አምስተኛው የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል

ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ከፍ ብሎ የሚሰማው የመዝሙር ድምፅና በማዕከሉ መግቢያ በር ላይ የተለጠፉ መንፈሳውያን ማስታወቂያዎች አካባቢው አንዳች ብርቱ ጉዳይ እንዳለበት ይመሰክራሉ፡፡ ብዙ የቆሙ መኪኖች፣ በሺሕ የሚቈጠሩ ምእመናን መንገዱን አጨናንቀውታል፡፡

ከዐዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ አህጉር የሚመጡ ምእመናንና ምእመናት ከግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ እግሮቻቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ አድርገዋል፤ ወደ ዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል፡፡ የጉዟቸው ምክንያት ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን አምስተኛው ዙር መንፈሳዊ ዐውደ ርእይ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን ዐውደ ርእይ ለማዘጋጀት ከዓመታት በፊት ዓቅዶ ሠርቷል፤ ዐውደ ርእዩ ለምእመናን ሊቀርብ የነበረውም ከመጋቢት 15-21 ቀን 2008 ዓ.ም የነበረ ቢኾንም ዳሩ ግን በሰዓቱ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ባይኾን ግልጽ ባልነበረ ምክንያት ዐውደ ርእዩ መታገዱ ሲሰማ ብዙ ምእመናን ተደናገጡ፡፡

የማኅበሩ ሥራ አመራር አባላትም፡- አይዟችሁ አትደንግጡ፤ ኹሉም በጊዜው ይኾናል፡፡ እግዚአብሔር በፈቀደበት ጊዜ ዐውደ ርእዩን እናሳያችኋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን በትዕግሥት ኾነን እንጠባበቅ፤ ወዘተ እያሉ ዐውደ ርእዩን በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩትን ምእመናን እያጽናኑ ከሚመለከታው አካላት ጋር ውይታቸውን ቀጠሉ፡፡

እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ ሲደርስ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት፣ በአባቶችና በእናቶች ጸሎት የማኅበሩና የተባባሪዎቹ ጥረት ተሳክቶ ዐውደ ርእዩ የሚታይበት ቀን ደርሶ እነሆ ከግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ለተመልካቾቹ ይፋ ኾነ፡፡

መስቀል ዐደባባይን በማቋረጥ ከሰሜን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ከፍ ብሎ ወደሚገኘው ቅፅር ግቢ ውስጥ ሲገሰግሱ የኢትዮጵያውያንን ባህል ገላጭ የኾነውንና ጠቢባኑ የተካኑበትን በረጅሙ ቆሞ ከርቀት የሚታየውን በኅብረ ቀለማት ያጌጠውን መሶብ ያገኛሉ፡፡

ይህንን መሶብ አለፍ እንዳሉ በግዙፉ መግቢያ በር ላይ አምስተኛው ዙር የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል፣ ከግንቦት 17-22 ቀን 2008 ዓ.ም የሚሉ ማስታዎቂያዎች በረጅም ብራና ቁልቁልና አግድም ተለጥፈው ይነበባሉ፡፡

ከታች ደግሞ የጸጥታ ባለሙያዎች ተመልካቾችን በጥንቃቄ እየፈተሹ ወደ ኤግዚብሽን ማዕከሉ ቅፅር እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡ የዐውደ ርእዩ ታዳሚዎችም በሩ ውስጥ የተመደቡትን የቲኬት ሽያጭ አስተባባሪዎች ፈቃድ ካገኙ በኋላ ወደ አዳራሾቹ ጥቂት እንደተጓዙ ከአስፋልቱ በስተቀኝ በኩል ተንጣሎ የሚታየውን ቍጥር አንድ አዳራሽን ያገኛሉ፡፡ ይህ አዳራሽ በቍጥር የመጀመሪያው ይሁን እንጂ በዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች ግን የመጨረሻው ነው፡፡

በአስተባባሪዎች መሪነት ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ጥቂት ተጉዘው ጊዜያዊ የእንግዶች ማረፊያ ድንኳን ውስጥ ቁጭ ብለው በድምፅና በምስል የታገዙ ልዩ ልዩ መንፈሳውያን መረጃዎችን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በተራ ቅደም ተከተላቸው መሠረት ወደ ትዕይንቱ አዳራሾች ያመራሉ፡፡

የኤግዚብሽን ማዕከሉ በስተሰሜን በኩልም ተጨማሪ የመግቢያ በር ያለው ሲኾን፣ እንደዋናው በር ኹሉ የመግቢያ ቅድመ ኹኔታዎችን ካሟሉ በኋላ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሲያመሩ በዋናው በር ከገቡ ታዳሚዎች ጋር በአንድ ድንኳን ውስጥ አብረው እንዲቆዩ ይደረጉና ወደ ትዕይንቶች ይገሰግሳሉ፡፡

ይህ መንፈሳዊ ዐውደ ርእይ በአባቶች ጸሎት ከተከፈተበት ዕለት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ ምእመናን እየተመለከቱት ሲኾን፣ የምእመናኑ ቍጥርም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው፡፡

