አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተሰጠ መግለጫ

ጳጕሜን ፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

005

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ቃለ በረከት ዘእምኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወተስዓቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡

  • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
  • ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
  • በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

ዘመናትና ዓመታት የማይቆጠሩለት እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከ2008 ዓ.ም ዘመነ ዮሐንስ ወደ 2009 ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ፡፡

‹‹ወእስምያ ለዓመተ እግዚአብሔር ኅሪተ፤ የተመረጠችውንና የተወደደችውን የእግዚአብሔር ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል›› (ኢሳ.61፡2፤ ሉቃ.4፡19)፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው እንደ ሌላው ሁሉ ዓመትም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ዓመት የጊዜ መለኪያ ነው፤ ጊዜም የሥራ መሣሪያ ነው፡፡

እግዚአብሔር ዓመታትን ለፍጡራኑ ሲሰጥ ለሥራ፣ ለኑሮ፣ ለምግብና ለጤና ወዘተ በሚመች አኳኋን በተለያዩ ሐውዘ አየራት ከፋፍሎና አመቻችቶ መስጠቱ ዓለም በእርሱ መግቦት የሚመራ መሆኑን ይበልጥ ያጎላዋል ፡፡

ከዚህም ጋር ጊዜያትን ለመለካት የሚያስችሉ መገብተ ብርሃን በጠፈረ ሰማይ ፈጥሮ ሰው በእነርሱ እየታገዘ ጊዜን በመለካት ለሥራውና ለኑሮው እንዲጠቀምባቸው አድርጎአል፡፡

ይህንንም በቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔርም ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ለምልክቶች፣ ለዘመናት፣ ለዕለታትና ለዓመታት መለያ ይሆኑ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ አለ›› በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፤ /ዘፍ.1፡14/፡፡

ስለሆነም ሰው ቀንን በብርሃነ ፀሐይ፣ ወርን በብርሃነ ወርኅ፣ ወቅትን በብርሃነ ከዋክብት፣ ወዘተ. እየለካ ወቅቱን በመዋጀት ለእርሻ ተግባሩ ማለትም ለአዝርእቱ ለአትክልቱ፣ ለፍራፍሬው ምቹ ወቅት የትኛው እንደሆነ በመለየትና በማወቅ በግብርና ተግባር በሚገባ እንዲጠቀምባቸው አስችሎታል፡፡

በሌላም በኩል እግዚአብሔር ለአበው የሰጠው ተስፋ – ድኅነት ማለትም ዘመነ ሥጋዌ ወይም ዘመነ ክርስቶስ በዘመነ ቀመር ስሌት አሠራር መቼ እንደሚሆን ቅዱሳን ነቢያት በኁልቄ ዓመታት ሲቆጥሩ፣ ሲከታተሉና ሲጠብቁ እንደነበሩ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በብዙ ቦታ ተጽፎአል፤

በተለይም ነቢዩ ዳንኤል በደልና ኃጢአት የሚደመሰስበት ዘመነ ክርስቶስ ሊደርስ እርሱ ከነበረበት ዘመን አንሥቶ ሰባ ሱባዔ እንደቀረው በግልጽ ጽፎአል፤ በትንቢቱ መሠረትም ተፈጽሞአል፤ (ዳን.9፡24-27)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም ይህ ሱባዔ ሲፈጸም የሆነውን ነገር ሲገልጽ ‹‹የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፤ ከሴትም ተወለደ ብሎአል፤›› /ገላ.4፡4/፡፡

ከዚያም አኳያ እግዚአብሔር ለማዳን ሥራ የመረጠው ወይም ለይቶ ያስቀመጠው ዓመት እንዳለ ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም ዓመት ምርጥ የሆነ የእግዚአብሔር ዓመት ተብሎ ተገልጾአል፡፡

ቅዱሳን ነቢያት እግዚአብሔር በገለፀላቸው ምሥጢር መሠረት የተወደደው፣ የተመረጠውና ምሕረት እንደዝናም የሚዘንብበት የእግዚአብሔር ዓመት እርሱም ዘመነ ክርስቶስ እንደሚመጣ ብቻ ሳይሆን መቼ እንደሚመጣ ጭምር ዓመታቱን በትክክል እየቀመሩና እየቆጠሩ ሲናገሩና ሲያስተምሩ መኖራቸው የዘመናት ቁጥር በሃይማኖት ዘንድም የላቀ ተፈላጊነት እንዳለው ያመለክታል፡፡

እግዚአብሔር የተናገረውን የማያስቀር ታማኝ አምላክ ነውና የተቆጠሩት ዓመታት በደረሱ ጊዜ፣ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመት ልጁን ወደዚህ ዓለም በመላክ ዓለሙን ከፍዳ ኃጢአት ታደገው፡፡

