gedamat 11

የኔታ ይቆዩን የገዳማት ዐውደ ርእይ በፓሪስ ከተማ

ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ደረጄ ግርማ

 

gedamat 11የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የፈረንሳይ ግንኙነት ጣቢያ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዋውቅ ዐውደ ርእይ ማዘጋጀቱን ገለጠ።

 

ዐውደ ርእዩም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ለሀገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ፣ በተለይም ጥንታዊ ገዳማት ትናንትና ዛሬ እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶችን ነባራዊ ሁኔታ የሚዳስስ፤ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን የሚጠቁም እንዲሁም ከሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጠበቀውን ድርሻ የሚያመላክት ዐውደ ርእይ ይቀርባል።

ከዚህም በተጨማሪ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስኮላርሸፕ፤ የላይ ቤት ትርጓሜ ፕሮጀክት እንዲሁም የቅዱስ ያሬድ 1500 ዓመት መታሰቢያ የሚያመላክቱ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ ዐውደ ርእዩም ሚያዚያ ፲፰ ቀን ፳፻፭ ዓም ለፓሪስ እና አካባቢ ምእመናን እንደሚቀርብ ተገልጿል። ከፓሪስ ደብረ ም/ቅ/ማርያም ሰበካ ጉባኤ ጋር በመተባበር ሚያዚያ ፲፱ ቀን ፳፻፭ ዓም ልዩ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን በዕለቱም በገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ከዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ለዚህ ዝግጅት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የማኅበረ ቅዱሳን ቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አንድ ልዑክ እንዲሚልክ ለማወቅ ተችሏል።

 
በአውሮፓ የምትገኙ ሁላችሁም በዝግጅቱ እንድትታደሙ የተጋበዛችሁ ሲሆን በርቀት ያላችሁ ለመርሐ ግብሩ ስኬት በጸሎት እንድታግዟቸው አስተባባሪ ኮሚቴው ጥሪውን አስተላልፏል።