሩ፡፡

በድኖቻቸውን የሰበሰበች ያቺንም ሴት ከእርሳቸው ጋር ቀበሯት፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ከመስከረም እስከ የካቲት፣ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ደርጅት፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ 20-21፡፡

01awropa

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥንና የሬድዮ ሥርጭት በአውሮፓ በስልከ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም

01awropaማኅበረ ቅዱሳን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን እንዲሁም በሬድዮ አያሰራጨ የሚገኘውን መንፈሳዊ መርሐ ግብር በአውሮፓም ምእመናን ባሉበት ሆነው በቀላሉ በስልክ ሥርጭቱን መከታተል እንዲችሉ ማድረጉን የአውሮፓ ማእከል አስታወቀ፡፡

በዚህም መሠረት በጀርመን የሚገኙ ምእመናን በ0699-432-98-11 ፣በእንግሊዝ /UK/ 033-032-63-60 በመደወል  መከታተል እንደሚችሉ ከማእከሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

በሰሜን አሜሪካም በተመሳሳይ ሁኔታ የቴሌቪዥንና የስልክ አገልግሎት መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ሥርጭት በስልክ የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ

ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን እየተዘጋጀ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ የሚሰራጨው መርሐ ግብር በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን በቀላሉ በተመቻቸው ጊዜ ስልክ ደውለው የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ።

ምእመናን 605-475-8172 ስልክ ቁጥር በመጠቀም በተመቻቸው ጊዜ መርሐ ግብሩን መከታተል እንደሚችሉ በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የስልክ አገልግሎቱ የሚሠራው በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን ብቻ ሲሆን በቅርቡ በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲኖር ማኅበረ ቅዱሳን በመሥራት ላይ ይገኛል::

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ሥርጭት በስልክ የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ

ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን እየተዘጋጀ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ የሚሰራጨው መርሐ ግብር በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን በቀላሉ በተመቻቸው ጊዜ ስልክ ደውለው የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ።

ምእመናን 605-475-8172 ስልክ ቁጥር በመጠቀም በተመቻቸው ጊዜ መርሐ ግብሩን መከታተል እንደሚችሉ በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የስልክ አገልግሎቱ የሚሠራው በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን ብቻ ሲሆን በቅርቡ በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲኖር ማኅበረ ቅዱሳን በመሥራት ላይ ይገኛል።

Â