ሰባቱ ሊቃነ መላእክት

ክፍል

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? እየበረታችሁ ነውን? አዲስ ዓመት ብለን መቁጠር ከጀመርን ሦስተኛው ወር ላይ ደርሰናል:: ልጆች! ለመሆኑ በትምህርታችሁ ምን ያህል ዕውቀት ቀሰማችሁ? መቼም በዕረፍት ጊዜ የነበራችሁን የጨዋታ ጊዜያችሁን ቀንሳችሁ ለትምህርታችሁ የበለጠ ትኩረት ሰጥታችሁ እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋችን ነው፡፡ በርቱ! ልጆች! ለሁሉም ጊዜ ስላለው አሁን ደግሞ ጊዜው የትምህርት በመሆኑ በርትታችሁ ተማሩ፤ ትምህርት ጥበበኛና አስተዋይ ያደርጋልና፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፈው የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን ቅዱሳን ሊቃነ መላእክት (የመላእክት አለቆች) የሚባሉት ሰባት መሆናቸውን ነግረናችሁ ነበር፡፡ እነርሱም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤል፣ ቅዱስ ሳቁኤል ናቸው፡፡ ባለፈው ትምህርታችን የመላእክት ሁሉ አለቃ ስለሆነው ስለ ቅዱስ ሚካኤል በጥቂቱ እንደ ጻፍንላችሁ ታስታውሳላችሁ? መልካም! አሁን ደግሞ በመጠኑ ሊቃነ መላእክት ስለ ሚባሉት ስለ ቀሪዎቹ እንማራለን፡፡ ትምህርቱን በትኩረት ተከታተሉ!

ቅዱስ ገብርኤል

ገብርኤል ማለት ››ሰውና አምላክ ማለት ነው፤›› ልጆች! ቅዱስ ገብርኤል በአገልግሎቱ የሚጠራባቸው ስሞችም አሉት፤ እመቤታችንን በማብሠሩ እንዲሁም ካህኑ ዘካርያስንም ልጅ እንደሚወልድ ስላበሠረ መልአከ ብሥራት ይባላል፤ መጋቤ አዲስም ይባላል፡፡ አዳምና ልጆቹ (የሰውን ልጆች ሁሉ) ከሞት የሚያድን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቶስ በሥጋ እንደሚወለድ የምሥራችን በማብሠሩ የሰው ልጆች አዲስ ሕይወትን እንደሚያገኙና ከጨለማ ሕይወት እንደሚወጡ የምሠራች ስለተናገረ መጋቤ አዲስ ተብሏል፡፡

ልጆች! ቅዱስ ገብርኤል ያዘኑትን የሚያጽናና፣ ደስ የሚያሰኝ፣ ጥበብና ማስተዋልን የሚሰጥም መልአክ ነው፤ ሦስቱን ሕፃናት አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ከነደደ እሳት እንዲሁም ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ከፈላ ውኃ ውስጥ ያወጣቸው ቅዱስ ገበርኤል ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክትንም በእምነት እንዲጸኑ የሰበካቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፤ ወርኃዊ በዓሉም ወር በገባ  በ፲፱ (ዐሥራ ዘጠኝ) ይታሰባል፡፡ ዓመታዊ ክበረ በዓላቱ ደግሞ ታኅሣሥ ፲፱ እና ሐምሌ ፲፱ ይከበራሉ፡፡

ቅዱስ ሩፋኤል

በቅዱሳን መላእክት ማዕረግ ሦስተኛው ሲሆን የሰላም የጤና መልአክ ነው፤ ልጆች! ቅዱስ ሩፋኤል የተሰጠው አገልግሎት ደግሞ ምን መሰላችሁ? እናቶች ልጅ ሲወልዱ በሰላም እንዲወልዱ የሚረዳቸው መልአክ ነው፡፡ እናቶቻችን እኛን ፀንሰው በነበረበት ጊዜ ስሙን እየጠሩ ሲጸለዩና ጸበሉን ሲጠጡ ልክ መውለጃቸው ጊዜ ሲደርስ ቅዱስ ሩፋኤል በሰላም እንዲወልዱ ይረዳቸዋል፡፡በመጽሐፍ ቅዱስም መጽሐፈ ጦቢት ላይ ታሪኩ እንደ ተጻፈልን ጦቢት የተባለን ሰው ዓይኑን አብርቶለታል፡፡ ወርኃዊ በዓሉም ወር በገባ በ፲፫ (ዐሥራ ሦስት) ይታሰባል፡፡ ዓመታዊ ክበረ በዓሉ ደግሞ ጳጉሜን ሦስት ቀን ነው፡፡

ቅዱስ ራጉኤል

ራጉኤል ‹‹እግዚአብሔር ጽኑ፣ኃያል (የኃያላን ኃያል እግዚአብሔር)›› ማለት ነው፡፡ ሰይጣንን የሚያሳድድ (የሚቀጣ) መልአክ ነው፤ በብርሃናት ላይ የተሸመም መልአክ ነው፤ በዚህም መጋቤ ብርሃን ይባላል፡፡ ብርሃናት (ፀሐይን፣ጨረቃን፣ ክዋክብትን) የሚቆጣጠር መልአክ ነው፡፡ ወርኃዊ በዓሉ ወር በገባ በአንድ ይከበራል፤ ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ደግሞ መስከረም አንድ ነው፡፡