የዐውደ ርእዩ አዘጋጆችና አስተባባሪዎቹ ምእመናኑ ረጅም ሰዓት በመቆም እንዳይጉላሉ በማሰብ የሚቻላቸውን ኹሉ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም ከኤግዚብሽን ማዕከሉ አዳራሾች በተጨማሪ ሰፋፊ ድንኳኖችን በማዘጋጀት ተጨማሪ መመልከቻ ቦታዎችን አመቻችተዋል፡፡

ትዕይንታተ ዐውደ ርእይ

ዐውደ ርእዩ በሦስት መንገድ ይጎበኛል፤ ይኸውም በገላጮች ማብራሪያ፣ በባነሮች (ብራናዎች) ላይ በተቀመጡ ጽሑፎችና መረጃዎች እንደዚሁም በድምፅ ወምስል በመታገዝ ነው፡፡ የዐውደ ርእዩ ዐበይት አርእስትም አራት ሲኾኑ እነዚህም፡-

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት፤ ሁለተኛው የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ፤ ሦስተኛው የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ፤ አራተኛው ደግሞ ምን እናድርግ የሚሉ ናቸው፡፡ የእያንዳንዳቸውን ጭብጥ ለማስገንዘብ ያህል የአርእስቱን ዐሳብ በአጭሩ እንመልከት፤

ትዕይንት አንድ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት

ይህ ትዕይንት ሀልዎተ እግዚአብሔር፣ ነገረ ድኅነት፣ ነገረ ማርያም፣ ነገረ ቅዱሳን እና ነገረ ቤተ ክርስቲያን የተካተቱበት ክፍል ነው፡፡ ሀልዎተ እግዚአብሔር በሚለው ርእስ እግዚአብሔር አምላክ በጊዜና በቦታ የማይወሰን፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፣ የፍጥረታት ኹሉ አስገኝ፣ ከመሥፈርትና ከአመለካከት ውጪ፣ እርሱ በገለጠው መጠን ብቻ የሚታወቅ እንጂ ባሕርዩ ተመርምሮ ሊደረስበት እንደማይቻል እንደዚሁም መልዕልተ ኵሉ (የኹሉ የበላይ) ኾኖ ሳለ በፈቃዱ የትሕትና ሥራ መሥራቱን ያስረዳል፡፡

ነገረ ድኅነት ደግሞ በአዳምና በሔዋን ምክንያት የዘለዓለም ሞት ተፈርዶበት የነበረው የሰው ልጅ ከሦስቱ አካላት አንዱ በኾነው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀልና ሞት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መቻሉን፤ ንደዚሁም እምነት፣ ምግባር እና ምሥጢራተ በቤተ ክርስቲያንን መፈጸም የሰው ልጅ ለመዳን የሚያስፈልጉት ነገሮች መኾናቸው በዚህ ርእስ ሥር ተካቷል፡፡

ትዕይንት ሁለት፡- የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ

በዚህ ትዕይንት የሐዋርያነትና የሐዋርያዊ አገልግሎት ትርጕም፣ ዓላማና አመሠራረትን ጨምሮ ስብከተ ወንጌል አንዴት እንደተስፋፋና እስከ ዛሬ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሱ ፈተናዎችን እንደዚሁም መልካም አጋጣሚዎችን በማካከተት ልዩ ልዩ መረጃዎችና ትምህርቶቸ ቀርበውበታል፡፡

ትዕይንት ሦስት፡- የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ

ይህ ትዕይንት ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለማስፋፋት ያሳለፈችውን ተጋድሎ፣ የመናፍቃንን ተፅዕኖና የሰማዕታትን ታሪክ፣ የተዋሕዶ ሃይማኖትን አስተምህሮ ለማስጠበቅ የተደረጉ ልዩ ልዩ ዓለም ዓቀፍና አገር ዓቀፍ ጉባኤያትን በዝርዝር ይዟል፡፡

ትዕይንት አራት፡- ምን እናድርግ?

ይህ ትዕይንት ደግሞ ምእመናን በዐውደ ርእዩ ከተመለከቷቸውና ከሰሟቸው እውነታዎች በመነሣት የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ከመጠበቅና ድርሻን ከማወቅ አኳያ ልዩ ልዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ወደፊት ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የሚያስረዱ መረጃዎችን አካቷል፡፡

ዐውደ ርእዩ ከነዚህ ዐበይት ትዕይንቶች በተጨማሪ የሕፃናት ትዕይንትም የተካተተበት ሲኾን፣ በዚህ ትዕይንት ለሕፃናት አእምሮ የሚመጥኑ መንፈሳውያን ትምህርቶች ተዘጋጅተውበታል፡፡ ሕፃናቱም ክፍሉ ውስጥ እየዘመሩ ይማራሉ፤ ይደሰታሉ፡፡

