ክረምት

 ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም.

ካለፈው የቀጠለ

ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ ያለው መካከለኛ ክረምት በመባል ይታወቃል፡፡ የክረምት ኃይልና ብርታት እንዲሁም ክረምትን ጥግ አድርገው የሚከሰቱ የተፈጥሮ ኃይላት ዑደት ያጸናበታል፡፡\ የዕለቱ ቁጥርም 33 ዕለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ ባሕርና አፍላግ ይሰለጥናሉ፡፡

መብረቅ የአምላክን ፈጣንነት፣ ነጎድጓድ የግርማውን አስፈሪነት፣ ባሕር የምሕረቱን ብዛት የሚያመለክቱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት ጥልቆቹ የውኃ ቦታዎች መጠናቸው ያድጋል፣ የወንዞች ሙላት ይጨምራል፣ ምንጮች ይመነጫሉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ዘይመይጦ ለመብረቅ ወያጸንኦ ለነጎድጓድ ዘርዋነ ያስተጋብዕ ወያበርህ ለመሃይምናን” /ድጓ ዘክረምት/ መብረቅን የሚመልሰው፣ ነጎድጓድን የሚያበረታው የተበታተኑትን ይሰበስባል፣ ለሚያምኑባትም ዕውቀትን ያድላል በማለት ብርሃንን ከምዕራብ ወደምሥራቅ እንደሚመልሰው ሁሉ መብረቅንም ካልነበረበት በጋ ወደሚኖርበት ክረምት የሚያመጣውና መገኛውን ደመና የሚፈጥርለት እርሱ ብቻ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ፍጻሜ ክረምት

ፍጻሜ ክረምት ከነሐሴ 22 አስከ መስከረም 25 ያለው 39 ዕለት ነው፡፡ ይህ ሦስተኛው ክፍል በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው ዕጓለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዐይነ ኲሉ ይባላል፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ብርሃን፣ ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ በመባል ይታወቃሉ፡፡

ከነሐሴ 22 እስከ ነሐሴ 29 ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት ውስጥ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች ይታወሳሉ፡፡ ዕጓለ ቋዓት ቁራን /የቁራ ግልገልን/ ሲያመለክት በሥነ ፍጥረት አቆጣጠርን ግን በክንፍ የሚበሩ አዕዋፍን ሁሉ ይወክላል፡፡

ቁራ ሲወለድ ያለ ጸጉር በሥጋው ብቻ ይወለድና ከጊዜ በኋላ ጸጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚህ ጥቋቁሮች አሞሮች እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው እናቱም አባቱም ጥለውት ይሸሻሉ፡፡ “እናቴና አባቴ ትተውኛልና እግዚአብሔር ግን ተቀብሎኛል” /መዝ.26፡10/ የሚለው የንጉሥ ዳዊት ቃል እናትና አባቱ ለጣሉትና ለጠሉት፣ ትተውት ለሞቱበት ሰው ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ድርጊት በሚፈጽመባቸው ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ በአምላክነቱ የሚያደርግላቸውን ርኅራኄ የሚያሳይ ቃል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚከባከበው የሚመግበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፍን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሕዋስያንን ብር ብር አያደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ እዮብ “ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው” ብሏል /ኢዮብ 38፡41/፡፡ ቁራው እግዚአብሔር የሚሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፣ በዚህን ጊዜ እናትና አባቱ መጥተው ይከባከቡታል፡፡

