ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጨረሻ ክፍል

የካቲት ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፬. ነገረ ማርያም

፬.፩ አንጢዲቆማርያጦስ

እነዚህ መናፍቃን “አፅራረ ማርያም (የማርያም ጠላቶች)” ይባላሉ፡፡ መድኃኒታችንን ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር በባልና ሚስት ልማድ ኖረች በማለት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የጽርፈት ቃል የሚናገሩ መናፍቃን ናቸው፡፡ ለኑፋቄያቸው መነሻ ያደረጉት የበኵር ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም የሚለው ንባብ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህ ንባብ እንዴት እንደሚፈታና እንዴት እንደሚተረጎም በማመሥጠር ለእነዚህ ዝንጉዓን መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና፣ ቅድስናና ዘለዓለማዊ ድንግልና ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ከተከራከራቸው በኋላ የመለኮትን አዳራሽ ሊቀርባት የሚችል የትኛው ሥጋዊ ነው? ምን ሰው ወደ መለኮት አዳራሽ ሊገባ ይችላል? በማለት ያሳፍራቸዋል፡፡ እኛ ግንድንግል ማርያምን የአምላክ እናት ናት፤ ከወለደችውም በኋላ ዘለዓለማዊት ድንግል ናት› እንላለን ይላል፡፡

፬.፪ “እመቤታችን በሩካቤ አልተወለደችም” ለሚሉ

አባ ጊዮርጊስ ለእነዚህ መናፍቃን መልስ ሲሰጥ “… መልአኩእነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወልድንም ትወልጃለሽብሎ የምሥራች በነገራት ጊዜወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?› ብላ ያደነቀች እርሷን እንደምንበሩካቤ አልተወለደችምይሏታል? እናቷ እርሷን ያለ ሩካቤ ፀንሳት ቢሆን ኖሮ ድንግልወንድ ስለማላውቅ ይህ እንደምን ሆንልኛል?› ባላለች ነበር! በማለት አባቷ ኢያቄም እናቷም ሐና መሆኗን በመጥቀስ ያሳፍራቸዋል፡፡

፬.፫ ድንግል ማርያምና መስቀልን ለሚያበላልጡ

ሊቁ እነዚህን ስለ ማርያምና ስለመስቀል እንደሚክዱ በጆሯችን የገባ ወሬ አለ፡፡ እኩሌቶቹ የወለደችው ማርያም ከመስቀሉ ትበልጣለች ይላሉ፤ እኩሌቶቹም በሕማማቱ ደም የተቀደሰ መስቀል ይበልጣል ይላሉ፡፡ እኛ ግን ማርያም አምላክን የወለደች እንደሆነች እናምናለን፡፡ መስቀሉም መለኮት በተዋሐደው የትስብእት ደም የተቀደሰ የብርሃን ማዕተብ መሆኑን እናምናለን በማለት ይመልስላቸዋል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከእነዚህም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለማጣመም ለሚሞክሩ ሌሎች ስሑታንም መልስ ሰጥቷል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡-

  • “ወደ ቤተ ክርስቲያን ኃይል አይወርድም፣ ኅብስቱም ወደ ክርስቶስ ሥጋነት፣ ወይኑም ደሙን ወደ መሆን አይለወጥም ለሚሉ ሊቁ ሲመልስ “‹ሰማየ ሰማያት የማይወስነው እግዚአብሔር አራት ጎኖቿ ባነሱ በሰው እጅ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ያድራል?› የሚሉ አሉ፡፡ እኛ ግንበጽርሐ አርያም ያለ አኗኗሩ ሳይጎድል ይቀድሳት ዘንድ የመለኮት ኃይል በቤተ ክርስቲያን ያድራል› እንላለንይላል፡፡ በተጨማሪም “… ከከሐዲዎች መነሣሣት የተነሣ እንዳትነዋወጥ ኃይል ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃታል፡፡ የሚጠብቃት እርሱ ሲሆን ኃይልን ትሸከመዋለች፤ ኃይል ትጎናጸፋለች፤ ኃይልም ትታጠቃለች፤ ኃይላትም ይከቧታል፤ የሠራዊት ጌታ ሠረገላ አድርጓታልና በማለት ይመልስላቸዋል፡፡
  • ስለ ሥጋ ወደሙም “‹ኅብስቱ የክርስቶስን ሥጋ፣ ወይኑም ደሙን መሆን ይችላልን?የሚሉ አሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ በተቀደሰ ጊዜ ኅብስት ከልማዳዊ ኅብስትነት ሥጋውን ወደ መሆን ይለወጣል፤ ወይንም ከልማዳዊ ወይንነት ደሙን ወደ መሆን ይለወጣል በማለት ምሥጢረ ቍርባንን ያብራራል፡፡ ለድንግል የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ መምጣት ልጅ ሆናት፤ እርሷም በልዑል ኃይል እናት ሆነችው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ እርሷ ባይመጣ፣ የልዑል ኃይልም ባይጋርዳት የልዑልን ልጅ ትሸከመው ዘንድ ባልተቻላት ነበር፡፡ ኅብስቱና ወይኑም እንዲሁ ካህኑ አቤቱ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም እንዲያደርገውበዚህ ኅብስትና ጽዋ ላይ ቅዱሱን ኃይል ትልክ ዘንድ እንለምንሃለን፤ እንማልድሃለንባለ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ሥጋና ደም ይሆናል በማለት ይመልሳል፡፡
  • ስለ ምሥጢረ ሥጋዌም የሚከተለውን ትምህርት ያስተምራል፤በማርያም ማኅፀን ፍጹም የሕይወት እንጀራ ተፀነሰ፡፡ ይኸውም ለተቀደሰች ምሥጢር የበረከት ፍሬ ሆኖ የተሰጠ ከአብርሃም ዘር የተገኘ ሥጋ ነው፡፡ ከባሕርይዋ ደምም በመንፈስ ቅዱስ መጐብኘት የወይን ፍሬ አፈራ፡፡ በአብም በመጋረዱ ኃይል የሚናገር የወይን ደም የመለኮትም ሥጋ ኅብስት ተፀነሰ፡፡ ስለዚህም መድኃኒታችንከሰማያት የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሥጋዬን የበላ የእኔን ሥጋ ስለበላ በሕይወት ይኖራል፤ ደሜንም የጠጣ ሞትን አይቀምስም› አለ፡፡ ዳግመኛምአብ ሕያው እንደሆነ እኔም የአብ ልጅ ስለሆንሁ ሕያው ነኝሥጋዬንም የበላ የእኔን ሥጋ ስለበላ በሕይወት ይኖራል› አለ፡፡ እንዲህ ያለውን ጸጋ አቃልለን እንደምን እንድናለን? እኛ ግን በመንበሩ ላይ ሆኖ በካህኑ እጆች የሚከብረው ኅብስትና ወይኑ ፍጹም የክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሆነ እናምናለን፡፡

፬.፬ ሰዱቃውያን

ሰዱቃውያን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ መናፍቃን ናቸው፡፡ ሊቁ ጌታችን በሥጋዌው ወራት በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም በማለት የመለሰላቸውን እየጠቀሰ መልስ ይሰጣቸዋል (ማቴ. ፳፪፡፴)፡፡

  • ነፍስ ከሥጋ ጋር ትሞታለች” ለሚለው፡- ይህ መናፍቅ ነፍስ ከሥጋ ጋር ትሞታለች፤ ሙታን በተነሡ ጊዜ ከሥጋ ጋር ትነሣለች የሚል ኑፋቄ ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ ሊቁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ በማለት የተናገረውን በመጥቀስ ነፍስ የማትሞት መሆኗን ይመልስለታል (ማቴ. ፲፡፳፰)፡፡ ነፍስ ከሥጋ ተለይታ በሲኦል ወይም በገነት እንደምትቆይ የአልዓዛርን ታሪክ ድሀውም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት የሚለውን በመጥቀስ ያሳፍረዋል (ሉቃ. ፲፮፡፳፪)፡፡
  • “… በዐርባ ቀን እግዚአብሔር በሕፃኑ ፊት ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ይልበታል፤ በእግዚአብሔርም እጅ ይፈጠራልበማለት የተሳሳተ ትምህርት ለሚያስተምሩ ዝንጉዓን፡ ሊቁ እግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስን በአዳም ላይ እፍ እንዳለ በሔዋን ፊት ላይ ግን የሕይወትን እስትንፋስ እፍ እንዳላለ እይ፤ ሕፃን ከእግዚአብሔር አፍ የሕይወትን እስትንፋስ መቀበል የሚገባው ቢሆን ሔዋን ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር አፍ ዳግመኛ የሕይወትን አስትንፋስ መቀበል በተገባት ነበር በማለት ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሕፃን ልጅ ከአባቱና ከእናቱ ዘር የማትሞት ነፍስን ይቀበላል የሚለው እንደሆነ ገለጸልን፡፡
  • “ኦሪት፣ ነቢያትና ሰንበት ተሽረዋልለሚሉ፡- በወንጌል መምጣት ኦሪት እንደ ቀረች፣ በሐዋርያትም ስብከት የነቢያት ትንቢት እንደጠፋ፣ ሰንበትም ትንሣኤ በሆነባት እሑድ እንደተሻረች የሚናገሩ አሉ፡፡ እኛ ግንኦሪት በወንጌል ስብከት ከበረች፤ ነቢያትም በሐዋርያት ትምህርት ከፍ ክፍ አሉ፤ ዓለምን ከመፍጠር ያረፈባት ሰንበትም የዓለም አዳኝ በተነሣባት በሰንበተ ክርስቲያን ዘውድን ተቀዳጀች› እንላለንበማለት ይመልስላቸዋል፡፡
  • አዳምና ነቢያት በሲኦል አልነበሩም ለሚሉ፡- አባ ጊዮርጊስ እንዲህ የሚሉትን መናፍቃን ነቢያት የተናገሩትን በመጥቀስ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በሲኦል ስለመኖራቸው፣ ገነትም ተዘግታ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ እየተጠበቀች መቆየቷን በመግለጽ ይገሥጻቸዋል፡፡
  • “ኤዶም ገነትና ሲኦል በሰማያት ናቸው” ለሚሉ፡- የተወሰኑት ኤዶም ገነት በሰማያት ናት፤ በምድር አይደለችም” ሲሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሲኦል በሰማያት ናት” ይላሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ገነትና ሲኦል ቁጥራቸው ከዓለመ ምድር እንጂ ከሰማያት እንዳልሆኑ ገነትን የሚያጠጡ ወንዞችን፣ አዳም ወደ ገነት እንዳይገባ በሱራፊ መጠበቋን ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ መልስ ሰጥቷቸዋል፡፡

በአጠቃላይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር መጽሐፉ የመናፍቃንን ስሕተትና የስሕተታቸውን ምክንያት ነቅሶ በማውጣትና መጽሐፋዊ የሆነ መልስ በመስጠት መናፍቃንንና ስሑታንን ገሥጿል፡፡ የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ለተነሡ ኑፋቄዎች መልስ መስጠት ቢሆንም ሌሎችንም ጉዳዮች በማንሣት መልስ እንደ ሰጠ ከላይ ተመልክተናል፡፡ አዲስ መናፍቅ እንጂ አዲስ ኑፋቄ የለም እንደሚባለው በመጽሐፉ የተጠቀሱ መናፍቃን ትምህርቶች ዛሬም ድረስ በተለያዩ አካላት እንደ አዲስ ሲጠቀሱና ሲነገሩ እንሰማለን፡፡ በዘመናችን የተነሡ መናፍቃንና ግብረ አበሮቻቸው የሚያስተምሩትም ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የለየችውና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንት መልስ የሰጡበት እንጂ አዲስ የተገለጠላቸው ትምህርት አለመሆኑን መረዳት ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ ትምህርቷን ያልሰሙ አላዋቂዎች ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን እንደማትሰብክ አድርገው ይናገራሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን እንዴት እንደምትሰብከው በሚያስረዳው በሚከተለው የሊቁ ቃል ጽሑፋችንን እናጠቃልላን፤

ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱሳን ሁሉ ንጉሥ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠራው ስሙ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያዳምጠው ቃሉ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚበላው ሥጋው የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠጣው ደሙ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ዜናውን ለሚነግር መታሰቢያው የጣፈጠ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የሰውም ልጅ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ያለ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እትራቶቹ ከእርሱ ጋር መስቀሉም በፊቱ ያለ፣ የአንድነታችን አለቃ፣ የትምህርታችን አስተማሪ፣ የእረኞቻችን አለቃ፣ የካህኖቻችን ሊቅ ነው፡፡ እርሱ ሰማያዊ ከሚሆን ከቸር አባቱና ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ከእኛ ጋር ይኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳም ድረ ገጽ ተከታታዮች! ይህ ትምህርት፣ ከጥር ፩ – ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