ከሁሉም በተለየ መንገድ ደግም የሁሉም ገባኤያት (የንባብ፣ የዜማ/የድጓ፣ የቅዳሴ፣ የቅኔ፣ የአቋቋም፣ የመጻሕፍትና የአቡሻሕር ጉባኤ ቤቶች) ሊቃውንት (መምህራን) ደቀ መዛሙርታቸውን ሲያስተምሩ እስከ ጎጆዎቻቸውና እስከሚጠቀሙባቸው ዕቃዎች ድረስ በተግባር ይታያሉ፡፡ የብራና መጻሕፍት አዘገጃጀትም በባለሙያ አባቶች ይብራራል፡፡

የማኅበረ ቀዱሳንን ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ እንደዚሁም የጽርሐ ጽዮንና የደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳውያን ማኅበራት አገልግሎት የሚቃኝባቸው ክፍሎችም የትዕይንቱ አካላት ናቸው፡፡ በማኅበሩ የሚዘጋጁ ንዋያተ ቅድሳትና መጻሕፍትም በሽያጭና በዕጣ መልክ ቀርበዋል፡፡

ማኅበረ ጽዮን የጉዞ ማኅበር፣ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል፣ ዮድ አቢሲንያ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ስለሚሰጧቸው ተግባራት የሚገልጹባቸው ክፍሎችም ተካተዋል፡፡

ትዕይንቶቹን ተመልክተው የሚወጡ ምእመናንም ኾኑ የሌሎች እምነት ተከታዮች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መውጫው በር ላይ ተሠይመዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ታዳሚዎች ጉብኝቱን ጨርሰው ሲወጡ ደግሞ የተሰማቸውን ስሜት ወይም ደግሞ ቅሬታ የሚያሰፍሩባቸው የአስተያየት መስጫ መዛግብት በብዛት ተደርድረዋል፤ ጎብኝዎቹም ስሜታቸውን እየጻፉ ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡

ከዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች ጎን ለጎንም ከግንቦት 17 ቀን 2008 ጀምሮ የአብነት ትምህርቶችን የተመለከቱ ጥናቶችና መንፈሳውያን ተውኔቶች እንደዚሁም መዝሙራት ከቀኑ 11፡00 እስከ ምሽት ድረስ ለጎብኝዎቹ በመቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለአምስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው ይህ ዐውደ ርእይ መታየት ከጀመረ እነሆ ዛሬ አምስተኛውን ቀን ያስቈጠረ ሲኾን፣ እጅግ በሚማርክ ኹኔታ በአባቶች ካህናትና በምእመናን ብቻ ሳይኾን በሌሎች ሰዎችም እየተጎበኘ ይገኛል፡፡

ትናንትናና ዛሬም በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በዐውደ ርእዩ ተገኝተው አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል፤ ማኅበሩ እየሠራ ያለውን ተግባር በማድነቅም ስሜታቸውን መዝገብ ላይ አስፍረዋል፡፡

ለዐውደ ርእዩ ድምቀት ከሰጡ ክሥተቶች መካከልም የሰንበት ት/ቤት ዘማርያን የመዝሙር ልብስ ለብሰው እየዘመሩ፤ እንደዚሁም በዛሬው ዕለት (ግንቦት 21 ቀን 2008 ዓ.ም) ጋብቻቸውን የፈጸሙ ጥንዶች ከአጃቢዎቻቸው ጋር በመኾን በዐውደ ርእዩ መታደማቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ዐውደ ርእዩ ከተከፈተበት ቀን ጀምሮ በአስተያየት መስጫ መዛግብቱ ላይ የሰፈሩትን አስተያየቶች ስናነብና ቃለ መጠይቅ ስናደርግ ብዙ ምእመናን በዐውደ ርእዩ ራሳቸውን እንዳዩበትና ስለሃይማኖታቸው በቂ ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው እንደዚሁም የድርሻቸውን ለመወጣት እንዳነሣሣቸው ተረድተናል፡፡

በተጨማሪም ዐውደ ርእዩ በዐዲስ አበባ ብቻ ሳይኾን በየአገሩ ቢታይ፣ ትዕይንቶቹ በብሮሸርና በሲዲ መልክ ቢሠራጩ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ጋር በጋራ በመኾን ማቅረብ ቢቻል መልካም ነው የሚሉና የመሳሰሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

በአንጻሩ በትዕይንቶቹ ገላጮችና በምስል ወድምፅ ዝግጅቶች መካከል የድምፅ መጋጨት እንዳይኖር ጥንቃቄ ቢደረግ፤ ግቢው ውስጥ በማኅበሩ የተዘጋጁ ምግቦችና መጠጦች ለሽያጭ ቢቀርቡ፤ ትዕይንቶቹ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቷቸው በስፋት ቢተነተኑ፤ አዳራሾቹ ውስጥ ረጅም ሰዓት መቆየት ባይኖር፤ ወዘተ የመሰሉ በርካታ አስተያየቶችንም ከአንዳንድ ጎብኝዎች ለመረዳት ችለናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