ደስያት ማለት በውኃ የተከበቡ ጠባብ ቦታዎች ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ኖኅ መርከብ ለፍጥረት መብዛት ምንጭ የሆኑ ነፍሳትን እንደያዘች ሁሉ አንዲት ደሴትም በውስጧ ብዙ ፍጥረታትን ትይዛለችና፡፡ ደሴት የኖኅ መርከብ ያረፈችበት የዓራራት ተራራ ምሳሌ ናት፡፡ እንዲሁም ከደሴያት የተጠጉ ድኅነትን እንደሚያገኙ ሁሉ በጥምቀት አማካኝነት ወደ ቤተ ክርስቲያን የተጠጉ ሁሉ ከሞት ሥጋና ከሞተ ነፍስ የሚጠብቃቸው የነፍሳቸውን እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኛሉና ደሴት የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡
ዓይን /ዓይነ ኲሉ፣ የሁሉ ዓይን/ የተጠቀሰው ሥጋዊ ዓይንን ለማመልከት ሳይሆን “ገንዘብህ ባለበት በዚያ ልብህ ይሆናል” /ማቴ.6፡21/ እንደተባለ የሥጋንም ሆነ የነፍስን ፍላጎት ለማሟላት የሚረዳ የሕሊና መሸትንና የመንፈስ ስብራትን የተመለከተ ፈቃደ መንፈስ ነው፡፡ “ልብ ካላየ ዓይን አያይም” እንዲሉ፡፡ /መዝ.136፡25/ ለሥጋ ምግብን የሚሰጥ “የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ” መዝሙረኛው እንዳለ፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ውኃውን በደመና አቁማዳ ይቋጥራል፣ ነገር ግን ደመናውን አይቀደድም፡፡ በዚህ መጋቢነት የሁሉ ነፍስ ዓይን እርሱን ተስፋ ያደርጋል” አለ፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነቱን እያሰብን ሳንታክት ወደ እርሱ ብንመለስ እርሱ ወደ እኛ ይመለሳል፣ ብንለመነውም ይሰጠናል በማለት ሊቁ ተናግሮአል፡፡

ከላይ ያየነው ፍጻሜ ክረምት የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን ሁለተኛው ክፍል የሚባሉት ብርሃን፣ ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ ይባላሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ስለብርሃን ተፈጥሮና የሥራ ባሕርይ አስመልክቶ “ዘአንተ ታመጽእ ርእየቱ ብርሃን ወፈለጥከ ብርሃነ ለአዝማን ወለጊዜያት፣ የብርሃንን ወገግታ የምታመጣው አንተ ነህ ዘመናትንና ጊዜያትን በብርሃን ማእከላዊነት የለየሃቸውም አንተ ነህ” /ድጓ ዘክረምት/ በማለት ሊቁ እንዲል፡፡

ድጓ ዘክረምት “እስመ ብርሃን ሠረቀ ሎሙ” እግዚአብሔርን መፍራት እንድታውቅ በጠዋት ፀሐይ፣ በነግህ ብርሃን ይወጣልሃል እንዲሁም ሆኖ ብርሃን ወጥቶአልና ሰው ወደ ሥራው ተሠማርቶ እስኪመሽ ድረስ ይውላል እንዲል ቅዱስ ያሬድ፡፡

ማጠቃለያ

በዚህ አጭር ጽሑፍ ሙሉ የቅዱስ ያሬድን ትምህርት መግለጽ ባይቻልም ለቅምሻ ያህል ቅዱስ ያሬድ በዘመነ ክረምት አስተምሮቱ ምን እንደሚመስል ተመልክተናል፡፡ ይህ ዘመን ጠልና የልምላሜ የዘርና የቡቃያ ጊዜ በመሆኑ ከቅጠል በቀር በምድር ላይ ከወደቁት ዘሮች አብዛኛው ፍሬ አይገኝባቸውም፡፡ ዘመኑ ለመንግሥተ ሰማያት ያልተዘጋጀ፣ የንስሐ ፍሬ ያላፈራ ሰው ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሸሽታችሁ በክረምት /ሞታችሁ ያለመልካም ሥራ/ እንዳይሆን ተግታችሁ ጸልዩ ያለው በደላችንን ባለማወቅ ለንስሐ ሕይወት ሳንበቃ በለጋነት ዕድሜያችን የምንሞተው ሞት አሳዛኝ መሆኑን ሲገልጽ ነው፡፡ ሊቁ በዚህ ክረምት /ዘመናችን/ ገና በቅጠል /ያለ ሥራ/ ሳለን ሽሽታችን /ሞታችን/ ያለፍሬ አይሁን በማለት ቅዱስ ያሬድ ድርሰቱን ከወንጌሉና ከዘመኑ ጋር በማጣጣም አስቀምጦልናል፡፡