debr 10

ደብረሊባኖስ ገዳምን የሚታደጉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ማለደ ዋስይሁን

 

debr 10

የደብረ ሊባኖስ ገዳምን በሁለንተናዊ መልኩ ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የገዳሙ ጸባቴ አባ ኃይለ መስቀል ውቤ አስታወቁ፡፡ ኅዳር 9 2005 ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ከገዳሙ ወዳጆች ጋር በተደረገው የምክክር መርሐ ግብር ላይ ይፋ እንደተደረገው ገዳሙ ያሉበትን ችግሮች ቀርፎ በቀጣይም አርአያ ምሳሌ ወደሚሆንበት ደረጃ የሚያደርሱትን እንቅስቃሴዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ለማከናወን መታቀዱን ጸባቴው ገልጸዋል፡፡

 

በዕለቱ በምክክር መርሐ ግብሩ የተገኙት፣ ገዳሙ የሚገኝበት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ገዳሙ በሁሉም ወገኖች ትኩረት ተነፍጎት የቆየ መሆኑን አውስተው በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ከነበረው ዘርፈ ብዙ ሚናና ከታዋቂነቱ አንጻር ጠያቂ ተቆርቋሪ አጥቶ መኖሩ ሲያሳዝናቸው መቆየቱን አውስተዋል፡፡ በዕለቱም የማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ገዳሙ አሁን ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያመለክት ጥናት በተለያዩ የመረጃ ማግኛ ዘዴዎች ተጠቅመው መሥራታቸው የተገለጸ ሲሆን የጥናቱም ውጤት ጠቅለል ብሎ በኢንጂነር ዮናስ ምናሉ እና በዶክተር ሳሙኤል ኃይለማርያም ቀርቧል፡፡

 

ወቅታዊ ሁኔታውን በማሳየት ሳያበቃም ወደፊት ተግባራዊ ለማድረግ ስለታሰቡት ፕሮጀክቶች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ወደፊትም እያንዳንዱ ፕሮጀክት የሚጠይቀውን የገንዘብ፣ የሙያ፣ የሰው ኃይል ወዘተ ፍላጎት ባመላከተ ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን ሁሉም በምክክሩ ላይ የተሳተፉ የገዳሙ ወዳጆች ተግባሩ በመላው ሀገሪቱ ያሉ ምእመናንን ያሳተፈ ሆኖ በጥብቅና በጥልቅ ሁኔታ  መጀመር አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

 

በዕለቱ በተደረገውም ውይይት ተሳታፊዎች በገዳሙ ብዙ ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ የገዳሙ አንገብጋቢ ችግሮች ቅድሚያ እንዲሰጣቸውና በየደረጃውም የገዳሙን ልዕልና የሚያስጠብቁና ምሳሌ የሚያደርጉትን ሌሎች ላቅ ያሉ ፕሮጀክቶች ወደመተግበር እንዲገባ ሲያሳስቡ ተስተውሏል፡፡ ይህንኑ በጎ ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያነሣሣ የሕዝብ ጉባኤና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በታኅሣሥ 14 2005 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በጥሪው የሚሳተፉና በቅስቀሳውም የሚሰማሩ እጅግ በርካታ ወገኖች የሚጠበቁ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው መርሐ ግብር እንደሆነም ተገልጿል፡፡