ቅዱስ ዑራኤል

ዑራኤል ማለት ‹‹የፀሐይ ብርሃን ማለት ነው፤›› ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ዑራኤል የሕይወትን ጽዋ የሚያጠጣ፣ ጥበብና ማስተዋልን የሚገልጥ መልአክ ነው፤ ምሥጢር ለአባቶቻችን እንዲገለጥላቸው ከእግዚአብሔር ተልኮ የሕይወት ጽዋን ያጠጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዕዝራ ለተባለው ነቢይ የሕይወት ጽዋ ያጠጣው መልአክ ይህ ነው፡።

ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በብርሃን ጽዋ የጌታችንን ክቡር (ቅዱስ) ደም በብርሃን ጽዋ ይዞ በዓለም ላይ ረጨው፤ ከዚያም ምድራችን ተቀደሰች፤ ይህ መልአክ እመቤታችን ጌታችንን ይዛ በተሰደደች ጊዜ እየመራ አገራችን ኢትዮጵያ መርቷታል፤ ወርኃዊ ክብረ በዓሉም ወር በገባ በ፳፪ (ሃያ ሁለት) ይታሰባል፡፡ ዓመታዊ ክበረ በዓሉ ደግሞ ጥር ፳፪ ቀን ነው፡፡

ቅዱስ ፋኑኤል

ፋኑኤል ማለት ‹‹የጻድቃን ጠባቂ ማለት ነው፡፡›› ልጆች! ይህ መልአክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሦስት ዓመቷ ቤተ መቅደስ ታኅሣሥ ሦስት ቀን ስትገባ ከሰማይ የምትመገበውን ኅብስት የምትጠጣውን ጽዋ ይዞላት መጥቷል፤ ይገርማችኋል ልጆች! በበረሃ በገዳም ማንም በሌለበት ለብቻቸው የሚኖሩ ባሕታውያን አባቶችንም እንደዚሁ ኅብስት የሚመግባቸው ይህ መልአክ ነው፤ ነቢዩ ኤልያስንም ይመግበው ነበር፤ ወርኃዊ ክብረ በዓሉ ወር በገባ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ ዓመታዊ ክበረ በዓላቱ ደግሞ ታኅሣሥ ሦስት እና ግንቦት ሦስት ይከበራሉ፡፡

ቅዱስ ሳቁኤል

ሳቁኤል ማለት ‹‹ምስጉን፣ ለእግዚአብሔር የቀረበ ማለት ነው፤›› ይህ መልአክ በደመናት፣ በባሕራትና በውቅያኖስ ላይ የተሾመ መልአክ ነው፤ ልጆች! ባሕራትና ውቅያኖሶች ገደባቸውን አልፈው በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የሚጠብቅ መልአክ ቅዱስ ሳቁኤል ነው፡፡ ወርኃዊ ክብረ በዓሉ ወር በገባ በስምንት ቀን ነው፡፡ ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ደግሞ ሐምሌ አምስት ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እነዚህ ቅዱሳን መላእክት የመላእክት አለቆች የተባሉ ናቸው፡፡ ሌሎችም እልፍ አእላፋት መላእክት አሉ፤ እነርሱም እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ እኛን የሚጠብቁ፣ ከፈጣሪያችን ተልከው መጥተው ከክፉ ነገር የሚታደጉን፣ የእኛን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱልን ናቸው፡፡ የእነዚህም ክብረ በዓል በኅዳር ወር በዐሥራ ሦስት ቀን ይከበራል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  ቅዱሳን መላእክት እንደ እኛ እንደ ሰዎች አይበሉም፤ አይጠጡም፤ አይደክማቸውም፤ እንቅልፍም አይተኙም፤ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ይኖራሉ፡፡ እኛም በተሰጣቸው ቃል ኪዳን ያማልዱንና መንገዳችንም የሠመረ እንዲሆን ይረዱናል፡፡

ልጆች! እንግዲህ እኛም እንደ መላእክት አምላካችንን እግዚአብሔርን ማመስገን አለብን፤ ለሰዎች መልካም ማድረግና ታዛዦች መሆን ይገባናል፡፡ ለሰዎች መልካም ስንሆን ክብራችን ከፍ እያለ እንደመላእክት አመስጋኞች እንሆናለን፤ ክፉ የምንሠራ ከሆነ ግን ክብር አይኖረንም፤ እንደ እንሰሳት ዝቅ ያልን ያደርገናል፤ ስለዚህ እንደ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን አመስጋኞችና ሰዎችን የምንረዳ እንሁን!

አምላካችን ከቅዱሳን መላእክት ረድኤትና በረከታቸውን ያድለን፤ አሜን!፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!