በመሆኑም በተጠቀሰው ዘመን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ መሥዋዕት ሆኖ የዓለምን ዕዳ – ኃጢአት በመሸከም የሰው ልጅን በምሕረቱ ስለተቀበለው ከልደተ ክርስቶስ ወዲህ ያለው ዘመን ምሕረት እግዚአብሔርን ለማሰብና ለማወጅ ሲባል ‹‹ዓመት ምሕረት›› ወይም እንደ ነቢዩ እንደ ኢሳይያስ አገላለጽ ‹‹የተመረጠ የእግዚአብሔር ዓመት›› ይባላል፡፡

እኛም ኢትዮጵያውያን በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ከመጀመሪያው ምእተ – ዓመት መጀመሪያ አንሥቶ ምሕረተ እግዚአብሔርን ገንዘብ ካደረጉ ሀገራት መካከል የመጀመሪያዎቹ ነንና ምሕረቱን ተቀብለን በዘመን አቆጣጠራችን ላይ ‹‹ዓመተ ምሕረት›› እያልን ምሕረተ እግዚአብሔርን ስናስታውስና ስናውጅ እንኖራለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ወምእመናት!

ዘመን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሆነ ቀደም ብሎ ከላይ ተገልጾአል፤ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደመሆኑም መጠን በጥንቃቄና በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፤

እግዚአብሔር ዘመናትን፣ ዓመታትንና ወራትን የሚሰጠን ለሃይማኖት ማጽኛ፣ ለሥነ ምግባር ማበልፀጊያ፣ ለንሥሐ ማጎልብቻ ለዕድገት፣ ለብልፅግና፣ ለልማት፣ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነትና ለስምምነት በአጠቃላይ የጎደለንን ለመሙላት ያጣነውን ለመተካት፤ የተስተካከለ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት እንዲኖረን ለማስቻል እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡

በመሁኑም ጊዜ ባለፈው አሮጌ ዘመን የጎደለብንን ሁሉ በአዲሱ ዘመን ለመሙላት እንድንችል በእግዚአብሔር የተሰጠን ልዩ ጸጋ ነውና በሥራ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ክፍለ ዘመናት ያመለጧት ብዙ ነገሮች እንዳሉ የሚታወቅ ነው፤ ይሁን እንጂ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ቀድሞ ያመለጧትን ነገሮች ለመሙላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ መገኘቷና በዚህም ያመጣችው ለውጥ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤

ይህም የእግዚአብሔር ጸጋ ነውና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ኢታስትት ጸጋሁ ዘላዕሌከ፤ ከአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል›› እንዳለው የተሰጠንን ጸጋ – ልማት በጥቃቅን ነገሮች ልናደናቅፈው አይገባም፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን የተገነዘብነው ዓቢይ ቁም ነገር ቢኖር ሰላም የልማት ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ነው፤ በሀገራችን እየፈነጠቀ ያለው የዕድገት ጮራ የሰላም ውጤት እንጂ የሌላ አይደለም፡፡

ከዓለም ተሞክሮ ልምድ ብንወስድም አሁን በከፍተኛ የዕድገት ጣራ ላይ የሚገኙ ሀገራት የልማታቸው ምሥጢር የሰላምና የአንድነት መረጋገጥ እንደሆነ ማስተዋሉ አይከብድም፡፡

ስለሆነም ያለ ሰላም ልማትና ዕድገት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለምና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለራሱ ልማት ሲል ለሰላም ጠበቃ መሆን አለበት፡፡

ባለፈው ዓመት ከዛሬ ሠላሳ አንድ ዓመታት በፊት ካጋጠመን ድርቅ ያልተናነሰ ከባድ ድርቅ ያጋጠመን ቢሆንም የሀገራችን ሕዝቦች ሰላማቸውንና አንድነታቸውን ጠብቀው ባስመዘገቡት ዕድገት ምክንያት ሀገራችን ችግሩን በራስዋ ዓቅም መቋቋም መቻሏ የሰላምና የአንድነት ጥቅም እንዲሁም እነርሱን ተከትሎ የተገኘው የዕድገት ጣዕም ምን ያህል እንደሆነ የተገነዘብንበት ዓመት ሆኖ አልፎአል፡፡

ስለሆነም አሁንም በተመረጠውና በተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት ውስጥ ሆነን ዛሬ በምንጀምረው አዲስ ዓመት እግዚአብሔር ቸርነቱን አብዝቶልን የዝናሙ ስርጭትና የእህሉ ቡቃያ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ስለሚታይ፣ ሕዝቡ በዚህ ተነቃቅቶ ሰላሙንና አንድነቱን በመጠበቅ የበለጠ ልማትና ዕድገት ለማስመዝገብ ጠንክሮ እንዲሠራ፣ እንደዚሁም ከድህነተና ከሰላም እጦት የበለጠ ሌላ ጠላት እንደሌለው ሕዝቡ ተገንዝቦ በአዲሱ ዓመት አለመግባባትን በውይይት፣ ድህነትን በልማት ለማሸነፍ በሁሉም አቅጣጫ እንዲረባረብ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡ ዘመኑን የሰላም፣ የአንድነትና የልማት ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ፤

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መስከረም 1 ቀን 2009

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