የማኅበረ ቅዱሳን አምስተኛው ዙር ዐውደ ርእይ ተጀመረ፡፡

ዐውደ ርእዩ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ከጠዋቱ 2፡00 እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ ለተመልካቾች ክፍት ኾኖ ይቆያል፡፡

ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀውና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው አምስተኛው ዙር መንፈሳዊ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የማኅበሩ ሥራ አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ እንደዚሁም የዐውደ ርእዩ ተመልካቾች በተገኙበት በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማእከል ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአባቶች ጸሎት ተጀምሯል፡፡

በጸሎተ ወንጌሉ የተሰበከው ምስባክ፡- ጥቀ ዐቢይ ግብርከ እግዚኦ ወኵሎ በጥበብ ገበርከ መልዐ ምድረ ዘፈጠርከ፤ አቤቱ ሥራህ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፡፡ የፈጠርኸውም ፍጥረት ምድርን ሞላ፤ /መዝ.፻፫፥፳፬/ የሚለው ትምህርት ሲኾን፣ የተነበበው የወንጌል ክፍልም ሉቃ. ፲፥፳፩-፳፬ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡

ጸሎተ ወንጌሉና ኪዳኑ እንደ ተፈጸመ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ ዐውደ ርእዩ በይፋ ለተመልካች ክፍት ኾኗል፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው በዚህ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን ማንነትና ሐዋርያዊ ተልዕኮ በዓለም፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎችና ከምእመናን የሚጠበቁ ጉዳዮች የትእይንቱ አርእስት ኾነው ይቀርቡበታል፡፡

ዐውደ ርእዩ ከግንቦት ፲፯-፳፪ ቀን ፳፻፰ (17-22 ቀን 2008) ዓ.ም፣ ከጠዋቱ 2፡00 እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ለተመልካቾች ክፍት ኾኖ ይቆያል፡፡

ከመጋቢት ፲፭-፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለተመልካች ሊቀርብ የነበረው ይህ ዐውደ ርእይ ለጊዜው ግልጽ ባልነበረ ምክንያት ታግዶ ቢቆይም፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ውይይት እገዳው ተነሥቶ ለእይታ በቅቷል፡፡