በዝቋላ ገዳም አካባቢ የተነሣው የእሳት ሰደድ እየተባባሰ መኾኑ ተነገረ

001

በዝግጅት ክፍሉ

መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አካባቢ መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቀትር ላይ የተነሣው ከፍተኛ የእሳት ሰደድ እየተባባሰ መኾኑን የገዳሙ አባቶች ተናገሩ፡፡

እሳቱ የተነሣበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም ትናንትና ረፋድ ላይ በቅርብ ርቀት ላይ ይጤስ የነበረው አነስተኛ እሳት ቀትር ላይ መባባሱንና እሳቱን ለማጥፋትም የገዳሙ መነኮሳት ከቅዳሴ በኋላ ወደሥፍራው መሔዳቸውን ከገዳሙ አባቶች መካከል አንዱ የኾኑት አባ ጥላኹን ስዩም ዛሬ ረፋድ ላይ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ዓርብ ረቡዕ›› በሚባለው አካባቢ የነበረውን እሳት ሌሊት ላይ በቍጥጥር ሥር ለማዋል ቢቻልም ‹‹የቅዱሳን ከተማ›› በተባለው ቦታ በኩል በአዱላላ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ያለው ቃጠሎ እየተስፋፋ መምጣቱንና ሰደዱን ለመከላከልም አስቸጋሪ መኾኑን አባ ጥላኹን ተናግረዋል፡፡

እሳቱ ወደ ገዳሙ እንዳይጠጋ የመከላከሉ ሥራ እንደቀጠለ መኾኑን የጠቀሱት አባ ጥላኹን እሳት ለማጥፋት ከደብረ ዘይት ከተማ ወደ ገዳሙ ከሔዱ ምእመናን መካከል አንድ ወንድም ከገደል ላይ ወድቆ እንደተጎዳና በአሁኑ ሰዓትም ሕክምና እየተደረገለት እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

እንደ አባ ጥላኹን ማብራሪያ የገዳሙ መነኮሳት፤ የደብረ ዘይት እና የአካባቢው ነዋሪዎች፤ እንደዚሁም የፌደራል፣ የክልሉና የወረዳው ፖሊስ ኃይል ከትናንትና ጀምሮ እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ቢገኙም የአካባቢው መልክዐ ምድር በረኃማ፣ ቍጥቋጦ የበዛበትና ነፋስ የሚበረታበት ወጣገባ ቦታ መኾኑ ሰደድ እሳቱን በቍጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት ከባድ አድርጎታል፡፡

በመጨረሻም ሰደዱ እየተስፋፋ ሔዶ በገዳሙ ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት እሳቱን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እንዲቻል መላው ሕዝበ ክርስቲያን በሚቻላቸው ዓቅም ዅሉ ትብብር ያደርጉ ዘንድ አባ ጥላኹን ስዩም በገዳሙና በመነኮሳቱ ስም ጥሪአቸውን ያስተላልፋሉ፡፡