የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ዛሬ አስመረቀ፡፡

ሰኔ ፲፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ለአምስትና ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ዛሬ ረፋድ ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ አስመረቀ፡፡

በምረቃው ሥርዓት ላይም ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያዎች ሓላፊዎች፣ የሀገረ ስብከት ሠራተኞች፣ የገዳማት፣ የአድባራትና የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ የኮሌጁ መምህራን፣ ደቀ መዛሙርትና ሠራተኞች፣ እንደዚሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂዎች ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ኮሌጁ ከተመሠረተበት ከ፲፱፴፭ ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ሊቃውንትን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው በዛሬው ዕለትም በቀኑና በማታው መርሐ ግብር ትርጓሜ መጻሕፍትን ተምረው በድምሩ ፪፴፮ (ሁለት መቶ ሠላሳ ስድስት) ዕጩ መምህራን መመረቃቸዉን፤ ከእነዚህ መካከልም አንደኛው ማየት የተሳናቸው፤ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች መኾናቸውን ተናገረዋል፡፡

በዕለቱ በመንፈሳዊ ኮሌጁ ደቀ መዘሙርትና ዕጩ መምህራን ያሬዳዊ ዝማሬ የቀረበ ሲኾን፣ በተጨማሪም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን የሚያወድሱ፤ አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲስተካከሉ የሚጠቁሙ ቅኔያት ከተበረከቱ በኋላ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎች ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከብፁዕ ሥራ አስኪያጁ እጅ የሽልማትና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

ተመራቂ መምህራኑም በተወካያቸው አማካኝነት የዓቋም መግለጫቸዉን ያሰሙ ሲኾን፣ በዓቋም መግለጫቸውም ለመምህራን የበጀት ማስተካከያ እንዲደረግና በኮሌጁ ከሚሰጡት የብሉያትና የሐዲሳት ትርጓሜ ትምህርቶች በተጨማሪ መጻሕፍተ ሊቃውንትና መነኮሳትም መካተት እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ተመራቂዎቹ አያይዘውም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጠብቀው እንደሚያስጠብቁ፤ የመናፍቃንን (የሐራ ጥቃዎችን) የኑፋቄ ትምህርት በጽናት እንደሚታገሉ፤ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸዉም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሕይወታቸዉን አሳልፈው እንደሚሰጡ፤ እንደዚሁም ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያወጣቸውን ቀኖናዎችን በማክበር ቤተ ክርስቲያንን በታዛዥነት እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በምረቃ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ሲያደርጉ እንደገለጹት መንፈሳዊ ኮሌጁ ያሉበት ችግሮች መዋቅራቸዉን ጠብቀው ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለቅዱስ ሲኖዶስ ቢቀርቡ ተገቢ እንደ ኾነ ገልጸው *ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጉዳዮችን በማጣራት ለችግሮቹ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነው* ብለዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊም አባታዊ ቃለ ምዕዳን በሰጡበት ወቅት ስብከተ ወንጌል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አገልግሎት መኾኑን ጠቅሰው የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጨምሮ ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ግንባር ቀደም በመኾን የጊዜውን የኑሮ ኹኔታ ባገናዘበ መልኩ የመምህራኑንና የደቀ መዛሙርቱን በጀት ለማስተካከል መዘጋጀት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ የምረቃ ሥርዓቱ ከቀኑ 6፡25 ተፈጽሟል፡፡