የአብነት ትምህርት ቤት ለመደገፍ የግንባታና የቋሚ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ቀረበ

መጋቢት 7/2004 ዓ.ም.

በዳዊት ደስታ


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ፍቼ ሀገረ ስብከት፣ በሰንዳፋ አዳማ በበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገጥመን የአብነት ትምህርት ቤት ለመደገፍ የግንባታና የቋሚ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ዕቅድ ከባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 18 ቀን 2004 ዓ.ም. በደብሩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ቀረበ፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት  መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የአብነት ትምህርት ቤቶች ፕሮጀክት ክትትል ባለሙያ የሆኑት ዲ/ን ጌታዬ መኮንን የአብነት ትምህርት ቤት ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ እንዲኖራቸው የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡ በመቀጠልም ለሚተገበረው ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ማእከል የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ፕሮጀክት ን/ክፍል ጸሓፊ አቶ አንዱዓለም ተስፋዬ የፕሮጅክቱን መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

 

በፕሮጀክት ትግበራው የግብርና ሥራ፣ የሰብል ምርት ፕሮጀክትና የወተት ላም እርባታ ዕቅድን ጨምሮ ለአብነት ተማሪዎቹ የማደሪያና መማሪያ ክፍል፣ የመጸዳኛና ንጽህና መስጫ፣ ቤተ መጻሕፍት እና ማብሰያ የማእድ ቤት ግንባታ ያካተተ ነው፡፡ ይህን ፕሮጀክት ለመተግበር 3.8 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን ከበጎ አድራጎት፣ ከማኅበራት፣ ከሠራተኛ ጉባኤያት፣ በአካባቢው ምእመናን ወጪው እንደሚሸፈን ከቀርበው ፕሮጀክት ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

የበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ አማኑኤል አያኔ በበኩላቸው የአብነት ተማሪዎቹ ያለባቸውን የመጠለያ፣ የምግብ እና የአልባሳት ችግር ለመፍታት የሚተገበረው ፕሮጀክት ዐይነተኛ ሚና እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት አጋዥ የሚሆኑ የአካባቢው ምእመናን ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለታ ቁምቢ የተባሉ ምእመን የአብነት ተማሪዎች ላለባቸው ችግር አቅሜ በፈቀደ መጠን ለትምህርት ቤቱ መሥሪያ ለሚያስፈልገው ቁሳቁስ ለመርዳት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 

በበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኘውን የአብነት ት/ቤት በዘላቂነት ለመደገፍ የታቀደው ፕሮጀክት ምእመኑ እንዲያውቀው የቀረበ ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት ዕቅድ ትግበራ ላይ ከ90 በላይ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ለዕቅዱ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