ጾመ ነቢያት

ኅዳር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ለሰው በተሰጠው የመዳን ተስፋ አስቀድመው ነቢያት ትንቢት በተናገሩት መሠረት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕተ ንጹሐን ቅድስት ድንግል ማርያም የመወለድን ምሥጢር (ምሥጢረ ሥጋዌ) መታሰቢያ በማድረግ ሕዝበ ክርስቲያን ጾመ ነቢያትን እንጾማለን፡፡ ይህ ጾም ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ በመሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ሊጾመው ይገባል፡፡ የ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት የዘመነ ሉቃስ ጾመ ነቢያት ኅዳር ፲፭ ጀምሮ እስከ ጌታችን የልደት በዓል ዋዜማ ታኅሣሥ ፳፰ ድረስ ነው፡፡ በታኅሣሥ ፳፱ በዓለ ልደትን መታሰቢያ በማድረግ የጾሙ ፍቺ ይሆናል፡፡

በዘመነ ብሉይ ነቢያት በእግዚብሔር ፈቃድ ስለሚፈጸመው የጌታችን መወለድ፣ ወደ ግብፅ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ መጠመቅ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት መከራ መቀበሉ፣ መሰቀሉ፣ በሦስተኛው ቀን መነሣቱ፣ በዐርባኛው ቀን ማረጉና ዳግም በዓለም ፍጻሜ ጊዜ ለፍርድ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግረዋል፡፡

ለአዳም በተገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ፍጻሜውን በተስፋ በመጠበቅ አምላካቸውን በጸሎትና በጾም ተማጽነዋል፡፡ ምንም እንኳን እነርሱ በዓይነ ሥጋ መውለዱን እና ገቢረ ተአምራቱን ማየት ባይችሉም በእምነት ነገረ ድኅነት እንደሚፈጸም ዐውቃዋል፡፡ ስለዚህም እኛም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የድኅነታችን መሠረት መሆኑን እንዲሁም የትንቢተ ነቢያት መፈጸሙን በማመን ጾመ ነቢያትን እንጾማለን፡፡

በጾመ ነቢያት የሚገኙትን ሳምንታት ደግሞ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

ዘመነ ስብከት

ዘመነ ስብከት ከታኅሣሥ ሰባት ቀን እስከ ታኅሣሥ ዐሥራ ሦስት ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት ናቸው፡፡ ይህ ወቅት ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ያለው ትውልድ የሚታሰብበት፣ ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያት በትንቢት፣ ዳዊት በመዝሙሩ በብዙ ምሳሌ ይወርዳል፤ ይወለዳል ሲሉ የተናገሩት የሚታሰብበት ነው፡፡ በዚህም ወቅት የሚዘመረው መዝሙር «ወልደ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ፤ ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን» የሚል ነው ቅዱስ ያሬድ፡፡ (መዝ.፻፵፫፥፯፣ኢሳ.፷፬፥፩)

በዘመነ ስብከት ከልደተ አብርሃም እስከ ልደተ ዳዊት ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከው ስብከት ይታሰባል፡፡ የሚነበበውም ምንባብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም በትንቢት እንደጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል፡፡ (ዮሐ.፩፥፵፩-፵፬)

ብርሃን

ከዘመነ ስብከት ቀጥሎ ያለው ሰንበት «ብርሃን» ሲሆን ከታኀሣሥ ፲፬ እስከ ታኅሣሥ ፳ ያሉትን ቀናት ያካትታል፡፡  በዚህ ወቅት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን ያለው ዐሥራ ዐራት ትውልድ ይታሰባል፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ዳዊት «አቤቱ ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፤ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ» በማለት እንደተናገረው ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ወገን የመወለዱ ትንቢት ይታሰባል፡፡ (መዝ.፵፪፥፫)

ቅዱስ ዮሐንስም ሲመሰክር «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ» በማለት ተናግሯል፡፡ ራሱ ጌታችን  «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም» ብሎ ተናግሯል፡፡ (ዮሐ.፩፥፮-፱፣፰፥፲፪) እንዲሁም ብርሃንን እውነት ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፤ ላክልን ሲል ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ስደድልን ማለቱ ነው፡፡

በዚህ ወቅት የሚዘመሩት መዝሙራት «ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ወይዜንዎ ለጽዮን በቃለ ትፍሥሕት፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፣ የምስጋናን ቃል ለጽዮን የሚነግራት ወልድ በክብር፣ በጌትነት እንደሚመጣ አስቀድሞ በኦሪት ነገረ፤ አስታወቀ» የሚሉ ናቸው፡፡

ኖላዊ

ከታኀሣሥ ፳፩ እስከ ታኅሣሥ ፳፯ ኖላዊ ይባላል ነው፤ የቃሉ ትርጉሙም እረኛ ማለት ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ሕዝቡን በነፍስ በሥጋ የሚጠብቅ ቸር እረኛ መሆኑን ለማመልከት ሳምንቱ በኖላዊ ተሰይሟል፡፡ ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚነበሩትን የእግዚአብሔር ሕዝብ በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንደሚወለድ በትንቢት መናገራቸውን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተብሏል፡፡

በዚህ ወቅትም የሚዘመረው መዝሙሩም «ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃለ እግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅና ቃሉ የሆነ ክርስቶስ ከላይ የወረደ ወደ ዓለም የመጣ እረኛ» የሚል ሲሆን የሚነበበው ደግሞ አንቀጸ አባግዕ የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ (ዮሐ.፲፥፩-፳፪) ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር» በማለት ተናግሯል፡፡ (፩ጴጥ.፪፥፳፭)

ነቢያት ይወርዳል፤ ይወለዳል ብለው የተናገሩት ትንቢት በመፈጸሙ በጌታችን ልደት መላእክት እና ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ እንስሳት በአንድነት ሆነው በደስታ የዘመሩበትን የልደት በዓል በተስፋ እያሰብንና እየጠብቅን ጾመ ነቢያትን ልንጾም ይገባል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር በቅዱሳን ነቢያት አማላጅነትና ተራዳኢነት ይምረን እና ከጾሙ በረከት ያሳትፈን ዘንድ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!