ቁስቋም ማርያም

ኅዳር ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በከበረች በኅዳር ስድስት ቀን የሚታሰበው በዓለ ደብረ ቁስቋም በመላው ዓለም በሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም በአዲስ አበባ ከተማ እንጦጦ አካባቢ በምትገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ‹‹መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን›› ቀሳውስት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራን እና ምእመናን በተገኙበት ከዋዜማው ከኅዳር አምስት ቀን በማኅሌቱ ጀምሮ በኪዳንና በቅዳሴ ከዚያም ለክብረ ታቦቱ በሚቀርቡ ወረቦችና መዝሙራት በመታጀብ ይከብራል፡፡

የዚህ በዓል መሠረታዊ መታሰቢያው እንደሚታወቀውና መጽሐፈ ስንክሳር ላይም ተመዝግቦ እንደምናገኘው ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከክብርት እናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከአረጋዊው ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በስደት ከነበሩበት ከግብጽ ሀገር ተመልሶ ደብረ ቁስቋም የገባበት ነው፡፡ ከሦስት ዓመትና ከስድስት የስደት ወራት በኋላ አሳዳጃቸው ኄሮድስ በመሞቱ መልአኩ ለዮሴፍ በነገረው መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ በደብረ ቁስቋም ተራራ ላይ ዐርፈዋል።

ጌታችንም ካረገ ከዘመናት በኋላ ደግሞ በኅዳር ስድስት ቀን በዚህ በደብረ ቊስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰብስቧቸዋል፤ ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል፡፡ ለዚህም የእስክንድርያ ሀገር ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቄዎፍሎስ ምስክሮች ሆነዋል፡፡

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

ምንጭ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር